ጥበብ በታሪክ ገፅ

መቅደላ ተሸነፍን እንዴ አልተሸነፍንም!

ዘመነ መሳፍንት ለሀገሪቱ ያመጣው ፋታ የማይሰጥ ውድቀት ዘግይቶ መፍትሔ ከማጣቱ በፊት መይሳው ካሳን ብቁ ታዳጊ አድርጎ የኢትዮጵያ አምላክ አስነሣው። አፄ ቴዎድሮስ በኢትዮጵያ ሊቃውንት ዘንድ የሚታየው ከፈጣሪ እንደተላከ የኢትዮጵያ ታዳጊ፣ የአንድነቷና የሉዓላዊነቷ ሐዋርያ ተደርጎ ነው። ለምሳሌ ዝክረ ነገር ስለ ንጉሡ ሲዘግብ “ነገር ግን የኢትዮጵያ የዕድሏ ኮከብ ባንድ አፍታ ብልጭ ብሎ ስለ ወጣ ለጊዜው አፄ ቴዎድሮስን አስነሣላትና የኢትዮጵያን አንድነት መልሰው እንደ ጥንቱ አቆሙላት” (ገጽ 760) ብሏል። መይሳው ካሳ ሲነግሥ “የተሰጠው ቴዎድሮስ የሚለው ስመ-መንግሥት (የንግሥና ቅብዓት ስም) በትንቢታዊ መጻሕፍት በተለይ በ”ፍካሬ ኢየሱስ” እና “ገድለ ሰማዕት ቅዱስ ፊቅጦር” ላይ ከተጠቀሰው “ቴዎድሮስ የተባለ ንጉሥ” ጋር በማመሳከር ፍርዱ የቀና ዓላማው የሰመረ ሁሉን እኩል አድርጎ የሚገዛ ንጉሥ አስቀድሞ በሊቃውንቱ፣ በካህናቱና በሕዝቡ ዘንድ በምኞትና በትንቢት የሚጠበቅ ስለነበረ ነው። የአፄ ቴዎድሮስ ዓላማም ከዚሁ ጋር ተሣሥሮ በአፈጸጸም በዘመኑ ሁሉም ባይሳካም ለሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል መድኅን ጀማሪ ለመሆን መብቃቱ ይታመናል።

 “አንድ የብረት አሎሎ በአንድ ጊዜ ሃምሳ ጋኖችን ለመሥበር ይበቃል” “A ball of Iron is enough to break fifty jars at a time” የሚለውን አባባል ይዞ ቋረኛው ካሳ የጀመረውና ቀስ-በቀስ እየተሳካለት የመጣው የአካባቢ ገዥዎችን የመጠቅለልና ጠንካራ ማእከላዊ መንግሥት የመመሥረት ተግባር (ፕሮጀክት) እስከ አሁን እንደምናውቅው በጣት የሚቆጠሩ ሹማምንትን በመርታት በቀላሉ የተሳካ አልነበረም። ከትላላቅ መንደሮች ገዥዎች ጀምሮ እስከ ትናንሽ የሠፈር አስተዳዳሪዎችና ባለተስፋ ራሶችን ሁሉ ጋር ጦርነት ብቸኛ አማራጭ በሆነበት ተግባር የንግሥና ዘመኑ በሙሉ ያካለለ አስቸጋሪና አድካሚ ትግል ነበር። ይህ ጠንካራና ዘላቂ ዓላማ የገናናነቱና የውድቀቱ ምክንያት ሆነ። እዚህ ላይ “ዘላቂ” የሚለው ቃል ያልከሸፈና በቀጣይ ያልተገሠሠ ስለሆነ ይሠመርበት።

በዘመኑ የነበሩ የሊቃውንቱን፣ የደራስያኑንና የጸሐፊዎችን አባባል በመቀመር መጋቢ ስብሐት ዓለሙ ዓጋ በበገና የዘመሩት መዲና ብዙ ታሪክ እንድናስታውስ ያግዘናል። “አባ ግራኝ ሞተ የሆዴ ወዳጅ፣ የሚያበላኝ ጮማ የሚያጠጣኝ ጠጅ” አባ ግራኝ የሚወክለው ቋረኛው ካሳን ነው። “ግራኝ ነው አሉ” ባልተጠበቀበት ያሸንፋል፣ በጦርነት ከኋላ አይሆንም፣ ራሱንም ለየት አድርጎ አያሳይም፣ በጠበቁት ሥልት ሳይሆን ባልጠበቁት ብልሃት ይረታል፣ በጠበቁት የራሱን ግዛት የማስከበር ዓላማ ሳይሆን ባልገመቱት የአንድነት ዓላማ በሁሉም ጠንካራ ውጊያዎች አሸንፏል። ከወታደሩ ተለይቶ አያድርም፣ አብሮ ይበላል፣ አብሮ ይፎክራል፣ ለብቻው ሲሆን በገና ይደረድራል፣ ክብረ ነገሥትን፣ ፍትሐ ነገሥትን፣ ታሪከ ነገሥትን ያነባል ያስነብባል። ዘመነ መሳፍንት በፈጠረው መልካም አጋጣሚ እንደፈለጉ ከየአካባቢው ገዥዎች ጋር ሲወጡ ሲገቡ የነበሩ አውሮፓውያን የሚናገሩትን የሥልጣኔና የዕድገት ደረጃ፣ የመንግሥት አስተዳደር ሥርዓት፣ የ“ብሔራዊ (ሕብረ ብሔራዊ) መንግሥት” (nation state) ምሥረታ ሂደት በጥንቃቄ ይጠይቃል። ለመንግሥቱ ጥንካሬና መለያ የሆኑ ዋና ዋና ጉዳዮችን ምንም ሳይቀር ይመረምር ነበር። በተለይ ለጥበብ በነበረው ፍቅር ጎንደር ላይ የአንዳንድ ሊቃውንትን መኩራራት በመታዘብ በሸንጎ መሐል “እስኪ አሁን ለጎንደር ወይዛዝርት አንባርና አልቦ ከሚሠራ አንጥረኛ ያለፈ ጥበበኛ አለ፣ በጄ እንደ አባቶቻችን እንደነፋሲል እንዲህ ዓይነት የሕንፃ ጥበብ የሚሠራ ጠቢብ አምጡልኝና ልሹመው ልሸልመው” ማለታቸውን ብርሃኑ ዘሪሁን ጠቅሰዋል።

 የአፄ ቴዎድሮስ አንዲትን ሀገር እንደገና የመሥራት ፕሮጀክት ጅማሬ በሊቃውንቱ፣ በካህናቱና በሕዝቡ ዘንድ ድጋፍ ነበረው። ራሳቸውን የሰፈርና የመንደር ወካይ አድርገው ሀገሪቱን በመከፋፈልና ሕዝቡን በመለያየት በየቦታው ጎጥ መሥርተው የነበሩ ገዥዎች አንድ በአንድ ሲሸነፉ ሕዝቡ በንጉሡ ላይ ይህ ነው የሚባል አመጽ አላደረገም ነበር። እየቆየ ሀገሪቱ ከነበረችበት የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ፣ ከራሳቸው የግል ባህርይ፣ በአንድ ጊዜ ሊቀረፍ ከማይችለው ድርብርብ ችግር፣ ነባሩን ላለመተው በየቦታው ከሚፈጠረው ያልተቋረጠ ትግል፣ ከወቅቱ የዓለም ፖለቲካና የኃይል ሚዛን፣ ከምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካና ወታደራዊ አሰላለፍ፣ ከሃይማኖትና ባህል እውነታዎች አንፃር እቅዱ በአንድ ጊዜ

“መቅደላና አካባቢው ምንም እንኳ ከአፄ ቴዎድሮስ በፊት በሌሎች ጥንታውያን ታሪኮች ቢታወቅም “መቅደላ አምባ” በሰፊው የሚታወቀው በአፄ ቴዎድሮስ ነው”

የሚፈለገው ደረጃ ላይ መድረስ አልቻለም። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታውን በጥሞና ላጠናው ሰው የተወጠነውን ረጅምና ዘላቂ አስተሳሰብ እሳቸው ባይሆኑ ማን ይጀምረው ነበር ያስብላል።

በሀገር ውስጥ ብሔራዊ አንድነትንና አሐዳዊ ሥርዓትን ለመመሥረት ካሰቧቸው አደረጃጀቶች ውስጥ፣ የግብር ሥርዓት፣ የወንጀለኛ ቅጣት፣ የሠራዊት ደመወዝ፣ የትምህርትና የሥልጣኔ ጅማሬ፣ የቴክኖሎጅ ፍላጎት፣ የዘመናዊ ጦር ምሥረታ፣ የሥራ ክብር፣ የውጭ ፖሊሲ፣ የቤተ ክህነት ሕግ፣ ለሥነ ጥበብ የሰጧቸው ከፍተኛ ቦታ፣ ከብዙ በጥቂቱ ሲሆኑ ንጉሠ ነገሥቱ ለወቅታዊው የዓለም ፖለቲካም ባዕድ አልነበሩም። ሀገሪቱ ከአፄ ፋሲል በኋላ በተከተለችው “ዝግ የውጭ ፖሊሲ” በወቅቱ በአውሮፓ ከተከናወኑት ለውጦች ብትርቅም ለአፄ ቴዎድሮስ የዘመናቸው ዓለም የደረሰበትን ሁለንተናዊ ደረጃ ለመረዳት ሩቅ አልነበረም። በተለይም የእንግሊዝ፣ የቱርክና የዋና ዋናዎቹ የወቅቱ አውሮፓ ኃያላን የፖለቲካና የውትድርና አሰላለፍ ያውቁ ነበር። ይሁን እንጅ ከልምድ ወይም ከብቁ አማካሪ አለመኖር፣ ወይም የንጉሠ ነገሥቱና የአውሮፓውያኑ ኃያላን ዓላማ አለመግጠም ውጤቱ ባልተጠበቀ መንገድ ተጓዘ። የአፄ ቴዎድሮስ ዓላማ ሀገርን አንድ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን እንደ ዘመነ አክሱም በዓለም የታፈረች ሉዓላዊት ሀገር እንድትሆን ማስቻልም ነበር። ራሳቸውንም “የኢትዮጵያ-ባል የኢየሩሳሌም- እጮኛ” ይሉ ነበር። “ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሳ ብሎ ስም- ዓርብ ዓርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም” (መ/ስ ዓለሙ-በገና) በግልጽ ስለሚናገሩ በወዳጅ መሰል ጠላቶቻቸው ሌላ ግምት ያሰጣቸው ይመስላል።

 አፄ ቴዎድሮስ እንግሊዝን መልካም የውጭ አጋር ማድረጋቸው ግልጽ የውጭ ፖሊሲ ነበር። ይህም ከምሥራቅ አፍሪካ አልፎ እስከ ኢየሩሳሌም የደረሰ ነበር። ለዚም በቂ መረጃ ነበራቸው። ምናልባት የወቅቱ የእንግሊዝ ዓላማ ሌላ ቢሆንስ? ጥንቱንም ኢትዮጵያ ከእንግሊዝ ጋር ያላት ግንኙነት የሚጀምረው በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት እንደሚሆን ፍንጮች ይጠቁማሉ። በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የአባ ጎርጎርዮስን ሥራ በመተርጎም የግእዝ-ጀርመን መዝገበ ቃላትና ሰዋስው ያዘጋጀ ዮብ ሎዶልፍ ሥራ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመው በዚያው ዘመን ነበር። በርከት ያሉ የአውሮፓ ተጓዦች ስለ ኢትዮጵያ የጻፉት የጉዞ ማስታወሻ ከ17ኛው መቶ ክፍል ዘመን ጀምሮ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉመዋል ወይም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተጽፈዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1790 የታተመው የእንግሊዛዊው ጀምስ ብሩስ “Travels to Discover the Source of the Nile” “የአባይን ምንጭ ፍለጋ ጉዞ” እንግሊዞች ስለ ኢትዮጵያ በቂ ዕውቀት እንደነበራቸው ያረጋግጣሉ። በዘመነ መሳፍንት እንግሊዝ በግብጽና በሱዳን ብዙ መቀመጫ በነበራት ወቅት ኢትዮጵያን አቋርጠው ወደ ሕንድና ወደ ደቡብ አረቢያ የሚጓዙ መንገደኞች ስለሀገሪቱ

“የአፄ ቴዎድሮስ ብሔራዊ የአንድነት ስሜት፣ ለዓለም ፖለቲካ ያለው አመለካከት፣ ለሀገሩ የሰነቀው አስደናቂና ዘላቂ ዓላማ፣ ራሱን ከማናቸውም ዓለም ኃያላን ጋር ማስተካከሉና በሌሎችም ምክንያት ጄኔራል ናፒየር እዚህ ቀረሽ የማይባልና አይደለም ኢትዮጵያን ሌላም ሀገር መውረር የሚያስችል ዝግጅት አደርገ ”

የመልክዓ ምድር አቀማመጥ፣ የአየር ንብረትና ወቅታዊ ወረርሽኞች ሳይቀር፣ የፖለቲካና ማኅበራዊ መዋቅር፣ የኢኮኖሚና የሃይማኖት ሁኔታ በቂ መረጃ ለመሰብሰብ ረድቷቸዋል። ከዚህም ከራስ ወልደ ሥላሴ ጋር የጠበቀ ግንኙነት የነበረው የእንግሊዝ ንጉሥ ሔንሪ ሣልሳዊ መልእክተኛ ሔንሪ ሶልት፣ ቻርልስ ቢካ በዋናነት ይጠቀሳሉ። ሔንሪ ለራስ ወልደ ሥላሴ ከእንግሊዝ ያመጣቸው በርካታ ሥጦታዎች በራስ ወልደ ሥላሴ ደብር የሚገኙ ሲሆን ሁኔታው የእንግሊዝ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ሊፈጥር ያሰበውን ግንኙነት የሚያሳይ ነበር። በኋላም ከሌሎች ደጃዝማቾችና ራሶች ጋር የነበራት ግንኙነት እንግሊዝ ከኢትዮጰያ ጋር ከዲፕሎማሲያዊ ግንኑነት ያለፈ ፋላጎት እንደነበራት የሚያሳዩ ነበሩ።

 በሃይማኖት ስም ለመግባት የነበራቸውም እቅድ እ.ኤ.አ. በ1824 እንግሊዝ በነበረው “Church Missionary Society” “የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ማኅበር” መጽሐፍ ቅዱስን በአባ አብርሃም ቅንብር በአማርኛ በማሳተም ያደረጉት ሥራ ለድብቅ ዓላማቸው መንገድ ጠራጊ ተደርጎ ተወስዷል። እነዚህ ሁኔታዎች ለአፄ ቴዎድሮስ የተደበቁና ከሳቸው ዕውቅና የራቁ አልነበሩም። ሁኔታውን በመረጃ ብቻ ሳይሆን በቅርብ ይከታተሉት ነበር። ንጉሠ ነገሥቱ በአውሮፓ ሥልጣኔ ሀገሩን ለማዘመን እንጅ “ሃይማኖትን በተመለከተ ነጠላውን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ከነትርጉሙ በቃላቸው የሚያመሠጥሩ ሊቃውንት አሉን” ብሏል። “የምንፈልገው ሰባኪ ሳይሆን ኪነ ጥበባዊ ሥልጣኔን የሚያስተምረን ነው” ብለው በግልጽ ቢናገሩም እንግሊዛውያኑ “ወደ ሃይማኖት በማዘንበል” የሰጡት መልስና አንዳንዱ “ዝምታ” ዓላማና ፍላጎታቸው የተለየ መሆኑን የሚጠቁም ስለነበር ንጉሡ በቀላሉ አላለፉትም።

 እስከአሁን እንግሊዝ ኢትዮጵያን ለመውረር አሰባ ነበር በማለት ደፍሮ የጻፈ ብዙም የለም። በአንፃሩ በቅርቡ የታተመው የማቴያስ መጽሐፍ (Matthies 2010: p168). “ናፒየር በኢትዮጵያው ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ላይ የከፈተው ጦርነት አንዱና ዋናው የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሲሆን ሀገር የመያዝ ዓላማ ሳይኖረው አውሮፓውያን ባልሆኑና አማፂ ቅኝ ተገዥዎች ላይ የእንግሊዝን ልዕለ ኃያላንነት ለማሳየት ያለመ ነበር” ብሏል። እንግሊዝም በቀጥታ ወረራ ከመፈጸም ይልቅ ሌሎች መንገዶችን መረጠች እንጅ ፍላጎቷ ግልጽ ነበር።

 ያም ሆኖ በውስጥ የዘለቀው ያላቋረጠ ጦርነትና እያደገ የመጣው ጥላቻ፣ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ የተፈጠረው ተቃውሞ፣ አልፎ አልፎ የተረፉት ራሶችና ደጃዝማቾች እንደገና ማንሠራራት ለንጉሡ ሞት ምክንያት ሆኑ። ጥላቻውም ፍርሃት ያለበት ነበር፣ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ከሁሉ የከፋው ሁኔታ ግን የዓላማቸው ተባባሪ ሆኖ ከመደገፍና በጋራ ሀገር ከማቅናት ይልቅ በተቃውሞ አሰላለፍ ንጉሡን የመክዳቱና በማንኛውም መንገድ የመጣሉ ፍላጎት የውጭ ድጋፍ ማግኘቱ ነበር። በገና ደርዳሪውም “መቅደላ አፋፉ ላይ ጩኸት በረከተ፣ የሴቱን አናውቅም ወንድ አንድ ሰው ሞተ” ብሎ ዘመረ። እንግዲህ በሴት በኩል የተሰለፉት እነማን እንደሆኑ የመዝሙሩ ደራሲ ያውቃል።

የመቅደላ ጦርነት ሚያዝያ 6 ቀን 1860 ዓ.ም

የአውሮፓውያኑ ዝንባሌ ከንጉሡ ፍላጎት ጋር አለመሄድ፣ ይልቁንም አፄ ቴዎድሮስ ቱርክን ከቀይ ባህርና ከሱዳን ወደቦች ሙሉ በሙሉ የማስለቀቅ ብቻ ሳይሆን ከኢየሩሳሌም የማስወጣት ዓላማ ሲሉ ለእንግሊዝ ለጻፉት ደብዳቤ ከእንግሊዝ ንግሥት መልስ አለመምጣቱ ለዲፕሎማቶች መታሠር ምክንያት ሆነ። እንግሊዝ ከቱርክ ጋር የነበራትን ወዳጅነት ላለማጣት ለአፄ ቴዎድሮስ ደብዳቤ የዝምታ መልስ ሰጠች። በቀጣይ ዲፕሎማቶቹንና ሚሲዮኖቹን “ለማስለቀቅ” በሚል ስም እንግሊዝ ጄኔራል ናፒየርን ከሕንድ ተነሥቶ ወደ ኢትዮጵያ እንዲዘምትና ንጉሡን ከነሕይወቱ እንዲማርክ አዘዘች። ይህም የናፒየር ዘመቻ “Napier’s expedition” በመባል የተሰየመው ተልእኮ ነው።

የአፄ ቴዎድሮስ ብሔራዊ የአንድነት ስሜት፣ ለዓለም ፖለቲካ ያለው አመለካከት፣ ለሀገሩ የሰነቀው አስደናቂና ዘላቂ ዓላማ፣ ራሱን ከማናቸውም ዓለም ኃያላን ጋር ማስተካከሉና በሌሎችም ምክንያት ጄኔራል ናፒየር እዚህ ቀረሽ የማይባልና አይደለም ኢትዮጵያን ሌላም ሀገር መውረር የሚያስችል ዝግጅት አደርገ። በጦርነት ሚዛን አፄ ቴዎድሮስ ከነበራቸው ዝግጅት በብዙ እጥፍ የዘለቀ አደረጃጀት ተከትሏል። ቢያንስ ቢያንስ ኢትዮጵያ ሲደርስ በግንባር ጦር ብቻ 14700 ጠብመዝጃ የታጠቁ፣ እጅግ የሰለጠኑና ልምድ ያላቸው ወታደሮች ከ27000 ደጋፊ ጦር ጋር፣ 19000 በቅሎዎችና ፈረሶች፣ 1700 አህዮች፣ 5700 ግመሎች፣ 44 ዝሆኖች፣ እግጅ በጣም የተራቀቁና በዘመኑ እዚህ ቀረሽ የማይባሉ 16 መድፎች፣ ሁለት ሞርታሮች፣ 16 ተወንጫፊ ሮኬት ተኳሾች፣ በዘመኑ በየትም ቦታ ጦርነት ላይ ያልዋሉ የጦር መሣሪያዎችን ታጥቆ መቅደላ ደርሷል። ከዚህ ጋር ሲነፃጸር የአፄ ቴዎድሮስ አቋም በታሪክ ሁሉ ሲዘከር ከሚኖረው ወደር የለሽ ጀግንነት በቀር በመሣሪያ አይደራረስም። በሠራዊት ቁጥሩም ናፒየር በብዙ እጥፍ ይበልጥ ነበር። በአፄ ቴዎድሮስ በኩል ከጥቂት ታማኝ መኮንኖቻቸው በስተቀር ሁሉም አምጾና ከድቶ ነበር። እንግሊዞች በቀይ ባህር ያገኙት የግብጽና የቱርክ ድጋፍ፣ በሀገር ውስጥ ያለው መከፋፈል ታክሎበለት ከወደብ እስከ መቅደላ ያለ ተቃዋሚና ድካም ተጉዘዋል።

ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 1860 ዓ.ም. በስቅለት በዓል ጦርነቱ ተጀመረ። በዚሁ ቀን የንጉሡ ታማኝ ጄኔራል ገብርዬ እየተዋጋ መስዋዕት ሆነ። በሁለት ቀናት እንግሊዞች መቅደላን ተቆጣጠሩ። እሁድ ሚያዝያ 5 ቀን በትንሣኤ ማግሥት (ማዕዶት) ወደ አምባው ደረሱ። ሚያዝያ 5 ቀን 1860 ዓ.ም. አፄ ቴዎድሮስም ራሳቸውን ለጠላት አሳልፈው ላለመስጠት በገዛ ሽጉጣቸው ራሳቸውን ገደሉ። በገና ደርዳሪውና ገጣሚውም “ፈረሱ አባ ታጠቅ ስሙ ቴዎድሮስ፤ ጠላትን ሚበትን እንደአውሎ ነፋስ። የእገሌንም ጎበዝ ሲንቁ ሲንቁ፣ የእገሌንም ጎበዝ ሲንቁ ሲንቁ፣ የእገሌንም ጎበዝ ሲንቁ ሲንቁ፣ ወንድ ያለ“ራስዎ” ገለውም አያውቁ። መቅደላ መቅደላ አንቺ ኩሩ ጎራ፣ ሴቱን ሁሉ ንቆ ሲኮራ ሲኮራ፣ ወንዱ አንቺን ወደደ ተኛ ከአንቺ ጋራ” ብለው ዘመሩ። (መ/ስ ዓለሙ ዓጋ፣ እና ዝክረ ነገር፣ ገጽ 586)

 መቅደላ በደቡብ ወሎ ዞን ምእራባዊ አቅጣጫ የሚገኝ፣ የበሽሎ ሸለቆን እያዋሰኑ ጫፋቸው ጠፍጥፎ ርስ በርስ የተሣሠሩና በአንዳንድ አቅጣጫቸው ለመውጣት የሚያስቸግሩ ተራሮች ያሉበት ቦታ ነው። አምባው በዛጉዌ ዘመን የጦር መለማመጃ ነበር፣ በ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አፄ ሱስንዮስ አንድ ክረምት በመቅደላ እንዳሳለፉና ታላቁ የመቅደላ አምባ መድኀኔዓለም ቤተ ክርስቲያንም በቦታው እንደነበር ዜና መዋዕሉ ይተርካል። በደብረ ሐይቅ አቡነ ብስጣውሮስ በአፄ ኢያሱ ቀዳማዊ ዘመን የደብሩ ዐቃቤ ሰዓት የመቅደላ ሊቅ እንደነበር ይናገራል። ገድለ አቡነ ብስጣውሮስ እንደሚተርከው በመቅደላና በአምባሰል መካከል ሰፊ ገበያ እንደነበር፣ የደብረ ሐይቅ ነዋሪዎችም መቅደላ ገበያ ይውሉ እንደነበር ይገልጻል። የአምባው ውበትና የተፈጥሮ አቀማመጥ እጅግ ማራኪና ለም ነው። ወደ ደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ያቀና ሰው በከተማዋ ዳር ያለውን በእነሱ አባባል “table mountain” (ጠረጴዛማ ተራራ) ሳይጎበኝ አይመጣም። ከተራራው ጠፍጣፋነት በቀር ሌላ ታሪክ የለውም። ለዚያ ተብሎ የተሠራው መወጣጫና መዝናኛ ድንቅ ነው። መቅደላን ያላየ የሚያሰኘው ተራራ እንደመቅደላ ታሪክ ቢሠራበት ምን ያደርጉት ይሆን ብሎ ማሰብ (መቆጨት) አይቀርም።

መቅደላና አካባቢው ምንም እንኳ ከአፄ ቴዎድሮስ በፊት በሌሎች ጥንታውያን ታሪኮች ቢታወቅም “መቅደላ አምባ” በሰፊው የሚታወቀው በአፄ ቴዎድሮስ ነው። ከንጉሠ ነገሥቱ በፊት የአካባቢው ነዋሪ ከ3000 ባይበልጥም በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ የመንግሥት ሥርዓት፣ ሠራዊት፣ ካህናት፣ አማካሪዎችና ሌላውንም አገልጋይ ሲያካትቱበት ቁጥሩ በብዙ እጥፍ ጨምሮ ነበር። ቋሚ ማእከላቸው ለማድረግ በመጣር ይመስላል፣ ቅጥሩ ያማረ ቤተ መንግሥት፣ ከጎንደር፣ ከላስታና ከአካባቢው በሙሉ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ የብራና መጻሕፍት ብሔራዊ ቤተ መዛግብት፣ የቤተ መንግሥቱ ልዩ ምሽግ፣ እስር ቤት፣ የንጉሠ ነገሥት እልፍኝ፣ የሰነድ ቤተ መዛግብት፣ የዕቃ (ገበዝ) ቤት፣ ዘውዶች፣ አክሊሎች፣ የልዕልና አልጋ፣ ዙፋን፣ እጅግ በርካታ ንዋየ ቅድሳት፣ የሊቀ ጳጳስ መኖሪያ፣ የአልባሳትና የክብር ጌጦች ማስቀመጫ፣ የከብቶች መኖሪያና የልዩ ልዩ ንብረቶች ግምጃ ቤት፣ የቤተ መንግሥት ዘብ መቆሚያና ሠራዊቱ በየማዕረጉ የሠፈረበት፣ ለሠራዊቱ የሚሰጡ ሽልማቶች እና የክብር ስጦታዎች ማስቀመጫ መድረክ ከዚህ ውስጥ ለምሳሌ ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ (ዝክረ ነገር፣ ገጽ 670) እንደገለጹት “በዘመነ መሳፍንት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ታላቁ የሰሎሞን ሽልማት (ኒሻን) መስጫ” በመቅደላ ተመስርቷል። አደረጃጀቱ የንጉሠ ነገሥቱን ፍላጎትና አርቆ አሳቢነት በሚገባ ያሳየ ነበር።

 ከዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ሞት በኋላ ጀኔራል ናፒየር ዋግ ሹም ጎበዜ መቅደላን እንዲረከብ ሐሳብ ቢያቀርብም ዋግ ሹሙ አልፈለገም። እንግሊዞች እንደ “ቁጣ መግለጫ” ወይም “በቃ ተናደድን” እንደ-ማለት በመሐንዲሳቸው የማፍረስ ጥበብ መቅደላን ሙሉ በሙሉ ደመሰሱት፣ ንብረቶቹን ዘረፉ፣ ከአምስት ቀናት ዝርፊያ በኋላ ትንሣኤን ውለው ሚያዝያ 10 ቀን 1860 ዓ.ም. የመቅደላን ቤተ መንግሥትና መላውን የንጉሥ ከተማ ለወሬ ነጋሪ እንዳይተርፍ አድርገው አቃጠሉት፣ (ማርካም 1861 እንደጻፈው) ጥንታዊውን የመቅደላ መድኀኔዓለምም ከዘረፉ በኋላ እሳት ለቀቁበት (ሆላንድ ሆዜር በ1862 እንደጻፈው)። በሙሉ መጥፋቱን ለሦስት ቀናት ካረጋገጡ በኋላ እንግሊዞች የዘረፉትን ንብረትና የማረኳቸውን የቤተ መንግሥት ሹማምንት (ልዑል ዓለማየሁና እቴጌ ጥሩወርቅ አሉበት) ይዘው ከዳግም ትንሣኤ በኋላ ወደ ሀገራቸው መጓዝ ጀመሩ። ዋና ዋናውን ዕቃ (ቅርስ) ከ15 በላይ በሆኑ ዝሆኖችና ከ200 በላይ በቅሎዎች ጫኑ። ይህ እንግዲህ በየወታደሩ ኪስና ትከሻ የተጫነውን ሳይጨምር ነው። ከዚህ የተረፈውን በጄኔራል ናፒየር ትእዛዝ ሚያዝያ 13 እና 14 ዋድላ ደላንታ ቅዳሜ ገበያ እንደባለቤት ቸበቸቡት፣ ከገበያ የተረፈውን በዋድላ ገደል ወረወሩት። ከመቅደላ የተዘረፉት ንብረቶችና ቅርሶች እንዲመለሱ አፄ ዮሐንስ አራተኛ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ጊዜውም ከነገሡ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነበር። በተለይ ክብረ ነገሥት መጽሐፍና ኩርዓተ ርእሱ የሚባለው የክርስቶስ ሥዕል እንዲመለስ በአጽንኦት በመጠየቃቸው “ክብረ ነገሥት” ተመልሷል። አንድ ዘውድ ለንግሥት ዘውዲቱ፣ አንድ ጽዋ ደግሞ ለቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ተመልሰው ነበር። ከተወሰዱት ከዐሥር በላይ የቤተ ክርስቲያን ታቦታት ውስጥ በእንግሊዝ ብሔራዊ ሙዚየም የነበረው የአቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ጽላት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክነት ዘመን ተመልሷል። አሁንም ቀሪዎቹን በርካታ ንዋየ ቅድሳትና ታቦታት ማስመለሱ ሊቀጥል ይገባዋል። አፍሮሜት በተባለ የቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አማካይነት በቅርቡ የተወሰኑ ቅርሶች ለናሙና ያህል ተመልሰዋል።

የጋፋት ውለታ (የኢንደስትሪ ማእከል)

ጋፋት ከደብረ ታቦር ሰሜን ምሥራቃዊ አቅጣጫ ጃን-ሜዳ ከሚባለው አካባቢ የምትገኝ መንደር ነበረች። አፄ ቴዎድሮስ ዋና ከተማቸውን ወደ ደብረ ታቦር ሲያዛውሩ ጋፋትን የዘመናዊት ኢትዮጵያ የቴክኖሎጅና የኢንዱስትሪ ማእከል አድርገው መሠረቷት። በዚህም በሃይማኖት ሚሲዮን ሰበብ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ አውሮፓውያን (ከእንግሊዝ፣ ከጀርመንና ከስዊዘርላንድ) የጦር መሣሪያና ሌሎች የአውሮፓ ሥልጣኔ ቴክኖሎጅ ውጤቶችን እንዲሠሩና ኢትዮጵያውያንን እንዲያሰለጥኑ አዘዙ። የመጀመሪያው ሥራ በርግጥ የጦር መሣሪያ ማምረት ነበር። ባህሩ ዘውዴ “ጋፋት ከምንም በላይ የቴዎድሮስን ሀገር የማዘመን ጥረት ማሳያ ናት” (ገጽ 34) ብሏል። ንጉሠ ነገሥቱ ከመሞታቸው አንድ ዓመት በፊት ጋፋት ትእዛዙ ፈርሶ እስረኞቹና ምርቱ ወደ ደብረ ታቦር ከዚያም ወደ መቅደላ ተወስደው እስከ ጦርነቱ በዚያው ቆይተዋል። በዚህ ቦታ ከተመረቱት መድፎች አንዱ “ሴባስቶፖል” ነበር። ስያሜው የሚያመለክተው አፄ ቴዎድሮስ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በተቀቡበት ዘመን በምዕራብ አውሮፓ፣ በክሬሚያ የሩሲያ ግዛት ለዐሥራ አንድ ወር ቱርክን፣ እንግሊዝን … ያሳተፈ “የሴባስቶፖል ውጊያ”ን የሚዘክር ሲሆን የንጉሡን ዓለም አቀፍ የመረጃ አድማስ ስፋት ያሳያል። ለምን ሰየሙት የሚለው ጥቂት ምርምር ይጠይቃል። ጋፋት ኢትዮጵያን በራስዋ ሀገር የተመረቱ የጦር መሣሪያዎችን የተጠቀመች አፍሪካዊት ሀገር የምታሰኝ የኢንዱስትሪ ማእከል ነች።

 መቅደላ የሽንፈት ግንባር አልነበረችም!!!

 ሰው ያውም ጀግና ሞተ የሚባለው ዓላማውና ጥረቱ ሲሞት ነው። ምኞቱ ሲከስር ነው። ሞት አይቀር፣ ሞተ ማለት ተከታይ ማጣት ነው። ግን “ዐፄ ተክለ ጊዮርጊስ ያፄ ቴድሮስን ፍለጋ ተከትለው አንድነትን ሲፈልጉ ጊዜው የአንድነት ጣዕም ያልታወቀበት ስለሆነ ሁሉም ጠፉ” በኋላም ዐፄ ዮሐንስና አፄ ምኒልክም ይህንኑ ጅምር እንደተከተሉ አልፈዋል” (ማኅተመ ሥላሴ፣ ገጽ 861)። ንጉሡ መቅደላ ከወደቁ በኋላ የጀመረው “ብሔራዊ (ሕብረ ብሔራዊ) መንግሥት” ፕሮጀክት አላቋረጠም፣ ዘመነ መሳፍንት አልተመለሰም። ራሳቸውን ገደሉ፣ ሞቱ፣ አበቃላቸው፣ አልተባሉም ይልቁንም “ሞት የሚያምርበት ንጉሥ ተባለ”። ሠዓሊ አገኝሁ እንግዳ በ1928 ነፃነቷን ለመጠበቅ በጋሻዋና በጦሯ ስለምትከላከል ኢትዮጵያ የተገጠመ

“በሃይማኖት ሚሲዮን ሰበብ ወደ ኢትዮጵያ የመጡ አውሮፓውያን የጦር መሣሪያና ሌሎች የአውሮፓ ሥልጣኔ ቴክኖሎጅ ውጤቶችን እንዲሠሩና ኢትዮጵያውያንን እንዲያሰለጥኑ አዘዙ። የመጀመሪያው ሥራ በርግጥ የጦር መሣሪያ ማምረት ነበር። ”

ግጥም፤ በሚል ዝክረ ነገር እንዳሠፈረው “በግራ በቀኝህ ጠላት መጥቶብሃል፣ በፊት በኋላህም ደመኛ ከቦሃል፤ በል ተነሣ ታጠቅ ሞት ባንት ያምርብሃል” (ገጽ 298)። አፄ ቴዎድሮስ ቢሞቱም “ብሔራዊ ጀግና” መባል አልቀረባቸውም። ዶናልድ ክረሚይ “ቴዎድሮስ ቢሞትም የጀመረው ጥረት አልተቋረጠም “የዘመናዊት ኢትዮጵያ አባት” መባልም አይበዛበትም። (Crummey 1969)። በመቅደላ አልተሸነፍንም፤ እንግሊዝም አንዲት ቅንጣት መሬት ሳትነካ፣ በገባችበት ወጣች፣ “ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኟቸው፣ ማረክን እንዳይሉ ሰው የለ በእጃቸው፣ ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው፣ ለወግ አይመቹም ተንኮለኞች ናቸው” (በገና መ/ስ ዓለሙ አጋ)። የቴዎድሮስ ዓላማና ጀግንነት ዘልቆ “ዐድዋን” ጨምሮ በኋላ ለተገኙት የድል አድራጊነት ወኔና የድል- ደጀን ነበር። አፄ ቴዎድሮስ መቸውንም ቢሆን “የሀገር ጀግና” የቆራጥነት፣ የዓላማ ጽናት፣ የታጋይነት፣ የአሸናፊነትና የአንድነት ምሳሌ ተደርገው ይቆጠራሉ።

 አፄ ቴዎድሮስ ለኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነቱ ከፍተኛ ፍቅር ነበራቸው፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እየሰፋ የመጣውን ልዩነት በጉባኤ እንዲፈታ በአዘዞና በደብረ ታቦር ጉባኤዎችን አድርገዋል። ለመጀመሪያ ጊዜ የእስክንድርያ ፓትርያርክ አቡነ ቄርሎስ 4ኛ ኢትዮጵያን የጎበኙት በአፄ ቴዎድሮስ ጊዜ ነበር። ጨካኝና ሩኅሩኅ፣ ሚስታቸውን እቴጌ ተዋበችን የሚሰሙ፣ ቁጡና ታጋሽ፣ አዛዥና ታዛዥ፣ ቸርና ጠያቂ ንጉሥ ነበሩ። ከጦር ያልተናነሰ የነገርና የስድብ ውጊያንም ያሸነፉ፤ እጅግ አስቸጋሪ ዘመንን በድል የተወጡ አስደናቂ ጀግና ነበሩ። “የኮሶ ሻጭ” ልጅ እየተባሉ ንግሥናቸውን ውድቅ ለማድረግ የነበረውን ሴራ ጥለው በዓላማቸው ተራምደዋል። ጳውሎስ ኞኞ “አፄ ቴዎድሮስ” በሚለው በ1985 የታተመ መጽሐፉ፤ “በየቦታው የሚሸመጠጥ የኮሶ ፍሬ እንኳን ያን ጊዜ በእኔም ዘመን ተሽጦና ገቢ አስገኝቶ ሰው አያስተዳድርም” ብሏል (ገጽ 9)። ለመሪነት የማይበቁ፣ የደሃ ልጅና ከዝቅተኛ የኅረተሰብ ክፍል ተገኙ የሚለውንም ሲጣላ “ራሳም በአንደኛው ቮሊዩም መጽሐፉ ላይ ሲጽፍ “አስተርን እንደጻፈው እናትየዋ ኮሶ ሻጭ መሆናቸውን ለማጣራት ሞክሬ ነበር። አንድም ሰው ኮሶ ሲሸጡ አይቻለሁ የሚል የዓይን ምስክር አላገኘሁም። ያገኘኋቸው ሁሉ የሚነግሩኝ የባላባት ዘር መሆናቸውን፣ አባታቸው የአማራ ሳይንት ራስ መሆናቸውን ነው። በአበሻ ውስጥ ታላላቅ ከሚባሉት ሰዎች ዘር መወለዳቸውን ነው ያጣራሁት” ብሏል። (ገጽ 10)፤ ጦርና ወሬን ድል ነስተው፤ ለሀገር ክብር ታግለው፣ ታሪክ ቀይረው፣ የሚጠራ ስም ይዘው በማለፋቸው፣ ሞቱ ወይም ተሸነፉ ሳይሆን “ጀግና” የሚለው ስም አብሯቸው ይኖራል። “አፄ ቴዎድሮስም በጀግንነት መቅደላም በታሪካዊ የድል አምባነት” ይዘከራሉ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top