ጥበብ በታሪክ ገፅ

ለወዳጅ የተጣፈ ማስታወሻ

አንድ፣ ጦጢትዬ፣ ደክሞኛል። የቻይናን ምድር ከረገጥኩ አንድ ቀን ከግማሽ ሆነ። ያለሁባት ከተማ ኢዩ ትባላለች። የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪ ከተማ ነች ይሏታል። በቻይናዎቹ አሰያየም አንድ የወረዳ ከተማ ነች። ስፋቷን፣ ዘመናዊነቷን፣ ስልጣኔዋን ማወዳደር ግን አይገባም። ለምሳሌ ከአንዱ የጅምላ ሻጮች ናሙና ማሳያ ቦታ ብትገቢ ጠዋት ሁለት ሰዓት ጀምረሽ ማታ አንድ ሰዓት ላይ ካላባረሩሽ በስተቀር ልትወጪ አትችይም። በጣም ሰፊ፣ በጣም ረዥም፣ በጣም ብዙ፣ አይገልፀውም። አጠቃላይ አምስት ፎቅ አለው። እያንዳንዱ ወለል (floor) የየራሱ የሆነ ምርት ማቅረቢያ ነው። እንዲህ አይነት የናሙና ማሳያ ቦታዎች እዚህች ከተማ ውስጥ ከ15 በላይ ናቸው። አስቢው አንዱኮ በራሱ አንድ ወረዳ ያክላል።

ያደክምሻል እንጂ ዞረሽ፣ አይተሽ፣ ተከራክረሽ አትጨርሺውም። የቻይና የጨርቃ ጨርቅ ምርቶች በብዛት ከዚህች ከተማ ነው የሚሄዱት። ሃንጁ ዋናዋ የክፍለ ሃገሩ ከተማ ስትሆን ኢዩ – ከሃንጁ የ130 ኪሎ ሜትር ርቀት አላት። በአዲስ አበባና በመቂ መካከል ያለ ርቀት በይው።

አዲስ አበባን ስለቅ በጣም ከፍቶኝ ነበር። የ14 ሰዓት በረራ መሆኑን ሳስበው ደግሞ በቃ ሳልጓዝ አቅለሸለሸኝ። ብችል ሃገሬ ብቆይ እመርጥ ነበር። ውስጤም “ደሞ ለቻይና” የሚል ‘ንቀት’ና ‘ማጣጣል’ ሲያዜም ነው የከረመው። ከመነሳቴ በፊት ስለምበላው ምግብ አሰብኩ – የሆዳም ነገር። በርካታ ‘ምርጥ’ እንቁራሪቶችና ዘመዶቻቸውን ገመትኩኝ – አስፈራኝ። ቆሎ መያዝ አማረኝ። ‘ፋራ’ የምባል መሰለኝ። ጭኮም መያዝ አማረኝ የ‘ባላገር’ነት አይነት ስሜት ተሰማኝ። ‘ዳቦ ቆሎንም’ አሰብኩት – እሱም “አርበኝነቴን” አስታወሰኝና ተውኩት። ‘መቅረትና- መሄድ’ በሚሉ የመንታ መንገድ ዜማዎች “ነፍሴን” ትንሽ አሳሰብኳት። በበርካታ የሃሳብ ውጣ ውረድ ነጠላና አስጨናቂ ዜማዎች ታጅቤ እንደከረምኩ እሁድ ከሌሊቱ ስምንት ሰዓት የአዲስ አበባን አየር ሰንጥቀን ወጣን።

አዳሜ ያንቀላፋል። አዳሜ ያልማል። አዳሜ ተቃቅፏል። አዳሜ ጀርባ ለጀርባ ተሰጣጥቷል። አዲስ አበባ አየር ላይ ሆኜ ለመጨረሻ ጊዜ እነዚህን አሳቦች ውስጤ አጫወትኳቸው።

 ቻይና – ሃንጁ … በሩቁ – በፍርሃትና በከፊል ጉጉት – ሃሳቤን ወደዚያ አዞርኩ። ጢያራያው ላይ ህንዶች ተሳፍረዋል። ሃበሾችም “ባለጋሪው ቶሎ ቶሎ ንዳው” እያሉ በርበሬያቸውን እያገሱ ተጓዥ ሆነዋል። እኒህ ቻይናዎችም አብረውን ሊሄዱ ተጐራብተውናል። አፍሪካኖች፣ በዛ ያሉት ደግሞ ናይጄሪያዎቹ ናቸው፣ አጃቢዎቻችን ነበሩ። ወይም እኛ የነሱ አጃቢ ነበርን።

የሚገርመው ጉዞ ከመጀመሩ ሁሉም ፎጣውን ተከናንቦ ከእንቅልፉ ጋር ተጨባብጦ ሄዷል። አቤት ፍጥነት፣ አቤት ግዴለሽነት። እስቲ አሁን ከ30 ሺ ጫማ ከፍታ ላይ ሆኖ ሰው ይተኛል?! አዳነች ጨብራሬ ይህን ጉድ ምን ትለው ይሆን? /አዳነች የኔና ያንቺ ምስለ-ሰብእናችን/። ገርሞኛል። እሷ ግን ላይገርማት ይችላል። የጨብራራ ነገር ሁሌም ግራ ወይም ግራ – ቀኝ ነው። የተመጠነ ፈገግታ ያላቸው የበረራ አስተናጋጆች ያጫውቱሻል። ግን አላማሩኝም። ከንፈራቸው ስስ ነው። ሳቃቸውም ስስ። አይኖቻቸው ግን ደስ ይላሉ። ተጫዋችና አጫዋች አይኖች።

 አቤት ጉዞ ፀጥ – ጭጭ ብሎ መሄድ። ጅቡቲን፣ የመንን፣ ሊባኖስን… አፍጋኒስታንን፣ ፓኪስታንን በጨለማ ውስጥ አለፍናቸውና በአገሬው ሰዓት አቆጣጠር ከማለዳው ሁለት ሰዓት ሲሆን ኒውደልሂ ገባን። በረጅሙ ጉዞ መሃል በርካታ ሃሳቦች እየመጡ እያጫወቱኝ አለፉ። አንዳንዶቹ ያስቁኝ ነበር። አንዳንዶቹ ያስገርሙኝ ነበር። አንዳንዶቹ ደግሞ ያስተክዙኝ ነበር። አንዳንዶቹ ዝም ብለው ያፋጥጡኝ ነበር። ሰው ለካ ከውስጡ ጋር ጥሞናውን ሰብስቦ ከተያያዘ ስንትና ስንት ጉድ አለበት አይደል’ንዴ? ወደ ራስ፣ ወደ ውስጥ መመልከት – ቻይኒስቶቹ እንደሚሉት ጥሞናን ወደ ውስጥ ማድረግ የሚገርም አለም ነው።

አዳነች ጨብራሬ ይህን ታውቀው ይሆን? ብቻ… ኒውደልሂ ላይ አንድ ሰዓት ቆየን። ያመጣን ፓይለትና አስተናጋጆች በሌሎች ተቀየሩ። ጉዞም ወደ ሃንጁ ተጀመረ። ከ37 ሺ ጫማ ከፍታ በላይ – ለስድስት ሰዓት ተኩል ተጨማሪ በረራ። እንደገና ወደ ውስጤ ተመለስኩ። አብሮኝ የሚጓዘው ሰው ከእንቅልፉ የሚመለሰው ቢራ ወይም ምግብ ሲቀርብ ብቻ ነው። ከህልሙ ጋር መጫወቱን የወደደው ይመስለኛል። ከህልም ጋር መጫወት መታደል ነው። ከ14 ሰዓት የአየር ጉዟችን ውስጥ ተደማምሮ 160 ደቂቃዎችን ብቻ ነው የነቃው። መታደል ይሆን? ፍቅር ይሰማኛል። ናፍቆት ይዳብሰኛል። መሳም ያምረኛል። መናደድ … ያላግጥብኛል። መቆጣት ደግሞ ጨጓራዬን ያናውጥብኛል። ግን ሁሉም ተደምረው በ37 ሺ ጫማ ከፍታ ላይ የምበር የፕላኔታችን ኮተታሙ ሰው አላሰኙኝም።

 “ይሁን አለች” ጦጢት ገርሟት።

 “ምኑ ነው የሚሆነው” ሲል ጠየቃት – የጦጢት አጫዋች።

 “የሆነውና እየሆነ ያለው ነገር ሁሉ” ስትል መለሰችለት።

 “አልገባኝም” ሲል ግራ መጋባቱን በሁሉ ነገር ገለፀላት።

 “እሱም ይሁን” አለች ጦጢት። እንዲህና እንዲህ እየወጣሁ እየወረድኩ – ሃንጁ ደረስኩ፤ ከምሽቱ ሦስት ሰዓት። መጀመሪያ ወላፈን ተቀበለኝ። ጋምቤላን መጀመሪያ ስረግጣት የገረፈኝ የበረሃ ወላፈን ሃንጁም ደገመኝ። በ45 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሙቀት መጠን። ደስ አለኝ። ሙቀት እወዳለሁ። በህይወቴ ውስጥ የተቀዛቀዘ ነገር አይመቸኝም። የሃንጁ የሙቀት ግርፋት – መልካም ስሜት ሰጠኝ።

እነሆ ሁሉ ነገሩ የቀጣጠነ አንድ ሃበሻ መጥቶ ተቀበለን። ጠይም ወጣት – መልከ ጥፉ ያልሆነ ነጋዴ- ቻይንኛውን እያንበለበለው ወደ ታክሲ ወሰደን።

“ዳሩሳ” እባላለሁ አለ። በመብራት የተንቆጠቆጠችው ሃንጁ አፉን አስፍቶ በከፈተው አውራ ጐዳና አድርጋ “እንኳን ደህና መጣህ አንተ ድሪቶ” በሚል ስላቅ ተቀበለችኝ። ሃንጁ ማደር አልቻልንም። ዳሩሳ እያከነፈን /እያበረረን ቢባል ይቀላል/ ከምሽቱ ሰባት ሰዓት ኢዩ አደረሰን። እነሆ አሁን ያለሁበት ባለ አራት ኮከብ የኢዩ ምርጥ ሆቴል ውስጥ ከተተን። እንቅልፍ አልነበረኝም። ግን ደግሞ ደክሞኛል። መፃፍ ፈልጌ ነበር – ግን ደግሞ አስጠልቶኛል። አሰብኩሽና ራሴን ገፋፋሁት፤ ለመፃፍ ግን አልቻልኩም። ቃሌን መጠበቅ አልቻልኩም። ብሽቅ! ቀሽም። ስንፍናን ከነጓዙ ተሸክሞ የሚሄድ 40ን የተሻገረ ወደል ዱርዬ! በቃ ተውኩት። እነሆ አሁን ደከመኝ ወይም ደበረኝና መፃፍ ላቆም ነው።

 ‘Sorry’ አለች ጦጢት።

 አሁን ሰአቱ በቻይና አቆጣጠር 6፡20 ነው ከምሽቱ። ነገ ልቀጥል። ደህና ሁኚ ጦጢት።

ሁለት፣

 12፡04 ሌሊት፣ በቻይና አቆጣጠር። ከምሽቱ አንድ ሰዓት በኢትዮጵያ። ቻንጅንግ ሆቴል፣ ክፍል ቁጥር 1516። ውሎ ያደክማል። ስራው የቀን ስራ ነው ማለት ይቻላል። አዎን የቀን ስራ። ኧረ ልክ አይደለሁም – የጉልበት ስራ ነው። እውቀት አይጠይቅም – ቋንቋ ግን ይጠይቃል። የዋህነት አይከለከልም – ግን ደግሞ ብልጥ መሆን ግድ ይላል። ረጋ ብሎ መነጋገር ይቻላል – ግን ትንሽ መጯጯህ አስፈላጊ ነው። ውሎዬን ሳስበው ድካም ተሰማኝ። ይህ ደግሞ የተነሳሳውን የመፃፍ ስሜቴን ሊወስድብኝ ነው። በቃ – ዘለልኩት። በመዝለል ታዋቂ አይደለሁ?

ዳሩሳ – የቻይና – አንበሳ! ይሄ ልጅ ገርሞኛል። ዳሩሳ የቻይናን ምድር ከረገጠ አራት ዓመት ሆነው። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንደጨረሰ የመንግስት ስራ ተቀጥሮ አፋር በረሃ መሃል ገባ። አንድ ዓመት ከምናምን ቀናት ሠራ። ደበረው። ወደ ቤተሰቦቹ ተመለሰ። አንድ አጐቱ በኮንስትራክሽን ድርጅቱ ውስጥ ቀጥሮ ወደ አሶሳ ላከው። ካንዱ በረሃ ወደ ሌላው – ተጓዘ። አሶሳንም ሁለት ዓመት ከምናምን ቀናት ተቀመጠባት፤ ይቅርታ ሠራባት። ኧረ አሁንም ይቅርታ ሠራላት። ምን ነክቶኝ ነው ባካችሁ? ስራ ሠራ። ያው ገቢው አነሰበት። የወጣት ነብሱ የበለጠ መስራት እንዳለበት ነገረችው። እንደልማዱ አሶሳን ተሰናብቶ ወደ ቤተሰቡ ተመለሰ። ተቀጣሪነት አስጠላው። “አያፈናፍንም” እንዳለችው ጦጣ። ይገርማል ውስጡ ብዙ ፈለገ። በገንዘብ ሀብታም የመሆን። በራስ መንገድ የመበልፀግ። ለራስም ለቤተሰብም የመስራት።

ከቀናቶች ባንዱ አንድ አጐቱ ስራ አግዘኝ ብሎ ወደ ዱባይ ወሰደው። ዱባይንም ወደዳት። ቀጠለና ወደ ቻይና ተሻገረ። እነሆ ራሱን ችሎ መስራት ከጀመረ አራት ዓመት ሆነው። “እሳት የበላ” ኤጀንት ሆኗል። በቻይና “ርካሽ” ምርቶች መክበር የፈለገ የመርካቶ “ወፍራም” ነጋዴ ወደሱ ይደውላል፤ ኢዩ መጥቶ ይገበያያል። ዳሩሳ የቻይናን ቋንቋ በመልመዱና በመቻሉ

“በእርግጥ የሚያናድዱ የቻይና ህፃናት ያጋጥሙሻል። ጥቁር ሲያዩ ይሸሻሉ፤ ወይም ይደበቃሉ። ለምን ሲባል የቆዳ ቀለምሽ ለቆ እንዳታጠቁሪያቸው”

ምክንያት የነጋዴዎቹን ምርቶች ወደ ካርጐ፣ ከዚያም ወደ አገር ቤት ይልካል። ኢዩን ከእግር እስከራሷ ያውቃታል። “ዳሩሳ” እሳት የበላ ‘ደላላ’ ወይም “ትራንዚተር” ሆኗል። አሁን የራሱ አለቃ ነው። ኧረ የሦስት ቻይናዎችም አለቃ ነው።

ይኸው ከዚህ ልጅ ጋር ከሰኞ ጀምሮ አብረን እየበረርን፣ እየከነፍን፣ እየሠራን ነው። የኛን ግዢ የሚሠራው እሱ ነው። አሪፍ ልጅ ነው። የነጋዴ ልብ የለውም። ሰውነቱ ይጐላል። አያጭበረብርም፤ ግን ደግሞ ማትረፍ ይፈልጋል። የሠራተኛ ደመወዝ አለበት። የቢሮ ኪራይና የእለት መኖሪያ ገንዘብ ያስፈልገዋል። ስለዚህም “ነጋዴ” መሆን አለበት – እንደምገምተው። በጥሩ የቤተሰብ ማሳ ውስጥ ተኮትኩቶ የመጣ ነው። ይገርማል። አሪፍ ወጣቶች፣ ሩህሩህ ወጣቶች፣ ሃላፊነት የሚሰማቸው ወጣቶች፣ ሰውነትን የማያስቀድሙ ወጣቶችን በዚህ ወቅት ማግኘት መታደል ነው። ዳሩሳ ይህ ነው። ሠራተኛው ንብ። በራሪው እርግብ። ተቆጪው አንበሳ። ወደድኩት። ዳሩሳ – ልቤ ውስጥ ገባ።

 ይኸው ደግሞ ክብረ አለም። የዳሩሳ ጓደኛ ነው። የሰሜን አካባቢ ነጋዴ። እቃ ለመግዛት ነው ወደ ኢዩ የመጣው። ታዳጊ ነጋዴ ነው፤ ዕድሜው 40ን ሊደርስ ጥቂት ቁጥሮች የቀሩት ይመስላል። አማርኛው ይጣፍጣል። ትግርኛ ጣል ስለሚያደርግበት። የጠገበ ሀብታም ነጋዴ መሆን አይፈልግም። “ሰውነትህን” ትረሳለህ ይላል። የተራበ ነጋዴ መሆንም አይፈልግም። መኖር አለበት – በአግባቡ ሚስቱንና ሦስት ወንድ ልጆቹን አሪፍ አድርጐ ማኖር ይፈልጋል። የሚሠራውም ለዚህ ነው። አይኖቹ የነጋዴ አይደሉም። አንደበቱ አይፈጥንም። ክብረ አለም ክብሩን ያውቃል። በልክና በአግባብ መኖር በሚለው የኑሮ መርሁ። ከዳሩሳ ጋር የተለያየ ቋንቋ ቤተሰብ ቢሆኑም የአንድ አገር ልጆች ስለሆኑ ይግባባሉ። ከሱ በላይ “ቅንነታቸው” ያፋቀራቸው ይመስለኛል። ለኔም ውስጤን የ“መልካምነት” ብርሃን አልብሰውልኛል። እንዴት አይነት ደጋግ ልጆች ናቸው!?

 ዳሩሳና ክብረ አለም ወደራሄል ቤት ወሰዱን። ራሄል በምድረ ኢዩ ያሉ ሀበሾችን በባህላዊ ምግብ መንፈሳቸውንና ትዝታቸውን የምታድስላቸው ልጅ ነች። ወጣት ናት። እንደ ሰማሁት የአንዱ ጥጋበኛ ሃብታም ነጋዴ “ቅምጥ ናት”። ሰውየው በወራቶች መሃል ብቅ እያለ ስለሚሄድ ታስተናግደዋለች። እንዳትሰለችበትመ ንግድ ፈጥሮላታል። ሃበሾች የሩዝ እንጀራ በክትፎ ወይም በዶሮ ወጥ ወይም በጥብስ አሊያም በተጋቢኖ ያገኛሉ።

“የጥጋበኛውን ዕድሜ” ያርዝመው ይላሉ – ሃበሾቹ ሲቀልዱ።

 “ለምን?” ሲባሉም፣

 “ይሄ ጥጋበኛ ባይጠግብ ኖሮ አይቀብጥም ነበር። ባይቀብጥ ኖሮ ደግሞ ራሄልን አናገኛትም ነበር። የሱ ጥጋብ እኛን ታደገን” ይላሉ።

 እናም “ጥጋበኛና ቅንዝረኛውን ነጋዴ አብዛልን” እያልን ነው ይላሉ። በሸክላ ድስት ተጋቢኖ፤ ቡና በጀበና! ኢዩ ውስጥ ተገኝቶ ነው። እነዚህ ሃበሾች እውነታቸውን ነው። ይሄ ጥጋበኛ ባይጠግብና ራሄልን “እነሆ በረከት” ባይላት ኖሮ መች እኔስ ዛሬ በሩዝ እንጀራ ተጋቢኖ እበላ ነበር? ያውም የጀበና ቡናዬን ፉት እያልኩ። “እና ያጥግብህ” አልኩት እኔም። እናም ጦጢትዬ ይኸውልሽ ራሄል የአገራችን ሰንደቅ ዓላማ “ሆቴሏ” በር ላይ ሰቅላ ሃበሾቹን ይዛቸዋለች። ሀበሻ የሰንደቅ ዓላማው ነገር ሞቱ አይደል!! እርግጥ ነው አገር ቤት በምትገኘው የጥጋበኛው ነጋዴ ሚስት ቦታ ሆኜ ነገሩን ሳየው “ሃጢያት” ነው። ግን ምን ይደረግ? ራሄልንን የመሰለች “ቅምጥ” ባለሬስቶራንት ኢዩ ምድር ላይ ማግኘት ያስደስታል።

 ለነገሩ ጥጋበኛውም ቢሆን እኮ የውርስ ነገር ሆኖበት ነው ያደረገው። የባህሉን፣ የወጉን፣ የደንቡን ነው የሠራው። የትናንቶቹ ቻይናን ባያውቋትም በየመድረሻው “ቅምጦች” ነበሯቸው። ወይ ጥጋብ! ራሄልን ከሰታት። ራሄል ሃበሾችን ሳበች። ሃበሾቹ በኢዩ ምድር ሲኳትኑ ይውሉና ወይ ምሳ አሊያም እራት ላይ ራሄል ቤት ይገናኛሉ። አቤት ፍቅር! ሰው ለምን በአገሩ እንዲህ ተነፋፍቆ፣ ተዋዶና ተከባብሮ አይኖርም? ዘይገርም አለ አቦይ ስብሃት፤ ነፍሱን ይማርና። ኢዩ ሃበሾች በብዛት አሉ። ግን የዲሲን ያህል ወይም የዱባይን ያህል አይበዙም። መብዛቱ ቀርቶ የሩብ – ሩብ፣ ሩብ፣ ሩብ፣ አሁንም ሩብ ያህል አይሆኑም።

የገባኝ ነገር ሰው መሆን ደስ ይላል። “ለምን?” ብላ ጦጢት ብትጠይቀኝ ኢዩ ሁሉም አይነት የሰው ዘር ይገኛል። ሁሉም ውስጥ የሚነበበው መንፈስ “ፍቅር” ነው። ሰዋዊ እሴት። ሰው የመሆን “ክብር”። በእርግጥ የሚያናድዱ የቻይና ህፃናት ያጋጥሙሻል። ጥቁር ሲያዩ ይሸሻሉ፤ ወይም ይደበቃሉ። ለምን ሲባል የቆዳ ቀለምሽ ለቆ እንዳታጠቁሪያቸው። ዛሬ ሊፍት ልንይዝ ቆመን አንዱ ህፃን የሆነ ነገር ተናገረና አፍንጫውን ያዘ። ዳሩሳ ተናደደ። እሱም የሆነ ነገር ለህፃኑ ጮክ ብሎ ተናገረ። የህፃኑ አባት ልጁን አልተቆጣም፤ ዳሩሳንም ቀና ብሎ አላየም። ምን እንዳለው ጠየኩት። “ጥቁሮቹ መጡና ሸተተኝ” ብሎ ነው ለአባቱ የነገረው። ዳሩሳ ደግሞ አንተ “ቆሻሻ” ምናምን ብሎ ነው የተናገረው። ዳሩሳ መናደድ አልነበረበትም። ህፃኑን የቀረፀው ቤተሰቡ ነው። ምን ይደረግ። ይህ እኮ ኢትዮጵያም አለ – በተለያየ ገፅታው። ስንቱን በቋንቋው ስናላግጥበት አይደል ያደግነው?! ግን መጥፎ አይደለም። ልጆችስ ምን አደረጉ የሰጠናቸውን ነው የሚቀበሉን። “የሆነ – ሆኖ” በክብረ አለም አማርኛ “መጥፎ ነገር የለም” እስማማለሁ። ባልስማማስ ምን አመጣለሁ? ሁላችንም በየራሳችን የሀሳብ ባህር ውስጥ አይደለ መርከባችንን አቅጣጫ የምናስይዘው።

 ኢዩ – አትከብድም። አዲስ ከተማ ነች – የ14 ዓመት ዕድሜ ያላት። ግን አትመስልም። ትጣፍጣለች። ጥንቅሽ ናት። ታባብላለች፣ የመጐተት አዚምም አላት። የፈረጃው ጠንቋይ ጎትት አስሮባት ይሆን? አላውቅም – ለውጪ ጉዞ እምብዛም ስለሆንኩ ይሁን እንጃ ብቻ ኢዩን ውስጤ ወዷታል። ቅልል ብላኛለች። ነፃ መንፈስ ፈጥራብኛለች። ክብረ አለም ዱባይን ያውቃታል። ሻንጋይን፣ ባንኮክን፣ ያውቃቸዋል። በኢዩ ግን ተማርኳል። አብሮኝ የመጣው የስራ ባልደረባዬ ህንድን ኖሮባታል። በተለይ ደልሂን። ዱባይን፣ ጣልያንና ሌሎች የቻይና ከተሞችንም ያውቃቸዋል። “ግልፅ” ባልሆነለት “መንፈስ” ወይም ስበት ኢዩን በተለየ አይን እንደተመለከታት ሩዙን እየበላ ነግሮኛል።

 ኢዩ ምን ያስጠላል መሰለሽ – የትራፊክ ህግ የለም። የመኪና ብዛት የመንገድ አጠቃቀም ስርዓታቸው ያበሽቅሻል። ግን ደግሞ አደጋ የሚባል ነገር የለም። በ30 ኪሎ ሜትር ሬዲየስ ውስጥ ትራፊክ ፖሊስ ካገኘሽ ሎተሪ በይው። ትራፊኩ መንገድ ላይ የለም። /ለነገሩ በየመንገዱ የወደሩት ካሜራ ያሳብቅላቸው የለ፣ ምን ያደክማቸዋል?/

 ሦስት፣

ኦገስት 4/2012፣ ከምሽቱ 6፡20 በአገሬው ሰዓት። ብዙ መፃፍ አልፈልግም፣ ትናንትም ምንም አልፃፍኩም። ምክንያቱም፣ 1ኛ ደክሞኝ ነበር ወይም፣ 2ኛ ደብሮኝ ነበር ወይም ደግሞ፣ 3ኛ የመፃፍ ፍላጐቴ ተሰርቆ ነበር። ወይ ጉድ አሁን ደግሞ ፃፍ ፃፍ እያለኝ ነው። ኢዩን እየወደድኳት የመጣሁ ይመስለኛል። ስለ ቻይናዎች ማወቅ እየሞከርኩ ነው። ከነሱ በላይ ደግሞ እዚህ ሁሉም የሰው ዘር አለ። ህንዶች ሆቴልና ቡቲክ ቤት ተከራይተው ይሠራሉ። ቱርኮች ጨርቃጨርቅ ይቸረችራሉ። የሩሲያና ካዛክስታን ሴቶች የ“ሽርሙጥና” ስራ ይሠራሉ። “ማሳጅ” የሚባል መጠሪያ አለው።

ድንገት አንዱን ባለ ታክሲ የሆነ ቦታ ውሰደኝ ትይዋለሽ። ችግር የለም ታክሲዎቹ በኪሎ ሜትር ስለሚሄዱ የዋጋ ውጣ ውረድ የለውም። “ግቢ” ይላል። በአስተርጓሚ ማውራት ይጀምራል።

 “ከየት ነው?” ይልሻል

 “ከኢትዮጵያ” “ማሳጅ ትፈልጋለህ?”

 “አልፈልግም።”

 “ለምን? እናንተ ኮ ትወዳላችሁ”

 “ምኑን?”

 “ማሳጁን”

 “አንተ ትጠላለህ?”

“እኔም እወዳለሁ፤ እንደውም አንዳንዴ ሚስቴ ገጠር ስትሄድ እኔም ወደ ማሳጅ እሄዳለሁ።

 ‘’ሚስትህ አታውቅም?’’

 ‘’ታውቃለች።’’

 ‘’አትናደድም?’’

 ‘’ምን ያናድዳታል? አገሩ እኮ በረሃ ነው።’’

 ያስቃል ብዙ ብዙ የአፍሪካ ሴቶች የሚያመሹበት

“የ“ኢዩ” ምሽት ገበያ የመንገዱን ዳር ይረከባል። በምሽት ገበያው ሁሉም ነገር አለ። ለምሳሌ ከአረቦቹ ፓስቲ ጀምሮ እስከ ህንዶቹ ቂጣ፣ ከሀበሾቹ የቢራ ላይ ወሬ አንስቶ እስከ ቻይናዎቹ ውሹ ድረስ። የምሽት ገበያው ሸቀጥ ብቻ አይቸረቸርበትም። ፈጣን ስዕል ማሳል ትችያለሽ”

“በቄ” ቤት ይባላል። ባለቤቱ ቻይናዊ ነው። የሀበሻ ዘፈን ይዘፈንበታል። ቢራ ይጠጣበታል። ሁሉም አይነት ቋንቋ ይወራበታል። በቂ ቤት ሩሲያውያንና አፍሪካውያን ሴቶች ወንዱን ይነድፉታል። ይጋብዛቸዋል። ይጋብዙታል። እነሆ በረከት ካማረው ገንዘብ መክፈል ብቻ ነው የሚጠበቅበት። አምሮቱን ያራግፉለታል። ምን ቸገራቸው ሃጢያቱ ለራሱ። አስተርጓሚዬ እንዳወራኝ “በቄ” ቤት ሽርሙጥና የሚሰሩ አፍሪካውያንና /የኛ ሴቶች የሉበትም/ ሩሲያውያን ሴቶች ብዙዎች በጋራ ቤት ተከራይተው ነው የሚኖሩት። እየሸቀሉ አሻግረው ቤተሰብ ይደጉማሉ። የቻይናዎቹም “እነሆ በረከት” አጫዋቾች እንዳሉ ሰምቻለሁ። ነገ ከቻልኩ አካባቢውን ሄጀ ማየት እፈልጋለሁ።

 ኢዩ ትገርማለች። በአለም ላይ ምርጥ የሚባሉ መኪኖች ሁሉ ኢዩ ውስጥ ይታያሉ። የደሃ መንደሮችን ለማየት ሞክሬ ነበር። የ “ኢዩ ደሃ” የአገሬ መካከለኛ ነዋሪ ማለት ነው። እርግጥ ነው አልፎ አልፎ አሮጊትና ሽማግሌ ለማኞች አሉ። አሮጊት ሊስትሮዎች ይታያሉ። ሁለቱም ግን ትጉ ናቸው ራሳቸውን ለማኖር። መዝናናት በጣም ይወዳሉ። አለባበሳቸው የሚመች ነው። ነፃ አለባበስና ነፃ የአኗኗር ዘዴ። አንዳንድ ሃበሾች ሲያወሩ እንደሰማሁት “ውስጣቸው አልሰለጠነም” ይላሉ። መቀበል ግን ይከብደኛል። ያልሰለጠነው “ኢዩ” ያለው የሀገሬ ልጅ እንዳይሆን እሰጋለሁ። መልካም አዳር።

አራት፣

ቅዳሜ፣ ኦገስት 4/2012፣ ከምሽቱ 5፡20። እነሆ ስለ አፍሪካውያን ላወራሽ ነው። ለወሬ አይደል የምተጋው? እዚህ በርካታ ምዕራብ አፍሪካውያን ሱቅ ከፍተው ትዳር መስርተው ይኖራሉ። እንደነገሩኝ በርካታ ቁጥር ያላቸው ምዕራብ አፍሪካውያን የሚኖሩት ጓንጁ ነው። ጓንጁ ምትሃተኛ ከተማ ነች ይባልላታል። መሄድና ማየት ነበረብኝ። ጊዜ አጠረኝ። ምዕራብ አፍሪካውያኑ ምን መሰለሽ የሚያደርጉት? የተሻለ ብር ያላቸውን ሴቶች /ቻይኒስቶቹን/ ይለዩና “ይወዳሉ”። የወንድ ‘’እጥረትም’’ ስላለ ሴቶቹ “ጠብ” ይላሉ “በፍቅር”። ፈጥነው ያገቧቸዋል። ፈጥነው ይወልዳሉ። ካገባሽና ከወለድሽ ደግሞ ንብረት መካፈል ይመጣል።

ስለዚህም አፈር ድሜ በልታ ያፈራችው ሃብት የኮርማውም ሃብት ይሆናል። ይሄኔ ሰውየው አገሬ ናፈቀኝ ይላል። ድንገትም “ቤተሰቦቼን ልይ እግረመንገዴንም ላስተዋውቅሽ” ይላል።

 “ማሬ አሪፍ ሃሳብ ነው” ትለዋለች አንገቱ ስር እየሳመችው።

 “ሺሼ” ይላል አጥብቆ ስሟት። እድሜም እየከዳት ስለሆነ ወፍራም ከንፈር ሲያርፍባት ልቧም ቅልጥ ይላል። ሰውየው ወደሀገሩ ይወስዳታል። ልቧን የበለጠ ዘርፎ ይመለሳል። ከዚያም ሁሉም ነገር ይሆናል። ልጆች ይወለዳሉ። ለብቻው አገሩ እየተመላለሰ የአገሩን ልጅ ያገባል ወይም ያስቀምጣል። ይህቺ ምስኪን “ኑሯችን” ትላለች። ኮርማው “አገሬ” ብሎ ይጓዛል። እንዲህና እንዲህ እያሉ ሀብት ይሰበስባሉ። እናም ምዕራብ አፍሪካውያኑ በዚህ “ኤክስፐርት” ናቸው ይባላል።

 ሃበሾቹስ? አንድ ሁለት ሃበሾች ቻይኒስቶችን አግብተዋል ባለሁበት ከተማ። ቀጥ ብሎ ኑሮ እያጧጧፉ ነው። መክዳትና ማምለጥን አያስቡም። እዚህ ያለው ሃበሻ ካለው መዝናናት፣ መደነስ፣ ማቀፍ፣ መጠጣት ይወዳል። ረጅም ሰዓት ቁጭ ብሎ በማውራትም ማንም አይደርስበት። ህንዶቹ የራሳቸውን ህይወት ይኖራሉ። ቱርኮቹም በተመሳሳይ። ሁሉም የየራሱ መሰባሰቢያ አለው። እርግጥ ነው እንዳየሁት መጤው አንድ አካባቢ መሰባሰብ ይወዳል።

 ፋቲያን

ይኸውልሽ ፋቲያን በሃንጁ ግዛት በኢዩ ወረዳ የምትገኝ የዓለማችን ‘’ትልቋ’ ገበያ ነች። ፋቲያን በአጠቃላይ አምስት ዲስትሪክቶች አሏት። እያንዳንዱ ዲስትሪክት ወይም አንዱ ዲስትሪክት ከሌላው ጋር የተያያዘ ነው። እንደ ባቡር ፉርጎ ቁጠሪው። በአጠቃላይ የ5ቱም ዲስትሪክቶች ርዝመት ከ15-25 ኪሎ ሜትር ይደርሳል። G +5 ነው ከፍታው።

 ፋቲያን ራሷን የቻለች ዓለም ነች። ሁሉም ነገር አለባት። ቻይና ራሷን የምትሸጥባት፣ ራሷን የምትገልፅባት፣ ለውጧን የምታሳይባት ሆና አግኝቻታለሁ። “ሚጢጢዋ” ከተማ ከተመሠረተች 18 ዓመት ይሆናታል። “ሚጢጢ” የምትባለው በቻይንኛ ነው። ከአዲስ አበባ ጋር ካወዳደርሻት አይገናኙም። ዘመናዊነት፣ የገቢ መጠን፣ ዕድገት፣ ጤና፣ ትምህርት የመሳሰሉትን በፍፁም እንደማነፃፀሪያ ማምጣት አይጠበቅብሽም።

 የፋቲያን ሴቶች አያምሩም ወይም አላማሩኝም። አጫጭሮች፣ ፉንጋዎችና ቢጫዎች፣ ግን ደግሞ ነፃ ናቸው። አቤት ነፃነት። ሊደፍራት የሚችል አዳም የለም። በፋቲያን ነጋዴ ይበዛል። የገበያ ማዕከሉ በር ጠዋት ሦስት ሰዓት ላይ ይከፈታል። ከምሽቱ 11 ሰዓት ይዘጋል። ይቀጥልና የ“ኢዩ” ምሽት ገበያ የመንገዱን ዳር ይረከባል። በምሽት ገበያው ሁሉም ነገር አለ። ለምሳሌ ከአረቦቹ ፓስቲ ጀምሮ እስከ ህንዶቹ ቂጣ፣ ከሀበሾቹ የቢራ ላይ ወሬ አንስቶ እስከ ቻይናዎቹ ውሹ ድረስ። የምሽት ገበያው ሸቀጥ ብቻ አይቸረቸርበትም። ፈጣን ስዕል ማሳል ትችያለሽ። ለምሳሌ እንደኔ አይነቱን ቶፋ በ10 ደቂቃ ምርጥ አድርጐ

መሳል ይቻላል። ከፈለግሽም፣ ቻይንኛ ከቻልሽ፣ ግጥም የሚያንበለብሉ ቡድኖችን ታገኚያለሽ።

“ማርዬ ወለላዬ

ቁመትሽ ለግላጋ

 አይኖችሽ ቢያደርጉኝ ወጋ ወጋ

 ክንፎቼ ታጠፉ የልቤን ማዕበል ሊያናጋ”

 አይነት ግጥሞች… ወይም ደግሞ ከፈለግሽ መቀነስ ትችያለሽ። ሙዚቃ ታዳምጫለሽ። አሮጊቶችና ሽሜዎች ዕድሜያቸውን በዳንስ ሲያዋዙና ህይወትን በልስላሴ ሲሞቋት ያጋጥምሻል። እንዲህ አይነት የምሽት ገበያ ለኔ የመጀመሪያ ነው። የኢዩ ሰዎች ህይወትን እየኖሯት ነው። 24 ሰዓት ህይወት ለደቂቃም አትቆምም። ለማኞቹ እንኳን 24 ሰዓት ይለምናሉ። ኢዩ ውስጥ ሦስት ዓይነት ቻይናዎች አሉ – እንደሰማሁት። ከጠቅላላው ነዋሪ ቁጥር 75 በመቶ ነጋዴ ነው። 10 በመቶ የመንግስት ሠራተኛ። ቀሪው 15 በመቶ በተለያየ መንገድ በሽቀላ መደብ ውስጥ የሚወድቅ ነው። ነጋዴው አዳዲስ ቢ. ኤም. ደብሊው ወይም ማርሰዲስ ወይም ሬንጅሮቨር ይነዳል። የመንግስት ሠራተኛው ወይ ሞተር ሳይክል አሊያም ሳይክል አለው። ይህም ከሌለው በየትኛውም አቅጣጫ ቢጓዝ የሚሄድበት የ1ብር ከ50 ሳንቲም አውቶብሶች አሉለት። የሚሸቃቅለው … ወይ ታክሲ አሊያም “ሌተስት” (አዲስ ሞዴል) ያልሆነ መኪና አለው። ሃበሻው እዚህ ውስጥ አለ። መኪና የለውም። ግን ቁጭ ብሎ ወሬ የሚሰልቅበት ቢራ መጠጫ ብር አለው። ህንዱ ሆቴል ወይም ሱቅ ከፍቶ ወይም ተከራይቶ ይሠራል። ከሀበሻ ውጪ የሚገኘው አፍሪካዊ ደግሞ በተለያዩ የ‘’ገቢና ሃብት መፍጠሪያ’’ ስራዎች ተሰማርቶ ሲሯሯጥ ማየት ትችያለሽ።

ኢዩ ትሞቃለች። ኤሲ (አየሩን መቆጣጠሪያ/ ማቀዝቀዣ) የሌለበት ቦታ የለም። ቤቱ፣ መኪናው፣ የገበያ አዳራሹ፣ ሆቴሉ፣ ኧረ ምን ቅጡ። አሁን ሙቀቱ በ40 እና 45 መካከል ነው። ተማሪዎች ዕረፍት ላይ ናቸው። የሚገርመው ቀዝቃዛው ወራትም ቢሆን በጣም ይቀዘቅዛል። በረዶ ያወርዳል ይላሉ። የአንቺ አይነት ቢጫ ጦጣ ቁምሳጥኑን ይዞ መዞር ግድ ይለዋል። እንደ ነገሩኝ ወንዶቹ በዚህ ሰዓት ኮርማ ይሆናሉ። ሴቶቹ ደግሞ ተዘጋጅተው ይጠብቃሉ። አበቦቹ ፍሬያቸውን ይሠራሉ።

 ጎዲያ፣ ይሄ ልጅ ሌላኛው ሀበሻ ነው። አራት ቀን አብሮኝ ቆይቷል። ከተማዋን አዙሮ አሳይቶኛል። ማታ ማታም በአራቱ ቀናት 8 ቢራዎች አጠጥቶኛል። አቤት ቢራ! ለካ የሰው አገር ቢራ እንዲህ ይጣፍጣል?!

 ሀበሻ ጠላ እየገለበጠ ሆዱን ሲጐሰር ኖሯል?! ጉድ እኮ ነው። አዎ – ጎዲያ ወደቻይና – ኢዩ – ከመጣ ሁለት ዓመት ሆነው። አመጣጡ ቋንቋ ሊማር ነው። በእግረ መንገድም ቢዝነስ ሊሠራ። መርካቶ ወይም ቦሌ ወይም የሆነ የአዲስ አበባ ጥግ የሚገኝ ወፍራም ነጋዴ ልጁን ወይም ወንድሙን ‘ቋንቋ’ ትምህርት ብሎ ቻይና ‘ኤክስፖርት’ ያደርጋል። ኤክስፖርት የተደረገው የቤተሰብ አባል ካንዱ የቻይና ቋንቋ ት/ቤት በወር ሁለት ሺ ብር እየከፈለ መማር ይጀምራል። ቤት በወር ሁለት ሺ ብር ይከራያል። ለወርሃዊ አስቤዛ ሁለት ሺ ብር ያወጣል። ለትራንስፖርት ሦስት መቶ ብር አካባቢ ያወጣል። እንግዲህ ጎዲያ 6300 ብር በወር ወጪ ያደርጋል። ይህን የቻይና ብር ወደ አገርኛ ምንዛሪ ስታመጪው በሦስት ማባዛት ነው። ጎዲያ በሁለት ዓመት ቆይታው የቻይናዎቹ ባህሪ በደንብ የገባው አልመሰለኝም። በፈጣኑ አለም ውስጥ ተረጋግቶ የሚኖር ልጅ ነው። ብዙም ደስተኛ አይደለም። ብዙም የተከፋ አይደለም። አሪፍ ልጅ ነው። ግን ፈዛዛም ነው። አንዳንዴ መንገድ ይጠፋበታል፤ የሚገርመው ደግሞ መንገዱን እኔ አሳየዋለሁ። ጎዲያ ከሁለት ዓመት በኋላ ራሱን የቻለ ነጋዴ መሆን ይፈልጋል። መቻሉን ግን እጠራጠራለሁ። ዳሩሳ እና ጎዲያ አይወዳደሩም።

አምስት፣

 ሃንጁ፣ ወደ ቤቴ ልመለስ ነው። ልቤ ተነስቷል። ሁሉም ነገር አስጠላኝ። ኢዩን ወደድኳት፤ ኧረ አፈቀርኳት ማለቱ ይቀልሻል። ከኢዩ በጠዋት ነበር የተነሳነው። ልቤ ከበድ አለኝ። ማልቀስም አማረኝ። ግን ግድ ነው። በሰፊው አውራ ጐዳና ላይ እየከነፍን ወደ ሃንጁ ተጓዝን።

 ሃንጁነት ትገርማለች። ታምራዊ ግንባታዎች አየሁባት። የሚጣደፍ ህዝብ። መኪናው ይጣደፋል። እግረኛው ይጣደፋል። አስፋልቱን መኪና ሞልቶ ይፈስበታል። የእግረኛውን መንገድ እንደው ሰው ሞልቶ ይፈስበታል። መታፈን ተሰማኝ። ኢዩ ትቀላለች። ሾፌራችን ወደ ሃይቁ ወሰደን። የሃንጁ ሃይቅ – የቱሪስቶች መሰባሰቢያ ነች። ሀይቁ የቻይናን ዘመናዊና ጥንታዊ የኑሮ ፍልስፍናና የአኗኗር ዘዴ የሚያሳዩ ግንባታዎችን በዙሪያው ይዟል። በሀይቁ ዙሪያ የሚከተሉትን ታያለሽ። የሚደንሱ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች፣ ጥንታዊ ተውኔት የሚያሳዩ ተዋንያን፣ ባህላዊ ሙዚቃና ድምፃውያን፣ ሰአሊዎች፣ የግጥም ምንባብና የአጫጭር ልቦለድ ትረካ አቅራቢዎች። ሀይቁ የኪነ-ጥበብ ሃይቅ ነው። ከዚያ በላይ ደግሞ የፍቅር ሀይቅ።

 የኪነ-ጥበብ ውሎ – በየቀኑ። ቱሪስት በነዚህ ክንውኖች ይዝናናል። ከደፈረ ራሱም ይሳተፋል። ግጥም ካለው ያነባል። ወይም አንዱን ትረካ ያቀርባል። ድምፁ አሪፍ ከሆነ ማንጐራጐር ይችላል። ዳንስ ካማረው መድረኩ ክፍት ነው። ይህም ከሰለቸሽ በባህላዊ ጀልባዎች ሀይቁ ላይ ፈልሰስ እያልሽ “አለምሽን” ታጣጥሚያለሽ። ከሀይቁ ጐብኚዎች ዕድሜ ክርኑን ያሳረፈባቸው ሰዎች ይበዙበታል። አውሮፓውያን ጥቂት ናቸው። አፍሪካውያን እኛ ብቻ ነበርን። ይኸውልሽ ሃይቁን አጣጥመን ስንጨርስ ቡና አማረንና ስታርባክስ ኮፊ ሀውስ ጐራ አልን። አንዷን ስኒ የሀገሬን ቡና በ99 ብር ጠጣሁ። እንዲህ ናት ህይወት። ሃንጁን ወድጃታለሁ ግን እንደ ኢዩ አላዝናናችኝም ወይም አልቀለለችኝም።

 አሁን ስሜቴም ተበላሽቷል። መፃፍ የምችል አልመሰለኝም።

 “ደህና ሁን” አለችኝ ቻይኒስቷ። አዳነች ጨብራሬ። ዝም አልኳት። ተበሳጨች። “ቶፋው ደህና ሁን” አለችኝ ደግማ።

 “ቅር ብሎኛል”

 “ከዓመታት በኋላ አገኘሁሽ። ግን ጊዜው በጣም አጠረ”

 ቻይኒስቷ አዳነች ጨብራሬ ተገርማ አየችኝ። “አብደሃል?” አይነት ነው አስተያየቷ። ይገባኛል – ለምን እንዲህ እንደምታየኝ። ሀገሬ እያለሁ ከዓመታት በፊት እንዲሁ ነው የሆነው።

“አመሰግናለሁ ግን” አልኳት በሃሳቤ አለም ውስጥ እየኳልኳት።

 “ሺሼ” አለችኝ።

 “ሞቆኝ ነበር። ተመችቶኝ ነበር።”

 “አትስጋ ገና ይሞቅሃል።”

አዳነች ጨብራሬ – ልቧ ሙሉ ነው። ትዘባርቃለች። ዘባረቀች። ሁሉም ነገር ተዘበራረቀ። እነሆ ጦጢት እዚህ ላይ ላበቃ ነው። ከቻልኩ እፅፋለሁ። ግን የምችል አይመስለኝም። ክምር የጉልበት ስራ ከፊት ለፊቴ ይጠብቀኛል።

 ኦገስት 5/2012 ሃንጁ አውሮፕላን ማረፊያ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top