የታዛ ድምፆች

2 የቤንች ተረቶች

1ይኼን ምን እንበለው

አንድ ሰው ገና ፀሐይ ሳትወጣ ማልዶ ወደ ሩቅ አገር ሲሄድ ከአንድ መፈናፈኛ ከሌለው ጣብቅ ስፍራ ወይም በር ላይ ሲደርስ አንድ ነብር ቁጭ ብሎ አገኘ። ነብሩም ሊጣላው ፈለገና ወዲያ ወዲህ እየተንጎራደደ መጥቶ ያዝኩህ ብሎ እንደገና ፊቱን ሲያዞር ሰውዬው ቶሎ ብሎ ጅራቱን ለቀም አደረገው። ጅራቱን ከያዘው በኋላ ነብሩና ሰውዬው ሲሳሳቡና ሲጓተቱ፣ ሲጓተቱ እንደቆዩ ከገላጣ ቦታ ላይ ይደርሳሉ።

 ነብሩ ሰውዬውን ለማየትአንገቱን ሲያዞር ሰውዬው ደግሞ ጅራቱን በሁለት እጁ ይዞ ሲታገሉ አንድ ሰው ከዱር ውስጥ ገብቶ እንጨት በመጥረቢያ እቀፍ፣ እቀፍ፣ እቀፍ እያደረገ ሲቆርጥ ሰማው። ወዲያው ድምፁን ከፍ አድርጎ፡- “ኧረ ነብር ሊበላኝ ነው! ኧረ የሰው ያለህ! ኧረ የጎበዝ ያለህ! ኧረ አንተ እንጨት የምትቆርጥ ሰውዬ ቶሎ ድረስልኝ” እያለ መጮኹን ቀጠለ።

 እንጨት ቆራጩም ጥሪውን እንደሰማ መጥረቢያውን ይዞ እየሮጠ መጣ። ከዚያ የነብሩንና የሰውዬውን ትግል በርቀት ቆሞ ማየት ጀመረ። ኋላም “አንተ ሰው! ምን እግዚአብሔር የፈረደብህ ሰው ነህ? ምን ስትል የዚህን ነብር ጅራት ያዝክና ትሰቃያለህ?” አለው።

ሰውዬውም “እባክህ ና! ይልቅ ና እና እኔ ጅራቱን እንደያዝኩት በያዝከው መጥረቢያ ራሱን ፍለጥልኝ! አትፍራ ይዤዋለሁ! ከእጄ አምልጦ አንተን ሊበላ አይችልም። እባክህ ና! ራሱን በለውማ!” አለው። በዚህም ጊዜ ባለመጥረቢያው፣ “አብደሃል እንዴ? ኧረ እንዲህ ዓይነት ጀብድ በአገራችን ተሠርቶ አያውቅም! የአንተ አሟሟት ሲያሳዝነኝ እንዴት እኔም ዓይኔ እያየ ወደ ሞት እጠጋለሁ?” አለውና ጥሎት ሄደ።

 ባለመጥረቢያው በዚህ ሁኔታ ሰውዬውን ጥሎት ከሄደ በኋላ በመንገዱ አንድም ሰው ቀኑን ሙሉ ዝር ሳይል ዋለ። ሰውዬውም የነብሩን ጅራት ይዞ ሲታገል እንደዋለ ሲታገል አደረ።

 በነጋታው ግን አንድ መንገደኛ መጣ። ከዚያ የነብሩን ጅራት ይዞ ሲታገል ውሎ ያደረው ሰውዬ፣ “እባክህ! አንተ የኔ ወንድም! ስለ እግዚአብሔር ብለህ ና እና ይህን ነብር በያዝከው ዱላ ራስ ራሱን ቀጥቅጥልኝ! እኔ ጅራቱን አለቀውም። አይዞህ አትፍራ – አያመልጥም፤ አይዞህ አትፍራ ናማ በያዝከው ዱላ ራስ ራሱን በለው!” ብሎ ለመነው።

 ሰውዬውም፣ “ኧረ እኔስ አላበድኩም! ነብርን ያህል ኃይለኛ ፍጡር እንዴት አድርጌ ነው ከፊቱ ቁሜ እንደወደቀ ግንድ የምመታው!

“ሰውዬውም በድርጊቱ በጣም እያዘነ የነብሩን ጅራት በመያዝ በፈንታው ለሊቱን ሲታገል አደረ። ከነጋ በኋላም በመንገዱ ሰው ይመጣል ብሎ ቢጠብቅ፣ ቢጠብቅ አንድም መንገደኛ ሳይመጣ ዋለ። ስለዚህ ከነብሩ ጋር ሲታገል ውሎ፣ እንደገና ሲታገል፣ ሲጓተት አደረ። በበነገታውም እንደዚሁ አንድም ሰው በመንገዱ ሳይመጣ ዋለ”

ሆሆ!” አለና ዝም ብሎ አልፎ ሊሄድ ካሰበ በኋላ እንደገና ዞሮ፣ “ግን ምን አደርጋለሁ? በሰው ላይ ይህን የመሰለ ፈተና ደርሶ እያየሁ እንዴት ብዬ ጥየህ እሄዳለሁ? ይህን እያየሁ እንዳላየሁ ዝም ብዬ ብሄድ ሁልጊዜ የኅሊና ወቀሳ እረፍት ይነሳኛል። ለሰውስ ይህን የመሰለ ነገር እያየሁ ዝም ብዬ መጣሁ ብዬ እንዴት ደፍሬ መናገር እችላለሁ? ትዝብት ነው። በል እኔ ጅራቱን ልያዝ፣ አንተ በዚህ በዱላ ራስ ራሱን ምታው” ብሎ መጣና ዱላውን ጥሎ የነብሩን ጅራት ያዘ።

 በዚህ ጊዜ የነብሩን ጅራት ይዞ ‹ስለእግዚአብሔር?› እያለ ሲማጠን የነበረው ሰው ያን ሰውዬ የነብሩን ጅራት አስይዞ በትሩን አንስቶ፣ “በል ወንድሜ እንግዲህ በተራህ ታገል” በማለት ጥሎት ሄደ።

ሰውዬውም በድርጊቱ በጣም እያዘነ የነብሩን ጅራት በመያዝ በፈንታው ለሊቱን ሲታገል አደረ። ከነጋ በኋላም በመንገዱ ሰው ይመጣል ብሎ ቢጠብቅ፣  ቢጠብቅ አንድም መንገደኛ ሳይመጣ ዋለ።

 ስለዚህ ከነብሩ ጋር ሲታገል ውሎ፣ እንደገና ሲታገል፣ ሲጓተት አደረ። በበነገታውም እንደዚሁ አንድም ሰው በመንገዱ ሳይመጣ ዋለ። ከዚህ በኋላ፣ “አይ! እንግዲህ ምን ማድረግ እችላለሁ። የር (እግዚአብሔር እንደማለት) ቢፈርድብኝ ነው እንጂ መች እንዲህ ካለ ካላሰብኩት ዕዳ ይጥለኝ ነበር!? አይ በቃ! ገና ስፈጠር በዚህ ልሞት የር ዕድሌን ቢቆርጠው ነው እንጂ! አይ ልጆቼ! አይ በድንገት እንደወጣሁ አኳዃኔን እንኳን ሳያዩ መሞቴ ያሳዝናል!” እያለ ሲያሰላስል ቆየ። በኋላ፣ “ኧረ ወዲያ! ይህም ዕድሜ ሆኖ፣ ይህም ከዕድሜ ተቆጥሮ እታገላለሁ!” አለና የነብሩን ጅራት ለቀቅ አደረገው። በዚህ ጊዜ ነብሩ እግሬ አውጪኝ ብሎ ዞሮ ሳያይ ሮጦ ሄደ። ሰውዬውም እንደ ነብሩ እግሬ አውጪኝ ብሎ እየሮጠ ወደ ቤቱ ሄደ ይባላል። 

2. ትዕግሥትም ትዕግሥትን ትጠይቃለች

በድሮ ዘመን ሦስት ሀብታም ወንድማማቾች ነበሩ። ከእነዚህ ወንድማማቾች መካከል ሁለቱ በሀብት ላይ ሀብት ለማግኘት፣ አንደኛው ደግሞ በሀብት ላይ ትዕግስት ለማግኘት ፈለጉና ወደ እግዚአብሔር ሄዱ። ከዚያም ከእግዚአብሔር ፊት ቀርበው ምኞታቸውን እንዲፈጽምላቸው ለመኑት። እሱም የለመኑትን ሰምቶ፣ “ተመልሳችሁ ሂዱና እንዲህ ካለ ሰፊ ሜዳ ላይ ቁጭ ብላችሁ ጠብቁ። መልዕክተኛዬ ከዚያው ከሜዳው ድረስ መጥቶ የምትፈልጉትን ሁሉ ይሰጣችኋል” ብሎ አሰናበታቸው።

ወንድማማቾቹም ተመልሰው በመሄድ እግዚአብሔር ጠብቁ ካላቸው ሜዳ ላይ ቁጭ ብለው ከአሁን አሁን ይመጣል እያሉ ቢጠብቁ፣ ቢጠብቁ ይመጣል የተባለው መልዕክተኛ የውሀ ሽታ ሆኖ ቀረ። በመጨረሻ በሀብት ላይ ሀብት እንዲሰጣቸው የለመኑት ሁለቱ ወንድማማቾች ከሜዳው ላይ ቁጭ ብለው መጠበቅ ታከታቸውና እየተነጫነጩ፣ “ኧረ ወዲያ! ምን ያለው እግዚአብሔር ነው? ዝም ብሎ ከአውላላ ሜዳ ላይ ለፀሐይና ለነፋስ ሰጥቶ በከንቱ ያስጠብቀናል! ከመጀመሪያውም ከዚህ የተቀመጥነው ሞኝነት ኖሮብን ነው እንጂ ሊሰጠን ቢፈልግ ኖሮ ከዚያው ከፊቱ እንደቆምን የጠየቃችሁትን ሰጥቻችኋለሁ ወይም ያላችሁ ሀብት ይበቃል ብሎ በመለሰን ነበር። መልዕክተኛ እልካለሁ፤ ምናምን ምን ያደርግልናል? እኛ የጠየቅነው ቢጨምርልን ብለን እንጂ ሀብት መቼ አጣን!” ብለው ተነስተው እየተናደዱ ወደ ቤታቸው ሄዱ።

“በሀብት ላይ ትዕግስትን ስጠኝ” ብሎ የጠየቀው ወንድማቸው ግን፣ “እኔ በሀብት ላይ ሀብት ስጠኝ ብዬ እግዜርን አላስቸገርኩትም። የለመንኩት በሀብት ላይ ትዕግስትን ስጠኝ ብዬ ስለሆነ ከዚሁ ቁጭ ብዬ መልዕክተኛው እስቲመጣ ድረስ እጠብቃለሁ” በማለት እነዚያ ወንድሞቹ ጥለውት ሲሄዱ እሱ ከሜዳው መሀል ቁጭ እንዳለ ሲጠብቅ ቆየ። የእግዚአብሔር መልዕክተኛም እነዚያ ወንድሞቹ ከሄዱ በኋላ ብዙ ሳይቆይ መጣ። እንደመጣም፣ “ሁለቱ ወንድሞችህስ የት ሄዱ?” ብሎ ጠየቀው።

 እሱም፣ “ሲጠብቁ፣ ሲጠብቁ ቆይተው ‹አይ! እግዚአብሔር ልመናችንን ባይሰማን ነው እንጂ መልዕክተኛው እሰከአሁን የዘገየው› ብለው ተስፋ ቆርጠው ሄዱ” ብሎ መልስ ሰጠው። መልዕክተኛውም፣ “ታዲያ አንተስ ለምን ከእነሱ ጋር አልሄድክም? ከዚህ ምን ታደርጋለህ?” ብሎ ጠየቀው።

በዚህ ጊዜ ሰውዬው፣ “እኔማ ድሮውንም በሀብት ላይ ሀብት ሳይሆን በሀብት ላይ ትዕግስትን ነበር የጠየቅኩት። ስለዚህ እግዜር የጠየቅሁትን ይፈጽምልኛል ብዬ ተስፋ በማድረግ እንደምታየኝ ቁጭ ብየ ስጠብቅ ነው የመጣህ” ብሎ መለሰለት።

 ይህን ካዳመጠ በኋላ መልዕክተኛው፣ “እግዚአብሔር በየበኩላችሁ የለመናችሁትን ለሁላችሁም ፈቅዶላችሁ ነበር። ስለዚህ ለእነሱ የፈቀደላቸውን በሀብት ላይ ሀብትና ለአንተም የፈቀደልህን በሀብት ላይ ትዕግስትን ጨምረህ ውሰድ። እነሱ የለመኑትን እስከሚቀበሉ መጠበቅ ሰላቃታቸው የእነሱንም ለአንተ ጨምሬ ሰጥቻለሁ” ብሎት ሄደ። ሰውዬውም በሀብት ላይ ሀብት ከዚያ ላይ ትዕግስትን የሚያክል ትልቅ ፀጋ ተቀብሎ በደስታ ኖረ ይባላል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top