በላ ልበልሃ

የፖለቲካ ባህላችንን ቅርጽ ለማስያዝ የቀረበ ጥሪ

በታዛ የ“በላ ልበልሃ” አምድ የሱልጣን አባዋሪ ጽሑፎች በተከታታይ መስተናገዳቸው ይታወቃል። ፅሑፎቹ ፖለቲካዊ ባህላችንን ለማረቅ የሚረዱ ነበሩ ብለን እናምናለን። ፀሓፊው በህብረተሰባችን ውስጥ የታዩ ፖለቲካዊ ተቃርኖዎችን ከአጼ ዘርአ ያዕቆብ ዘመን አንስቶ እስከ ደረስንበት ጊዜ በትንታኔ መልክ አቅርቦልናል።

 ሱልጣን አባዋሪ ፅሑፉን ሲጀምር አንድ የሆነ የጋራ ፖለቲካዊ ባህል የሚጋሩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተለያዩ የፖለቲካ ርዕዮቶችን ሊከተሉ እንደሚችሉ ያለውን እምነት አካፍሎናል። የፖለቲካ ባህል የሚባለው እሳቤ በአሜሪካዊው “ጋብርኤል አልሞንድ” ራሱን ችሎ በጥናት መቅረብ ከጀመረበት ከ1950ዎቹ (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ የዓለም ፖለቲካ ተቀያይሯል። ፖለቲካዊ ባህልን እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ህዝብ በጋራ ልንቀበለው የሚገባ ጥልቅ እሳቤ ሲሆን የፖለቲካ አመለካከትና አስተሳሰብ ግን ለተለያዩ ወገኖች የሚተው የግል መስመር መሆኑን ተገንዝበናል።

 በአንድ ሀገር ውስጥ ያለን የፖለቲካ ባህል ስንመዝን በሥራ ላይ ያለውንም የዲሞክራሲ ብቃት የምንመዝንበት መስፈርት ሆኖ ይቀርባል። ይህም በተለያዩ መንገዶች ሊገለፅ ይችላል። የፖለቲካ አካላትና አስተሳሰቦች ህብራዊ መሆን ለዚህ አንዱ ተጠቃሽ ጉዳይ ነው። የፖለቲካ ባህሉ የዳበረ ህዝብ ለመነጋገር፣ ለመከራከር የታደለ ነው። አልፎ ተርፎም ሁለንተናዊ የፖለቲካ አመለካከቱ የበሰለ ይሆናል ብለን እናስባለን። ከመገዳደልና በሾኬ ከመጠላለፍ ባለፈ በአንድ ጠረጴዛ ዙርያ ተቀምጠን እንድንከራከርና ወደ ጠቃሚና ዘላቂ መፍትሔ እንድንሸጋገር ያስችለናል።

ፖለቲካዊ ባህል ለሌሎች ማህበረሰቦች አስተሳሰቦችና ላልተጠበቁ ፖለቲካዊ ዕድገቶች ቦታ መስጠትን ይሻል። ቢጎመዝዙንም የሚጋጩ አስተሳሰቦችን ዥው አድርገን መጨለጥን የግድ ይላል። መላው ህዝባችን በሀገሪቱ ፖለቲካዊ ህይወት ውስጥ ባይተዋር ሳይሆን፤ እንደ አንድ ንቁ ዜጋ የሚሳተፍበትን ምህዳር ማዘጋጀት ይጠይቃል። የታዛ መጽሔት ዓላማም ይኸው ነው።

አሁን ሀገራችን አስፈሪ በሆነ መስቀለኛ መንገድ ላይ ቆማለች። ጥጆቹ እንደጠፉበት እረኛ ወዲያና ወዲህ ትንከራተታለች። ነፍስያዋ ይባዝናል። እኛም ልጆቿ መላው ጠፍቶን ዝናብ እንደመታው የበግ መንጋ አንገታችንን ደፍተንና በግራ መጋባት ጨለማ ወስጥ ተውጠን እንገኛለን። በፖለቲካው ኩሽና ውስጥ ምን እንደሚሠራ እንኳ በትክክል ሳናውቅ አንቀላፍተናል።

“እጅግ ወሳኝ የሆኑ ለውጦች ወይም ንቅናቄዎች የሚጀምሩት ከሥር ወደ ላይ እንጂ ከላይ ወደ ታች አይደለም። ጆኒ ኔይስቢት እንደጻፈው “በባህልም ዘርፍ ሁኔታው እንደዚያ ነው”

የትኛውን አማራጭ መከተልና ምንአይነት ውሳኔ መውሰድ እንዳለብንሳናውቅ በቀቢፀ-ተስፋ ተጀቡነንእንኳትናለን። ግን እስከመቼ? ብለንራሳችንን መጠየቅ ያለብን ዛሬ ነው።ዛሬ ካለፈ ነገ የዘገየ ይሆናል። የፖለቲካባህላችንን ሊያርቅ (ሊያስተካክል)የሚችል ተቋማዊ መዋቅር እንኳአለመፍጠራችን ነው ለዚህ የዳረገን።ፖለቲካዊ ባህል ዲሞክራሲንእንድናጎለብት የሚያደርገን ተቋማዊመዋቅር ነውና በፖለቲካ መድረኩላይ የምንታይ ወገኖች ሁሉ በድፍረትልንመክርበትና ልንዘክርበት ይገባል።

አሁን የተያያዝነው የግራ መጋባት ጉዞ የሚቀጥል ከሆነ ከዚህ ቀደም በአውሮፓ የታየው የቫይማር አደጋ (Weimar disaster) ሊከተል እንደማይችል ምንም ማረጋገጫ የለንም። የፖለቲከኞችና የብዙዎቻችን ችግር ታሪክ ጥሎልን ካለፈው ሁኔታ መማር አለመቻላችን እንደሆነ ይታመናል።

 የቫይማር ሪፐብሊክ አደጋ በታሪክ ውስጥ የተከሰተ ታላቁ ትራጀዲ እንደነበር ይታወሳል። የጀርመኑ የናዚ ፓርቲ ከአንድ አነስተኛና እዚህ ግባ ከማይባል ቡድን ወደ ቀንደኛ ብሔርተኛ ፓርቲነት የተለወጠውና ዓለምን ያናወጣት የተፈጠረውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውጥንቅጥ በመጠቀም እንደነበር ታሪክ መዝግቦታል። በታላቁ የኢኮኖሚ ድቀት (Great Depression) መከሰት ምክንያት የጀርመን ዲሞክራሲ (በ1848 ነበር የተጀመረው) በቀጥታ ወደ ናዚ አምባገነንነት እንዲያድግ መሠረት ጥሏል። በጀርመን በአንድ ወቅት የተከሰተው ሁኔታ በሌላ ሀገር አይደገምም ብሎ መገመት አይቻልም። በጀርመን የቆየው ባህላዊ ልምድ ሁለት መሠረታዊ እኩይ ፖለቲካዊ መስመሮችን ይዞ ነበር- አምባገነናዊነትንና ዘረኝነትን። የእኛም ሀገር ፖለቲካዊ ባህል ጥንታዊና ኋላቀር (Parochial) ስለሆነ በቀላሉ ሊጠለፍ እንደሚችል ማስተዋል ይኖርብናል።

 በደግም ይሁን በክፉ፣ እስቲ ኢትዮጵያውያን ነን ብለን እናስብ። ስለ ሥነ-ጥበብ፣ ስለ ስፖርት፣ ስለ ሙዚቃ፣ ስለ ኪነት፣ ስለ ቴያትር ወዘተ. በተነጋገርን ቁጥር ኢትዮጵያን የምንወዳትና የምናፈቅራት በራሳችን መንገድ ነው። ይህ የየግል ጎዳና የጋራ ህብር ይሆናልና ሊያጣላን አይገባም። እንዲያውም ይበልጥ ሊያሰባስበን ነው የሚገባው። አፈወርቅ ገብረኢየሱስ፣ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ ሀዲስ ዓለማየሁ፣ አማኑኤል አብርሃም፣ ጸጋዬ ገብረመድህን፣ በአሉ ግርማ፣ ሙላቱ አስታጥቄ፣ እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ፣ ወዘተ. ደማቸው ምን ዓይነት ነው? እኔ ሳፊ ኦሮሞ ነኝ፣ የጠራሁ አማራ ነኝ፣ ወይም እንደ ወርቅ የተኮላሁ ትግሬ ነኝ፣ ብለው ራሳቸውን አስገምተው ያውቃሉን? አያውቁም። የእነዚህን ሰዎች የአእምሮ ጭማቂዎች በኮመኮምን ቁጥር እነዚህ ሰዎች የእከሌ ወገን፣ የእኛ ወይም የእነሱ ዘር ናቸው ብለን ጠይቀን እናውቃለን ወይ? እንደ እኛ እምነት ወደዚህ ደረጃ ወርደን አናውቅም።

 መጽሔታችን በፖለቲካ ባህላችን ዙርያ የተጻፈውን የሱልጣን አባዋሪ ጽሑፍ ሲያስተናግድ ዓላማው የኢትዮጵያ የቆየ የፖለቲካ ባህል ምን እንደሚመስል አሳይቶ ክርክር ለመፍጠርና ወደ አንድ የውይይት መድረክ እንድንሰባሰብ ለማገዝ ነው። ለዚህም ነው ተከታታይ ጽሑፎችን ያስተናገድነው። ሁሉም ኢትዮጵያውያን (ኢትዮጵያውያን አይደለንም ብለው የሚያምኑትንም ቢሆን ጨምሮ) ሃሳብ እንዲገበያዩበትና የጋራ የመወያያ አጀንዳ እንዲኖራቸው ማድረግ ነው ዓላማችን።

 አሁን የደረስንበት የፖለቲካ ሁኔታ “በዝም አይነቅዝም” አባዜ የሚያስጉዘን አይደለም። ከተነጋገርንና ከተመካከርን የተሻለ ፖለቲካዊ ባህል ልናዳብር እንችላለን። ካልተነጋገርንና ከተኮራረፍን ግን ሁላችንም ተያይዘን ወደ መቀመቅ እንወርዳለን።

በኢትዮጵያዊነታቸው የማያምኑ ወገኖች ቢኖሩ እንኳ በጋራ ፖለቲካዊ ባህላችን አለማመን መብታቸው ነው። ብሔርተኛ ወገኖች የሆኑትም እንዲሁ። ሁሉም ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ይዘምር አንልም። ዳሩ ግን በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያ የጋራ ፖለቲካችን ላይ እንወያይ ነው ቁምነገሩ። ምናልባትም እነዚህ ወገኖች ኢትዮጵያ “የጋራ ነፍስ” የላትም ሊሉን ይችላሉ። የጋራ የሚያደርጋት ባህል የላትም ብለው አክ እንትፍ ሊሉንም ይችላሉ። ምንም አይደለም፤ ይከራከሩን። እኛ ግን መድረኩን እንፍጠርላቸው ነው ዋናው ጉዳይ።

 እውነቱን እንነጋገርና ለመሆኑ ኢትዮጵያ የጋራ ነፍስ የላትም? እንዴት ነው ነገሩ? እንዴት ነው ኢትዮጵያን በጋራ ነጽሮት የምንመለከተው? ለዚህ መልስ የምናገኘው በጋራ ቆመን ስንወያይ ብቻ ነው። ከኋላቀር ፖለቲካዊ ባህል ተላቀን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሲቪል- ባህል ለመዝለቅ ብቸኛው መንገድ ቁጭ ብሎ መነጋገርና መመካከር ነው። ከቆየው ወገኛና ነፍጣዊ አመለካከት ተላቀን ሰውኛ መንገድ መከተል ይኖርብናል። በሀሳብና በሀሳብ ብቻ ላይ የተመሠረተ ተቺ አርበኛ መሆን ያስፈልጋል። እንደዚያ ሲሆን ነው ሀገራችን የሁላችንንም ልብና ስሜት የምትገዛው። ከፖለቲካዊ ቀውስ ወጥተን ፖለቲካዊ ለውጥ ማምጣት የምንችለው። እስቲ ሁላችሁም ቆም ብላችሁ አንድ ጥያቄ ጠይቁ። ለመሆኑ ሲቪላዊ ፍቅርን (civic love) ለኢትዮጵያ ልናመጣ እንችላለን?

 ዛሬ የምናያቸው የአውሮፓ ሀገራት ከሁለት ምዕተ-ዓመታት በፊት እንደዛሬዎቹ የአውሮፓ ሀገራት አልነበሩም። የተበጣጠሱ፣ በፖለቲካ ልሂቃን ፍላጎት አርቴፊሻል የወሰን ክልል የተሰጣቸው ነበሩ። እነ ቢስማርክ፣ እነ ጋሪባልዲ ስማቸው የገነነው ይህን ወሰን በመጣሳቸው አልነበረምን? የትናንቷን ኢትዮጵያም ከዚህ ለይተን መመልከት የለብንም። ወደፊት ልናያት ስለምንመኛት ኢትዮጵያ ስናስብ የሰከነ፣ ሁሉንም ዜጋ “ዜጋ” ያሰኘና በምክንያታዊነት ላይ የተመሰረተ የሀገር ፍቅር ኖሮን ፖለቲካዊ ባህላችንን ስናበለጽግ ነው የምንጠነክረው።

 ወደ አውሮፓ እንመለስና ታሪኳን ስንቃኝ የምንደርስበት እውነታ አለ። እስከ ቅርቡ 1945 (እ.ኤ.አ) አውሮፓውያን በትርምስ፣ በጦርነትና በጡንቸኝነት ላይ ነበር የተመሠረቱት። ለዚህም ነው ቲምቲ ጋርተን አሽ የተሰኘ ጸሐፊ የዛሬዋን አውሮፓ ሲመዝን “በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተች ኤምፓየር” ሲል የጠራት። እኛስ ተመሳሳይ ሀገረ-መንግሥት አያስፈልገንም?

እጅግ ወሳኝ የሆኑ ለውጦች ወይም ንቅናቄዎች የሚጀምሩት ከሥር ወደ ላይ እንጂ ከላይ ወደ ታች አይደለም። ጆኒ ኔይስቢት እንደጻፈው “በባህልም ዘርፍ ሁኔታው እንደዚያ ነው። እውነተኛ የሆኑና አስፈላጊ የባህል ለውጦችም ከባለሥልጣናት ወይም ከዕውቅ ሰዎች ሳይሆን የሚጀምሩት ከተራው ሰው ነው። እያንዳንዱ ሰው ልዩነትን ለማምጣት ከፈለገ ዕርዳታውን የሚፈልጉትን በመርዳት ማሳዬት ይኖርበታል” ሲል አሳስቧል። እኛ የምንለው ልዩነትን እናምጣ ነው።

 በተለይ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች፣ ልሂቃን፣ ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች የፖለቲካ ባህላችን እንዲዳብርና እንዲጎለብት የየድርሻችሁን ትወጡ ዘንድ ታዛ ጥሪዋን ታስተላልፋለች። አስተያየቶቻችሁንና ጽሑፎቻችሁን በተከታታይ ለማስተናገድ ቋሚ አምዶቿን ክፍት አድርጋ የምትጠብቃችሁ መሆኗንም በዚህ አጋጣሚ ታበስራለች።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top