አድባራተ ጥበብ

የጃኖ መንታ መንገድ

ጃኖ ሲባል

በመድረክ የሙዚቃ ክዋኔ-ጥበብ፣ በአልበም ሆነ በስቱዲዮ የተቀረጸ ሙዚቃ፣ ሁለቱ እንስትና ሁለቱ ተባዕት ድምፃውያን በአቻነት ጎልተው ይታያሉ። በአንድ ዘፈን የቀጥታ ክወና ላይ ከድምፃዊው እኩል አጃቢ ድምፃውያኑም ሆኑ ሙዚቀኞቹ ይሳተፋሉ፣ ይወዛወዛሉ፣ ይደልቃሉ። ጊታር ተጫዋቾቹ (ቤዝ እና ሊድ)፣ ሳክስፎን ተጫዋቹ፣ ከበሮ መቺው (ድራመር)፣ ኪቦርድ (ኦርጋን) ተጫዋቹና በአድማቂነት የሚሳተፈው ተጋባዥ መሰንቆ መቺው ከተለመደው የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ የአጨዋወት ይትባህል ደመቅ ባለ መልኩ፣ የውዝዋዜ ወድምጽ የስሜት ጡዘት ላይ ወጥተው፣ ታዳሚዎችንም ወደዚያ የስሜት ከፍታ ይወስዷቸዋል፣ በኢትዮ-ሮክ የሙዚቃ ሥልት። በተጫወቱባቸው መድረኮች ሁሉ ዘፍነው ያዘፍናሉ። ጨፍረው ያስጨፍራሉ። ለህዝብ ባቀረቧቸው ሙዚቃዎች በእጅጉ ያዝናናሉ – የጃኖ ባንድ መላ አባላት።

ይህ የጃኖ ባንድ የክዋኔ ጥበብ ከፍታ ዝም ብሎ በተለምዶ (business as usual) የተፈጠረ አይደለም ይላሉ የሙዚቃ ባለሙያዎች። የጃኖ የጋራ የሙዚቃ ስኬት ውጤት በጥበብ ርዕይ- ልቀት፣ በእውቀት ብስለት፣ በብዙ ትጋትና ልምምድ፣ በዘመናዊ ሙዚቃ መሳሪያና ሳውንድ ሲስተም ድጋፍ፣ በገንዘብ አቅም፣ ብርታት፣ ጥምረትና በህዝባዊ ዜማዎች ድምቀት የተፈጠረ ነው ባይ ናቸው።

 ለዚህ የሙዚቃ ባንድ ክስተት መፈጠር ከጀርባ ያሉ ሁለት ምሰሶዎችና ሁለት ሁነኛ አጋሮች አሉ። እነዚህ ሰዎች በየበኩላቸውና በየሚናቸው ከባንዱ ምሥረታ ጋር በተያያዘ ጎላ ብለው ይጠቀሳሉ። አቶ አዲስ ገሠሠ የባንዱ መፈጠር ሃሳብ አመንጪና ሙዚቃዊ መንገዱን ተላሚ፣ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ለባንዱ ምሥረታ እውን መሆን የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ሰጪ፣ ሳሙኤል ዘነበ (ፒ.ኤች.ዲ) እና የምሩ ጫንያለው (ፒ.ኤች.ዲ) በታላቅ  አጋርነትና በተግባር ተሳታፊነት ባንዱ ህያው እንዲሆን አስተዋጽዖ አበርክተዋል።

 የጃኖ ባንድ ምሥረታ ትልመ ሃሳብ፣ “ጃኖ የኢትጵያን የሙዚቃ ጥበብ የሚያሳድግ፣ በዓለማቀፍ ደረጃ የሚያስተዋውቅ፣ ወደ ዓለማቀፉ ገበያ የሚያሸጋግር፣ የሙዚቃውን ኢንዱስትሪ ገቢ የሚያሳድግ አንድ ትልቅ ዘመናዊና ዓለማቀፋዊ ባንድ ነው” ይላል።

በውጥኑ መሠረትም የዛሬ ሰባት ዓመት የተግባር ጉዞው ተጀመረ። አቶ አዲስ ገሠሠ በዓለም ዓቀፍ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ገበያ ላይ ያላቸውን ተሞክሮ፣ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ገንዘባቸውንና የሞራል ድጋፋቸውን፣ ዶ/ር ሳሙኤል ዘነበና ዶ/ር የምሩ ጫንያለው ደግሞ የተግባር እገዛቸውን አዋህደው አንድ አጋር ቡድን (ፓርትነር) መሠረቱ። ይህም አጋር ቡድን ‹‹ትሪዮ ኢንተርቴይንመንት›› የሚል ካምፓኒ መስርቶ በሥራ አስኪያጅነት አቶ አዲስ ገሠሠን ሰየመ። በሥሩም ጃኖ ባንድን አዋቅሮ ማስተዳደር ቀጠለ።

‹‹ትሪዮ ኢንተርቴይንመንት›› በየሚጫወቱት የሙዚቃ መሣሪያ ዘርፍ ጥሩ አቅም አላቸው የተባሉ ሙዚቀኞችን ከመለመለና ‹‹ኦዲሽን›› (የሙያ ብቃት መለኪያ ፈተና) ከሰጠ በኋላ፣ በሂደት ጥሩ ድምጽ ያላቸውን ወጣት ድምፃውያን በመፈለግ፣ ጃኖ ባንድ “ሀ” ብሎ ሙዚቃዊ ትጋቱን ጀመረ። ከአንድ ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜም ቀን ከሌት በተከታታይ ልምምዱን አጧጧፈ። ከብዙ ልፋትና ጥናት በኋላም፣ ጃኖ በተመሠረተ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ፣ የመጀመሪያ አልበሙ ‹‹ኤርታሌ›› በገበያ ላይ ዋለ።

 የሙዚቃ ሥራዎቻቸውንና አልበሙን ወደ ህዝብ ያቀረቡበት መንገድ ደግሞ በጥናት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ፣ ብዙ ወጣትና ጎልማሳ አድናቂዎችንና ደጋፊዎችን በቀላሉ አፈሩ ይሉናል የባንዱ የቅርብ ሰዎች።

 በዚህ ሂደት ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ሁለቱ አጋሮች ዶ/ር ሳሙኤል ዘነበና ዶ/ር የምሩ ጫንያለው ከባንዱ ሲለቁ፣ ሌላኛው አቶ ሳሙኤል ተፈራ (የአቶ አዲስ ገሠሠ ዘመድ) ደግሞ የጃኖ ምክትል ሥራ አስኪያጅ ሆነው የባንዱን አባላት አሰባስቦና አግባብቶ በመያዝ ባንዱን ማገልገል ጀምረው ነበር። በሂደት አቶ አዲስ ገሠሠ የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ሥራ አስኪያጅነታቸውን አቁመው ሙሉ ጊዜያቸውን ወደ ‹‹ትሪዮ ኢንተርቴይመንት›› ጃኖ ባንድ አደረጉ። ሁሉም የባንዱ አባላትም በደስታና በታላቅ ተስፋ ትጋታቸውን ቀጠሉ ይሉናል ምንጮቻችን።

ኢትዮ-ሮክ

በአጭር ጊዜ ውስጥም ጃኖ ባንድ ጥበባዊ ብቃትን ማሳየት ጀመረ። በኢትዮጵያ የተለየ የሙዚቃ እንቅስቃሴም አመላከቱ ይሉናል። ለየት ካሉበት የሙዚቃ ዘዬ አንደኛው ኢትዮ-ሮክ የሙዚቃ ሥልትን ማስተዋወቃቸውና መከተላቸው ሲሆን፣ በሙዚቃ አቀራረባቸው ደግሞ (እነርሱ እንደሚሉት) ከዚህ በፊት የነበሩት ትላልቅ ባንዶች ሳይቀሩ ያስለመዱትን ፍዝ የመድረክ አቀራረብ (አብዛኞቹ ከሙዚቃው ጋር ብዙም እንቅስቃሴ አያደርጉም ነበር ይላሉ) ኃይል ባለውና እንደ ቀድሞው ሳክስፎንን ሳይሆን፣ ጊታርን ማዕከል ባደረገ አነቃቂ የቡድን መድረክ አቀራረብ መተካታቸው ነው። ለዚህም የረዳቸው ባንዱ የራሱ ድምፃውያንና ሙዚቀኞች ስላሉትና ዘወትር አንድ ላይ ለአንድ ዓላማና ግብ ስለሚተጉ ነው ይሉናል።

እንደ ምሳሌም ሮሃ ባንድ፣ ዋሊያስ ባንድና ሌሎች ትላልቅ ባንዶች ያሳኳቸውን አዎንታዊ መንገዶች አጎልብቶና ዓለማቀፋዊ ደርዝ አስይዞ ወደ ፊት በመሄድ፣ ቀደምት ባንዶች ደከም ብለውበታል ተብለው የተተቹበትን የሙዚቃ ዘርፍና ዘዬ በማጎልበትና ድምቀት በመስጠት፣ ሁሉም በአንድ ላይ የሚጎሉበትንና በአጠቃላይ ውጤቱም ዘወትር የሚታወሱና የሚወደሱ ደማቅ ዜማዎችን ለአድማጭ ማቅረብ የሚሉት ዋናዎቹ ግቦቻቸው ናቸው።

 በዚህም ሂደት ጃኖ ባንድ እንደ አንድ የሙዚቃ ቤተሰብ፣ ድምፃውያኑም ሆነ ሙዚቀኞቹ በጋራ ለጋራ አልበምና መድረክ የሚሰሩበት አንድ የሙዚቃ ማዕከል ሆነ። ስለዚህ ይህ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ አዲስ ክስተት እንደሆነ አስረግጠው የሚናገሩ አሉ።

 የሙዚቃው ቀረፃ፣ ቅንብር፣ ሚክሲንግና አሬንጅመንት በጣም በጥንቃቄና በላቀ ባለሙያ የሚሰራ ነው። የጃኖ ባንድ የራሱ ባለሙያዎች ቢኖሩትም እንኳ የተወሰኑት ሙዚቃዎች ለላቀ ጥራት ሲባል ትልቅ በሚባሉ የሳውንድ ስቱዲዮዎች ውስጥ ነው የተቀረጹት ይሉናል። እነዚህን ሥራዎች ታዋቂው የሙዚቃ አቀናባሪ ቢል ላስዌል (Bill Laswell) የእጅጋየሁ ሺባባው (ጂጂ) የቀድሞ ባለቤት በኒው ዮርክ ትልቅ ስቱዲዮ ውስጥ ነው ሚክስ ያደረገው። ይህም ከጀርባ ባሉት የጃኖ ባንድ መሥራቾችና አጋሮች ጥንካሬ የመጣ ነው ባይ ናቸው።

 ከሙዚቃ አቀራረብ ባሻገር ደግሞ፣ በእውቀትና በስልት ወጣቱ የማኅበረሰብ ክፍል ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ ባንድ ነው። በዚህም ትጋቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ያሉ የበርካታ ወጣት ተማሪዎችን አድናቆት አትርፏል።

 ሌላው ባንዱ በተጠና መልኩ ራሱን ለገበያ ማቅረቡ ነው ይሉናል። እንደሌሎች ባንዶች ገበያው እርሱን ፈልጎ እስኪመጣ ጃኖ አይጠብቅም። ገበያውን ራሱ ይፈጥረዋል። ‹‹ማርኬተብል›› ነው። ጥሩ አድርጎ ብራንድ ፈጥሮ በጥሩ ዋጋ ራሱን መሸጥ ችሏል። በዚህም በሀገር ውስጥና በውጪ አገራት በርከት ያሉ ኮንሠርቶችን ለማቅረብ የቻለበትን ዕድል ፈጥሯል። ይህም በኢትዮጵያ የሙዚቃ ባንድ ታሪክ ውስጥ ብዙም የተለመደ አይደለም በማለት ገልጸውልናል።

ጃኖ ባንድ ኢትዮ-ሮክ የሙዚቃ ሥልትን በዋናነት አስተዋውቋል። ማስተዋወቅ ብቻም ሳይሆን፣ ሮክን ከኢትዮጵያ ሙዚቃ ጋር ቀላቅሎ መስራት አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ ሽሮ በተግባር አሳይቷል። ይህ የአይቻልም አስተሳሰብ የበቀለው ዝም ብሎ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ከሮክ ጋር በጣም የተራራቀ ስለሆነ ነው። ምክንያቱም፣ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዜማዊ (ሚሎዲ)፣ ብዙ ቅላፄ ያለውና ተረጋግቶ የሚሰራ ዓይነት ሲሆን ሮክ ደግሞ በጣም ጮክ ብለህና በስሜት ጡዘት እየተንቀሳቀስክ የሚዘፈን ስለሆነ ነው። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ቅኝት ‹‹ፔንታቶኒክ›› ሲሆን የውጩ ደግሞ ‹‹ዲያቶኒክ›› ነው። በእርግጥ ቅኝቱ ‹‹ዲያቶኒክ››ም ሆኖ የሚዘፈኑ የውጭ ዘፈኖች አሉ። በአማርኛም አሁን አሁን ብዙ ‹‹ዲያቶኒክ›› ዘፈኖች አሉ። በዋናነት የቅኝቱ ነገር ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ስልት ‹‹ኢነርጂ››ና የሮክ ሙዚቃ ‹‹ኢነርጂ›› በጣም የተለያየ መሆኑ ነው ከባድ ያደረገው።

 ሆኖም፣ የጃኖ ባንድ ድምፃውያንና ሙዚቀኞች በየቀኑ አንድ ላይ ሆነው ተከታታይ ልምምድ ያደርጉ ነበር። እንደውም አራቱ ባለሙያዎች አንድ ላይ ይኖራሉ። ለተወሰነ ጊዜ የጥናቱን ሂደት ለማፋጠንና ጥሩ የሙዚቃ ጥበብ ከባቢ ለመፍጠር ታስቦ ነው አብረው መኖር የጀመሩት። ከባንዱ ምስረታ በኋላ የመጀመሪያውን ሦስት አራት ዓመት በየቀኑ ለአራትና ለአምስት ሰዓታት ያለማቋረጥ ያጠኑ ነበር ይላሉ ውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን።

ሀገራዊ ገበያው ደራ፤ ዓለማቀፍ ገበያው ራቀ!

ከመጀመሪያው የጃኖ ባንድ አልበም መውጣት በኋላ እውቅና መጣ፤ በሀገር ውስጥ ገበያው ደራ። በሃገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ የተሳኩ ኮንሰርቶችን ለማቅረብ ቻሉ። አዲስ አበባ ውስጥ በላፍቶ የገበያ ማዕከል (ሞል)፣ በትሮፒካል ጋርደን፣ በጣይቱ ሆቴል፣ እንዲሁም ለሁለት ወር ያህል በክለብ ኤች. ቱ. ኦ. በቋሚነት አቅርበዋል። በተጨማሪም በመቀሌ (አራት ጊዜ)፣ በባህርዳር፣ በሀዋሳ፣ በአዳማ፣ በጎንደርና በጅማ ከተሞች ኮንሰርት አቅርበዋል።

 ከኢትዮጵያ ውጪ ደግሞ አቶ አዲስ ገሠሠ በነበሩበት ሰዓት መጀመሪያ በአሜሪካ ኒው ዮርክ ከተማ የተወሰኑ ትላልቅ ፕሮዲዩሰሮች በተገኙበት ኮንሰርት አቅርበዋል። አቶ አዲስ ገሠሠ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሙዚቃ ዝግጅት አቅራቢዎች ጋር ትሥሥር ስለነበራቸው ነው ኮንሰርት የማቅረብ ጉዞው በአሜሪካ የተደረገው።

ሆኖም፣ አቶ አዲስ ገሠሠ የነበራቸው የሙዚቃ ትሥሥር አሁን ካለው የሙዚቃ ትውልድ ዝግጅቶች ጋር የተሠናሠለ ባለመሆኑ የታሰበውን ያህል ኮንሰርት በአሜሪካ ማቅረብ ሳይቻል ቀረ ይላሉ። እርሳቸው አብዛኛውን ጊዜያቸውን (ሃያና ሰላሳ ዓመታት) ከነቦብ ማርሌይ ቤተሰቦች፣ ከሌሎች ታዋቂ ሙዚቀኞች፣ ከዳሎል ባንድ፣ (ወንድሞቻቸው ዘለቀ እና ደረጀ ገሠሠ የነበሩበት) ከእጅጋየሁ ሺባባው (ጂጂ) እና ከባለቤቷ ጋር ነበር የሰሩት። ነገር ግን በዚህ ጉዞ ያኛው ዓይነት የሙዚቃ ገበያ በቅጡ አልነበረም። የአሁኑ የሙዚቃ ዝግጅት የማሰናዳት ትሥሥር መስመር የተለየ ነው። በዚህ ምክንያት አቶ አዲስም ሆነ የባንዱ አባላት እንደሚፈልጉት ሳይሆን ቀረ ይላሉ።

ጃኖ ባንድ ብዙ ዓለማቀፋዊ ገበያ እየሞከረ የነበረ ባንድ ነበር። ሆኖም በውጭ ያሉ የሙዚቃ ፕሮዲዩሰሮች መጀመሪያ ባንዱ በአገር ውስጥ ምን ያህል ተቀባይነት (fun base) አለው ብለው ያጠናሉ። ምክንያቱም የሀገር ውስጥ ገበያው የራሱን ሚና እንደሚወጣ ስለሚያውቁ ያንኑ ማረጋገጥ ይፈልጋሉ።

 የጃኖ ዓይነት ባንዶች በአፍሪካ ውስጥ በርካታ ናቸው። ዓለማቀፍ ፕሮዲዩሰሮች ብዙ አማራጭ ስላላቸው ገበያቸውን በጥንቃቄ አጥንተው ነው የሚገቡት። በዋናነት ትርፍን ታሳቢ የሚያደርጉ ናቸውና። ነገር ግን አገር ውስጥ ያገሩን ህዝብ ባገሩ ቋንቋ ካሸነፈ፣ ይሄ ባንድ ለዓለም አቀፍ መድረክ ብቁ ነው የሚል ፍንጭ ይሰጣቸዋል። የምትዘፍንበት ቋንቋ እና የምትከተለው የሙዚቃ ሥልትም ሚና አለው ለዓለማቀፉ ገበያ።

 ያም ሆኖ፣ ዓለማቀፍ ገበያውን ሰብሮ ለመግባት ተግዳሮት ቢገጥምም፤ በአሜሪካ በዘጠኝ ያህል ግዛቶች የሀበሻ ‹‹ዲያስፖራ››ን ማዕከል ያደረጉ ኮንሰርቶች አቅርበዋል። በአውሮፓም በስዊዘርላንድ፣ በጣልያን፣ በጀርመንና በስዊድን፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ደግሞ በእሥራኤል፣ በዱባይ፣ በአቡዳቢ፣ በባህሬን፣ በቤይሩት፣ ወዘተ ለሀበሻ የ‹‹ዲያስፖራ›› አባላት ኮንሰርት ማቅረብ ችለዋል።

ሆኖም በድምፃውያንም ሆነ በሙዚቀኞች ተስፋ ተጥሎበት የነበረው በአቶ አዲስ ገሠሠ በኩል ዓለማቀፋዊ የሙዚቃ ጉዞዎችን ማድረጉና ዓለማቀፍ ስኬቶችን መቀዳጀቱ እያደር ርቆ የተሰቀለ ተስፋ ሲሆን መቀዛቀዝ አስከትሏል። ድምፃውያኑም ሆኑ ሙዚቀኞቹ ዓይኖቻቸው ሊያሳኩ ያሰቡትን ዓላማና ግብ ከመመልከት ይልቅ፣ በባንዱ ውስጥ ባሉ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ከአንድነት ወደ ልዩነት፣ ከስምምነት ወደ አለመግባባት ማምራት ጀመሩ። በመጀመሪያ ከአመራር አባላቱ ጋር ወደ መጋጨት፣ ለጥቆም እርስ በእርስ ወደመናጨትና ወደጥቅም ግጭት ውስጥ መግባታቸውን ምንጮቻችን ያስረዳሉ። ሁኔታው በዚሁ ሲቀጥልም የባንዱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አዲስ ገሠሠ ከባንዱ ራቅ ማለትን ልማዳቸው አደረጉት ይላሉ።

የአቶ አዲስ ገለል፤ የአቶ ሳሙኤል ከፍ ማለት

የአቶ አዲስ የቀድሞ የሥራ አጋር የነበሩ ትላልቅና ዓለማቀፍ ፕሮዲዩሰሮች (ለምሳሌ የጂጂን አልበም ፕሮዲዩስ ያደረገው ክሪስ ብላክዌል) አሁን ካለው ገበያ ገለል ማለት ትጋታቸውን እያቀዘቀዘባቸው ሊሄድ ችሏል። የቢዝነስ ሰው ስለሆኑም ቀስ እያሉ ወደ ሌላ አትራፊ የቢዝነስ ዘርፍ ትኩረት ማድረግ ጀምረው የጃኖ ባንድን ሥራ በተጓዳኝ ያዙት ይሉናል።

 ከፍ ብሎ በተጠቀሱት ምክንያቶች የጃኖ ባንድ ዓለማቀፋዊ ተደማጭነት ገና ብዙ ጊዜ የሚወስድ መሆኑ ሲታወቅ፣ ከአሜሪካ ጉዞ መልስ የአቶ አዲስ ገሠሠ እንቅስቃሴ እየደከመ ሄዶ ጭራሽ ወደ ጃኖ ባንድ ብቅ ማለቱንም አቆሙ ይሉናል። ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከሚያስተዳድሯቸው ድርጅቶች ጋር በተያያዘ በተፈጠረባቸው ችግሮች ምክንያት ከሀገር ገለል ማለት፣ ወደ ሀገር ቤት ከተመለሱም በኋላ በሕግ ጥላ ሥር መሆን፣ ጃኖ ባንድ ከእርሳቸው ይገኝ የነበረው የፋይናንስና የቁሳቁስ ድጋፍ ሙሉ ለሙሉ ተቋረጠ። በዚህ የተነሳም የባንዱ አባላት የመለማመጃ ቦታና ስቱዲዮ እስከማጣት ደረሱ በማለት ያስረዳሉ።

በአቶ አዲስ ገሠሠ የዓለማቀፍ ሙዚቃ መድረክ ትሥሥር ተሞክሮ ላይ ተመስርቶ የነበረው የድምፃውያንና የሙዚቀኞች ተስፋ ወደ መክሰሙ ሲቃረብ፣ ከእርሳቸው ጋር የጥቅም ድርሻ ይገባኛል ጥያቄዎች አንስተው፣ በሰሯቸው ሥራዎች ገቢና ወጪያቸው ኦዲት እንዲደረግና ለወጪዎቹም ሠነድ እንዲቀርብ ጠየቁ። ይህም ከባንዱ መሥራች ጋር ቅራኔና ግጭት ውስጥ ከተታቸው።

 ይህ ሁኔታ ሲከሰት አብረው በአንድነት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ ስለሙዚቃ ጥበብ ሲሉ የሙዚቃ ገዳም ውስጥ የነበሩት ድምፃውያንና ሙዚቀኞች አቶ አዲስ ገሠሠን ገለል ካደረጉ በኋላ፣ በሙዚቃ ሥራ ላይ አንደኛው የሌላኛውን ሚና አሳንሶ ወደ ማየትና የራሱን ሚና ደግሞ የላቀና አይተኬ አድርጎ ወደ ማሰብ አዘነበለ። በውጤቱም እከሌ ለምን ቀረ? ምን ይሰራል? ይህስ እንዴት ይሆናል? በሚል የጀመሩት እሰጥ አገባ እያደር እየተካረረ ወደ ጥቅም ግጭት ተለወጠ። ድምፃውያንም የባንዱ የፊት-ገጽ እንደመሆናችንና ሌላ የትም ቦታና ምንም አይነት ተጓዳኝ የጥበብ ሥራ ስለማንሰራ ከሙዚቀኞች የላቀ ድርሻ ሊኖረን ይገባል የሚሉ ጥያቄዎችን አነሱ።

ጃኖ ባንድ ወደ መፍረስ ቁልቁል ሲንደረደር፣ ደርሰው በርከት ያሉ ወጪዎችን በማውጣት እንደገና ባንዱ እንዲያንሰራራ (ለቤት ኪራይ፣ ለመለማመጃ ቦታ፣ ለስቱዲዮ ግንባታና ለመሳሰሉት አስፈላጊ ወጪዎችን በማውጣት) ያደረጉት የባንዱ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል ተፈራ (የአቶ አዲስ ገሠሠ ዘመድ) ወደ ዋና ሥራ አስኪያጅነት ከፍ ብለው ባንዱን ማስተዳደር ቀጠሉ።

 ይህ ሂደት ጃኖን እንደ ባንድ ከመፍረስ ቢታደገውም ቅሉ፣ የራሱን ጫና አሳርፎ በባንዱ ምሥረታ ሂደት ላይ አቶ አዲስ ገሠሠ አላሳኩትም የተባለውን የጃኖ ባንድን የሕግ ሥያሜ (ሕጋዊ ሰውነት) በሙዚቀኞችና በድምፃውያን ሕብረት በፒ. ኤል. ሲ. ደረጃ ያወጣሉ ተብለው ሲጠበቁ፣ አቶ ሳሙኤል ተፈራ የባንዱን ፈቃድ በስማቸው አወጡትና ሁሉንም ወገን ኩም አደረጉት። ከዚህ ጊዜ በኋላም ድምፃውያን የሙዚቃ ስኬት ህልውናቸው ወርቃማ የወጣትነት ጊዜያቸውን ካሳለፉበት ከባንዱ ስያሜ (ብራንድ) ጋር በመቆራኘቱ ድጋፋቸውን ለባንዱ መሪ ለአቶ ኪሩቤል ተስፋዬ ሳይሆን ለዋና ሥራ አስኪያጁ ለአቶ ሳሙኤል ተፈራ ሰጡ። ሙዚቀኞችና ድምፃውያንም በሽማግሌ እንኳ ለመታረቅ ባለመቻላቸው በሁለት ጎራ መከፈላቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል።

 ቀጥለን ከባለሙያዎቹና ከወቅቱ የባንዱ ሥራ አስኪያጅ ጋር ወዳደረግነው ቃለመጠይቅ እናልፋለን። በዚህ አጋጣሚ አቶ አዲስ ገሠሠን ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አለመሳካቱን ለውድ አንባቢያን ለመግለጽ እንወዳለን።

“ጃኖ ሁሉም በአንድ የነበሩበት ነው”

ሙዚቀኛ ሔኖክ መሐሪ

ሙዚቀኛ ሔኖክ መሐሪ የ‹‹መሐሪ ብራዘርስ ባንድ›› አባል ሲሆን፣ የጃኖ ባንድ ባልደረቦች ውዝግብ ውስጥ በነበሩበት ጊዜ፣ ችግሩ በሠላም እንዲፈታና የባንዱ አባላት ሥራቸውን በጋራ እንዲቀጥሉ ለማስማማት ጥረት ካደረጉ የቅርብ ‹‹ሽማግሌዎች›› አንዱ ነው። በባንዱ ውስጥ ስለተፈጠሩ ነገሮች ሦስተኛ ዓይን ሆኖ የተፈጠሩ ችግሮችን ያመላክተን ዘንድ የሚከተለውን ቃለ-መጠይቅ አቅርበንለታል።”

ታዛ፡- በኢትዮጵያ የሙዚቃ ጥበብ ውስጥ የጃኖ ባንድ አበርክቶ ምንድን ነው ትላለህ?

ሔኖክ መሐሪ፡- በየሀገሩ፣ በየዘመኑ፣ የሚከሰቱ ተሰጥዖዎችና ሙዚቃዎች አሉ። ለእኔ፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ጃኖ ባንድ እንደ አንድ ትልቅ ክስተት ነው። በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ውስጥ በጣም ደስ ከሚያሰኙኝ ስብስቦች አንዱ ናቸው። ይዘውት የመጡት የሙዚቃ አቅጣጫ፣ ተፈጥሯዊ ጉልበቱ፣ በኢትዮ-ሮክ ስልት፣ አዳዲስ ‹‹ሳውንድ›› በመጠቀም፣ ይበልጡኑ የሙዚቃ መሠረቱን ጊታር ላይ ያደረገ ግን ኢትዮጵያዊ ቅኝቶችን በዘመናዊ መንገድ በብዛት የሚያቀነቅን የሮክ ሙዚቃ ሥልት ነው የሚጫወቱት።

 ብዙ ጊዜ የኢትዮጵያን ሙዚቃ አስተውለህ ከሆነ፣ የትንፋሽ መሳሪያዎችን ‹‹ብራስ›› (ሳክስፎን፣ ትራምፔት) መሠረት ያደረገ ነው። ሂደቱም ዘፋኙ ሲዘፍን፣ የ‹‹ብራስ ሴክሽን›› ይቀበላል። ልክ እንደ ጥያቄና መልስ ዓይነት አቀራረብ ነው። ምልልሱ (ዳያሎግ) በ‹‹ብራስ›› መሳሪያዎችና በዘፋኙ መሐል ነው። ለሰላሳ- አርባ ዓመት የኢትዮጵያን ሙዚቃ ‹‹ሼፕ›› ያደረገው የትንፋሽ መሳሪያዎች ‹‹ብራስ›› ነው። በተለይ ከሮሃ ባንድ ጋ የተያያዙ ሙዚቃዎችን አስተውለህ ከሆነ፣ ዘፋኙ የተወሰነ ነገር ካለ በኋላ፣ ቴነር ሳክስፎን ይገባና ሜሎዲ ይጫወታል። ይሄ ነበር የሙዚቃ ልማድ የነበረው።

 አሁን ይሄ የሙዚቃ ልማድ ወደ ጊታር ማዕከልነት ተቀይሯል። እንደሚታወቀው ሮክ ሙዚቃ መሠረቱ ጊታር፣ ቤዝና ድራም ነው። ጃኖዎች ጊታርን መሠረት አድርገው ግን የለመድነው ‹‹ሜሎዲ›› ሳይጓደልብን በአዲስ ጉልበት ሥራዎችን አቅርበዋል። እነዚህ ቀደም ሲል በትንፋሽ መሳሪያዎች የሙዚቃ መግቢያ- መውጪያ የሚሰራላቸው ሜሎዲዎች፣ ወደ ጊታር ሚሎዲዎች (ሪፎች) መጥቷል። ስለዚህ፣ ጃኖ ባንድ የሮክ ድምፅ፣ የሮክ ሳውንድ ያለው ኢትዮጵያዊ ቅኝትን በዓለማቀፍ ደረጃ ለማስደመጥ የሞከረ የወጣት ባንድ ነው።

 ትኩረት የሚያደርጉባቸው ዋና አድማጮቻቸው ወጣቶች ናቸው። ስለዚህ፣ እየዘፈኑም፣ እየጨፈሩም የሚሰሩት ሙዚቃ ለወጣቶች በሚሆን መልኩ ታስቦበትና ታቅዶበት ነው። ሙዚቃውም ይህንኑ ቡድን ይጠይቃል። ምክንያቱም ሙዚቃው የሚፈልገውን ራሱ ይጠይቅሃል። ቆመህ ተክዘህ የምትሰራው ሙዚቃ አይደለም። የሚጠይቀውን ነገር እያደረጉ፣ የመድረክ እንቅስቃሴዎችን እያደረጉ ደስ የሚል ነገር ፈጥረዋል።

ታዛ፡- ጃኖ ባንድ ከሁለት ሊከፈል የቻለው በምን ምክንያት ይመስልሃል?

 ሔኖክ፡- እኔ እንደሚገባኝ ይህ ሁኔታ በእነርሱ የተጀመረ አይደለም። ዓለም አቀፍ ሁኔታ ጭምር ነው። ምናልባት ለኛ አዲስ ሆኖብን ወይም እነሱ በጣም ‹‹ፖፑላር›› (ታዋቂ) ስለነበሩና በጣም ብዙ መሥራት በሚጠበቅባቸው ሰዓት መለያየታቸው እውን ስለሆነ ይሆናል እንጂ፣ ይሄ በሙዚቃ ሙያ የተለመደ ባህሪ ነው። በሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ አለማቀፍ ባንዶችን ካየህ ብዙዎቹ ይሄን መንገድ አልፈውበታል። ለምን መሰለህ ሙዚቃ መንፈሳዊ ስራ ነው። ተኳርፈህ የምትሰራው ስራ አይደለም። ራስህን መዋሸት የማትችልበት የጥበብ ሙያ ነው። እኔ እነሱን እንደነሱ ሁኜ እረዳቸዋለሁ። ለምን ብዙ ጠልቀን የማናውቃቸውን ነገሮች አብረው ስላሳለፉ በጉዳዩ ላይ እነርሱን ለማስማማት ሽማግሌ ብትሆንም፣ እዛ ውስጥ ድረስ ገብተህ መቆፈር አትችልም። ከውጭ ያለውንና አንተ የሚመስልህን ነው ለማስማማት የምትሞክረው። አንዳንዴ ኑሮ ራሱ ይለያይሃል፣ ቢዝነስ ያለያየሃል፣ አንዳንዴ ደግሞ እድሜ ያለያይኃል፣ የጥቅም ግጭትም ይኖራል። ስለዚህ፣ ከነዚህ ውስጥ አንዱ ነው የሆነው። ከውጭ ሆነን ስናይ እነሱ ያልገለፁዋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ግን መስማማት የማይችል ዓይነት የጥቅም ግጭት እንደሆነ ነው የገባን። ስለዚህ ምንም ማድረግ አትችልም፤ በሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ የሚጠበቅ ነው።

 ታዛ፡- ሽማግሌዎች ለማስማማት ምን ያህል ሞከራችሁ?

ሔኖክ፡– እኔ፣ ኤልያስ መልካና ሔኖክ ተመስገን እንዲሁም ሌሎችም ብዙ የሞከሩ እንዳሉ አውቃለሁ።

ታዛ፡- አሁን መጨረሻ ላይ ሙዚቀኞቹና ድምፃውያኑ ለየብቻ ነው የሆኑት?

 ሔኖክ፡- አዎ! እንደዛ ነው። ለሁለት ነው የተከፈሉት። ግን አንዳንዴ ቆፍረህ ቆፍረህ መጨረሻ ላይ ይደክምሃል እንጂ መፍትሔ አይመጣም። ለምን መፍትሔው ከእነሱ ጋር ነው ያለው። ስለዚህ ቆርጠናል ለመለያየት ካለህ አንድ ሰው ሞክረህ ሞክረህ ሞክረህ መጨረሻ ላይ በቃ ትተወዋለህ። እንደ ሽማግሌ ደግሞ መሄድ የምትችልበትን ያህል አጥር ማበጀት አለብህ። ግን እኛም እነሱም ተማምነን ነው መጨረሻ ላይ መፍትሄ ወዳሉት የተሄደው፤ እንጂ አብረው እንዲቀጥሉ በጣም ተሞክሯል። ሆኖም መጨረሻ ላይ ላለመስማማት ተስማምተዋል።

 ታዛ፡- በዕርቅ ሄደቱ ላይ የባንዱን መሥራች ባለቤቶች አካታችሁ ሞክራችሁ ነበር?

ኖክ፡- እነርሱ መጀመሪያውኑ ከባንዱ ስለራቁ ሽምግልና ውስጥ አልነበሩም። ከአቶ አዲስ ገሠሠ በኋላ ሥራ አስኪያጅ የሆነው አቶ ሳሙኤል ተፈራ ግን በሁሉም ሽምግልና ላይ ነበረ። እርሱ ከዘፋኞቹ ጋር ባለው ቡድን ውስጥ ነው ያለው። በሽምግልናው ላይ ብዙ መወራት የነበራቸው ዝርዝር ነገሮች ተነስተዋል። እንደውም ኤልያስ መልካ በጣም ብዙ ነገር ለፍቷል። ከሁላችን በላይ እሱ ጊዜ ሰጥቶ ብዙ ለፍቷል። እኔም ሁሉንም በጋራና በተናጠል ለማነጋገር ሞክሬያለሁ።

በመጨረሻ ሁሉንም የሚያግባባ በመሰለን ነገር ላይ ነው ተስማምተው እንዲለያዩ ያደረግነው። ሁሉም ሰው የሚገባውን ያገኛል። ራሳቸው ተማምነው ነው ይህን ያደረጉት፤ እኛ አይደለንም ውሳኔውን ያሳለፍነው። እንዲስማሙ ግን ግፊት አድርገናል። በእርግጥ አንተም ተው፣ አንተም ተው ብለን ከስሜታዊነት በረድ እንዲሉ ነው ያደረግነው እንጂ መፍትሄው ከራሳቸው ነው የመጣው። ችግራቸውን በሽምግልናም አትፈታውም። ምክንያቱም የባንዱ ፈቃድ መጀመሪያ የተወሰደ ነው። ምንም ማድረግ የሚችሉበት ዕድል የላቸውም። ወደየትም ልትወስደው አትችልም። ባለው ሁኔታ ላይ ግን ሁሉም የሚጠቀሙበትን ዕድል መስመር አስይዘን ነው የሸመገልናቸው።

 ታዛ፡- እንደገና የመዋሃድ ዕድልስ ያላቸው ይመስልሃል?

 ሔኖክ፡– እንግዲህ ምኞቴ ተመልሰው አንድ ላይ ሆነው እንዲሰሩ ነው። ምን ታያለህ ካልከኝ ግን ከዛ ከባለፈው ሁኔታ የተለየ አዲስ ነገር አልጠብቅም። ግን ያው ምኞቴ ሁልጊዜም አብረው ሆነው ቢሰሩ ነው።

 ታዛ፡- አሁን ጃኖ ባንድ ማን ነው? ሙዚቀኞቹ ወይስ ድምፃውያኑ?

 ሔኖክ፡- ለኔ ጃኖ ባንድ ማለት ሁሉም በአንድ ላይ፣ በስምምነት፣ በህብረት፣ የነበሩበትና የፈጠሩት ውህድ ቃና ነው። ሙዚቀኞችም፣ ድምፃውያን አንድ ላይ የነበሩት ሁሉ ጃኖ ባንድ ናቸው። አሁን ጊታሪስት በጊታሪስት ይተካል፣ ድምፃዊም በድምፃዊ ይተካል፣ በጋራ የምትፈጥረው የሙዚቃ ኬሚስትሪ ግን አይተካም። ስለዚህ አንደኛ ጃኖን ጃኖ ያደረገው ነገር አብረው ተዋህደው፣ ህብረት ፈጥረው፣ አንድ ላይ ለሰባት ዓመታት ተንከባለው የፈጠሩት የሙዚቃ ቃና (ልክ እንደ ወይን) ነው። የሙዚቃ ባንድ እንዲህ በቆይታ ነው የሚሰራው እንጂ ከዚህ ከዛ ተገጣጥሞ ባንድ አይሰራም። አንድ ላይ ለብዙ ጊዜ ስትታሽ ምርጥ ወይን በቆይታ እንደሚገኝ ሁሉ ምርጥ ባንድም ብዙ አብሮ በአንድነት በመቆየትና በመስራት የሚፈጠር ነው፤ በመለያየት ግን አይደለም።

ጃኖ የአቶ ሳሙኤል የግል ድርጅት ሆኗል”

ኪሩቤል ተስፋዬ (የጃኖ ባንድ ኪቦርድ ተጫዋችና ባንድ መሪ የነበር)

ታዛ፡- የጃኖ ባንድ መሥራቾች፣ ሙዚቀኞችና ድምፃውያን የጋራ ስምምነታችሁ ምን ነበር?

ሙዚቀኛ ኪሩቤል ተስፋዬ፡- ባለሙያውም ሆነ የሙዚቃ አድማጬ የሚረካበት አገር አቀፍና ዓለማቀፍ ትኩረት የሚስብ ባንድ መስርቶ፣ ጥሩ ጥሩ ሙዚቃ በመሥራት በዓለማቀፍ ገበያ መግባትና ከኛ በኋላ ለሚመጡት የሙዚቃ ተተኪ ትውልዶች ዓለማቀፉን የሙዚቃ መንገድ የሚያመላክት እንዲሆን ነበር ስምምነታችን። ትልቅ ነበር ህልማችን። ስንጀምርም ሆነ እስካሁንም ያቆየን ይሄ የጋራ ፍላጎታችን ነበር።

 ታዛ፡- የችግሩ ዋና ምክንያት ምንድን ነው?

 ኪሩቤል፡- አቶ አዲስ ገሠሠ በዋናነት የጃኖ ባንድ ምሥረታ ሃሳብ አመንጪ ናቸው። ሆኖም ባንዱ ላይ ምንም መዋዕለ ንዋይ አላፈሰሱም። ሁሉንም ወጪያችንን የሚችሉት አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ነበሩ። እርሳቸው በተፈጠረባቸው ችግር ከሀገር ሲወጡና በኋላም እስር ላይ ሲውሉ ግን ሁሉ ነገር ተስተጓጎለ። እናም እያንዳንዱ ወጪያችን አንድ ሥራ ሰርተን ገንዘብ ካገኘን በኋላ ‹‹ሪፈንድ›› የምናደርገው ነው የሆነው።

ታዛ፡– መጀመሪያ እንዴት ነበር?

 ኪሩቤል፡- የባንድ ምሥረታው ሂደት ጥሩ ነገሮች አሉት፤ ብዙ ከባድና መጥፎ ነገሮችም አሉት። ስለዚህ፣ በዛ ቆይታ ውስጥ እስካሁን የመጣነው የነበረንን ዓላማና ጎል በመጠበቅ ነበር። ይህንን ነገር ይዘን አንድ ቦታ እንደርሳለን በሚል ነው እንጂ፣ ለኑሮ አቋራጭ ብዙ መንገዶች ነበሩ። ሁሉም ሰው በየተናጠል ገንዘብ መስራት ይችላል። እንደገናም ደሞ የየግል ዝና የሚፈልግ ባለሙያ ሁሉ ከዚህ ውጪ ተንቀሳቅሶ አገር ውስጥ ስኬታማ መሆን የሚችል ነው።

ታዛ፡- የጃኖ ባንድ መሥራቾች፣ ሙዚቀኞች እና ድምፃውያን የተነጣጠላችሁት በምን ሁኔታ ነው?

ኪሩቤል፡- እንግዲህ የተፈጠሩት ችግሮች ብዙ ናቸው። አሁን ከአቶ አዲስ ገሠሠ ጋር የነበረን ውል የግል ኮንትራት ነበር። ሁላችንም ይሄን ያወቅነው ቆይቶ ነው። ‹‹ጃኖ›› የሚለው ሥያሜ ራሱ ከተማው ውስጥ በጣም ታዋቂ ሆኖ ገኖ ሳለ፣ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች ግን የሚታወቅ አልነበረም። እኛም በወቅቱ የዚህ እውቀቱ አልነበረንም። አቶ አዲስ ከኛ ጋር እንደ ባንድ ሳይሆን፣ እንደ ግለሰብ የኮንትራት ውል ነበር የተፈራረሙት። እሳቸው ከኛ ጋር ሁለት ውል አላቸው። አንደኛው- ለእያንዳንዳችን በግል የሥራ አስኪያጅነት ኮንትራት አላቸው። ይህ ውል በየስድስት ወሩ ይታደሳል። ሁለተኛው ኮንትራት ደግሞ የ‹‹ሪከርዲንግ›› ውል ነው። ሶስት አልበም በተከታታይ ለ‹‹ትሪዮ ኢንተርተይንመነት›› እንድናቀርብለት የሚል ነው። ይሄ ደግሞ በየሁለት ዓመቱ ይታደሳል። ሆኖም ይህን ውል አላደስንም። በሕጋዊ መልኩ ይህ ነበር በእኛ እና በአቶ አዲስ ገሠሠ መካከል የነበረው አግባብ ያልሆነ ግንኙነት።

 ታዛ፡- ከዛ ምን ተፈጠረ?

 ኪሩቤል፡- ከአቶ አዲስ ገሠሠ ጋር ተለያየን። ሆኖም ከእርሳቸው ጋር ስንለያይ የነበረውን ክፍተት ለመሙላት መጀመሪያ ጃኖ ባንድ ሕጋዊ በሆነ መስመር ውስጥ መግባት ነበረበት። ማን ምን እንደሆነ በደምብ የሚያስረዳ ሕጋዊ ማስረጃ መያዝ ነበረብን። አቶ አዲስ ገሠሠ እዚህ ነገር ላይ ምንም ፍላጎት የላቸውም። ከሦስት ዓመት በፊት ከአሜሪካ እንደ ተመለስን ጀርመን አገር ኮንሰርት ሰራን። ለአቶ አዲስ ገሠሠ ፍላጎት መዳከምና ከዚህ ሥራ እንዲሸሹ ምክንያት የሆነው የአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከመንግሥት ጋር በተፈጠረ ችግር ከሀገር መውጣት ነው። በዚህ ጊዜ ከአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ይቀርብልን የነበረው የገንዘብ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ። ሙዚቃ የምንለማመድበት ቤት እንኳ የእርሳቸው ንብረት የነበረ ቤት ነበር። ሥራ ማስኬጃ ምንም ወጪ አልነበረንም። ከዛ በኋላ ከዚያ ቤት እንድንለቅ ተደርጎ ያ ቤት ለመንግስት ተመላሽ ሆነ።

አቧሬ አካባቢ በ10 ሺህ ብር የወር ኪራይ ሌላ ቤት ተከራይተን መሥራት ጀመርን። ያኔ ነገሮች እንደ ቀድሞው መቀጠል አልቻሉም። አቶ አዲስ ገሠሠ የአቶ ኤርሚያስ አመልጋ ድጋፍ ከተቋረጠና እርሳቸውም በሌሉበት ሁኔታ፣ ቀደም ሲል የነበረውንም ወጪ በሙሉ እኛ የምናውቀውንም፣ የማናውቀውንም ሰርታችሁ ከምታገኙት ገንዘብ የምትተኩት ዕዳ ነው አሉን።

 የመጀመሪያው አልበም ውል ከነኮንሰርቱ ነበር። ስለዚህ በስፖንሰር ወደ አምስት ሚሊዮን ብር አካባቢ ነበር የተገኘው። ስፖንሰር ያደረገንም ሜታ ቢራ ነበር። የሙዚቃ ጉዞውን ራሳችን ወጪ አድርገን እንድንሰራና የነዚህንም ትርፍ ከዛም የቀረው ገንዘብ ግማሹ ኢንቨስት ተደርጎ፣ ግማሹ የቀረው በትንሹ ወደ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር አካባቢ ከኪሴ ያወጣሁት ወጪ ነው በሚል አቶ አዲስ መልሰው ወሰዱት።

 ታዛ፡- ወጪ ገቢያችሁ በትክክልና በሕጋዊ መንገድ አይታወቅም?

 ኪሩቤል፡- ምንም ዓይነት ትክክለኛ ሕጋዊ ሠነድ ሳይኖር፣ ትንንሽ ብጣሽ ወረቀቶችና የተወሰነ ማስታወሻ ወረቀት ብቻ በማቅረብ ሁለት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር ወጪ ነው አሉን። በመጨረሻም ከስፖንሰራችን ጋር የተደረገውን ውል ማየት እንፈልጋለን ስንላቸው ደግሞ ‹‹አይመለከታችሁም፤ ምክንያቱም ውሉ በእኔ (ትሪዮ ኢንተርቴይንመንት) እና በሜታ በኩል እንጂ፣ በጃኖና በሜታ በኩል ስላልሆነ አያገባችሁም›› የሚል መልስ ነበር የሰጡን። በኋላ አቶ ኤርሚያስ ሲመጡ በግል አነጋገርናቸው። ‹‹እዚህ ነገር ውስጥ የተጭበርበረ ነገር አለ አሉንና እንደገና ቁጭ አድርጌ ልዳኛችሁ›› አሉ። አቶ አዲስ ገሠሠም ባሉበት እኛም በተሟላንበት በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ አማካኝነት ቁጭ ብለን ተነጋገርን። በመጨረሻም እኔና አቶ ሳሙኤል ተፈራ (የአቶ አዲስ ገሠሠ ዘመድ) ነው የነበርነው። በባንዱ ያላቸው የስራ ድርሻም ጉዳይ አስፈፃሚ ነበሩ። የባንዱ አባላትን እርስ በርስ ለማስተባበር ደግሞ በጣም ጥሩ ጓደኛችን ነበሩ። እንግዲህ እሳቸውም አቶ አዲስ ጥሩ አለማድረጋቸውን ከእኛ ጋር ተስማምተው እኛም (ድምፃውያን፣ ሙዚቀኞችና አቶ ሳሙኤል ተፈራ) ተጭበርብረናል በሚል አንድ አቋም ያዝን።

በመጨረሻም አቶ አዲስ አባላቱን በድለዋልና ገንዘቡን መመለስ አለባቸው በሚል እኔና አቶ ሳሙኤል ጉዳዩን ለማስጨረስ በአባላት ተወክለን አነጋገርናቸው። አቶ አዲስም ‹‹ካሁን በኋላ ከባንዱ መውጣት ነው የምፈልገው፤ በራሳችሁ ተንቀሳቀሱ›› የሚል ሃሳብ አቅርበው ከባንዱ ራቁ። የባንዱ የሥራ እንቅስቃሴ ጭራሽ እየተዳከመ ሄዶ ያለ ሥራ ተቀመጥን። በዚህ ጊዜ ነው ብዙዎቹ የባንዱ አባላት (ኪቦርዲስቱ፣ ጊታሪስቱ፣ ቤዝ ጊታሪስቱ) ሁሉ የለቀቁት። በኛ በኩል ነገሮችን ለማስተካከል አቶ አዲስን በግልጽ አነጋግረን ነበር። እሳቸው ግን ‹‹እስካሁን ያለውን ነገር በሙሉ ለናንተ ትቼላችሁ እኔ ከዚህ ነገር መውጣት እፈልጋለሁ።›› የሚል ሃሳብ አቀረቡ። እኛም ትክክል ያልነበረና በአግባቡ ያልተወራረደ ገንዘባችንን ጠየቅን።

 ታዛ፡- ምን ያህል ገንዘብ ጠየቃችኋቸው?

ኪሩቤል፡- በቀጥታ ገንዘብ መጠየቅ ሳይሆን፣ ለምሳሌ ሜታ ስፖንሰር አድርጎን የመጨረሻ ክፍያውን ፈጽሞ ነበር። ግን የባንዱ አባላት ምንም አላየንም፣ ሰብሰብ ያለ የኮንሰርት ገንዘብ ነበር አላየንም፣ ብዙ ግልጽ ያልሆኑ ሂሳቦች ነበሩ፤ እሱን ነው የጠየቅነው። ሂሳብ አሰርቼ ያለውን ነገር በወረቀት አምጥቼ አስረዳችኋለሁ፣ አሁን የሂሳብ ሠራተኛዬ ስለሌለ ነው አሉ። በዚህ ነበር በሠላም የተለያየነው። ገንዘቡም ተሰልቶ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር አካባቢ ነበር።

ታዛ፡- በዚህ ወቅት በባንዱ አባላት መካከል ለሁለት የመከፈል ዝንባሌ ይታይ ነበር?

 ኪሩቤል፡- በዛን ሰዓት የባንዱ አባላት ሁሉ አንድ ነው የነበርነው። ድምፃውያንና ሙዚቀኞች የሚል ክፍፍል በጭራሽ አልነበረም።

 ታዛ፡- የሙዚቃ አባላት ከሌሎች ባንዶች እና በግልም የማቀናበር ሥራ ትሰሩ ነበር፤ ይህ በድምፃውያን በኩል ቅሬታ አልፈጠረም ትላለህ?

 ኪሩቤል፡- እኔ ወደ ጃኖ ባንድ ስቀላቀል ባንዱ አትኩሮት አድርጎ እንዲሰራ፣ ለአድማጭ/ ተመልካችም አዲስ ፊት ይዞ እንዲወጣ ሌላ ቦታ አትስሩ፤ ሌላ ቦታ ሰርታችሁ የሚከፈላችሁን ገንዘብ በደሞዝ እኛ እንስጣችሁ ይሉን ነበር አቶ አዲስ። እኔ ፈቃደኛ አልነበርኩም።  ምክኒያቱም በቋሚነት ዘመን ባንድ እሰራ ነበር፤ ባንዱን ለመልቀቅ የግድ ሌላ ሰው መተካት ነበረብኝ። በወቅቱ ጃኖ ደግሞ ገና በልምምድ ላይ ስለነበር ደንቡ አስገዳጅ አልነበረም። እናም ለአንድ ዓመት ያክል በዘመን ባንድ ተጫወትኩኝ። ድራመራችን ዮሐንስም ከበፊት ጀምሮ ሌላ ቦታ ይጫወታል። በኋላ ግን ሁላችንም አቁመናል። አቶ አዲስ ከባንዱ ወጥተውም እንኳ ሌላ ቦታ አንጫወትም ነበር። እኔ እስካሁንም የትም አልጫወትም።

 ታዛ፡- ታዲያ አቶ አዲስ ከሄዱ በኋላ ለሁለት የከፈላችሁ ምክንያት ምንድን ነው?

 ኪሩቤል፡- ከአቶ አዲስ ጋር ከተለያየን በኋላ ከምሥረታ ጋር በተያያዘ የተዛባውን ሕጋዊ ሁኔታ በፍጥነት ማስተካከል ነበረብን። በጃኖ ባንድ ፈንታ የአቶ አዲስ ድርጅት ‹‹ትሪዮ ኢንተርቴይመንት›› ነበር በሕግ የሚታወቀውና ከማንኛውም ሦስተኛ ወገን ጋር ውል የሚፈጽመው። አቶ አዲስ ከባንዱ ሲለቁ ይህን ሕጋዊ ሁኔታ አስተካክለው አይደለም የሄዱት። ስለዚህ እንደ አዲስ ፈቃድ ማውጣት ያስፈልገን ነበር፤ ባንዱን ለማስቀጠል። ይሄን ነገር እንዲያጣራልን ለአቶ ሳሙኤል ተፈራ ኃላፊነት ሰጠነው። እሱ ግን የጃኖ ባንድን ፈቃድ በሥሙ አውጥቶ መጣ። ከሥራ አስኪያጅነት ባሻገር በሕግም የጃኖ ባንድ ባለቤት ሆነ ማለት ነው። ይህን ባንድ ለመበታተን ትልቁ ምክንያት ይህ ነው። የባንዱ ባለቤትነት አሁንም የአባላቱ ሳይሆን ቀረ።

ታዛ፡- የእናንተ (ሙዚቀኞችና ድምፃውያን) ሃሳብ ምን ነበር?

ኪሩቤል፡- የኛ ሃሳብ ባንዱ ውስጥ ያለነው አባላት በሙሉ ‹‹ሼር›› ሆነን ፒ. ኤል. ሲ. በማድረግ መንቀሳቀስ ነበር። አቶ አዲስ ገሠሠ ምንም ነገር ሳያደርጉልን ነው የወጡት። በዛ ላይ ሁሉም ሰው እኩል ድርሻ እንዳለው ነው የሚታወቀው። ስንካፈልም ገንዘቡን እኩል ለዘጠኝ ነበር የምንካፈለው (አራት ድምፃውያን፣ አምስት ሙዚቀኞችና እርሳቸው)። ወጪም ስናደርግ እኩል ነበር። አቶ አዲስንም እንደ አንድ የጃኖ አባል ነበር የምንቆጥራቸው። እርሳቸውም እንደዛ ነበር የሚያስቡት።

ታዛ፡- አቶ ሳሙኤልን ለምን እንዲህ እንዳደረጉ አልጠየቃችኋቸውም?

 ኪሩቤል፡– ጠይቀነዋል። የሰጠን ምላሽ ‹‹አይ አሁን ተነስተን ፒ. ኤል. ሲ. ማድረግ ከባድ ነው። ምክንያቱም ወደ አምስት መቶ ሺህ ብር ካፒታል ይጠይቃል፤ ሌላም ሌላም በሚል ነገሮችን አወሳሰበብን። ከዛ ሁሉም አባላት አይ በቃ ስንደራጅ ወደ እኛ (ፒ. ኤል. ሲ.) እናዞረዋለን በሚል ሁኔታው ለጊዜው ተዳፈነ።

 በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆነን ባንዱን ከችግር ማውጣት ስለነበረብን ወደ ሥራ ገባን። ባንዱ እንዲነቃቃ ክለብ ኤች. ቱ.ኦ. መጫወት ጀመርን። ሁለት ‹‹ሲምፕል›› ሙዚቃዎችንና ሁለት ቪድዮ ሰራን። እንዲያውም አብዛኛው የአውሮፓ አገሮችን በዚህ በሁለተኛው ‹‹ቱር›› ነው ያዳረስነው። ከአቶ አዲስ ገሠሠ በኋላ ማለት ነው። በዚህ ውስጥ ብዙ መስዋእትነት ተከፈለ። ይህ ሁሉ የሆነው እንግዲህ ከሁለት አመት ከዘጠኝ ወር በፊት ነበር። በዛን ወቅት በራሳችን መንቀሳቀስ ጀመርን። ጥሩ ፍቅር ነበረን፣ ጥሩ መተሳሰብ ነበረብን፣ ግን ብዙም አልቀጠለም።

 ታዛ፡- ለምን?

 ኪሩቤል፡- ሒሳብ ላይ ችግሮች መፈጠር ጀመሩ። ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች መምጣት ጀመሩ። ምንም ዓይነት የሒሳብ ሪፖርት የለንም። ‹‹ኦዲት›› አይደረግም። ‹‹አካውንታንት›› የለንም። አንዳንድ ገንዘቦች ሲዝረከረኩ ሲታይ በእርስ በርስ ግንኙነታችን ላይ ‹‹ቴንሽን›› (ስጋት) ፈጠረ። እኛ ደግሞ ከአቶ አዲስ ጋር የነበረን ተሞክሮ ጥሩ ስላልነበረ አሁንም ነገሮች ጥሩ ወዳለመሆን አመሩ። እነዚህ ሁኔታዎች ያለመተማመን ስሜት መፍጠር ጀመሩ። ለምን? ይሄን ነገር በዋነኝነት አቶ ሳሙኤል ተፈራ ናቸው የሚሰሩት። እኔ የባንዱ መሪ ስለሆንኩ የአባላቱን ድምጽ ነው የማስተጋባው። ይሄም በእኔና በርሳቸው መካከል አለመግባባትና ግጭት ፈጠረ። በመሐል አቶ ሳሙኤል በዋነኝነት ሁለቱን ድምፃውያን (ዲበኩሉን እና ኃይሉን) አክብሮ በማስጠጋት፣ በማማከርና አብሮ አንዳንድ ነገሮችን በመከወን፣ ሌሎቹን አባላት ደግሞ ቸል የማለት ነገር አመጣ። ይህም አባላትን የመከፋፈያ ዘዬ ነበር። በዚህም ላይ ሌላ ከፍተኛ ችግር መጣ።

 ታዛ፡- ምን ዓይነት ችግር?

 ኪሩቤል፡- ለሁለተኛ ጊዜ አውሮፓ የሙዚቃ ጉዞ አድርገን ከመጣን በኋላ እና አልበማችንን ሪከርድ ካደረግን በኋላ ስራ አልነበረንም። ረዘም ላለ ጊዜ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ አልነበረንም። ገንዘባችን ተመናምኖ አልቋል። ጭንቀት መጣ። በዚህ የተነሳ እኛ አቶ ሳሙኤልን እንወቅሳለን። ለምን ባንክ ውስጥ ገንዘብ አልኖረንም? ይህን በቅጡ ማኔጅ ማድረግ ቢችል ኖሮ በዚህ ሰዓት አንቸገርም ነበር በሚል። በባንዱ አባላት መካከልም ኃይለኛ ችግር መጣ። በዚህ ላይ አቶ ሳሙኤል ማናጀራችን ይሆናሉ ብለን እኛ የሾምናቸው አይደሉም። ስለዚህ ሌላ የሚመጥን ማናጀር ማግኘት አለብን አልን። ስራውን በአግባቡ ማኔጅ የሚያረግ፣ በእውቀት፣ በእቅድና በካላንደር የሚሰራ ማለት ነው።

 በዚህ ላይ ከአውሮፓ ስንመጣ የመጨረሻው የጀርመን ሾው ተሰርዞብን በ24 ሰዓት ውስጥ እንድትለቁ ተብለን ነው ከአውሮፓ የወጣነው። ያ ለምን ሆነ? ቪዛችንና የቆይታ ጊዜያችን እኩል አልነበረም። ይሄን ነገር መከታተልና ማስተካከል የአቶ ሳሙኤል ድርሻ ነበረ። ትልቅ ገንዘብ የምናገኝበት ሾው እያለን በማኔጅመንት ችግር ተበላሸ። እኛም አደገኛ በሆነ ሁኔታ ተመለስን። ሌላ ጊዜ ወደ አውሮፓ እማንመለስበት አስጊ ሁኔታ ተፈጠረ። ያ ደግሞ ተስፋችን ያጨልማል።

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ድምፃውያን ደግሞ እኛን መውቀስ አመጡ። እናንተ ሌላ ቦታ ትሰራላችሁ፣ በግላችሁ ሙዚቃ ታቀናብራላችሁ፣ ስለዚህ የእኛ ህመም ሊሰማችሁ አይችልም አሉ። ይህ ጎራ የያዘ ትልቅ እሰጥ- አገባ ፈጠረ።

 ከዛ በኋላ የነበረውን ነገር ስናስተውል ሁለቱ ድምፃውያን (ዲበኩሉ እና ኃይሉ) ከአቶ ሳሙኤል ጋር አንድ ላይ የመወገን ሁኔታ አየን። ሌሎቻችን (ሁለት እንስት ድምፃውያንና አራት ሙዚቀኞች) አንድ ላይ ነው የነበርነው። አዲሱ አልበማችን እስኪወጣ ጠብቀን በባንዱ መቆየት አለመቆየታችን ላይ ውሳኔ ለማድረግ። ምክንያቱም እኛ ተጠቃሚ አልሆንም። ወይ ወደ ዓለማቀፍ ሙዚቃ ገበያ አልገባን፤ ወይ የሀገር ቤት ተጠቃሚነታችንን አላጎላን። ከኛ በኋላ የመጡ ነጠላ ዜማ የለቀቁ ዘፋኞች እንኳ መኪና ይገዛሉ፣ የሙዚቃ ‹‹ቱር›› ያደርጋሉ፣ በራሳቸው ልኬት ውጤታማ ሆነዋል። ሰው በስማቸው ይጠራቸዋል። እኛ ግን ሥማችን ጃኖ ነው፤ ሁላችንም እኩል ድርሻ ስላለን እኛ ተጎድተናል፤ ጃኖ ከፈረሰ እኛም የሙዚቃ ህይወታችን ይበላሻል የሚል ሥጋት በተለይ በድምፃውያን አካባቢ ተፈጠረ። በቃ ባንዱ ዓላማውን እንደሳተ ተረዳን። ሁኔታውን ለማስተካከል በግሌ ማኔጀራችን የነበረውን አቶ ሳሙኤልን በተደጋጋሚ አነጋግሬዋለሁ። ግን ችግሩን ከማባባስ ውጪ መፍትሄ ሊያመጣ አልቻለም።

ድምፃውያንም አልበሙ ተቀባይነቱ ከጎላ በጋራ ለመቀጠል ሆኖም እንደ በፊቱ እኩል የሆነ ድርሻ መቅረት አለበት የሚል ነበር ሃሳባቸው። በሙዚቃው ላይ እንደየድርሻችን የሚል ነገር አመጡና የድምፃውያን ድርሻ ከፍ ማለት አለበት አሉ።

 ታዛ፡- እንደ ባንድ መሪ ይህን ለማስተካከል ምን አደረግክ?

ኪሩቤል፡- የነበረውን ችግር ፈትቶ ሁሉንም ለማስማማት፣ ሁሉንም ከአቶ ሳሙኤል ጀምሮ በተናጠል አነጋግሬና ፍላጎታቸውን  በቅጡ ተረድቼ አንድ ትልቅ የጋራ የስራ መመሪያ ‹‹ፕሮፖዛል›› አቀረብኩኝ። ያ እንደ ባንድ አብሮ በልቶ፣ አብሮ ጠጥቶ፣ አብሮ ተቸግሮ፣ አብሮ ተደስቶ የሚሰራውን ነገር ለመመለስ። ያም ምንድን ነው? የስራ ክፍፍል በመፍጠር አባላት በሰሩት ልክ ያግኙ የሚል አዲስ የሥራ መንገድ ነው ያቀረብኩት። ሁሉም በደስታና በጭብጨባ ነበር የተቀበሉ።

አሁን እኔ ከሚገባኝ የሥራ ድርሻ በላይ እንደምሰራ አባላት ሁሉ ያውቃሉ። የባንዱን ሳውንዶች በሙሉ እኔ ነኝ የምቀዳው። ላይቭ ቪድዮዎች ሁሉ። ለዚህ ስራ ምንም የሚከፈለኝ ነገር የለም። ባንዱን እመራለሁ፤ አስተባብራለሁ። ሚካኤል ኃይሉ የባንዱን ሥራዎች በሙሉ ያቀናበረው እሱ ነው። ግን ለዚህ ሥራችን ክፍያ አልነበረንም።

 እንደ መፍትሄ ከዚህ በኋላ የሚመጡት ክፍያዎች በሙሉ ሁለት ቦታ ላይ እንዲከፈሉ፤ ከፊሉ የ‹‹ፐርፎርማንስ›› ሌላኛው ከፊል ደግሞ በባንዱ ውስጥ እንደ ችሎታችንና አገልግሎታችን መጠን በምንሰራው ሥራ ልክ እንዲሆን። ስለዚህ ማንም ሰው መድረክ ላይ ወጥቶ እስከ ዘፈነ ድረስ የዚያ ገንዘብ 50 በመቶ ይደርሰዋል። ለምን 50 በመቶ ደረሰው ለሚለው ደግሞ በግሉ ምን ሰራ የሚለውን ጥያቄ ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ይሄ ነበር የመጣው መፍትሄ። ሁሉም በደስታ ከተቀበሉት በኋላ በነጋታው በስልክ አንድ ሳምንት እናስብበት አሉን። ደውሎ እንዲህ ያለን ድምፃዊ ኃይሉ ነበር። ከዛ በኋላ ደግሞ እኛ ሌላ ‹‹ፕሮፖዛል›› ልናሰራ ፈልገናል አሉ፤ ለዚህ ነው አንድ ሳምንት ያሉት።

 ተገናኝተን መነጋገር ጀመርን። መግባባት አልቻልንም። አቶ ሳሙኤልም ግልጽ የሂሳብ ሪፖርት ማቅረብ አልቻለም። እነርሱም ያመጡትን ወረቀት እንኳ በቅጡ ሳይመለከቱ ነበርና በኋላ ራሳቸው ደንግጠው አፈሩበት።

 ታዛ፡- እስቲ ግልፅ አድርገው?

ኪሩቤል፡- አንድ ሳምንት ያሉት ‹‹ፔፐር›› ለማሰራት ነው ለካ። እነሱ እሚያውቋቸው ሰዎች ጋር ነበር ያሰሩት። አንድ ኤን. ጅ. ኦ. ያላቸው ሰዎች ጋ ነው ያሰሩት። እነሱ ደግሞ እዛ ወረቀት ላይ የራሳቸውን ጥቅም የሚያስከብሩ ነገሮችን ከተውበታል። የጃኖን ‹‹ማርኬቲንግ›› እና ሌሎች ነገሮች ይህ አካል (ፔፐሩን የሰሩት) ሊወስዱ ማለት ነው። ጓደኞቻችንም ሳያነቡት ነበር ያመጡት። እናም ተደናገጡ። ከሰዎቹም ጋር ተጋጩ። መጨረሻም ነባሩን የመግባቢያ ሰነድ (ፕሮፖዛል) ለማስተካል ሞከርን። የመጀመሪያው ነገር ባንዱ እንዲቀጥል ሕግን በሚመለከት የባንዱን የሕግ ባለሙያ የባንዱን ሕጋዊ ነገሮች እንዲያስፈጽምና በአባላቱ ባለቤትነት ፒ. ኤል. ሲ. እንዲሆን ነበር። ሆኖም ባንዱ በአቶ ሳሙኤል ባለቤትነት በመያዙና ለፒ. ኤል. ሲ. ለውጥ ፈቃደኛ ባለመሆኑና ሁለቱን ወንድ ድምፃውያን ከጎኑ በማድረጉ፤ በሂደትም እንስቶቹን ከኛ በመነጠሉ ሊሳካ አልቻለም። በዚህ ሁኔታ የመጨረሻ ስብሰባ አድርገን ተለያየን።

በመሐል ኮክ ስቱዲዮ ላይ እጩ ነበርንና ከማኔጀራችን ጋር ለአምስት ሰው በጀት ተይዞ ተጋበዝን። ሆኖም አቶ ሳሙኤል የጃኖ ባንድ ሙዚቀኞች ሁለቱ ወንዶች ብቻ ናቸው ሴቶቹ ተቀባዮች በመሆናቸው መሄድ የለባቸውም ብሎ ሊያስቀራቸው ሞከረ። ነገር ግን ከጋባዦቹ ጋር ተነጋግረን ካልሆነ ማንም መሄድ የለበትም የሚል አቋም ያዝን። እንደማይሆን ሲገባቸው ሁሉም ድምፃውያን እንዲሄዱ ተስማሙ። ከዚህ በኋላ እንስት ድምፃውያንን በጫና ከኛ ነጠሏቸውና ለሙዚቃ ህይወታቸው ስኬት ሲሉ የባንዱን የባለቤትነት ሕጋዊ ሥም ወደ ያዙት ወደ እነርሱ ጎራ ተሰለፉ። ድምፃውያንም ፖስተር ላይ እነርሱ ብቻ መውጣታቸውን እንደ ዝና በር ቆጠሩት። ባንዱም የአቶ ሳሙኤል ድርጅት ሆነ። አቶ ሳሙኤልም በግልጽ እኔ ለዚህ ባንድ በጣም ለፍቻለሁና ይገባኛል አለ። የፈለግኩትን ሙዚቀኛ እየቀጠርኩኝ እሰራበታለሁ። ከእናንተ ጋር መስራት አልፈልግም ብለዋል። በቃ ጃኖ የአቶ ሳሙኤል የግል ድርጅት ሆኗል።

“ባንዱን ከመበተን አትርፌያለሁ”

አቶ ሳሙኤል ተፈራ

ታዛ፡- ጃኖ ባንድን ከምሥረታው ጀምሮ በምክትል ሥራ አስኪያጅነት አገልግለዋል፤ አቶ አዲስ ገሠሠ ከባንዱ ገለል ካሉ በኋላ ደግሞ የባንዱ ሥራ አስኪያጅ ሆነዋል። በመጨረሻም አብዛኛው የባንዱ የሙዚቃ አባላት ተበትነዋል። አባላቱን በአንድ ማሰባሰብ ለምን ተሳነዎት?

 አቶ ሳሙኤል ተፈራ፡- የባንዱ ድምፃውያን ከጃኖ ውጪ የትም አይሰሩም። የሙያቸው የሥነምግባር ባህሪይም፣ የልጆቹ ባህሪይም ይሄን እንዳያደርጉ ይከለክላቸዋል። በነርሱ በኩል ምንም ችግር አልነበረም። ሙዚቀኞቹ ደግሞ ሌላ ቦታ የመስራት ዝንባሌውም ዕድሉም አላቸው። ይሄ ሁኔታ በባንዱ ውስጥ የ‹‹ኮሚትመንት›› ችግሮች አመጣ። በሙዚቀኞች በኩል ለባንዱ ሥራ ቅድሚያ ያለመስጠት ዝንባሌ ተከሰተ። ይህ ችግር ደግሞ ወደ ጥቅም ግጭት ከፍ አለ። ይህ ችግር ከአመሰራረቱ ጀምሮ የተበላሸና ልክ ያልሆነ ነገር ስለነበረው ነው።

 ታዛ፡- ምንድን ነው ልክ ያልሆነው ነገር?

 አቶ ሳሙኤል፡- እኔ ድምፃውያንና ሙዚቀኞች እኩል ክፍያ ይገባቸዋል የሚለውን ነገር አላምንበትም። ምክንያቱም በሙዚቃው ውስጥ ያላቸው አበርክቶ ስለሚለያይ ነው። በሙዚቃው ውጤት ላይም የተለያየ አስተዋፅኦና ሚና ነው ያላቸው። እና እነዚህ ነገሮች ከመጀመሪያው ከግንዛቤ መግባት ነበረባቸው። ይህ ባለመደረጉ ለግጭት አጋልጦናል።

 ታዛ፡- አቶ አዲስ ገሠሠ ከባንዱ ገለል ካሉ በኋላ፣ እርስዎ የባንዱን ፈቃድ በግል ስም ጠቅልለው እንደወሰዱት፤ ይህም ችግሩን እንዳባባሰውና ባንዱን ለሁለት እንደከፈለው ሙዚቀኞች ገልጸውልኛልና ለምን እንዲህ ሆነ?

 አቶ ሳሙኤል፡- በጣም ያሳዝናል። በዛን ወቅት ባንዱን ከመፍረስ ለመታደግ ነበር የሰራነው። ባንዱ ሊበተን ጫፍ ደርሶ ነበርና። ሊበተን ጫፍ ሲደርስ ሁላችንም የተለያዩ አቅጣጫዎችን ማየት ጀመርን። ያኔ የንግድ ፈቃድ ምናምን ዋና ቁም ነገራችን አልነበረም። ፈቃድ ስናወጣ ባንዱ በአካውንቱ ብር ኖሮትም አይደለም። በጋራ ተመካክረን፣ ከመጨነቃችን የተነሳ የባንዱን ስም ትተን ሁሉ በሌላ ለመስራትም አስበን ነበር። በዚህ ሂደት ውስጥ የሙዚቃ ባንድ የሚል ንግድ ፈቃድ ነው በኔ ስም የወጣው። ይህን ያደረግነው ባንዱን ለማትረፍ ሲባል ብቻ ነው።

 ታዛ፡- ይህ የተደረገው በሁላችሁም፡- በድምፃውያኑም፣ በሙዚቀኞችም፣ በርስዎም የጋራ ስምምነት ነው?

 አቶ ሳሙኤል፡- ሁሉም ያውቃሉ። ይህንን ነገር ደግሞ ለማድረግ ከኔ በላይ አቅሙም፣ ችሎታውም፣ ልምዱም ያላቸው ልጆች የሉም። በዚህ ነገር ላይ በየቀኑ ነበር በግልፅ የምናወራው።

 ታዛ፡- ከመጀመሪያው ፈቃዱን በእርስዎ ስም ማድረጉ ለምን አስፈለገ? በሁላችሁም ስም በጋራ ማድረግ አይቻልም ነበር?

 አቶ ሳሙኤል፡- መጀመሪያ ባንዱን ከመበተን እናትርፈውና ከዛ ወደ ፒ. ኤል. ሲ እናመጣዋለን የሚል አመለካከት ነው ያለን። ምክንያቱም በወቅቱ ፒ. ኤል. ሲ ለማድረግ ምንም አቅም አልነበረንም። የቤት ኪራይ እንኳ የምንከፍለው አልነበረንም። አይደለም የቤት ኪራይ የኪስ ገንዘብ እንኳን አልነበረንም። ባንዱ የሚላስ የሚቀመስ ገንዘብ አልነበረውም። በቃ ባንዱ ተበትኖ እኮ ነበር። ስለዚህ መጀመሪያ ባንዱን ማዳን ነው ያለብን። ከዛ የቡድን መንፈስ ማምጣት ነው። ከዛ በኋላ ነው አንተ አንድ ቦታ ላይ ቆመህ የምታስበው ወይም የአቅጣጫ እስትራቴጂ የምታወጣው እንጂ በሞተ ነገር ላይ እንዲህ ቢሆን እንዲህ ቢሆን ማለት አይቻልም። እኔ ከቤተሰቤ በማመጣው ገንዘብ ነው አንድ ላይ ቆይተው መሥራት የቻሉት። ንግድ ፈቃድ፣ ያ ሁሉ ሕጋዊ ሂደት የተጠናቀቀው እኔ ባወጣሁት ገንዘብ ነው። ባንዱን ከመበተን አትርፌዋለሁ።

 ታዛ፡– በዚህ ሳቢያ ከድምፃውያን በቀር የባንዱ ሙዚቀኞች ሁሉ ተበትነዋል?

አቶ ሳሙኤል፡- ሙዚቃ ተጫዋቾቹ ወጥተዋል። ሚካኤል ብቻ ነው ከኛ ጋር ያለው። ሌሎቹ ሶስቱ ድራመሩ፣ ኪቦርድ ተጫዋቹና ቤዝ ጊታሪስቱ ናቸው የተበተኑት። ስማቸውም ኪሩቤል ተስፋዬ፣ ዮሐንስ መኮንን፣ ዳንኤል ነጋሽ ናቸው። ሚካኤል ኃይሉ ወደ ባንዱ ተመልሶ እኛ ጋ ነው ያለው። አዲሱን አልበም በሙሉ ሙዚቃውን ያቀናበረው እሱ ነው።

 ታዛ፡– ከሙዚቀኞቹ ይልቅ ለድምፃውያን ነው ቀረቤታዎ ይባላል። እውነት ነው?

አቶ ሳሙኤል፡- የባንዱ አባላት ሁሉ አንድ ላይ በህብረት ጠንክረን አለመዝለቃችን ከኔ በላይ የሚያንገበግበው ሰው የለም። ለምን ብትለኝ እጅግ የተለፋበት የጥበብ ጉዞ ነው ያደረግነው። በሁሉም ነገር ላይ ተለፍቶበታል። እና እኔ ድምፃውያኑን አቅርቤ ሙዚቀኞቹን ገፍቼ አይደለም። ከጅምር ያልተስተካከለው ነገር ነው ነገሮችን በዚህ መንገድ ያስቀጠለው።

ጃኖ ባንድ የጥበብ ህልማችንነው፣ በፍጹም አይመክንም

ድምፃዊ ዲበኩሉ ታፈሰ

ታዛ፡- በአንተ ምልከታ የጃኖ ባንድ ምሥረታ እንዴት ነበር?

ድምፃዊ ዲበኩሉ ታፈሰ፡– ጃኖ ባንድ የተመሠረተው በአቶ ኤርሚያስ አመልጋ፣ በአቶ አዲስ ገሠሠና አቶ ሳሙኤል ተፈራ በሚባሉ ሰዎች ነው። የባንዱ ኢንቨስትመንት ላይ ትልቁን ሚና ይጫወት የነበረው አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ነበረ። ጃኖ ባንድ ብራንድ እንዲሆን በብዙ መንገድ ጠንክሮ ሰርቷል። ስለባንዱ ‹‹አይዲያ›› (ሃሳብ) ያመነጭም ነበር። አቶ ኤርሚያስ አመልጋን አሁንም ድረስ የምናከብረውና የምናደንቀው ሰው ነው።

 ኢትዮ-ሮክ የሚባለውን የሳውንድ ዘዬ እንድንጀምር አስተዋፅኦ ካደረጉ ሰዎች አንዱ ደግሞ ሙዚቀኛ አበጋዝ ክብረወርቅ ነው። ጃኖ ሲባል ምን ዓይነት ‹‹ሳውንድ›› (የሙዚቃ ስልት) ያለው ባንድ ነው? የሮክ ባንድ ነው? የሬጌ ባንድ ነው? የጃዝ ባንድ ነው? ይሄ ሳውንድ በምንድን ነው የሚለየው ብሎ የራሳችን ሳውንድ ይኖረን ዘንድ ሙያዊ ምክር ለግሶናል።

ከአቶ አዲስ ገሠሠ ጋ የተለያዩ የሙዚቃ ጉዞዎችን አድርገናል። አቶ አዲስ በማኔጅመንት ጥሩ የሆነ ብቃት ያለው ሰው ነው። ሆኖም ግን እኛ በምንሄድበት እና እሱ በሚሄድበት ‹‹ስፒድ›› (ፍጥነት) ባለመመጣጠናችን ለመለያየት በቅተናል። ምክንያቱም ይሄ ለእኛ ህይወት ነው። እድሜ ልካችን ልንኖርበት የመረጥነው ሙያ ነው። እሱ ደግሞ በተጓዳኝ ብዙ ቢዝነሶች ነበሩት። ስለዚህ ያንን እና ይሄንን ማመቻቸት አልተቻለም። እናም መጨረሻ ላይ ከሥራ አስኪያጃችን ከአቶ አዲስ ጋር ለመለያየት በቃን። ከሙዚቀኞች ውስጥም እንደዚሁ ለባንዱ ሙሉ ጊዜና አትኩሮት ለመስጠት የተቸገሩ ባለሙያዎች ነበሩና ከእነርሱም ጋር በስተመጨረሻ ለመለያየት በቅተናል። እኛ ደግሞ ጃኖ ባንድን አጥብቀን ይዘን ሙያችንን በንቃት ቀጥለናል። ጃኖ ባንድ ጉዞውን ቀጥሏል።

 ታዛ፡- ድምፃውያንና ሙዚቀኞች ለሁለት ተከፈላችሁ ማለት ነው?

ዲበኩሉ፡- ሙዚቀኛ ሚካኤል ኃይሉ ለተወሰነ ጊዜ ከእኛ ጋር አልነበረም። አሁን ግን ሁሉንም ነገር አገናዘቦ፣ የእኛ መንገድ ትክክል መሆኑ ገብቶት ወደ እኛ ተመልሷል። ስለዚህ፣ ጃኖ ባንድ ለሁለት ተከፈለ ማለት አይቻልም። ሌሎቹ ሙዚቀኞች ባንዱ ሲመሰረት ጀምሮ ከእኛ ጋር የነበሩ አይደሉም። ስለዚህ የተወሰኑ ሙዚቀኞች ለቀዋል ነው የሚባለው።

 ታዛ፡– የጃኖ ባንድ ሙዚቃዊ ቃና የተፈጠረው በነበሩት ሙዚቀኞችና በእናንተ በድምፃውያን የጥበብ ጥምረት ነው፤ አሁን እነርሱ በሌሉበት ሁኔታ ጃኖ ባንድ አለ ማለት ይቻላል?

 ዲበኩሉ፡- ከማይክል ጃክሰን ጋር ብዙ ጊታሪስቶች ተጫውተዋል። ሙዚቃዊ ቃናው ተለወጠ እንዴ!? የነበረው ሳውንድ ተቀየረ!? ዘ ዌይለርስ ባንድ ውስጥ ብዙ ጊታሪስቶች ተጫውተዋል። ቦብ ማርሊ ሲጫወት ሙዚቃዊ ቃናው ተለወጠ እንዴ!? አልተቀየረም።

በሌላም በኩል የነበረው የሙዚቀኞች ስብጥር በመጉደሉ ምክንያት የፈረሱ ብዙ ባንዶችም አሉ። ስለዚህ ያንን የምናውቀው በማድመጥና በመስማት ነው። ብዙ ሥራዎችን የሰራን ሰዎች ባንዱ ውስጥ አለን።

ታዛ፡- በባንዱ ውስጥ ችግሮች መከሰት የጀመሩት ከአቶ አዲስ ገሰሰ ገለል ማለት በኋላ ነው ወይስ ከበፊትም ጀምሮ ነው?

 ዲበኩሉ፡- ለሙዚቃ በነበረን የጋለ ፍቅር ሳቢያ፣ ሁላችንም ሙዚቃ መሥራቱ ላይ ብቻ ነበር ያተኮርነው። እና ደግሞ በጊዜው የምንሞላው ብዙ ተስፋ ነበር። ያ ደግሞ ለአንድ ጀማሪ ሙዚቀኛ ተስፋ ነው። የሚያጠነክርህም ይህ ተስፋ ነው። ይሁንና በሂደት የመሸወድም፣ የመታለልም ነገር ይመጣል። በሂደት ነገሮችን ስናስተውል አቶ አዲስ ቃል የገቡትን ብዙውን ነገር በተግባር ማሳካት ሳይችሉ ቀሩ። የእሳቸውም ‹‹ኮሚትመንት›› (ቁርጠኝነት) እየቀነሰ መጣ። ስለዚህ ከእሳቸው ጋር ተለያየን። አቶ ሳሙኤል ተፈራ (ማኔጀራችን) ትልቅ መስዋዕትነት ከፍሎ ባንዱን እንዲቀጥል አደረገ።

 ከአቶ አዲስ ገሠሠ ጋር ከተለያየን በኋላ፣ ባንዱ እንዳይፈርስ ሳሚ ብዙውን ድርሻ ተወጥቷል። ግን በዛ መሐል እያንዳንዳችን ተደጋግፈንና ተጋግዘን መሄድ በሚገባን ሰዓት ላይ በሙዚቀኞቹ በኩል የ‹‹ኮሚትመንት›› ችግር መጣ። መስዋዕትነት ለመክፈል ህይወታችንን የሰጠነው ሙያ ላይ ያለን ቁርጠኝነት እየተለያየ መጣ። ስለዚህ፣ እኔ የህይወትህን ዓላማ እንዳትፈጽም ወደ ኋላ የምጎትትህ ከሆነ፣ መለያየት አለብን። ከተወሰኑ ሰዎች ጋ የተለያየንበት ምክንያት ይህ ነው።

 ታዛ፡- በጋራ ጓደኞቻችሁ ሽምግልና መስማማት ሳትችሉ ቀራችሁ?

 ዲበኩሉ፡- ጃኖ ባንድ የጥበብ ህልማችንና ‹‹ፓሽናችን›› (ፍቅራችን) ነው። በፍጹም አይመክንም። ይህን የጃኖ ባንድ ‹‹ብራንድ›› ለመፍጠር ብዙ ለፍተናል፤ ብዙ ተቸግረናል፤ ብዙ ደክመናል፤ ለዓመታት ያለምንም ሌላ አትኩሮትና ሥራ ስንሰቃይለትና ስንሞትለት የከረምንበት ህልማችን ነው። ስለዚህ ይህ ህልማችን መክኖ እንዲቀር አንፈልግም። በብዙ ልፋትና ትጋት የተገነባ ‹‹ብራንድ›› ነው ጃኖ፤ እስካሁን አለን፤ አሁንም በዚሁ ትጋት እንቀጥላለን።

“ላለመስማማት ተስማምተናል”

ድምፃዊ ኃይሉ አመርጋ

ታዛ፡- ጃኖ ባንድ ውስጥ እንዴት ልትመለመልና ልትቀላቀል ቻልክ? ድምፃዊ ኃይሉ አመርጋ፡- ከጃኖ ባንድ ምስረታ በፊት እኔ፣ ዲበኩሉ ታፈሰ እና ሚካኤል ኃይሉ (ጊታር ተጫዋች) አንድ ባንድ ውስጥ ነበር የምንሰራው። ከሰባት ዓመት በፊት ዳግማዊ አሊ ባንድ ውስጥ የሃ ባንድ የሚባል ነበረ። እዛ በምንጫወትበት ጊዜ ነው ለጃኖ ባንድ የተመለመልነው።

 ታዛ፡- ጃኖ ባንድ ውስጥ በማኔጅመንቱ፣ በድምፃውያንና በሙዚቀኞች መካከል የነበረው የሥራ ግንኙነታችሁ ምን ይመስል ነበር?

 ኃይሉ፡- በአመሰራረቱ ላይ ትክክለኛ አካሄድ አልነበረም። ሁሉም ሰው፣ ብዙ አስተዋፅኦ ያለውም ትንሽ አስተዋፅኦ ያለውም እኩል የሚካፈልበት፣ ጥርት ያለ ሕግና ደምብ የሌለበት ነበር። ከጊዜ በኋላ ብዙ ባለሙያዎችና መዚቀኞች እየወጡ፣ በነርሱ ፋንታ ሌሎች ሙዚቀኞች እየተተኩ አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ ደርሰናል።

ታዛ፡- ምንድን ነው ትክክል ያልሆነው ነገር?

 ኃይሉ፡- የመጀመሪያው ሥራ አስኪያጃችን አቶ አዲስ ገሠሠ ይህንን (የጃኖ ባንድ) ሃሳብ ሲያመጣ፣ ሁሉም ሰው እኩል መካፈሉ በአባላት መሀል ፍቅርና መተሳሰብን ያመጣል የሚል አስተሳሰብ እንደነበረው ትዝ ይለኛል። ግን ያ ነገር በጊዜ ሂደት ትክክለኛ አካሄድ አልነበረም። ምክንያቱም ብዙ የሚለፋ፣ ብዙ የሚጥርና ብዙ አስተዋፅኦዎችን የሚያበረክት ባለሙያ እንዳለ ሁሉ፤ በጣም ትንሽ የሚባለውን አስተዋፅኦ የሚያበረክት ሙያተኛም አለ።

 ታዛ፡- የሙያው ሁኔታ ነው ይህን የፈጠረው ወይስ የግለሰብ ባህርይ?

ይሉ፡- የግለሰቦች ባህርይም፣ የሙያቸው ሁኔታም ነው ይህን የፈጠረው። የግለሰቦች ባህርይ ስልህ አንዳንድ ሰው ሙሉ ለሙሉ ትኩረቱን ለሙያው ሰጥቶ፣ ህይወቱን ሙሉ ጊዜውን ለሥራው ሰውቶ የሚሰራ አለ። አንዳንድ ሰው ደግሞ ሌሎች ሥራዎችን እየሰራ፣ ይሄን እንደተጨማሪ ስራ የሚሰራው አለ። በተለይ ድምፃውያን ጋ ስትመጣ፣ የባንዱ የፊት ገፆች እንደመሆናችን መጠን ሌላ ቦታ ሄደን መንቀሳቀስ አንችልም። ሌሎች ስራዎችንም መስራት አንችልም። ስለዚህ፣ በዚህ ባንድ ብቻ የተያዝን ነን።

በሌላ በኩል፣ የራሱን ህይወት በዋናነት የሚያስተዳድርበት ሌሎች ስራዎች ያሉትና የጃኖ ባንድን ሥራ እንደ ተጨማሪ የሚሰራ፣ ባንዱ ገቢ ሲያገኝ ደግሞ ከኛ እኩል የሚካፈል አለ። እነዚህ ነገሮች እየቀጠሉ ሲሄዱ ችግሮች እንደሚመጡ እናውቅ ነበር። ስቱዲዮ ውስጥ የሚያቀናብሩ ልጆች አሉ። ሌሎች ባንዶች ውስጥ የሚጫወቱ ሙዚቀኞች አሉ። እነሱ ገቢያቸው በሌላም በኩል አለ። እኛ ግን የባንዱ የፊት ገፆች ሆነን ሳለን፣ ሌሎች ነገሮችን ሳንሰራ እየቀረን፣ የጃኖ ባንድ ገንዘብ ሲመጣ፣ ከነዛ ሌሎች ስራዎችን እየሰሩና ሌላ ገንዘብ ከሚያገኙት ጋር እኩል እንካፈላለን። ሙሉ ጊዜያችንን ለባንዱ የሰጠን ሰዎች ከፊል ጊዜያቸውን ከሰጡ ሰዎች ጋር ነበር የምንካፈለው። ይህ አግባብ አልነበረም።

ታዛ፡- ድምፃውያን በሙዚቃው ላይ ላቅ ያለ ድርሻና አስተዋፅኦ አለን፤ ሆኖም የምናገኘው ገቢ “ከኛ ያነሰ ድርሻ” ካላቸው ሙዚቀኞች እኩል መሆኑ ጎድቶናል የሚል አመለካከት ነው ያላችሁ?

 ኃይሉ፡– አዎን! ይህ ሁኔታ በሂደት በባንዱ ውስጥ ብዙ ችግሮችን አምጥቷል። መጀመሪያ ለመቻቻል ሞክረን ነበር። እነዛ ሌሎች ስራዎችን በተጨማሪ የሚሰሩ ሰዎች፣ የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋቾችና የባንዱ አባላቶች ቅድሚያ ለባንዱ ሥራዎች እንዲሰጡና ባንዱ በሚፈልጋቸው ጊዜ መገኘት እንዳለባቸው ስንነጋገር አለመግባባቶች እየተፈጠሩ መጡ። በዚህ አለመግባባት ብዙ ሰው ከባንዱ ለቋል። እነዚህ ችግሮች ካመሰራረቱ ጀምሮ የነበሩ ናቸው፤ ተንከባለው ተንከባለው እዚህ ደረጃ የደረሱት። እነዚህን ችግሮች ለመፍታት የተደረገ እንቅስቃሴ ነበር። አንደኛው መተዳደሪያ ደምብ ያስፈልገናል የሚል ነው። ካዛ በኋላ፣ ሁሉም ሰው በሙዚቃው ላይ በሚያበረክተው አስተዋጽዖ ልክ ክፍያ እንዲያገኝ የሚያደርግ ነበር። የባንዱን ህልውና ለማስጠበቅ ነበር እርስ በርስ ተነጋግረን ይህን ሃሳብ ያመጣነው። ከዛ ይህ ሃሳብ ሲመጣ በድምፃውያንና ሙዚቀኞች መካከል ብዙ ጭቅጭቅና ክርክር አመጣ። መግባባት ሳይቻለን ቀረ። መጨረሻ ላይ ምንድን ነው መደረግ ያለበት እያልን እየተወያየን ባለንበት ሰዓት ግማሾቹ ከማናጀራችን (አቶ ሳሙኤል) ጋር በሃሳቡ ስላልተስማሙበት መውጣት ፈለጉ።

 ታዛ፡- ይቅርታ፤ እኔ ባለኝ መረጃ የባንዱ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አዲስ ገሠሠ በተለያዩ ምክንያቶች ከባንዱ ገለል ካሉ በኋላ፣ የባንዱን ህልውና ለማስቀጠል መጀመሪያ ሙዚቀኞች ‹‹ፕሮፖዛል›› ሰርተው አመጡ። ያንን ፕሮፖዛል እናንተ ሳትቀበሉት ቀራችሁ። ቀጥሎ ደግሞ እናንተ (ድምፃውያን) ‹‹ፕሮፖዛል›› ሰርታችሁ አመጣችሁ። በዚህም ላይ እነርሱ ሳይስማሙ ቀሩ። ለምን መስማማት አቃታችሁ?

 ኃይሉ፡- የጃኖ ባንዱ ፈቃድ በአቶ ሳሙኤል ተፈራ ስር ሆኖ ራሳችን ማስተዳደር ስንጀምር ነው እነርሱ ያንን ‹‹ፕሮፖዛል›› ሰርተው ያመጡት። ሁላችንም ያለን ሃሳብ የኢትዮጵያን ሙዚቃ የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስና ባለን አቅም መሠረት ሁሉም ሰው በሚገባው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆን ነበር። ከጊዜ ሂደት በኋላ ደግሞ ሁሉም ሰው እኩል አስተዋፅኦ በሚያበረክትበት ሰዓት ላይ አቶ ሳሙኤል ተፈራ ጃኖ ባንድን ወደ ፒ.ኤል.ሲ ለመቀየር ነበር ሃሳቡ። በዚህ ሂደት ላይ ሳለን እነርሱ ጃኖ ባንድ አሁኑኑ ወደ ፒ.ኤል.ሲ መቀየር አለበት የሚል ሃሳብ አመጡ።

 መጀመሪያ የባንዱ አባላት በሕግና በደምብ መተዳደር ከጀመርንና ሁሉም ሰው ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ፣ ሙሉ ኃላፊነቱን ወስዶ መስራት የሚችልበት ሁኔታ ሲፈጠር ባንዱ ወደ ፒ.ኤል.ሲ ይቀየራል በሚለው ሃሳብ እንዲስማሙ ጠየቅናቸው። ይሄን ሃሳብ ደግሞ እነርሱ ሳይቀበሉት ቀረ።

ታዛ፡- አቶ አዲስ ገሠሠ በተለያዩ ምክንያቶች ራሳቸውን ከባንዱ ማግለላቸው በባንዱ ላይ የህልውና ችግር እንደፈጠረ፣ በዚህም ወቅት ድምፃውያንም ሆናችሁ ሙዚቀኞች በአንድነት ቆማችሁ እንደነበር፣ በኋላ ግን አቶ ሳሙኤል የባንዱን ፈቃድ በራሳቸው ስም ማድረጋቸውን ተከትሎ ድምፃውያን ወደ እሳቸው መወገናችሁን በዚህም የተነሳ ለሁለት እንደተከፈላችሁ ይነገራል። ስለዚህ ምን ትላለህ?

ኃይሉ፡- ከዚያ በፊትም ጃኖ ስም እንጂ፣ ፈቃድ ደረጃ አልደረሰም። አቶ አዲስ ካቆሙ በኋላ በኛ አቅም የሚቃናም አልነበረም። መሆን የሚችለው ነገር ምንድን ነው? አቶ ሳሙኤል ተፈራ ድሮ ካመሰራረቱ ጀምሮ (ምክትል ሥራ አስኪያጅ ነበር) እኛን እየደገፈን፣ እርስ በርስ ወንድማማችነትን እንድንፈጥር፣ እንድንግባባ፣ ባህሪ ለባህሪ እንድንተዋወቅ እና የያዝነው ዓላማ ትልቅ እንደመሆኑ መጠን ትዕግስትና የዓላማ ፅናት እንዲኖረን በሃሳብም በገንዘብም በብዙ መንገድ ሲደግፈን ነው የቆየው። መጨረሻ ላይ ከአቶ አዲስ ገሠሠ ጋር አለመግባባት ውስጥ ስንገባ ያለን አማራጭ ባንዱን በራሳችን መቀጠል ነው። ባንዱን በራሳችን ለመቀጠል ስንሞክር ደግሞ በቅርባችን ያለው ታማኝ ወንድማችን አቶ ሳሙኤል ነው። እና የንግድ ፈቃዱን እንዲያወጣ፣ እያንዳንዱን ነገር እንዲጨርስ ተነጋግረንና ተግባብተን ነው የንግድ ፈቃዱን ያወጣው። የንግድ ፈቃዱን ካወጣ በኋላም ብዙ ነገሮች ሰርተናል። ሆኖም፣ የስራ አስተዋፅኦዋችን እና ሙሉ ጊዜያችን ከመስጠታችን ጋር በተያያዘ ስንነጋገር አለመግባባታችን እየጠነከረ ግጭቶች እየበረቱ መጡ። አመሰራረቱን በትክክለኛው መንገድ ለማስተካከል ስናስብ ደግሞ ግጭቱ ጎላ። የሙዚቀኞችና የድምፃውያን ጎራ ተፈጠረ። የሙዚቀኞቹ ጎራ ሁሉም ሰው እኩል ድርሻ ኖሮት ሙሉ ለሙሉ ፒ.ኤል.ሲ መሆን አለበት አሉ። እኛ ደግሞ ድርሻ የሚሰጠው እንደሚያበረክተው አስተዋፅኦና እንዳለው ‹‹ኮሚትመንት›› ታይቶ እንጂ፣ ዝም ብሎ ለማንም እኩል ድርሻ ሊሰጥ አይገባም አልን።

 አሁን ለምሳሌ ቤዚስቱ የዛሬ ሁለት ዓመት አካባቢ ነው ባንዱን የተቀላቀለው። ያበረከተውም ከሰባት ዓመታት አንፃር ስታስበው ጥቂት ነው። ኪቦርዲስታችንም ቢሆን የመጀመሪያው አልበም ላይ አልነበረም። እዚህኛው አልበም ላይም ያበረከተው አስተዋፅኦ ሁለት ዘፈኖች ላይ ነው ኪቦርድ የገባው። በርግጥ በሌሎች በሌሎች የሰራቸው ብዙ ቁም ነገሮች አሉ። ግን በአስተዋፅኦ ደረጃ ስትመጣ ብዙ ያላደረጋቸው ነገሮች ደግሞ አሉ። ድራመሩም ጋ ስትመጣ ሌሎች ባንዶች ላይ ይጫወታል። ከሌሎች ባንዶች ጋር ቪዲዮ ሁሉ እስከመስራት ደርሷል። እና ለባንዱ ሙሉ ጊዜያቸውን ከመስጠት አንፃር ያላቸው ‹‹ኮሚትመንት›› እዛ ደረጃ ላይ አያደርሰንም። እኛ (ድምፃውያን) ከባንዱ ምስረታ ጀምሮ፣ በባንዱ ሥራ ውስጥ ብቻ ያለን ሰዎች ነን።

 ስለዚህ፣ መጀመሪያ በአመሰራረቱ ላይ ሕጉንና ደምቡን ተከትሎ ነገሮች ከተስተካከሉ በኋላ፣ ሁሉም ሰው የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ታይቶ ድርሻ ተሰጥቶት ወደ “ፒ. ኤል. ሲ” (ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ) ይቀየራል በሚለው ሃሳብ አልስማማም አሉና እነርሱም በራሳቸው በኩል፣ እኛም በራሳችን በኩል ላለመስማማት ተስማምተናል።

“ሙዚቃን… ካገለገልከው… ያገለግልሃል”

ድምፃዊት ሔዋን ገብረወልድ

ታዛ፡- በሙዚቃ ህይወትሽ ጃኖ ባንድ ምን ጨመረልሽ?

 ሔዋን ገብረወልድ፡- ጃኖ ባንድ ሙዚቃን በደንብ እንዳውቅ ረድቶኛል። ሙዚቃ በጣም ከባድና ምን ያህል ልፋት፣ ምን ያህል ‹‹ኮሚትመንት›› እንደሚያስፈልገው በተግባር አውቄበታለሁ። ሙዚቃ ድምፅ ስላለህ ብቻ እንደ ቀልድ የምትይዘው አይደለም። በጣም ዋጋ የሚከፈልበት ትልቅ ሙያ እንደሆነ በተግባር በህይወቴ የተማርኩበት ባንድ ነው- ጃኖ። ይህን እኔ የተማርኩትን ሁሉ፣ ሌሎች ሙዚቀኞችም ልምዱን ቢወስዱ በጣም ደስ ይለኛል። ጃኖ ባንድ ውስጥ ለእያንዳንዱ ሙዚቃ ጥናቱ፣ ልፋቱ፣ ድካሙ የህይወት ያህል ነው። ሪከርዱ ላይ ያለው ጥንቃቄ ያስደስታል፤ የመድረክ ክዋኔው (ፐርፎርማንሱ) የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለውጦታል ብዬ አስባለሁ። በሙዚቃ ደረጃ ላይ ሁሉ ትልቅ ‹‹ስታንዳርድ›› ፈጥሯል ብዬ አስባለሁ።

 ታዛ፡- የጃኖ ባንድ ጠንካራ ጎን ምንድን ነው?

ሔዋን፡- የቡድን ሥራ፤ የጋራ ቅንጅትና የሙዚቃ ውህደት ነው ጥንካሬው። እንደ አንድ ሰው የራስህን አስተዋፅኦ ታደርጋለህ። ደግሞ ሌላውን የሙዚቃ አጋርህን ማገዝ በሚገባህ መንገድ ታግዛለህ፤ ትተጋገዛለህ፤ የጋራ ሥራ- የጋራ ስኬት ያመጣል። ታዲያ ይህን ሁሉ ስታደርግ የግል ጣጣህን ሁሉ እዛው ትተህ ነው። ማህበራዊ ህይወት ሁሉ የለህም። የሙዚቃ ገዳም በለው። በየቀኑ ትገናኛለህ፣ ትለማመዳለህ፣ አዲስ ነገር ትፈጥራለህ፣ ሪከርድ ታደርጋለህ። ሃያ አራት ሰዓት በሙዚቃ ጥበብ ላይ ነው አዕምሮህ፣ ልቦናህ፣ መንፈስህ ሁሉ። ሁልጊዜ ለሙዚቃ ክዋኔ ዝግጁ መሆን አለብህ። ሌላ

“እኔ አሁን የራሴን ብናገር ሙዚቃውን ብዬ እንጂ ጥቅም ምናምን ብትለኝ አይገባኝም”

‹‹ኮሚትመንት›› ውስጥ መግባት የለብህም። አንዳንድ የባንዱ አባላት ሌላ ህይወት ውስጥ፣ ሌላ ‹‹ኮሚትመንት›› ውስጥ ስለገቡ ይመስለኛል አሁን የተፈጠረው ችግር የተከሰተው። በዚህ ሁኔታ ጃኖ ባንድ ቢያንስ ወደ ስድስት- ሰባት አባላት የቀድሞ ሥራ አስኪያጃችንን አቶ አዲስ ገሠሠን ጨምሮ ብዙ ሰው ገለል አድርጓል። እስካሁን በዓላማ ፅናት የተወሰነ ሰው ነው ያለው።

ታዛ፡- ጃኖ ባንድ የገጠመው ችግር ምንድን ነው? በአባላት መካከል መለያየትን የፈጠረው የጥቅም ግጭት ነው ይባላል። አንቺ ምን ትያለሽ?

 ሔዋን፡– የጥቅም ግጭት ሳይሆን፣ በተወሰኑ አባላት ዘንድ የተፈጠረ የዓላማ ፅናት መጉደል ነው። አንዳንድ ሰው እስከ መጨረሻው ሙዚቃን ሊፈልግ ይችላል። አንዳንድ ሰው ደግሞ በተጓዳኝ ሌላ ነገር ሊፈልግ ይችላል። ግን እዚህ ጋ ያለን ሰዎች አምስታችን (አራት ድምፃውያን እና አንድ ሙዚቀኛ) ሙዚቃውን ፈልገን፣ ‹‹ፐርፎርማንሱን›› ፈልገን ነው ያለነው።

በሌላም በኩል ይሄ ሁኔታ በሙዚቃው ዓለም ያለ ነገር ነው። አንዳንድ ሰው የሆነ ደረጃ ሊፈልግ ይችላል፤ አንዳንድ ሰው ደግሞ ብር ሊፈልግ ይችላል፤ ሌላው ደግሞ ሌላ ነገር ሊፈልግ ይችላል። ሁሉም ሰው የየራሱ ዓላማና ግብ አለው። እኔ አሁን የራሴን ብናገር ሙዚቃውን ብዬ እንጂ ጥቅም ምናምን ብትለኝ አይገባኝም። የሙዚቃው እድገት ግን ጥቅማ ጥቅሙን ሁሉ ያመጣዋል። ስለ ጥበብ ‹‹ኳሊቲ›› (ጥራት) እጨነቃለሁ። ስለ ምርጥ የመድረክ ጥበብ አስባለሁ። አንድ ዘፈን ስሰራ እንኳ ጥራት ያለው ስቱድዮ ሄጄ በድንቅ ‹‹አሬንጅመንት›› (ቅንብር) ዘፈኑ እንዲቀዳ እፈልጋለሁ። ሚክሲንግ፣ ማስተሪንግ ሁሉ በጥሩ ሁኔታ እንዲሰራ እፈልጋለሁ። ዛሬ ሙዚቃን ከልብ ካገለገልከው፣ ነገ ሙዚቃው አንተኑ ያገለግልሃል።

በአጠቃላይ፣ ጃኖ የሚለው ስማችን ራሱ የኢትዮጵያ የክብር ልብስ ነውና፣ በክብር እየተጋን የተሻለ ሙዚቃ መስራት እንፈልጋለን። ለሙዚቃ ጥበብ ብዙ ዋጋ ከፍለናል። ወደ ፊትም ብዙ ዋጋ እንከፍላለን።

ታዛ፡- ቀጣዩ የሙዚቃ ትልማችሁ ምንድን ነው?

 ሔዋን፡- የአጭር ጊዜ ዕቅዳችን፣ በሚገባ ተዘጋጅተን የተለያዩ አገራት ላይ የሙዚቃ ዝግጅት ጉዞ ማድረግ ነው። ጋሽ ሙላቱ አስታጥቄ ኢትዮ- ጃዝ በሚል የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለዓለም ለማስተዋወቅ የተለያዩ ስራዎችን ሰርቷል። እኛ ደግሞ ኢትዮ- ሮክ በሚል በዓለም ላይ የተለያዩ ሥራዎችን መስራት እንፈልጋለን።

“ጃኖ ባንድ ጉዞውን ቀጥሏል”

ድምፃዊት ሀሌሉያ ተክለፃድቅ

ታዛ፡- ከጃኖ ባንድ በፊት በኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የነበረሽ ተሳትፎ ምን ይመስላል?

 ሀሌሉያ ተክለፃድቅ፡– ሙዚቃን የጀመርኩት ገና በልጅነቴ ነው። አጀማመሬም በመስማት፣ በማዳመጥ፣ በመውደድና በማፍቀር ደረጃ ነበር። ይበልጡኑ ቀልቤን ከሳቡ ሙዚቀኞች አንዱ ደግሞ ማይክል ጃክሰን ነበር። ከህፃንነቴ ጀምሮ ነው የማይክል ጃክሰንን ሙዚቃዎች አደምጥ የነበረው። ለሙዚቃዎቹ የሰራቸውን ‹‹ክሊፖች›› እና የመድረክ አቀራረቡንም እመለከት የነበረው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው። እሱ ነው በሙዚቃ ያነቃቃኝ ወይም ‹‹ኢንስፓየር›› ያደረገኝ ማለት እችላለሁ። በባንድ ደረጃ ግን ‹‹አኩስቲክ›› ባንድ ውስጥ እሰራ ነበር። የነበረኝ ቆይታም ወደ አንድ ዓመት ወይም ከዛ በታች ይሆናል።

 ታዛ፡- ጃኖ ባንድ ውስጥ እንዴት ልትሳተፊ ቻልሽ?

ሀሌሉያ፡- ጃኖ ባንድ በምስረታ ላይ እንደነበር ሰምቼ ነበር። በወቅቱ በቀድሞ ማኔጀራችን ተመልምዬ ነው ወደ ባንዱ የተቀላቀልኩት። እናም ጃኖ ባንድ ውስጥ ከምሥረታው ጀምሮ ነበርኩ፤ አሁንም አለሁ፤ ወደፊትም በባንዱ ውስጥ እቆያለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

 ታዛ፡- ጃኖ ባንድ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ምን የተለየ አስተዋፅኦ አድርጓል ትያለሽ?

ሀሌሉያ፡– እንደ እኔ አመለካከት ጃኖ ባንድ በመጀመሪያ ከሙዚቃው በስተጀርባ (ብዙ አድማጭና ተመልካች የማያውቀው) የኪነጥበብ ባለሙያ ወጣቶች ለአንድ ዓላማ በጋራ ተሰባስበን ለረጅም ጊዜ አብረን እየኖርን የመስራትንና የመልፋትን ፋይዳ በተግባር አሳይተናል። በዚህ የጥበብና የመዋሃድ ሂደትም አዲስ ኢትዮ-ሮክ የሚባለውን የሙዚቃ ሳውንድ ፈጥረን፣ ያን ጥበብ እየሰራን በሂደትም እያሳደግን ያለን ሙዚቀኞች ነን። ይህ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ትልቅ ፋይዳ ያለው ይመስለኛል።

 አሁን ደግሞ እንደምታየው ማኔጀራችን አቶ ሳሙኤል ተፈራ ስቱድዮ አዘጋጅቶልን በሙዚቃው ሂደት ወደፊት እየሄድን ነን። አሁን ሙዚቃን በመስራት ላይ ለሚገኙት ወጣቶችም ሆነ ከኛ ቀጥሎ ለሚመጡ ወጣቶች አብረን እንድንሰራ ነው ዓላማችን። ስቱዲዮውም የተገነባው ለዚህ አገልግሎት ነው።

 ታዛ፡- ‹‹ለራስህ ነው›› በሚል ስያሜ በቅርቡ ለአድማጭ ባቀረባችሁት አልበም ላይ የነበረሽ ተሳትፎ ምን ይመስላል?

ሀሌሉያ፡- እንደተመለከትከው አልበሙ የተለያዩ የሙዚቃ ስልቶች፣ የተለያዩ ‹‹ሪትሞች›› ተካተውበታል። በቋንቋ ደረጃም ለምሳሌ ሶማልኛ፣ ኦሮምኛና የተለያዩ የአማርኛ ቅኝቶችን ይዟል። በሙዚቃ መሳሪያም ከዘመናዊ ሙዚቃዎች ባሻገር መሰንቆ አለው፣ ክራር አለው። ኢትዮ ሮክ የሚባለውን ስልት በደንብ ገልፀን አውጥተናል ባይ ነኝ። እኔም አልበሙ ላይ በነጠላ ሶስት ስራዎች አሉኝ።

 ታዛ፡- በአንቺ ምልከታ ጃኖ ባንድን ለሁለት የከፈለው ምክንያት ምንድን ነው? ሙዚቀኞቹ ለብቻ ድምፃውያኖቹ ለብቻ የተነጣጠላችሁበት?

 ሀሌሉያ፡- በየግላችን የተለያየ ህይወት አለን። የተለያየ ፍላጎት ሊኖር ይችላል። ይህም የተለየ ዓላማን ሊከስት ይችላል። ዝርዝሩን መናገር አልፈልግም። ሆኖም ሰባት ዓመት የቆየ የሙዚቃ ቡድን ነው። ዝም ብሎ አይከስምም። አሁን ነገሮች እየተስተካከሉ ናቸው። ጃኖ ባንድ ጉዞውን ቀጥሏል። በርትተን እየሰራን ነው ያለነው። አልበማችንን በናፍቆት ሲጠብቁ ለነበሩ አድናቂዎቻችን ሁሉ የመድረክ ሥራዎችም ለማቅረብ በሂደት ላይ ነው ያለነው።

“ኢትዮ ሮክ የሚባለውን ስልት በደንብ ገልፀን አውጥተናል ባይ ነኝ”

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top