ጣዕሞት

የትውልድ አደራ ታሪካዊ መጽሐፍ በገበያ ላይ ዋለ

የልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ‹‹የትውልድ አደራ›› ታሪካዊ መጽሐፍ በሦስት ክፍል፣ በ14 ምዕራፍ እና በበርካታ ታሪካዊ ፎቶግራፎች ተሠናሥሎ በገበያ ላይ ውሏል።

‹‹የትውልድ አደራ›› የተሰኘው የልዑሉ መጽሐፍ ዓርብ መጋቢት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የሳይንስ አካዳሚ ዋና ጽ/ቤት ነበር የተመረቀው። ልዑሉ በቀጥታ በተሳተፉባቸው ታሪካዊ ኹነቶች ላይ የነበሩትን ሁኔታዎች፣ የወቅቱን ቋንቋ፣ አመለካከት፣ ወግ እና ሥነምግባር ተከትለው መጻፋቸው ተወስቷል።

 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ ‹‹መጽሐፉ የአንድ በሃያኛው መቶ ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሚኒስትርነት፣ በአውራጃና ጠቅላይ ግዛት አገረ ገዢነት የረጅም ዘመን አገልግሎት የሰጡ ሹም ግለ ታሪክ ስለሆነ፣ ትልቅ ታሪካዊ ፋይዳ ያለው ነው›› ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ኤመሪተስ ፕሮፌሰር ሺፈራው በቀለ በበኩላቸው ‹‹ይህ መጽሐፍ ለታሪክ ጥናት አስተዋጽዖ የሚያደርግ ቀዳማይ ምንጭ ነው፤ አንደኛ የመሣፍንት ልጆች አስተዳደግ ላይ ያለንን ግንዛቤ ያበለጽጋል፤ ሁለተኛ የጠቅላይ ግዛት አስተዳደርን በሚመለከት በተለይ ለሀገራችን የልማት ታሪክ ጥናት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፤ ሦስተኛ ኢድህን አስመልክቶም የልዑል ራስ መንገሻ ሥዩምን ዕይታ ያቀርባል›› ብለዋል።

 ይህን የግል ትውስታ (ግለ ታሪክ) ለመፃፍ ያነሳሳቸውን ምክንያት ‹‹በሀገራችን ታሪክን የመጻፍ አስፈላጊነትና ጠቃሚነት እየጎላ መጥቷል፤ እኔንም የሕይወቴን ታሪኬን እንድጽፍ ያነሣሣኝ ምክንያት ይኸው ነው።›› ያሉት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፣ የመጽሐፉን አበርክቶ ‹‹የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ነፃነትና አንድነት አክብረው ለማስከበር ውድ የሕይወት መሥዋዕትነት ለከፈሉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ይሁን›› ብለዋል።

 መጽሐፉ ለሕትመት የበቃው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በሥሩ ባቋቋመው የኢትዮጵያ አካዳሚ ፕሬስ ነው።

የአዳም ረታ “አፍ” (ሥግር) ልብ ወለድ በገበያ ላይ ዋ

በኢትዮጵያ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ በተለየ የአጻጻፍ ስልቱ የሚታወቀው ደራሲ አዳም ረታ፣ ከሰሞኑ አፍ (ሥግር ልብ ወለድ) የተሰኘ መጽሐፉን ለአንባቢያን አበርክቷል።

ማክሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በርከት ያሉ የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎችና አፍቃሪዎች በተገኙበት ነበር አዳም መጽሐፉን ያስመረቀው።

ደራሲ አዳም ረታ መጽሐፉንና የአፃፃፍ ስልቱን አስመልክቶ ከጋዜጠኞችና ከአንባቢዎች ለቀረቡለት ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል።

 ስለ”ሥግር” ልብ ወለድ ምንነት ማብራሪያ ሲሰጥ የጌሾ ተክልን እንደ ምሳሌ አንስቷል። ‹‹የጌሾ ተክል ቅርንጫፉ ከዋናው ክፍል ተነጥሎ ራሱን እንዲችል ማድረግ ማሥገር ይባላል። ቶማስ ኬን በመዝገበ ቃላቱ ይህን ሃሳብ (to transmit, to transfer, to crossover) ሄደ፣ አለፈ፣ ተራመደ፣ ተሻገረ ይለዋል። በዚህ ፍች የመሻገር ጽንሰ ሀሳብ በውስጠ ታዋቂነት አለው።

 ይህን ጽንሰ ሃሳብ የፍልስፍና መሠረት ሰጥቶ የሚገልጽ ቃል ስፈልግ ‹‹ራይዞም›› የሚል ቃል አጋጠመኝ። የአማርኛ ቃል ትርጉም ስፈልግለት አንድ ጓደኛዬ አባቱን ጠይቆ ‹‹ሥግር›› የሚል ቃል ይዞልኝ መጣ።

ይህ ቃል በአጋጣሚ ሲፈጠር ጽንሰ ሃሳባዊ መሠረት ለመስጠት እየሞከርኩኝ በአጋጣሚ የተገራ የአፃፃፍ ስልት አገኘሁ። ስለዚህ ሥግር ልብ ወለድ የሚያስፈልገው፡- ማንኛውም ልብ ወለድ ሥግር ልብ ወለድ ስለሆነ፣ ወደ ኋላ በመመለስ አጀማመሩን ማስተካከል እና ማሳየት ስለሚችል፣ ይህም ልብ ወለድ ራሱን ሥግር ከደራሲው ኢጎ መታገሉ።

ይህ ሥግር ልብ ወለድ ታሪኩ ሲሰራ መጀመሪያ የሥነጽሑፍ መርበብት ተስፋውም የመርበብቱ መስፋት እና መርቀቅ ነው። በዚህም የሀገሪቱ የሥነ-ጽሑፍ መልክአ ምድር ተለዋዋጭ የንባብ እና የሂስ ባህል አንድ ነገር መፍጠር ነው። በአጠቃላይ ሥግር ልብ ወለድ ይህ ነው።›› ብሏል- ደራሲ አዳም ረታ።

በዚህ የአፃፃፍ ዘዬ የደራሲው አንደኛው መጽሐፍ ከሌላው መጽሐፍ ጋር በጉዳይ፣ በታሪክ፣ በገጸባህርይ ወዘተ ግንኙነት ሊኖረው ይችላል፤ አለውም። የአንድ መጽሐፍ ርዕሰ ጉዳይ በዚያው በመጽሐፉ ላይ ብቻ አያልቅም፤ በሌላ ሥራ ልንጠቀምበት እንችላለን ብሏል።

 በዝግጅቱ ማጠናቀቂያ ላይ ለመርሃ ግብሩ መሳካት አስተዋፅኦ ላበረከቱ ግለሰቦች ምስጋና አቅርቦና በስሙ የተፈረመ መጽሐፍ በስጦታ አበርክቶ ዝግጅቱ ተጠናቋል።

 “አፍ” የአዳም ረታ አስረኛ መጽሐፍ ሲሆን፣ በ254 ገፆች ተቀንብቦ በ80 ብር ዋጋ ለገበያ የቀረበ ወጥ ልብ ወለድ ነው።

አርቲስት ፍቃዱ ሁለት መቶ ሺህ ብር ለገሰ

ተዋናይ ፍቃዱ ተ/ማርያም ሁለቱም ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጪ በመሆናቸው የገጠመውን የጤና ችግር ለመታደግ በቀረበ ህዝባዊ ጥሪ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የተዋናዩን የሀገር ውስጥ የህክምና ወጪ ሙሉ በሙሉ እሸፍናለሁ ብሏል።

 ታዋቂው ተዋናይ ፈቃዱ ተክለማርያም በሁለቱም ኩላሊቶቹ ላይ ያጋጠመውን ህመም አስመልክቶ ወደ ቀድሞው ጤንነቱ እንዲመለስ ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ ጥረት እያደረጉ ባሉበት ወቅት፣ የኢፌዴሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አርቲስቱ በሀገር ውስጥ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የሚያደርግበትን የህክምና ወጪ ሙሉ በሙሉ እሸፍናለሁ ሲል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

አርቲስት ፈቃዱ ተክለማርያም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቲቪ በሽታ በጎ ፈቃድ አምባሳደር በመሆን ለ5 ዓመታት ያለምንም ክፍያ ማገልገሉን የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሳውቋል።

 አርቲስቱ የገጠመውን የጤና እክል በመረዳት የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ለማቋቋም የወሰኑት የሙያ አጋሮቹና የጥበብ ቤተሰቦች፣ መጋቢት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በአፍሮ ዳይት ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በጋዜጣዊ መግለጫውም ወቅት አርቲስት ፍቃዱ ተክለ ማርያም ከአገር እና ከሕዝቡ ከተሰበሰው ገንዘብ ላይ (ሁለቱ ኩላሊቶቿ አገልግሎት የማይሰጡ) ለ19 ዓመቷ ሜላት አሰፋ ለሕክምና ወጪ እንዲሆናት 200 ሺህ ብር (ሁለት መቶ ሺህ ብር) ድጋፍ አደርጓል። በወቅቱም አርቲስቱ

 “ እኔ በራሴ ጉዳይ ሰው ፊት መቅረብ ብዙም አይሆንልኝም። ፈተና ሲገጥመኝ የለመድኩት እመብርሀንን ከነልጇ ማስቸገር ነው። እሷም ማማለድዋን ልጇ መድሀኔ አለምም ፀሎቴን መስማቱን ለአንድም ቀን እምቢ ብለውኝ አያውቁም ዛሬ የመጣሁት ላመሰግን ነው። ግን ከዚህ ሁሉ በፊት ያስጨነቀኝ አዲስ ጉዳይ ገጠመኝ፤ እኔ ስልሳው ላይ ነኝ፤ የቀሩኝ አመታት ከጣቶቼ ቁጥር አይበልጡም፤ እና ይህች ገና ነገዎቿ ተደርድረው የሚጠብቋት የ 18 አመት ቀንበጥ ሁለቱም ኩላሊቶቿ ደክመው በገንዘብ እጦት ስትሞት እያየሁ እኔ ቀድሜ ልታከም አልችልም፤ በዚህች አንድ ሳምንት ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ያስተማረኝ ፍቅርም ይህንን አያሳይም። በዚህ ምክንያት እኔ መሞት ካለብኝ ልሙት እንጂ እቺ ልጅ ሳትድን እኔን ቢላ አይነካኝም። እናም እንድኖር የምትፈልጉ ከሆነ መጀመሪያ እሷን አድኑልኝ። ለአሁን ያስፈልጋታል የተባለውን፤ህዝብ ከሰጠኝ ላይ ቀንሼ እሰጣታለሁ። እስከመጨረሻው ድረስ ለኔ የመጣ በረከት ሁሉም ለሷም እንደሚደርስ ቃል እገባለሁ። ከሰጣችሁኝ ላይ ቀንሼ ይህን በማድረጌ ለድፍረቴ ይቅርታ እጠይቃለሁ”

ሲል በወቅቱ የተሰማውን ስሜት ተናግሯል።

 ኮሚቴው በ”Go Fund me. Help Save Fikadu T/Mariam’s life” 75 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ለማሰባሰብ አቅዶ እንቅስቃሴ ጀምሯል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስም በ10 ቀናት፣ በ1,325 እርዳታ ሰጪዎች 64,881 የአሜሪካን ዶላር መሰብሰብ ተችሏል።

 • ደራሲ ሰዓዳ የተሳካ የኩላሊት ንቅለ ተከላ አደረገች

ደራሲ ሰዓዳ መሐመድ በቱርክ አንካራ ከተማ ‹‹ኦዚል ሜዲካል ፓርክ›› ከወር በፊት የተሳካ የኩላሊት ንቅለ-ተከላ ሕክምና አድርጋ ጤንነቷ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ቤተሰቦቿና የሙያ አጋሮቿ ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል።

 በአሁኑ ጊዜ ደራሲ ሰዓዳ መሐመድና የኩላሊት ለጋሿ ግለሰብ፣ ለሌላ ምርመራና ክትትል በቱርክ በቀጠሮ ላይ መሆናቸውን የገለጹልን ቤተሰቦቿና ወዳጆቿ፣ ሰዓዳ እና የኩላሊት ለጋሿ ምርመራና ክትትላቸውን እንደጨረሱ ወደ ሀገር ቤት እንደሚመለሱ ነግረውናል። ከሰዓዳ ጋር አብሯት ቱርክ የተጓዘው ታላቅ ወንድሟ አብዱል ሐኪም፣ ሰዓዳ ‹‹ሕክምና እንዳገኝና ጤናዬ እንዲስተካከል የበኩላቸውን አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሁሉ፤ በተለይ ጉዳዩ ወደ ህዝብ እንዲደርስ ለረዱኝ የሀገር ውስጥና ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬን በፈጣሪ ስም አቀርባለሁ›› ማለቷን አስታውቋል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top