ጥበብ በታሪክ ገፅ

የቦረናው ሸኽዬ ሰብእናና የባህላዊ እርቅ

መነሻ። ወዳጄ መስፍን መሰለ፣ በ‹‹ታዛ›› ቅጽ 1 ቁጥር 4 የታህሳስ ወር እትም ‹‹ባህላዊ ዕርቅ ለመልካም አስተዳደር ብልጽግና›› በሚል ርእስ ጥቅል የሆነ ገለጻ፣ ማብራሪያና አልፎ አልፎም ትንተና አስነበበን። የሚታረቁበት ጉዳይ እንጂ የሚያስታርቅ ሽማግሌ እንደ ቁምጣ አጠጠ በሚባልበት በዛሬ ጊዜ በባህላዊ የእርቅ ስርአቶቻችንና እሴቶቻቸው ዙሪያ መወያየቱ ወቅታዊ ሳይሆን አይቀርም። ወዳጄ መስፍን እንደገለጸው ባህላዊ የእርቅ ስርዓት ስኬት በሽማግሌዎቹ፣ (ሽማግሌዎቹ የኃይማኖት መሪም ይሁኑ ታዋቂ ግለሰቦች) በእነዚህ ሰዎች የመሰማት፣ የመደመጥ፣ የመታዘዝ፣ ወዘተ ሰብእና ላይ የተመሰረተ ነው ማለት ይቻላል። በዛሬው ጽሑፌ፣ ከወዳጄ መስፍን ጥቅል ጉዳይ ወጣ ብዬ፣ ከዛሬ 130 አመት በፊት በአንድ መንፈሳዊ አባት አማካኝነት ስለተመሰረተ ባህላዊ የእርቅ ስርዓት፣ ሰብእናና እሴቶቻቸው ለማስተዋወቅ እሞክራለሁ።

 ባለታሪኩ። ባለታሪኩ ሸኽ ሸሪፍ ኢብራሂም ጡሃ ይባላሉ። የአካባቢው ሰው ‹‹የቦረናው ሸኽዬ፣ የቦረናው ጌታ፣ ሸኽ ሸረፈዲን›› በሚሉ ስያሜዎች ያውቃቸዋል፤ በነዚሁም ስሞች ይጠራቸዋል። ሸኽ ሸሪፍ፣ በዛሬው የቦታ አከላለል በደቡብ ወሎ ዞን፣ በከላላ ወረዳ፣ ደገር በሚባለው አካባቢ ከ1833 እስከ 1882 ለሰላሳ ዘጠኝ ዓመታት እንደኖሩ ይታመናል። ሸኽ ሸሪፍ ሸረፈዲን በእስልምና መንፈሳዊ ልቅናቸውና ብቃታቸው ሀጂ ወሌ አህመድ (1972) እንደገለጿቸው ‹‹የወልዮች/የጻዲቆች ሁሉ ሻኛ›› የተባሉ ነበሩ።

 እኒህ ባለታሪክ ከአባታቸውና በወቅቱ ከነበሩ አሊሞች (የእስልምና መምህሮች) መንፈሳዊ ትምህርት ከወሰዱ በኋላ በ1860 አካባቢ ታላቁን የደገር መስጊድ አቋቁመው ለህዝባቸውና ለተከታዮቻቸው መንፈሳዊና ማህበራዊ አገልግሎት መስጠት እንደጀመሩ ይታመናል። በዚህ ሁለ ገብ አገልግሎታቸው ሁሉም ሰው እንዳባቱ የሚያያቸው፣ ‹‹የቦረናው ሸኽዬ/ እርዱኝ አባብዬ›› እያለ የሚጠጋቸው፣ ችግሩን የሚያካፍላቸው፣ እሳቸውም መሀመድ (2009) ከመስክ እንዳገኘው ‹‹አላህ በሰጣቸው ከራማ ድውያንን ይፈውሱ፣ መውለድ የተቸገረ ልጅ እንዲወልድ ያደርጉ፣ በድብቅ የተፈጸመን ወንጀል በማጋለጥ ወንጀልን ይከላከሉ፣ ሃብት የራቀው ሃብታም እንዲሆን፣ የተጣላ እርቅ እንዲያወርድ ወዘተ. ያደርጉ እንደነበር፣ በግል ህይወታቸውም ለጋስ፣ ገራገርና ሚዛናዊ ፍርድ ሰጪ እንደነበሩ›› ይነገርላቸዋል። ይህን ሰብእናቸውም በመንዙማ ዜማ ይገልጹታል። ለምሳሌ ይሆን ዘንድም ጥቂቶቹን እነሆ።

 ምሳሌ አንድ – የሰብእና ብቃታቸው

 ምጥቀት

 ጌታው ሸረፈዲን የደግዩ ኑር፣

 አላህ ትልቅ እጣ አድሎት ነበር፣

 ሰውም ጅንም ቢሆን አውሬውም የዱር፣

 ሁሉም አቤት ብሎ ተገዝቶ ነበር።

 ምሳሌ ሁለት – ፍትሃዊነታቸው

ማዳቸው ገበያ ለሁሉ ሚበቃ፣

 በሳቸው የሸሸ አንድም አልተጠቃ፣

 ለቁሙም ለሙቱም የሆኑት ጠበቃ።

 ምሳሌ ሶስት – የሁሉም ስለመሆናቸው

 ጥላው የሚበቃው በሁለት አገር፣

 በሱ ይወሰላል እስላሙም ካፊር፣

ሴትም ወንድም ቢሆን አብዲም ቢሆን ሁር፣

 በሱ ተወስሎ የለውም ችጋር።

 ምሳሌ አራት – ለፈጣሪ የማማለድ ብቃታቸው

 በጌታው ሸህዬ በቦረናው ጌታ፣

 እባክህ ጌታዬ አርግልን እርዳታ፣

 በሳቸው የሸሸ ይድናል ባንዳፍታ።

 ምሳሌ አምስት – ተፈቃሪነታቸውና ተከባሪነታቸው

የደገር ሙሽራ የቦረናው ጣይ፣

ረህመት ደህንነት ይውረድ ባንቱ ላይ

አላህ የሾመዎት ከሁሉም በላይ፣

ከራማሁ ይፋ ነው ያለ እንደ ጣይ፣

ለካ አላህ ወደደው ዛትሁን የሚያይ።

የባለ ታሪኩ አፋዊ ተረኮች። ሸኽ ሸሪፍ ኢብራሂም ጡሃ በህይወት በረበሩ ጊዜም ሆነ በሞት ከተለዩ በኋላ በእሳቸው ወይም በሳቸው ከራማ ተፈጸሙ የሚባሉ የልቅናና የብቃት ማረጋገጫ የሆኑ ተረኮች አሏችው። ተረኮቹ የሸኹን የተለየ ተሰጥኦና ችሎታ የሚገልጹ፣ በህዝባቸው መካከል ተጽእኖ የሚፈጥሩ ማሳያ ሲሆኑ፣ በዚህ ጽሁፍ በአካባቢው ተዘውትረው ከሚታወቁ ተረኮቻቸው አንድ ሶስቱ እንደወረደ እንደሚከተለው ቀርበዋል።

ተረክ አንድ፡- አንድ ሰው የሸኹን ወልይነት ለመፈተን ይነሳሳል። እንደ ሴት ቀሚስ ለብሶ፣ እጆቹን ጉርሽጥ ሞቆ፣ እዛውያቸው ይቀመጣል። ሸኹ እከለዋቸው (የግል መቀመጫቸው) ሆነው ሀድራው እንደሞቀ መናገር ይጀምራሉ። በመካከል ‹‹አንች ከመንዝ የመጣሽ ሴትዮ›› ይላሉ። ሰውየው ‹‹ለበይክ/አቤት›› ይላል። ሸኹ ‹‹ምን ብለሽ ነው የመጣሽው›› ሲሉ ይጠይቃሉ። ሰውየውም ‹‹ልጅ ይሰጡኝ ብዬ›› ይላቸዋል። ‹‹ አብሽሪ ያልሽው ተሰቶሻል›› ብለው ያሰናብቱታል። እንዳሉትም ይሆናል። እቤቱ ተመልሶ እሚስቱ ጋር ሲተኛ ሰውየው ያረግዛል። ጉድ ይፈላበታል። አንድ ወር፣ ሁለት ወር፣ … እያለ ዘጠኝ ወሩ ይገባል። ቤተሰብ ተረበሸ፣ አገር ጉድ አለ። የማይሆን ሲሆን ጊዜ በሬ ይዞ ሸኹ ዘንድ ይመጣል። ‹‹አባባ ሸኽየ! ወይ አንድ መላ አድርጉልኝ፣ ወይም ነብሴን አውጡልኝ›› ሲል ያለቅስባቸዋል – ኸለዋቸው ላይ ተደፍቶ። … ሰውየው መሀን ሚስት ነበረችው። ከሚስቱ ጋር እንዲመጣ አዘዙት። ሚስቱን ይዞ መጣ። አባብየም የባልና ሚስቱን

እሴቶቻቸው

መምጣት እንዳወቁ ‹‹በሉ እንግዲህ እንደምትገናኙ አድርጋችሁ ተኙ›› አሏቸው። ባልና ሚስቶቹ እንደታዘዙት አደረጉ። በዚያው የሱ እርግዝና እሷ ላይ ግልብጥ ብሎ አደረ። ምጥ የሷ ሆነ፣ እርግዝና የሱ ሆነ።

 ተረክ ሁለት፡- የቦረናው ሸኽዬ የዱር እንስሳ የተገራላቸው ነበሩ። በተለይ አንበሳ በመጋለብ ይታወቃሉ። … አንድ ጊዜ ደረሶቻቸውን ተነሱ አሉ። ተነሱ። ‹‹አንዳችሁ ሞራ ያዙ። አንዳችሁ ደግሞ ምላጭ ያዙ። አንዳችሁ ደግሞ እሳት ያዙ አሉ።›› ከዚያ በኋላ ‹‹ተከተሉኝ›› አሉ። ከቤት ወጡና ወደ ጫካ ገቡ። ደረሶቻቸውም ተከተሏቸው። አንድ ወንዝ አካባቢ ሲደርሱ አንበሳ አገኙ። አንበሳው ተንጋሎ ይጮህ ነበር። ከዚያ ሸኹ እግሩን ያዙት። እግሩ ውስጥ ጋሬጣ አገኙ። ከዚያ ላንዱ ደረሳቸው እግሩን ያዝልኝ አሉት። ከዚያ ምላጩን ተቀበሉ። እግሩን በምላጩ ሰነጠቁና ያን ጋሬጣ አወጡለት። የቁስሉን ቦታ በያዙት ሞራ በእሳት ተኮሱት። ይኸ ሁሉ ሲሆን አንበሳው አይንቀሳቀስም ነበር። ተኩሰው እንደጨረሱ አንበሳውን ተነስ አሉት። ተነሳ። አንበሳውም ምንም እንዳልነበረበት ሆኖ ወደሚፈልግበት ተነስቶ ሄደ።

 ተረክ ሶስት፡- ሴትዮዋ ልጅ የምትወድ ደግሞ ልጅ ያጣች ነበረች። ሸኽዬው ዘንድ ቀርቦ ልጅ ያጣ የለም የሚሉ ወሬ እንደሰማች አንቀልባ ተሸክማ፣ አገር አቋርጣ፣ የአባይንና የወለቃን ወንዞች ተሻግራ እሸኽዬው ኸለዋ (የግል የተመስጥኦ ክፍላቸው) ትደርሳለች። ለሸኽዬው የመጣችበትን ጉዳይ ታስረዳለች። ‹‹ልጅ ትሰጡኝ ብዬ ነው የመጣሁት›› ትላቸዋለች። ሸኽዬው በቀረበላቸው ጥያቄ ተገርመው ተመስጥኦ ውስጥ ይገባሉ። ከቆይታ በኋላ ‹‹እኔ ልጅ የመስጠት ቅዋ (አቅም፣ ችሎታ) የለኝም። ባይሆን አላህ እንዲሰማሽ ዱኣ አደርግልሻለሁ›› ሲሉ ይመልሱላታል። ‹‹እኔ የመጣሁት ልጅ እንድትሰጡኝ ነው። ልጄን ሳይሰጡኝ ባዶ አንቀልባ ይዠ አልመለስም›› ትላቸዋለች። ሸኹ ሴትዮዋ በሳቸው ላይ ያላትን እምነት እንደተረዱ ወደ ጓሮ ዘወር ብለው አነስተኛ መጠን ያላት ድንጋይ ይዘው፣ በጫት ቱፍታ እትፍ አትፍ አድርገው ‹‹ይኸ ልጅሽ ነው። ይኸን አዝለሽ ሂጂ›› ብለው ይሰጧታል። ሴትዮዋም የተሰጠችውን ደንጋይ በአንቀልባዋ እንደ ልጅ አዝላ አገሯ ትመለሳለች። ያን ደንጋይ እንደ ልጅ ስትንከባከብ በመካከሉ ታረግዝና ትወልዳለች። በወለደች በሁለት አመቱ ልጁ ይሞታል። የሰፈሩ ሰዎች ሊቀብሩት ወዲያ ወዲህ ሲሉ ሴትዮዋ እንዳይቀብሩት ትከለክላለች።

 የሞተ ልጅ አስክሬን ተሸክማ ሸኽየው ዘንድ ትመለሳለች። ኸለዋቸው ሳታገኛቸው ትቀራለች። የት እንደሄዱ ብትጠይቅ ወንዝ እንደሄዱ ይነግሯታል። እየተጣደፈች ሄዱበት ወደተባለው ወንዝ ታመራለች። እንዳገኘቻቸው ያዘለችውን አስከሬን አውርዳ ‹‹ይኸው ልጅዎ! የሚያድግ እንጂ የሚሞት ልጅ መቼ ጠየቅሁዎት›› ትላቸዋለች። ሸኽየው እሬሳውን ከአጠገባቸው አጋድመው ወንዙ ዳር ሶላት ይጀምራሉ። ከዚሁ መካከል የሞተው ልጅ ያስነጥሳል። በዚያው ነብሱ ይመለሳል። ሴትዮዋም ልጅዋን አዝላ ወደ አገሯ ትመለሳለች። ወንዙም ‹‹አጢሴ›› የሚል ስም ወጣለት ይባላል።

በእነዚህ የሸኽ ሸረፈዲን ሚታዊ ተረኮች እውነተኛነት የሚጠራጠሩ ወይም የማያምኑ የቁስ አካላዊ ርእዮት ተከታይ የሆኑ ሰዎች ይኖራሉ። የአለም ተፈጥሮ መንፈሳዊና ቁስ አካላዊ ባህሪ እንዳለው ለሚያምኑቱ ደግሞ ተረኮቹ እውነት ናቸው ብለው ሊቀበሉ ይችላሉ። የሁለቱንም ወገኖች ምልከታና አረዳድ ወደ ጎን ትተን ተረኮቹን እንደ ሜታፎርና ትእምርት ወስደን ብናስተነትናቸው ሸኹ በአማኞቻቸው ዘንድ የፈጠሩትንና የተገለጹበትን የሰናይ ልእለሰብ ሰብእና እንረዳለን። ከተረክ አንድ ሸኹ የተደበቀን ምስጢር የማወቅ፣ የዋሸንም ሆነ የከዳን የመቅጣት ሰብእና እንዳላቸው ተደርገው እንደተሳሉ እንረዳለን። ከሁለተኛው ተረክ ሸኹ ለሰው ብቻ ሳይሆን ለእንስሳትም ሳይቀር አዛኝ እንደነበሩ፣ በሶስተኛው ተረክ ሸኹ ልባቸው የጸዳ ወይም የነጻ፣ በዚህም ለመድሃኒትና የደህንነት ልእለ ሰብ ሰብእና እንደተሰጣቸው እንገነዘባለን።

 አባባ ሽፋው። ‹‹አባባ ሽፋው›› የሸመገለ ሰው ስም አይደለም። በተቃራኒው ደግሞ ሽማግሌ ነው። ሁኔታው እንዴት ሆኖ? ሊያስብል ይችላል። ታሪኩ ወዲህ ነው። ‹‹አባባ ሽፋው›› የሸኹ፣ የሸኽ ሸረፈዲን አንካሴ ስም ነው። እሳቸው በህይወት እያሉ ሁለት ታላቅና ታናሽ አንካሴዎች ነበሯቸው። ትንሹ አንካሴ ሸኹ በህይወት በነበሩበት ወቅት፣ ታላቁ አንካሴ ሸኹ ከሞቱ በኋላ እሳቸውን ወክለው ለሽምግልና የሚቆሙ/የሚቀመጡ አንካሴዎች ናቸው።

የሸኽ ሸረፈዲን ሁለቱ

አንካሴዎች በመኖሪያ ቤታቸው

የአንካሴዎቹ ስያሜ መነሻ ደግሞ የቃል ታሪካቸው የሚከተለውን ይመስላል። ሸኹ በአንድ ወገን ለሽምግልና ሲንቀሳቀሱ በሌላ ወገን እሳቸውን ወክለው ለሽምግልና የሚቆሙ ‹‹አባባ ሽፋው›› የሚባሉ አበጋር ነበራቸው ይባላል። በአንድ አጋጣሚ ‹‹አባባ ሽፋው›› ታመው ይሞታሉ። አማኞቻቸውም እንደ አባባ ሽፋው ሆኖ እንዲያገለግለን ልጅ ይውለዱልን ይሏቸዋል። ሸኹ የህዝባቸውን ጥያቄ ከሰሙ በኋላ ‹‹ሁሉም ሰው አባባ ይለኛል፣ ሰው እንዴት ከልጁ ይወልዳል? ባይሆን ተናግሮ ሰው የማያስቀይም፣ አብሉኝ አጠጡኝ ብሎ ሰው የማያስቸግር፣ ሞት የማያገኘው ይህንን አንካሴዬን ስለ ሽፋው ሰጥቻችኋለሁ›› ብለው አንካሴያቸውን ባርከው ሰጧቸው፤ ከዚያን ጊዜ አንስቶ አንካሴያቸው ‹‹አባባ ሽፋው›› ተባለ ይባላል።

 ሁለተኛው አንካሴም እንዲሁ አገር ተሰብስቦ እሳቸውን የሚተካ ልጅ እንዲወልዱ ይማለዷቸዋል። ሸኹም ከልጆቻቸው ልጅ እንደማይችሉ ካስረዱ በኋላ ከእጃቸው የማይለያቸውን አንካሴ አንስተው ‹‹ይህን አንካሴየን ሸፍኣ/መዳኒት አድርጌ ሰጥቻችኋለሁ፤ በሱ ምሎ የካደ ይጠፋል›› አሏቸው ይባላል። ‹‹ሸፍኣ›› የሚለው ቃል ሲደጋገም ቀድሞ ወደሚያውቁት ቃል ‹‹ሽፋው›› ተለወጠ። ህዝቡም ሸኹ ከሞቱ በኋላ በዚህ አንካሴ ‹‹በአባባ ሽፋው›› የተጣላን በማስታረቅ፣ የተሰረቀን በማስመለስ፣ የተጋደለን ደም በማድረቅ ሲገለገሉበት እስከ አሁን ደርሷል።

አባባ ሽፋው በጨርቅ ታሽጎ በሸኹ ቤተሰቦች ውሳኔ በአንድ ሽማግሌ ቤት ይቀመጣል። ከጨርቁ ተገልጦ አይታይም። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለአባባ ሽፋው የሽምግልና ብቃት በወረዳው አስተዳደር እውቅና ተሰጥቶትና ቤት ተሰርቶለት በዚያ ቤት ውስጥ ይኖራል።

የአባባ ሽፋው መኖሪያ

አባባ ሽፋውን እርቅ። አባባ ሽፋው በአንድ አካባቢ ችግር ሲፈጠር በሸኹ ኸሊፋ/ወራሽ ትእዛዝ ለሽምግልና እንዲወጣ ይደረጋል። ጥያቄው ከተበዳይ ወይም ከበዳይ ወይም ከአካባቢው ሰው ሊቀርብ ይችላል። አባባ ሽፋው በቀረበው ጥሪ መሰረት፣ በታዋቂ ሽማግሌዎችና አስታራቂዎች ታጅቦ እንደ ጉዳዩ ክብደት እተበዳይ ወይም እበዳይ ቀዬ ግርዶሽ ተጋርዶለት እንዲሰፍር ይደረጋል። የአባባ ሽፋው ለሽምግልና መውጣት ለሚመለከታቸው በዳይና የበዳይ ቤተሰቦች፣ ተበዳይና የተበዳይ ቤተሰቦች እንዲሰሙ ይደረጋል።

የአባባ ሽፋውን ለሽምግልና ወጥቶ አልቀርብም፣ አልታረቅም የሚል ተበዳይ ወይም በዳይ አይኖርም። አህመድ እንድሪስ (2006) የተባለ የሸኹ ኻዲም/አገልጋይ ትረካ ‹‹አባባ ሽፋው ለሽምግልና ወጥቶ አልታረቅም ቢል ወይ ይታመማል፣ ወይ ከብቱ ገደል ይገባል ወይ ከብቶቹ በሽተኛ ይሆናሉ፣ ከለት ወደለት የዚያ ሰው ዝርያ እየተመናመነ እየጠፋ ቀያቸው እዚህ ቦታ ነበር እስተሚባል ድረስ ይጠፋሉ፤ ህዝቡም ያገላቸዋል …›› ተብሎ ይታመናል። ስለዚህ የሁለቱም ወገኖች ቤተሰቦች ፈጥነው ለአባባ ሽፋው እጅ ይሰጣሉ። አባባ ሽፋውን ያጀቡ ሽማግሌዎችና አስታራቂዎች ይሰየማሉ።

 አጠቃላይ የሽምግልና ስርዓቱን በበሌ፣ በጉማና በጫት ሽምጠጣ ስርዓተ ክዋኔ ይፈጸማል። የበሌው ስርዓት ሁለቱ ወገኖች በአባባ ሽፋው ሽማግሌዎች ለመሸማገል፣ ውሳኔያቸውንም ለመቀበል በሸኽ ሸረፈዲን ስምና በአንካሴያቸው በሀላ/ምህላ የሚገቡበት ስርዓት ነው። ሁለቱም ወገኖች ተራ በተራ ‹‹ከሽማግሌዎች ቃል ብወጣ የሸኾቹ አንካሴ እሾህ ሆኖ ይውጋኝ›› ሲሉ ምህላ ይፈጽማሉ። ከዚህ ሰዓት ጀምሮ በዳይም ሆነ ተበዳይ በክፉ ነገር መፈላለግ አይችሉም።

ከምህላው በኋላ ተበዳይ በደሉን፣ በዳይ መልሱን በመጀመሪያ በተናጠል ከዚያም ፊት ለፊት እንዲያቀርቡ ያደርጋሉ። ሽማግሌዎቹ የተበዳይና የበዳይን ጭብጥ ከሰሙ በኋላ ተጨማሪ ምስክር ወይም መረጃ ካስፈለጋቸው ቀጠሮ ይቆርጣሉ። የቀጠሮው ቀን ደርሶ ውሳኔ እስኪሰጥ ድረስ አባባ ሽፋው በሰፈረበት ቦታ እንዲቆይ ይደረጋል። በቀጠሮው እለት ተበዳይና የተበዳይ ወገኖች፣ በዳይና የበዳይ ወገኖች አባባ ሽፋው የሽምግልና ቦታ ይቀርባሉ። ሽማግሌዎቹም የተበዳይንና

“የጫት ሽምጠጣ ስርዓት የአባባ ሽፋው የሽም ግልና ስርዓት የመጨረሻው ክፍል ነው። በዚህ ክፍል ተበዳይና የተበዳይ ወገኖች ከበዳይና የበዳይ ወገኖች ጋር ሆነው በጋራ በግ ገዝተው ለሽማግሌዎቹ ‹‹ኮርማ ጀባ›› የሚሉበት፤ በጋራ ጫት ይዘው ‹‹ጫት ጀባ›› የሚሉበት ሂደት ነው። ሁለቱም ወገኖች በህብረት ምግቡን አዘጋጅተው ሽማግሌዎቹን ይጋብዛሉ”

 የበዳይን ጭብጦች ግራ ቀኙን ካዩ በኋላ ለተበዳይ ለበደሉ የሚመጥን ካሳ ይቆርጣሉ። በደሉ የሞት ከሆነ ደግሞ ለሞተው ሰው ማካካሻ የሚሆን ጉማ ይወስናሉ።

የጫት ሽምጠጣ ስርዓት የአባባ ሽፋው የሽምግልና ስርዓት የመጨረሻው ክፍል ነው። በዚህ ክፍል ተበዳይና የተበዳይ ወገኖች ከበዳይና የበዳይ ወገኖች ጋር ሆነው በጋራ በግ ገዝተው ለሽማግሌዎቹ ‹‹ኮርማ ጀባ›› የሚሉበት፤ በጋራ ጫት ይዘው ‹‹ጫት ጀባ›› የሚሉበት ሂደት ነው። ሁለቱም ወገኖች በህብረት ምግቡን አዘጋጅተው ሽማግሌዎቹን ይጋብዛሉ። እርስ በርሳቸው እየተገባበዙና እየተጎራረሱ፣ ዳግመኛ በክፉ እንደማይፈላለጉ፣ በደሉ መሰረዙን፣ ደም መቃባቱ መድረቁን፣ ኃጢያቱ መንጻቱን ያረጋግጣሉ።

 ከምግብ በኋላ ሽማግሌዎቹ ሀድራ ተቀምጠው ጫት እየቃሙ፣ ቡና እየቃሙ፣ ወዘተ የሸኽ ሸረፈዲንን ከራማ እየተረኩ፣ በዳይንና ተበዳይን እየመረቁ፣ ቀሪ ህይወታቸው የፍቅርና የሰላም እንዲሆንላቸው ዱኣ/ጸሎት እያደረጉ ይቆያሉ። ከሀድራው በኋላ አባባ ሽፋው ታጅቦ ወደመጣበት ይመለሳል። በዚሁ የእርቅ ስርዓቱ ይፈጸማል።

 ‹‹አባባ ሽፋው›› ጥንትም ሆነ ዛሬ ከከላላ ወረዳ በተጨማሪ በደራ፣ በጫቀታ፣ በጃማ ወዘተ አካባቢዎች እየተዘዋወረ የእርቅ ስርዓት የሚፈጸምበት አንካሴ እንደሆነ አለ።

ሲጠቃለል። የሸኽ ሸረፈዲን ታሪክ በዚህ አያበቃም። ጌታው ሸኽዬ ወይም የቦረናው ሸኽዬ ወይም ሸኽ ሸረፈዲን ከዛሬ 150 አመት በፊት ደገር ላይ ያቋቋሙት የሱፊ ማእከል ሌሎች መንፈሳዊና ማህበራዊ ክዋኔዎች እየተካሄዱበት ይገኛል። በዚህ ጽሁፍ በተሟላ መልኩም ባይሆን የሸኽ ሸረፈዲንን የእርቅ ጥበብና እስከ ዛሬ የዘለቀና ተጽእኖ የፈጠረ ሰብእና ለማስቃኘት የሞከርኩ ይመስለኛል።

 እዚህ ላይ ከሸኽ ሸረፈዲን ሰብእና የአስታራቂ ሽማግሌነት ሰብእና ምን አይነት እንደሆነ ማስተንተን እንችላለን። ሽማግሌነት በእድሜ አይወሰንም። ሸኽ ሸረፈዲን በዚህ አለም በሕይወት የኖሩት ለሰላሳ ዘጠኝ አመት ብቻ ነው። ለሽማግሌነት እንደጊዜውና ቦታው በእውቀትና በጥበብ መካንን ይጠይቃል። ሽማግሌነት በሃብት ወይም በስልጣን ወይም በሆነ መንገድ እውቅና በማግኘት የሚሰጡት አይደለም። በውስጥም በውጭም የሰናይ ሰብእና አክሊል ለብሶ መገኘትን ይፈልጋል። ሸኽ ሸረፈዲን የዚህ ሰብእና ባለቤት ነበሩ ማለት ይቻላል። ለሽምግልና መቀመጥና መሸምገል ልዩነት አላቸው። ሽምግልና ተቀምጦ ለመሰማትና ለመደመጥ የሽማግሌነት እነዚህና ሌሎች እሴቶች ያስፈልጋሉ። ያ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ የሚከተለው ዘፈን አዝማች ይሆናል፡-

ቀለም ተቀባ ወይ ሰው ሁሉ ዘንድሮ፣

ሽማግሌ ጠፋ ሽበት እንደ ድሮ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top