አድባራተ ጥበብ

አሳቢው መንግስቱ ለማ

ከ1977 አካባቢ ጀምሮ የተወሰኑ የኢትዮጵያ አውራ ደራሲያንን የህይወት ታሪክ፣ ፍልስፍና እና የድርሰት ስራ ለማጥናት ደኅና ተነሳስቼ ነበር። ከእነዚህ ፀሓፍት መሀከል አንዱ አቶ መንግስቱ ለማ ነበሩ። የድርሰት ስራዎቻቸውን መዘርዝር (bibliography)፣ በኢትዮጵያ ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና ጆርናሎች ያሳተሟቸውንና በታላቋ ብሪታንያ (የተሻለ የሚሆነው UK ነው) በሚገኙ ኢትዮጵያውያን የተማሪዎች ማኅበር በሚታተም መጽሔት ውስጥ የታተሙትን ጽሑፎቻቸውን መዘርዝርና የጽሑፎቹንም ፎቶ ኮፒዎች አዘጋጅቼ ነበር። ለመዘርዘር በሚያዳግቱ ረዥም ሰበቦችና ምክንያቶች ስራውን ሳነሳ ስጥል እስከዛሬ አለሁ። ለመጨረሻ ጊዜ ያነሳሁት በ1981 ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ትናንት ከሰዓት በኋላ ነው ፋይሎቹን የተመለከትኋቸው። እውስጣቸው ካገኘኋቸው ማስታወሻዎች ጥቂቶቹን አደራጅቼ ነው ለዛሬው የ15ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ያቀረብኩት።

 ያኔ ልፅፍ ካሰብኳቸው ምዕራፎች አንዱ “አሳቢው መንግስቱ ለማ” የሚል ነበር። ነገሮችን ከመሰረቱ የመመርመር፣ መሰረታዊ ጥያቄዎች እያነሱ ስለ ማህበራዊ ልማት የመመራመር አዝማሚያቸው በድርሰቶቻቸውና ባንዳንድ መጣጥፎቻቸው ውስጥ የተንሰራፋ ይመስለኛል። ምንም እንኳ ከዚህ ዓለም በሞት ከመለየታቸው በፊት በነበሩት ሁለት ወይም ሶስት ዓመታት እንግሊዝ ሀገር በመነበሬ ያልተገናኘን ቢሆንም፣ እሁሉም ቦታ ቀላል በሚመስሉ ወጎች ውስጥ ጭምር መሰረታዊ ጥያቄዎችን እንደ ቀልድ የማንሳታቸው ጉዳይ እስከ ሐምሌ 21 ቀን 1980 የቀጠለ መሆኑን እገምታለሁ። አሳቢው፣ “ቀልደኛው” እና ደራሲው መንግስቱ እስከ መጨረሻዎቹ ቀናት ድረስ አብረው መቆየታቸውን የሚያመለክት፣ ሆስፒታል እየተመላለሱ ይጠይቋቸው ከነበሩት ተማሪዎቻቸው ሁለቱ ያጫወቱኝን አንድ አጋጣሚ እንደ ሰማሁት አድርጌ ላውጋችሁ።

 አየር እንዲያገኙ በማለት ተማሪዎቻቸው ከመኝታ ክፍላቸው ይዘዋቸው ይወጣሉ። ያወጧቸው ወይ “ስትሬቸር” ላይ አድርገዋቸው ወይም አልጋቸው ላይ እንደነበሩ ነበር አሉ።

ተማሪዎቹ ከሁለቱ አንዱ እየገፋ ሲያንሸራሽሯቸው፣ አቶ

መንግስቱ ሰማዩን ያዩ ኖሮ፣ “ይህንን ነገር እስከዛሬ ከዚህ point of view (ከዚህ አቅጣጫ፣ እዚህ ጋ ሆኜ) አይቼው አላውቅም ነበር። ይገርማል! አሉ!!” አሉ። ይህንን ስሰማ፣ የተጠቀሙባቸው ቃላትና የአጋጣሚው ገለፃ ከወሬ አባት፣ ወሬ አባት ሊለያዩ መቻላቸውን አሰብኩ እንጂ እንዲያ ዓይነት ነገር ሊናገሩ መቻላቸውን ጨርሶ አልተጠራጠርኩም። ይህ የሆነው ትረካውን አድምጬ ስጨርስ ወዲያው በሃሳቤ የመጣው፣ “ጉባኤ ቃና” የሚለው በ“የግጥም ጉባኤ” ውስጥ የታተመው ግጥማቸው ወዲያው ትዝ ብሎኝ ስለነበር ይመስለኛል። ግጥሙ የሚከተለው ነው፡-

ሰማይ ጠቀስ ሆነ ሚሱሪ ኩራቴ

 በላዬ ደመናን የዝቅዝቅ ማየቴ ፤

ሰማይ ጠቀስ ሆነ ሚሱሪ ኩራቴ።

(1955፡5) እግጥሙ ውስጥ ከበላዩ ሆነው ደመናውን ወደ ታች አዩት። ይህ የሆነው በአውሮፕላን ሲበሩ ይመስላል። ግጥሙ ከታተመበት ጊዜ ጀምሮ ብንቆጥር እንኳ፣ ከ26 ዓመታት በኋላ ያንኑ ነገር (ማለትም፣ ሰማዩን ወይም ደመናውን፣ ወይም ደግሞ “ነገሩን”) ለመጀመሪያ ጊዜ በጀርባቸው ተኝተው፣ ሽቅብ ማየታቸውን እንዳዲስ ገጠመኝ፣ አልጋ ይዘው እንኳ አስተውሎታቸውን፣ ትዝብታቸውን (observation) ያጋራሉ። “ህይወትን በኮሜዲ ስለው፣ ሰውን አስቀው ኖረው በዚያው መንገድ አለፉ?” ነበር በውስጤ ያልኩት። ቀጥየም፣ የእርሳቸው ነገር እንደ ማሽላ እንደ ነበር፣ በአንድ አጋጣሚ፣ የምር ባወጉኝ ወግ ውስጥ ጠቅሰውት ስለነበር፣ ይህንን ትረካ ስሰማ ያንንም በማስታወሴ ውስጤ ተሸማቅቆ ነበር። ለጊዜው ዋናው ቁምነገር፣ አቶ መንግስቱ በእንደዚህ ዓይነቱ፣ ሞት በአካባቢው እያንዣበበ ባለበት፣ ለብዙ ሰው ፈታኝና አሳዛኝ በሆነ አጋጣሚ ሳይቀር መሰረታዊ የህይወትን ጉዳዮች የሚያነሱና ቀድመውም ኮሜዲውን የሚያስተውሉ መሆናቸውን ማመልከት ነው። ይህቺን ያህል መግቢያ ካቀረብኩ በኋላ ወደ ርዕሴ ባቀና መልካም ይመስለኛል።

ቀድሞ የተገለፀው ርዕሴ፣ ያው “አሳቢው መንግስቱ ለማ” የሚል ነው። “ሰው ከሌሎች እንስሳት የሚለየው በማሰቡም ነው” ከተባለ ቆይቶ ሳለ አቶ መንግስቱን “አሳቢ” ማለት ነገር መደጋገም ሊመስል ይችላል። ምክንያቱም አቶ መንግስቱ ሰው ስለሆኑ አሳቢ መሆናቸው የተረጋገጠ ነውና። እዚህ ላነሳው የፈለግሁት ቁምነገር ግን ከዚህ የተለየ ነው። “አሳቢ” ስል ማለት የምፈልገው፣ በየቀኑ እያንዳንዱ ትምህርት ቤት ገብቶ ያልተማረ ተርታ ሰው፣ ወይም ስለ አንድ ሙያ የተማረ፣ ወይም ባንድ ሙያ የሰለጠነ ሰው የየእለት ስራውን ሲያከናውን ከሚያስበው፣ ለየት ስላለ ማሰብ ነው። ግምበኛው፣ እንጨት ፈላጩ፣ የአውቶቡስ ካርኒ ቆራጭዋ፣ መምህሩ፣ ለማኙ፣ የፊዚክስ ፕሮፌሰሯ፣ ሰርካዊ ተግባራቸውን ሲያከናውኑ እያሰቡ ነው። የሀሳባቸው ዓይነትና ልክ እንደየተግባራቸው ዓይነትና ልክ ይለያያል። ሁሉም ግን እያሰቡ ነው የሚሰሩት።

ግምበኛ ሁሉ ግን አንድ አይመስለኝም። አንዳንዱ ግምበኛ በቀላል፣ በቀለጠፈ፣ ብዙ ጉልበትና ጊዜ በማይፈጅ መንገድ ግምቡን ስለሚገነባበት ዘዴ ደጋግሞ ያስብ ይመስለኛል። ልምዱን ፅፎ ሲያሳትም እኛ አገር አይገኝም እንጂ፣ ግምባታውን ግን ያቀለጥፍበት ይመስለኛል። ዘመድ፣ ወዳጅ፣ ጎረቤት ግምበኞችንና ሌሎች በአካባቢው ያሉትን ግምበኞች አዲሱን አገነባብ እያሳየ፣ እያስተማረ ችግራቸውን ያቀልላቸውም ይሆናል። ይህ ሰው ስለሙያው አስቦ፣ ሌሎች ሰዎች ስለሙያው ከእርሱ በፊት፣ ቢያንስ በእርሱ አካባቢና ሀገር ያላሰቡትን አሰላስሎ፣ ያቅሙን ያህል አዲስ መንገድ ቀዷል ማለት ነው።

 ከዚህች ቀላል ምሳሌ እንደምንረዳው፣ ሰውየው ሌላ ሰው የሚያደርገውንና የሚለውን መልሶ የሚያደርግና የሚናገር፣ የሚያነበንብ በቀቀን ሳይሆን፣ በሚደረገውና በሚነገረው ላይ ተመስርቶ፣ የራሱን ልምድና እውቀት አክሎ፣ በሙያው ተጨማሪ እውቀትና ተጨማሪ የትግበራ ዘዴ ለመፈልሰም የተጣጣረና የደረሰበትንም ውጤት ከብጤዎቹ ጋ የሚጋራ ነው። ይህ አንድ ዓይነት አሳቢ ነው።

 ሌላ ዓይነት አሳቢ ደግሞ አለ። የሰውን ምንነት፣ የመኖርን ፍች፣ የሞትን፣ የፍቅርን፣ የጠብን፣ የዓለምን፣ የፍጥረትን በጠቅላላ ወዘተ. ኬትመጣ (origin) ስራዬ ብሎ ከእኛ ይበልጥ ጊዜና ትኩረት ሰጥቶ፣ ከመሰረቱ

ግምበኛ ሁሉ ግን አንድ አይመስለኝም። አንዳንዱ ግምበኛ በቀላል፣ በቀለጠፈ፣ ብዙ ጉልበትና ጊዜ በማይፈጅ መንገድ ግምቡን ስለሚገነባበት ዘዴ ደጋግሞ ያስብ ይመስለኛል። ልምዱን ፅፎ ሲያሳትም እኛ አገር አይገኝም እንጂ፣ ግምባታውን ግን ያቀለጥፍበት ይመስለኛል

የሚጠይቅና የሚመራመር አለ። አንዳንዱ ደግሞ፣ ባንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚታየውን ቁሳዊና መንፈሳዊ ህይወት ተመልክቶ ስለእርሱ በተለያየ መንገድ ይመራመራል። ማኅበረሰቡን በቅርበት ከማጥናቱ በፊትም በወጉ ተሰናድተው የማይገኙትን፣ ስለማኅበረሰቡ ቁሳዊና መንፈሳዊ ህይወት የሚናገሩት መረጃዎች የሚደራጁበትን መንገድ ያስባል። ከዚያ በኋላ መረጃዎቹን ይሰበስባል፣ የሰበሰባቸውንም ለቀልጣፋ አገልግሎት በሚመች መንገድ በመዘርዝር ያሰናዳል። የተሰበሰቡትን አንድ ባንድ፣ በጥሞና ያጠናና የተለያዩ ግኝቶች ላይ ይደርሳል።

 እንዲህ እያልን፣ ስለተለያዩ አሳቢዎች፣ ፈላስፋዎችና ተመራማሪዎች ልንወያይ እንችላለን። እንደዚህ ዓይነት ሰዎች በሚኖሩበት ዓለም፣ በአካባቢያቸው በሚያዩት እውነታ (reality) እና በራሳቸው ሕይወት ረክተው፣ ከሞላ ጎደልም፣ ለመኖር የሚያስችል መጠነኛ መፍጨርጨር አድርገው፣ ዝም ብለው መኖር የሚችሉ አይደሉም። ወይ ተፈጥሯቸው፣ ወይ ትምህርታቸው፣ ወይ ልምዳቸው፣ ወይም ደግሞ ከእነዚህ ሁለቱ ወይም ሶስቱም አርፈው እንዲቀመጡ፣ በሰርካዊው ኑሮ ላይ ብቻ የተመሰረተ የሕይወት ፍች ተቀንብበው፣ ድግግሞሹን እያመነዠጉ እንዲኖሩ አይፈቅዱላቸውም። ሁሌ ተጨማሪ ነገር ይፈልጋሉ። ስለግል ሕይወታቸው ስለአካባቢያቸው ስለማኅበረሰባቸው እና ስለዓለም ተጨማሪ ፍች ይፈልጋሉ። በተለየና መልካም በሚመስላቸው መልክ ይህንኑ ሕይወት ለመረዳት፣ የተሻለ በሚመስላቸው መንገድ ለማደራጀትና ስርዓት ለማስያዝ ይሞክራሉ።

የእንዲህ ዓይነቶች ሰዎች በአንድ ሀገር ውስጥ በብዛት መኖርና አለመኖር በየሀገሩ ባህል፣ ታሪክና ሌሎች ብዙ ጉዳዮች የሚወሰን ይመስለኛል። በኢትዮጵያ ውስጥ ምን ያህል ጥልቅ አሳቢዎች እንዳሉ ለማጥናት የሞከረ ሰው መኖሩን አላውቅም። በኢትዮጵያ “የሀሳቦች ታሪክ” (A History of Ideas) የሚባል ነገርም የተሰራ አይመስለኝም። ባንድ ወቅት፣ ለአንድ ዓመት ተኩል ያህል መሰረታዊ ጥሬ- ነገር (raw material) በመሰብሰብ ተጀምሮ የጨነገፈ ያንድ ግለሰብ ደፋር ሙከራ እንደነበረ አውቃለሁ። ይህ ማለት ግን ምንም ማለት አይደለም። የታሪክና የስነ-ጽሑፍ አጠናን እና አተናተናችን፣ ጠቅላላ ቅኝቱና ቃናው ከእንዲህ ዓይነቶቹ መሰረታዊና ጠቃሚ ቁምነገሮች በመራቁ በጣም የሚመሳሰል ይመስላል። የፍልስፍናና የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያዎቻችንም ቢሆኑ ወደዚህ ዓይነቱ መሰረታዊ ጥናት ፊታቸውን ለመመለስ የሚያበቃ ንቃት እስከዛሬ ያገኙ አይመስሉም። ሌላው ቢቀር፣ የቅርብ-የቅርቡን እንኳ ለመስራት አልቻልንም። በአርካይቭ የተቀመጡትን ያማርኛ ጽሑፎች፣ በ“አእምሮ”ና በ“ብርሃንና ሰላም” ጋዜጦች የወጡትን ጽሑፎች እና እስከ 1928 የታተሙትን መጻሕፍት ብቻ መሰረት አድርጎ ሊስሰራ የሚችለውን የሃሳቦች ታሪክ ጥናት መሞከር አልቻልንም። ጉዳዩ ከጠቅላላው የሀገራችን የትምህርት፣ የባህልና የግለሰብ ሁኔታ ጋር የተያያዘ ስለሚመስለኝ ይህንን በዚሁ ላቁም። “ብርሃንና ሰላም” ጋዜጣ ለእንዲህ ዓይነቱ ምርምር ጥሩ መነሻና መለማመጃ እንደሚሆን ግን ለመጠቆም እወዳለሁ። እስከ 1966 በወጡት በሌሎች ጋዜጦች፣ መጽሔቶችና መጻሕፍት ላይም፣ ጊዜ ሊወስድ ቢችልም፣ ተመሳሳይ ስራዎችን በቡድን በመስራት መጀመር ይቻላል። እስከዚያው ግን በየግላችን ባስተዋልነው ላይ የተመሰረተውን መናገር ይጠበቅብናል። በረዥም የሕይወት፣ የትምህርት፣ የምርምርና የማስተማር ልምዳችንና እውቀታችን የተመሰረተን አስተውሎት ሳንጭር ብናልፍ ተከታዩን ትውልድ መነሳሻ ሀሳብ እንኳን ነፈግነው ማለት ይሆናል። በዚህ እምነት ላይ ተመርኩዤ ነው ስለ አቶ መንግስቱ ለማ አሳቢነት አንዳንድ ነጥቦችን ልጫጭር የተነሳሁት እንጂ ደርዝ ያለው ነገር ዛሬ አቀርባለሁ ብዬ አይደለም።

በዚህ ፅሁፍ ውስጥ፣ አቶ መንግስቱ እስከ ሀምሌ 21 ቀን 1980 ድረስ በጻፏቸው ጽሑፎችና በተዘገቡት ንግግሮቻቸው ውስጥ የተንሰራፋውን ሀሳብ ወይም የተንሰራፉትን ሀሳቦች ለመግለፅ አልሞክርም። ያ፣ አንድ ሳተና (ቀልጣፋ)፣ የበሰለ የስነ-ጽሑፍ ተማሪ፣ ለዱክትርና (ለ ፒ.ኤች.ዲ) የሚደክምበት ስራ ይመስለኛል። እኔ ለማመልከት የምሞክረው እ.አ.አ. በተለይ በ1952 (በ1944 ዓ.ም. ገደማ) ያደረጉትን ሙከራ ብቻ ነው። እ.አ.አ. በጁላይ 1949 (1941 ዓ.ም.) በጻፉት ሌላ መጣጥፍ ውስጥ ከሀገር መሰልጠን ጋር የተያያዘውን ጥቅል ሀሳብ ዱካ ቀድመው የሰጡ ነጥቦችንም ለመጠቃቀስ እሞክራለሁ።

 አሳቢነታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘግቦ የተገኘው “ኢትዮጲስ” በሚል የብዕር ስም፣ “ዘ ላየን ከብ” (The Lion Cub) በተባለ፣ እ.አ.አ. ጁላይ 27 1949 መታተም የጀመረ፣ በታላቋ ብሪታንያ ውስጥ ይማሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማኅበር መጽሔት ውስጥ ባሳተሙት “The Best System of Ideas” (“ሽግየው ወይም ልሂቁ የሀሳቦች ስርዓት”) በተሰኘው መጣጥፋቸው ባሰፈሩት ጥቅል ሀሳብ ሊሆን ይችላል። በመጽሔቱ ሶስት ገደማ ገፆች ውስጥ፣ የዛሬ 55 ዓመት (ዛሬ 69 ዓመት ሆኖታል) በእንግሊዝኛ ያሳተሙት መጣጥፍ በጣም እምቅ የሚባል ነው። በርእሱ ውስጥ ያሉት ቃላት ያዘሏቸውን ሀሳቦች በማፍታታትና፣ ከእነርሱ ጋር አያይዞ ጥያቄዎች እየጠየቀ የሚጓዘውን መጣጥፍ በተገቢው መንገድ አብራርቶ መግለፅ ጊዜ ይወስዳል። ስለዚህ፣ ዋና ዋና የመሰሉኝን ነጥቦች ብቻ፣ ከመጣጥፉ በረዥሙ እየጠቀስኩ ጭምር ያለኝ ጊዜ የሚፈቅደውን ያህል አወሳለሁ።

 በጽሑፉ ውስጥ፣ በታላቋ ብሪታንያ ያሉ ኢትዮጵያውያንን እንደ መልእክተኞች ይቆጥሯቸውና ወደ ሀገራቸው ሲመለሱም ለላኳቸው ሰዎች የሚፈልጉትን መልእክት ማድረስ እንዳለባቸው አርገው ይናገራሉ።

መልዕክቱም በየሙያቸው የሚማሩት ትምህርት መሆኑን ይገልፁና “የምናደርሰው መልእክት በእርግጥ እሱ ብቻ ነው?” ሲሉ ይጠይቃሉ። የተለያዩ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂና የስነጥበብ ሙያን የተማሩና በእነዚህ ሙያዎች የተካኑ (specialise ያደረጉ) ሰዎች እንደሚያስፈልጉ አይጠረጠርም ካሉ በኋላ፣ ሰዎቹ ግን የተማሩባቸውን መጻሕፍት እንደ ወንጌል የሚቆጥሩ፣ የሚያምኑና የሚያመልኩ መሆን እንደሌለባቸው አጥብቀው ይናገራሉ። ከማኅበራዊ ሳይንስና መስኩ ከሚመረምራቸው ፕሮብሌሞች ጋር የማይተዋወቁ፣ የዘመናዊው የምዕራብ ኢንዱስትሪ ልማት መለዮ የሆኑት የሙያ ግትር ተክህኖ እና የግትር ባለሙያዊነት ሰለባዎች (victims) መሆን እንደሌለባቸው ያመለክታሉ። እንዲህ ዓይነቱ የሙያ ተክህኖ በሙያው ጥቃቅን ዝርዝሮች ላይ ብቻ መመሰጥን አበረታትቶ የወቅቱን ሙሉ ገጽታ ከማየት ይጋርዳል የሚል ነው ምክንያታቸው። ይህንን ካሉ በኋላ አከታትለው ጥያቄዎች ይጠይቃሉ።

What is the use, for a country like ours, of an engineer who possesses the most up-to-date ideas about the making of houses, roads and about bridge making, but who is ignorant of the social purpose of his activities, who ignores the social reality of his (her) society? The same may be asked about the economist, the lawyer, the artist and the like. We may thus begin to see that the most up-to-date ideas any special subject or profession, craft or technique is not all that is wanted of us that we should acquire; that the Nature of our Mission is such that we cannot, and should not, be satisfied with mere professional “know how.” We must, in addition, have ideas on and about subjects and matters that seem to belong to “spheres” outside our particular field of study; which is not, by the way, to say that one should be a specialist in every field, which is an impossibllity. In short, our duty to our senders demands of us that we should not retum merely “qualified” but also armed with the best system of ideas- best, that is for the Ethiopia of our time (The Lion Cub, Spring 1952፡ p.16).

 ስለ ቤት፣ ስለ መንገድና ስለ ድልድይ ስራ የዘመኑ ቁንጮ እውቀት ባለቤት የሆኑ፣ ስለሚገነቧቸው ቤቶች፣ መንገዶችና ድልድዮች ማኅበራዊ ፋይዳ ምንም የማያውቁ፣ የሀገራቸውን ማኅበራዊ እውነታ ችላ ያሉ መሀንዲሶች ለእንደኛ ዓይነቱ ሀገር ምን ይጠቅማሉ? ይህንኑ ጥያቄ ስለኢኮኖሚስቶቹ፣ ስለጠበቆቹ፣ ስለ ከያኒዎቹ እና ስለሌሎቹ ባለሙያዎች መጠየቅ ይቻላል። ስለዚህ፣ ከእኛ የሚጠበቀው፣ ባንድ መስክ ወይም ሙያ፣ ጥበብ ወይም ቴክኒክ በዘመኑ ቁንጮ የተባለውን ሀሳብ መቅሰም ብቻ አይደለም ማለት ነው። የተልእኳችን ምስጢር ከዚህ የላቀ ነው። በሙያ እውቀት ብቻ መርካት የለብንም፣ ልንረካም አይገባም። በተጨማሪ፣ ከየራሳችን ሙያ ውጭ ያሉ መስለው ስለሚታዩ ርእሰነገሮችና ጉዳዮችም አንዳንድ እውቀት ሊኖረን ይገባል። ይህ ማለት እያንዳንዱ ሰው በሁሉም ሙያ ይካን ማለት አይደለም። ይህ ሊሆን የማይችል ነገር ነው። ባጭሩ፣ ለላኪዎቻችን ማሟላት ያለብን ግዴታ በአንድ ሙያ ተክኖ መመለስን ብቻ ሳይሆን፣ ለዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ሸጋ በሆነው በልሂቁ የሃሳቦች ስርዓት መታጠቅንም ነው (ዘ ላየን ከብ፣ 1944፡ ገጽ 15)።

 (ማስታወሻ፣ በአማርኛው ቅጅ ፆታ እያፈራረቅሁ አንባቢያንን እንዳላስቸግር ብዬ ነው በብዙ ቁጥር የተረጎምኩት። አቶ መንግስቱ በዚያን ጊዜ ስለነበራቸው የፆታ ጉዳይ ንቃት የእንግሊዝኛውን ቅጅ ያስተውሉ። “የኢትዮጵያ መንግስት” ወይም “የኢትዮጵያ ህዝብ” ወይም “የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ” ማለት የፈለጉ አይመስልም። ለዚህ ይመስለኛል “ላኪዎቻችን”ን የመረጡት። ቁም ነገሩ በዘመኑ ከነበራቸው አመለካከት ጋር የተያያዘ ይመስለኛል። “ሀሳባቸው የሚያደላው ወደ የትኛው ይመስልሀል?” ተብዬ ብጠየቅ ግን “ወደ ኢትዮጵያ ህዝብ” የምል ይመስለኛል።)

 በጊዜው “ለዛሬዪቱ ኢትዮጵያ ሸጋ የሆነውን ሃሳብ ይፈልጉ” ማለት አንባቢያንን እንዳያሳስትም የሚቀጥለውን ማብራሪያ ፈጥነው ያክላሉ። እያንዳንዱ ሀገር ከሌላው የተለየ ሊሆን ቢችልም፣ ኢትዮጵያም በራሷ መንገድ ልዩ ብትሆንም፤ ከሌሎች ሀገሮች ልምድ የምትቀስመው የላትም ማለት እንዳልሆነ ይገልፃሉ። በ18ኛው ክፍለ ዘመን እንግሊዝ ከነበራት የመሰልጠን ዕድል፣ ኢትዮጵያ በ1944 የነበራት የመሰልጠን ዕድል የተሻለ መሆኑን ይገልፁና፣ ይህ ሁኔታ በኢትዮጵያውያን እና በአፍሪካውያን ላይ ከፍተኛ ኃላፊነት እንደጣለ ይጠቁማሉ። ወደመነሻ ጥያቄያቸው ይመለሱናም፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሸጋ የሚሆነው ሁሉ፤ ለኢትዮጵያም ሸጋ እንደሆነ ይናገራሉ። ሸጋ የሚሆነውን የሚወስኑትም የኢትዮጵያ ፕሮብሌም ባሕርይ፣ የሀገሪቱ ፍላጎትና ማኅበራዊ እውነታዎቹ እንደሆኑ ያስረዳሉ። የእነዚህን ምንነት ለማወቅ ደግሞ፣ መጀመሪያ እነሱ ምን እንደሆኑ ለማወቅ መፈለግ፣ ማጥናት፣ መመራመር እና መጠየቅ፣ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የመልሱን ፍንጭና መልሱንም ፈልጎ ማግኘት ያስፈልጋል ይላሉ።

 በዚሁ ጽሑፋቸው፣ በወቅቱ የኑሮ፣ የጤናና የትምህርት ደረጃ በኢትዮጵያ እያደገ መሆኑን አይክዱም። ነገር ግን ገና ማደግ፣ ካደጉት የአውሮፓ ሀገሮች ጋር ኢትዮጵያ እኩል እስክትሆን ድረስም በጣሙን ማደግ እንዳለበት አስረግጠው ይናገራሉ። “ልሂቁ/ሸጋው የሀሳብ ስርዓትም” በበጣም ፈጣን፣ በቀጥተኛ እና በማይቀለበስ መንገድ ተጉዘን እግባችን እንድንደርስ የሚያደርገን ነው ይላሉ። እርሱን ማግኘትም ከኢትዮጵያውያኑ ተማሪዎች ተልእኮና ተግባር አንዱ መሆኑን ይገልፃሉ።

 ይሁንና ይህንን ዓላማ አሟልቶ ከታሰበው ግብ ለመድረስ የሚያስችሉ ሁለት ቅድመ- ሁኔታዎች እንዳሉ አቶ መንግስቱ ይገልፃሉ። እነርሱም፣ አንደኛው፣ የኢትዮጵያ ወጣቶች፣ ከሁሉም በላይ፣ በፅልመታዊ አተያይና በመላሸቅ (decadence) ስሜት ከተዋጡት ከምእራባዊያን ምሁራን ጋር የሚተቃቀፍ የአብሮነት ስሜት ሳይኖራቸው ኢትዮጵያዊነታቸውን ይጠብቁ ያሉት ነው። ሁለተኛው፣ በዘመናቸው የነበሩትን አንገብጋቢ፣ አከራካሪና ዓበይት ጥያቄዎችን ያለምንም አድሏዊነት የሚመረምርና የሚዳኝ አእምሯዊ ነፃነትን የሚጨምር እውነተኛ የነፃነት ስሜትን ያለምልሙ ያሉት ነው። የሚጋጩ ሀሳቦች፣ የሚቃረኑ ባለስልጣኖች፣ የሚፃረሩ ፍልፍስናዎች እና የሚፋለሙ “የአኗኗር መንገዶች” (ርእዮተዓለሞች ማለታቸው ይመስለኛል) ባሉበት ዓለም፣ በተወሳሰቡ፣ በተቆላለፉና በሚጠላለፉ ጋዜጦችና ሬድዮኖች የሚተላለፉትን ስፍር የለሽ ሀሳቦች በንስር ዓይን ለመመልከት፣ የአእምሮን ዓይን መሳል ያስፈልጋል ሲሉ ይመክራሉ።

በእርግጥ፣ እዚህ ሸጋ ወይም ልሂቅ እተባለው የሀሳብ ስርዓት ጋ እንዴት እንደምንደርስ ግልጥልጥ አርገው የተናገሩት ነገር ባይኖርም፣ እንድንፈልገው ግን ኢርቱእ በሆነ መንገድ ይጎተጉታሉ። ለእየተማሪው፣ ለእየሰዉ የተዉት ይመስላል። ለጊዜው ይህንን ብቻ ጠቁሜ የመጣጥፉን ሀሳብ በጥቅሉ የማስተዋወቅ ስራዬን ላቁምና ስለጥንታዊው የኢትዮጵያ ቅኔ ወደ ፃፉት መጣጥፍ ላቅና።

አቶ መንግስቱ በዘመናዊውና በባህላዊው አኗኗርና እውቀት መሀከል ድልድይ ለመስራት መሞከር ማስፈለጉን የተረዱ፣ ከሁለቱም ስልጣኔዎች መልካም-መልካሙን መውሰድ ጠቃሚም ተገቢም፣ መሆኑን የዛሬ 52 ዓመት ገደማ (ዛሬ 66 ዓመት ሆኖታል) ባሳተሙት The Future of Classical Ethiopian Poetry (“የጥንታዊው የኢትዮጵያ ቅኔ የወደፊት ሚና”) በተባለ መጣጥፍ የገለፁ ሰው ነበሩ። ስለ ግእዝ ቅኔ የጻፉትን ይህንን መጣጥፍ የጀመሩበት፣ የመጀመሪያው ዓረፍተነገር እንዲህ የሚል ነበር፡- “As principle of cultural progress, the preservation of the best in the past is as important as the adoption of the best from the modern” (የዚህ ዓረፍተነገር ሀሳብ ትርጉም፡- “ካለፈው ሸጋ- ሸጋውን/መልካሙን መቅረስ፣ ከዘመናዊው ሸጋ-ሸጋውን/መልካሙን መርጦ እንደመከተል ሁሉ አስፈላጊ ነው የሚለው ሃሳብ፣ ጠቃሚ የባህላዊ ዕድገት መርሕ ነው” የሚል ነው።) ይህንን ለማለት የቻሉት፣ ስለ ሁለቱም ያኗኗርና የእውቀት ስልቶች ጠንቅቀው ያውቁ ስለነበር ይመስለኛል። እንዲያው ከመጻሕፍት አግኝተው፣ በ“ተብሏል! ተደንቋል!” ስሜት የቀዱት ሃሳብ አይመስልም።

 በዚሁ መጣጥፍ፣ ስለ ቅኔ የሚደረገው ምርምርና እርሱን የመቅረስ ስራ አነስተኛ መሆኑን ያወሳሉ። ቅኔን በመቅረስ በኩል የቅኔ ቤቶች ያላቸውን ሚናና በቅኔ ቤቶች ስላለው የቅኔ ሂስ ስርዓትም ያወጋሉ። ስለ ግእዝ ቅኔ ቅርፅና ይዘት፣ ቅኔ ቤቶችም እነዚህን ለጀማሪው ተማሪ ስለሚያስተምሩበት ዘዴ ከገለፁ በኋላ፣ ግእዝ ቅኔ ለአማርኛ ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ለሚጻፉ ግጥሞች በቅርፅ ረገድ አስተዋፅኦ ሊኖረው እንደሚችል አበክረው ያሳስባሉ። ይህም ብቻ አይደለም። በሀገራቸው ረቂቅ የስነ-ጽሑፍ ቅርስ ልዩ ልዩ ጥልቅ መልኮች ያላቸው መተማመን፣ ይኸው ቅርስ ከኢትዮጵያ ውጭም ላሉ የዓለም ገጣምያን የሚያስተምረው ብዙ እንዳለ በልበ- ሙሉነት እንዲናገሩ አድርጓቸዋል።

 ይህንን መጣጥፍ የጻፉበት አንዱ ዋናው ዓላማ፣ የቅኔን ተሃድሶ ከድኅረ-ጣልያን ሃገር መልሶ የማቋቋምና የመገንባት ስራ ጋር አያይዞ፣ በድርሰት በኩል መደረግ አለበት ስለሚሉት አጠቃላይ ተግባር ትውራዊ መሰረት (theoretical base) መጣል ይመስለኛል። ይህንን መጣጥፍ እስከጻፉበት ወቅት፣ በ“አዲስ ዘመን” ጋዜጣ ከታተሙትና ከዚያም በፊት በ“ብርሃንና

አሳቢነታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ተዘግቦ የተገኘው “ኢትዮጲስ” በሚል የብዕር ስም፣ “ዘ ላየን ከብ” (The Lion Cub) በተባለ፣ እ.አ.አ. ጁላይ 27 1949 መታተም የጀመረ፣ በታላቋ ብሪታንያ ውስጥ ይማሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ማኅበር መጽሔት ውስጥ ባሳተሙት “The Best System of Ideas” (“ሽግየው ወይም ልሂቁ የሀሳቦች ስርዓት”) በተሰኘው መጣጥፋቸው ባሰፈሩት ጥቅል ሀሳብ ሊሆን ይችላል

ሰላም” ጋዜጣ ውስጥ፣ ከኢትዮጵያ ስነ-ጽሑፍ ጋር በተያያዘ ከታተሙት መጣጥፎች ጋር ሲነፃፀር የአቶ መንግስቱን መጣጥፍ ያህል፣ በወቅቱ በከፍተኛ ሁኔታ ይታይ የነበረውን የግእዝን ቅኔ አደራረስና ይዘት አብራርቶ፣ ለወደፊቱ የሀገር ውስጥ ቋንቋዎች የስነ-ጽሑፍ ሂደት ሊኖረው የሚችለውን ጠቀሜታ ተረድቶ ሊያስረዳ የሞከረ ኢትዮጵያዊ አልነበረም ማለት ይቻላል። ቢኖርም ሀሳቡን የገለፀበትን ጽሑፍ እስከዛሬ አላየሁም።

 የአማርኛም ይባል የኢትዮጵያ ስነ-ጽሑፍ ሂስ፣ በተለጣጣቂ ውይይት በእውቀት መኪያሄድና መዳበር በሚጀምርበት ጊዜም፣ አቶ መንግስቱ ለማ ከመጀመሪያው ረድፍ ከሚሰለፉት፣ ከዋናዎቹ መሀከል እንደሚሆኑ አልጠራጠርም። እኔ እስከማውቀው፣ “ጥበበ ቃላት” በሚል ርእስ በ1948 በወጣቶች ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ) ባደረጉት ንግግርና ስለ ሂስ በጻፉት ሌላ የጋዜጣ መጣጥፍ ውስጥ ስለስነጽሑፍና ስለሂስ የቀረበው ሃሳብ፣ ከእርሳቸው በፊት ስለስነጽሑፍ ይጻፉ የነበሩትን አስተያየቶች በከፍተኛ ደረጃ ስርዓት ለማስያዝ የሞከረ፣ የመጀመሪያው፣ በኢትዮጵያዊ፣ በአማርኛ የቀረበ ሃሳብ ነው። አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በታተመው በዚህ ንግግርና ስለሂስ በጻፉት በሌላው መጣጥፋቸው ባቀረቡት ውስጥም፣ አቶ መንግስቱ አሳቢ መሆናቸው በውል ይታያል። በዚህ ሀሳብ ዛሬ አልገፋም። ምክንያቱም፣ የዛሬው ተልእኮዬ ስለ ሚዛናዊ የልማት ጎዳናና ስለባህል እድገት ጠልቀው ሲያስቡ፣ ሲተውሩ ያገኘኋቸው ሰው መሆናቸውን መግለፅ ብቻ ስለሆነ ነው። አንድ ቀን፣ ጉዳዩን ከዛሬው በተሻለ ምረት (seriousness) እመለስበት ይሆናል የሚል ጥብቅ ተስፋ አለኝ።

ከማብቃቴ በፊት ግን፣ አንድ ማነቃቂያ ሀሳብ እንዳጋራችሁ ፍቀዱልኝ። ለመነሻ ያህል፣ እስከ 1966 ዓ.ም. በየውጭ ሀገሩ ስለተማሩ ኢትዮጵያውያን የምናውቅ የምናውቀውን ለምን እየጻፍን በጋዜጣና በመጽሔት አናሳትምም? ማሳተም ካልፈለግን ደግሞ፣ ተመራማሪዎች እንዲገለገሉባቸው፣ ለምን በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ቤተመጻሕፍት የመዛግብት ክፍል አናስቀምጣቸውም?

 ለምሳሌ፣ በእንግሊዝ ሀገር የተማሩ ኢትዮጵያውያን እነማን ነበሩ? ምን-ምን ተማሩ? ምን-ምን ጻፉ? ወደ ሀገራቸው ተመልሰው እምን-እምን ስራ ላይ ተሰማሩ? በሌሎች የአውሮፓ ሀገሮችና በአሜሪካ የነበሩ የኢትዮጵያ ተማሪዎች፣ ተማሪ ሆነው ምን ጻፉ? ምን ተናገሩ? የጻፏቸው ጽሑፎች የታተሙ ከሆነ ምን-ምን ላይ ነው የታተሙት? ያልታተሙ ከሆነ ደግሞ የት ይገኛሉ? ያደረጓቸው አንዳንድ ንግግሮች ተቀርፀዋል? የተቀረፁ ከሆነ የት-የት ይገኛሉ? እነዚህን እና ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን እያነሱ፣ እራሳቸው እውጭ ሀገር የተማሩቱ፣ በየግላቸው የሚያውቁትን ብቻ እንኳ በግማሽ፣ ወይም ባንድና በሁለት ገፅ ቢጽፉ በጣም ጠቃሚ የሚሆን ይመስለኛል። ረዥምና ብዙ መጻፍ ከተቻለ ጥሩ ነው፣ የግድ ግን አይደለም። በወጉ የምናውቀውን ቁምነገር መጻፍና ሲያበቃ ማቆም፣ ከአንድ ወይም ከሁለት ሳምንት በኋላ ደግሞ እንደገና አንብቦ፣ የሚቃና ቢኖር አቃንቶ፣ ለአንባብያን ማቅረብን ቢያዘወትሩት፣ ለራስ የሚያረካ፣ ለሌላው ጠቃሚ ልምድ የሚሆን ይመስለኛል። ሌላው ቢቀር ለቅድመ- 1966 ዓመታት ጠቅላላ ታሪክ እና፣ በተለይም ለሀሳቦች ታሪክ ጥናት አንድ ተጨማሪና ጠቃሚ ምንጭ ይሆነናል ብዬ አስባለሁ።

 ሰኔ 21 ቀን 1996፣ ለ15ኛው የደራሲ መንግስቱ ለማ መታሰቢያ በዓል በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ፣ በባህል ማእከል አዳራሽ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተነበበ። 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top