ጥበብ በታሪክ ገፅ

በባህል ሙዚቃ ረገድ የእኔ ትግል የነበረው ብሔራዊ ሙዚቃ ነው”

ተስፋዬ ለማ

ከአምስት ዓመት በፊት በሞት የተለየን ታዋቂ የሙዚቃ ባለሙያ ተስፋዬ ለማ የተወለደው አዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አጠገብ ነው። አባቱ በቤተመንግስት በግርማዊት እቴጌ መነን እልፍኝ አስከልካይ ነበሩ። እናቱ ደግሞ የቤት እመቤት። ቄስ ትምህርት ቤት ገብቶ እስከ ዳዊት ተምሯል። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በተፈሪ መኮንን ተከታትሏል። ከልጅነቱ ጀምሮ ስሜቱ ወደ ሙዚቃ ያጋድላል። ሠርግ ላይ፣ በጥምቀት፣ በመስቀል፣ በተለያዩ በዓላት ሰዎች ሲዘፍኑ ሲያይ ስሜቱ ወደዚያ ይሄዳል። የክብር ዘበኛ ሙዚቀኛ ክፍል “የነጥላሁን ገሠሠ፣ የነተፈራ ካሳ፣ የነብዙነሽ በቀለ፣ የእነ እሳቱ ተሰማና የመሳሰሉትን ሥራዎች ሲሰማ ይሳባል።  በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ዛሬ አዲስ አበባ) ዩኒቨርሲቲ ኪነጥበባት ወቴያትር [Creative Arts Center] ውስጥ ይቀጠራል፡ ፡ ዲሬክተሩ ታዋቂው የቴያትር ባለሙያና መምህር አቶ ተስፋዬ ገሠሠ ነበር፣ ማዕከሉ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያን በሥሩ ይዟል፡፡ ዜማና ግጥም መድረስ ጀመረ። ለእነ ፀሃይ እንዳለ፣ ለእነ ጌታ መሳይ አበበ፣ ለእነ ዘሪሁን በቀለና ለመሳሰሉት የሚሰጣቸው ዜማዎችም እየተወደዱለት መጡ። ሆኖም ዩኒቨርሲቲው ኦርኬስትራ ኢትዮጵያን ለማስተዳደር አልፈለገም። ቀደም ሲል 20 ያህል አባላቱን ቀጥሎ የቀሩትን 15 ባለሙያዎች አሰናበተ። ያኔ ተስፋዬና ሙዚቀኞቹ ከዩኒቨርሲቲው ወጡ፡፡ 

ከአለማየሁ ገ/ሂወት ጋር የተደረገ ቃለ-መጠይቅ

  ስለ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ምን ያስታውሳል?

  ሺ ሰማንያ ተብሎ በሚጠራው ሠፈር ውስጥ ቤት ተከራይተን በሠርጎች፣ እንዲሁም ቱሪስቶች ሲመጡ እንሠራ ነበር። የማልዘነጋው ወንድሜ፣ ወዳጄ የሆነው ቻርልስ ሳተን ያኔ ለሰላም ጓድ [Peace Core] ተልዕኮ መጥቶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪንግ ኮሌጅ የእንግሊዝኛን ቋንቋ ያስተምር ነበር። ታዲያ የዚህ ኦርኬስትራ መቅረት አሳዝኖት “በእኔ ምትክ ሌላ ሰው መድቡና እኔ ድጋፍ አሰባሳቢ [Fund raiser] ሆኜ አስተዳድረዋለሁ፣ ከመፍረስ አድነዋለሁ” ብሎ አለቃውን ጠየቀና ተፈቀደለት። ከዚያ ከልዩ ልዩ ኤምባሲዎች ጋር በመፃፃፍ የነፃነት ወይም ብሔራዊ በዓላቸው ሲሆን እንዲጋብዙን አግባባቸው፡፡ በተለይ ከአሜሪካ ኤምባሲ ብዙ ጥሪዎች አመጣልን። ኦርኬስትራውም ከመፈራረስ ዳነ። ቻርልስ በዚህ አላበቃም። አሜሪካ መጥቶ መሰንቆውን እየተጫወተ ‘ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ የሚባል የጥንት ሙዚቀኞችን የያዘ ቡድን ሊፈርስ ነው፣ የዓለም ሃብት ነውና እርዱኝ’ ብሎ ወደ ሶስት ሺህ የአሜሪካን ዶላር ሰብስቦ ላከልን። ያን ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የኑሮው ሁኔታ በጣም ግሩም ነበር። ስምንት ብር ምን የመሰለ በግ ይገዛል። እንደውም ቆዳው ሲሸጥ ስጋውን በነፃ እንደመብላት ነበር። ጤፍም ቢሆን መቶ ኪሎ ሰላሣ ብር እንደዚህ ቢሆን ነው። እና ያ ገንዘብ በእውነቱ ለአስራ ስድስታችን ከአንድ ዓመት ተኩል በላይ ደሞዛችንን ሊሸፍን ቻለ።

ከዚያ ወደ አሜሪካ ሄደን ትርኢት እንድናቀርብ “ሼልደንስ ኦፈር” ከሚባል የሙዚቃ አስተናባሪ ድርጅት ጋር ተነጋግሮ ተመለሰ። ከሁለት ወር ዝግጅት በኋላም አሜሪካ ሄደን ከሃያ በላይ በሆኑ ክፍለ ግዛቶች [States] ትርኢታችንን በማሳየታችን የኢትዮጵያ ሙዚቃ ተደናቂነትን ሊያገኝ ቻለ። በእውነቱ ወጥ በሆኑት ባህላዊ መሣሪያዎች በመሰንቆ፣ በክራር፣ በከበሮና በመሳሰሉት ስለሠራንና የኢትዮጵያን ሙዚቃ ለአሜሪካ የማስተዋወቂያ ጊዜ ስለነበር በጥሩ ሁኔታ ተቀበሉን። በኒው ዮርክ ታይምስም፣ በዋሽንግተን ፖስትም፣ በሌሎችም ጋዜጦች ምስጋና አገኘን። ተመልሰን ስንመጣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደግሞ አሜሪካን አገር ያሳተምነውን ሸክላ ያለቀረጥ በነፃ እንድናስገባ ፈቀዱልን። ከዚህ በኋላ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ እየጠነከረ መጣ። እኔም በርካታ ድርሰቶችን ሠራሁ። ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ባገሪቱ ከሚገኙ የሙዚቃ ቡድኖች እንደ አንዱ ሆኖ ለረጅም ዘመን ሲሠራ ቆይቶ ደርግ ሲመጣ ባለሙያዎቹ ወደ ማዘጋጃ ቤት እንዲዘዋወሩ ተደረገ። እኔም አምባሳደር ቴያትር ተመደብኩኝ። ዘመኑም ሆነ የሕዝቡ አስተሳሰብ እየተለወጠ ስለመጣ በወጣቶች የተገነባ የባህል ሙዚቃ ማቋቋም አለብኝ ብዬ ተነሳሳሁ። በወቅቱ የባህል ሚኒስትር የነበሩት ዶክተር ሃይሌ ወልደትንሳኤም ፈቀዱልኝ። በአሁኑ ጊዜ ታዋቂ የሆኑትን እነ ነዋይ ደበበን፣ ፀሃይ ዮሃንስን፣ ሻምበል በላይነህን፣ ኤልያስ ተባባልን፣ ሰለሞን ተካልኝንና እነዚህን ሁሉ ያፈራውን ቀድሞ አምባሳደር ቴያትር ሁዋላም ራስ ቴያትር የተባለውን መሰረትኩ።

ከሀገር ለምን ወጣ?

አወጣጤ ከህዝብ ለህዝብ ጋር ሲሆን የተለያዩ ዓለማትን ከዞርን በኋላ ወደ አሜሪካ መጣን። ሆኖም በደርግ መንግሥት እስርና ፈተና ደርሶብኝ ስለነበር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ኑሮ የስጋትና የጭንቀት እንጂ በነፃነት የሚሠራበት አገር ስላልሆነ በዚያም ላይ በሽተኛ ስለሆንኩኝ ይህን ወስኜ አሜሪካን ሃገር ቀረሁ።

በምን ምክኒያት ታሰረ?

ተስፋዬ ለማ፦ አንድ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው የባህል ማዕከል እየሠራሁ የአያልነህ ሙላቱን ግጥም፣ የበሰለ ፍሬ፣ መብላት ካማራችሁ ልጆች አትንጫጩ፣ ባፍ አምላክ ብላችሁ በጣም አትቸኩሉ፣ በጣም አትክነፉ ዝንጀሮው ቅርብ ነው፣ ይወርዳል ከዛፉ። የሚል ያለበትን ሳስጠና ያባዛሁትን ወረቀት ያዩ ሰዎች ጠቁመውብኝ ኖሮ ዝንጀሮ ያልከው ሊቀመንበሩን ነው ብለው አሠሩኝ። በመጨረሻ አቶ ፈቃደ አዘዘ (ዛሬ ዶክተር) ተሯሩጦ አስፈታኝ። (በሌላ አጋጣሚ ይህንኑ ጉዳይ አንስተው ከቃለ መጠይቅ አድራጊው ጋር ሲጫወቱ አቶ አያልነህ ሙላቱ ግጥሙን የፃፈው በአፄ ኃይለሥላሴ ዘመን መሆኑን ከታተመበት የዩኒቨርሲቲው መፅሄት ጋር ማቅረቡ ፍችውን እንዳቀላጠፈለት ተናግሯል።)

“ተስፋ ሙዚየም”ን እንዴት ከፈተ?

አሜሪካ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በጣም ብዙ ነው። አንድ የባህል ማዕከል ያስፈልገዋል። እርግጥ ከሃገር ውጪ ሙዚየም ወይም የባህል ማዕከል ማቋቋም በኢትዮጵያ መንግሥት የማይታሰብ ነገር ቢሆንም እዚህ ባሜሪካ የማያቸውን ብዙ ትላልቅ ድርጅቶች ግለሰቦች ናቸው።

እና ደርግ ከወደቀ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ሄጄ ከወዳጄና ጓደኛዬ ከአበበ ከበደ ጋር ጥናት አደረግን። የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሙዚየም ካየሁ በኋላ “ኢትኖግራፊክ ሙዚየም ነው” በዛው መልክ አሜሪካ ውስጥ አንድ ሙዚየምና ብዙ ሙዚቀኞችም ወደዚህ ስለመጡ አንድ የባህል ሙዚቃ ቡድን ማቋቋም አለብኝ ብዬ ተነሳሁ። የግብርና፣ የሽመና፣ የውጪና የቤት መገልገያ ዕቃዎችን፣ የጦር መሳሪያዎችን፣ እንደ ጦር፣ ጋሻ፣ ጎራዴ ያሉትን፣ የፈረስ ዕቃዎችን አሰባሰብኩ። እንደዚሁም ኢትዮጵያ ከሉሲ ጀምሮ ጥንታዊ ቅርሶች ያሏት ሃገር በመሆኗ ግማሹን በፎቶግራፍ፣ ግማሹን በመፅሃፍ መልክ አዘጋጅቼ፣ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ “ተስፋ ሙዚዬም” በሚል ከፈትኩ። ሙዚየሙ ለአምስት ዓመታት ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ከቆየ በኋላ ታመምኩ፡፡ ስታመም እነዚህ እቃዎች የነበራቸው የመጨረሻ ዕድል መንገድ ላይ መጣል ነበር። በዚህ ጊዜ ይሄ የኢትዮጵያ ቅርስ ነው ብዬ ለኢትዮጵያ ኤምባሲ አስረከብኩኝ። እኔም ይኸው በዚሁ [Rock Creek Manor] በሚባለው የህክምናና እንክብካቤ ማዕከል አንዳንድ ድሮ የማስታውሳቸውን ነገሮች በመፃፍ ላይ አለሁ።

የዜማ እና የግጥም ድርሰቶችን ለእነማን ሰጠ?

ዝነኛ ከሆኑልኝ ሥራዎች በፀሃይ እንዳለ “ሞት ነው ያጠቃቸው”፣ “የህፃኑ ለቅሶ”፣ “ማናለ?” በጌታ መሳይ አበበ ደግሞ “ይሰማሻል ወይ?”፣ በጥላሁን ገሠሠ “አልማዝን አይቼ አልማዝን ሳያት”፣ “ዘንድሮ”፣ “ፍቅርሽ ነው የጎዳኝ”፣ “ችኩል ችኩል ብለሽ”፣ “ምስጋና አይብዛ”፣ የመሳሰሉት ይገኙበታል። አሁን እየቆየሁ ስሄድ እረሳቸዋለሁ:: ከዚህ ሌላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያለሁ ወደባህል ማዕከሉ የሚመጡ ወጣቶችን ሥራ እያየሁ እንደ “ከበደና ማሚቴ”፣ “ለትንሽኮ”፣ ያሉ አጫጭር ቴያትሮችን አቅርቤያለሁ። በኦርኬስትራ ኢትዮጵያም በኩል እንዲሁ በርከት ያሉ ናቸው፣ አንዳንዶቹ እንደውም ወደ ሕዝብ አልቀረቡም። በሬዲዮም አልተቀረፁም። ኤክስፐርመንታል የሆኑ ሥራዎችንም በሃገር መሣሪያ ብቻ ሞክሬያለሁ።

ስለ መጽሐፎቹ ዝግጅት ምን ይላል?

የኢትዮጵያን ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች የሚያስተዋውቀውን መፅሃፍ የፃፍኩት የደርግ ሁኔታ ስላላማረኝ ነው። በየክፍለሃገሩ ዞሬ የሰበሰብኳቸውን የሙዚቃ መሣሪያዎች ስድስት ኪሎ ቤት ተከራይቼ ቱሪስቶችና አንዳንድ ሰዎች እንዲጎበኙት አድርጌ ነበር። ከዚያ በኋላ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ሲወረስ ጥቂቶቹን ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ግማሾቹን ደግሞ ለያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ለመስጠት ሳስብ መሣሪያዎቹ እንደዚህ ተጠብቀው እንደሚኖሩ እርግጠኛ አልነበርኩም። ስለዚህ ለምን ፎቶግራፍ አስነስቼ በመፅሃፍ መልክ አላስቀራቸውም አልኩና የኢትዮጵያ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በሚል ርዕስ አሳተምኩት።

 እዚህ ከመጣሁ ደርግ ሊወድቅ ሁለት ዓመት ሲቀረው “የደርግ ኑዛዜና የጠረጴዛ ዙሪያ ጨዋታዎች” ብዬ ፃፍኩ። መፅሃፉ ደርግ ከመነሻው ጀምሮ በሬዲዮና በጋዜጣ ለሕዝቡ የማይሆን ተስፋ እየሰጠ፣ የማይሠራ ተግባር እየሞከረ እንዴት ወደ ውድቀቱ እንደደረሰ ለማሳየት ይሞክራል።

 በኢትዮጵያ ህዝብ፣ ኢኮኖሚና ጠቅላላ ሁኔታ የደረሰውንም ችግር ያሳያል። ከዛ በኋላ ደግሞ በተለያዩ ጊዜያት ግማሹ በትምህርት ግማሹ በስደት እየመጣ አሜሪካ ውስጥ ብዙ ህዝብ መሰብሰቡን አይቼ ይህ ሕብረተሰብ ምን እያደረገ ነው? በአሜሪካ ሕይወት ውስጥ የሚገጥሙት ሁኔታዎች ምን ይመስላሉ? በሚል “አንድ ወቅት ባሜሪካ” ብዬ ያለውን የሕብረተሰቡን ያኗኗር፣ ያስተሳሰብ ሁኔታና የኑሮ አቅጣጫ በመጠኑ የሚጠቁም በተለይ በዋሺንግተንና ባካባቢው ነዋሪ ሕዝብ ላይ በተመሠረተ ሁኔታ የታየኝን ነገር ፅፌያለሁ።

ቻርለስ ሳተን ማነው?

በእውነቱ ቻርልስ ሳተን በጣም የሚገርምና ልዩ የሆነ ሰው ነው። የዛሬ ሰላሣ አምስት ዓመት ገደማ ገና የሃያ ዓመት ወጣት ሆኖ ነው ወደ ኢትዮጵያ የሄደው። ቨርጂን አይላንድ የሚባል ቦታ እንደ ቅድመ ዝግጅት የአማርኛ ቋንቋ አስጠንተዋቸው ኖሮ አዲስ አበባ እንደገባ በአማርኛ ፅፎ ሲናገር እዚያ የነበሩት የኤርፖርቱ ሠራተኞች ሁሉ ገረማቸው። ከዚያ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር ሆኖ፣ በአማርኛ ደግሞ የተሻለ ውጤት ስለነበረው የሰላም ጓድ አባላትን አማርኛ ለማስጠናት ይመጣል። ታዲያ አንድ ቀን ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ የሚል ማስታወቂያ ተለጥፎ ያያል። ኦርኬስትራ ማለት በዚህ አገር ሲምፎኒ ኦርኬስትራ ስለሆነ በመቶና በሁለት መቶ የሚቆጠሩ ሙዚቀኞች ያሉበት ነው። ባውሮፓና በሌሎቹም በሰለጠኑት ሃገሮች ሲምፎኒ ኦርኬስትራ አለ መቼም። እና ኦርኬስትራ ሲል እንደዚያ መስሎት መጥቶ ቢያይ ክራርና መሰንቆ ነው ያለው። ከዛ ይህን መሰንቆ መማር እፈልጋለሁ አለ። እና ጌታ መሳይ አበበን አስተማሪ ሰጠነው። ጌታ መሳይ በሃገራችን ከታወቁ መሰንቆ ተጫዋቾች አንዱ ነው። በጥቂት ጊዜ ውስጥ ቻርልስን መሰንቆ ጥሩ አስተማረው። በቀን አንድ ሰዓት በጧት ክፍል ከመግባቱ በፊት እየተማረ በስድስት ወራት ውስጥ የሚያስገርም ችሎታ ባለቤት ሆነ።

የየትኛውን የሙዚቃ መሳሪያ አስጠናው?

በዚያን ዘመን የነጥላሁን ገሠሠ፣ የነዓለማየሁ እሸቴ፣ የነታምራት ሞላ ሙዚቃ በዘመናዊ ሙዚቃ በጦር ሠራዊት፣ በክቡር ዘበኛ ሲቀርብ ሕዝቡ ገና አዲስ ስለሆነበት የባህሉን ሙዚቃ ጭራሽ ጠልቶት ነበር።

የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ሙዚቀኖች በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ልደት አዳራሽ ውስጥ ከአምስት ዘፈን በላይ ሲያቀርቡ “ውጡ” ይላቸው ነበር። “አንፈልግም” ይላል። “ክቡር ዘበኛ፣ ጦር ሠራዊት፣ ዘመናዊ…” ይላል። ያን ጊዜ ኪነጥበባት ወቴያትር ገና አልገባሁም። በጣም አዘንኩ። ሽማግሌዎቹ እየተሰቀቁ አምስት ዘፈን እንኳ ሳይጫወቱ ይወጣሉ። በኋላ ቻርልስ መሰንቆ አጥንቶ እንደጨረሰ ይህንን ፈረንጅ መሰንቆ አስይዤ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ባጫውት የሕዝቡ አስተሳሰብ ይለወጣል አልኩና “መሰንቆ ጨዋታ” የምትል የመሰንቆ ዜማ ደረስኩለት፣ እና የአሰፋ አባተን “ሸጊቱ” አጠና። ከዚያ ባንዱ ዘመን መለወጫ በዓል ላይ ስንቀርብ የሕዝቡ አዕምሮ ተለወጠ። እንዴት ይሄ ፈረንጅ የኛን የባህል መሣሪያ አክብሮ ተማረው? ለካስ የኛ ሙዚቃ የእውነት ሙዚቃ ነው፣ ለካ ሌላ ሰው ሊጫወተው ይችላል? ማለት ጀመረ። ከዛ በኋላ እነ ማዕረጉ በዛብህ፣ እነ ብርሃኑ ዘርይሁን፣ እነ ሙሉጌታ ሉሌ፣ እነ ጳውሎስ ኞኞና ሌሎችም ጋዜጠኞች ‘የእኛን ነገር ማድነቅ አለብን፣ የእኛን ነገር ማክበር አለብን’ ብለው በጋዜጦቻቸው ሁሉ የሚያበረታታ ነገር ሲያሰፍሩ ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ እያደገ መጣ። የበለጠ ተቀባይነት አገኘ። እና አምስት ደቂቃ ከመጫወት ወደ ሰላሣ ደቂቃ ወደ አንድ ሰዓት እየተሸጋገረ መጣ።

ወዳጅነቱን እንዴት ያስታውሳል?

ቻርልስ ከዚህም ሌላ በኢንዲያና ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ዓመታት የሙዚቃ ትምህርት እንድከታተል ረድቶኛል። አሜሪካ በስደት ስመጣም እዚህ ለጀመርኩት የባህል ማዕከል በገንዘብ፣ በምክርና በልዩ ልዩ መንገዶች ረድቶኛል። ታምሜ ነርሲንግ ሆም ከገባሁም በሳምንት ሶስት ጊዜ ይደውልልኛል፣ በወር አንድ ጊዜ እየመጣ ይጠይቀኛል። የቻርልስን ቤት ብታይ የአንድ ኢትዮጵያዊ ቤት ነው የሚመስለው፣ ሥዕሉን፣ የጠረጴዛ ልብሱን፣ ጋሻውን፣ ጦሩን ምኑን ሁሉን ይዞ መጥቶ እሱ ቤት ስትገባ ኢትዮጵያ የገባህ ነው የሚመስልህ። ለኢትዮጵያ ትልቅ ፍቅር አለው። ወደፊት አይናችንን በምንገልጥበት ጊዜ ሃገራችንን በተለያዩ መስኮች በሕክምና፣ ሕፃናትን በመርዳት፣ ትምህርት ቤት በማቋቋም፣ ወዘተ ያገለገሉ ብዙ የውጪ ሃገር ሰዎች ስላሉ “ታንኪው” ብለን የማመስገን ባህል በምንገነባበት ጊዜ ቻርልስም እንደማይዘነጋ ተስፋ አለኝ።

የኢትዮጵያን ሙዚቃ ዕድገት በምን መልኩ አየው?

የኢትዮጵያ ሙዚቃ በሚለው ዘርፍ መነጋገር ከጀመርን በጣም ረዥም ዘመን አይደለም። ዘፈን በሚለው ነገር የሄድን እንደሆን የሰው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ ሲያለቅስ፣ ሲተክዝ፣ ሥራ ሲሠራ፣ የባህል ሙዚቃ በየሃገሩ አለው። በተለያዩ ክፍለሃገራት፣ በየብሔረሰቡ፣ እንደ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጡ፣ እንደባህሉ፣ እንደልምዱ በኢትዮጵያ ውስጥ በጣም በርከት ያሉ ሙዚቃዎች አሉ። ሙዚቃ ብለን፣ ይሄም ለካ ሙያ ነው፣ ይሄም ለካ ያበላል፣ ይሄም ለካ ሥራ ነው ብለን ማየት የጀመርነው ግን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ነው። እና በመጠኑ በአፄ ምኒልክ። በዚያን ጊዜ ንጉሠ ነገስቱ በስደት ላይ በነበሩበት ጊዜ የአርሜኒያ ሙዚቀኞች ኢየሩሳሌም ላይ ሲጫወቱ አይተው እነሱን ይዘው መጡ።

በኢትዮጵያ ግን በጊዜው ሙዚቀኛ ዝቅ ተደርጎ ነበር የሚታየው። “የጨዋ ልጅ” የሚሠራው ሥራ ስላልነበረ አርመኖቹን የሚተካ ጠፋ። ጃንሆይ ያመጧቸው የኛን ልጆች እንዲያሰለጥኗቸው ነበር። ከዛ እኔ “የጨዋ ልጅ” ነኝ እንዴት ጥሩምባ እነፋለሁ? እያሉ ሲያስቸግሩ ከጎጃም አካባቢ ቤኒሻንጉሎች መጥተው ሠለጠኑ። ከዚያ ቀስ በቀስ እነሱን እያዩ ሌሎችም መማር ጀመሩ።

 የሙዚቃችን ታሪክ ውስጥ እንደገለፅኩትም በኋላ የክብር ዘበኛ ሙዚቀኛ ክፍል ተረከበው። የፖሊስ ሠራዊት ከክብር ዘበኛ ሠራዊት ሰለጠነ። የጦር ሠራዊትም ሰለጠነ። ከጣሊያን ወረራ ጋር በተያያዘ ስለሃገርና ስለአንድነት ለማስተማርና የሕዝቡን ወኔ ለማነቃቃት ሲባል ለሃገር ፍቅር ቴያትር መሠረት የሆነው እንቅስቃሴም እንዲሁ በግብታዊነት የተጀመረ ነው። የኢትዮጵያ ሙዚቃ በዩኒቨርሲቲ ተጠንቶ፣ ተመክሮበት፣ የባህሉ ይህን መስመር መያዝ አለበት፣ ከውጪ የምንወስደው ሙዚቃ ደግሞ በዚህ መልክ መራመድ አለበት ተብሎ የተጀመረ አይደለም። ራፕ መጣ፣ ሬጌ መጣ፣ ቱዊስት መጣ፣ ምን መጣ እያልን ከዚህ ነው የምንኮርጀው። ክላሲካል ሙዚቃ አላችሁ ወይ ቢባል የለንም፣ የጃዝ ሙዚቃ አላችሁ ብንባል የለንም። አሁን ለምሣሌ በኢንተርናሽናል ደረጃ ኢኮኖሚስት ከሆንክ የትም አገር ኢኮኖሚስት ትሆናለህ ትምህርቱን ካገኘህ። የኢትዮጵያን ሙዚቃ ግን ሌላ ቦታ ወስዶ ማሰለፍ አይቻልም። ምክንያቱም በትምህርት የተደገፈ አይደለም። በባህል ሙዚቃ ረገድ የእኔ ትግል የነበረው ብሔራዊ ሙዚቃ ነው። ከየብሔረሰቡ የተውጣጣ የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች ሙዚቃ በደንብ ለማንፀባረቅ የሚችል። ያ እንግዲህ ከአንድ መቶ ሃያ በላይ በሆኑ ሰዎች የሚቀናበር ነው። ለዶክተር ኃይሌም ያቀረብኩት ጥናት የኢትዮጵያ ሕዝብ ስንባል ብዙ ነን፡፡ በሰሜንም በምስራቅም፣ በደቡብም በምእራብም ያለው ይቀናበርና ይዋሃዳል። ከዚያ በላይ ደግሞ ብሔራዊ ኦርኬስትራ – ዳንሱን፣ አፈ ታሪኩን፣ ዜማውን፣ ሙዚቃውን፣ የበለፀገውን ይዞና በየአይነቱ ሆኖ በትምህርት እያደስነው ኢትዮጵያን የሚወክል የሚያኮራ ሆኖ ይቋቋማል። አሁን የምናቀርበው ለአዲስ አበባ ጠጋ ያሉትን ዶርዜን፣ ጋምጎፋን፣ ጉራጌን፣ ኦሮሞን፣ እንደዚህ ብቻ ነው እንጂ ወደ ውስጥ አልገባንም። በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የጋምቤላ ሙዚቀኞችን ለመጀመሪያ ጊዜ ያመጣሁ እኔ ነኝ። የኮንሶንም። ግን ያ ህልሜ ሳይሳካና ተግባራዊ ሳይሆን ቀረ።

 አሁን ሙዚቀኞቻችን እዚህ ሃገር ሲመጡ አበሻው ተከትሏቸው ባይመጣ ብዙዎቹ ሥራም አያገኙ ነበር። ቋንቋ አይችሉ፣ ትምህርቱም የላቸው። አሁን እንዲችው ሠርጓን፣ ድግሷን፣ … ምናምኗን እየሠሩ ነው መኖር የቻሉት። እንጂ በመደበኛው የሙዚቃ ዓለም [Main stream] ውስጥ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ዘሩም የለም። ለምሣሌ ምዕራብ አፍሪካ፣ ደቡብ አፍሪካ በጣም ፖፑላር ነው። የእነ ኬንያን፣ የጋናን፣ የደቡብ አፍሪቃን ሙዚቃ አሜሪካ ውስጥ እንደ ራሳቸው ሙዚቃ ነው የሚሰሙት። ዓለም አቀፋዊ ባህሪይ [International touch] ያለው ነው። እኔ ይህንን በሃቅ ነው የምናገረው። በእውነቱ ሊታሰብበት ይገባል።

ሙዚቃ ሲያቀናብር የተለየ ባህርይ ያሳይ ይሆን?

ተስፋዬ ለማ፦

እኔ በሕይወቴ ብዙውን ጊዜ ብቸኛ ነኝ። አዲስ አበባ እያለሁ ቤቴ ውስጥ የራሴን ድባብ [Atmosphere] ፈጥሬ ነበር የምኖረው። የመቃብር ቦታ አለው፣ ቤተክርስቲያን አለው፣ አንዳንዱ ክፍል። ካሜሪካ የወሰድኳቸው አንዳንድ መብራቶች አሉ። ልክ የሆነ ገጠር ውስጥ የገባህ ነው የሚመስልህ። እዛ ውስጥ ቁጭ ብዬ አንዳንድ ሃሳቦች ይመጡልኛል። እነዛን እመዘግብና ለዘፈን የሚሆኑ አሉ፣ በግጥም መልክ የሚቀመጡ አሉ። አንዳንዴ ቴያትር ቤት ስሠራ “ያዝ” እለዋለሁ ክራሩን ወይ መሰንቆውን። ከዚያ ቅኝቱን አስይዤው እኔ በፉጨት የምፈልገውን ነገር አስረዳዋለሁ። ዋናው ምንድን ነው ሙዚቃ አእምሯችን ውስጥ ነው ያለው። በኢትዮጵያ አንድ የሌለው ግንዛቤ ፉጨትን ወይም ድምፅን እንደሙዚቃ መሣሪያ አናየውም። የሙዚቃ ምሁራንና ሳይንቲስቶች እንደሚሉት በጣም ፍሌክሲቭል የሆነና ማንኛውም የሙዚቃ መሣሪያ የማይተካው ሙዚቃ ድምፃችን ውስጥ ነው ያለው። ይሄ እኛ በእጃችን የፈጠርነው መሣሪያ ከእኛ ቀጥሎ ነው የሚመጣው። እና እዚህም አገር እነ ኧርሳ ኪት [Eartha Kitt] በእኔ አይነት ስልት ነው እያፏጩ፣ እያዜሙ ዜማ የሚያስጠኑት። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይሄንን እንደ ሙዚቃ መሣሪያ ስለማያዩት በግማሽ ደረጃ ነው በሙዚቃ መሣሪያ የሚፅፉት። እና ለሙዚቀኞች አስረዳቸዋለሁ። ቆንጆ የሆነ ዜማ ይወጣል። እና እንቆራጠጣለሁ፣ አንዳንድ ጊዜም ዜማው አልመጣ ሲል በቃ እየተንጎራደድኩ እሠራለሁ።

“በ1994 ዓም. በ2ኛው ዙር ሽልማት በሙዚቃ ዘርፍ የእድሜ ልክ አገልግሎት ተሸላሚ አድርጎታል፡፡ በመሸለሙ ምን ተሰማው?”

በእውነቱ እኔ በጣም ነው የተደነቅኩት ሰዎችን የማሰታወስ፣ የማመስገን ባህል በመጀመሩ፡፡ ያን ጊዜ በእውነቱ ከልብ ነው የመረቅኩት፡፡ በግል ደግሞ ለዚህ ታስቤ በመመረጤ ታላቅ ደስታ ነው የተሰማኝ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ እንደነ ኢዩኤል ዮሐንስ ያሉት በርካታ ሙያተኞች ለዚህ ዕድል ሳይበቁ በማለፋቸው በጣም ነው የማዝነው፡፡ እኛን ሁሉ ያስተማሩን እነ ሳህሌ ደጋጎ፣ ምትክ የማይገኝላቸው እነ ጥላሁን ገሠሠና ሌሎችም መሸለማቸው ደስ የሚያሰኝ ነው፡፡ በእውነቱ እኔም በተሸለምኩበት ወቅት እነ ጌታቸው ደባልቄ እና ወጣቶችም መሸለማቸው ትልቅ ሥራ ነው፡፡

መቆሙ የሚያሳስብ ጉዳይ ነው። እዚህ አገር ኤሚ አዋርድ፣ ቶኒ አዋርድ፣ አካዳሚ አዋርድ፣ ምን የሚባሉትን ግለሰቦች ናቸው ያቋቋሟቸው። እና መንግሥትም ሆነ አቅም ያላቸው ግለሰቦች እንዲህ ያለውን ጥረት መደገፍ አለባቸው። በመሠረቱ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች እኮ ጠንካራ ሕግ ባለበት አገር ቢሆኑ ኖሮ የኢትዮጵያ መንግሥት በአራትና በአምስት ቢሊዮን ብር ዕዳ በተጠየቀ ነበር። ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ሥራቸውን በሬዲዮና በቴሌቪዥን በነፃ ነው ሲጠቀሙበት የኖሩት። እዚህ አገር ቤተክርስቲያን እንኳ ገዝቶ ነው። እንዲህ ባለ ምዕራፍ ሶሥት ቁጥር አራት ወይም በማርቆስ ወንጌል ላይ ተመሥርተህ ሃይማኖታዊ የሆነ ድርሰት [Composition] ፃፍልኝ ይልሃል። በሚሊዮን በሚቆጠር ነው የሚከፍሉት። እነሱም በዚያው ደረጃ ነው የሚያገኙበት። እና የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አይኑን በገለጠበት ጊዜ ሃምሳና መቶ ሺህ ብር በየዓመቱ ሽልማት ለመስጠት አንድ ሚሊዮን ማውጣት ማለት አሥር ሳንቲም ከማውጣት እኩል ነው – በመንግሥት ደረጃ። እና እንደው ይህንን መልዕክት ዛሬ ገና ማስተላለፌ ነው። ባጋጣሚ የሚደርሳቸው ከሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት ትልቅ ዕዳ አለበት። የኢትዮጵያ ሙዚቀኞችና ሌሎችም ባለሙያዎች ከዚያም በላይ ይገባቸዋል። ሽልማትና ምስጋና ደግሞ የሰለጠነ ሕዝብ ባህል ነው።

ማስታወሻ

በኢትዮጵያ ኤምባሲ በአደራ ተቀምጠው የነበሩት የሙዚየሙ ቁሳቁሶች ቺካጎ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ማዕከል ተሰጥተዋል። የአቶ ተስፋዬ ሥራ የሆነው “የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ” በ2005 ዓ.ም. በአሜሪካ የታተመ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ደግሞ በሻማ መፅሐፍ አሳታሚ አማካይነት በሃገር ውስጥ ለህትመት በመዘጋጄት ላይ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top