አድባራተ ጥበብ

በመንግስቱ ለማ ‹‹ዕውቀት እና ልምድ ለተተኪው ትውልድ›› ላይ ቅኝት

ፀሐፌ ተውኔት፣ ገጣሚ፣ መምህር እና ዲፕሎማት መንግስቱ ለማ፣ በሀገራችን የኪነጥበብ ታሪክ ጎልተው ስማቸው ከሚነሱ ታላላቅ የኪነጥበብ ሰዎች አንዱ እና ዋነኛው ናቸው። ምንም እንኳ እኔ እና የኔ ዘመነኛ እርሳቸውን በአካል አግኝተን ከቃላቸው ለመማር፣ ከግራቸው ስር ተቀምጦ እውቀትን ለመቅሰም ባንታደልም፣ ታትመው ዘመን በተሻገሩ ስራዎቻቸው፣ የኛ መምህራን እና የልምድ አካፋይ በሚሆኑን ተማሪዎቻቸው አንደበት እና ትምህርት፣ በታላላቅ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ስለርሳቸው በተሰሩ ጥናቶች አማካኝነት አቅማችን በፈቀደው ልናውቃቸው እና ልንረዳቸው ሞክረናል። በዚህም መንግስቱ ለማ በርሳቸው ተማሪ በነበሩ መምህራን አጠራር ‹‹አብዬ መንግስቱ›› የኢትዮጵያ ቴአትር ካያቸው ጊዜ የማይሽራቸው ፀሐፌ ተውኔቶች ዋነኛው እና መሪው፣ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የስነግጥም ታሪክ ፈር ቀዳጅ ከሆኑ የተዋጣላቸው ባለቅኔዎች ከዋኖቹ አንዱ መሆናቸውን ለመረዳት ጊዜ አይፈጅም።


ይህ አጭር ጽሑፍ ሰፊ በሆኑት የመንግስቱ ለማ ስራዎችም ሆነ በርሳቸው ታሪክ ላይ የሚያተኩር ሳይሆን በ1980 ዓ.ም. በ‹የካቲት› መጽሔት ከሰላሳ ዓመታት በኋላ ደግሞ በ‹ታዛ› መጽሔት ታትሞ በወጣው ‹‹ዕውቀት እና ልምድ ለተተኪው ትውልድ›› በተሰኘ ሥራቸው ላይ ነው። የጽሑፌም ዓላማ ይህ መጣጥፋቸው በተለይ ለእኔ እና ለእኔ
ዘመነኞች ሊሰጠን የሚችለውን ትርጓሜ በጣም በአጭሩ ለመመርመር መሞከር ነው።
ጽሑፉ የአንድ ወጣት ገጣሚ እና የሌላ ደራሲ ግንኙነት እና በተለይ በስነ-ግጥም ዙርያ ያደረጉትን የጋራ የሀሳብ እና የተመስጦ ጉዞን ይተርካል። ታሪኩ ወጣቱ ባለቅኔ ምክር እና ሀሳብ ምናልባትም አድናቆትን በመሻት በደራሲው መንግስቱ ለማ አጠራር ወደ ‹‹አንጋፋው›› ደራሲ ቤት ያመራል። በመጀመሪያው የቃል ምልልሳቸው ምናልባት ወጣቱ ቤቱ የመጣው ገንዘብ ፍለጋ ከሆነ ‹‹ራሴም ያለሁበት ስለሆነ ወደ ሌላ ሰው ብትሄድ ይሻልሀል›› ሲል አንጋፋው ምክር አዘል ትዕዛዝ ቢሰጡትም ወጣቱ ባለቅኔ ጉዳዩ ከገንዘብ ጋር ያልተገናኘ መሆኑን አበክሮ በማስረዳቱ የድርሰቱ ትኩረት ወደሆነው እና የወጣቱ የቅኔ ስራ እና ችሎታ የሚታይበትን ጉዳይ በዝርዝር ወደመመርመር ይገባሉ። በዚህም የአንጋፋው የቅኔ እና የድርሰት ፍላጎት መጀመሪያ ከወጣቱ ባለቅኔ ጋር ፈፅሞ የሚገናኝ ባይመስልም እየቆየ ግን በተረጋጋ ውይይት እና መተማመን ወደ አንድ ደረጃ ለመድረስ ይሞክራሉ። በዚህም ‹‹ከአንድ ሺህ በላይ ግጥም ፅፌአለሁ›› የሚለው ወጣቱ ገጣሚ ‹‹ካሉህ ግጥሞች ልመለከትልህ የምችለው ጥሩ ናቸው ያልካቸውን አስሩን ብቻ ነው›› ብለው አንጋፋው አንድ ሺውንም ግጥም ለማንበብ ፍላጎት ባለማሳየታቸው ወጣቱ ገጣሚ ‹‹እርስዎ ጋ በመምጣቴ ተሳስቻለሁ፤ እርስዎም እንደሌሎቹ ነዎት። አንጋፋ የምትባሉት እንደዚህ ናችሁ፤ አዲስ ሀይል፤ ትኩስ የድርሰት ጉልበት ሲያጋጥማችሁ፤ በአናቱ ላይ ቀዝቃዛ ውሀ መቸለስ ብቻ ነው፡፡
ሚቀናችሁ። መቅናት ይቀናችኋል።›› የሚል ሀይለ ቃል ሰንዝሮ ከአንጋፋው ደራሲ ቤት ይወጣል። አልቀረም በሳምንቱ ይመለሳል። በዚህም ሰፊ ቁም ነገር ወደተሞላበት ውይይት እና ምክክር ይዘልቃሉ። ስለ ግጥም እና ቅኔ ልዩነት፣ ስለ ቅኔ ዓይነቶች፣ የቅኔን ባህርያት እና መሰል ጉዳዮችን እያነሱ ይወያያሉ። እንደ መንግስቱ ለማ አገላለፅ ‹‹አንጋፋ እና ወጣት ሰም እና ወርቅ ሆኑ››። ከብዙ ውይይት እና መማማር በኋላም ወጣቱ በቅኔ ትምህርቱ ‹ስለተመረቀ› በአንጋፋው መኖርያ ቤት የምሳ ግብዣ ይደረግለታል። በዚህም ቀድሞ ከነበረው የቅኔ ችሎታ እና ተሰጥኦ ወደ ሌላ ደረጃ እንዲሸጋገር አንጋፋው ይረዳዋል።


የመጣጥፉን ታሪክ የተለያየ ሰው በተለያየ መንገድ ሊተነትነው እና ሊመረምረው ይችላል። ጽሑፉን በሶስት ምዕራፎች ከፋፍሎ ያተመው ‹ታዛ› መጽሔት የመጀመርያው ክፍል (መስከረም 2010) የተስፋዬ ገሠሠን ሀሳብ ጠቅሶ ‹‹ይህ ፅሁፍ የመንግስቱ ለማ ኑዛዜ እንደሆነ ታውቃላችሁ?›› ብሏል። አንደኛው የመመልከቻ መነፅር ይህ ሲሆን ምናልባትም መንግስቱ ለማ በትምህርት እና በህይወት ያካበቱትን እውቀት ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍን አጥብቀው የሚሹ ሰው በመሆናቸው የዚህን ፅሁፍ ሀሳብ ከዚህ አንፃር መመልከት ይቻላል።
መንግስቱ ለማ ጥንታዊ ወይም ሀገራዊ ቅርስ የሆኑ ባህሎች እና ተግባራት ተረስተው እንዳይቀሩ እና ‹ዘመንኩ› ከሚለው ትውልድ ጋር ሳይቃቃሩ ምናልባትም ዝመናውን አግዘው ሊሄዱ ይችላሉ የሚል እምነት እና ተግባር እንደነበራቸው ከዚህ ፅሁፍ ባሻገር ሌሎች ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። በ1953 ዓ.ም. ‹‹የአባቶች ጨዋታ›› (ገጽ 1) አሰኝተው ባሳተሙት መጽሐፍ መግቢያ ላይ እንዲህ የሚል ሀሳብ አስፍረው ነበር።


ከጨዋታዎቹ አብዛኞቹ ባገራችን ሽማግሌዎች ዘንድ የታወቁ እና የቆዩ ናቸው እንጂ የአዲስ ልብ ወለድነት ጠባይ ያላቸው አይደሉም። ስለዚህ ቁጥራቸው ‹የአባቶች ቅርስ› ከሚባለው ነው ለማለት ይቻላል። በጽህፈት መመዝገባቸውና ለአዲሱ ትውልድ መተላለፋቸው ተገቢ የሆነበትም ምክንያት ይኸው ነው። የአባቶችን ቅርስ ለዛሬው እና ለነገው ትውልድ የማስተላለፉ ተግባር አስፈላጊ መሆኑን ስለሀገራችን ጠቅላላ ጉዳይ የሚያስቡ ተመልካቾች ሁሉ (የሚረዱት) … ነው።
በራሳቸው ግለ ታሪክ መጽሐፍ (1988፣ ገጽ 15) ‹መንደርደርያ› ምዕራፍ ላይም ‹‹ሰው ሀምሳ ዓመት ከሆነው በኋላ አንድ አይነት ግለ-ታሪክን የያዘ (Authobiographical) የሆነ ፅሑፍ ለተከታዩ ትውልድ ማቆየት እንዳለበት በመገንዘብ አንድ ጥሩ ደብተር ገዛሁ።›› ይላሉ። በዚሁ ሀሳብ ላይም ለማከል ያህል ተስፋዬ ገሠሠ ‹ባለ ላምብሬታው ደራሲ› በተሰኘው መጣጥፉ የመንግስቱ ለማን ባህላዊ የሆኑ እውቀቶች እና ተግባራት መጠበቅን አስመልክቶ ‹….እነዚህ ተግባራቱ ሊጠፉ የሚችሉ ታላላቅ ቅርሶችን ለአሁኑ እና ለመጪው ትውልድ ያተረፉ በመሆኑ ከፈጠራ ስራዎቹ ጎን ለጎን ከፍተኛ ክብር እና ግምት የሚሰጣቸው ክንዋኔዎች ናቸው› ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።


ምንም እንኳ መንግስቱ ለማ የአባቶችን ትምህርት እና ልምድ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ እጅጉን ቢተጉም በአመለካከታቸው ግን ‹ተራማጅ› ከሚባሉት ወገን ነበሩ። በፅሁፎቻቸውም በግል ኑሯቸውም (የተለያዩ መረጃዎች እንደሚያሳዩት) ከቀደመው ትውልድ የሚጠቅመውን ዕውቀት እና ተግባር በመውሰድ ከቀጣዩ አዲስ ትውልድ ጋር አብሮ ማስኬድ እንደሚቻል ያምኑ ነበር። ይህንንም በተመለከተ የቅርብ ወዳጃቸው የነበሩት የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት


“መንግስቱ ለማ በጥንታዊቷ እና በአዲሲቷ ኢትዮጵያ መካከል እጅግ አስፈላጊ እና ጠቃሚ ማያያዣ ቀለበት ነበር ለማለት እደፍራለሁ። የመጀመርያ ትምህርቱን ከጥንቱ የሀገሪቱ የቤተክርስቲያን ትምህርት ቤቶች የቀሰመ እንደመሆኑ ህይወቱን በመላ ለክላሲካል የግዕዝ ቋንቋ እና በአጠቃላይም ለኢትዮጵያ ጥናት አውሏል ለማለት እደፍራለሁ። ይህም ቢሆን ግን መንግስቱ በሌላ ጎኑ ለማህበራዊ ዕድገት እና መሻሻል ራሱን የሰጠ ዘመናዊ ኢንተሌክቿል ነበር”


በመንግስቱ ለማ ግለ-ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ የሚል ጽሑፍ አስፍረዋል፡-
ከሁሉም ነገር በላይ ግን በኔ አስተሳሰብ መንግስቱ ለማ በጥንታዊቷ እና በአዲሲቷ ኢትዮጵያ መካከል እጅግ አስፈላጊ እና ጠቃሚ ማያያዣ ቀለበት ነበር ለማለት እደፍራለሁ። የመጀመርያ ትምህርቱን ከጥንቱ የሀገሪቱ የቤተክርስቲያን ትምህርት ቤቶች የቀሰመ እንደመሆኑ ህይወቱን በመላ ለክላሲካል የግዕዝ ቋንቋ እና በአጠቃላይም ለኢትዮጵያ ጥናት አውሏል ለማለት እደፍራለሁ። ይህም ቢሆን ግን መንግስቱ በሌላ ጎኑ ለማህበራዊ ዕድገት እና መሻሻል ራሱን የሰጠ ዘመናዊ ኢንተሌክቿል ነበር።


ይህ ‹ዕውቀት እና ልምድ ለተተኪው ትውልድ› የተሰኘ ጽሑፍም የዚህ ልፋት ውጤት ይመስላል። ከአንደኛው ትውልድ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ዕውቀትን ለማስተላለፍ እና ለማሸጋገር ከሚደረግ ጥረት የመነጨ፣ የተስፋዬ ገሠሠን ሀሳብ ለመድገም ‹ኑዛዜ› ነው። በመሆኑም ይህ ጽሑፍ በዋናነት በተለይ በአሁን ሰዓት ላለው የኪነጥበብ መንገዳችን የሚከተሉትን ዋና ዋና አንኳር ሀሳቦች ያቀብላል ብዬ አስባለሁ።


ሀ) ባህላዊ እና ዘመናዊ፤ ሀገራዊ እና ውጫዊ
የሀገራችን ሰፊው የስነፅሁፍ ታሪክ ሁለት መልክ አለው። አንደኛው ሀገራዊ ሌላኛው ውጫዊ። ውጫዊው መልኩ በተለያዩ ጊዜያት እና በተለያዩ ምክንያቶች ከሌሎች ሀገራት የተቀበልናቸው ስልቶች እና መንገዶች ናቸው። በተለይ እኔ በተማርኩበት የቴአትር ጥበብ ሙያ፣ በአንድ በኩል ሰፊ የሆነ የክዋኔ ጥበብ ባህል ያለን ህዝቦች ሆነን በሌላ በኩል ደግሞ ሙሉ በሙሉ የአውሮፓ አሰራር እና ቅርፅ የያዘ የቴአትር ጥበብ የቴአትር ቤቶቻችንን ከብቦ እንመለከታለን። ምንም እንኳ የሀገራችንን ባህል እና ክዋኔ በቴአትራችን ለማካተት ታላላቅ እና ወጣት ባለሙያዎች በተለያየ ጊዜ ቢጥሩም በቂ ግን አይደለም።


ይህ የመንግስቱ ለማ ጽሑፍም ይህንን ሀሳብ በሚገባ ያነሳል። የቆየውን ባህል እና ስርዓት ከአዲሱ ወይም ‹ዘመናዊ› ከምንለው ጋር በማዳበል የራስን ማንነት መቅረፅ እንደሚቻልም ይመክራል። በተለይ በድርሰቱ ውስጥ የተቀረፀው ወጣቱ ገጣሚ የተለያዩ የዓለማችንን ፀሀፊዎች ስራ አላነበብኩም ማለቱን ተከትሎ በአንጋፋው ደራሲ እንዲህ የሚል ምክር ይለገሰዋል።


አንድ ደራሲ መጀመርያ፤ የገዛ ሀገሩን የስነ ድርሰት ገፅታ ማወቅ፣ ሁለተኛ የዓለምን ስነ ድርሰት ገፅታ መገንዘብ አለበት። ይህን ለማድረግ ሲፈልግ ያገርንም ሆነ የውጭ ሀገርን የስነ ድርሰት ከብዙ በጥቂቱ ምርቱን ከግርዱ ለይቶ ምርጥ ምርጡን ለመቅመስ እና ለማጣጣም ብሎም ለመመገብ የማይችልበት ምክንያት የለም።
ይህም ሀሳብ መንግስቱ ለማ የሀገራቸውን ባህል እና ዕውቀት የሚወዱ እና የሚያከብሩ ብቻ ሳይሆን አዲስ ባህል እና ዕውቀትም ቢሆን ጠቃሚ የሆነውን ለይቶ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን የሚመክሩ እና በተግባርም በስራዎቻቸው እንደሚታየው የሚተገብሩ መሆናቸውን ያሳያል። የኢትዮጵያን ባህል ከሌላው ዓለም ጋር ወይም በጥንታዊው ቅርፅ ላይ ተራማጅ አስተሳሰቦችን ማገናኘት ብቻ ሳይሆን በተለያየው የኢትዮጵያ ቋንቋ መሀል አዲስ አይነት የኪነጥበብ መንገድ መክፈትም እንደሚቻል ይመክራሉ። አንጋፋው እና ወጣቱ ደራሲ በሰፊው መነጋገር እና መማማር ከጀመሩ በኋላ ወጣቱ ገጣሚ ‹‹‹ቅኔ› ከመውደዱ የተነሳ እንደ ክፍለ ዮሀንስ ያለ ቅኔ በግዕዝ ሳይሆን በአማርኛ ቋንቋ፣ በሀይማኖታዊ ሳይሆን በዓለማዊ ተራማጅ ርዕስ አዲስ ለመግጠም ጓጓ።›› ሲሉ ሊሆን የሚችል ሀሳባቸውን ያቀብላሉ።


በተለይ የግንኙነት መረብ እጅግ በበዛበት እና ሉላዊነት በተንሰራፋበት በአሁኑ ጊዜ የራስን ማንነት እና ቀለም ይዞ መገኘት እጅግ አስፈላጊ እና አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ለቁጥር የሚያታክቱ መረጃዎች በየሰኮንዱ በሚዘንበቡት በዚህ ጊዜ የቀደመውን የአባቶችን ታሪክ እና ቅርስ ጠብቆ ማቆየት ለጥያቄ የማይቀርብ የእኔ እና የዘመነኞቼ የስራ ግዴታ ነው።


ለ) የጽሑፍ ጥበብ
የጽሑፍ ጥበብን ማለትም ልቦለድን፣ ስነ ግጥምን ወይም ቴአትርን በተመለከተ የተለያዩ የሀገራችንም ሆነ የውጪ ምሁራን ብዙ ብዙ ንድፈ ሀሳቦችን አስቀምጠዋል። የተለያዩት ንድፈ ሀሳቦችም በልዩ ልዩ መንገድ ጥቅም ላይ ውለዋል። በተለይም ደግሞ መንግስቱ ለማን ጨምሮ የብዙ የታላላቅ ደራስያን ልማድ በሆነው እና በተለያዩ ባለሙያዎችም የሚደገፈው አንድ የፈጠራ ጽሑፍ ወደ


“አንድ ደራሲ መጀመርያ፤ የገዛ ሀገሩን የስነ ድርሰት ገፅታ ማወቅ፣ ሁለተኛ የዓለምን ስነ ድርሰት ገፅታ መገንዘብ አለበት። ይህን ለማድረግ ሲፈልግ ያገርንም ሆነ የውጭ ሀገርን የስነ ድርሰት ከብዙ በጥቂቱ ምርቱን ከግርዱ ለይቶ ምርጥ ምርጡን ለመቅመስ እና ለማጣጣም ብሎም ለመመገብ የማይችልበት ምክንያት የለም”


አንባቢ ወይም ተመልካች ዘንድ ከመቅረቡ በፊት ደግሞ ደጋግሞ መጻፍን በተመለከተ ብዙ አስተያየቶች በየጊዜው ተነስተዋል። በተለይም ደግሞ በሀገራችን የቴአትር ጥበብ መሪ ሚና ባላቸው መንግስቱ ለማ ተደጋግሞ ይነሳ ነበር። በቴአትር ትምህርታችን ወቅት መንግስቱ ለማ ለተማሪዎቻቸው አበክረው ያስተምሩት ነበር የሚባለውን ‹‹ቴአትር ይፃፃፋል እንጂ አይፃፍም›› መርህ ከተለያዩ መምህራኖቻችን በተደጋጋሚ ሰምተነዋል። ተምረነዋል። ይህ ሀሳብ በተለያየ መንገድም መታየት ይችላል። አንድም የኪነጥበብ ስራ (የመጨረሻም ባይኖረው) ለደራሲው የመጨረሻውን ጥራት ሊያጎናፅፍ የሚችለው ደግሞ ደጋግሞ በመስራት እና በመተንተን ነው። ትንታኔውም ስራውን ከብዙ ማዕዘናት ለመመርመር እና ለመመልከት ዕድል የሚሰጠው ሲሆን ለአንባቢ ወይም ለተመልካች በቀረበም ጊዜ ግሩም የኪነጥበብ ዕርካታን ያጎናፅፋል። በሌላ በኩል አንድን የኪነጥበብ ስራ ደጋግሞ መጻፉ የደራሲውን የመጻፍ ክህሎት ያሳድጋል። በተደጋጋሚ በሚፅፍበት ጊዜ የስራውን ጥራት እያሳደገ ግላዊ ክህሎቱንም ያበረታል።


‹ዕውቀት እና ልምድ ለተተኪው ትውልድ› በተሰኘው ጽሑፍም መንግስቱ ለማ ይህንን ሀሳብ ይበልጥ ሲያጠናክሩት እናነባለን። አንጋፋው ወጣቱን ደራሲ አንድን ግጥም ስንት ጊዜ እንደሚፅፈው ይጠይቃል። ወጣቱም ‹‹አንድ ጊዜ ነዋ። እኔ አንድ ግጥም አንድ ጊዜ ነው የምፅፈው። መሰረዝ መደለዝ የሚባል ነገር አልወድም። በንፁሕ ወረቀት ላይ ገና ሲወጠን ጀምሮ ቁልጭ ብሎ ሲሰፍር ነው ግጥም ደስ የሚለኝ።›› ይሄኔ ‹‹አንጋፋው የመጣበትን ሳቅ ገታ። ‹አንደኛ ረቂቅ፤ ሁለተኛ ረቂቅ፤ ሶስተኛ ረቂቅ የለህማ?›› ሲል ይጠይቀዋል። ይህ ጥያቄ በታሪኩ የመጨረሻ ክፍል ባግባቡ መልስ ያገኛል። ወጣቱ ሰፊ ከሆነው የአንጋፋው ህይወት እና ልምድ ከቀሰመ በኋላ ቀድሞ አንድ ጊዜ ብቻ የጻፋቸውን ግጥሞች መልሶ ተመልክቶ በአንዳንዶቹ ላይ ይፈርድባቸዋል፤ ለአንዳንዶቹም ‹ይፈርዳል››።


አሁን አሁን በተለይ በግጥም ስራዎች ህትመት ላይ የሚታየው እውነት የዛሬ ሰላሳ ዓመት መንግስቱ ለማ ከጻፉት እውነት የባሰ እንጂ የተሻለ አይደለም። ሌላው ቀርቶ በዩኒቨርሲቲ የምናስተምራቸው በጣም ወጣት የኪነጥበብ ተማሪዎቻችን መሰረታዊ የሆኑ የአጻጻፍ ስልቶችን ባግባቡ ሳይጨርሱ አንድ ጊዜም ለማይሞላ ፋታ የጻፏቸውን ‹ግጥሞች› እና ሌሎች ስራዎች ድንገት ታትመው ማየት አዲስ ነገር አይደለም። ግጥሞቹም ሆነ ልዩ ልዩ የኪነጥበብ ውጤቶቹ መታተም እና ለዚህም መብቃታቸው እጅግ ደስ የሚያሰኝ ተግባር ቢሆንም በንባብ እና በህይወት ልምድ ያልተገራ በመሆኑ የወጣቶቹን ተሰጥኦ በተገቢው መንገድ ማውጣት እና ብስለታቸውንም ለማሳየት ሲሳነው ይስተዋላል። የህትመት መንገዱ ዛሬ ዛሬ እጅግ ቀላል ስለሆነ ብቻ ሁሉም እየተነሳ ማሳተሙ ቀደም ብሎ መንግስቱ ለመምከር የሞከሩትን አለመስማት ይመስላል …ምክንያቱም ‹ቴአትር.. (በሰፊው ደግሞ የኪነጥበብ ስራ) ይጻጻፋል እንጂ አይጻፍምና›። ወጣቱ ገጣሚም የተሳሳተው እንደ መንግስቱ ለማ አባባል ‹‹ግጥሙን በፈጠራ ግልቢያ የሽምጥ በመጻፉ ሳይሆን ከጻፈው በኋላ በምዘናዊ ቴሌስኮፕ መነፅር ሳይመረምረው በመቅረቱ ነው።››


በመሆኑም ቴክኖሎጂ ሃሳብን እጅግ እየደገፈ እና እያገዘ በሚገኝበት በዚህ ዘመን፣ ቴክኖሎጂው ስለተገኘ ብቻ ተሯሩጦ ወደ ህትመት መሄድ የገበያ ጩኸት ከማሟላት የተሻገረ ተግባር አይኖረውም። ከዚህም ባሻገር በዘመናችን አስቸጋሪ ሆኖ የታየው መጻሕፍትን ለማሻሻጥ የሚሰጡ የመጻሕፍት የጀርባ አስተያየቶች (blurbs) እና የመግቢያ ጽሑፎች ለመንግስቱ ለማም ሀሳብ ሆኖባቸው እንደነበር ያሳያል። ወጣቱ ገጣሚ አንጋፋውን እንዲህ ይጠይቀዋል፣
‹‹አሁን በቅርቡ የማሳትመው የቅኔ መጽሐፌ መጀመርያ ላይ የሚውል አምስት ገፅ ያህል መግቢያ እርስዎ የታወቁ አንጋፋ ደራሲ እንደመሆንዎ ቢጽፉልኝ ለገበያው በጣም ይረዳኝ ነበር።››


ሽፋኖቻቸው የሚያምሩ፣ ርዕሶቻቸው ከመማረክ አልፈው ለማንበብ እጅግ የሚያጓጉ እና የሚያስደነግጡ የኪነጥበብ ስራዎች በህዝቡ ዘንድ ከሚታወቁ ሰዎች አስተያየት ጋር ተዳብሎ ገበያውን አጥለቅልቆ ማየት የተለመደ ነው። አሁን አሁንማ የሚታወቁም ይሁን የማይታወቁ ሰዎች አስተያየት ሳይታከልበት መጻሕፍትን ማሳተም የተከለከለ እስኪመስል ድረስ እጅግ የበዙ የህትመት ውጤቶች ላይ መመልከት ልማድ ሆኗል። በርግጥ የተለያዩ ባለሙያዎች ለልዩ ልዩ የስነጽሑፍ ስራዎች አስተያየት መስጠታቸው እና አንባቢን ማበረታታቸው የሚገባ ቢሆንም ሲከፍቷቸው ባዶ ለሆኑ የኪነጥበብ ስራዎች ግን በህዝብ ዘንድ በልዩ ልዩ ሙያ ያገኙትን ዝና እና ተቀባይነት በመጠቀም ደራሲውን ለመጥቀም አንዳንድ ጊዜም ባላነበቡት ጉዳይ አንባቢን ማሳሳት ግን የተገባ ተግባር አይደለም። ይህ ሀሳብ ምንም እንኳ በዛሬው የኪነጥበብ ኢንዱስትሪያችን እጅግ አሳሳቢ ነገር ቢሆንም መንግስቱ ለማ ግን ከዛሬ ሰላሳ ዓመት በፊት አሳሳቢነቱን ሳያወጉን አላለፉም።


“አንዳንዱ አይነት ግጥም ይመዘናል። የሚከነዳም ሞልቷል።›› ይላሉ መንግስቱ ለማ። በሰፊው የኪነጥበብ ባህርም የሚመዘኑ እና የሚከነዱ የኪነጥበብ ስራዎች ሞልተዋል። ይህንን ደግሞ ስፋቱን ተገንዝቦ በሚገባ የሚመረምር እና የሚተነትን የሂስ ተግባር ሊኖረን ይገባል። ይህ የሂስ ተግባር ምርቱን ከግርዱ እየለየ መልካሙን ስራ እንድንከተል ያልሆነው ደግሞ እንዲሻሻል ይረዳል። የመንግስቱ ለማም ሀሳብ ይህንን ሰፊ ምኞት ያዘለ ነው። ጠንካራ ሀያሲ ያለው ኪነጥበብ ሁልጊዜም ቢሆን ለታዳሚው መልካም ስራን ማቅረብ ሙያው ሆኖ ይቀራልና።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top