ቀዳሚ ቃል

ቀዳሚ ቃል

ውድ አንባቢያን፣ በታዛ ቁጥር 7 ከምታገኟቸው መጣጥፎች መካከል ለጽሑፍ አበርካቾች ያቀረብነው ጥሪ ይገኝበታል። ይኸውም ባለፉት ስድስት ተከታታይ ጽሑፎቹ ስለፖለቲካ ባህላችን ገፅታ ሲያስነብበን የነበረው የሱልጣን አባዋሪ ጽሑፍ መጠናቀቁን ተከትሎ ነው። ስለዚህም የታሪክና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን፣ በፖለቲካው መስክ የተሰማሩ ወይንም ፖለቲከኛ የነበሩ፣ ወይንም ከልምድና ከንባብ ራሳቸውን ያስተማሩ ወገኖች በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ ሃሳባቸውን ያጋሩን ዘንድ ተጋብዘዋል።

መስፍን ማሞ ተሰማ ከሃምሳ አምስት ዓመታት በፊት የታተመውን የጄኔራል አቢይ አበበን መጽሐፍ ያስቃኘናል። በዚሁም ጄኔራሉ በወቅቱ ያነሷቸው ጉዳዮች ምን ያህል ከዚህ ዘመን የሃገራችን ችግሮች ጋር የተመሳሰሉ እንደሆኑ እንገነዘባለን። “አሳቢው መንግስቱ ለማ” የሚለው የዶ/ር ፈቃደ አዘዘ ጽሑፍ ደግሞ የባለታሪኩን ቀደምት ሥራዎች እያነሳ የአስተሳሰብ ደረጃቸውን ያሳየናል።

ባለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ የሙዚቃ መድረክ ጎላ ብለው ከታዩት ሙያተኞች መካከል የጃኖ ባንዶቹ ድምፃውያንና ሙዚቀኞች ይገኙባቸዋል። በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ ሥራዎቻቸውን እያቀረቡ በርካታ አድናቂዎችን ያተረፉት እነዚሁ ባለሙያዎች ዛሬ ግን አንድ ላይ አይደሉም። ሙዚቀኞቹና ድምፃውያኑ የየራሳቸውን የተለያየ መንገድ ይዘዋል። የታዛ ዘጋቢ ከባንዱ አባላት አብዛኞቹንና የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በሽምግልና ከተሳተፉት መካከል አንዱን አነጋግሯል። ሌሎች በርከት ያሉ ጽሑፎችንም ይዘናል።

 በመጨረሻ እስከዛሬ ከአንባቢያን ከደረሱን መልዕክቶች መካከል የተወሰኑትን በዚህ እትም ሰብሰብ አድርገን ለማቅረብ ሞክረናል። የተመረጡትም ከሞላ ጎደል የቀሩትን ይወክላሉ ብለን እናምናለን። ብዙ የምናሻሽላቸው ነገሮች እንዳሉ ግልጽ ነው። የስርጭቱ ጉዳይ አንዱና ዋናው ችግር ነው። አብዛኞቹ አስተያየት ሰጪዎች ከአዲስ አበባ ወይም ከአካባቢው መሆናቸው ይህንኑ አመላካች ነው። መጽሔታችን በሁሉም ክልሎችና በከፍተኛ የትምህርት ተቋሞቻችን ትዳረስ ዘንድ እየሰራን ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለአዲስ አበባ አንባቢያን ከአዟሪዎች በተጨማሪ መጽሔታችን በሻማ ቡክስና በሸዋ ሱፐር ማርኬት (Shopping Center) ቅርንጫፎችም ትገኛለች። በክልሎች ለሚገኙ አንባቢያን ደግሞ በሜጋ ማከፋፈያ ድርጅት በኩል ማግኘት የምትችሉ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን። አንዳንድ አንባቢያን እንደጠቆሙንም በተቻለ መጠን የምንይዛቸው ጽሑፎች መላ ኢትዮጵያን የሚዳስሱ እንዲሆኑ ለማድረግ እየተጋን ነው። በዚህ ረገድ የእናንተ የውድ አንባቢያን ድጋፍና ትብብር እንደማይለየን ተስፋ እናደርጋለን።

 እንደተለመደው ጻፉልን፣ ሃሳብ አስተያየታችሁን አካፍሉን።

መልካም ንባብ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top