ዘባሪቆም

‘ሰርፕራይዝ !’

በአንድ አገርኛ ተከታታይ ድራማ “ሰርፕራይዝ” የምትል ህፃን ልጁን በአማርኛ “የምስራች” እንድትል የሚያርም አባት፤ እርሱ ራሱ ቃሉን እንደወረደ ሲጠቀም ሰማሁት። ይህን በቁምነገር ያጫወትኩት አንድ ወዳጄ ታዲያ “እርሱንም አባቱ ቢሰማው ኖሮ ያርመው ነበር” ሲል ቀለደብኝ። ነገሩን ቆይቼ ሳጤነው ግን ምላሹ ከቀልድነት ያለፈ እውነታ እንዳለው ተረዳሁ።

‘ሰዎች ሁልጊዜም ወጣቶችን ይወቅሳሉ’ በሚል ርዕስ ቢቢሲ ያወጣው የቅርብ ጊዜ ጽሑፍ በየዘመኑ የነበረ ወጣት “ራስ ወዳድ፣ አዋቂ ነኝ ባይ ግን ሰነፍ፣ አብዝቶ የሚመኝ በዚያው ልክ ደግሞ የሚያማርር” ወዘተ ከሚል ተመሳሳይ ወቀሳ እንደማያመልጥ 2ሺህ ዓመት ወደኋላ ተጉዞ በማስረጃ ያብራራል። ለምሳሌ ‘ሃሳብን የመግለፅ ችግር: የዘመኑ ወጣቶች ውድቀት!’ በሚል ርዕስ በ1936 (እ.አ.አ) የወጣ አንድ ጽሑፍ ብዙ ወጣቶች ስሜታቸውን በቃልም ሆነ በጽሑፍ መግለፅ እንደሚቸገሩ ሲዘግብ በተመሳሳይ በ2014 ‘Why can’t college students write anymore?’ (የኮሌጅ ተማሪዎች ለምን መጻፍ ተሳናችው?) በሚል ርዕስ የወጣ የ‘ሳይኮሎጂ ቱዴይ’ ጽሑፍ የወጣቶች የቋንቋና ሃሳብን የመግለፅ ክህሎት ከቀደሙት ዓመታት ማሽቆልቆሉን ይገልፃል።

 ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የለት ኑሯችን አካል የሆነው ‘ሰርፕራይዝ’ በአማርኛ “የምስራች” ከሚለው የባህላችን አንድ ገፅታ ጋር ቅርበት ቢኖረውም የሚለይበት ጉልህ ባህሪም አለው። የአማርኛችን ‘የምስራች’ የደስታ መልዕክት ማስተላለፊያ ሲሆን ‘ሰርፕራይዝ’ የሚለው ቃል ካሉት ትርጉሞች መካከል በ Merriam Webster Web Dictionary አገላለፅ ‘an attack made without warning’ (ያለማስጠንቀቂያ የሚደርስ ጥቃት) የሚል ይገኝበታል። ይህን ትርጓሜ እንደቃሉ በቀጥታ የወረስነው እንደሆን ደግሞ እስራኤል ፍልስጤምን በድንገት/በስውር የመደብደቧ ዜና “በቦምብ ሰርፕራይዝ አደረገች” ተብሎ ላለመዘገቡ ዋስትና አይኖረንም። የሌባ ጆሮ ይደፈንና በአንድ ጎደሎ ሌሊት ጨለማን ተገን አድርጎ በገጀራ ሰው የሚያድን ቀማኛ እጅ ላይ ወደቁ እንበል። ልብስዎን አስወልቆ ከፈተሸ በኋላ የረባ ነገር ሲያጣ “ሰርፕራይዝ ላደርግዎ ነበር” ብሎ በፈገግታ የሚሸኝ አይናውጣ ወንበዴ በቅርብ ላለመምጣቱስ ምን ማረጋገጫ አለን?

የ‘ሰርፕራይዝ’ን ትርጓሜ ልቀትና ርቀት ለማሳየት በናትና ልጅ መካከል የተቀለደች ቀጭን ምሳሌ ልጨምር። ልጅ እናቱ ወንድም እንድትወልድለት ይጠይቃል። እናት አዎንታዋን ገልፃ ነገር ግን አባቱ ከሃገር ስለወጣ እስኪመለስ መጠበቅ እንዳለባቸው ትነግረዋለች። የዘንድሮ ልጅ መልስ አያጣም:- “በቃ ሲመጣ ለምን ‘ሰርፕራይዝ’ አናደርገውም?”

 መጪው የሚያዚያ (ኤፕሪል) ወር ሲታሰብ ‘ኤፕሪል ዘፉል’ አብሮ ይታወሳል። ይህ ደግሞ ለዚህ አይነት ድርጊት የተመቸ አጋጣሚ ከመሆኑ ጋር ጥንቃቄ እንዳያጥረን በአልበርት ካሙ ተወዳጅ ድርሰት ‘ዘ ስትሬንጀር’ ውስጥ የተጠቀሰ የአንድ አስተማሪ ታሪክ አንስቼ ልሰናበት።

በቀድሞዋ ቼኮዝሎቫኪያ አንድ መንደር ውስጥ ነዋሪ የነበር ግለሰብ የህይወት እድሉን ለማቃናት ወደ ውጪ ሃገር ይሰደዳል። ከ25 ዓመታት በኋላ ሃሳቡ ሞልቶ፣ ሃብት አካብቶ፣ ሚስት አግብቶና ልጆች አፍርቶ ቤተሰቦቹን ለማየት ወደ ትውልድ አገሩ ይመለሳል። እናትና እህቱ በበኩላቸው በዚያው በቀያቸው አነስተኛ ሆቴል ከፍተው ይተዳደሩ ነበር። ወጣቱ ቤተሰቦቹን ቀጥታ ከማግኘት ይልቅ ‘ሰርፕራይዝ’ ሊያደርጋቸው በማሰብ ልጆቹንና ሚስቱን ሌላ ሆቴል አሳርፎ እናቱ ሆቴል ውስጥ በሌላ ስም በእንግድነት አልጋ ያዘ። እናቱና እህቱ ጨርሶ አላወቁትም።

በዚያን እለት ማታ እራት ላይ በጣም ብዙ ገንዘብ እያወጣ የሃብቱን ልኬት ሲያስጎበኛቸውና ሲያስጎመዣቸው አምሽቶ ወደ ማረፊያ ክፍሉ ሄደ፤ በህይወት ግን አልተነሳም። የገዛ እናትና እህቱ ቀጥቅጠው ገድለው ንብረቱን ከዘረፉ በኋላ ሬሳውን ወንዝ ውስጥ ጣሉት። በማግስቱ ጧት ሚስቱ ወደ ሆቴሉ በማቅናት የባሏን ማንነት ስታሳውቅ የእናቱና የእህቱ ምላሽ ራሳቸውን ማጥፋት ብቻ ነበር።

 በሉ…

 ከእንዲህ ያለው ጉድ ጠብቆ፣

 ከድሜና ጤናው መርቆ፣

 ከክፉው እየታደገን፣

 ፈጣሪ ‘ሰርፕራይዝ’ ያድርገን

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top