ስርሆተ ገፅ

“ራሴን የማርቀው ዝነኛ ፊትእንዳይኖረኝ ነው” የቴያትር ደራሲና አዘጋጅ መዓዛ ወርቁ

የቴያትር ደራሲና አዘጋጅ መዓዛ ወርቁ በሥራዎቿ ጉልህ ባለሙያ ናት። በኑሮ ይትባህሏ ደግሞ የግል ነፃነቷን ስለምታስቀድም ከአደባባይ ከለል ብሎ መኖርን ትመርጣለች። በአሁኑ ጊዜ በፋና ቴሌቪዥን በተከታታይ በመቅረብ ላይ የሚገኘውን ‹‹ደርሶ መልስ›› ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በመፃፍና በማዘጋጀት ላይ ትገኛለች። በእንግሊዝኛ ቋንቋ የደረሰችውን ‹‹ዴስፐሬት ቱ ፋይት›› ተውኔት ‹‹ከሰላምታ ጋር›› በሚል ተርጉማ ለሀገር ቤት ተመልካችም አቅርባዋለች። በዚህ ተውኔቷ በዓለማቀፍ ደረጃ ሽልማት አግኝታበታለች። በአፍሪካ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ መድረኮችም ቀርቧል፤ በብዙ የዓለም ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለመድረክ በቅቷል። ዘጋቢያችን በፈጠራ ሙያዋ ዙሪያ እንደሚከተለው አነጋግሯታል።

 ታዛ፡- ድርሰቶችሽ ሁሉ በተውኔት፣ በራዲዮ ድራማና በተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎች ቅርጽ ነው ወደ ህዝብ እየደረሱ ያሉት፤ ለምን በዚህ ዘርፍ ብቻ አተኮርሽ?

መዓዛ ወርቁ፡- ከልጅነቴ ጀምሮ በተለያየ መንገድ ራሴን ስገልጽ ቆይቻለሁ። በውዝዋዜ (ዳንስ) ራሴን ገልጬ አውቃለሁ። በሥዕል ራሴን ገልጬ አውቃለሁ። በሂደት በቀለም ትምህርት ገፍቼ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከገባሁኝ በኋላ ደግሞ ያጠናሁት ቴያትር ነው። እንደምታውቀው ቴያትር የሚከወን ጥበብ ነው፤ ከሚከወን ጥበብ ውስጥ ደግሞ አንዱ ድራማ ነው። ይህ ጥበብ በጣም ተመችቶኛል። በግሌም ማንኛውንም ጽሑፍ ስጽፍ ከመተረክ ይልቅ መነጋገር ይቀለኛል። ገጸባህሪዎቼ የሚያስቡትንም፣ የሚናገሩትንም በንግግር ቅርጽ (ዳያሎግ) መግለጽ ይቀለኛል። ይህም ድራማ ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል።

 ታዛ፡- ድርሰቶችሽን ለማዘጋጀት የመጀመሪያ ምርጫሽ ራስሽ ወይስ ሌላ ባለሙያ?

መዓዛ፡– እኔ በዋናነት የምወደውና የሚመስጠኝ ሥራ ደራሲነት ነው። ስለዚህ ድርሰት ጽፌ አንድ ጥሩ አዘጋጅ ተቀብሎኝ ቢያዘጋጀው ደስ ይለኛል። እንዳለመታደል ሆኖ ብዙ ጊዜ (በተወሰነገጠመኝ መደምደሜ አይደለም) አንድ ድርሰት እጽፍና ያንን ሥራ ወደ መድረክ ማምጣት ወይም ደግሞ ወደ ተመልካች ማቅረብ ስፈልግ፣ ለዛ ሥራ የማጫቸው አዘጋጆች እኔ በምፈልገው መጠን ሳይሆኑልኝ ሲቀሩ ራሴው ብጨርሰው ይሻላል ብዬ እገባበታለሁ። ይህም በውዴታ ሳይሆን በድፍረት ነው። ስለዚህ፣ ብዙ ጊዜ የራሴን ሥራዎች ራሴ ወደ ማዘጋጀቱ አዘንብያለሁ። ይህም ሆኖ ግን ሌላ አዘጋጅ ያልነካው ሥራ የለኝም። ከሬድዮ ሥራዎቼ በስተቀር፣ የቴሌቪዥንም ሆነ የመድረክ ሥራዎቼን እንደገና ተቀብዬ ነው የሰራሁት። ለምሳሌ በራሴ ሥራዎች ላይ አልተውንም፤ ሌላ ሥራ ብሰራ ደስ ይለኛል። እኔ ከፃፍኩኝ በኋላ ሌላ ሰው ቢረከበኝ በጣም ደስተኛ ነኝ። ግን ድርሰቱ የሚጠይቀውን አቅም፣ የምናብ መግባባት፣ ጊዜ እና ሙያዊ ‹‹ዲሲፕሊን›› ያለውን አዘጋጅ ለማግኘት ብዙ አልታደልኩም።

ታዛ፡- የሌሎች ደራሲያን ስራዎችን አዘጋጅተሸ ታውቂያለሽ?

 መዓዛ፡- ሬድዮና ቴሌቪዥን ላይ አዘጋጅቼ አውቃለሁ። በተለይ የሬድዮ ድራማዎችን በብዛት አዘጋጅቼ አውቃለሁ። የመጀመሪያ ስራዬ እንደውም የሌላ ሰው ድርሰት ማዘጋጀት ነበር። ‹‹አቋራጩ›› የሚል ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ነበር። የመጀመሪያ የቴሌቪዥን ሥራዬ እሱ ነው። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተላለፈ ድራማ።

ታዛ፡– ብዙ ጊዜ ለድርሰትሽ የሚሆኑ ሀሳቦችን ከየት ነው የምታገኝው? በምንስ ትነቃቂያለሽ?

መዓዛ፡- ከመኖር ነው ሃሳቦችን የማገኘው። ግን ደግሞ በውስጡ ንባብ አለበት፣ ጥናትም አለበት፣ የራሴ ምልከታ አለበት፣ የሰዎች ልምድም አለበት፣ የራሴም ልምድ አለበት። ድርሰት ውስጥ እነዚህን ሁሉ ታገኛለህ። ግን ለመፃፍ ‹‹ኢንስፓየር›› የሚያደርግሽ ላልከኝ ህይወትን ስኖራት፣ አካባቢውን ሳየው፣ ማህበረሰቡን ሳየው፣ አገሬን ሳይ ያለው ማህበራዊ ለውጥ፣ የፍትህ መጓደል፣ እኔ ውስጤን የሚሰማኝ ነገር፣ ትክክል አይደሉም የምላቸው ነገሮች ብዙ ጊዜ የጽሑፎቼ መነሻ ናቸው። እዛ ምልከታ ውስጥ ግን የኔ ብቻ ምልከታ አይደለም፤ ጥልቀት እንዲኖረው ስፈልግ የሌሎች ሰዎች ምልከታ፣ ጉዳዩ ላይ የበለጠ ማውራት፣ የበለጠ ማንበብ፣ የበለጠ ጥናት አደርጋለሁ።

 ታዛ፡- በድርሰት ለምታነሺው ርዕሰ ጉዳይ ቅድሚያ ጥናት ታደርጊያለሽ ወይስ በምናብ ጉዞ ነው የምትጽፊው?

 መዓዛ፡- እንደማነሳው ርዕሰ ጉዳይ የሚወሰን ይመስለኛል። አንዳንድ ጊዜ ጥናት የማያስፈልጋቸው ዝም ብለህ በመኖርና በማወቅ የምታቀርባቸው ጉዳዮች አሉ። እዛ ላይ ለድርሰትህ የራስህ ምናብ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የግድ ጥናት የሚያስፈልጋቸው ርዕሰ ጉዳዮችን ልታነሳ ትችላለህ። ካንተ ዕውቀት ወይም ካንተ የሥራ ዘርፍ ውጭ የሆኑና የግድ ጥናት የሚያስፈልጋቸው። ስለዚህ ለነሱ ሲባል ጥናት ይደረጋል። እንዲሁም በማንኛውም በምታነሳውርዕሰ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ጥናት ብታደርግ ያግዝሃል እንጂ ምንም የሚጎዳህ ነገር የለም። ምናብ ግን ዋናው ጉዳይ ነው። አንድን ደራሲ ደራሲ የሚያሰኘው የሚፈጥረው ምናብ ነው። እንጂ ለመመልከትማ ማንኛውም ሰው ማየት ይችላል። ግን ምናብ ስትጨምርበትና በጥሩ የአፃፃፍ ቴክኒክ ስትፈጥረው ነው ድርሰት የሚሆነው ወይም አንድን ደራሲ ደራሲ የሚያሰኘው።

ታዛ፡- በህይወትሽ ድጋሜ የመፈጠር ዕድል ቢሰጥሽ ቅድሚያ የምትከውኝው ምንድን ነው? ወይም በአንቺ ድርሰት ስያሜ ‹‹ደርሶ መልስ›› ዕድል ቢኖርሽ ምን ታደርጊያለሽ?

መዓዛ፡- ይሄ ጥያቄ በፋና ቴሌቪዥን እየታየ ካለው ‹‹ደርሶ መልስ›› ድራማ ጋር ተያይዞ የቀረበ ይመስለኛል። ድርሰትና ዝግጅቱ የኔ ነው። አሁን የቆምኩበት ቦታ ላይ እኔን ያንፀባርቃል ብዬ አስባለሁ። በዚህ ምድር በድጋሚ የመፈጠር ዕድል ባገኝ ‹‹ደርሶ መልስ›› ድራማ ያነሳቸውን ርዕሰ ጉዳዮች፡- በሀገራችን ውስጥ ፍትሐዊነት እና እኩልነት እንዲሰፍን፣ ሙስና እንዲጠፋ፣ ሁሉም ሰው ከኢኮኖሚው ተሳታፊ የሆነበት ማህበረሰብ እንዲፈጠር መትጋትና ሲፈጠርም ማየት እፈልጋለሁ። አሁንም ቢሆን በምችለውና በሙያዬ እየሰራሁ ነው። ስለዚህ ይሄን አስተሳሰብ ወደ ገፀባህርይ ስትቀይረው እኔ ማስበውን እንዲያስቡ ወይም እንዲጠይቁ የፈቀድኩላቸው ናቸው። እየኖሩና እየጠየቁ የሚጓዙ ተገዳዳሪዎች ናቸው። ለምን እንዲህ ይሆናል? ለምን ሙስና ይኖራል? ለምን እኩል አልሆንም? ለምን ሰው በላቡ ብቻ አያድርም? ለምን ሰው የሰው ላብ ይነጥቃል? እንዲህ እንዲህ ዓይነት ጥያቄዎችን ያነሳሉ።

ታዛ፡- በሙያሽ ለኅብረተሰቡ ብዙ አበርክተሻል፤ በማኅበረሰቡ ተለይቶ መታወቅን ደግሞ አትፈልጊም። ለምን?

 መዓዛ፡- ራሴን እማርቀው ዝነኛ ፊት እንዳይኖረኝ ነው።

ታዛ፡- ዝነኛ ፊት ማለት?

 መዓዛ፡- ብዙ ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት ላይ የምታየው ወይም ደግሞ በሶሻል ሚድያ ገፆች ላይ ተለጥፎ እምታየው የተለመደና የታወቀ ፊት እንዳይኖረኝ ጥንቃቄ አደርጋለሁ። ምክንያቱም እኔ በነፃነት መኖር የምፈልግ ሰው ነኝ። አንዳንድ ጊዜ መንገድ እየሄድኩ እንኳን ሰዎች ትክ ብለው እንዲያዩኝ የማልፈልግና በጣም ነፃነቴንና ብቻዬን ያለሁ እስኪመስለኝ ድረስ በመንገድ መሄድ የምፈልግ ሰው ነኝ። ያንን ነፃነቴንና ህይወቴን አሳልፌ ለመስጠት አሁን ዝግጁ ስላልሆንኩ ነው ይህን የማደርገው። ምናልባት ቀስ በቀስ ሰዎች ሊያውቁኝ ይችላሉ፤ አሁን ግን ለስራዬም አይመችም። ምክንያቱም ስራዬ የተለያዩ ቦታዎች ላይ እንድሄድ ያደርገኛል፣ ከተለያዩ ሰዎች ጋር በነፃነት እንዳወራ ያደርገኛል፣ ያለ ይሉኝታ የማነሳውን ጉዳይ እንዳነሳ ይጠይቀኛል፣ እነዚህ ነገሮች ነፃነት ይፈልጋሉ። በነገራችን ላይ ሰዎች ፊቴን ባያውቁትም ስራዬን ግን ያውቁታል። ስለዚህ ብዙ ሰዎች ወይ መልኬን አያውቁትም፣ ወይ ስሜን አያውቁትም፣ ስሜን ለሌላ ሰው ሰጥተውትምይምታታባቸዋል። ለምሳሌ ከአዜብ ወርቁ ጋር ስማችንና ስራችን ስለሚቀራረብ የማምታታት ነገር አለ። ከሌሎች ሰዎችም ጋር የማምታታት ነገር አለ፤ ሌላ ዓይነት ፊት የማሰብ ነገር አለ፤ ነፃነቴን እስካልተጋፋ ድረስ ችግር የለውም።

 ታዛ፡- በድርሰቶችሽ ላይ በምትስያቸው ዋና ገፀ ባህሪያት ላይ የሚታየው ያሰቡትን ነገር ለማሳካት ትጉህ፣ ቁጡ እና ትንታንግ የመሆን ነገር ያንቺ ባህሪይ ተጽዕኖ ይሆን?

መዓዛ፡– ምናልባት በስራዎቼ ውስጥ የኔ ባህርይ ሊንፀባረቅ ይችላል። በተለይ በገፀ ባህርዮቼ ላይ ሊንፀባረቅ ይችላል። ነገር ግን እኔ ምክንያቱ የሚመስለኝ አሁን የምታያቸው ስራዎቼ ውስጥ የምታየው የተቆጡ ፊቶች ሊያሳኩት የፈለጉትን ነገር ለማሳካት የሚጣጣሩ በመሆናቸው ነው። እንዲያም ሆኖ የኔን ስራዎችና ድርሰቶች ከሳቅ ጋር ነው የምታያቸው። መነሻቸው ምሬት ቢሆንም እንኳ ምሬታቸውን ለተመልካች አያጋቡም፤ እየሳቅክ ነው የምታየው። ነገር ግን፣ ብዙ ጊዜ የማነሳቸው ጉዳዮች መነሻቸው እኔ ትክክል አይደለም የምላቸው ጉዳዮች ናቸው። ይሄ ነገር መለወጥ አለበት፣ እንዲህ መሆን አይገባውም ብዬ ከልቤ ተሰምቶኝ የተናደድኩበት ጉዳይ ይሆንና ድርሰቱ ላይ ሲመጣ ገጸ ባህሪያቱም ነገሮቹን ለመለወጥ የሚሰሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ‹‹ደርሶ መልስ›› ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማን በፋና ቴሌቪዥን ልታይ ትችላለህ። እንዲሁም፣ ከዚህ በፊት የነበረውን ‹‹ከሰላምታ ጋር›› ቴያትር እና ሌሎቹንም ስራዎቼን ብታይ፣ የማነሳቸው ጉዳዮች እኔ እንዲለወጡ የምፈልጋቸው፣ ትክክል ያልሆነ ወይም ደግሞ ሚዛናዊ ያልሆነ ግንኙነት ብዬ እማስበው ስለሚሆንና ለተሻለ ለውጥ ስለምሰራቸው ገፀ ባህርያቱ አንድ ቁምነገር ወይም ግብ ለማሳካት የሚተጉ ናቸው። ስለዚህ በጣም ታጋዮች ናቸው። በጣም የነቁም ናቸው። ለስላሳ፣ ለፈስፋሳ፣ የተሸነፉ ምናምን ዓይነት ገፀ-ባህርያት አይደሉም።

ታዛ፡- ‹‹ዴስፐሬት ቱ ፋይት›› የተሰኘ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተፃፈ ተውኔት አለሽ፤ በምስራቅ አፍሪካ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ተወዳድሮና ተመርጦ ለመድረክ በቅቷል። ወደ አማርኛም ‹‹ከሰላምታ ጋር›› በሚል ተርጉመሽ በተለያዩ ቦታዎች ለዕይታ ቀርቧል። ይህ ሥራ ‹‹የእራት ቴያትር›› ተሰኝቶም ነበር። እንደዛ ነው ቴያትሩ?

መዓዛ፡- አንድ ነገር ስትጽፍ እኮ ‹‹ዲነር ቴያትር›› ልጻፍ ብለህ አትነሳም። አንድን ቴያትር ‹‹ዲነር ቴያትር›› የሚያሰኘው በሚቀርብበት ቦታ እራት እየተበላ ስለሚታይ ነው፤ ሆቴል ስለቀረበ። እና በተለይ ጣይቱ ሆቴል ጃዝ አምባ ላውንጅ ይታይ ነበር። ሆቴሉ ሲቃጠል ተቋርጧል። እንዲሁም ግዮን ሆቴል ‹‹አፍሪካ ጃዝ›› በሚባለው ቦታ ሲታይ ስለነበረና ተመልካቾች ምግብ እየበሉና እየጠጡ ያዩ ስለነበረ ሰዎች ‹‹ዲነር ቴያትር›› ብለው ሰይመውታል። ከሚታይበት ቦታ አንፃር ካልሆነ በስተቀር እኔ ስሰራው የትም ቦታ ላይ ሊታይ የሚችል ቴያትር ነው መስራት የምፈልገው ብዬ ስለተነሳሁ ‹‹ዲነር ቴያትር›› ብለህ ስትገድበው ደስ አይለኝም።

“ብዙ ጊዜ የማነሳቸው ጉዳዮች መነሻቸው እኔ ትክክል አይደለም የምላቸው ጉዳዮች ናቸው። ይሄ ነገር መለወጥ አለበት፣ እንዲህ መሆን አይገባውም ብዬ ከልቤ ተሰምቶኝ የተናደድኩበት ጉዳይ ይሆንና ድርሰቱ ላይ ሲመጣ ገጸ ባህሪያቱም ነገሮቹን ለመለወጥ የሚሰሩ ሊሆኑ ይችላሉ”

‹‹ዲነር ቴያትር›› ብትለውም ግን ግድ የለኝም።

ታዛ፡ ‹‹ዴስፐሬት ቱ ፋይት›› ወይም በአማርኛ ‹‹ከሰላምታ ጋር›› ተውኔትን በእንግሊዘኛ ቋንቋ የፃፍሽው በአዲስ አበባ ቴያትር ቤቶች አካባቢ ላይ ባሉ ቢሮክራሲያዊ ሁኔታዎች ተበሳጭተሸና ከእነርሱ ተጽዕኖና ሥፍራ ለመራቅ ብለሽ ነው ይባላል። እውነት ነው?

መዓዛ፡– ይኸውልህ መጀመሪያ ‹‹ዝነኞቹ›› የሚል ቴያትር ፃፍኩኝና ባሉት ቴያትር ቤቶች (ሀገር ፍቅር ቴያትር፣ ብሔራዊ ቴያትር፣ አዲስ አበባ የቴያትርና ባህል አዳራሽ ወይም ማዘጋጃ ቤት ቴያትር) ለማስገምገም ጥረት አደረግን። ሁለት ቦታዎች ላይ ተገምግሟል። የታየው ግን በአዲስ አበባ ቴያትርና ባህል አዳራሽ ነው። ግን ወደነዚህ ቴያትር ቤቶች ለማስገምገም በሄድንበት ሂደት ውስጥ ያየኋቸው ያሰራር መዝረክረክ፣ የጊዜ መራዘምና የግንኙነት ችግር ከፍተኛ ነው። አንድን ደራሲ ወይም ድርስት ተቀብሎ አበረታትቶና ምቹ ሁኔታ ፈጥሮ ለመስራት ችግር አለባቸው።

ለኔ ይሄ ስርዓት እሚያሰራኝ አይደለም። አንድን ስራ ሰርተህ በቀላሉ ወደ መድረክ ማምጣት የማትችል ከሆነ ከባድ ነው፣ ለደራሲው ህመም ነው ብዬ ስላሰብኩኝ፣ ከዚህ በኋላ ‹‹ዝነኞቹ›› ከታየ በኋላ ወደዚህ ሥፍራ መቅረብ እንደሌለብኝ ተረዳሁ።

‹‹ዝነኞቹ››ን ለመድረክ ለማብቃት በጣም አታካችና ረጅም መንገድ ነው የተጓዝነው። በወቅቱ እኔ ትክት ብሎኝ ስለነበረ ከዚህ በኋላ ሥራዬን ወደ ቴያትር ቤቶች ይዤ አልሄድም ብዬ ወስኛለሁ። ነገር ግን የተማርኩትም፣ የምወደውም፣ ዝንባሌዬም ቴያትር ስለሆነ በእነርሱ ሥርዓት ውስጥ የማልገባበትን ሥራ እሰራለሁ፣ መንገድ እተልማለሁ። ስለዚህ ቴያትር ስሰራ ለየት ያለ ቦታን እና ሁኔታን ታሳቢ አደርጋለሁ። ለምን አንድ ተመልካች ያለበት አይሆንም? ለምን ትንሽ ቦታ ላይ አይሆንም? ብቻ ባለው ሁኔታ ውስጥ ሊሰራ የሚችል ስራ ነው መስራት ያለብኝ ብዬ ውሳኔ አደረግኩ። ‹‹ከሰላምታ ጋር›› ቴያትር የተጠነሰሰው በዚህ መንገድ ነው። ከችግር ነው የተወለደው ማለት ነው።

 ‹‹ዴስፐሬት ቱ ፋይት››ን ልጽፍ እያልኩ ባለሁበት ሁኔታ ደግሞ አሜሪካን አገር ውስጥ ያለው በፊልምና በቴያትር ላይ የሚሰራ ‹‹ሰን ዳንስ ኢንስቲቲዩት›› ምስራቅ አፍሪካ ላይ የቴያትር ፕሮግራም አላቸው። ሰን ዳንስ ኢንስቲዩቲት የምስራቅ አፍሪካ የቴያትር ፕሮግራም ለ2011 የተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ የቴያትር የጽሑፍ ሥራዎችን ይጋብዝ ነበር። ሥራዎችን አወዳድረው የቴያትር ቤተ-ሙከራ (ቴያትር ላብ) ዓይነት አድርገው ጽሑፍህን እንድታሻሽል፣ ሀሳብህን በደምብ፣ በነፃነት እንድትሰራ ‹‹ኢንድፔንደንት›› የሆኑ፣ ነፃ አሳቢ የሚባሉ ደራሲዎችን (ጸሐፌ ተውኔቶችን) ለማበረታታት ተብሎ የተዘጋጀ መድረክ ነው።

ሥራዬን ወደዛ ስልክ ሰን ዳንስ ውስጥ ያሉት ሰዎች በሙሉ እንግሊዝኛ ተናጋሪዎች ስለሆኑ በአማርኛ ብጽፍ የሚያነብልኝ ስለሌለ ከነሱ ጋር ለመግባባት ብዬ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ፃፍኩት። ርእሱን ‹‹ዴስፐሬት ቱ ፋይት›› ለፀብ ወይም ለትግል የቆረጠች ማለት ነው። ዋና ገጸባህርያዋ ሴት ስለሆነች። ከዛ ተውኔቱ ለ2011 ዓ.ም. የቴያትር ሥራ ተመረጠ። ከምስራቅ አፍሪካ አራት ጽሑፎች ተመረጡ፤ ከተመረጡት አራት ሥራዎች ውስጥ አንዱ የኔ ነበር። የቴያትር ቤተሙከራው ወይም ‹‹ቴያትር ላብራቶሪ›› ኬንያ ውስጥ ነበር የተደረገው እናም ገጸ ባህርይዋን በጣም ወደዷት። ከተለያዩ አገሮች፡- ከአሜሪካ፣ ከእንግሊዝ የመጡና ከምስራቅ አፍሪካ የተለያዩ አገራት የመጡ ባለሙያዎች ናቸው የቴያትር ጽሑፉ ላይ ‹‹ኢክስፐርመንት›› ያደርጉ የነበረው። ጥያቄ ትጠየቃለህ፤ እንድታሻሽልና የማሰቢያ ቦታ የማመቻቸት ነገር ነበር። በጣም ደስ ብሏቸው ስለነበረ፣ እኛ አገር እንውሰደው የሚል ጥያቄ ያኔ ነው ያቀረቡት። ከኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ የተጠሩት የምስራቅ አፍሪካ ባለሙያዎች። እንዲሁም ከአሜሪካ ደግሞ ሰን ዳንስ ውስጥ ያሉት ሰዎች ይሄ ቴያትር ኒውዮርክ ላይ መታየት አለበት ብለው ወደ ኒውዮርክ እንድሄድ ጥሪ አቀረቡልኝ።

 በዚህ መሠረት የቴያትር ‹‹ወርክ ሾፕ›› ተዘጋጅቶ፣ ቴያትሩ ኒውዮርክ ‹‹ባሪሸንኮቭ አርት ሴንተር›› የሚባል ቦታ በ2012 ላይ እንዲቀርብ ተደረገ። ባሪሸንኮቭ በታዋቂው ሩሲያዊው የዳንስ ባለሟል የተሰየመ ቴያትር ቤት ነው። ኬንያም ሲሰራ፣ ኒውዮርክም ሲሰራ፣ ፍሊፕ ኢምበርግ የሚባል አሜሪካዊ የታወቀ የቴያትር ዳይሬክተር ነው ያዘጋጀው። እኔ መታዘብ ነው፤ አሜሪካ ውስጥ ቴያትር እንዴት እንደሚሰራ ማየት፣ ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋራ መተዋወቅ እና ልምድ መለዋወጥ ነበር የሚጠበቅብኝ፤ በተለይ ኒውዮርክ በነበርን ጊዜ። ከዛ በኋላ የ‹‹ኢንተርናሽናል ውመን ፕለይ ራይትስ ኮንፈረንስ›› (የሴት ፀሐፌ ተውኔቶች ዓለማቀፍ ጉባኤ) የሚባል አለ በየሁለት ዓመቱ በተለያዩ አገሮች የሚዘጋጅ። በ2012 በስዊድን ስቶክሆልም ውስጥ ይደረግ ነበር። ከዚያ የተለያዩ አገራት ቴያትራቸውን ላኩና እዛ ላይ ይቅረብ ተብሎ ጥሪ ሲደረግልኝ እኔ ‹‹ዴስፕሬት ቱ ፋይት››ን ላክሁ። ስቶክሆልም ላይም ደግሞ ቀረበ ማለት ነው። ስቶክሆልም ላይ አቀራረቡ ‹‹ስቴጅ ሪዲንግ›› ይባላል። ከተለያዩ 50 አገራት የተውጣጡ ሴት ፀሐፊዎች በነበሩበት ነው የቀረበው። ከዛ በኋላ ዩጋንዳ ውስጥ በዩጋንዳ ተዋንያን ፕሮዳክሽኑ ተሰርቶ በዩጋንዳ ብሔራዊ ቴያትር ለመቅረብ ችሏል። በዩጋንዳ የተሰራው ፕሮዳክሽን ሩዋንዳና ብሩንዲም ተጉዞ በዩጋንዳ ተዋንያን ቀርቧል። በኬንያ ውስጥ ደግሞ ኬንያ ናሽናል ሙዚየም ውስጥ በኬንያ ተዋንያን ተሰርቷል። በጀርመንኛ እና በሰርቢያ ቋንቋም ተተርጉሟል።

 ታዛ፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ቴያትሩ በሀገር ቤት አልቀረበም ነበር?

መዓዛ፡ በ2014 እ.ኤ.አ. ይህን ተውኔት ልጽፍ ሳስብ መጀመሪያ ዓላማዬ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲታይ ነበር፤ ለኢትዮጵያውያን ተመልካቾች ነውና የምጽፈው። ስለዚህ ይህ ቴያትር ለኢትዮጵያውያን ተመልካቾች መቅረብ አለበት አልኩኝና በእነዚህ አገራት ላይ ከቀረበ በኋላ ነው ‹‹ከሰላምታ ጋር›› ብዬ ወደ አማርኛ የተረጎምኩት። ርዕሱ አይመሳሰልም ግን የራሴ ምክንያት አለኝ። እዚሁም ራሴ አዘጋጀሁት። በጣይቱ ሆቴል ጃዝ አምባ ላውንጅ፣ ግዮን ሆቴል አፍሪካ ጃዝ ቪሌጅ እና በዓለም ሲኒማ ለሶስት ወራት ያህል ታይቷል። ኤድናሞልም ታይቷል። ያኔ እንደውም በሲኒማ ቤቶች እና በሆቴል ውስጥ ቴያትር ማሳየት አልተለመደም ነበር። ቴያትር በመቶ ብር ሲታይ የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም።

 ታዛ፡- ከሰላምታ ጋር ቴያትር በአቀራረቡ ምን ዓይነት ነው?

መዓዛ፡- ‹‹ከሰላምታ ጋር›› ቴያትር ‹‹ኮንቴምፖራሪ›› የሚባል ዓይነት ነው። ዘመነኛ ወይም ደግሞ ይሄ ሞደርን ቴያትር ሳይሆን ‹‹ፖስት ሞደርን›› ዓይነት ቅርፅ ያለው ነው። ፖስት ሞደርን ማለት የተለያዩ ቅርፆችን ለኔ አስተሳሰብና ላወጣው ለምፈልገው ዓይነት ስሜትና አስተሳሰብ እሚመቸኝን ማንኛውንም የቴያትር ቅርፅ ተጠቅሜ የፃፍኩት የተለየ አተራረክ ወይም ደግሞ አመደራረክ ልትለው ትችላለህ። አንድ ነገር ስትል ምንም ዓይነት ‹‹ኮንቬንሽን›› አይገድባቸውም። ስለዚህ ኮንቬንሽናል ዓይነት ‹‹ሪያሊስቲክ›› ስራ ነው አትልም። ምክንያቱም ‹‹ሪያሊስቲክ›› ያልሆነ ነገርም አለው። ‹‹ሲምቦሊክ›› የሆነ ነገር እጠቀማለሁ፤ እዛ ውስጥ ወለፈንድ (አብሰርድ) የሚመስል ነገርም ታይበታለህ። ኮሜዲ ነው፣ ትራጄዲ ነው፣ ድንቃይ (ሜሎ ድራማ) ነው፣ ግራ ያጋባሃል። ብዙ ነገር ውስጡ አለበትና።

ታዛ፡- አሁን ሥራዎችሽን ለዕይታ የምታቀርቢው በምን መንገድ ነው?

መዓዛ፡- ኪቫ መልቲሚድያ ፕሮዳክሽን የሚባል የቴያትርና የፊልም ስራ የሚሰራ ተቋም አለን። ባለቤቴና የኔ ፕሮዲዩሰር ያቋቋመው ነው። ‹‹ከሰላምታ ጋር››፣ ‹‹ደርሶ መልስ›› እና ሌሎች የሬድዮ ጽሑፍችን ከተለያዩ ተቋማት ጋር ስንሰራም የምናቀርበው በዚህ ተቋም ስር ነው።

ታዛ፡- እንደ አንድ ደራሲ ሀገርሽን ስትመለከቺ ምንድነው የሚያሳስብሽ?

መዓዛ፡- ሁሉም ነገር ያሳስበኛል፤ እሚያሳስቡኝን ነገሮች ደግሞ እኔ ባለኝ አቅም በድርሰቶቼ እያነሳኋቸው ነው። የፍትሕ መጓደል ያሳስበኛል፤ በሰዎች መካከል የእኩልነት መጓደል ያሳስበኛል፤ ሙስና ያሳስበኛል። የአየር ንብረት ለውጥ ያሳስበኛል። ሰው ደስተኛ ሆኖ አለመኖሩ ያሳስበኛል። ይሄን ሁሉ ነገር ስታጠቃልለው ማህበራዊም ጉዳይ፣ ኢኮኖሚያዊም

“ብዙ ጊዜ እንደውም እኔ እኮ ከስራዎቼ ፊት ባለቤቴ አለ። እሱ እንደውም ባይኖር ኖሮ እነዚህን እስካሁን ሳወራባቸው የነበርኩትን ሥራዎች ልሰራ አልችልም ነበር። ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ በስራ የሚያጋጥሙኝን ተግዳሮቶች እሱ ነው የሚጋፈጣቸው። ፕሮዲዩሰሬም ስለሆነ”

ጉዳይ መፍትሄው ፖለቲካዊ ስለሆነ፣ ፖለቲካዊ ዘዬኣችንና ባህላችን ያሳስቡኛል።

ታዛ፡- በፋና ቴሌቪዥን እየቀረበ ያለው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ‹‹ደርሶ መልስ›› ረብ ያለው ሥራ ነው ብለሻል። ምናልባት ቀደም ብዬ በጥያቄ እንዳነሳሁልሽ ይህን ሥራ በተለይ ወደሽው ይሆን?

 መዓዛ፡- በአሁኑ ጊዜ እሱን እየፃፍኩኝ ስለሆነ፣ በተለየ እምወደው ስራ አሁን ላይ እሱ ነው የሚሆነው። ከደርሶ መልስ በኋላ ግን ሌላ የበለጠ የምወደው ሥራ ይመጣ የለ! ረብ ያለው መሆኑን የምንገልፅበት ምክንያታችን ደግሞ ከምናነሳው ርዕሰ ጉዳይ በመነሳት ነው። ያነሳነው ርዕሰ ጉዳይ በተለይ አሁን አገራችን ውስጥ ከምንኖርበት ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ኑሮ ጋር ተያይዞ ወቅታዊና ሁሉንም ሰው የሚመለከት ረብ (relevance) ስላለው ነው። ዝም ብለን አይተነው የምንተወው ሳይሆን እንድንለውጠው፣ እንድናስበውና እንድንጠይቅ የሚያደርገን ስለሆነ ነው። ዝም ብሎ ቀልድ፣ ቧልትና ጨዋታ ያልሆነ ‹‹ሲርየስ›› ጉዳይ የሚያነሳ ነው። ረብ ስትል ቅርፁንም፣ ዘውጉንም ምኑንም ነው የምታነሳው። ይዘቱ ዝም ብሎ አይደለም። እያንዳንዷ የምናቀርባት ንግግር፣ የምንሰራው ድርጊት ትርጉም አለው።

ታዛ፡- ሴት ነሽ፣ ባለ ትዳር ነሽ፣ የልጆች እናት ነሽ፣ የሙሉ ጊዜ ደራሲ ነሽ፣ ይሄን ሁሉ ነገር እንዴት ነው አጣጥመሽ የምትመሪው?

መዓዛ፡- እኔ ደስ ባለኝ፣ በፈለግኩትና በፈቀድኩት መንገድ ሳልፈራ በድፍረት መኖር ነው የምፈልገው። የህይወት መንገዴ ይሄ ነው። ይህ ጽሑፌም ላይ አኗኗሬም ላይ ይንፀባረቃል። ባለትዳር ነኝ። ልጆችም አሉኝ። ግን ልጆቼ ስራዬንና ሀሳቤን እንዲያከብሩልኝ አድርጌ ነው የማሳድጋቸው። እኔን የፈጠረኝም ሆነ እኔ የፈጠርኩት ቤተሰብ ሀሳቤን እና አቋሜን እንዲያከብርልኝ አድርጌ ነው የምኖረው። ልጆቼም ሥራዬንና ሃሳቤን ያከብሩልኛል። ማሰብ ስፈልግ ማሰቢያ ጊዜና ቦታ ይሰጡኛል። ባለቤቴም በእጅጉ ያግዘኛል። ብዙ ጊዜ እንደውም እኔ እኮ ከስራዎቼ ፊት ባለቤቴ አለ። እሱ እንደውም ባይኖር ኖሮ እነዚህን እስካሁን ሳወራባቸው የነበርኩትን ሥራዎች ልሰራ አልችልም ነበር። ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ በስራ የሚያጋጥሙኝን ተግዳሮቶች እሱ ነው የሚጋፈጣቸው። ፕሮዲዩሰሬም ስለሆነ። ብዙ ነገሮችን ከልሎ የሚይዝልኝ እሱ ነው። መከለል ደግሞ ለደራሲ እንዴት ዓይነት ነፃነት እንዳለው ልነግርህ አልችልም። በዚህ ሁሉ ነገር ውስጥ ደግሞ ሴትነቴን አስቤው አላውቅም። እንደ ሰው ነው የማስበው። እንደ ማንኛውም ችግር እንደሚያጋጥመው ሰው እኖራለሁ። በእርግጥ ሴት በመሆኔ ምን ዓይነት ችግር እንደሚገጥመኝ አውቃለሁ። በስራዎቼ ውስጥም እታገላቸዋለሁ። ግን ይህ ችግር የገጠመኝ በሴትነቴ ነው ብዬ አላስብም። ካላመንኩበት ምንም ነገር አላደርግም፤ በራሴ ብቻዬን ብቆምም ብቸኝነት አይሰማኝም።  

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top