አጭር ልብወለድ

ዱብ ዕዳ

ትዳር እንደ ሎተሪ ዕጣ ነው። ጥሩ ሴት ካጋጠመህ ሕይወትህ በደስታ የተሞላ ይሆናል። ካልሆነ ግን እንደ ሳማ ሲለበልብህ ትኖራለህ። ለእኔ መንበረን ማግኘቴ ሎተሪ የወጣልኝን ያህል ነው የምቆጥረው። በጣም ደስተኛ ነኝ። መንበረ ታከብረኛለች፣ ትንከባከበኛለች። እኔም አፀፋውን በፍቅር እመልስላታለሁ- ሳፈቅራት ለጉድ ነው። መንበረ አመለ ለስላሳና የተረጋጋች ሴት ናት። የሕይወቴ ምሰሶ፣ የደስታዬ ምንጭም ናት። ከ10 ዓመት በኋላም ፍቅራችን ገና አፍላ ነው- አልቀዘቀዘም።

 መንበረን የማውቃት ከሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ጀምሮ ነው። ከተዋወቅን ድፍን 16 ዓመታችን ነው። መንበረ ብዙ ግርግር አትወድም። በዚህ ረጅም የትዳር ጊዜያችንም መጠጥ የሚባል ነገር ንክች አድርጋ አታውቅም። አንድ ቢራ ወይም አንድ ብርጭቆ የወይን ጠጅ እንድትሞክር ደጋግሜ ብገፋፋትም ሁልጊዜ አሻፈረኝ እንዳለችኝ ነው።

የጋብቻችንን 10ኛ ዓመት በዓል በልዩ ሁኔታ እንድናከብር ፈለግሁኝ። ነገር ግን ይኼ በዓል ለባለቤቴ ድንገተኛ (surprise) እንዲሆን ነው ያሰብኩት። የምወዳት ባለቤቴን፣ የእርሷንና የኔን የቅርብ ጓደኞች እንዲሁም ሚዜዎቻችንን በሙሉ ፔንጉዊን የተባለ ዕውቅ ምግብ ቤት ልጋብዛቸው ወሰንኩኝ። ፔንጉዊን፤ ቆንጆ የባህል ምግብና ሙዚቃ ያለው መዝናኛ ሥፍራ ነው። ዕለቱ ቅዳሜ ነው። ማታ አንድ ሰዓት ላይ። ይኼን ፕሮግራም የማታውቀው መንቢ ማታ በ1 ሰዓት ላይ ከጓደኛዋ ከመሠረት ጋር ቀጠሮ እንዳላቸው የነገረችኝ ማለዳ ነው- እዚያው ፔንጉዊን። እኔና ወዳጆቻችን ቀደም ብለን ተገናኝተናል። መንቢና መሠረት ከግማሽ ሰዓት በኋላ ደረሱ። መንቢ ዓይኗን ማመን አቃታት። የዚያ ሁሉ ሰው መሰባሰብ ትንግርት ሆነባት። «ምንድን ነው ነገሩ» አለች፤ ከዳር እስከ ዳር እያየችን። «እንኳን ለ10ኛ ዓመት የትዳር በዓላችን በሠላም አደረሰን» ብዬ ከመቀመጫዬ ተነስቼ አቅፌ ሳምኳት፤ ጓደኞቻችን በጭብጨባ አጀቡን። መንበረ የምትናገረው ጠፍቷት አፏን ከፍታ ቀረች። «እኔ ቀኑን እንኳ የምታስታውሰው አልመሰለኝም ነበር። ደስታዬ ከመጠን ያለፈ ነው፤ እወድሃለሁ!» አለችኝ ዓይኗ እንባ አቅሮ። እኔም ባባሁ። እንባዬ ጉንጬ እስኪደርስ ድረስ መውረዱን አላወኩም ነበር።

እራት ቀረበ። ቢራውም ውስኪውም በዓይነት በዓይነት ተደረደረ። ፌሽታ በፌሽታ ሆንን። ሁላችንም የድሮ ጨዋታ እያነሳን መሳቅ መጫወት ጀመርን። ቀደም ብሎ ያዘዝኩትን ትልቅ የበዓል ኬክ አስተናጋጇ ተሸክማ መጣች። «የምወድሽ ባለቤቴ መንቢ፤ እንኳን ለ10ኛ ዓመታችን አደረሰን» የሚል ጽሑፍ የተጻፈበት በአስር ሻማ የታጀበ ነው- ኬኩ። መንቢ ልታምነው አልቻለችም። ሻማዎቹን አጥፉ ተባልንና በሁለት በሦስት ትንፋሽ አጠፋናቸው። እኔና መንቢ አንድ ቢላ ለሁለት ይዘን ኬኩን ቆረስን። ጽዋ አንስተን አጋጨን። እኔ በውስኪዬ፣ መንቢ በኮካዋ። ቤት ውስጥ የነበሩት ሌሎች እንግዶችም በጭብጨባ አጀቡን። አንዳንዶቹም ከሩቅ ‘እንኳን ደስ ያላችሁ’ ይሉን ነበር። በአጠቃላይ ነገር አለሙ ሁሉ የሰርጋችንን ዕለት ነው ያስታወሰኝ። መጠጡን እየጠጣን ጨዋታውም እየደራ መጣ። የቤቱ ባለቤት አንድ ጠርሙስ የዱከም ወይን ጠጅ ይዘው መጡና «ደስ ብሎኝ ነው፤ ፍቀዱልኝ» አሉና ፈቃዳችንን ሳይጠብቁ ወይኑን ከፈቱት። ለሁሉም ከቀዱ በኋላ ለመንበረ ሊቀዱላት ሲሉ «በጣም አመሰግናለሁ፤ እኔ አልጠጣም» አለች እንደተለመደው። «እባክሽ የኔ ልጅ ጠጪ። እኔ ከሚስቴ ጋር 30 ዓመት ቆይቻለሁ። እርሷም እንዳንቺ አትጠጣም ግን በየዓመቱ በዓላችንን ስናከብር ብቻ ወይን ትጠጣለች። ምንም ማለት አይደለም፣ ለበዓሉ ድምቀት ነው» ብለው ሊገፋፏት ሞከሩ። «እኔ በሕይወቴ ቀምሼው አላውቅም፤ ጋሼ ይቅርብኝ» ብላ እጇን ብርጭቆው ላይ ደፋች። ዛሬ ልትሸነፍ ነው ብዬ ደስ አለኝ። እውነት ነው! ለ10ኛ ዓመት በዓላችንማ መጠጣት አለባት! «እባክሽ ግብዣቸውን አትናቂ። እንደሳቸው ሚስት በዓመት አንድ ጊዜ ባይሆንም እንኳ በየ10 ዓመቱ እንኳን ሞክሪ» ብዬ እጇን ከብርጭቆው ላይ አነሣሁት። ጓደኞቻችንም በጋራ፤ «እባክሽ ጠጪ ምንም አይልሽም! አላበዛሽውም እንዴ!» አሏት። መንቢ መጨረሻ ላይ ተሸነፈች። ወይኑ ተቀዳላት፤ ብርጭቋችንን አጋጨን። ኮሶ እንደሚጠጣ ሰው ፊቷን አጨማዳ ፉት አለች። ቤቱ በሳቅና በጭብጨባ ተሞላ። የቤቱ ባለቤት መንቢን ለማጠጣት የመጡ ይመስል «በሉ ተጫወቱ» ብለው ወደ ሥራቸው ተመለሱ።

ሰዓቱ እየመሸ ሲሄድ ሙዚቃው እየተሟሟቀ መጣ። የዳንሱ መድረክ ሞላ። መንቢ ቀስ እያለች የመጀመርያ ብርጭቆዋን ጨረሰች። አንዱ ወዳጃችን ከመቀመጫው ተነስቶ ሁለተኛ ቀዳላት፤ ጠጥታ ስለማታውቅ የመጀመሪያው ሞቅ ያደረጋት መሰለኝ። ደስ ብሏት ትፈነድቅ ጀመር። ድሮ ከመጋባታችን በፊት የገጠመንን አስቂኝ ነገሮች እያነሳች።

ሁለተኛውን ብርጭቆ ስትጨርስ ሦስተኛውን የቀዳችው ራሷ ናት- አሁን ማንም አልገፋፋትም። የጀማሪ ነገር! ሦስተኛውን ብርጭቆ በአንድ ትንፋሽ ጭልጥ አደረገችው።

«ኧረ አንቺ፤ ውሃ አረግሽው እንዴ? አልኮል እኮ ነው!» አልኳት- ደንግጬ።

«ውድ ባለቤቴ፤ መንግይይዬ ጠጪ ጠጪ እያልክ እድሜ ልኬን የምትነዘንዘኝ አንተ ነበርክ። አሁን ደግሞ አትጠጪ! ብሰክርም አንተ ከጐኔ አለህልኝ እኮ» አለችኝ እየተኮላተፈች። ከዚያም አራተኛ ብርጭቆዋን መሙላት ጀመረች። ነገረ-ሥራዋ ቢያስፈራኝም እንደፈቀደች ብዬ ተውኳት።

ይኼን ጊዜ ነው አንድ ጥቁር የቆዳ ጃኬት የለበሰ ጐረምሳ ወደኛ ጠረጴዛ በመቅረብ «ከሩቅ ሣይሽ ነበር፤ በጣም ደስ ያለሽ ትመስያለሽ፤ ለምን ይቺን ዘፈን አንጫወትም?» ብሎ መንቢን የጠየቃት። መንቢም እንደ መኮሳተር ብላ «አንተ፣ ደፋር ነህ! ባለቤቴ እዚህ ተቀምጦ እርሱን ሳታስፈቅድ እንዴት ለዳንስ ትጠይቀኛለህ!» አለችው። ጐረምሳው ደነገጠ። ወደኔ ዞር አለና «ይቅርታ የኔ ወንድም፣ አላወቅኩም ባለቤትህ በጣም ውብ ናት። ይሄን ዘፈን ስለምወደው አብረን እንድንደንስ ፍቀድልኝ» ብሎ ትከሻዬ ላይ እጁን ጣል አደረገ።

«ምንም ችግር የለም፣ የ10 ዓመት የጋብቻ በዓላችንን እያከበርን ነውና ደስ ብሎናል» አልኩት። «እንኳን ደስ ያላችሁ! እንግዲያውማ ለምን ሁላችሁም ተነስታችሁ አንድ ላይ አንጨፍርም?» አለ። «ግድ የለም

“መንቢ አልተመለሰችም። ጓደኞቻችን እየተንጠባጠቡ መሄድ ጀመሩ። መጨረሻ ላይ ከቀሩት ሦስት ወዳጆቻችን አንዱ፣ «እንዴ ስማ መንጌ አንድ ዳንስ ብሎ አልነበር እንዴ የወሰዳት? ከረመ እኮ! ኧረ ሂድና ጥራት፣ እኛም እንሂድበት» አለኝ”

አንተ አስደንሳት እኔ ደክሞኛል» አልኩና ወደ መንቢ ዞር ብዬ «ተነሺ ተጫወችለት» አልኳት። መንቢ እየሳቀች አራተኛውን ብርጭቆ ጨልጣ ተነሳች። ወቸ ጉድ ባትጠጣ ኖሮ ይኼ ሁሉ ጨዋታ አምልጦኝ ነበር። ሁሌም መጠጣት አለባት! አልኩኝ- በስካር ስሜት።

«አመሰግናለሁ፣ ከአንድ ሙዚቃ በላይ አላቆያትም» አለና እጇን ይዞ ወደ ዳንሱ መድረክ ወሰዳት- ጐረምሳው። መንቢ እየተንገዳገደች ተከተለችው።

የመጀመሪያው ዘፈን አልቆ ሁለተኛው ቀጠለ። ዳንሱ መድረክ ላይ ብዙ ሰዎች ስለነበሩ መንቢና ሰውየው አይታዩኝም። ሦስተኛው ሙዚቃ አልፎ አራተኛ፣ ከዛም አምስተኛው ዘፈን ቀጠለ። መንቢ አልተመለሰችም። ጓደኞቻችን እየተንጠባጠቡ መሄድ ጀመሩ። መጨረሻ ላይ ከቀሩት ሦስት ወዳጆቻችን አንዱ፣ «እንዴ ስማ መንጌ አንድ ዳንስ ብሎ አልነበር እንዴ የወሰዳት? ከረመ እኮ! ኧረ ሂድና ጥራት፣ እኛም እንሂድበት» አለኝ። ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ዳንሱ ወለል ላይ እየተጋፋሁ በዓይኔ ፈለግኋቸው። መንቢም ሰውየውም የሉም፤ ደነገጥኩ! መልሼ ጓደኞቻችን ጋ ሄድኩና፤ «ኧረ የሉም የት ገቡ!» አልኳቸው። እነሱም በየፊናቸው ቤቱን አሰሱት። አንደኛው ጓደኛዬ ውጪ ወጥቶ ዘበኛውን ጠየቀው።

«የኔ ወንድም፤ እንደምታየው ሰው ብዙ ነው፤ ማንን ብዬ ላስታውስ ብለህ ነው» ሲል መለሰለት- ዘበኛው።

ድንጋጤዬ እየቆየ ወደ ስጋት ተቀየረ። መንቢ ምን ሆናብኝ ይሆን? አደጋ ገጠማት እንዴ! እያልኩ መጨነቅ ጀመርኩ። ከአሁን አሁን ትመጣለች ብለን ቁጭ ብለን በጭንቀት ጠበቅናት። መንቢን የበላት ጅብ አልጮህ አለ። ሞባይሏ ላይ ብደውል አትመልስም። ምናልባት ቤት ሄዳ ይሆን ብዬ ቤት ደወልኩ- ሠራተኛዋ አልገባችም አለችኝ። ከለሊቱ 9 ሰዓት ሆነ። ጓደኞቼ ለፖሊስ እናመልክት የሚል ሃሳብ አቀረቡ። እኔ ግን ተቆጣሁ። «ምን ብዬ? ሚስቴ ከወንድ ጋር ሄደች… ብዬ ቅሌት ልግባ እንዴ?» ብዬ ጮህኩባቸው።

ጓደኞቼን በአሉበት ትቼ መኪናዬን አስነስቼ ወደ ቤቴ ሄድኩ። ክፉ ክፉ ሃሳቦችና ጥርጣሬዎች በጭንቅላቴ ተመላለሱብኝ። ለካ ሚስቴን አላውቃትም ነበር! ከማላውቃት ሴት ጋር ነበር እንዴ የምኖረው! የፈለገ ብትጠጣ እንዴት የማታውቀውን ሰው ተከትላ ትሄዳለች? ብዙ ጥያቄዎች ብዙ ጥርጣሬዎች በአዕምሮዬ ውስጥ ተፈራረቁብኝ… ከሰውየው ጋር ተቃቅፋ ተኝታ ታየኝና አማተብኩ። የለም አታደርገውም! አልኩኝ- ለራሴ። የቅናት መንፈስ በውስጤ እንደሳት ተንቀለቀለ። መኝታ ቤቴ እየተንጎራደድኩ ላይ ታች እል ጀመር። መንበረ አስጠላችኝ። አስር ዓመት በከንቱ እንዳለፈ ቆጠርኩት። በአንድ ምሽት የትዳሬ ምሰሶ ፈረሰ ማለት ነው? የደስታዬ ምንጭ ሊደርቅ? አልጋው ጎን ያለው ኮመዲኖ ላይ ጉብ ያለውን የመንበረን ፎቶ አንስቼ አፍጥጬ እያየሁት «ለምን? ለምን?» እያልኩ ጠየኩት። የምታሾፍብኝ መሰለኝ- ፎቶው ላይ ያለችው መንቢ። መሬት ላይ በኃይል አፍርጬ በእግሬ መስታወቱን አደቀቅሁት- ነካ ያደረገኝ መሰለኝ።

እግሬ እንደ አሸዋ የደቀቀውን መስተዋት የበለጠ እያደቀቀ ሳለ ሞባይሌ ጮኸ- ክው አልኩ። ከሌሊቱ 11 ሰዓት ሆኗል- መንበረ ናት።

በደከመ ድምፅ፤ «መንጌ መንግዬ ጉድ ሆንኩ…» አላስጨረስኳትም «አንቺ ባለጌ! አታፍሪም! ደሞ ትደውያለሽ» ብዬ ጆሮዋ ላይ ዘጋሁባት።

መልሳ ደወለች።

«ስሚ ክፉ አታናግሪኝ! ሠይጣኔን አታምጪብኝ! አንቺ ወራዳ ሆነሽ እኔንም አዋረድሽኝ! እዛው የወሰደሽ ሰውዬ ጋ እደሪ። አትረብሺኝ» አልኩና ፋታ ሳልሰጣት ጆሮዋ ላይ ዘጋሁባት።

ለሦስተኛ ጊዜ ደወለች።

«መንግዬ በምትወዳት እናትህ በወርቅዬ ይዤሀለሁ፤ አትዝጋብኝ! የኔ ጌታ አንዴ አድምጠኝ» ብላ ለቅሶ በተሞላበት ድምፅ ለመነችኝ።

የናቴን ስም ስላነሳችብኝ «እሺ ቀጥዪ» አልኳት።

«መንግዬ እኔ እኮ መጠጡ እራሴ ላይ ወጥቶብኝ ነው። የዳንስ መድረኩ ላይ ስወጣ የሙዚቃው ጩኸትና ብልጭ ድርግም የሚለው መብራት ጭንቅላቴን አዞረኝ አቅለሸለሸኝ። የመጀመሪያውን ሙዚቃ እንኳን አልተጫወትኩም። ሰውዬውን ትቼ ወደ ሽንት ቤት ሮጥኩ። የሚያዞረኝ ስሜት እስኪለቀኝ ድረስ ሽንት ቤት ውስጥ ገብቼ ቁጭ አልኩ፤ እዛው ቁጭ ያልኩበት እንቅልፍ ይዞኝ ሄደ»

«ምን? ምንድን ነው የምታወሪው? አሁን የት ነው ያለሽው»

«እዛው ፔንጉዊን ነዋ!!!… ቶሎ መጥተህ ውሰደኝ››

ፔንጉዊን ደረስኩ- ዘበኛውን አነጋግሬ ወደ ውስጥ ገባሁ። መንቢ ሶፋው ላይ ጅው ብላ ተኝታለች። ሌሊቱን ሙሉ ሳስብ የነበረውን ሃሳብ እያውጠነጠንኩ መንቢን ትክ ብዬ ተመለከትኳት። ከፍተኛ የሃዘንና የፀፀት ስሜት ውስጥ ገባሁ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top