ጥበብ በታሪክ ገፅ

የአድዋ ጦርነትና ድል በተለያዩ ጠቢባን ዓይን

አንድ መቶ ሃያ ሁለት ዓመት ስለሆነው የአድዋ ጦርነትና ድል ታላቅነት ብዙ ተብሏል። በታላቅ መስዋዕትነት የተገኘ ድል መሆኑንም የታሪክ ሰነዶች ይነግሩናል። በአውደ ውጊያው የተሳተፉና ሂደቱን በቅርብ የተከታተሉ፣ እንዲሁም የጦርነቱን ወሬ ከወላጆቻቸው ገና በትኩሱ የሰሙ ወገኖቻችን በስዕል፣በእንጉርጉሮና በጽሁፍ የተውልን ምስክርነትም ይህንኑ እውነታ ያጠናክርልናል።

ድሉን ታላቅ የሚያደርገውም መላ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆመው የጋራ ክንዳቸውን በጋራ ጠላታቸው ላይ መሰንዘራቸው ነው። ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ (1999) እንዳሉትም “ለንጉሠ ነገሥቱ ነፃነትና የሃገር ድንበርን የማስከበር ጥሪ ጦር ያልላከ የአገሪቱ ክፍል አልነበረም”። በዚህም የሃገራቸውንና የወገናቸውን ክብር አስጠብቀዋል፤ የቅኝ ገዢዎችን ምኞት አምክነዋል። አልፈው ተርፈውም በቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ ለነበሩ ሕዝቦች ተስፋና ኩራት ሆነዋል።

በሃገር ውስጥም ሆነ በውጪ የምንኖር ኢትዮጵያውያንም በቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ጀግንነትና ቆራጥነት የምንኮራ መሆናችንን በተለያዩ መንገዶች መግለፃችን አልቀረም። ሆኖም የአድዋን ድል ዓመት ጠብቀን ከማክበር ባለፈ ሃገራዊና ዓለማቀፋዊ ተምሳሌታዊነቱን አጉልተን ተጠቅመንበታል ማለት አይቻልም።

ከዓመታዊ ክብረ በዓሉ ባሻገር አድዋ የሚታሰበው ችግር ሲገጥመንና ለመንፈስ ማነቃቂያነት ስንፈልገው ብቻ ይመስላል። ይህ ሁኔታ በማይጨው፣ በሶማሊያና በባድመም ጦርነት ጊዜ ታይቷል። ሃብተማርያም (የአባት ስም አልተጠቀሰም፣ 1927) የተባለ ገጣሚ ከፃፈው የተቀነጨበውን እንደ ምሳሌ እናምጣ፦

 መቼ አሁን ሆነና፣ ይህማ ጠባችን

 የቆየ አይደለም ወይ፣ ቀድሞ ካባታችን

ቆርጠንም አንሰጥ፣ እኛስ ከርስታችን

 እንሟከራለን፣ እንደልማዳችን።

ይላል በማይጨው ጦርነት ዋዜማ የተፃፈው ግጥም። ከፍ ብለን እንደጠቀስነው ዓላማው የዘማቹንም ሆነ የደጀኑን ሕዝብ ወኔ ለማነሳሳት ነው። ከዚህ ባለፈ አድዋን እንደ ቋሚና ዘላቂ የኩራት ምንጭ አድርገን አልወሰድነውም። ጠላት በግፍ ላዘመታቸውና በጦርነቱ ለሞቱበት ወታደሮች ሃውልት ሲያቆም እኛ የአድዋ ጀግኖቻችን ደም በፈሰሰባቸው ታሪካዊ ቦታዎች ላይ መታሰቢያ የሚሆን ቋሚ ቅርስ አላስቀመጥንም።

ዘመኑ ያፈራቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተጠቅመን ለጎብኚዎች ምቹ ሁኔታዎችን አልፈጠርንም። ሃገራችንም ሆነች ሕዝቦቿ ከቱሪዝም መስክ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሥርዓት አልዘረጋንም። ከሁለት ዓመት በፊት በወጣ መረጃ መሠረት በአንድ ሩብ ዓመት ብቻ 70 ሺህ ያህል ያገር ውስጥና የውጪ ቱሪስቶች አክሱምን ጎብኝተዋል። ከአክሱም ተነስቶ አድዋ ለመድረስ የሚወስደው ጊዜ ከሰላሳ ደቂቃ በታች ነው። ጦርነቱ የተካሄደባቸውን መስኮችና አመራር የተሰጠባቸውን ቁልፍ ቦታዎች (Command posts) ለይተን ብናመለክት እንኳ ከፊሉን የአክሱም ጎብኚ ልንስብ በቻልን ነበር።

እዚህ ላይ ትግራይ ውስጥ በሰላም ጓድነት ያገለገለችና ዳንኤላ ሆክዋተር የተባለች አሜሪካዊት የተናገረችውን መጥቀስ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም።

“ኢትዮጵያ ወይም ኤርትራ ውስጥ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከተሰማሩ፣ አፍሪካውያን አውሮፓውያንን ድል ያደረጉበትን ገናና ታሪክ መስማትዎ አይቀርም። እኔም ትግራይ ውስጥ ሳለሁ የአድዋን ከተማ በጎበኘሁበት ጊዜ በኢትዮጵያና በጣሊያን መካከል ስለተፈፀመው አስደናቂ የጦርነት ታሪክ ከስራ ባልደረቦቼ ሰምቻለሁ” (ትርጉም የእኔ) ብላለች። እዚህ ላይ ልብ ማለት ያለብን በወሬ ደረጃ ‘ሰማሁ ’እንጂ ‘አየሁ ’አለማለቷን ነው። ዓመት ሁለት ዓመት በሃገራችን ለቆዩ ሰዎች ከቃል ወሬ ባለፈ ምንም ልንሰጣቸው ወይም ልናሳያቸው ካልቻልን ለጥቂት ቀናት ለሚመጡ ጎብኚዎችማ ምንም ያህል እንዳልታሰበበት ግልጽ ነው።

ሌላው ቀርቶ “ድሉ አይናችንን ገልጦልናል፣ የእኛም ድል ነው” ከሚሉ አፍሪቃውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር እንኳን ተባብረን አላከበርነውም። ፑች ካሚ የተባለ ደቡብ አፍሪቃዊ ፀሃፊ ለምሳሌ እንዲህ ይላል። “የአድዋ ጦርነት መላውን አህጉር ማንበርከክ እንደማይቻል በገሃድ ያሳየና ለአፍሪቃም ታላቅ አርኣያነት ያለው ነው። … ኢትዮጵያም ይህንን የግፍ ወረራ ለመቋቋም የቻለች ብቸኛ ሃገር” መሆኗን ያረጋግጣል።

ለጥቆም “ኢትዮጵያ የአፍሪቃ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት መቀመጫ የሆነችው በአጋጣሚ አይደለም። ይልቁንም አምባገነኖችንና ግፈኞችን መጋፈጥ እንደሚቻል በማሳየት በመላው ዓለም ለሚገኙ አፍሪቃውያን የፅናት ምሳሌ ሆናለች” (ትርጉም የእኔ) ሲል አትቷል።

ስለዚህም ዋናው ነገር ለአያሌ ዓመታት ያልፈፀምናቸውን ተግባራት እንደምን ልናከናውናቸው እንችላለን? ብለን መጠየቁና መነጋገሩ ላይ ይመስለናል። እነዚህም ተግባራት የዘርፈ ብዙ ባለሙያዎችን፣ ተቋሞችን፣ የግል ባለሃብቶችንና የመንግስትን ድጋፍና ትብብር ግድ የሚሉ ናቸው። ይህች አጭር ጽሑፍ የአድዋን ድል 120ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ የካቲት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. በአድዋ ከተማ በተዘጋጄ ጉባኤ ከቀረበ ጽሑፍ ላይ አጠር ብላ የተወሰደች ናት። የዛሬ ትኩረቷም የአድዋን ጦርነትና ድል አስመልክቶ ከፃፉ ወይንም ሃሳባቸውን በተለያዩ የጥበብ መስኮች ከገለፁ ጠቢባን ሥራዎች የተወሰኑትን መመልከት ነው። በዚህ ሂደት የውጭ ሃገር ዜጎችንም እናመጣለን። ሰብዓዊነትን ድንበር አይገድበውምና! እንደሚታወቀው ጣሊያኖች በኤርትራ የባህር ድንበር አካባቢ ትንኮሳውን/ወረራውን የጀመሩት ከአድዋው ጦርነት ዘጠኝ ዓመታት ያህል አስቀድሞ ነበር። ይህን የተመለከቱትና:-

 ሰይፉ ተሰብሮ፣ ካልተንተራሰው

 አይሰጥም ካሳ፣ ሃገሩን ለሰው

 ተብሎ የተገጠመላቸው አፄ ዮሐንስ በራስ አሉላ አባ ነጋ የሚመራ ጦር ይልኩበታል። አባ ነጋ አሉላ፣ የደጋ ላይ ኮሶ በጥላው ያደክማል፣ እንኳንስ ተቀምሶ! የተባለላቸው ጀግና የጦር ሰውም ተልዕኳቸውን በሚገባ ተወጡ። ባህሩ ዘውዴ እንደጻፉት፣ ጥር 21 ቀን 1879 ዓ.ም. በሰሃጢ የነበረውን ሃይል ለመደገፍ በሚጓዝ የጠላት ጦር ላይ በራስ አሉላ መሪነት በተካሄደ ድንገተኛ የደፈጣ ውጊያ 500 ያህል ጣሊያኖች ተገደሉ። የቀሩትም ለማፈግፈግ ተገደዱ። ይህንኑ የጦር አውድማ ነው ሚሸል ካማራኖ የተባለ ሠዓሊ “የዶጋሊ ጦርነት” በሚል ርዕስ በሸራው ላይ የቀረፀው። የጣሊያን መንግስት ለሙታኑ ቋሚ መታሰቢያ የሚሆን ስዕል ያዘጋጅ ዘንድ ሰዓሊውን የተኮናተረው ከዶጋሊው ጦርነት አንድ ዓመት በኋላ ነበር። የተሰጠው ሃላፊነትም በምፅዋ አካባቢ በጣሊያን ላይ የደረሰውን ወታደራዊ ሽንፈት ማሳየትና የአምስት መቶዎቹም ሞት የጀግና ሞት መሆኑን ማመልከት ነበር። የሃገሪቱን ተፈጥሮና የሕዝቧን ሁኔታ ለማወቅ ይረዳው ዘንድም ለአምስት ዓመታት ያህል ኤርትራ ውስጥ ተቀምጧል። ዓመታትን የወሰደው ግዙፍ የስዕል ስራ (4.45 ሜትር በ 7.48 ሜትር) ሲጠናቀቅ ግን የአድዋው ጦርነት ተካሄደ። እናም “ጣሊያን ውስጥ ፖለቲካዊ የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለ” የተባለ ሌላ ከባድ ሽንፈት ተከናነቡ።

ቀጥለን ደግሞ ከአድዋ ጦርነት ጋር የተያያዙ ስዕሎችን እንመለከታለን። ቀድመን የምንመለከተው በጥንታዊው የአሳሳል ዘዴ የቀረበውን ይሆናል። የወገንና የጠላት ጦር ፊት ለፊት ገጥመዋል። ወደ ጨበጣ ውጊያ እየተሸጋገረም ይመስላል። የፈረሰኛው ቅዱስ ጊዮርጊስ ምስልም በኢትዮጵያ ባንዴራ ዙሪያውን ተከቧል። የሁለቱ ሃገራት ባንዴራዎችም ማዶ ለማዶ ሆነው ይታያሉ።

ተከታዩ ስዕል ደግሞ በዘመናዊ መልክ የቀረበ ሲሆን የእቴጌ ጣይቱ ሰብዕና የተቀረፀበት ነው። ባንድ እጇ መስቀል በሌላው ሽጉጥ ይዛ ትታያለች።መስቀሉ የቆሰሉትንና የተዳከሙትን እያበረታታች የሚሸሹትን እያወገዘች መሆኗን ይጠቁማል። ሽጉጡ ደግሞ በጦርነቱ ላይ እንደ ተዋጊም እንደ ጦር መሪም ያላትን ቀጥተኛ ተሳትፎ ያመለክታል።

ሌሎች ጥንታዊ ስዕሎችም እንዲሁ ጣይቱን ከነሽጉጧ ቀርፀዋታል። ከበስተጀርባዋ የሃይማኖት አባቶች መታየታቸውም የእነሱ ድጋፍ ያላት መሆኑን ጠቋሚ ነው። በሌላ በኩል መስቀሉም ሆነ ካህናቱ በጦርነቱ ህይወታቸው ላለፈ ጀግኖች ፀሎተ ፍትሃት ለማድረግም ያገለግላሉ። በውጊያው አውድ ላይ የወደቁ ጀግኖችን የሚወክል ሰማዕት ከጋሻውና ከጠብመንጃው ጎን ይታያል። በጀግንነት እየተዋጉ ያሉትም በርካቶች ናቸው።

ቀደም ባሉት ጊዜያት የጦርነት ዝግጅቶች ሲደረጉ – ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት ሲባል – የተዋጊውን ወገን ወኔ የሚያነቃቁ የኪነት ባለሙያዎችም አብረው ይዘምቱ ነበር። በተፋፋመ ውጊያ ውስጥ ሆነው ያቅራራሉ፣ ይፎክራሉ። በአድዋው ጦርነት ወቅት የነበረውን ሁኔታ ደግሞ አፈወርቅ ገብረኢየሱስ (1921) ሲገልፁ:- “ነጋሪቱ ውጋ ውጋ እያለ ሲጎሰም፣ መለኸቱ ባንድ ወገን አይዞህ ግፋ ግፋ ቀኑ ያንተ ነው፣ የሚል እየመሰለ ሲክላላ ሲንጠረጠር፣ ባንድ ወገን ደግሞ አቅራሪ

ኧረ ጉዱ፣ ኧረ ጉዱ በዛ

በጀልባ ተሻግሮ፣ አበሻን ሊገዛ!

እያለ እያቅራራ ተጓዙ ተጓዙና መቀሌ … ደረሱ” ብለዋል። በሚቀጥለውም ስዕል “አዝማሪ ፃዲቄ እየሸለለችና እየፎከረች ስታዋጋ” ተብላ በስም የተጠቀሰች ከያኒ በፈረስ ላይ ተቀምጣለች። እጎኗ መሰንቆ የሚጫወት ባለሙያም አለ። ከጎኗና ከበስተጀርባዋ ተዋጊዎችና መድፍ ተኳሾች፣ ከፊት ለፊቷ ደግሞ የጠላት ወታደሮችና መትረየስ ተኳሾች ይታያሉ። ከዚህ ባሻገር የተዋጊው ጦር አባላት ራሳቸው መሳሪያቸውን እየነቀነቁና እየተንጎራደዱ ይሸልላሉ፣ ይፎክራሉ። በእንደነዚህ አይነት አጋጣሚዎች ስሜታቸው የተነካ ገጣሚዎች የተውልን ስንኞችም ጥቂት የሚባሉ አይደሉም። ወ/ጊዮርጊስ ወ/ዮሐንስ የጠቀሱት (1927) ሕዝባዊ ገጣሚ ለምሳሌ፣

“ነፃነቱዋን ሊሽር ማንም አይቻለው

ክበቡዋ ጥንት ነው የተመሠረተው”

ሲል ተቀኝቷል።

ቀጥለን እገሌ ከማንላቸው መሰል ሕዝባዊ ገጣሚያን ሥራዎች የተወሰኑትን ልናካፍላችሁ ወደናል። እነዚሁ ገጣሚዎችም የማናውቀውን የታሪካችን ክፍል በማሳየት ትልቅ አስተዋጽዎ አድርገዋል። አላጌ ላይ ማጆር ቶዞሊ የተገደለበትን ሁኔታ ዶ/ር ስርግው ሃብለስላሤ (1992) ሲገልፁ፦

“ቶዞሊ ከወዲህ ወዲያ እየተዘዋወረ በሚያዋጋበት ጊዜ ድንገት ፊታውራሪ አባ ውርጂ ከሚባል የራስ መኮንን ሰው ጋር ተገናኙ። ሽጉጡን እስኪያወጣ ድረስ አባ ውርጂ ጊዜ አልሰጠውም። ትግል ገጠመው። ተያይዘው ገደል ገቡና የሁለቱም የሕይወት ፍጻሜ ሆነ” ብለዋል። ይህን የሰማ ወይንም የተመለከተ ገጣሚ ታዲያ:-

ጄኔራል ባሕር፣ ማጆር ቶዞሊ

ማን ይነካዋል፣ ያለ ፈጣሪ

ገደል ሰደደው፣ አንድ ፊታውራሪ!

ብሎ ተቀኝቷል። ዶ/ር ስርግው እንደጻፉት በዚሁ ውጊያ ከወደቁት መካከል “የላስታና የዋግ ጦር መሪ የነበረ” ጊድን ገብሬና “ጥይት በቀሚሷ ጫፍ እየቋጠረች ስታቀብል” የሞተች እህቱ ይገኙበታል። የሚከተሉት ስንኞች ታዲያ ለነዚሁ ጀግኖች ክብር የተገጠሙ ናቸው።

ያ ጊድን ገብሬ፣ የባሕር አዞ

አሁን ይደርሳል፣ ጥይቱን መዞ።

ያ ጊድን ገብሬ፣ ጥቁሩ አንበሳ

የላስታው ውጋት፣ የዋግ ነቀርሳ።

የጊድን እህት፣ ምጥን ወይዘሮ

ጥይት አቀባይ፣ እንዳመልማሎ።

ስለ ፊታውራሪ ገበየሁ ጀግንነት ደግሞ:-

የንጉሥ ፊታውራሪ፣ የጎራው ገበየሁ

አላጌ በሩ ላይ፣ ማልዶ ቢገጥማቸው

ለምሳም አልበቁት፣ ቁርስ አደረጋቸው።

አድዋ ኢየሱስን፣ ጠላት አረከሰው

ገበየሁ በሞቴ፣ ግባና ቀድሰው።

ስለ ሊቀ መኳስ አባተ ጀግንነት በተለይም “የተኮሰው የመድፍ ጥይት ተሻግሮ በጣሊያኖቹ መድፍ አፈ ሙዝ” ስለመቀርቀሩ (ስርግው ሃብለሥላሤ) እንዲህ ተብሏል:-

አባተ አባ ይትረፍ፣ ነገረኛ አዋሻኪ ሰው

ይህን መድፍ ከዚያ መድፍ፣ አቆራረጠው

አበሻ ጉድ አለ፣ ጣሊያን ወተወተ

ዓይነ ጥሩ ተኳሽ፣ ቧያለው አባተ።

የገበየሁና የበሻህ አቦዬን ሞት ተከትሎ ደግሞ:-

ገበየሁ ቢሞት፣ ተተካ ባልቻ

መድፍ አገላባጭ፣ ብቻ ለብቻ

ያ በሻህ አቦዬ፣ ያ ጎራው ገበየሁ፣ ሁለቱም ያበዱ

እንቅር አይሉም ወይ፣ አንዱ ሲሄድ አንዱ

ሕዝባዊ ገጣሚያኑ እገሌ ያልተባሉትን ሰማዕታትም አልዘነጓቸውም።

ለዚያ ለወታደር፣ መች ያዝንለት አጣ

አሞራ እንኳን ወርዶ፣ ፊቱን ነጭቶ ወጣ።

በማለት ባንድ ፊት ሞታቸው ምንኛ አሳዛኝ መሆኑን ሲጠቁሙ፣ በሌላ ፊት ደግሞ የሰማዕታቱ ብዛት አስከሬን የማንሳቱን ተግባር እንዳከበደው በተዘዋዋሪ አመልክተዋል። ስለ ሕዝባዊ ግጥሞች የምንለውን ከማገባደዳችን በፊት የጦርነቱን አጠቃላይ ሁኔታ የሚያሳይ አንድ ግጥም እናክል።

ዳኛው በዲሞትፈር፣ በለው በለው ሲል

ያ ቃኘው መኮንን፣ ደጀኑን አፍርሶ፣ ጦር ሲያደላድል

አባተ በመድፉ፣ ሃምሳውን ሲገድል

ባልቻ በመትረየስ፣ ነጥሎ ሲጥል

የጎጃሙ ንጉሥ፣ በለው ግፋ ሲል

እቴጌ ጣይቱ፣ ዳዊቷን ዘርግታ፣ ስምዓኒ ስትል

ለቆሰለው ጀግና፣ ውሃ ስታድል

እንዲህ ተሰርቶ ነው፣ የአድዋው ድል።

በርካታ ዘመናዊ ገጣሚያንም ስለ አድዋ ጽፈዋል። ብዙዎቹ የድሉን ዓመታዊ መታሰቢያ በዓል ተከትለው ሥራዎቻቸውን በጋዜጦችና በመጽሔቶች አሳትመዋል። በራዲዮና በቴሌቪዥን አቅርበዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሶሻል ሚዲያዎችም መጠቀም ጀምረዋል። ከቀደምት ደራሲያን መካከል ፀጋዬ ገብረመድህንና ሠይፉ መታፈሪያን የመሳሰሉት የጻፏቸውን ግጥሞች በመጽሐፎቻቸው አካተዋቸዋል። (በዚህ እትም የቀረበው የመስፍን መሰለ መጣጥፍ የሁለቱንና የሌላ አንድ ገጣሚን ሥራ በጥልቀት ይተነትናል።) ደራሲ ፀጋዬ አድዋን “ምኒልክ” በተሰኘ ተውኔቱም ውስጥ ዳግም ይዘክረዋል። በአድዋና በጀግኖቿ ታሪክ ላይ ተመስርተው ከተጻፉ ተውኔቶች መካከል የደጃዝማች ግርማቸው ተክለሃዋሪያት “አድዋ”፣ የሻምበል ታምራት ገበየሁ “ውጫሌ 17”፣ የጌትነት እንዬው “እቴጌ ጣይቱ” እና በተክሌ ደስታ ተጽፎ የተዘጋጄውና በእቴጌዋ ስም በተሰየመው ጣይቱ የባህልና የትምህርት ማዕከል በአሜሪካ የቀረበው “ጣይቱ” ይገኙበታል። ጥቂት የማይባሉ የውጪ ሃገር ሰዎችና ኢትዮጵያውያንም በአድዋ ጦርነትና ድል ዙሪያ ጽፈዋል። ከሃገር ውስጥ ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ፣ አቶ ተክለፃድቅ መኩሪያ፣ ፕሮፌሰር ባህሩ ዘውዴ፣ ከውጪ ክሪስ ፕራውቲ፣ ሬይሞንድ ጆናስ፣ ፖል ሄንዚ፣ ሃሮልድ ማርከስ (1995) ሻን መክላሽላን (2011)፣ ማዕምረ መናሰማይ፣ ጌታቸው መታፈሪያና ጳውሎስ ሚልክያስ (አርታኢዎች) ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ታዋቂው የፊልም ባለሙያ ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማም “አድዋ” (Adwa: An African Victory) የተሰኘ ዘጋቢ ፊልም እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1999 የሠራ ሲሆን በዚሁ ዓመትም በቬኒስና በተለያዩ ታዋቂ የፊልም ፌስቲቫሎች ታይቷል። ፕሮፌሰር ኃይሌ “የአድዋ ልጆች: ከአርባ ዓመታት በኋላ” (The Children of Adwa: 40 Years Later ) የተሰኘውን ተከታይ ዘጋቢ ፊልምም በማጠናቀቅ ላይ ይገኛል። የአድዋ ጦርነት ውጤት እንደታወቀ በርካታ ዓለማቀፍ ጋዜጦች ሰፊ ሺፋን እንደሰጡት መረጃዎች ያመለክታሉ። የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ለምሳሌ ማርች 3 እና 4 ባወጣው እትሙ በዐቢይ ርዕስነት ዘግቦበታል። ከዘገባዎቹ መረዳት እንደሚቻለው ድሉ ብዙዎችን አስደንቋል፤ አስደንግጧልም።

በተለይ ጣሊያን ውስጥ በወቅቱ ከፍተኛ ሽብርና የሕዝብ ተቃውሞ ማስነሳቱን ይህን ተከትሎም ዩኒቨርሲቲዎችና ቴያትር ቤቶች መዘጋታቸውን ክሪስ ፕራውቲ (1986) ጽፋለች። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ስልጣኑን ለመልቀቅ መገደዱን ጨምራ ገልፃለች። ከአድዋው ሽንፈት በኋላ ከጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ለመልቀቅ የተገደደውን ክሪስፒ ለማሽሟጠጥ የተዘጋጁ ሥዕሎችም በርካታ ነበሩ።

አንድ ታዋቂ የፈረንሳይ ጋዜጣም (Le Petit Journal) በድሉ ማግስት (ማርች 1886) የእቴጌ ጣይቱን፣ በነሃሴ ደግሞ የአፄ ምኒልክን ምስል በፊት ገጹ ጉልህ ይዞ ወጥቷል።

ቀጥለን ደግሞ ስለአድዋ ጦርነትና ድል በዜማ የቀረቡ ሥራዎችን እንመለከታለን። ከድሉ ታላቅነትና ታሪካዊነት አንፃር ሲታይ ዜማዎቹ ብዙ አይደሉም። እንዲያውም በጣት የሚቆጠሩ ናቸው ማለት ይቻላል።

ቀደም ያሉቱ አጋጣሚዎችን ተመርኩዘው በፉከራና በቀረርቶ መልክ የሚቀርቡ እንጂ እንደዚህ ዘመን ሙዚቃዊ ሥራዎች በሲዲ ወይም በዲቪዲ የሚዘጋጁ ባለመሆናቸው እንደልብ ማግኘት አልተቻለም። ስለዚህም ከአድዋ ጦርነትና ድል ጋር በቀጥታ የተያያዙና በቀላሉ ያገኘናቸው ዜማዎች ሶስት ናቸው ማለት ይቻላል። እርግጥ ነው አንጋፋው ድምፃዊ ጥላሁን ገሠሠ:-

“የጀግኖች ደም ጥሪ፣ ቃሉ ቀሰቀሰኝ

ለታሪክ አደራ፣ ለድል ታጠቅ አለኝ።”

እያለ የተለያዩ ጀግኖቻችንን የጦር ሜዳ ውሎና መስዋዕትነት ዘክሯል። አልፎ ተርፎም የትናንቱን ጀግንነት ለዛሬው አርበኝነት ስንቅ እንድናደርገው መክሯል። ከቅርብ ጊዜዎቹ የዚህ ትውልድ ከያኒያን እጅጋየሁ ሺባባው (ጂጂ)፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) እና ለየት ባለ አቀራረባቸው የሚታወቁት “የኛ” የተሰኘው የልጃገረዶች ባህል ቡድን አባላት ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዙ ናቸው። የጂጂ እንጉርጉሮ ዐቢይ ጉዳይ ለእኔ በሕይወት መኖር፣ ለእኔ ክብርና ነፃነት ዋጋ የከፈሉ አሉ ነው።

“በደግነት በፍቅር፣ በክብር ተጠርቶ

በክብር ይሄዳል፣ ሰው ሊኖር ሰው ሞቶ

የተሰጠኝ ህይወት፣ ዛሬ በነፃነት

ሰው ተከፍሎበታል፣ ከደምና ካጥንት።”

ትለናለች። እናም የድሉን ጣፋጭነትና አኩሪነት መከራን ከተቀበሉልን ጀግኖች ሰማዕትነት ጋር ከነሰቀቀኑ የሚያስገነዝበን ነው። አንርሳቸው፣ ዛሬም ነገም እናስታውሳቸው፣ እናክብራቸው ነው ይዘቱ። “ክብር ሞቱ ለሰማዕቱ” እንዲሉ። ገድላቸውን፣ ታሪካቸውን (ብሎም ታሪካችንን) እንተርከው፣ ዓለም በደንብ ይወቀው ነው ቀዳሚ መልዕክቱ።

“ትናገር አድዋ፣ ትናገር ሃገሬ

እንዴት እንደቆምኩኝ፣ ከፊታችሁ ዛሬ።

በኩራት በክብር፣ በደስታ በፍቅር

በድል እኖራለሁ፣ ይኸው በቀን በቀን

ደግሞ መከራውን፣ ያን ሁሉ ሰቀቀን።”

ለዚህም በአውደ ውጊያው የተሰለፉትን የጦር መሪዎቹንም ሆነ ስም የለሾቹን ጀግኖች ስም ሳትጠቅስ በአንድነት ታወድሳለች፣ ታመሰግናለች።

“ምስጋና ለእነሱ፣ ለአድዋ ጀግኖች

ለዛሬ ነፃነት፣ ላበቁኝ ወገኖች” እያለች።

ቴዲ አፍሮ በበኩሉ ታሪካዊ እውነታዎችን እየተከተለ አፄ ምኒልክንና እቴጌ ጣይቱን ጨምሮ ታዋቂ የጦር መሪዎችን በስም ይጠቅሳል፣ ከድሉ በስተጀርባ ያሉትን ጀግኖች ያነሳሳል። መነሻ ያደረገውም የአፄ ምኒልክን የክተት አዋጅ ነው።

“ኑ አድዋ ላይ እንክተት

ያ የጥቁር ንጉሥ አለና፣

የወኔው እሳት ነደደ

ለአፍሪቃ ልጆች ድል ቀና!”

በሌላ በኩል በቀደምት ከያኒያን ካልሆነ በስተቀር በዚህ ዘመን ብዙም የማይነሳውን ቅዱስ ጊዮርጊስን የሥራው አካል አድርጎታል።

“ጊዮርጊስ ፈረሱ ቆሞ ሳይ፣

ድል ቀናኝ ሳልል ዋይ።”

እያለ። እንደገናም ወደ ክተት አዋጁ ተመልሶ፣ ማለትም አፄ ምኒልክ “… ወስልተህ የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ። አልተውህም። ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም” ያሉትን ተከትሎ:-

“ወደ አድዋ ሲሄድ፣ ምኒልክ ኑ ካለ

ኧረ አይቀርም፣ በማርያም ስለማለ።”

ሲል ታሪኩንና የሕዝቡን የድጋፍ ስሜት አስተሳስሮ ተርኮታል። እንደውም ተደጋግሞ እንደሚባለው ሕዝቡ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ገንፍሎ መውጣቱን አግዝፎ ለማሳየት፣ እንዲሁም የእቴጌ ጣይቱን ጉልህ የመሪነት ሚና ለማፅደቅ፣…

“የቀፎ ንብ ሲቆጣ፣ ስሜቱ

ከፊት ሆና መራችው፣ ንግስቱ

ወይ አለና፣ ስትጠራው ጣይቱ!

ወይ ሳልላት፣ ብቀር ያኔ፣

እኔን አልሆንም፣ ነበር እኔ።”

ይለናል። በመጨረሻም፣ እንደ ጂጂ ሁሉ፣ ቴዲ አፍሮም ያ ትውልድ ያን ጥሪ ባይቀበልና ህያው መስዋዕትነትን ባይከፍል ኖሮ፣ በወኔና በፅኑ የሃገር ፍቅር ስሜት ባይጋደል ኖሮ፣ የዛሬ ማንነቴን አላገኝም ነበር ይለናል። በቀላል፣ ነገር ግን ትርጉም ባላቸው፣ ቃላት የተገነባው የቴዲ ዜማ ከበስተጀርባ በሚሰማ ህብረ ዝማሬ መታጀቡም ድምቀት ሰጥቶታል።

የ“የኛ” ቡድን አባላትም በጋራ በተጫወቱት “ጣይቱ” የተሰኘ ዜማ የእቴጌ ጣይቱን ሰብዕና አጉልተው አሳይተዋል። በእቴጌ ጣይቱ ታሪክ ውስጥ ጎልተው የሚታወቁ ሁነቶችን እየነቀሱ የሚገባትን ክብር ከመስጠታቸው በተጨማሪ ለወጣት ልጃገረዶች ያላትን በጎ አርኣያነትም በአድናቆት አስታውሰዋል።

“ኩሩ ንግስት፣ የሴት አርበኛ

አትንኩኝ ባይ፣ ፍርድ አወቅ ዳኛ

ከወርቅም ወርቅ፣ እሳት የፈተናት

ለእኔም ላንቺም፣ የመንፈስ ንቃት ናት።

“የአድዋ ጦርነት ውጤት እንደታወቀ በርካታ ዓለማቀፍ ጋዜጦች ሰፊ ሺፋን እንደሰጡት መረጃዎች ያመለክታሉ። የኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ለምሳሌ ማርች 3 እና 4 ባወጣው እትሙ በዐቢይ ርዕስነት ዘግቦበታል። ከዘገባዎቹ መረዳት እንደሚቻለው ድሉ ብዙዎችን አስደንቋል፤ አስደንግጧልም።”

ፊታውራሪ፣ እመት መላዪቱ

ጭንቅ ቀንን፣ ያነጋች ጣይቱ

አድዋ ላይ፣ ዘምታ ያዘመተች

ደግ እመቤት፣ ፍቅር አዋቂ ነች።”

ጣይቱን ከማድነቅና ከማወደስ አልፈውም በእርሷው ብርሃን ፈለጓን ተከትለው የሚጓዙ መሆናቸውን፣በየተሰለፉበት መስክ የጣይቱን ሰብዕና ወርሰው፣ እርሷን ሆነው ሃገራቸውን ለማገልገል መቁረጣቸውን በስሜትና በሚያማልል የጥበብ ቃና ያውጃሉ።

“ያገር እናት፣ ያች ልበ ብርቱ

በልቤ ውስጥ፣ በርታለች ጣይቱ።

የጀግናዋ ልጅ ነኝ፣ የጣይቱ ፍሬ

የቁርጥ ቀን ብልሃት፣ እኔም አለኝ ዛሬ።

ጣይቱ ማለት፣ እኔ ነኝ ዛሬ

አለሁልሽ ባይ፣ ለእናት ሃገሬ።”

በስተመጨረሻ ጥንታዊና ባህላዊው ፉከራ መታከሉም ጣይቱ የኖረችበትን ዘመን ወደኋላ ተመልሰን እንድንመለከት ያደርገናል። የጣይቱን ብልህነትና የአመራር ብቃት እንዲሁም በባለቤቷ ዘንድ የነበራትን ተቀባይነትም ከአፄ ምኒልክ የተለየ ሰብዕና ጋር አሰናስለው:-

“እምዬን አክብሯት፣ እሷም አክብራው

በንግስቱ ብልሃት፣ አገር የመራው

የእድገት መሠረቱ፣ የማለዳ ጮራ

ምኒልክ ወንድ ነው፣ በሴት የሚጠራ።”

በማለት አቅርበውልናል። በዚህም የጦርነቱ ዋና አቀንቃኝ ጣይቱ ስለመሆኗ ጣሊያኖችን ጨምሮ በአንዳንድ የውጪ ሃገር ሰዎች የተገለጸውን ሃሳብ ሞግተዋል። ቀደም ብለን እንደጠቆምነው በውጪ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንም የአድዋን ድል በየዓመቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ያከብራሉ። እንደዚህ ባሉት ዝግጅቶችም ላይ ብዙውን ጊዜ የየአካባቢው መንግስታት ተወካዮችና የኢትዮጵያ ወዳጆች ተሳታፊ ይሆናሉ። አልፎ ተርፎም የድሉን ታላቅነትና ፋይዳ የሚያሳዩ መግለጫዎችን ያወጣሉ። በቅርቡም አሜሪካ ውስጥ ኢትዮጵያውያን በብዛት የሚኖሩበት የሜሪላንዱ ሞንትጎመሪ ካውንቲ መጋቢት 2008ን “የአድዋ ድል ወር” ተብሎ እንዲከበር ሲያውጅ የኢትዮጵያውያንና የትውልደ ኢትዮጵያውያን አስተዋጽኦ መዘከር እንዳለበት በማሳሰብም ጭምር ነው።

ክብርና ሞገስ ለጀግኖቻችን! h�ݨ3zG

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top