ጥበብ በታሪክ ገፅ

የአድዋ ድልና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን

አፍሪካዊው የነፃነት ታጋይና የዓለም አቀፉ የሰላም ኖቤል ሽልማት አሸናፊ ኔልሰን ማንዴላ የአድዋ ድል በአፍሪካውያን፣ በአፍሪካ አሜሪካውያን፣ በሀገራቸው በደቡብ አፍሪካና በመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ትግል ውስጥ ትልቅ መነቃቃትን የፈጠረ አንጸባራቂ ድል መሆኑን በትልቁ ያሰምሩበታል።

ማንዴላ የሀገራችን ኢትዮጵያ የረዥም ዘመን የነፃነት ታሪክና ገናና ሥልጣኔ እንዲሁም በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ አውሮፓውያንን የሃፍረት ሸማ ያከናነበውና በባርነት፣ በቅኝ ግዛትና በጭቆና ቀምበር ሥር ለነበሩ ጥቁሮች ሁሉ የነፃነትን ዜና ያበሰረው ታላቁ የአድዋ ድል በእርሳቸውና በደቡብ አፍሪካውያን የፀረ-ባርነትና የፀረ-አፓርታይድ ትግል ውስጥ መቼም የማያረጅ፣ ሕያውና ደማቅ አሻራ እንዳለው ይስማማሉ። ከአድዋው ድል በኋላ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ፣ በጥንታዊቷና በነፃዪቱ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ስምና ጥላ ስር የተቀጣጠሉ የፀረ-ቅኝ ግዛትና የፀረ-አፓርታይድ የነፃነት እንቅስቃሴዎችም በራስ መተማመንን፣ ክብርን፣ አንድነትን፣ በማንነት መኩራትን እንዳስገኙ ጨምረው ተናግረዋል።

ታሪክ እንደሚመሰክረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሰማያዊው መንፈሳዊና ሐዋርያዊ ተልዕኮዋ ባሻገር በኢትዮጵያ ታሪክና ሥልጣኔ፣ ባህልና ቅርስ፣ ነፃነትና አንድነት፣ ኪነ- ጥበብና ኪነ-ሕንፃ፣ ሕግና ፍትሕ፣ ሥነ ጽሑፍና ፍልስፍና ዕድገት ውስጥ ግዙፍና ደማቅ አሻራ ያላት ሃይማኖታዊ ተቋም ናት። ቤተ ክርስቲያኒቱ ከአገራችን ነፃነትና አንድነት፣ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ክብር ጋር በተያያዘ ስሟ በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስላት፣ ስለ ነፃነት፣ ፍትሕና የሰው ልጅ ክብር በቃልም በተግባርም ጭምር ያስተማረች ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ተቋም ናት።

ከዚህም የተነሣ ቤተክርስቲያኒቱ በተለያዩ ጊዜያት የውጭ አገር ወራሪዎች ዒላማ ሆና መቆየቷን የሚመሰክሩ በርካታ የታሪክ ድርሳናት አሉ። ለዚህ ደግሞ ዋነኛ ምክንያቱ ቤተክርስቲያኒቱ ለምዕመኖቿ ስለ አገር ክብር፣ ስለ እውነት፣ ስለ ፍትሕ፣ ስለ ነፃነትና አንድነት የምታስተምር ተቋም በመሆኗ ነው። እናም ይህችን ጠንካራ ሃማኖታዊ ተቋም ማዳከም ለብዙዎቹ የአገሪቱን የነፃነት ዋልታ ከመሠረቱ መናድ መስሎ ስለሚሰማቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ሲያጠቋት ኖረዋል።

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሕዝቡ በአገሩ፣ በነፃነቱ፣ በአንድነቱና በሃይማኖቱ ላይ የመጣውን ወራሪ ኃይል ሁሉ በአንድነት ሆኖ እንዲመክት፣ ከአምላኩ ዘንድ ለተቸረው ነፃነቱና ሰብአዊ ክብሩ ቀናኢ በመሆን ዘብ እንዲቆም ስታስተምር የኖረች መሆኗ በበርካታ የታሪክ ድርሳናት የተመዘገበ ነው። እስቲ ከላይ ያነሳሁትን እውነታ የሚያጠናክሩልኝን ጥቂት ምስክርነቶች ከታሪክ መዛግብት ላጣቅስ።

ከጥንት ጀምሮ ኢትዮጵያን በአካል ተገኝተው የጎበኙ አያሌ የውጭ ተጓዦች፣ አሳሾችና የታሪክ ተመራማሪዎች ስለ ኢትዮጵያና ስለ ሕዝቦቿ በጋራ የሚመሰክሩትና የሚስማሙበት አንድ እውነት አለ። ይኸውም ‹‹ኢትዮጵያውያን ለሃይማኖታቸውና ለነፃነታቸው ቀናዒዎች ናቸው›› የሚል ነው።

ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ዳንኤል ሮፕስም በ1963 (እ.ኤ.አ) ‹‹አክሌዥያ›› በሚባልና በፓሪስ ከተማ በሚታተም ጋዜጣ ‹‹የኢትዮጵያን ቤተክርስቲያን ታውቃላችሁን?›› በሚል ርዕስ ‹‹… ወራሪዎች የኢትዮጵያን ምድር በግፍ የያዙ ስለመሆኑ ታሪክ ያወሳል፤ ነገር ግን ሃይማኖቷ ኃይሏና የእንቅስቃሴዋ መሳሪያ ሆኖ በመገኘቱ ነፃነቷን መልሳ አግኝታለች።

በማዕከላዊው ክፍለ ዘመን ‹‹የካህን ዮሐንስ ግዛት›› በአረመኔው ዓለም ተከቦ የክርስቲያን ምሽግ ሆኗል እየተባለ ስለ ኢትዮጵያ ይነገር የነበረው ሁሉ ፍጹም ልበ-ወለድ ታሪክ አይደለም። ከሁለት ሺሕ ሜትር በላይ ከፍታ ያለውን ደጋማና ለምለም መሬት ቁልቁል የሚያዩት ቀይ፣ ጥቁርና ሰርጥነት ያላቸው የእሳተ ገሞራ ውጤት ባሕርይ ያላቸው ጠረጴዛ መሰል ተራራዎች የጊዜን ውሽንፍር እንዳሳለፉትና የባሕር ዓሣም ሳይበገርና ሳይላላ ማዕበሉን እንደሚያሳልፍ … ኢትዮጵያም በታሪክ ውስጥ ጠንካራ ስፍራዋን ይዛ በነፃነቷና በልዑላዊነቷ ቆይታለች…›› በማለት ጽፏል።

ይህችው ጥንታዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን በአድዋው ጦርነትም ለዘመቻው የክተት ጥሪ ከማስተላለፍ ጀምሮ በተለያዩ የጦርነት ዓውደ ግንባሮች በመሳተፍ ጭምር ታላቅ የሆነ መንፈሳዊና ታሪካዊ አደራዋን ተወጥታለች። በአድዋው ዘመቻ በመቶ ሺህዎች ከዘመተው የኢትዮጵያ ጦር አብዛኛው ጦር፣ ሰይፍ፣ ጋሻና የነፍስ ወከፍ መሳሪያ ይዞ ነው በዘመናዊ የጦር መሣሪያና በሚሊተሪ ሳይንስ ከሰለጠነ ጦር ጋር ለመግጠም የኢትዮጵያን አምላክ ተስፋ አድርጎ የተመመው።

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ሠራዊታቸውን ክተት ብለው ወደ አድዋ የዘመቱትም የቅዱስ ጊዮርጊስን ታቦት፣ ሊቀ ጳጳሱን አቡነ ማቴዎስን፣ በርካታ ካህናትንና መነኮሳትን አስከትለው ነበር። የአድዋን ጦርነት በሰፊው የዘገቡ የአገር ውስጥና የውጭ ተመራማሪዎችም “በጦርነቱ ዕለት ብዙ መነኮሳት የሰሌን ቆባቸውን እንደደፉ፣ ወይባ ካባቸውን እንደደረቡ የቆዳ ቀሚስ ለብሰው ግማሹ በንጉሠ ነገሥቱ ዙሪያ፣ ግማሹ ከእቴጌ ጣይቱ ዘንድ የቀሩትም ከተዋጊው መኳንንትና ወታደር ጋር ሆነው ወዲያና ወዲህ እየተላለፉ ሊዋጋ ወደ ጦርነቱ የሚገባውን እያናዘዙና ከጦርነቱ ሊሸሽ ያለውንም እየገዘቱ፣ ሲያበራቱና ሲያዋጉ መዋላቸውን” ጽፈዋል። በአድዋ ጦርነት የነበረውን ሁኔታ “ታሪከ ዘመን ዘዳግማዊ ምኒልክ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ጸሐፌ ትዕዛዝ ገ/ሥላሴ በሥዕላዊ መንገድ እንዲህ አስቀምጠውታል።

“ንጉሡ ወደ ጦርነቱ ቦታ ሲደርሱ አቡነ ማቴዎስና የማርያምን ታቦት የያዙት ካህናት በኋላቸው ነበሩ። እቴጌ ጣይቱም ከዘበኞቻቸውና ከሠራዊቱ ጋር ሆነው በአቡነ ማቴዎስና በታቦቷ ጎን ነበሩ። የአክሱም ካህናት ቅዳሜ ማታ እንደ ጥንቱ አስተዳድሩን ብለው ለንጉሡ ለማመልከት መጥተው አድረው የነበሩት፣ በዚህን ጊዜ የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ሥዕልና ሰንደቅ ዓላማ ይዘው በእቴጌ ጣይቱ ግንባር ተሰልፈው ነበር። የጽዮን እምቢልተኞችም መለከታቸውንና እምቢልታቸውን እየነፉ በእቴጌይቱ ፊትና በሠራዊቱ ፊት ይጫወቱ ነበር። … ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ እስከ 4 ሰዓት ድረስ ተኩስ ሳያቋርጥ ከሁለቱም ወገን ሲተኮስ ድምፁ እንደ ሐምሌ ነጎድጓድ፣ ከተኩሱ የሚወጣውም ጢስ የተቃጠለ ቤት ይመስል ነበር። በዚህ ቀን በዓድዋ በዓይናችን ያየነውንና በጆሮአችን የሰማነውን ለመጻፍ ችግር ነው። በዚህ ጊዜ እቴጌ ጣይቱ በማጅራታቸው ድንጋይ ተሸክመው፣ በጉልበታቸው ተንበርክከው በጋለ ጸሎት ወደ ኢትዮጵያ አምላክ እግዚአብሔር ይማጸኑ ነበር።”

Addis Ababa – Ba’ata Maryam Church

በሌላ በኩል ታዋቂው ታሪክ ጸሐፊ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ “አፄ ምኒልክና የኢትዮጵያ አንድነት” በሚለው መጽሐፋቸው “እቴጌ ጣይቱ በተፋፋመው የአድዋ ጦርነት ውስጥ ጥላ አስይዘው፣ ዓይነ ርግባቸውን ገልጠው፣ በእግር እየተራመዱ በንጉሠ ነገሥቱ ልጅ በወ/ሮ ዘውዲቱና በደንገጡሮች ታጅበው በጦርነቱ መካከል መገኘታቸውን፣… አቡነ ማቴዎስም የማርያምን ታቦት አስይዘው፣ ከቀሳውስትና ከመነኮሳት ጋር ሆነው፣ የጊዮርጊስን ስብሐተ ፍቁርን እያዜሙ ሲከተሉ ዜማው ሳያልቅ በፊት ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት መደምደሙን” ጽፈዋል።

ኢጣሊያዊው ጸሐፊና የታሪክ ምሁር ኮንቲ ሮሲኒም “ከልዩ ልዩ ምንጭ እንዳገኘሁት፣ ከሐበሾችም ጽሑፍ እንደተረዳሁት፣ ጦርነቱ ሲጀመር አፄ ምኒልክ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ራስ መኮንን፣ ራስ መንገሻ አቲከም፣ ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ሌሎች የጦር ሹማምንትና መሳፍንቱ ሁሉ ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በአንድነት ሆነው ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ በአድዋ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ሲያስቀድሱና በጸሎት ሲማጸኑ ነበር…” በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል።

አድዋ ላይ በተካሄደው ጦርነት ለነፃነታቸው ቀናኢ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ዘርና ሃይማኖት ሳይለዩ፣ ሴት፣ ወንድ፣ ወታደር፣ ገበሬ፣ ካህንና መነኩሴ ሳይሉ የተሳተፉበት ነው። የድሉ መንስኤም ይኸው የኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ አንድነትና ልዩ ኅብረት ነው። ከአድዋው ድል በኋላ አፄ ምኒልክ ለወዳጅ መንግሥታት በጻፏቸው ደብዳቤዎችም ድሉ ከእግዚአብሔር የተገኘ እንደሆነ ከመግለጻቸው በላይ ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ነፃነት ሲሉ ተገደው በገቡበት ጦርነት ምክንያት ደም በከንቱ በመፍሰሱ የተሰማቸውን ኀዘኔታም ለፈረንሳዊው ሙሴ ሸፍኔ ገልጸውለታል። መጋቢት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. በጻፉት በዚሁ ደብዳቤ “… ከአላጌ ጦርነት በኋላ፣ ጣሊያኖችን ጦርነት ይቅር፣ የክርስቲያንም ደም በከንቱ አይፍሰስ፣ ዕርቅ ይሻላል ብላቸው እምቢ ብለው መጥተው በጥጋባቸው ዓድዋ ላይ ተዋግተው ድል ሆኑ። እኔ ግን በድንቁርናቸው ብዛት የነዚያን ሁሉ ክርስቲያን ደም በከንቱ መፍሰሱን እያየሁ ድል አደረኳቸው ብዬ ደስ አይለኝም። ነገር ግን በግፍ የመጡ ሰዎች ናቸውና እግዚአብሔር ግፉን አነጣጠረን…” ብለዋል።

በተመሳሳይ ለመስኮቡ ንጉሥ ለዛር ኒኮላስ በላኩት ደብዳቤም “እንደ አውሮፓ ነገሥታት ሥራት ሁሉ ጠብ መፈለጋቸውን ሳያስታውቀኝ፣ እንደ ወምበዴ ሥራት ሌሊት ሲገሰግስ አድሮ ሲነጋ ግምባር ካደረው ዘበኛ ጋር ጦርነት ጀመረ። ጥንት ከአሕዛብና ከአረመኔ አገራችን ጠብቋት የሚኖር አምላክ ከእኛ ባይለይ በእግዚአብሔር

“የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ለጦርነቱ በቂ ዝግጅት እንዲደረግ በመምከር፣ ሕዝቡን በማዘጋጀት፣ በክተት ዘመቻውና በዓውደ ግንባር ጭምር በመሳተፍ ሀገራችን ኢትዮጵያ በነፃነቷ፣ በሉዓላዊነቷ ታፍራና ተከብራ እንድትቆይ የበኩላቸውን መንፈሳዊና ታሪካዊ ድርሻ ተወጥተዋል”

ኃይል ድል አደረግሁት…” በማለት ድሉ ከኢትዮጵያ አምላክ የተገኘ መሆኑን ገልጸውላቸዋል። የአድዋ ድል አውሮፓውያን ‹‹ኢትዮጵያውያን ያልሠለጠኑ፣ አረመኔ ሕዝቦች ናቸው›› የሚለውን ከንቱ አስተሳሰባቸውን በዓለም ፊት እርቃኑን ያሳየ፣ ያጋለጠም ነው። ኢትዮጵያውያን ጀግኖች የጦር ምርኮኞች አያያዝ ሕግ ሳይጸድቅ፣ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ኮንቬንሽንና ድንጋጌዎች ከመውጣታቸው በፊት ለወረራ በግፍ የመጣው የጣሊያን ምርኮኛ ሰራዊት የሚገባውን ክብርና እንክብካቤ እንዲያገኝ በማድረግ በዓለም ፊት የሞራል ልዕልናቸውን፣ የበላይነታቸውንና ለሰው ልጆች ያላቸውን ፍቅርና ክብር አሳይተውበታል።

ስለሆነም የአድዋው ድል ኢትዮጵያ በጦር ግንባር ብቻ ሣይሆን በዲፕሎማሲው መስክም ድል ተጎናጽፋ ለሰው ልጆች ሁሉ ነፃነት፣ አንድነትና ክብር ዘብ የቆመች ልዑላዊት ሀገር መሆኗን ለዓለም ያስመሰከረችበት ነው። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንም ኢትዮጵያውያንን ሁሉ በማስተባበር ለድሉ መገኘት የተጫወተችውን ሚና ታሪክ ምንጊዜም የሚዘክረውና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ሕያው ቅርስ ነው ማለት ይቻላል። አውሮፓውያን በአፍሪካ ያደረጉትን የቅኝ ግዛት መስፋፋት ዘመቻና ጣሊያኖች ደግሞ እግራቸውን የሚዘረጉበትን የምሥራቅ አፍሪካ ማማተራቸውንና ዓይናቸውን በኢትዮጵያ ላይ መጣላቸውን አፄ ምኒልክና ኢትዮጵያውያን ቀድመው ተረድተው ነበር። የጣሊያንን የግዛት ማስፋፋት ዘመቻ በጥንቃቄ ሲከታተሉ ከነበሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት መካከል አለቃ ለማ ኃይሉ ከጦርነቱ አምስት ዓመት በፊት ትንቢታዊ ቅኔ መቀኘታቸውን ልጃቸው ደራሲ መንግሥቱ ለማ ባሳተሙት “መጽሐፈ ትዝታ ዘአለቃ ለማ ኃይሉ ወልደ

ታሪክ” ላይ ተገልጿል። እነሆ ቅኔው ፡-

ምኒልክ ግበር ላዕለ ሮምያ/ሮማ መጠነ እዴከ ትክል፣

አምጣነ ለአጺድ በጽሐ ማእረራ ወመዋዕሊሃ ለኃጉል፣

ዓዲ ተዘከር ውስተ ወንጌል፣

ላዕለ ሮምያ በለስ ኢሀሎ አስካል፣

በከመ ይቤ ወልደ ያሬድ ቃል።

ትርጉም፡-

ምኒልክ በሮማ ላይ እጅህ እንደቻለ መጠን አድርግ፣

መኸሯ ለመታጨድ፣ ቀኗም ለጥፋትቀርቧልና።

ዳግመኛ በወንጌል ያለውን አስብ፣

በሮምያ/በበለስ ላይ ፍሬ የለም እንዳለ ወልደ ያሬድ/ቃል(ወልድ)።

ሊቁ አለቃ ለማ እንደተነበዩትም ከአምስት ዓመት በኋላ የኢትዮጵያና የጣሊያን ጦርነት ተካሄደ፣ ሮማም በኢትዮጵያውያን ጀግኖች ተጋድሎ ታላቅ ውርደትና ሽንፈትን ተከናነበች። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሊቃውንት ለጦርነቱ በቂ ዝግጅት እንዲደረግ በመምከር፣ ሕዝቡን በማዘጋጀት፣ በክተት ዘመቻውና በዓውደ ግንባር ጭምር በመሳተፍ ሀገራችን ኢትዮጵያ በነፃነቷ፣ በሉዓላዊነቷ ታፍራና ተከብራ እንድትቆይ የበኩላቸውን መንፈሳዊና ታሪካዊ ድርሻ ተወጥተዋል። በዚህም ቤተክርስቲያኒቱ ለአፍሪካውያን፣ ለአፍሪካ አሜሪካውያንና ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌትና ዓርማ የመሆን ክብር እንድትጎናጸፍ አስችሏታል።

ይህን እውነታ የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ምቤኪ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2002 ዓ.ም. በሕግ የክብር ዱክትርና ማዕረግ ባበረከተላቸው ጊዜ በልደት አዳራሽ ባደረጉት ንግግራቸው “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለአፍሪካና ለመላው ጥቁር ሕዝብ ነፃነት፣ ክብርና ዓርማ የሆነችና የአፍሪካ ታሪክ፣ ባህልና ቅርስ ማከማቻ ማዕከል” መሆኗን ገልጸዋል። እግዚአብሔር አፍሪካን ይባርክ!! 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top