በላ ልበልሃ

የብሔርተኝነት ስካርና እርክቻው

ከመንግስቱ ንዋይ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ በኋላ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኩሽና ውስጥ ሲቦኩና ሲጋገሩ የነበሩ ሁለት ዋነኛ ጉዳዮች ነበሩ። አብዮታውያኑ ኢትዮጵያ በምትባል ሀገረ መንግስት ውስጥ መቀጠል ወይስ መውጣት አለብን የሚል የፖለቲካ ንትርክ ፈጠሩ። ንትርኩ ወደ ፖለቲካዊ እርክቻ ተለውጦ አንዱ ወገን መደባዊ የትግል መስመር ይዞ ሲጓዝ ሌላኛው ወገን የተማሪውን ግልብ ስሜትና የእነ ጀብሃን የፖለቲካ መስመር ማለትም “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል” የሚለውን መስመር ይዞ ተመመ። ይህ አካሄድ በሀገረ መንግሥቱ ማዕቀፍ ውስጥ መቆምን ሳይሆን ከዚያ ወጥቶ ወደ ዳር መንግሥትነት ማዘንበልን ፈጠረ። ሁኔታው ረዥሙን ጦርነት ጫረ።

ይህ ሁኔታ የሄርማን ሄስን ልብወለድ መጽሐፍ “ደሚያን”ን (Demian) ያስታውሰኛል። በመጽሐፉ ማጠቃለያ የተጻፈው መልካም ማሳያ የሚሆን ይመስለኛል። ዋናው ገጸ ባህሪይ ደሚያን ለጓደኛው ለሲንክሌር “ጦርነት ይከሰታል፣ ግን ታያለህ ሲንክሌር፤ ይህ የመጀመሪያው ነው የሚሆነው። ምናልባትም ትልቅ ጦርነት ይሆናል፣ በጣም ትልቅ ጦርነት። አዲሱ ሥርዓት ተጀምሯል፤ አሮጌው ላይ ተጣብቀው ለቀሩት አዲሱ ጦርነት እጅግ አስፈሪ ይሆንባቸዋል። ታዲያ አንተ በዚህ ወቅት ምን ታደርጋለህ?” ሲል ጥያቄውን ይደመድማል። ሲንክሌር ለዚህ መልስ አልሰጠም። እኛም የሀገራችን ጉዳይ ተቆርቋሪዎች መልስ ለመስጠት ሳንችል ቀረንና ጎራ ለየን። ጦርነቱም ቀጠለ። ጎራም ለይተን አልቀረንም፤ እስከ መጨረሻው በጦርነት ቋያ ስንቃጠል ኖርን። አሁንም ድረስ ቋያው እየለበለበን ዕውር ድንበራችንን እንጓዛለን። በዚሁ “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል” በሚለው ጉጥ ስርጓጉጥ ውስጥ የተጓዙት እነ ጀብሃ፣ ሻዕብያ፣ ግገሓት፣ ተሓህት (ህወሓት) እና ኦነግ ዋነኛ ተጠቃሾች ናቸው። የፖለቲካ ባህላችን አንድ አካል የሆነው የመገዳደል ፖለቲካ በእነዚህ የብሔርተኞች መስመር ጉዞውን ቀጥሏል። የብሔርተኞች ፖለቲካ በመገዳደል ብቻ ሳያቆም ራሳቸውን መልሰው እስከ መግደል ይወስዳቸዋል።

ዳንኤል ፍራይድ የተባለው ዕውቅ የአሜሪካን ዲፕሎማትና ፖለቲከኛ ስለ ብሔርተኞች ሲገልጽ “ብሔርተኝነት እንደ ርካሽ መጠጥ ነው። በመጀመሪያ ሰካራም ያደርግሃል፣ ከዚያም ለጥቆ ያሳውርሃል፣ ከዚያም ይገድልሃል” (Nationalism is like cheap alcohol. First it makes you drunk, then it makes you blind, and then it kills you.) ያለውን ማስታወስ ያስፈልጋል። እስቲ በዚህ የፖለቲካ መስመር የነጎዱትን ሁሉ የፖለቲካ ባህላችን እንዴት አስተናገዳቸው የሚለውን በደምሳሳው እንመልከት።

 ከኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦነግ)፣ ከሲዳማ አንድነት ንቅናቄ (ሲአን) እና ከኦሮሞ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) በስተቀር ሌሎች ብሄረተኞች በሙሉ የትጥቅ ትግላቸውን ያካሄዱትና ለውጤት የበቁት በሰሜን ኢትዮጵያ ነው። በ1965 ዓ.ም. የተመሰረተውና ግንባር ገድሊ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ (ግገሓህት) የሚባለው ቡድን በሀብታሙ አለባቸው አገላለጽ “ወደ ሚመስለኝና ወደ ሚዛመደኝ ወገኔ መልሱኝ” ብሎ የተነሳ ነበር። ግገሓህት የትግራይን የማይተካ ኢትዮጵያዊ መሠረትነት እንደ አልባሌ ጃኬት አውልቆ ጥሎ የኤርትራና የትግራይ አንድነት ብቻ ለዘላለም እንዲኖር የፈከረ ድርጅት ነበር። በሌላ አነጋገር ትግራይ ከአጼ ምኒልክ አገዛዝ ጀምሮ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ሆናለች በሚል ትግራይን ከኢትዮጵያ በመገንጠል ከወገኖቹ ኤርትራውያን ትግሬዎች

“በመደባዊ ትግል የሚያምነው ኢሕአፓም ከተሓህት ጡጫ አላመለጠም። ተሓህት “ኢሕአፓ የንዑስ ከበርቴ ትምክህተኛ ፓርቲ ነው፣ የብሔር ጥያቄን አይቀበልም በማለት ከ1970- 1972 ዓ.ም. ድረስ እያሳደደ ከትግራይ ምድር አስወጥቶ በጀብሃ ጉያ ውስጥ እንዲጠለል አደረገው”

(ከበሳዎች ጋር) መቀላቀል ነበር እርክቻው። ይህ አስተሳሰብ ከመነሻው በድንቁርና የተመራና የትግራይ ህዝብን ኢትዮጵያዊነት በውል ካለመቀበል የመነጨ ነበር። ኢትዮጵያዊነትና የትግራይ ህዝብ የአንድ ሳንቲም አንድ ገጽታ መሆናቸውን ካለማወቅ ይመነጫል። በዚህ ረገድ አስማማው ኃይሉ የትግሉን ወቅት አንድ ሁኔታ ያስታውሳል እንዲህ እያለ፡- በ1969 ዓ.ም. ኢሕአፓና ሕወሓት የድርጅታቸውን ዓላማ ካስረዱ በኋላ ያካባቢው አዛውንት ማሳረጊያውን ንግግር አደረጉ። አዛውንቱ ወደ ህወሓት አባላት እጃቸውን ዘርግተው “እናንተ ከሆዳችን የወጣችሁ ልጆቻችን ናችሁ” ወደ ኢሕአሠ አባላትም ፊታቸውን አዙረው “እናንተ ደግሞ ከሁሉም የኢትዮጵያ ግዛት መጥታችሁ ለእኛ ስትሉ ነው የምትታገሉት። የሆነ ሆኖ እኛ የትግራይ ሰዎች የሆን ስንቀር ኢትዮዽያ ከማን ጋር ልትቀር ነው? ስለሆነም እኛ ኢትዮጵያ ከሚል ጋር ነው የምንወግን” ማለታቸውን ያስታውሳል። የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነት አቋሙ ለአንዲት ሰከንድ እንኳ እንደማይደራደር የኝህ አዛውንት አንኳር ማሳሰቢያ የትግራይን ሕዝብ ልብ ለመረዳት በቂ ነው። ወደ ብሄርተኞቹ ስንመለስ፤ ገብሩ አሥራት በትግራይ ፖለቲካዊ መድረክ ሁለት ፖለቲካዊ አዝማሚያዎች መከሰታቸውን ያስረዳል። እነዚህም “ፖለቲካ ትግራይና” እና “ፖለቲካ ሽዋና” የሚባሉ ነበሩ። ፖለቲካ ትግራይና ትግራይን ከሸዋ አገዛዝ አላቆ ከኤርትራ ጋር በማቆራኘት አንድ የትግራይ ትግርኝ ግዛት [ቆላውን ኤርትራ አይመለከትም] ለመመስረት የሚሻና በሚሊዮኖች ይደገፍ የነበረ ሲሆን፤ ፖለቲካ ሽዋና ደግሞ ትግራይን በሸዋ ውስጥ ከነበረው ማዕከላዊ መንግሥት ጋር ለማቆራኘት የሚሻ አዝማሚያ ነበር።

ግገሓህት የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ነው ብሎ በመቀጠሉ ከጀብሃ ጋር ተቆራኘ። እንዲያውም ከጳጳሱ ቄሱ እንደሚባለው ገና ሳይጠናከር ከጀብሃ ጋር ሆኖ የተለያዩ ጥቃቶችን በኢትዮጵያ ላይ ፈፀመ። በ1967 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤትና በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ጥቃት አድርሶ ንፁሃን ዜጎች እንዲጎዱ አደረገ። አረቦች ከስትራቴጂ አንፃር እነሱን በመርዳት ኢትዮጵያን ለማዳከም ሌት ተቀን ደፋ ቀና እንዳሉ ሁሉ፣ ጀብሃም የእነሱን መንገድ እየተከተለ ሀገሪቱ ውስጥ ቀውስ በመፍጠር ነፃነታቸውን በቀላሉ ለመቀዳጀት ደክመው ነበር። ጀብሃ በዚህ መንገድ ሊቀጥል ቢፈልግም ሁኔታው አልጋ በአልጋ አልሆነለትም።

አንጋፋው ጀብሃና ከዚያ አፈንግጦ የወጣው ሻዕቢያ እያንዳንዳቸው የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ በሳንጃ ተሞሸላለቁና የሳህል ተራራሮች በደም አበላ ታጠቡ። የመበቃቀሉ ፖለቲካዊ ባህል በሁለቱ ድርጅቶች ብቻ ሳይወሰን በሻዕቢያም ውስጥ ገብቶ ሻዕቢያ ለሁለት ተከፈለ። የሻቢያ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ የነበረው ዑስማን ሳሊሕ ሳቤህ ተገንጥሎ በመውጣት የራሱን ድርጅት “ሕዝባዊ አርነት ኃይሎች”ን አቋቋመ። የኤርትራ ቡድኖች ግንኙነታቸው በጥርጣሬ፣ በፉክክርና ኢትዮጵያውያንን በማበጣበጥ ጥቅም ማግኘት በመሆኑ ሻዕቢያ በሳህልና በምዕራቡ ቆላ ባደረገው ወሳኝ ጦርነት ጀብሃን ውልቅልቁን አውጥቶ ከትግል ሜዳ አኮላሸው።

አሁን ደግሞ ወደ እኛዎቹ ግገሓህትና ተሓህት (ህወሓት) እንመለስ። ግገሓት ከአመሠራረቱ ለጀብሃ ያጎበደደና ለትግራይና ለኤርትራ አንድነት የቆመ በመሆኑ ራሱን ወደ ዳር አገርነት ያወጣ ድርጅት ነበር። ይህም ከኢትዮጵያዊነት ገሸሽ የማለት አባዜው በወጣትና በምሁራን የትግራይ ተወላጆች ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም። በዚህ ጊዜ ተሓህት (ከ1972 ዓ.ም. በኋላ ሕወሓት ተብሎ የሚታወቀውን) የግራ ቀደም ወጣቶችና ምሁራን ተቀባይነት የነበረው በመሆኑ በግገሓህት አባላት አሠራር ውስጥ ዲሞክራሲያዊነት አለመኖሩ ወደ ተሓህት እንዲጠጉ አድርጓቸዋል። ግገሓህትና ተሓህት አልፈው ተርፈው ሠራዊታቸውን ለማዋሃድ ዝግጅት አደረጉ። ሆኖም በክርክርና በድርድር የማያምነው የፖለቲካ ባህላችን ለዚህ ዝግጁ አልነበረም። ገብሩ አሥራት እንደሚነግረን የተሓህት አመራር የግገሓህትን ኃይል በእንቅልፍ ላይ እንዳለ በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሤራ ጠነሰሰ። በዚህም አላቆሙም። ከወደፊት ጓዶቻቸው ጋራ ተቃቅፈው የተኙ ግገሓህቶች ጎህ ሲቀድ የጠበቃቸው የጥይት ቁርስ ነበር። ገብሩ “አሁን መለስ ብዬ ሳየው ተሓህት የወሰደው እርምጃ ትክክል አልነበረም። ግገሓህት ራሱን የቻለ የፖለቲካ ድርጅት እንደመሆኑ በውስጡ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ ማበጀት የነበረበት ራሱ መሆን ነበረበት” ሲል ይቆጫል።

 በዚያች የትግራይ ምድር የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት (ኢዲህ፣ ጠርናፊት) እና ተሓህትም የተቀናጀ ፀረ ደርግ እንቅስቃሴ ለማድረግ አልታደሉም። ምክንያቱም የፖለቲካው መድረክ መቻቻል ያልታየበትና አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ብቻ ያለመ በመሆኑ ነበር። አረጋዊ በርሄ እንደሚያስታውሰው ወሳኝ የሆኑ የተሓህት ታጋዮችና የጦር ኮማንደሮች በኢዲህ ውጊያ ተገደሉ። ሆኖም የተሓህት የብቀላ ርምጃ አላቆመም።

ደምን በደም የመመለስ ፍጅቱ ተጠናከረ። በጥር 1970 ዓ.ም. ተሓህት ኃይሉ ፈርጥሞ በመውጣቱ እንደዚያ ኢዲህ ከተራራ ተራራ ሲያንቆራጥጠው እንዳልነበረ የጽዋው ገፈት ቀማሽ ሆነ። ተሓህት ተከዜን ተሻግሮ በወልቃይት ምድር ሙሉ ድል ተቀዳጀ። ለደረሰው ጥፋት ግን ተጠያቂ የሆነ አልነበረም። እንዲያውም ላለቀው ህዝብና የንብረት ውድመት ማን ተጠያቂ እንደሆነ ሳይታወቅ በ1983 ዓ.ም. የሽግግር መንግሥት ምስረታ ወቅት በአንድ አዳራሽ ውስጥ ተቀምጠው ስለ ኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል ተወያይተው እንደነበር እናስታውሳለን። እሱም ቢሆን በፖለቲካ ባህላችን መጥፎ አዚም ሳቢያ ለዘለቃው አልተጓዘም።

በመደባዊ ትግል የሚያምነው ኢሕአፓም ከተሓህት ጡጫ አላመለጠም። ተሓህት “ኢሕአፓ የንዑስ ከበርቴ ትምክህተኛ ፓርቲ ነው፣ የብሔር ጥያቄን አይቀበልም በማለት ከ1970-1972 ዓ.ም. ድረስ እያሳደደ ከትግራይ ምድር አስወጥቶ በጀብሃ ጉያ ውስጥ እንዲጠለል አደረገው።

በአጠቃላይ ተሓህትና ኢሕአፓን ያጣሏቸው ምክንያቶች፤ ማን በማን ላይ ቀድሞ ጠብ ጫሪ ሆነ የሚለው ለድርጅቶቹ ወገናዊነት  ባላቸው ሰዎች የተለያዩ ምክንያቶች ሲሰጡ ቆይተዋል። ዋናው መሰረታዊ ምክንያት ግን አንዱ ሌላውን ርዕዮተ- ዓለማዊና ፖለቲካዊ ጠላቴ ነው ብለው በመፈረጃቸው ነው ማለት ይቻላል። ኢሕአፓ ተሓህትን “ጠባብ” ሲለው ተሓህት ደግሞ ኢሕአፓን “ትምክህተኛ” ይለዋል። የየድርጅቶቹ አመራሮችም በነዚህ ሁለት የተፈበረኩ ቃላት መፋጀታቸውን ቀጠሉበት። ጀብሃና ሻዕቢያም ሁለቱን ኢትዮጵያዊ ድርጅቶች እርስ በርስ እያነካከሱ የፖለቲካ ጢባ ጢቤ ይጫወቱ ነበር። ጀብሃ ኢሕአፓን፣ ሻዕቢያ ደግሞ ተሓህትን በመደገፍ በኃይል ሚዛናቸው ላይ ሁነኛ ለውጥ አሳርፈዋል። ምንም እንኳ ህወሓት በሻዕቢያ የተረዳ ድርጅት ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት ሁለቱም በውስጣዊ ቅራኔ ተወጣጥረው ቆይተው እንደነበር መካድ አይቻልም። ቅራኔው በተለይ በሻዕቢያ ጀብደኝነትና ንቀት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ህወሓት ከሌሎች የኢትዮጵያ ድርጅቶች በተለየ “የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ ነው፤ የኤርትራ ህዝብ ጠመንጃ አይዘቀዝቅም”፣ መፍትሔውም ነፃነት ነው እስከማለት አልፎ ሄዷል። የህወሓት ከፍተኛ አመራር የነበረው ገብሩ አሥራት “ህወሓት ከኤርትራውያን በላይ ለኤርትራ ተቆርቁሯል” ሲል ሄሷል። በሌላ አገላለጽ ከጳጳሱ ቄሱ ሆኗል ነው አንድምታው። ከዚሁ ጋር ልንተችበት የሚገባው የኦሮሞ ብሔርተኛ ድርጅቶችን ጉዳይ ነው። በተለይ ኦነግ። ኦነግ ከማናቸውም የኦሮሞ ድርጅቶች በላይ የኦሮሞን ማንነትና ብሔርተኝነት አጎልብቷል።

በትጥቅ ትግሉ ሂደት እንደ ቻይናው ዳላይ ላማ ትግሉ ከዳር ባይደርስም አዝጋሚ በሆነ መልኩም ቢሆን የኦሮሞ ብሄርተኝነትን አጎልብቶ ዘልቋል።

የ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዮትም ለኦሮሞዎች “ኦሮሞ” የማንነት መጠሪያ ዘላቂ ከማድረጉም በላይ ኦሮምኛ በኢትዮጵያ ሚድያ ውስጥ እንደ አንድ ቋንቋ ሆኖ ጥቅም ላይ እንዲውል አድርጓል። ከኦነግ ቀድሞ እንደተፈጠረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ENLF) ያሉ ብሔርተኛ ድርጅቶች በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው የኦሮሞን የብሔር፣ የቋንቋና የሀይማኖት መብት ለማስከበር ጥረዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር የተባለው ድርጅት በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ሳይታወቅ እንደ ድርጅት ራሱን ሳያጠናክር በኖ ጠፍቷል።

ማርክሲስቱ ኃይሌ ፊዳ በኢትዮጵያ አብዮት ውስጥ ባለው መሪነት የኦሮሞ የነፃነት ጥያቄ ጉዳይ በአጀንዳ መልክ ወጥቶ ፖለቲካዊ ጥያቄ አልሆነም ነበር።

ከ1968 ዓ.ም. በኋላ ኦነግ ጠመንጃ አንስቶ ወደ ምሥራቅ ሀረርጌ ተራሮች ሲወጣ ነው “የነፃነት”ን ጉዳይ ማቀንቀን የጀመረው። ላለፉት 40 ዓመታትም ምንም እንኳ ፖለቲካዊ ግቡን ባይመታ የኦሮሞ ፖለቲካዊ መንፈስ ሆኖ ዘልቋል። ባህሩ ዘውዴ እንደጻፈው “ከሻዕቢያ የቴክኒክ ድጋፍ ያገኝ የነበረው ኦነግ በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ (ሐረርጌና ባሌ) እና በምዕራብ ኢትዮጵያ (ወለጋ) የሽምቅ ውጊያ ማካሄድ ቢጀምርም በነበረበት ውስጣዊ ክፍፍልና አብዛኛውን የኦሮሞ ህዝብ መቀስቀስ ባለመቻሉ የደርግን ሥርዓት እምብዛም ሊፈታተነው አልበቃም።” እነ ዚያድ ባሬ ሳይቀሩ የኦሮሞ

“በዚያች የትግራይ ምድር የኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ህብረት (ኢዲህ፣ ጠርናፊት) እና ተሓህትም የተቀናጀ ፀረ ደርግ እንቅስቃሴ ለማድረግ አልታደሉም። ምክንያቱም የፖለቲካው መድረክ መቻቻል ያልታየበትና አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ብቻ ያለመ በመሆኑ ነበር”

ብሔርተኝነትን መጠቀሚያ ለማድረግ ሲሉ “የሶማሌ አቦ ነፃነት ግንባርን” በ1968 ዓ.ም. መሥርተው ነበር። ባሬ ታላቂቱን ሶማሊያ ለመፍጠር ባለው ዕቅድ መሠረት ኦሮሞዎች ሶማሊያዊ ሆነው ሊለወጡ የሚችሉ “ጥሬ እቃዎች ” ናቸው (The Somali ruling group claimed that the Oromo were pre-ethnic raw materials who could be Somalized) የሚል የአስተሳሰብ ድፍረት እንደነበረው መሐመድ ሐሰን የኦሮሞ ብሐርተኝነት ዕድገት በሚል ጽሑፉ አስፍሮታል። አንዳንድ የኢትዮጵያ ኤሊቶች የኦሮሞ ብሔራዊ ማንነት ከተጠናከረ ኢትዮጵያን ያፈራርሳታል ብለው እንደሚሰጉት ሁሉ የሶማሊያ ገዥ ልሂቃንም የታላቋን ሶማሊያ ህልም ያጨናግፍብናል ብለው በኦሮሞ ትግል ላይ ሻጥር እንደሚፈጽሙ ይታወቃል።

ወደፊትም አይተኙም። እንግዲህ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ካቆጠቆጠበት ከ1950ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ጠንካራ ትግል ገጥሞታል። ይህም የሆነው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ከመነጋገር ይልቅ መገፋፋትን፣ ጥርጣሬንና በሾኬ መጣልን ስለሚያስቀድም መቀራረብ አልተፈቀደም። እስከ ዛሬም ድረስ በራሱ በኦሮሞ ብሔርተኞች መካከል በሁለት ጎራ የተከፈለ ቅራኔ ይስተዋላል። አንዱ ኢትዮጵያዊነትን ፈጽሞ የማይቀበል ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮጵያዊነት በእኩልነት የሚል ወገን ነው። ኢትዮጵያዊነትን ፈጽሞ አክ-እንትፍ የሚለው ብሔርተኛ የልሂቃን ሃይል በመሐመድ ሐሰን አባባል ብሔራዊ ሃይማኖት፣ የሃገር ባህል አለባበስ፣ ብሔራዊ አርማዎች (ቤተ ክርስቲያን፣ ሰንደቅ ዓላማ፣

ብሔራዊ የህዝብ መዝሙር) በኢትዮጵያ ብሔርተኝነት ስም ለሚንቀሳቀሱት የአማራና የትግራዮች ብቻ ናቸው ብለው ራሳቸውን ከኢትዮጵያዊነት ፕሮጀክት የሚያገሉ ሁነዋል። ሌሎችና በሰፊው የኦሮሞ ህዝብ ተቀባይነት ያላቸው የኦሮሞ ብሔርተኞች አስተሳሰብ ደግሞ (የእነ ዶ/ር መራራን ቡድን ጨምሮ) “ኦሮሞ ግንድ ስለሆነ አይገነጠልም” የሚሉ ናቸው። አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ጐምቱ ፖለቲከኞች እንደሚስማሙበት የኦሮሞ፣ የአማራና የትግራይ ልሂቃን የኢትዮጵያን የፖለቲካ ባህል ለማሳለጥ በተቻላቸው መጠን አይንና ናጫ ሳይሆኑ ሀላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።

አንድ ላይ ሁነው በትብብር፣ በመመካከር፣ በመከራከር ከሠሩ የህዝባቸውን መጻኢ ዕድል ያሻሽላሉ። ከተበታተኑ ግን እርስ በእርስ ይጠፋፋሉ። ከመጠፋፋት ይሰውራቸው በሚል ምርቃት ይህን ጽሑፍ ለዛሬው ከመቋጨቴ በፊት አሁንም የሔርማን ሔስ መጽሐፍ ውስጥ በዛ ክፉ የአየር ሁኔታ ውስጥ የተጠቀሰውን ዲያሎግ ማቅረብ ይኖርብኛል።

ደሚያን እንዲህ ሲል ይጀምራል፡- “ተቀመጥ በጣም የደከምክ ይመስለኛል። እጅግ በጣም አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ነው። ውጪ እንደነበርክ ያስታውቃል። ለአሁኑ ሻይ አለልህ” ይለዋል ለሲንክሌር።

 ሲንክለርም መልሶ “ዛሬ አንድ ነገር የተፈጠረ ይመስለኛል” አልኩት፤ ከዚያም “ነጎድጓድ ብቻ አይደለም የዛሬውስ” ስለው በጥርጣሬ መልክ ተመለከተኝ።

“ያየኸው ነገር አለ?”

“አዎ ለአንድ ለተወሰነ ጊዜ በግልጽ በደመናው ውስጥ ምስል አየሁ”

“ምን ዓይነት ምስል?”

“የወፍ ምስል”

“ጭልፊት ነው? ለመሆኑ ስለ ወፍ ታልማለህን”

“አዎ የእኔው ጭልፊት ነው። መልከ ብጫ የሆነ ትልቅ ጭልፊት። በሰማያዊው -ጥላሸት ደመና ውስጥ በረረ”

ደሚያንም በረዥሙ ተነፈሰ።

በሩ ተንኳኳ። ሽማግሌው አሽከር ሻይ ይዞ መጣ።

“ራስህን እርዳ ሲንክሌር። እንዲያው በዕድል አይደለም ወፉን ያየኸው።”

“በዕድል? እንዲህ ዓይነቱን ነገር አንድ ሰው በዕድል ነው

እንዴ የሚመለከተው?”

“ትክክል ነህ። ማንም አይመለከተውም። ወፍ ልዩ ነገር

አለው። ምን እንደሆነ ታውቃለህ?”

“አላውቅም። በመጻኢ ዕድላችን ላይ አንድ ያልተጠበቀ አጉል ምልኪ የሚያመጣ ይመስለኛል። ይህ በመሆኑም ሁላችንን ያሳስበናል…” እያለ ምልልሱ ይቀጥላል። አዎን! እኛም ተኝተን በተነሳን ቁጥር የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን መጻኢ ዕድል ሊያሣስበን ይገባል። ምን አይነት ምልኪ ይሆን በህልማችሁ የምታዩት? አጉል ወይስ በጎ ምልኪ?

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top