በላ ልበልሃ

የመንግስት ድጋፍ ለባህል-ስነጥበባት ኢንዱስትሪ ልማት

መግቢያ

ባህል ቁሳዊና መንፈሳዊ፣ ወይንም ተጨባጭና ረቂቅ በሚል ሁለት ጎራ ሲከፈል በእያንዳንዱ ጎራ ስር ያሉ መደቦች በአያሌው የሰፉ ናቸው። ከሰው ልጅ መፈጠርና የዘመናት እድገት ጋር በመቆራኘት የተከሰቱትንና በሂደት መልክ የያዙትን ተጨባጭና ረቂቅ እሴቶች ሁሉ የሚያጠቃልልም ነው። ባለብዙ ዘርፍ የሆነውን የረቂቅ ባህሉን አንድ አንድ አካል ማለትም ስነጥበባትንም የሚያቅፍ ነው። ባህል፣ የሰው ልጅ በራሱ ለራሱ የፈጠረው፣ በተወሰነ ማህበረ- ኢኮኖሚያዊ የእድገት ደረጃ የራሱ መገለጫና መለያ የሚያደርገው ነው። ባህል በገዢ ነባራዊ ሁኔታ ተፅእኖ የመዳበርና የመለወጥ ባህሪ ያለው በመሆኑ፣ በዚህ ሂደት ውስጥ ቀድሞ የነበሩት አላባውያን ከዘመን መጣጣም ተስኗቸው እየደበዘዙ መሄዳቸውና ከነአካቴው መጥፋታቸው እውነት ነው። የእነዚህ የአያት ቅድመ አያቶቻችን የሺዎች አመታት የህይወት ጭማቂዎች በዘመን ሲለወጡና ሲሻሩ ደብዛቸው እንዳይጠፋ ተንከባክቦና ሰንዶ ለተከታዩ ትውልድ ማስተላለፍ፣ እንዲሁም የተደረሰበትን ባህል ለሰው ልጅ በሚጠቅም መልኩ ማበልፀጉ፣ ለማህበራዊ ስልጣኔ ከሚኖረው ፋይዳ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እጅጉን የጎላ ነው። የአንድ ማህበረ-ሰብ ባህል፣ ስነ-ጥበብና ኢኮኖሚ ሊነጣጠሉ የማይችሉ፣ በጠበቀ የግንኙነት ሰንሰለት የተቆራኙ ናቸው። ዋናውና መሰረቱ ኢኮኖሚ ሆኖ በባህል ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖም ወሳኝ ነው። በአንጻሩም ባህል ኢኮኖሚውን መጋቢ ነው። የሁለቱ ተስተጋብሮ በማህበራዊ ህሊና ላይ የሚፈጥረው አዎንታዊና አሉታዊ ውጤት እንዳለ ሁኖ፣ በኢንዱስትሪ መስክ የሚያስገኘው አገራዊ ጠቀሜታ የትየለሌ መሆኑ በበለፀጉ አገሮች ምሳሌነት የሚረጋገጥ ነው።

“የባህሎች ጥንካሬና የፈጠራ ልማት በእግሩ የቆመና ቀጣይነት ባለው የባህል ኢንዱስትሪ መሰረት ላይ ያረፈ ነው” እንደሚባለው ሁሉ የባህል ኢንዱስትሪም በአኳያው ትልቅ ግምት የሚሰጠው የስራ መስክ በመፍጠርና ባህላዊ ምርቶችን በመፈብረክ በአንድ አገር ኢኮኖሚ ውስጥ ትርጉም ያለው ሚና ይጫወታል። እንዲህ አይነቱ ተስተጋብሮ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ሲታይ የመንግስትን ጣልቃ ገብነትና ድጋፍ የሚሻ ሁኖ ይገኛል። የተለያዩ አገሮችን ልምድ በማሳየት፣ ተሞክሮዎች ከአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚሰምሩበትን አኳኋን ማመላከቱ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብአት በመሆን ለአገራችን ባህል መበልፀግና ለዘርፉ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ መዳበር የበኩሉን ድርሻ እንደሚያበረክት ይታመናል።

የመንግስት ድጋፍ ለባህል ልማት፣ የአገሮች ተሞክሮ

በባህል ዘርፍ የመንግስት ሚና ምን ሊሆን እንደሚገባና እንደማይገባ የባህልና የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን በየጊዜው የተለያዩ አመለካከቶችን ያንፀባርቃሉ። አንዱ ወገን፣ ኢኮኖሚው ራሱ ባህሉን ስለሚመራ የመንግስት ጣልቃ መግባት በባህል ላይ ቁጥጥርን እንደሚፈጥር ያምናል። ሌላው ወገን ደግሞ መንግስት ማንኛውም የአገር ልማት እንደሚመለከተው ሁሉ፣ የባህል ነፃነት በተጠበቀበት አግባብ ለባህል ልማትም ተገቢ ሚና መጫወት እንዳለበት ይከራከራል። ዞሮ ዞሮ መጠኑ ይለያይ እንጂ የሁለተኛው ወገን ክርክር ሚዛን እየደፋ የተጻረሩ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ርዕይ በሚያራምዱ መንግስታት በተግባር ሲውል ይታያል።

መንግስት ባህልን በምን መልኩ ይደግፍ? አገራችን የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን አቅጣጫ ተከትላ በመንደርደር ላይ የምትገኝ ናትና፤ የነፃ ገበያ ስርዓቱን በጽኑ መሰረት ላይ የገነቡ አገሮች መንግስታት ለባህል የሚሰጡትን የዳበረ የድጋፍ ተሞክሮ ማገናዘቡ ለወደፊቱ ትልማችን የሚያገለግለን ምላሽ ያበረክታል። ከዚህ አንፃር የአሜሪካ፣ የካናዳ፣ የቻይና፣ የአውስትራሊያ፣ እንዲሁም የአፍሪካ ናሙናዎች በቅደም ተከተል ይዳሰሳሉ።

የአሜሪካ ተሞክሮ

በአሜሪካ፣ መንግስት ለፈጠራ ስራ ድጋፍ ማድረግ የጀመረው የኮፒ ራይት ስርዓትን በአገሪቷ ህገ-መንግስት እንዲደነገግ በማድረግ ነው። ይህም የተደረገው የፈጠራ ባለመብቶች ስራቸው የሚያስገኝላቸው ጥቅም እንዲከበርላቸው ዋስትና በመስጠት ለሀገር የሚጠቅም የፈጠራ ስራ እንዲያከናውኑ ለማበረታታት ነው። ይህ የቅጂ መብትን የማስከበር ጉዳይ የታለመው ሀሳብን ከመግለጽ ነፃነት ጋር ተቆራኝቶ የፈጠራ ስራ ባለ መብቶች ሀሳባቸውን የመግለጽ መብትን በብቃት እንዲያረጋግጡ ለማስቻል ነው።

ይሁንና የቅጂ መብትን ማስከበር ብቻውን ፈጠራን በማነቃቃት ረገድ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ከጊዜ በኋላ ግንዛቤ አግኝቶ፣ በ20ኛው ክፍለ ዘመን ከቀረጥ መቀነስ ጋር የተያያዘ ተጨማሪ የገንዘብ ማበረታቻ ማድረጉ ፈጠራን እንደሚያጎለብት ታመነበት። በመሆኑም አትራፊ ላልሆኑ የባህልና የስነ-ጥበብ ተቋማት ገንዘብ ለሚለግሱ በጎ አድራጊዎች የቀረጥ ቅነሳ እንዲደረግላቸው ተወሰነ። በቀረጥ ቅነሳው አማካይነት ስነ ጥበብን የመደገፍ ሁኔታ እስከዛሬ የሚሰራበት ሆነ።

አሜሪካ በታላቅ ቀውስ (Great Depression) ውስጥ ገብታ በነበረችበት ወቅት መንግስት ሌላ የድጋፍ አማራጭ ተከትሎ ነበር። ባህልና ስነ ጥበብን ለማስፋፋት በገንዘብ ከመደጎም ይልቅ ስራ ያልነበራቸውን የስነ ጥበብ ሰዎች በቅጥር ወደ ስራ ለማሰማራት መዋቅር መስርቶ በርካታ ሰዎችን መንግስት በስራ ላይ ደልድሏል። ይህንንም ተግባር (በ1970 እ.ኤ.አ. ፌደራል የቅጥርና የስልጠና ማስፈጸሚያ የተሰኘ) ድንጋጌ በማውጣት አጠናክሮታል።

ከዚህም በኋላ ቢሆን መንግስት ባህልና ስነ ጥበብን መደገፍ አለበት በሚሉና መደገፍ የለበትም በሚሉ ፈላስፋዎች፣ የህግ ምሁራንና የፖለቲካ ንድፈ ሃሳባውያን መሀል ክርክሩ ተጋግሎ ነበር።

መንግስት ስነ ጥበብን በገንዘብ መደገፍ የለበትም የሚሉ ሃያሲያን፣ መንግስት ስነ ጥበብን ከመደጎሙ በፊትም ቢሆን ታላላቅ የስነ ጥበብ ስራዎች አብበው ነበርና ያለ መንግስት ድጋፍ ስነጥበብ ሊያድግ ይችላል የሚል መከራከሪያ ነበር ያነሱት።

ሌሎች ደግሞ ያለ መንግስት ድጋፍ ስነጥበብ ሊያድግ አይችልም በማለት አጥብቀው ተቃወሙ። የተቃዋሚዎች ሃሳብ አሸናፊነትን አግኝቶ በአሜሪካ ኮንግረስ ውሳኔ መሰረት በ1965 እ.ኤ.አ. ናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዘ አርትስ (ብሄራዊ ልጋሽ ለስነጥበባት) የተሰኘ የመንግስት ድጋፍ ሰጭ ድርጅት ተቋቁሞ እስከዛሬ ሊዘልቅ ቻለ።

የአሜሪካ ኮንግረስ ይህን ድርጅት ለመመስረት በወሰነበት ወቅት በነፃ የማሰብ፣ ሃሳብን በነፃ የመግለፅና በነፃነት የማጠየቅ ጉዳይ ላይ አፅንኦት አድርጎ ነው። ኮንግረሱ ድርጅቱ እንደ ባህል ጉዳይ ዋና ተጠሪ መታየት እንደሌለበትም አስምሮበታል።

የአሜሪካ ሴኔት ከዚሁ ጋር በማያያዝ ከስነ-ጥበብ ሰው ታላላቅ እሴቶች መሀከል አንዱ ህብረተ ሰቡ የራሱን ጠንካራና ደካማ ጎን ለይቶ የሚገነዘብበት የመመርመሪያ መስታዎት መሆኑን እውቅና በመስጠት፣ ስነ ጥበባዊ ስራ በደረጃው ላቅ ያለ መሆን እንደሚኖርበትም አስረግጠዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ በተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ስነ ጥበብ ራስን የመግለፅ ሙሉ ነፃነት የሚቀዳጀው ጥበብ ለግሉ ዘርፍ ሲተው ብቻ እንደሆነና፣ ፌደራል መንግስቱ ጥበብን በቀጥታ ከደገፈ በባህል ላይ ፖለቲካዊ ቁጥጥር ወደ ማድረግ እንደሚገፋፋው በመግለፅ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር። ከነ አካቴውም የሀገሪቷ የበጀት አቅም ውስን በሆነበት ሁኔታ እንዲህ አይነቱ ልገሳ ቅንጦት እንደሆነና፣ ጥበብ የመንግስት ጉዳይም እንዳይደለ በ1981 እ.ኤ.አ. አበክረው የተከራከሩ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ነበሩ። በክርክሩ ሊያሸንፉ ግን አልቻሉም። ይህ መከራከሪያ ባህልና ስነ-ጥበብን ለመደገፍ ለማይሹ የአፍሪካ መንግሥታት እንደ ሰበብ ሲያገለግል ይስተዋላል።

በሮናልድ ሬጋን ዘመንም የአገሪቱ የአስተዳደርና የበጀት ዳይሬክተር የብሄራዊ ልጋሽ ለስነጥበባት በጀት 50 በመቶ ዝቅ እንዲል ሃሳብ አቅርቦ፣ እጅግ ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶበት ስለነበረ በ10 በመቶ እንዲወርድ ተደረገ። በ1995 እ.ኤ.አ. ደግሞ በ40 በመቶ ተቀንሷል። እንዲያም ሆኖ ድርጅቱ በአመዛኙ በዓመት 100 ሚሊዮን ዶላር ከመንግስት ድጎማ እያገኘ ሊቀጥል ችሏል።

የአሜሪካን ኮንግረስ ለዚህ ድርጅት ልዩ አስተዳደራዊ ጥበቃ እንዲደረግ በየጊዜው እየጠየቀ ነው። የፌደራል ቢሮክራሲው በአገሪቷ የባህል ፖሊሲ አማካይነት አሉታዊ ጫና እንዳያሳድር በውሳኔ አሰጣጥ ላይ ከመንግስት ውጪ ያሉ ሰዎች እንዲሳተፉ ይገፋፋል። ለዚህም ሲባል የስነ ጥበባት ብሄራዊ መማክርት እንዲቋቋም ተደርጓል። ከመንግስት የገንዘብ ድጋፍ የሚሻ ማንኛውም ሰው ወይም ድርጅት የሚያቀርበውን ፕሮፖዛል መርምሮ ለሊቀመንበሩ የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርበውም ይሄው መማክርት ነው።

የመማክርት አባላት የሚሆኑትም፣ የመንግስት አባላት ያልሆኑ፣ በስነ ጥበባት ዘርፍ የላቀ አበርክቶና አገልግሎት የሰጡ፣ በዘርፉ ሰፊ እውቀት ያካበቱ ወይንም በክህሎታቸው የታወቁ ወይንም ከፍተኛ ግንዛቤ ያላቸው የተከበሩ ሰዎች ናቸው።

በካናዳ የባህል ኢንዱስትሪ ድጎማ

 የካናዳ መንግስት ከኮንፌዴሬሽን ጀምሮ ለስነ ጥበብ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ጃክሌይ ሀርቤይ (2011) ያትታል። በተለይም በ1957 እ.ኤ.አ. የካናዳ የስነ ጥበባት መማክርትን በፌደራል ደረጃ በመመስረት የካናዳ ህዝብ የባህል ውጤቶች እንዲፈጠሩና የባህል ዘርፉ ተቀጣሪ ቁጥር እንዲያድግ ረድቷል። በ1990ዎቹ ከካናዳ አጠቃላይ የስራ ሃይል 3.1 በመቶ (447,400 ሰዎች) የባህል ዘርፍ ተቀጣሪዎች ነበሩ። በካናዳ የተለያዩ የመንግስት መዋቅር ደረጃ ማለትም በፌደራል፣ በክልላዊና በከተማ ደረጃ የባህልን ጉዳይ የሚያስተናግዱ መምሪያዎች የተቋቋሙ ሲሆን በተዋረድም የስነ ጥበብ ምክር ቤቶች ተደራጅተዋል። ለስነ ጥበባትና ለባህል ተቋማት የመንግስት ገንዘብ ድጎማ የሚደረገውም በነዚህ ሁለት አካላት ማለትም በመምሪያዎቹና በምክር ቤቶቹ አማካይነት ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ከባህል ተቋማት ውጪ ባሉ እንደ የኢኮኖሚ ልማት መምሪያ፣ የቱሪዝምና የትምህርት ተቋማት አማካይነት የገንዘብ ድጎማ ከመደረጉ ባሻገር፣ በሎተሪ ገቢ እንዲደጎሙ ማድረግም ሌላው የድጋፍ ዓይነት ነው። የካናዳ የውጭ ጉዳይ መምሪያ የውጭ ንግድ ክፍልም የስነ ጥበብ ተቋሞች በውጭ አገር ስራቸውን እንዲያቀርቡ፣ እንዲያስተዋውቁና ገበያ እንዲያፈላልጉ የገንዘብ እርዳታ ያደርጋል።

የካናዳ የቅርስ መምሪያም የባህል ኢንዱስትሪ ልማት ፈንድ አቋቁሞ፣ በካናዳ ልማት ባንክ አማካይነት ለባህል ኢንዱስትሪ የብድር አገልግሎት ኢንዲሰጥ ያደርጋል። በፌደራል ደረጃ የካናዳ ፊልም ልማት ኮርፖሬሽን ተመስርቷል። የካናዳ መንግስት ባህልን የሚደግፍበት አንዱ መንገድ በቀረጥ ነው። ከውጭ የሚገቡ የባህልና ስነ ጥበብ መሳሪያዎችን ከታክስና ከቀረጥ ነፃ በማድረግ፣ እንዲሁም ለበጎ አድራጊ ለጋሾች የቀረጥ ቅነሳ በማድረግና ለፊልም ኢንቨስትመንት ከወለድ ነፃ ብድር በመስጠት ድጋፍ ያደርጋል።

በ1996-1997 እ.ኤ.አ. በካናዳ የነበሩት 602 ፕሮፌሽናል የትውን ጥበባት ኩባንያዎች ካስፈለጋቸው የገንዘብ መጠን 32 በመቶውን የሸፈነው መንግስት ነበር። ለርዕየ ጥበባትና ለእደ ጥበባት ዘርፍ ተቋማት በ1997-98 መንግስት 57 ሚሊዮን ዶላር ለግሷል።

በዚሁ ዓመት 2300 የሚሆኑ የቅርስ ተቋማት (ሙዚየም፣ ኤግዝቪሽን ማዕከል፣ የታሪክ ስፍራዎች፣ ጋለሪዎች፣ ቤተ-መዛግብት፣ ኦብዘርቫቶሪ፣ አኩዋሪየም፣ ዙዎች) ከሚንቀሳቀሱበት 1.1 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 62 በመቶው በመንግስት የተመደበ ነበር። በፊልም ዘርፍም ፌደራል መንግስቱ የካናዳ ብሔራዊ የፊልም ቦርድን መስርቶ በሱ አማካይነት ድጋፍ ያደርጋል።

የካናዳ የስነ ጥበባት መማክርት፣ ለስነ ጥበባት፣ ለፊልም ተቋማትና ለቪድዮ ገንዘብ ይለግሳል። ቴሌፊልም ካናዳ በሚያስተዳድረው የካናዳ ፊቸር ፊልም ፈንድ ለፊልም ድርሰት፣ ለፊልም ዝግጅት ግብይትና ማስታወቂያ ድጋፍ ይደርጋል።

በ2000 እ.ኤ.አ. የካናዳ ፊቸር ፊልም አሽቆልቁሎ በነበረበት ወቅት የፌደራሉ መንግስት አዲስ ፖሊሲ በመንደፍ የፌደራል የገንዘብ ድጋፍን በእጥፍ በማሳደግ በዓመት 1 ሚሊዮን ዶላር የነበረውን 100 ሚሊዮን ዶላር በማድረስ ከአደጋ አትርፎ ታላቅ እመርታ እንዲታይ አድርጓል። የክልል የስነ ጥበባት ምክር ቤትና ሌሎች የመንግስት አካላትም እንዲሁ ድጎማ ያደርጋሉ። የካናዳ ፌደራል መንግስት ለካናዳ የድምፅ ምዝገባ ልማት ፕሮግራም 10 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ በጀት በመመደብ በብድርና በልገሳ የድምፅ ሪኮርዲንግ ኢንዱስትሪውን ያበረታታል። የገንዘብ ድጋፍን የሚያስተዳድሩለት የካናዳ ስነ ጥበባት መማክርት፣ የካናዳ ቅርስ መምሪያና የኢንዱስትሪ ህብረት ናቸው። በገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ ፌደራል መንግስቱ በ1971 እ.ኤ.አ. ባስተላለፈው የሬዲዮ ጣቢያዎች የዘፈን ኮታ መመሪያ፣ የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን አነቃቅቷል። በካናዳ ያሉ ኤ.ኤምና ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች በየሳምንቱ ከሚሰሙት ሙዚቃዎች ውስጥ ቢያንስ 35 በመቶ የካናዳ ሙዚቃዎች እንዲሆኑ መወሰኑ የስነ ጥበባት ኢንዱስትሪዎች የካናዳን ሙዚቃ ለማምረት ተበረታትተዋል።

የካናዳ መንግስት የመፃህፍት ህትመት ኢንዱስትሪ ልማት ፕሮግራም ነድፎ 30 ሚሊዮን ዶላር የአመት በጀት በመመደብ የካናዳውያን ደራሲዎች ሥራ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር አንባቢያን እንዲደርስ ያበረታታል። የፌደራል ቅርስ መምሪያና የካናዳ ሮያል ባንክም በቅንጅት ለመጽሐፍ አሳታሚዎች የብድር አገልግሎት ያበረክታሉ።

የፌደራል ስነ ጥበባት መማክርትና የአንዳንድ ክልሎች የስነ ጥበባት መማክርት እንዲሁ የገንዘብ እርዳታ ያደርጋሉ። ከዚህም የተነሳ አሳታሚዎች በሁለት ዓመት ውስጥ ከ1996-1997 እ.ኤ.አ. 10,500 መጻሕፍት በማሳተም 1.9 ቢሊዮን ዶላር አስገብተዋል። ማበረታቻው ከ1991- 1996 ባሉት ስድስት ዓመታት በየዓመቱ 20 በመቶ የህትመትና ሺያጭ እመርታ እንዲገኝም ረድቷል።

በ1999 እ.ኤ.አ የካናዳ መፅሔት ፈንድ አቋቁሞ ለሶስት ዓመት የሚደጉም 150 ሚሊዮን ዶላር መድቦ ነበር። 80 በመቶ የኤዲቶሪያል ይዘታቸው ካናዳዊ የሆኑ መፅሔቶች የዚህ ፈንድ ቀጥታ ተጠቃሚ ናቸው። አነስተኛ መፅሔቶችን ለማሳደግም በመስኩ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና ፕሮጀክቶች ድጋፍ ያደርጋል። የመጽሔቶችን ስርጭት ለማገዝ ደግሞ በፖስታ እንዲከፋፈሉ በማድረግ ወጪውን ይደጉማል። በተጨማሪም በመጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ ለሚወጡ ማስታወቂያዎች ቀረጡን ይቀንሳል።

በ2000 እ.ኤ.አ. የካናዳ ፊቸር ፊልም አሽቆልቁሎ በነበረበት ወቅት የፌደራሉ መንግስት አዲስ ፖሊሲ በመንደፍ የፌደራል የገንዘብ ድጋፍን በእጥፍ በማሳደግ በዓመት 1 ሚሊዮን ዶላር የነበረውን 100 ሚሊዮን ዶላር በማድረስ ከአደጋ አትርፎ ታላቅ እመርታ እንዲታይ አድርጓል። የክልል የስነ ጥበባት ምክር ቤትና ሌሎች የመንግስት አካላትም እንዲሁ ድጎማ ያደርጋሉ።

የካናዳ ፌደራል መንግስት ለካናዳ የድምፅ ምዝገባ ልማት ፕሮግራም 10 ሚሊዮን ዶላር ዓመታዊ በጀት በመመደብ በብድርና በልገሳ የድምፅ ሪኮርዲንግ ኢንዱስትሪውን ያበረታታል። የገንዘብ ድጋፍን የሚያስተዳድሩለት የካናዳ ስነ ጥበባት መማክርት፣ የካናዳ ቅርስ መምሪያና የኢንዱስትሪ ህብረት ናቸው። በገንዘብ ብቻ ሳይሆን፣ ፌደራል መንግስቱ በ1971 እ.ኤ.አ. ባስተላለፈው የሬዲዮ ጣቢያዎች የዘፈን ኮታ መመሪያ፣ የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን አነቃቅቷል። በካናዳ ያሉ ኤ.ኤምና ኤፍ.ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች በየሳምንቱ ከሚሰሙት ሙዚቃዎች ውስጥ ቢያንስ 35 በመቶ የካናዳ ሙዚቃዎች እንዲሆኑ መወሰኑ የስነ ጥበባት ኢንዱስትሪዎች የካናዳን ሙዚቃ ለማምረት ተበረታትተዋል።

የካናዳ መንግስት የመፃህፍት ህትመት ኢንዱስትሪ ልማት ፕሮግራም ነድፎ 30 ሚሊዮን ዶላር የአመት በጀት በመመደብ የካናዳውያን ደራሲዎች ሥራ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር አንባቢያን እንዲደርስ ያበረታታል። የፌደራል ቅርስ መምሪያና የካናዳ ሮያል ባንክም በቅንጅት ለመጽሐፍ አሳታሚዎች የብድር አገልግሎት ያበረክታሉ።

የፌደራል ስነ ጥበባት መማክርትና የአንዳንድ ክልሎች የስነ ጥበባት መማክርት እንዲሁ የገንዘብ እርዳታ ያደርጋሉ። ከዚህም የተነሳ አሳታሚዎች በሁለት ዓመት ውስጥ ከ1996-1997 እ.ኤ.አ. 10,500 መጻሕፍት በማሳተም 1.9 ቢሊዮን ዶላር አስገብተዋል። ማበረታቻው ከ1991- 1996 ባሉት ስድስት ዓመታት በየዓመቱ 20 በመቶ የህትመትና ሺያጭ እመርታ እንዲገኝም ረድቷል። በ1999 እ.ኤ.አ የካናዳ መፅሔት ፈንድ አቋቁሞ ለሶስት ዓመት የሚደጉም 150 ሚሊዮን ዶላር መድቦ ነበር። 80 በመቶ የኤዲቶሪያል ይዘታቸው ካናዳዊ የሆኑ መፅሔቶች የዚህ ፈንድ ቀጥታ ተጠቃሚ ናቸው። አነስተኛ መፅሔቶችን ለማሳደግም በመስኩ ለሚደረጉ እንቅስቃሴዎችና ፕሮጀክቶች ድጋፍ ያደርጋል። የመጽሔቶችን ስርጭት ለማገዝ ደግሞ በፖስታ እንዲከፋፈሉ በማድረግ ወጪውን ይደጉማል። በተጨማሪም በመጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ ለሚወጡ ማስታወቂያዎች ቀረጡን ይቀንሳል።

የብሔራዊና ክልሎች የስነ ጥበባት መማክርት፣ እንዲሁም የካናዳ ማህበራዊና ስነሰብ ጥናትና ምርምር ምክር ቤት፣ ለምሁራዊ ምርምርና ስነ ጽሑፍ መፅሔቶች (ጆርናሎች) ገንዘብ ይረዳሉ። በእንዲህ ዓይነት ድጋፍ ከ1996-97 እ.ኤ.አ. የመጽሔቶች ብዛት 1550 ደርሶ 539 ሚሊዮን ቅጅዎች ተሽጠዋል።

የቻይና መንግስት ድጋፍ ለባህል

በማኦ ዘመን ማንኛውም የባህል ወጪ ይሸፈን የነበረው በመንግስት ብቻ ነበር። የዲንግ የኢኮኖሚ ሪፎርም ከታወጀ በኋላ ግን ጥበባትንና ባህልን የማራመዱ ሀላፊነት የመንግስት ብቻ መሆኑ ቀርቶ ከገበያ ኢኮኖሚ ጋር እንዲዋሃድ ተደርጓል። በመሆኑም ቀድሞ በባህል አብዮት ሳቢያ ጠብቦ የነበረው የፈጠራ ምህዳር ሊሰፋና ከ1970ዎቹ እስከ 1980ዎቹ አጋማሽ ባለው ጊዜ እጅግ በርካታ የስነ ጥበባት ውጤቶች ሊመረቱ ችለዋል። በአሁኑ ወቅት ባህልና ስነ ጥበባት በቻይና ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ከንግድ ጋር ተያይዘዋል። ቢሆንም መንግስት ከፍተኛ ወጪ ለሚጠይቁ ድራማዎች፣ ኦፔራዎች፣ ሙዚቃና ዳንሶች፣ እንዲሁም የተለያዩ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ከፍተኛ በጀት በመመደብ እየደገፈው ይገኛል። ይህም ብሔራዊ ኩራትን በመንግስትም በህዝቡም ዘንድ አሳድሯል። የቻይና መንግስት በስነ ጥበባት ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ የሚያከናውነውን ተግባር የሚወዳደረው አገር የለም። በአጠቃላይ በዓለም ላይ ያሉት የስነ ጥበባት ምርቶች ቢደመሩ ከቻይናዎቹ ጋር በቁጥር የሚስተካከሉ አይደሉም።

የቻይና መንግስት በ2000 እ.ኤ.አ. ለስነ ጥበባት የመደበው በጀት 3.6 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን፣ በ2005 በእጥፍ ያህል አሳድጎት 6 ቢሊዮን ዶላር አድርሶታል። ታላቁን የብሔራዊ ቴያትር በ365 ሚሊዮን ዶላር በቤጂንግ እንዳሳነፀው ሁሉ ለሌሎች ከተሞች የስነ ጥበባት ማካሄጃ ግንባታዎችና ቁሳቁሶችም ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ያወጣል። እንዲያም ሆኖ የመንግስት የስነ ጥበባት ተቋማት በራሳቸው የውስጥ አስተዳደር እየተመሩ ከፍተኛ ገቢ እንዲያስገቡ ይበረታታሉ። የግል የስነ ጥበባት ድርጅቶችም ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ የ147 ሚሊዮን ዶላር የብድር አገልግሎት ከመንግስት የኢንዱስትሪና ንግድ ባንክ በየዓመቱ ያገኛሉ።

የአውስትራሊያ መንግስት ድጋፍ

የአውስትራሊያ መንግስት የባህል ተቋማት በገበያ ኢኮኖሚ ውጤታማ እንዲሆኑ እገዛ ያደርጋል። በዚህም የአውስትራሊያ የባህል ኢንዱስትሪ ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ የስራ መስክ ሆኗል። ከ1989 እስከ 1990 እ.ኤ.አ. ባለው ጊዜ ውስጥ 13 ቢሊዮን ዶላር ለባህል ፍጆታ መዋሉ ይህንኑ ያመለክታል።

የአውስትራሊያ መንግስት ለባህል ኢንዱስትሪው የድጋፍ ፕሮግራም በመዘርጋት ለባህል አራማጆችና ተቋማት ገንዘብ ከመደጎም አልፎ የባህል ኢንዱስትሪው ምርት ከፍ እንዲል፣ የባህል ዘርፍ ውጤቶች ለውጪው ገበያ እንዲቀርቡ፣ ኢንዱስትሪው በአዲስ ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ፣ የአእምሮ ሃብት ጥበቃ እንዲያገኝ፣ የባህል ውጤት ፍላጎት ከፍ እንዲልና በባህል ኢንዱስትሪው ላይ ተከታታይ ጥናትና ምርምሮች እንዲካሄዱ የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ ይንቀሳቀሳል።

የአፍሪካ መንግስታት ድጋፍ

በርካታ የአፍሪካ አገሮች በተለይም የኬንያ፣ የጋና፣ የግብፅ፣ የናይጄሪያና የደቡብ አፍሪካ የበለፀጉ አገሮችን አሰራር ተከትለው ለባህል ልማት ዘላቂነት ያለው ድጋፍ ያደርጋሉ። የኬንያ መንግስት በተለይ ለባህልና ስነ ጥበብ ርዳታ ለሚያደርጉ የንግዱ ማህበረ ሰብ አባላት የታክስ እፎይታ የሚያገኙበትን ስርአት ዘርግቶ ያበረታታል።

የጋና መንግስትም በተመሳሳይ መልኩ ለባህልና ስነ ጥበባት ዘርፎች ልገሳ ለሚያደርጉና ስፖንሰር ለሚሆኑ ድርጅቶች የታክስ እፎይታ ይሰጣቸዋል። የባህል ባለአደራ ቋት (Cultural Trust Fund) አቋቁሞ ገንዘብ በተለያየ መንገድ ወደዚሁ ቋት እንዲፈስ ያደርጋል። መንግስት የራሱን ልዩ መዋጮ በማስቀመጥ፣ ከብሔራዊ ሎተሪ ገቢ 10 በመቶ ወደ ቋቱ በመላክ፣ ከኤግዚቪሽኖች እና ማስታወቂያዎች እንዲሁም ከኮፒ ራይት ጥበቃ ከሚገኙ ገቢዎች በመቶኛ በመለገስ ባንኮችና አበዳሪ ድርጅቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግና የፊልም ኢንዱስትሪ ኢንቨስትመንት የሚበረታታበትን ሁኔታ በማመቻቸት ለባህልና ስነ ጥበብ ድጋፍ ያደርጋል። የግብፅ መንግስትም ተመሳሳይ ድጋፍ የሚያደርግ ሲሆን ጠንካራ ብሔራዊ የሲኒማ ኮርፖሬሽን ማደራጀቱ ልዩ ግምት የሚያሰጠው ነው።

የመንግስት ድጋፍ ለባህል በኢትዮጵያ

በየዘመኑ የተነሱ የተወሰኑ መንግስታትም እንደየርእያቸው ለባህልና ስነ ጥበብ ድጋፍ ያደርጉ ነበር። የአክሱም ዘመኑ ንጉስ አፊለስ፣ ያሬድን በሙዚቃና ውዝዋዜ ፈጠራው ያበረታታው የነበረው የ6ኛ ክፍለ ዘመኑ አጼ ካሌብ ወራሽ አጼ ገብረመስቀል፣ የ12ኛ ክፍለ ዘመኑ ንጉስ ላሊበላ፣ የ15ኛ ክፍለ ዘመኑ አጼ ዘርአ ያዕቆብና የ17ኛው ክፍለ ዘመን አጼ ፋሲል ከሌሎች ነገስታት በተለየ ለባህል ግንባታና ስነ ጥበብ መበልፀግ ልዩ ትኩረት ሰጥተዋል። በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ ዘመን (ዘመነ መሳፍንት) ሊጠቀስ የሚችለው የአጼ ቴዎድሮስ የጋፋት እደ ጥበባት ተሞክሮ ነው።

በ20ኛው ክፍለ-ዘመን ማክተሚያ ላይ አጼ ምኒሊክ ወደ ውጭ አገር በላኳቸው እንደነ ተክለሃዋሪያት ተክለማሪያም ያሉ ወጣቶችና ፈረንጅ ነጋዴዎች አማካይነት ወደ ኢትዮጵያ መግባት ለጀመረው ዘመናዊ ስነ ጥበብ ልዩ ድጋፍ ሰጥተዋል።

የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግስትም ከፍተኛ የገንዘብና ሞራል ድጋፍ ሰጥቷል። በተለይ በዚህ ዘመን ቀድሞ ላልነበሩ ቴያትር ቤቶች፣ የሙዚቃ ቡድኖች፣ ሙዚዬሞች፣ የስዕልና ቅርፃቅርፅና የሙዚቃ ትምህርት ቤቶች፣ የቅርስ ጥበቃ ተቋማት፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ቤተ-መዛግብት፣ የሬዲዮና ቴሌቪዥን ጥበባት፣ የስነ ጽሑፍ ህትመቶች ወዘተ መሰረት የተጣለ ሲሆን እንደ ሲኒማ ባሉት ዘርፎች የግል ባለሀብቶች እንዲሰማሩ ማበረታቻ ይደረግላቸው ነበር። እንዲያም ሆኖ የሳንሱር ጫናው ለጥበቡ ዕድገት መሰናክል ሆኖ ቆይቷል። በዚህም አፈወርቅ አዳፍሬና አቤ ጉበኛ በመሳሰሉት ደራሲያን ላይ ይደርስ የነበረውን ስቃይ በታሪክ ተዘግቧል። የደርግ መንግስት ደግሞ በዩኒቨርሲቲ የቴያትር ጥበባት ትምህርት እንዲጀመር፣ የፊልም ማዕከል እንዲደራጅ፣ በየከፍተኛውና በተወሰኑ ክፍለ-ሀገሮች የኪነት ቡድኖች እንዲቋቋሙ፣ ሁለት ተጨማሪ የቴያትር ቤቶች እንዲመሰረቱ፣ ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት እንዲቋቋምና ደራሲያንን እንዲረዳ የገንዘብ ድጋፍ ያደርግ ነበር። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱ የስነ ጥበብ ድጋፍ፣ መንግስቱ ይወስዳቸው በነበሩት ተቃራኒ እርምጃዎች ምክንያት የሚጠይም ሆኗል። በተለይም ለባህል መስክ ይደረግ የነበረው የገንዘብ ድጎማ ከኢትዮጵያ ህዝቦች አኳያ ፍትሐዊ አለመሆኑ፣ በግል ይዞታ ስር የነበሩ የስነ-ጥበብ ተቋማትን መውረሱ፣ ሃሳብን የመግለፅ ነፃነትን በተደራጀ የሳንሱር ጽሕፈት ቤት በቁጥጥሩ ስር ማዋሉ፣ መርካቶ በሰባተኛ አካባቢ ድራማ በማሳየት ላይ የነበሩትን በመድረክ ላይ መረሸኑ፣ የመብት ጥያቄ ያነሱ የብሔራዊ ቴያትር ጠቢባንን ማሰሩና በወቅቱም አንድ የአዲስ አበባ ባህል አዳራሽ ባለሙያ ሲገደል የተወሰኑት መቁሰላቸው፣ ከደራሲ በአሉ ግርማ ህልፈት ጋር መጣቀሱ ከድጋፉ ይልቅ ከባህልና ስነ ጥበብ ጋር የነበረው አሉታዊ ግንኙነት እንዲገዝፍ አድርጎታል።

የኢፈዴሪ መንግስት ያራመደው የፖለቲካና ማህበረ-ኢኮኖሚ አካሄድ የባህልና ስነ-ጥበብ አቅጣጫን በተወሰነ መልኩ የተለየ አድርጓል። በህገ መንግስቱና ከዚያ በመነጩ የኢኮኖሚ፣ የባህልና ተጓዳኝ ፖሊሲዎች ውስጥ ስለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ባህልና ስነ ጥበብ መከበር እንዲሁም ስለቅድመ ምርመራ መወገድ ድንጋጌዎችን አውጥቷል። ከዚህ አቅጣጫ ጋር ተያይዞም የሚካሔዱ ፌስቲቫሎች፣ የሚቀረፁ የሙዚቃና የዳንኪራ ቪሲዲዎች፣ የሚቀነባበሩ ፊልሞች፣ የሚመሰረቱ የባህል ተቋማት፣ የሚታተሙ መጻሕፍት፣ መጽሔቶችና ጋዜጣዎች፣ የሚቋቋሙ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች፣ ጋለሪዎች፣ የኤግዚቪሽን ማዕከላት፣ ሙዚዬሞች፣ የስነ-ጥበባ ትምህርት ቤቶች ብዛት ከማንኛውም ጊዜ በላይ ጎልቶ ይታያል። እንደ ቀደሙት መንግስታት በተወሰነ መጠንም ቢሆን ለስነ ጥበባት ማዕከላት የገንዘብ ድጎማውን ቀጥሎበታል። ይሁንና ከተደነገጉት የህገ-መንግስቱ አንቀጾች አፈፃፀም አግባብ ጋር የሚጣረሱ ተግባራቱና አንዳንድ የወጡ መመሪያዎች በስነ ጥበባት በተለይም በቴያትር ዕድገት ላይ ጉልህ ተግዳሮቶችን መፍጠራቸው አልቀረም። የኢትዮጵያ የፊልም ማዕከል መፍረሱና በባህል የኢትዮጵያ የፊልም ማዕከል በፍረሱን፡ በባህል ፖሊሲው ውስጥ ከተዘረዘሩት የድጋፍ ድንጋጌዎች ውስጥ በሁለት አሰርት ዓመታት የተከናወኑት እጅግ ውስን መሆናቸው፤ በተለይ የቀረጥ ተጽእኖ መንግስት ለባህልና ስነጥበባት ሊያደርገው ከሚገባ ድጋፍ ጋር እየተያያዘ የዘወትር መከራከሪያ ሆኗል።

ከዚህ በመነሳት ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱት የተለያዩ አገሮች ተሞክሮዎችን በማገናዘብ፤ ለፈጣን የባህልና የስነ ጥበባት ልማት መንግስት ምን ማድረግ እንደሚጠበቅበት እንደሚከተለው ለመጠቆም ይሞከራል።

ለባህልና ለስነ ጥበባት ከመንግስት ምን

ድጋፍ ይጠበቃል?

. ብሔራዊ የስነጥበባት የገንዘብ ድጋፍ ድርጅት ማቋቋም፣

. ከመንግስት የገንዘብ ድጋፍ የሚሻ ማንኛውም

አካል የሚያቀርበውን ፕሮፖዛል መርምሮ የውሳኔ ሀሳብ የሚሰነዝርና በአገሪቱ የስነ ጥበባት ጉዳይ ላይ የሚመክር ብሔራዊ የስነ ጥበባት የመማክርት ጉባኤ ማቋቋም፣

. በስነ ጥበባት ዘርፍ የላቀ አበርክቶና አገልግሎት የሰጡ፣ በዘርፉ ሰፊ ዕውቀት ያካበቱ ወይንም በክህሎታቸው የታወቁ ወይንም ከፍተኛ ዝንባሌ ያላቸው የተከበሩ ሰዎች ለዚሁ የመማክርት ጉባኤ አባልነት ተመልምለውና በፓርላማ ቀርበው እንዲፀድቁ ማድረግ፣

. በክልልና በዞን ደረጃም በተመሳሳይ ሁኔታ የስነ ጥበባት መማክርትን መመስረት፣

. አትራፊ ላልሆኑ የስነ-ጥበብ ተቋማት ገንዘብ ለሚለግሱ በጎ አድራጊዎች የቀረጥ ቅነሳና እፎይታ እንዲደረግላቸው መወሰን፣

. በኢኮኖሚ ልማት፣ ቱሪዝም፣ ትምህርት፣ ጤና፣ መከላከያ፣ ጸረ-ሙስና፣ ኢንዱስትሪ፣ ንግድና ውጭ ጉዳይ የተሰማሩ የመንግስት ተቋማት ለስነ ጥበባት የገንዘብ ቋት እንዲፈጥሩ ማነቃቃት፣

. ብሔራዊ ሎተሪ ለስነ ጥበባት ዕድገት የገንዘብ አቅም የሚያዳብርበትን አግባብ መፍጠር፣

. ባንኮች ለባህልና ለስነ ጥበባት ኢንዱስትሪው የብድር አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፣

. የፈረሰው የኢትዮጵያ ፊልም ኮርፖሬሽን እንዲያንሰራራ ማድረግ፣

. ከውጭ የሚገቡ የባህልና የስነጥበባት ዕቃዎችን ከቀረጥ ነፃ ማድረግ፣ ከጎጂ ምርት ጋር ተመሳስሎ በባህልና ስነ ጥበባት ዘርፎች ላይ የተጣለው ቀረጥ እንዲስተካከል ማድረግ፣

. ብሔራዊና ክልላዊ የፊልም ቦርድ ማቋቋም፣

. በፊልም ቦርድ አማካኝነት ለፊልም ተቋማት፣ ለቪድዮና ለፊቸር ፊልም ድርሰት፣ ዝግጅት፣ ስርጭት፣ ግብይትና ማስታወቂያ ድጋፍ የሚያርግ የፈንድ ተቋም መመስረት፣

“እንደ ቀደሙት መንግስታት በተወሰነ መጠንም ቢሆን ለስነ ጥበባት ማዕከላት የገንዘብ ድጎማውን ቀጥሎበታል። ይሁንና ከተደነገጉት የህገ-መንግስቱ አንቀጾች አፈፃፀም አግባብ ጋር የሚጣረሱ ተግባራቱና አንዳንድ የወጡ መመሪያዎች በስነ ጥበባት በተለይም በቴያትር ዕድገት ላይ ጉልህ ተግዳሮቶችን መፍጠራቸው አልቀረም”

ለድምፅ ዘገባ መርሐ ልማት ፕሮግራም የዓመት በጀት በመመደብ በስነ ጥበባት መማክርት በኩል በብድርና በልገሳ የድምፅ ሪኮርዲንግ ኢንዱስትሪውን ማበረታታት፣

. የመጻሕፍት የህትመት ኢንዱስትሪ ልማት ፕሮግራም በመመስረትና የአመት በጀት በመመደብ የደራሲያን ስራ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር አንባቢያን እንዲዳረስ ማድረግ፣

. ባንኮች የመጻሕፍት አሳታሚዎች የብድር ፕሮግራም ዘርግተው አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፣

. የመጽሔት ፈንድ በመደብ የኤዲቶሪያል ይዞታቸው ከሞላ ጎደል አገርኛ የሆኑ መጽሔቶች የዚህ ፈንድ ቀጥታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ፣

. አነስተኛ መጽሔቶችን ለማሳደግ በኢንዱስትሪ ግንባታና አቅርቦት መርሀ ግብር ድጋፍ ማድረግ፣

. የመጽሔቶችን ስርጭትን ለማገዝ መጽሔቶች በፖስታ በሚከፋፈሉበት ወጪ ላይ ድጎማ ማድረግ፣

. የፌደራልና የክልሎች የስነ ጥበባት መማክርት ለስነ ጥበባት ጥናትና ምርምር እንዲሁም ለምሁራዊና ስነ ጽሑፋዊ መጽሔቶች ህትመት ቋሚ የገንዘብ ድጋፍ እንዲያደርጉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት።

. የባህልና የፊልም ፖሊሲን እንዲሁም መመሪያዎችን መፈተሸ፣

. የአገር ውስጥ የባህል ኢንዱስትሪ በአዳዲስ ቴክኖሎጂ ታግዞ ምርቱ ከፍ የሚልበትንና ወደአለም አቀፉ ገበያ የሚቀላቀልበትን ዘዴ መተለም፣

. ባለጸጐች ሊሰማሩባቸው ዝግጁ ያልሆኑባቸውን የባህል ዘርፎች ለይቶ ተቋማትን ለመገንባትና ለማደራጀት ጥረት ማድረግ፣

. የዩኒቨርሲቲዎቹ የስነ ጥበባት ትምህርት ካሪኩለሞችና መርሀ ግብሮች ደረጃቸውን የጠበቁ መሆናቸውን ማረጋጥ፣

. የመንግስት የባህልና ስነ ጥበባት ተቋማት በነፃ አስተዳደር እየተመሩ በላቀ የስነ-ጥበብ ውጤት አማካይነት ከፍተኛ ገቢ እንዲያስገኙ የተሻለ ስልት መንደፍ፣

. በአገሪቱ የሚገነቡና ከፍተኛ ገንዘብ የሚፈስባቸው የባህልና ስነ ጥበባት ተቋማት ዲዛይንና ግንባታቸው ሙያዊ ደረጃቸውን የጠበቁና ከብልሹ አሰራር የጸዱ መሆናቸው የሚረጋገጥበትን መንገድ መዘርጋት፣

. የስነ ጥበባት ትምህርት ከሙአለ ሕፃናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በስርአተ ትምህርቱ እንዲካተት ማድረግ፣

. በስርአተ ትምህርቱ ውስጥ ስነ ጥበባትን እንደ ማስተማሪያ ዘዴ ለመገልገል ብልሀቶቹን ከበለጸጉ ሀገሮች ቀስሞ በተግባር ላይ ማዋል፣

. ማህበረ ሰቡ የራሱን ጠንካራና ደካማ ጎን የሚመለከትበት፣ በደረጃው ላቅ ያለ ስነ ጥበባዊ ስራ እንዲከናወን የተሟላ የጥበባዊ ገለፃ ነፃነት እንዲዳብር ማድረግ፣

. የቅጂ መብት ስርዓት ድንጋጌ እንዲጠናከርና የፈጠራ ባለ መብቶች ጥቅም እንዲከበር የመንግስት ድጋፍ ወጥና ዘላቂ የሚሆንበትን ስልት መንደፍ፣

. አመታዊ የስነ ጥበባት ፌስቲቫሎች ከክልል እስከ ወረዳ ባሉ ተቋማት አመራር በዘላቂነት እንዲካሄድ ማድረግ፣

. በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ ለነዋሪው ማህበራዊና ባህላዊ አገልግሎት በአረንጓዴ መስክነት ተከልለው የነበሩ መሬቶችን ለሺያጭ ጨረታ አለማቅረብ፣ የተሸጡትን ወደ ነበሩበት መመለስ፣

. በምርምር የታገዘ የባህል የስነ ጥበብ ሰነድና ምዝገባ ስልት መዘርጋት፣

. ማንኛውም ግንባታና ምርት ሲካሄድ ለጥበባዊ እሴቱ ልዩ ትኩረት ካልተሰጠ ኪሳራ እንደሚያስከትል አስተውሎ መንቀሳቀስ፣

. አገር በቀል ባህሎች ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ፖለቲካዊና ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚውሉበትን መንገድ በተደራጀ ጥናትና ምርምር መደገፍ፣

. የመተሳሰብ፣ የመደጋገፍ፣ የመከባበር፣ የመቻቻል፣ የመፈቃቀር፣ የማምረት፣ የነፃነት፣ የሀቀኝነት፣ የእኩልነት፣ የዲሞክራሲያዊነት፣ የአንድነት እሳቤ ሰርፆ ዘላቂ ባህል እንዲሆን ከሙአለ ሕፃናት እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያሉት የየክፍሎቹ ስርዓተ-ትምህርቶች በጥሞና እንዲመረምሩ ያላሰለሰ ድጋፍ ማድረግ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top