ማዕደ ስንኝ

ዝክረ ዓድዋ ግጥሞች፤ በ3 ግጥሞች ላይ የተደረገ የይዘት ትንተና

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ የዓድዋ ድል በሦስት ገጣሚያን ዘንድ እንዴት እንደተዘከረ ማሳየት ነው። ገጣሚያኑ በዓይነ-ልቦናቸው ወደ ኋላ ተመልሰው በብዕራቸው የከተቧቸውን ግጥሞች ከታሪካዊ እውነታው ጋር ለማገናዘብ ተሞክሯል። ይህም የተደረገበት ምክንያት እንዴት ነበረውን ለማወቅ ይረዳል በሚል እምነት ነው። ከዚህ ባሻገር ገጣሚያኑ የሰሙትንና ያነበቡትን ታሪክ በግጥሞቻቸው እንዴት አቀረቡ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስም ያስችላል። ይህ ጽሑፍ የዓድዋን ድል አንድ መቶኛ ዓመት ምክንያት አስመልክቶ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ከቀረበ ሰፋ ያለ ጥናት ላይ አጠር ብሎ የቀረበ ነው።

የዓድዋ ድል በቅኝ ገዢዎችና ተገዥዎች መካከል በነበረው ግንኙነት አዲስ ሁኔታ የፈጠረ ነው። ይህን አዲስ ምዕራፍም ዳኘው ወልደሥላሴ (1974፤6) እንደሚከተለው ገልፀውታል።

“ቁጥራቸው 20‚000 የሚሆን የሠለጠኑ የአውሮፓ ወታደሮች ካልሰለጠኑ የአፍሪካ ወታደሮች ጋር ጦርነት ገጥመው በመደምሰሳቸው በዓለም ታሪክ ውስጥ የሌለ ነገር ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረሱ የሚያስደንቅ ሆነ። … ጦርነቱን አስደናቂና አስገራሚ ያደረገው የሞቱትና የቆሰሉት ሰዎች ብዛት ብቻ አይደለም። የጦርነቱ ውጤት ለቅኝ ገዥዎች ወደፊት የሚገጥማቸውን ችግር የሚያመለክት አሳሳቢ ዜና መሆኑም ጭምር ነው።”

ይህ ድል ቅኝ ገዥዎችን ሁሉ አስደንግጧል፤ በቅኝ የመግዛት ፍላጎታቸውን አጨልሟል። ለቅኝ ተገዥዎች ደግሞ ብሩህ ተስፋ አመልክቷል። ዓለሜ እሸቴ (1970፤15) እንዳሉትም “የዓድዋ ጦርነት ድል የኢትዮጵያ ነፃነት ድል፤ የአፍሪካ ነፃነት ድል በኢምፔሪያሊዝም ላይ ሆንዋል”።

የዓድዋን ድል ያስገኙ የኢትዮጵያ ጀግኖች ጦርነቱን ለመሩት ለንጉሡና ለንግሥቲቱ እንዲሁም ከፍተኛ ተሳትፎ ለነበራቸው መሳፍንትና መኳንንትም በተለያዩ አጋጣሚዎች በቃልም በጽሑፍም ግጥሞች ተደርድረውላቸዋል።

 በዚህ ጽሑፍ ሥራቸው ከቀረበው ከሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፣ ፀጋዬ ገብረመድህንና ንጋቱ መርሻ ሌላ ሰዓሊ አገኘሁ እንግዳ፣ ገዝሙ (የብዕር ስም?)፤ ሐሰን አማኑና ሌሎችም ስለ ዓድዋ ድልና አበው ጀግኖች በጽሑፍ ግጥም ደርድረዋል። በዚህ ጥናት የሁሉንም ማቅረብ ባለመቻሉ የሦስቱን ብቻ ቀጥለን እንመለከታለን። ግጥሞቹ የተመረጡበት ምክንያት ለዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ባላቸው ቅርበት ነው።

 በአቶ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው “የተስፋ እግር ብረት” (1969፤144-149) መጽሐፍ ውስጥ ከተካተቱት ግጥሞች መካከል “የድል በዓል ማለዳ” ይገኝበታል። ግጥሙም ዓድዋ ላይ ሞቶ ስለቀረ አንድ ወታደር መታሰቢያነት የቀረበ ነው። ይኸው ግጥም “የዐድዋ ድል” በሚል ርዕስ በ1965 ዓ.ም. በመነን መጽሔት ለአንባቢያን ቀርቦ ነበር። በግጥም መድብላቸው ተካትቶ ለአንባቢያን እንደገና ሲቀርብ ከግጥሙ ርዕስ ጀምሮ ተሸሽሏል። ግጥሙም በመታሰቢያነት (ለአያታቸው?) ለአቶ ፍሬው ወርቁ ዓድዋ ለቀሩት እንደሆነ ከርዕሱ ቀጥሎ ተመልክቷል። “የዐድዋ ድል” በሚል ርዕስ ግጥሙን የደረሱት የሚያዚያ 27 ድልና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 10ኛ ዓመት በዓል በሚከበርበት ወቅት ነው።

የአምስቱ ዓመት የጠላት ወረራ የተደመደመበት ቀን በሚከበርበት ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ በየአውራ ጎዳናው የተሰቀለው የኢትዮጵያ ባንዴራ ከርቀት በሚመጣ ነፋስ እየተውለበለበ ሲያዩና በነፋስም የባንዴራዎች ውልብልብታ በሚፈጥረው “ጭብጨባ” “የልባቸው ብብት” መነካቱንና ስሜታቸው መኮርኮሩን ያስነብባሉ። ብብቱን የተኮረኮረ ሰው ይስቃል። የእንክትክት ሣቅ። ለተነካው ስሜቱ መልስ መስጠት ስለአለበትና የሚመልሰውም በሳቅ በመሆኑ። ደራሲውም ድምቅምቅ ባንዴራችን ስሜታቸውን በመንካቱ መልስ የሰጡት ብዕር ከወረቀት አገናኝተው ነው። የብዕራቸውን ውጤትም ለአንባቢያን አጋርተዋል።

የባንዴራዎቹ ጭብጨባ

 የቀለማቱ አበባ

 እየተራገበ በየካቲት ነፋስ።

 ያ ተራግቦት፣ ቀስ በቀስ

 የልቤን ብብት ነክቶኝ

 የእንክትክት ሣቁን አሣቀኝ።

እና ነን ሲርቤ

ሲርባ ሎላ ነን ሲርቤ።

በሲርባውም ሰክሮ ልቤ

የስካር ሲርባ ነን ሲርቤ።

የድል በዓሉን ምክንያት በማድረግ የአዲስ አበባ ከተማን ያደመቀው የኢትዮጵያ ባንዴራ የደራሲውን “ስሜት” ሲኮረኩራቸው ሳቃቸውን በኦሮምኛ ነው የገለፁት። በመሆኑም ስሜታቸውን የፈነቀለው ሣቅ ሰውነታቸውን የጦርነት ዘፈን ያዘፍነዋል። ይህም ሐዋሪያት በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው “በመንፈስ ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች” ተናገሩ (የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር፣ 1980፣ የሐዋሪያት ሥራ ምዕራፍ 2 ከቁጥር 1-4) ከሚለው ጥቅስ ጋር የሚመሳሰል ነው።

ደራሲ ሰይፉ ግጥም በመድረስ መንፈስ ተሞልተው በአማርኛ የሚጽፉትን ግጥም ቀደም ሲል የሚያውቁትን የኦሮምኛን ቋንቋም ተጠቅመው አቅርበውልናል። በዘፈኑም ሰክረው ዘፈናቸውን ይቀጥላሉ። በስሜታቸው መነካት ዓይነ ልቦናቸው ከብዙ ዓመታት በፊት ዓድዋ ላይ ወደ ተፈፀመ ገድል በመጓዝ አንድ ወታደርን እንዲያዩ እንዳደረጋቸው ይገልፃሉ።

እርግፍ እርግፍ ከትከሻ

በስካር ላይ ስካር ስሻ

የስካሩ ሲርባ ስሜት

አምታቶኝ

ዐይነ ልቦናዬ

ትቶኝ

የቀፎዬን

ሄደ

እስካድዋ ዘለቀ

እዚያም አንዳጽም አደነቀ

በዐይነ ልቦናቸውም ያ ወታደር ከብዙ የጦርነቱ ተሳታፊዎች ጋር በጥይት ተመትተው ድፍትፍት ሲሉ ይመለከታሉ። ይህ ብቻ አይደለም። ለሀገር ለወገን ሲሉ ከጠላት ጋር ሲተናነቁ የወደቁት ወታደሮች በቅሎ ተሸልሞ፣ ከየአድባራቱ መስቀል ወጥቶ፣ ነጋሪት እየተጎሰመ ፍታታቸው ሲከናወን፣ የጀግና ወጉ ደርሷቸው፣ እየተፎከረ፣ ጠላትን ጥለው መውደቃቸው በፎካሪ እየተነገረ፣ ለክብራቸው ጥይት እየተተኮሰ፣ ሀዘንተኛን በሚያጽናና፣ የቀሪን ወኔ በሚቀሰቅስ ሁኔታ በወግ በማዕረግ ለግብአተ መሬት አለመብቃታቸውንና ቀባሪ ማጣታቸውን ደራሲው ይቀኛሉ።

ዐጽሙ የዛሬ ስንት ዓመት

ከስንቱ ስንቱ ስንቱ ጋር

በዚያ በውጊያ ድንቁርቁር፣

ጥይት ከመድፍ ሲወጣ

ጠመንጃ መትረየስ ሲንጣጣ

የወደቀው የሚቀብረው ሲያጣ

ያ ወታደር

የሚደነቅ

በዚያን ቀን ቢወድቅ

ኖረ ዐፈር ቅጠል ለብሶ

ድንጋይ ተንተርሶ።

ዐይነ-ልቦናዬ ያን ዐጽም ያያል

የድል ሜዳውን ይቃኛል።

በዓድዋ የጦርነት ውሎ የሞተ ኢትዮጵያዊ ጀግና ዕለቱኑ ጥርኝ አፈር ማግኝት ቀርቶ በጥይት ተመትቶ ድፍት ካለበት ወይም በጉራዴ ተቀልቶ ከወደቀበት ቅጠል ያለበሰው ይኖር ይሆን? የጥይት ኃይል በየትም አቅጣጫ ከጣለው አቃንቶ አስተካክሎ የዘላለም እንቅልፉን እንዲያሸልብ የረዳ አባት፣ ልጅ፣ ወንድም፣ ዘመድ ወይም የጦር ሜዳ ጓድስ ይኖር ይሆን? የካቲት 23 የዓድዋ የጦርነት ውሎን በዓይናቸው የተመለከቱና በጽሑፍ ያሰፈሩ ሁሉ እንዳሉት በዚያ በሰንበት ዕለት ይህንን ለማድረግ ማንኛውም የጦርነቱ ተሳታፊ አለመቻሉን ያስረዳሉ። የወገን ጦር ትኩረቱ ጠላትን ጥሎ መውደቅ እንጂ ከጎኑ በተለየው ወንድሙ ማዘንና ለጠላት ፋታ መስጠት እንዳልነበረ ቆስሎ የሚያጣጥረውም የሚያሰበው ስለራሱ ሳይሆን የጠላትን ሽንፈት እንደነበረ ጸሐፌ ትዕዛዝ ገብረሥላሴ (1959፤262) እንደሚከተለው ገልፀውታል።

 “አፄ ምኒልክም ከበቅሎ ወጥተው ወደሱ [ወደተኩሱ ቦታ] መንገድ ጀመሩ። ሰልፉ ግን ጌታው ከሎሌው ጭፍራው ከአለቃው አልተገናኘም። በየፊቱ ክምር እንዳየ ዝንጀሮ ወደ ጦሩ ወደ መድፉ ይሮጥ ነበር። ሠራዊቱም ስለሀገሩ ስለመንግሥቱ ተናዶ ነበርና መድፉ ይመታኛል፣ ነፍጡም ይጥለኛል እሞታለሁ ብሎ ልቡ አልፈራበትም። ተካክሎ ጀግና ነበር። ጌታው ቢወድቅ ሎሌው አያነሣውም፤ ወንድሙ ቢወድቅ ወንድሙ አያነሣውም ነበር። የቆሰለውም ሰው አልጋው ይቁም እንጂ ኋላ ስትመለስ ታነሣኛለህ በመሃይምን ቃሌ ገዝቼሃለሁ ይለው ነበር። …” ጦርነቱ በአንድ ቀን ጀምበር በመጠናቀቁ፤ ጠላትን ድል መንሳቱን ያረጋገጠው የኢትዮጵያ ጦር ከጎኑ የተለየ ወንድሙን፣ አባቱንና ጓዱን ቆስሎ ከሚያጣጥርበት ወይም ከወደቀበት ለማንሣት ጊዜ አገኘ። ንጉሡ አፄ ምኒልክ በዚሁ ጦርነት በተካሄደበት ቦታ ለአራት ቀናት ቆይታ በማድረግ የሞተውን ሲያስቀብሩ መሰንበታቸውን ገብረስላሴ ጨምረው ጽፈዋል። ሌላው የደራሲው ዐይነ-ልቦና አካላቸው ካለበት የዘመን ክንዋኔ ርቆ እንዲሄድ ያደረገው በየዓመቱ የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሲከበር የሚሰማው የተኩስ ድምጽ፣ የሚጎሰመው ነጋሪት እንደሆነ ግጥማቸው ያስረዳል። በየዓመቱ የዓድዋን ድል ለማስታወስ የሚንዱዋዱዋውን መድፍና የሚጎሰመውን ነጋሪት በሕይወት ያሉት ብቻ ሳይሆኑ፤ ጠላት ጥሎ የወደቀው ጀግናም ለዘላለም ካሸለበበት ሕይወት ዘርቶ፣ በሚሰማው የተኩስ ድምጽ ነቅቶ፣ የተኩሱን ምንነት እንደሚጠይቅ በዓይነ-ልቦናቸው ይመለከታሉ። ያ ወታደር ከሞት ነቅቶ ለጠየቀው ጥያቄ መልስ ራሱ ያገኛል። የሚንዱዋዱዋው መድፍ፣ የሚተኮሰው፣ “ገብር ገብር” የሚለው ነጋሪት የሚጎሰመው፣ እሱ ሕይወቱን ሰጥቶ ያስገኘውን ድል ለማክበር መሆኑን ይረዳል።

ባድዋ ድል በዓሉ ማለዳ

የበዓል መድፍ ሲንዱዋዱዋ

(ዱዋ ዱዋ ዱዋ ዱዋ!)

ከሞት እንቅልፍ ተቀስቅሶ

ያ ዐጽም ዙርያውን ደባብሶ

ጉሮሮውን ጠረገ

እህህህህህ! እህህህህህ!

እና ጠየቀ

ዱዋ ዱዋው ምንድነው?

ገብር ገብሩስ የማነው?

እና ያዳምጣል።

በቅጣላቅጠሉ ኮሸሽታ ተናድዋል

ቆይቶ ግን ይገባዋል

መሆኑ

መድፉ

በሕይወቱ የተገዛ የድል አብስሮ

ገብር ገብሩም አብሮ።

ደራሲው በሰንበትለት ዓድዋ ስለወደቀ አንድ ወታደር እያሰቡ ቆይተው በዓይነ-ልቦናቸው ከሄዱበት ሲመለሱ “ቀፎአቸውን” ቆመው፤ ዐይናቸው ቦዟል። ሰውነታቸው ፈዟል። ከተጓዙበት ተመልሰው ከፈዘዙበት ሲነቁ አስተውሎታቸው በአዲስ አበባ በየጎዳናው ላይ ከተሰቀለው፣ ከሚያፈቅሩት ባንዴራ ላይ ሆኖ ያገኙታል። ከአያት ለልጅ ልጅ በተላለፈ የባንዴራ ፍቅር መታሰራቸውንም ይገነዘባሉ።

የነፃነት ምልክት የሆነው ባንዴራችን የድሉን በዓል ለማክበር በየቦታው ተሰቅሎ ከሩቅ ጋልቦ የዚያን ዓድዋ ላይ የወደቀ ወታደር “ዐጽሙን ስሞ” እሱ የወደቀበትን “ተረተር ተሳልሞ” የመጣ “የነፃነት ነፋስ” ባንዴራችን ያውለበልባል፤ “ያስጨበጭባል”። ያን ዐጽም ስሞ

ያንን ሜዳ፣ ተረተሩንም ተሳልሞ

ጋልቦ የመጣ ነፋስ

በደስ ደስ

ያስጋልብ አስጋልብ

ውልብ ልብ ልብ ልብ ልብ ልብ

ባንዴራዎቻችን ሲውለበለቡ

ሲያጨበጭቡ

ባዲሳባ

ያድዋ ድሉ ድሉ ድሉ ድሉ አበባ።

ያ ወታደር በሞተበት የዓድዋ ጦርነት ለት ጉራዴ ተመዞ ተሰንዝሮ በሰው አካል ላይ አርፎ በፀሐይ የሚብለጨለጭ መልኩ በነጭ ደም መቅላቱን በግጥማቸው ያስነብቡናል። የወገንም የጠላትም ጦር በሳንጃ ከመተራተር፤ በጉራዴ ከመሞሻለቅ በጦር ከመሰፋፋት በተጨማሪ በመድፍ እየታገዙ የየራሳቸውን የውጊያ ቀጣና ለማስፋት በሚደረገው ፍልሚያ ከኢትዮጵያውያን አርበኞች የተተኮሰ የመድፍ አረር በጠላት መድፍ አፍ በመቀርቀር መሰነጣጠሩንና የጠላትን የመድፍ ሩምታ ፀጥ ረጭ ማድረጉንም ደራሲው በግጥማቸው ያስነብቡናል። በዚህም አንባቢው የእሳቸውን ስሜት በመጋራት ዓድዋ ላይ ስለተፈፀመው የውጊያ ጀብዱ እንዲያሰላስል ቀስቅሰዋል።

 እዚያ ሜዳ፤ እዚያ ተረተር

አንድ ነገር

የጠቅላላ ጎራዴ

ስለት

ተመዞ፣ ተሰንዝሮ፣ በቆራጥነት በዘዴ

በደም ሲቅላላ

ደሞ ደሞ ሌላ ነገር

የመድፍ አረር

በጠላት መድፍ አፍ ሲቀረቀር

ሆድ ዕቃውን ሲያጋጭ

ሲያፋጭ

ሲያደርገው ጭጭ ምጭጭ

ያንን ነጭ፡-

ላስተዋለው አስቀምጦ፣ በጥቁር ዓለም

ድሉ የኛ ብቻ አይደለም።

የዚያንለታውን የሥጋ ምትር

ባስታወሰ ቁጥር

ነጭ

ሲያር ይኖራል፣ ፀጉሩን ሲነጭ።

 አቶ ሰይፉ ጠረጴዛ ተደግፈው ብዕር ከወረቀት አገናኝተው በአይነ-ልቦናቸው ወደኋላ ሄደው በዓድዋ የጦርነት ውሎ ሕይወታቸው ያለፈን አንድ ወታደር በመዘከር ያቀረቡልን ግጥም ዓድዋ ላይ የሞቱ ብዙ ኢትዮጵያውያን ጀግኖችን እንድናስባቸው የጦርነቱን ውሎና አሟሟታቸውን በአእምሯችን ይስሉልናል። በታሪክ ተመዝግበው የማናገኛቸው አበው ጀግኖቻችን ለነፃነት መስዋዕትነት ከፍለው ለማለፋቸው ሜዳውና ተረተሩም ቋሚ ምስክራቸው ነው።

የወደቀበቱ ሜዳው

ተረተሩ

ቀን የማይለውጠው ምስክሩ

የዚያ ጀግና ኩሩ።

በማለት የግዑዝ ነገሮችን ምስክር ሰጭነት ደራሲው አስነብበውናል። የአቶ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ግጥም አንድ ዓድዋ ላይ ድፍት ብሎ ስለቀረ ወታደር ትኩረት ይሰጣል። ስለ አንድ ወታደር መስዋዕትነት ማውጋቱም ብዙዎች ዓድዋን በብዕራቸው ባወሱ ቁጥር በዓለማዊውም ሆነ በፈረስ ስማቸው /በአብዛኛው ከዓድዋ መልስ የሞቱ/ የሚያወሱት ትልልቅ አርበኞችን በመሆኑ በትኩረት ይለያሉ። በመሆኑም ታሪክ መሞታቸውን ከስማቸውና ከጀግንነት ሥራዎቻቸው ጋር ዘግቦ ያላቆየንን ብዙ አበው ጀግኖችን የሚወክል ግጥም ስላቀረቡልን ደራሲውን ያስመሰግናቸዋል።

 የአቶ ሰይፉ የቃላት አጠቃቀም ቀላልና የዕለት ከዕለት መግባቢያ ሆነው በተገቢው ቦታቸው የተቀመጡ ናቸው። ሙዚቃዊ ቃናን ለመፍጠር ይመስላል ፊደላትንና ቃላትን ደጋግመው ሲጠቀሙ ይስተዋላል።

በጥሩ የዘይቤ አጠቃቀማቸውም ዓድዋ ላይ የወደቀ አንድ ወታደር ያስገኘው ድል በሰላሙ ጊዜ በየዓመቱ መድፍ በመተኮስ ነጋሪት በመጎሰም ሲከበር ሞትን ድል ነስቶ ከላይ የተጫነውን አፈር ገልጦ ከተንተራሰው ድንጋይ ቀና ብሎ ስለሰማው የዱዋዱዋቴ ድምፅ ምንነት ለማወቅ እንደሚጠይቅ በመግለጽ አይነ-ልቦናችን ውስጥ ጎላ ብሎ እንዲታየን አድርገዋል። በዚሁ የሰውኛ /Personification/ ዘይቤ አጠቃቀማቸው በመቀጠልም “ዱዋዱዋው ምንድነው? ገብር ገብሩስ የማን ነው?” ብሎ መጠየቁን ያስነብቡናል። ሞት እንቅልፍ ሆነና ለሚቀጥለው የድል ዓመት እንዲያደርሰው ፈጣሪውን በመለመን ተመልሶም በመተኛት ማንኮራፋቱን ይገልፃሉ።

 ከዚያንን አድርሶት

ካመት ዓመት አድርሰኙን ጸሎት

ተኛ ተመልሶ

ድንጋዩን ተንተርሶ

አፈር ቅጠሉን ለብሶ።

ከዚያን ያንኮራፋል

ኮ-ር ኮ-ር።

ኮ-ር ኮ-ር።

እንደዚሁም በቅብልብል

ኮ-ር ኮ-ር።

ኮ-ር ኮ-ር።

የወደቀበቱ ሜዳው

ተረተሩ

ቀን የማይለውጠው ምስክሩ

የዚያ ጀግና፣ የዚያ ኩሩ።

ደራሲ ጸጋዬ ገብረመድህን በበኩላቸው እሳት ወይ አበባ (1966፤ 54-56) በሚለው የግጥም መድብል ውስጥ ካካተቷቸው ግጥሞች መካከል “ዋ! … ያቺ ዓድዋ” በሚል ርዕስ ያቀረቡት ይገኝበታል።

“ጀሎ መገን፣ ዘራፌ ሲል ቆራጥ ጀግና መዞ ካራ፣ ባራቴዬሪን ገብቶት ግራ አውዓሎም ላይ ሲንጠራራ፣ ማነው? ያየ፣ የነበረ፣ ያንን ታሪክ የሚያወራ”

የግጥሙ ርዕስ በቃለ አጋኖ የሚጀምር ከመሆኑም በላይ ደራሲው በዓይነ-ልቦና ወደኋላ ርቀው ሄደው ከዓመታት በፊት ዓድዋ ላይ ስለተፈፀመ ትልቅ ታሪካዊ ገድል የቋጠሩትን ስንኝ ተደራሲያን ሲያነቡ፣ እሳቸው ወደኋላ ተመልሰው ርቀው ሄደው የሰንበትለቱን የዓድዋ የጦርነት ውሎ በአይነ-ልቦና እንዳዩት ሁሉ የአንባቢያንም አስተውሎት ግጥሙን ከመፃፋቸው በፊት ዓመታት ካስቆጠረው የጀግኖች ተጋድሎ ላይ እንዲሆን ይገፋፋሉ። ደራሲ ጸጋዬ ገብረመድህን አንባቢው አብሯቸው እንዲታደም ለማድረግ ይጥራሉ። አንባቢ ምን ተሠራ? ምን ተፈፀመ? ብሎ እንዲጠይቅ፣ የዓድዋን የተጋድሎና ድል ታሪክ እንዲመረምርና ግርምታቸውን እንዲጋራ ይጋብዛሉ።

 ደራሲ ጸጋዬ ገብረመድኅን ስለ ዓድዋ ከፃፉት ግጥም የመጀመሪያዎቹን ስንኞች ስናነብ የዓድዋን ከተማ አካባቢ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ የሚገልጡ ሆነው እናገኛቸዋለን። ጦርነት የተካሄደበት የዓድዋ ከተማ ዙሪያ በተራራ ሰንሰለቶች የተከበበ ነው። ከተራራ ሰንሰለቶቹ አንዱ ሰማያታ ሲሆን ይህም ከሌሎቹ ተራሮች ከፍተኛው ነው። ይህንን ተራራ ዓድዋ ከተማ ሆኖ ሲመለከቱት ቀጥ ብሎ የቆመ የአለት ክምር ጫፉ ከሰማይ ጋር የተገናኘ የሰማይ ምሰሶ ይመስላል።

 አበው ዓድዋ ላይ የፈጸሙት ተጋድሎና ያገኙት ነፃነት በዘመን የራቀ ግን ዝንተዓለም የሚታወስ ታላቅ ታሪካዊ ምስክር ነው። ኢትዮጵያውያን በተለያዩ ጊዚያት ሀገራቸውን ለመውረር ህዝቧን በቅኝ ግዛት ሥር ለማማቀቅ ከሚፈልጉ ጠላቶች ጋ በተለያየ ጊዜና ቦታ ጦርነት አካሂደዋል። ሆኖም ከጠላት ጋ ከተደረጉት ጦርነቶች ከፍተኛው የድል ታሪክ የተፈጸመው ዓድዋ ላይ ነው። የዓድዋ ድል ታላቅ ታሪካችን የተመዘገበበት በመሆኑ እንደተፈጥሯዊ አለት የማይሞት፣ የማይሻርና የማይረሳ ዘለአለማዊ የታሪክ ገድላችን ነው። የደራሲው ግጥም የሚያስረዳን ይህንኑ እውነታ ነው።

 የዓድዋ ድል መገኘት ለኢትዮጵያውያን በራስ የመተማመን ስሜታቸውን የበለጠ አጠንክሮላቸዋል፣ አዳብሮላቸዋል። የጠላት በዘመናዊ መሣሪያና የውጊያ ስልት መጠናከር፤ ከአበው ጀግኖቻችን የውጊያ ወኔ በላይ እንዳልሆነ አስገንዝቧቸዋል። ይህ በመሆኑም ለዓድዋ የጦርነት ጥሪ አበው ጀግኖቻችን አወንታዊ መልስ ሰጥተው እንደተሰለፉ ሁሉ ልጆቻቸውም በ1928 ጠላት ያደረገውን ወረራ ለመመልከት በዓድዋ የድል ስሜት ተነሳስተው ዘምተዋል። ተዋግተዋል። ይህንኑ የዓድዋ የድል ስሜት ጀግኖች አባቶቻችን እንደገና መታደማቸውን ደራሲው በሸጋ ብዕራቸው ገልጸውታል።

ባንቺ ብቻ ሕልውና

 በትዝታሽ ብጽዕና

 በመስዋዕት ክንድሽ ዜና

 አበው ታደሙ እንደገና…

 ዋ!

 ደራሲው ግጥሙን የደረሱት አበው ጀግኖቻችን ንጹሕ ደማቸውን ባፈሰሱበት መሪር የሞት ጽዋቸውን በተቀበሉበት ቦታ ከመሆኑም በላይ በወርሀ የካቲት 1964 ዓ.ም. ነው። ይህም መስዋዕትነት የከፈሉና ለድሉ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሁሉ የሚዘክሩበት ወቅት ነው። በዓድዋ ጦርነት ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል። ዓድዋ ላይ የተከሰከሰው አጥንት፣ የፈሰሰው ደም፣ የተከፈለው የሕይወት መስዋዕትነት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ነው። እነሱም ከባርነት ቀንበር ታድገውናል፤ ነፃነታችን አስከብረውልናል። እናም ዓድዋ እነዚያ በታሪካችን የምናውቃቸው ኩሩ ኢትዮጵያውያን ታላቅ የታሪክ ቅርስ የሰሩበት፣ የኢትዮጵያዊነት ምስክር መሆኗን ደራሲው ያስረዳሉ።

ዋ! …

ዓድዋ የዘር ዓጽመ ርስትዋ

የደም ትቢያ መቀነትዋ

በሞት ከባርነት ሥርየት

በደም ለነጻነት ሥለት

አበው የተሰዉብሽለት

ዓድዋ

የኩሩ ትውልድ ቅርስዋ

የኢትዮጵያውነት ምስክርዋ

በዓድዋ የዘመቻ ጥሪ ወደ ዓድዋ የዘመተው ጦር ከጠላት ጋ በተደረገው ጦርነት ይቀሰቀስ የነበረው ከጠቅላይ ጦር ሠፈር በሚጎሰም ነጋሪት ነበር። ይህም ቀደም ሲል የነበረ የውጊያ ባህል መሆኑ ነው። የወራሪው የኢጣሊያ ጦር የውጊያ እንቅስቃሴ በመድፍ ይደገፍ እንደነበር ሁሉ ኢትዮጵያውን ጀግኖችም ከፈረንሳይ መንግሥት በተገኘ መድፍ እየታገዙ ተዋግተዋል። ውጊያው የተካሄደው በጎራዴ፣ በሳንጃ፣ በጦርና በነፍስ ወከፍ መሣሪያም እንደነበር የታሪክ መረጃዎች ያረዳሉ። ከጠላት የሚወረወርን ጦር ለመመከት ኢትዮጵያውያን ባህላዊ የመከላከያ መሣሪያዎችን ጋሻን ለመመከቻነት ተጠቅመዋል። በእነዚህና ሌሎችም መሣሪያዎች በመታገዝ ኩሩ ኢትዮጵያውያን በዓድዋ የጦርነት አውድማ ደማቸውን አፍሰዋል። የዓድዋ ጀግኖች አጽም ትንሣዔ በየዓመቱ ሲከበር ደማቸው የነፃነታችን ሕዋስ በመሆን እንደሚያገለግለን የደራሲ ጸጋዬ ገብረመድህን ግጥም ያስገነዝበናል።

ሲቀሰቀስ ትንሣዔዋ

ተግ ሲል ሲንር ትቢያዋ

ብር ትር ሲል ጥሪዋ

ድው እልም ሲል ጋሻዋ

ሲያስተጋባ ከበሮዋ

ሲያስገመግም ዳኘው መድፍዋ

በጊዜው ንጉሥን ጨምሮ መሣፍንቱና መኳንንቱ ከዓለማዊ ስማቸው በተጨማሪ በፈረስ ስም ይጠሩ ነበር። ይህንን ከግጥሙ መረዳት ይቻላል። ዋ!… ዓድዋ…

ያንችን ጽዋ ያንችን አይጣል

ማስቻል ያለው አባ መቻል

በዳኘው ልብ በአባ መላው

በገበየሁ በአባ ጎራው

በአባ ነፍሶ በአባ ቃኘው

በለው ብሎ፣ በለው በለው!

ደራሲው በግጥማቸው ውስጥ በፈረስና በዓለማዊ ስማቸው የዘረዘሯቸው ጥቂቶቹን የዓድዋ ጀግኖች ብቻ ነው። ደራሲው ለግጥማቸው አዝማች የተጠቀሙት ዓድዋ ላይ የተፈጸመው ታሪካዊ ገድል ያሳደረባቸውን የመገረም ስሜት በቃለ አጋኖ ምልክት በመግለጽ ነው። ይህም አንባቢው የስሜታቸው ተጋሪ እንዲሆን ረድቷቸዋል።

 ደራሲ ጸጋዬ ገብረመድህን በቃላት አጠቃቀማቸው እጅጉን የሚመሰገኑ ናቸው። ሠፊ ሃሳብን በጥቂት ቃላት ፍንትው አድርገው ገልጸዋል። ቃላትም በተገቢው ቦታቸው ተገቢውን ጉዳይ እንዲገልጹ ተደርጓል። ገጣሚው ቃላትን ደርድረው ያቀረቡትን የዓድዋ ድል ጉዳይ በዘይቤያዊ ንግግሮች ምስል እየፈጠሩ አንባቢያን ለቀረበላቸው ጉዳይ ቅርበት እንዲኖራቸው አድርገዋል።

ዋ!…

ዓድዋ ሩቅዋ

የዓለት ምሰሶ አድማስ ጥግዋ

ሰማይ ጠቀስ ጭጋግ ዳስዋ

ዓድዋ

በሚለው አርኬ ሕያው የታሪክ አምዳችን የተመዘገበበት የዓድዋ መልክዓ ምድራዊ አቀማጥ የቀረበው በዓለት ምሰሶ ተመስሎ ነው። ይህም የአለት ምሰሶ ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ በአይነ ልቦናችን እንድንቃኝ ያደርጋል።

ጉድ አይቼ መጣሁ እግሬ ደርሶ (2)

የድንጋይ ወጋራ የድንጋይ ምሰሶ።

የሚለው የታቦት ግጥም የሚደመጠው አንድም የምሰሶውን ጥንካሬ ለመግለጽ አለዚያም ያልተለመደ ነገር መደረጉን ለመጠቆም ነው። የዓድዋ ከፍታ የተገለጸው በአድማስ ነው። አንድን ቦታ ስንመለከት መሬትና ሰማይ የተገናኙበት በሚመስለን ነገር መሆኑ ነው። ይህ የምድርና ሰማይ መወሰኛ ጠፈር የምንለው ነው። በወርሃ ጥርና የካቲት ጭጋግ ምን መስሎ እንደሚታይና የጸሐይን ሙቀት በመቀነስ ከለላ እንደሚሆነን ይታወቃል። ጭጋግ ባህላዊውን ዳስ ተክቶ ነው የቀረበልን። ታዲያ ገጣሚው እነዚህንና ሌሎችን ዘይቤዎች በመጠቀም ነው ያቀረቡትን ጉዳይ አንባቢያን በአእምሯቸው ሥዕል ሥለው እንዲመለከቱ ያደረጉት።

 ሌላው ገጣሚ አቶ ንጋቱ መርሻ “ማነው? ያየ፣ የነበረ፣” በሚል ርዕስ በየካቲት መጽሔት 9ኛ ዓመት ቁጥር 5 ባቀረቡት ግጥም ዓድዋ ላይ የተገኘውን ድል ከመዘከራቸውም በላይ በእሳቸው የሕይወት ዘመን የሚገኘውን ትውልድ ወር ተረኛነቱን አስገንዝበውታል። ተተኪው ትውልድም በዓድዋ የድል ፋና በመመራት እናት ሀገሩን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበውታል።

 በሌላ በኩል ድሉ ኢትዮጵያውያንን ብሎም ጥቁር ሕዝቦችን በሞላ ዘለዓለማዊ ኩራት አጎናጸፈ። በቅኝ ግዛት ይማቅቁ የነበሩ ሕዝቦችንም የነፃነት ተስፋ አስጨበጠ። በአቶ ንጋቱ መርሻ ግጥም የመጀመሪያዎቹ ስንኞች የምንረዳው ይህንን እውነታ ነው።

የቅኝ ግዛት የግፍ ምጽዓት፣

ተገድቦ የቆመበት፣

የነፃነት ጥሪ ደወል፣

የተስፋ ድምጽ ያሰማበት፣

በዓለም ታሪክ የሚታወስ፣

መልካም ምዕራፍ የተቸረ፣

የተለየ መራር ሽንፈት፣

ቆዳ አምላኪን ያሸበረ፣

ዘጠና ዓመት የኖረ፣

መላ ጥቁርን የሚያኮራ፣

በአፍሪካ ቀንድ የተሠራ።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከንጉሡ አፄ ምኒልክ ለቀረበለት የዘመቻ ጥሪ ሀገሩንና ወገኑን የመጠበቅ የትውልድ ግዴታ እንዳለበት በመገንዘብ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ያለውን የጦር መሣሪያ አዘጋጅቶ፣ ደረቅ ስንቁን ሰንቆ፣ አብሮት ከሚዘምተው ወንድሙ ጋር ተመካክሮ፣ በአካባቢው ያለውን የጦር መሪ በመከተልና በዘመናዊ ትጥቅና ስንቅ የሚደገፈውን የኢጣሊያ ጦር በመግጠም ድል ማድረጉን ከተለያዩ የታሪክ መጻሕፍት እንረዳለን። ደራሲውም ይህንኑ ታሪካዊ እውነታ በግጥማቸው አጉልተው ያስነብቡናል።

ጀግና ታጥቆ፣ ጦሩን ስሎ፣

የራሱን ስንቅ ተሸክሞ

አገር ካገር ተጠራርቶ

ከዳር እዳር ነቅሎ ተሞ፣

ወራሪውን ለመመለስ፣

ግዳይ ጥሎ ድል ለመንጠቅ፣

ከጣሊያን ጋ ፍልሚያ ሲገጥም፣

በዓድዋ አምባ ሲተናነቅ፣

ማነው? ያየ፣ የነበረ፣

የጭንቋን ቀን የሚያወሳ፣

ከመከራው ገፈት ቀምሶ

ጣፋጭ ድሏን እሚያገሳ።

ኢጣሊያ ለሁለተኛ ጊዜ ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ በቅኝ ግዛትነት ለመያዝ የተንቀሳቀሰችው ከአርባ ዓመታት በኋላ በመሆኑ በአፄ ምኒልክ መሪነት የተገኘው የዓድዋ ድል ጠላትን ለአርባ ዓመታት እንደገታ እንገነዘባለን። የአቶ ንጋቱ ግጥምም ይህንኑ ታሪካዊ እውነታ ነው የሚገልጸው። ልበ ሙሉው አባ ዳኘው፣ ተምዘግዛጊ ጦሩን ሲሰብቅ፣ ለአርባ ዓመታት የሚበቃ፣ ቅጣት ሰጥቶ በደም ሲጠምቅ። በደራሲ ጸጋዬ ገብረመድኅን ግጥም ላይ እንደተመለከትነው ሁሉ፣ አቶ ንጋቱ መርሻም በታሪክ ስማቸውን ከምናውቃቸው የዓድዋ ጀግኖች መካከል ጥቂቶቹ የፈጸሙትን ጀብዱ በመግለጽ በግጥሞቻቸው ያወሷቸዋል። ጠላትን በመሰለልና ከመሸገበት እንዲወጣ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ለኢትዮጵያውያን ማሸነፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱት ኢትዮጵያውያን መካከል ባሻ አውዓሎም አንዱ ነበሩ። እሳቸውም እንደ ታላላቆቹ የዓድዋ ጀግኖች ሁሉ በግጥሙ ውስጥ ስማቸው ተጠቅሷል።

 ጀሎ መገን፣ ዘራፌ ሲል

ቆራጥ ጀግና መዞ ካራ፣

ባራቴዬሪን ገብቶት ግራ

አውዓሎም ላይ ሲንጠራራ፣

ማነው? ያየ፣ የነበረ፣

ያንን ታሪክ የሚያወራ።

ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ (1980) እንደገለጹት የኢጣሊያ የስለላ ኃላፊ ለኢትዮጵያ ሠራዊት የነበራቸውን ንቀት በጆሯቸው የሰሙት አውዓሎም ተቆጭተው ከጓደኛቸው ከብላታ ገብረእግዚአብሔር ጊላ ጋር በመምከር በራስ መንገሻ ዮሐንስ አማካኝነት አፄ ምኒልክን ተዋወቁ። የኢጣሊያን ጦር የውጊያ እቅድ የሚያበላሽ ዘዴ ከተዘየደ በኋላ በባሻ አውዓሎም አማካኝነት ለጄኔራል ባራቴዬሪ እንዲነገረው ተደረገ። ባራቴዬሪ በበኩሉ የአውዓሎምን መረጃ ትክክለኛነት በመቀበል ጦሩን ወደፊት አንቀሳቀሰ። ጦርነቱ ብዙ ሳይቆይ ከመጀመሩም በላይ ኢጣሊያኖች የአውዓሎምን መረጃ በመጠራጠራቸው አንዱ መኮንን “አውዓሎም አውዓሎም” እያለ ሲጣራ፣ አውዓሎም ሰምቶ “ዝወዓልካዮ አየውዕለኒ” (አንተ በዋልክበት አያውለኝ) ብሎ እንዳፌዘበት ተገልጿል። ገጣሚውም ይህንኑ ታሪካዊ እውነታ ነው የገለጹት።

 አቶ ንጋቱ መርሻ ለግጥማቸው አዝማች አድርገው የተጠቀሙት የግጥሙን ርዕስ “ማነው ያየ፣ የነበረ፣” የሚለውን ጥያቄ ነው። በዚህም የዓድዋ የድል ታሪክ የየዘመኑ ትውልድ የሀገርና የወገን ኃላፊነት እንዳለበት የሚያስተምር ታሪካዊ መረጃ መሆኑን ይገልጻሉ። ሆኖም በዓድዋ ጦርነት የተካፈሉ አበው የአይን ምስክርነት ለመስጠት በአካል ሊገኙ እንደማይችሉ በማመን ታሪካዊውን የዓድዋን ድል በአካል ተገኝተው ከመዘገቡ ወይም መረጃ ከሰጡ ሰዎች የተጠናቀሩ የታሪክ መረጃዎች የዛሬው ትውልድ ባለአደራና ወርተረኛ መሆኑን እንደወረሰ ያስረዳሉ።

ማነው አብሮ የነበረ፣

የዓድዋን ገድል እሚያወራ።

አዎ! ያየ የነበረ

ቁልጭ አርጎ ተናግሮታል

ታሪክ ጽፎ በደም ከትቦ

ለዚህ ትውልድ አውርሶታል።

የግጥሙ ትኩረት የዛሬው ትውልድ ከዓድዋ ድል ምን ተምሯል? የዚህ ትውልድ ተከታይስ ምን ይማርበታል? የሚል ነው። በመሆኑም የእሳቸው ዘመን ትውልድ የዓድዋ ጀግኖችን ዓርማ በማንሣት ባለበት የሶሻሊስት ሥርዓት በመመራት በምሥራቅና በሰሜን የሀገራችን ክፍል ለሰላም፣ ለአንድነትና ለእኩልነት ከውጭና ከውስጥ “አድኅሮት” ኃይላት ጋር እንደታገለ ያመለክታሉ።

ይህም ትውልድ ባለ አደራው

 “ባለሣምንት ወርተረኛው”

ቀይ ዓርማውን ተቀብሎ

በኅሊናው ጽላት ስሎ

በወረሰው ቆራጥነት

በሶሻሊስት አርበኝነት

ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነት

ለተጨባጭ እኩልነት

ጠላቱን ሁሉ ሲያሳፍር

አንኮታኩቶ ቅስሙን ሲሰብር።

የዓድዋን ታሪክ በማድለብ

ግዳይ ለሰላም በማቅረብ

የእናት ሀገሩን ህልውና

የአንድነቷን ውሉን ሲያከር፣

ሲያከር፣ ሲያከር ሲደውር

መጪው ትውልድ አባቶቹ ያቆዩትን በጎ ተግባር ተረክቦ የራሱን የታሪክ ቅርስ በመገንዘብ የሀገሩን ዳር ድንበር የማስከበር ኃላፊነት እንዳለበት ደራሲው ያስገነዝባሉ። ይህንንም ሲያደርግ ነው የነፃነታችን ምልክት የሆነው ባንዴራችን በነፃነት አደባባያችን

“ማነው አብሮ የነበረ፣ የዓድዋን ገድል እሚያወራ። አዎ! ያየ የነበረ ቁልጭ አርጎ ተናግሮታል ታሪክ ጽፎ በደም ከትቦ ለዚህ ትውልድ አውርሶታል።”

በመውለብለብ ሀገራችን በድል የምትኖረው በማለትም ተተኪውን ትውልድ ያሳስባሉ።

ወደፊትም ይኸው ፋና፣

በቅርስነት ተሸጋግሮ

ታሪክ ዞሮ ተቆጣጥሮ

በተተኪው ልቦና አድሮ

ይቺ እማማ እናት ሀገር

በድግግም ድል ታጅባ

አረንጓዴ ብጫና ቀይ

ውብ አርማዋን አውለብልባ

በመስከረም ጥቢ ኮከብ

በቀይ ብርሃን ደምቃ ቀልታ

ትኖራለች ኢትዮጵያችን

ለዘለዓለም በድል ኮርታ፡፡

የተሰመረባቸው ስንኞች የያዙትን ትጉም የምንረዳው በምርምር ቅኔ ነው። “በመስከረም ጥቢ ኮከብ” ሲል በ1967 ዓ.ም. በመስከረም ወር የተገኘውን ለውጥና በየዓመቱ እናከብረው የነበረውን የለውጥ ቀን ያመለክታል። “በቀይ ብርሃን ደምቃ ቀልታ” ሲልም በተገኘው ለውጥ እንከተለው የነበረውን የሶሻሊስት ርዕዮተ- ዓለም ዓርማ ማለት እንደሆነ እንገነዘባለን።

 ግጥሙ በአብዛኛው የቀረበው ዝርው በሆነ መንገድ ነው። ዓድዋ ላይ የተገኘውን ድል በቀጥታ የሚነግር፣ የእሳቸውም ሆነ የሚመጣው ትውልድ ኃላፊነት ምን እንደሆነ የሚነግረው፣ የሚቀሰቅሰው በዝርው አገላለጽ ነው። ሆኖም ጥቂት ስንኞች በጥሩ ዘይቤ አጠቃቀም ተገልጸው ይገኛሉ። ይህም የአንባቢው ትኩረት በእነዚሁ በዘይቤ በተገለጹ ጥቂት ስንኞች ላይ እንዲሆን ያደርጋል።

ምድረ- ዓድዋ ቀውጢ ስትሆን

ድል አርግዛ ድል ስታምጥ

ያ- “ነጭ-አሞራ” በአረር ሲጋይ

በጆቢራ ሲተራመስ

በጥቁር ሕዝብ፣ በጥቁር አፈር

የውርደት ማቅ ከል ሲለብስ

ቆንጥር ጥሻው “ዕልል!” ሲል

የዓድዋ ጋራ ሲያስተጋባ

እናት መሬት ስትፈነድቅ

የደስታ እንባ ስታነባ

ማነው? በደምብ ያስተዋለ

ያቺን ሌሊት በዚያች አምባ።

በተለዋጭ ዘይቤነት የተጠቀመባቸው “እርግዝና” እና “ምጥ” የሚሉት ቃላት የያዙት እሳቤ የሰው ልጅን ሥነ-ሕይወታዊ ልምድ የሚገልጹ ናቸው። “ዕልልታ” እና “ፍንደቃ” የደስታ ስሜት የወለደው እንባ፣ የደስታ መግለጫዎች በመሆናቸው ከእያንዳንዱ አንባቢ መልካም የሕይወት ገጠመኝ ጋር የጠነከረ ግንኙነት አላቸው።

 ግጥሙ ለአንባቢያን የቀረበበትን ወቅት ስንመለከት በምሥራቁ የሀገራችን ክፍል የሶማሊያ ወራሪ ኃይል ከተመታ ከስምንት ዓመት በኋላ ሲሆን በሰሜኑ የሀገራችን ክፍልም ጦርነት ይካሄድ በነበረበት ጊዜ ነው። በመሆኑም አቶ ንጋቱ የዓድዋን ድል በብዕራቸው የዘከሩት ለሰላም፣ ለእኩልነትና ለሀገር አንድነት ወርተረኛው ትውልድ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ሶሻሊስታዊ አርበኝነትን እንዲያጠነክር፣ ተተኪው ትውልድም የአባቶቹን ፋና እንዲከተል ለማስገንዘብ መሆኑን ከግጥሙ መረዳት ይቻላል።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያውያን የዓድዋን ድል በዓል ሲያከብሩ አባቶቻቸው ጠላታቸው የነበረውን የኢጣሊያ ወራሪ ጦር አንድ ሆነው በመውጋት እንዳሸነፉት ሁሉ የአንድነት ስሜታቸውን ማጠንከሩ እጅግ ተገቢነት ያለው የወቅቱ የኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top