ቀዳሚ ቃል

ውድ አንባቢያን፣

የካቲት ወር በሃገራችን አያሌ ታሪካዊ ሁነቶች የተፈጸሙበት እንደሆነ የታወቀ ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት የዘከርነው የየካቲት ሰማዕታት መታሰቢያና ሰሞኑን ያከበርነው የአድዋ ድል አገራችንን ለማስከበርና ነፃነታችንን ለማስጠበቅ ታላቁን መስዋዕትነት የከፈሉልንን አባቶቻችንና እናቶቻችን ያስታወስንበትም ነው። የወርሃ የካቲቷ ታዛም ከሁለቱ ዐበይት የጀግንነትና የመስዋዕትነት ታሪኮቻችን በአንዱ በአድዋ ጦርነትና ድል ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን ይዛ መጥታለች። አገራችን ኢትዮጵያ በተለይ በአሁኑ ወቅት ያለችበትን ሁኔታ ለሚገነዘብ ቅን ዜጋ ከአድዋ ድል የበለጠ አስተምህሯዊ ዋጋ ያለው ታሪክ የለንም። ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ፣ ኢትዮጵያውያን አንድ ከሆኑ ምንም አይነት ኃይል ሊበግራቸው፣ ምንም አይነት ችግር ሊፈታቸው እንደማይችል ለዓለም ያስመሰከሩበት ታሪካቸው ነውና።

ታዛ በሌሎቹ አምዶቿም ሦስት ጠቢባንና ሥራዎቻቸውን የሚዘክሩ ጽሑፎችን ይዛለች። ዓለማየሁ ገበየሁ ስለገጣሚና መምህር ደበበ ሰይፉ የብርሃን ፍቅር ምስጢሮች ያጫውተናል። ተሾመ ብርሃኑ ደግሞ ልንዘነጋው የተቃረብን የሚመስለውን ታላቅ የመድረክ ፈርጥ ወጋየሁ ንጋቱን ያስታውሰናል። በሙያ ብቃቱና በመድረክ ዲስፕሊኑ ሁሉም በከፍተኛ አድናቆት የሚያከብረው የመድረክ ባለሙያ ነበር ወጋየሁ። ተተኪው ትውልድ አርአያነቱን ይወርስ ዘንድ በስፋትና በጥልቀት ሊጻፍበት ይገባል ብለንም እናምናለን። ስለሌሎች አንጋፋ የጥበብ ባለሙያዎችም እንዲሁ። በቅርቡ “ባሩድና ብርጉድ” የተሰኘ ኤግዚቪሽኑን ለሕዝብ ክፍት ያደረገው ሠዓሊና ቀራፂ በቀለ መኮንንም የታዛ እንግዳ ነው። እናም ስለሥራዎቹ  ያወጋችኋል። እምነቱን ያጋራችኋል።

 ተከታታዩ የሱልጣን አባዋሪ ጽሑፍ ደግሞ በዚህ ወር የዘውጌ ፖለቲካ አቀንቃኞችን አመጣጥና የተጓዙበትን መንገድ ያስቃኘናል። ዘውጌኞቹ እርስ በርስና ፀረ ደርግ አቋም ይዘው ከተሰለፉ ሌሎች ድርጅቶች ጋር ሳይቀር የገቡትን ጦርነትና የ“መገዳደል” ታሪካችንን ሌላ ገጽታ በመረጃ አስደግፎ ይነግረናል። ሌሎች አዝናኝና ቁምነገር አዘል ጽሑፎችንም ይዘናል። እንደተለመደው ጻፉልን፣ ሃሳብ አስተያየታችሁን አካፍሉን።

መልካም ንባብ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top