ስርሆተ ገፅ

“ካልነቀነቅከው ሁሉም ጥበብ ወዳቂ ነው”

ሠዓሊ፣ ቀራፂ፣ ገጣሚ እና የጥበብ መምህር በቀለ

አርቲስት በቀለ መኮንን፣ በቅርቡ ‹‹ባሩድና ብሩጉድ›› ሲል የሰየመውና በአብዛኛው የ‹‹ኢንስታሌሽን›› ሥነ- ጥበባዊ ሥራዎቹን የያዘው ዓውደ ርዕይ በጀርመን የባህል ማዕከል- ገብረክርስቶስ ደስታ አዳራሽ በመታየት ላይ ይገኛል። ከዚህ ቀደም ብላክ ቦክስ፣ ዕድልና ምርጫ፣ እንቆቅልሽ፣ አዲሱ ቀመር፣ ማረሻ … በሚል ሥያሜ ዓውደ- ርዕዮችን ማቅረቡ ይታወሳል። በዓውደ ርዕዩ አዳራሽ ሥራዎቹን እየተመለከተ የነበረው ዘጋቢያችን ባለሙያውን እንደሚከተለው አነጋግሮታል።

ታዛ ‹‹ባሩድና ብርጉድ›› የጥበብ ዓውደ-ርዕይን በዚህ ዓውድ፣ በዚህ ፎርምና ቅርጽ እንድትሰራው ያስቻሉህ የህይወት ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? ሰውና ልብሱ!?

 አርቲስት በቀለ መኮንን፡- ይህ ሥራ ረጅም ጊዜ የወሰደ ነው። በነዚህ ጊዜያት ውስጥ ብዙ ነገር ታስተውላለህ። ሁል ጊዜ ሃሳቦች ይኖሩሃል። ከነዛ ውስጥ ለዕቅድህ የሚመችህን፣ የሚመስልህንና የምትወስነውን እያነጠርክ- እያነጠርክ ነው የምታወጣው። የኔ ሥራዎች በሃሳብ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ሃሳቡን ወደ ዕይታዊ ጥበብ መለወጥ ነው። ይህ ደግሞ ረጅም ሂደት፣ ረጅም ሃሳብ፣ ረጅም መነሳትና መውደቅ ይፈልጋል። ሃሳቡ ኢሉስትሬት አይደለም የሚደረገው፤ ማለት በስዕል አይለወጥም። ሥዕል የራሱ ቋንቋ አለው። ሃሳብ የራሱ መንገድ አለው። ጽሑፍም የራሱ መንገድ አለው። ሁሉም ራሳቸውን የቻሉ ናቸው። እሱን ለመለወጥ ረጅም ጊዜ ይወስዳል።

 ሰውና ልብሱን ከልጅነት ጀምሮ ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ነው፤ ግን እንደዋዛ እንመለከተዋለን። አሮጌ ስለለበስክ ልትናቅ ትችላለህ። ጥሩ ስለለበስክ በትልቅነት ልትታይ ትችላለህ። የተቀደደ ስትለብስ በሌብነት ልትጠረጠር ትችላለህ። ነጠላ ስለለበስክ በሃይማኖተኛነት ልትወሰድ ትችላለህ። ልብሶች ከሰውየው በፊት፣ ከማንነት በፊት፣ እንደ ታፔላ ሆነው ቀድመው ያስፈርጃሉ። ይሄ በህይወት ውስጥ የተለመደ ነገር ነው። ፍርድ ቤት ድረስ አስተሳሰብ በማዛባት፣ ስለሰው ሰብዕና ያለንን አስተሳሰብ ቀድመው የሚያስወስኑ ናቸው- ልብሶች።

“እንዳልኩህ ሃሳቡ ውበት ብቻ ሊሆን ይችላል። ወይም የሚተረክና የሚተላለፍ ሃሳብ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ያ ሃሳብ ያ ውበት የሚፈልገው፣ የሚገባው መንገድ አለ። ያንን መንገድ እመርጣለሁ ”

ያው በዋዛ ፈዛዛ የምንተዋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። አንዱ ሰውና ልብሱ ነው። ሽማግሌ ይለብሳል፣ ልጅ ይለብሳል፣ ሴት ትለብሳለች፣ ወንድ ይለብሳል፣ ሁሉም ይለብሳል። በሙያ፣ በፆታ፣ በሹመት፣ በሽረት፣ በእሥር፣ በአሳሪ፤ በመሳሰሉት ሁሉ ሰው የሚገልጸውን ይለብሳል። ከዚህ ሁሉ የትኛውን ነው የምትመርጠው? ለምንድን ነው የምትመርጠው? እንደ ጥበብ ሰው ትመርጣለህ፤ ለዚህ ጊዜ እነዚህን ሁለቱን ነው ‹‹ባሩድና ብርጉድ›› ስል በምድራዊውና በሰማያዊው ህይወት በምንለው ወሳኝ የሆኑ፣ ትልቅ ተጽዕኖ ያላቸውና የማያወላዱ የወታደሩንና ሃይማኖታዊውን ጨርቆች ነው የመረጥኩት። ሌላ ጊዜ ቢሆን ደግሞ ሌላ እመርጥ ይሆናል፤ አላውቅም። እነዚህ ሞቅ ያሉ እና ቀዝቃዛ ናቸው። ከቀለማቸው አንፃር ሊያጫውቱህ የሚችሉ ዓይነቶች ናቸው። በእነርሱ መጫወት፣ ንግግሮችን፣ ታሪኮችን፣ ኑሮዎችን፣ ሃሳቦችን፣ በእነርሱ መቃኘት ነው ያደረግኩት።

ታዛ፡- የህይወት ፍልስፍናህ ምንድን ነው? ህይወትን እንዴት ነው የምትረዳው?

 በቀለ፡- አንድ መንገድ የለም፤ ህይወት እንደሰጠህም ትኖራለህ። በየጊዜው ተሞክሮ እየፈጠርክ፣ እያነጠርክ ነው የምትኖረው። መጀመሪያ ሰው መሆን ምንድን ነው? ለምንድን ነው የምትኖረው? ከዛ በኋላ በምን በኩል ነው የምትናገረው፣ የምትተነፍሰው? የዚህን ዓለም ጉዳይ ከሌላው ሰው ጋር የምትካፈለው? እነዚህ ሁሉ ወሳኝ ነገሮች ናቸው። እኔ በዚህ በኩል ነው የተሰለፍኩት፤ በሥነ-ጥበብ መስመር። እውነትን መከተል፣ እውነት ራሱ ምንድን ነው ብሎ መፈተን፣ መጠየቅ፣ በተቻለ መጠን የጥበብ ሰው ሁሉ ከመንጋው ጋር የማይሰለፍ፣ አመለካከቱ በሙያው የተቀረጸ፣ አቅጣጫውን በተፈጥሮ በተሰጠው፣ በእውቀት ባዳበረው ሙያ የሚያይና ለሌላ የሚተርፍ አመለካከት የሚያበረክት፣ ሃሳብ የሚያበረክት መሆን አለበት ባይ ነኝ። እኔ አዝናኝ አይደለሁም፤ አሳሳቢ ነኝ። በእርግጥ ጥበብን ስትከውን በደረቁ እያስጨነቅክ አይደለም፤ ሆኖም እኔ ከማዝናናቱ ጎራ አይደለሁም። ወደ ማሳሰቡ ጎራ ነኝ ብል ይቀለኛል።

 ታዛ፡- ጥበብ ለአንተ ምንድን ናት?

በቀለ፡- እንደማንኛውም ሙያ ነው። ነገር ግን ግላዊ ነው፤ የግል እምነት፣ የግል እውቀት፣ የግል አመለካከት የሚቀርጸው የጋራ ሃሳብ። የጋራን አስተሳሰብ በተለይ በዚህ ዘመን የምንጋራውን አስተሳሰብና ህይወት፣ በተሰጠህ ተሰጥዖና ባዳበርከው ልምድና እውቀት፣ ሌላ አንፃር (አንግል ) ማሳየት ማለት ነው። በአጭር ቋንቋ ጠያቂ መሆን ማለት ነው።

 ታዛ፡- አንድ የጥበብ ሰው ምን ዓይነት ሰብዕና ያስፈልገዋል ብለህ ታስባለህ?

በቀለ፡- ብዙ ዓይነት ሰብዕና ሊኖረው ይችላል። እንደ ሰው ልጅ ስታስበው ማንኛውም ሰው ያን ያህል የተለየ አይደለም። ሰው ሰው ነው። ከሙያው ጋር ሲገናኝ ግን በየጊዜው የሚያዳብረው፣ የሚያከማቸው፣ የሚያነጥረው ሙያው ራሱ መልሶ ይቀርጸዋል። የተለየ አመለካከት፣ ያልተለመደ አመለካከት፣ እዛ ውስጥ እውነትም፣ እውቀትም፣ ውበትም አለ፤ በሃሳብ ባነጠርክ ቁጥር። እና ለዚህ ዓለም ያለው ትርጉም ከተርታው ሰው የተለየ እንዲሆን ተሰጥዖ- እውቀት- ልምድ- ችሎታ አለው። እነዚህ ነገሮች ተደምረው በጋራ የምናውቃቸውን ነገሮች ነው እንደገና የሚወልደው። ነገር ግን ሲወልደው አዲስ አድርጎ ነው። እንድንጠይቅ፣ እንድንደሰት፣ እንድንናደድ፣ እንድንበሳጭና አሃ እንድንል ማድረግ አለበት።

 ታዛ፡- በጥበብ የምትሰራውን ሃሳብ ትኖረዋለህ? እንደኖርከው ደግሞ በጥበብ ትገልጸዋለህ?

 በቀለ፡- እኔ የማምነውን ነገር ብቻ ነው የምሰራው። የማምነው ስል ውበት ሊሆን ይችላል፤ ሃሳብ ሊሆን ይችላል። ደግሞም እኖረዋለሁ።

ታዛ፡- አንተ በሥዕል፣ በቅርፃ ቅርጽ እና በግጥም ሃሳብህን እና ስሜትክን ትገልፃለህ። ሃሳብና ስሜትክን ለመግለጽ የበለጠ የሚስብህ ዘውግ የትኛው ነው?

በቀለ፡- ከዘውጉ ይልቅ ሃሳቡ ነው የሚስበኝ። እንዳልኩህ ሃሳቡ ውበት ብቻ ሊሆን ይችላል። ወይም የሚተረክና የሚተላለፍ ሃሳብ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ያ ሃሳብ ያ ውበት የሚፈልገው፣ የሚገባው መንገድ አለ። ያንን መንገድ እመርጣለሁ። ብዙ ጊዜዬን ብዙ ሰዓቴን በትምህርትም ገበታ ቢሆን ያሳለፍኩት በዕይታዊ ጥበባት ላይ ስለሆነ ምናልባት ለዛ የሚመቹ ሃሳቦችን፣ ለዛ የሚሆኑ ሂደቶችን እየመረጥኩ ሃሳቦችን በዛ መንገድ በማብላላት ላይ ላዘነብል እችላለሁ። ትምህርቴም፣ ብዙ ልምዴም፣ የማስተምረውም፣ ደመወዜም እንጀራዬም እዛ ላይ ስለሆነ ሊሆን ይችላል። ሃሳብ ራሱ መውጫውን ይጠቁማል። ያኔ ካልተመቸው እቀይራለሁ።

 ታዛ፡- በጥበብ ውስጥ የላቀ ጥበብ የቱ ነው? አንዳንድ የጥበብ ባለሟሎች ዜማ (ሜሎዲ) ሙዚቃ ነው የጥበብ ንጉሥ/ንግሥት ይላሉ። ሌሎች ደግሞ ግጥም ነው ይላሉ። ሌሎችም የዕይታ ጥበብ ነው በማለት ይገልፃሉ። ለአንተ የቱ ነው የላቀው ጥበብ?

በቀለ፡- ልክ ነህ የተለያዩ ትንታኔዎች አሉ። ጸሐፊዎች በተለያዩ ምክንያቶች ዜማን ሙዚቃን ከፍ ያደርጉታል። ፍጹም ረቂቅ ‹‹abstract›› ስለሆነ፤ ምንም ነገር ኮፒ ስለማያደርግ። በተለያዩ ሌሎችም ምክንያቶች። ፍጹም መንፈሳዊ ስለሆነ ምናምን ይላሉ። ሊሆን ይችላል። ነገር ግን የሚሻለው በየትኛውም ዘውግ፣ በየትኛውም ቅርጽ ይሁን ብቻ የተሳካ ሆኖ የወጣው፣ የተመልካችን አዕምሮ፣ ህሊና፣ ስሜት፣ የሚነቀንቀው ጥበብ ሁሉም ጥሩ ነው። ጥበበኛ በየትኛውም ዘርፍ ጥግ ድረስ ሄዶ ካላሳካ ሁሉም ይከሽፋሉ እንጂ የገባህበት ዘውግ ትልቅ ነው ተብሎ ስለተነገረህ ትልቅ አትሆንም። ለዚህ ትልቅ ምሳሌ የሚሆኑት የጃፓን ቢላ ቀራጮች፣ ቢላ ሞራጆች ናቸው። የጃፓኖች የቢላ ሥለት ሁልጊዜ ይገርመኛል። ሥለቱ እስከ ምን ጥግ እንደሚሄድ ያውቁታል። ሁሉም ሙያ የራሱ

 “ዓለም ያለህባት ሠፈር ብቻ አይደለችም። ያለህበትም ሠፈር አንድ ሰሞን ከዓለም ተውሶ ያመጣው ነገር ነው ያለው። ስለዚህ እርሱን እንደ ሃይማኖት መያዝ ትልቅ ስህተት ነው”

 መንገድ፣ የራሱ ልቀት፣ የራሱ ጥግ አለው። ነቅናቂነት። ካልነቀነቅከው ሁሉም ጥበብ ወዳቂ ነው። ከነቀነቅከው ደግሞ ሁሉም ይሰራል።

ታዛ፡- የጥበብ ሰው እንድትሆን በአስተዳደግህ፣ በአኗኗርህ፣ በህይወትህ መንስዔው ምንድን ነው?

 በቀለ፡- ይሄን ነገር ደጋግሜ አስቤዋለሁ። ተፈጥሮ ይመስለኛል፤ ተፈጥሮዬ። ቤተሰብ እንዳትል በቤተሰቤ እንደዚህ ዓይነት ሙያ ያለው ሰው የለም። አካባቢ እንዳትል ጥሩ ጥሩ ጀግኖች ወታደሮች የነበሩበት፣ ካምፖች ሁሉ የነበሩበት ደብረዘይት ከተማ ውስጥ ነው የተወለድኩት። አየር ኃይል በራሪዎች፣ የሰማይ ዘላዮች፣ ተኳሾች፣ ያሉበት ከተማ ነው። እንደገና ዙሪያው ውሃ ነው፤ ጥሩ ጥሩ ዋናተኞች ያሉበት ነው። እና ዙሪያውን ስታስተውል ከተፈጥሮ በስተቀር ከሥነጥበብ ጋር የሚያገናኝ ነገር የለውም። ስለዚህ የራስ ተፈጥሮ ይመስለኛል፤ እንደ አካባቢው ቢሆን፣ መሆን የነበረብኝ አየር ኃይል በራሪ መሆን፣ ወይም አየር ወለድ መሆን፣ አሊያም ስፖርት የመሳሰለው ነበር በልጅነቴ ስመለከተው የሚያማልለኝና ወደ ዝንባሌ የሚወስዱ መንገዶች ነበሩ። ምናልባት እነዛ ዝንባሌዎች ያልወሰዱኝ ጠንከር ያለ ለጥበብ የተመቸ አፈጣጠር በውስጤ ነበረ ማለት ነው።

 ታዛ፡- የምታደንቃቸው ሠዓሊዎች እነማን ናቸው? በምን አደነቅካቸው? (ከሀገር ውስጥም ከውጪም፤ ከቀድሞዎቹም፣ በመካከል በአንተ ዘመን እና አሁን ደግሞ ከወጣት ተማሪዎችህ)

በቀለ፡- ብዙ ሰውን በተለያየ ችሎታው ማድነቅ ያስፈልጋል። ብዙ ናቸው። ከኛ በፊት ብቻ ሳይሆን ከእኛም በኋላ አሁንም እየወጡ ያሉ ተስፋ ያላቸው ልጆች አሉ። ከኛ በፊትም ብዙ አሉ፤ ግን አንዱን ስትጠራ አንዱ እንዳይቀየም እንተወው እንጂ። አስተማሪዎቻችንም የነበሩ አሉ። በውጪ አገራትም በሙያቸው ሠዓሊ የሆኑ፣ እንዲሁም በሙያቸው ሠዓሊ ያልሆኑ እንዲሁ ተደባልቀው የሚኖሩ መዓት አስደናቂ ነገሮች አሉ። በእርግጥ እንደ ሌላው ሙያ ሁሉ ዝም ብሎ የሚግተለተል አሸር ባሸር አለ- በዚህ ዘመን። ለዚህ ነው አንዳንድ ሰዎች ቶሎ ተስፋ ቆርጠው እንደው ድሮ ቀረ ሁሉ ነገር የሚሉት ያለምክንያት አይደለም። ብዙ አሸር ባሸር አለ። ነገር ግን እዛም ውስጥ የዘመኑን ጥያቄ፣ የዘመኑን ምሳሌ፣ የዘመኑን ቋንቋ፣ የሚናገር አስደናቂ፣ አሳሳቢ ጥበብም አለ- በዚህ ዘመን ላይ። ከውጪ አገራትም አፍሪካውያንም፣ አውሮጳውያንም፣ ቻይኖችም አሉ የማደንቃቸው።

 ታዛ፡- የማትሸጠውና ከአንተ እንዲለይህ የማትፈልገው የጥበብ ሥራ አለህ?

በቀለ፡- እንደምታየው እኔ እኮ የሚሸጥ ነገር አይደለም የምሰራው። ታይቶ የሚፈረካከስ፣ የሚጣል ነው፤ ሥራዎቼ ለጌጥነት የሚሆኑ አይደሉም። እኔ በዘመናዊ የሃሳብ ሥራዎች ላይ አተኩራለሁ። የሚያወያዩ፣ ንግግር የሚፈጥሩ፣ የሚያሳስቡ ሥራዎችን ነው የምሰራው። ስዕል እንደ ድሮው በጌጥነት የተገደበ አይደለም። እንደ ሳይንስ እየተለወጠ እያደገ ነው የሚሄደው። ምክንያቱም ከዓርባና ሃምሳ ዓመት በፊት ሥዕልን ሸቀጥ ማድረግ ተቃውሞ ተነስቶበት ነበር። ከዛ ለመውጣት በሃሳብ ላይ ማተኮር። የሙያው ከፍታ ላይ ለመድረስ። ሸቀጥነትን ለማስቀረት ብዙ ሰዓሊዎች ታግለዋል። አንድ ግለሰብ መጥቶ እንደ ሸቀጥ የሚገዛውና የሚጠቀልለው እንዳይሆን። ይህ ዓይነቱ ጥበብ ይቅር ለማለት ሳይሆን ሁሉም ጥበብ ሸቀጥ መሆን የለበትም ነው። የሆነው ሆኖ አንዳንዴ በተሰማኝ ጊዜ እሱንም እሰራለሁ። ደጋግ ሰዎች አሉ እንደሱ ዓይነት ነገር ለማየት የሚመጡ። ለእነርሱ የሰራሁት አለ። ግን እንደዚህ ጽንፈኛ ሆኜ ይሄን እሸጣለሁ፣ ያንን አልሸጥም ብዬ አላውቅም። ምናልባት ጊዜን ለማስታወስ የሆነ ዘመንን ለማስታወስ ከሆነ መርጠህ የምታስቀረው ነገር ይኖራል እንደ መዘክር።

 ታዛ፡- ሥዕል ላይ ሃሳብ ይቀድማል ወይስ ጥበቡ የሚገለጽበት ውበት ይቀድማል? አንተ ሃሳብ ላይ የምታተኩር ስለመሰለኝ ነው?

 በቀለ፡- ሁለቱም እኩል አስፈላጊዎች ናቸው፤ ሁለቱም እኩል ቀዳሚዎች ናቸው። አሁን አሁን ግን ልክ ነህ ሃሳብ ላይ አተኩራለሁ። አየህ እድሜህ እየጨመረ ሲመጣ ኃላፊነት እየተሰማህ ትሄዳለህ። በእርግጥ ገና በሙያው ጀማሪ እያለህ  ሥለህ፣ ቀርጸህ፣ ሰርተህ ትምህርት ቤትም ሆነ ከትምህርት ቤት ወጥተህ በሥዕል መጫወት ቋቅ እስኪልህ ድረስ ከሄድክ በኋላ አእምሮህ ‹‹እና ምን ይጠበስ?›› (So what?) ይልሃል። የዚህን ጊዜ ፋይዳ ወዳለው ሃሳብ ፍለጋ ረጅም ርቀት ትጓዛለህ። ሆኖም በመጀመሪያዎቹ ጊዜ ወይኔ ይቺ ጨረቃ፣ ያቺ ጸሐይ፣ ወይኔ ይሄ ሥዕል ትላለህ። ይህ መማለል አሁንም ይኖራል ግን አንደኛህ ላይሆን ይችላል እንደ ልጅነትህ ብዙ አታጯጩህም። ወደ ሃሳብ መሻገር ትፈልጋለህና። በኋላ በህይወትህም፣ በሙያህም፣ በማህበረሰብህ፣ በአካባቢህ፣ በሀገርህ፣ በዓለም ሁሉ የሚመጡ ሃሳቦች አሉ። ብዙ ነገሮችን ስታነብ፣ ስታይ፣ ስትወያይ፣ ስትኖር ብዙ ጥያቄዎች ይመጣሉ ከመልሶቹ የበለጠ። እና እነርሱን ታብላላለህ፤ የኃላፊነት ሰው ትሆናለህ።

ታዛ፡- ታዲያ የአንተ ጥቅም ምኑ ላይ ነው? እንደምረዳው የምትኖረው ሥዕልን በማስተማር፣ በመሳልና በመቅረጽ ነው። እነዚህ አሁን በተለያዩ የዘመናዊ ጥበብ ቅርጽ (ለምሳሌ ኢንስታሌሽን) ያቀረብካቸው ቀላል የማይባል ወጪ ያላቸው ናቸው። ግን ደግሞ ተሽጠው ገንዘብ የሚያስገኙ አልመሰለኝም?

 በቀለ፡- እውነትህን ነው፤ እጅግ ብዙ ወጪ ነው የሚያስወጣው። በሌላ ሀገር የሀገርህ መንግስት የዜጋውን፣ የማህበረሰቡን እሴት ይደጉማል። ብዙ አገሮች ላይ አደጉም- በማደግ ላይ ሆኑም፤ ድሃ ሆኑም- ሃብታም፣ የሀገራቸውን የጥበብና የባህል እሴቶች ይደጉማሉ። እኛ ሀገር ይሄ እውቀት ስለሌለ፣ ልማዱ ስለሌለ፣ ከሌለ አልሰራም በሚል ዝም አትልም። የራሳችንን ስጋ እየበላን፣ ደማችንን እየጠጣንም ቢሆን እንሰራለን። ወጣቶቹም እንደዛ ነው የሚያደርጉት፤ ራሳቸውን በራሳቸው እየገደሉ ነው የሚሰሩት። በበኩሌ ከማስተማር ከማገኘው፣ ባለኝ ችሎታ የማገኛቸውን ሥራዎች ለምሳሌ ግለሰብ፣ ድርጅት፣ መንግሥት ይሄንን እንዲህ ብትሰራልኝ ሲሉ እሱን በመስራት በማገኘው ገንዘብ ይህን ጥበብ እየደጎምኩ፤ አቻችዬ የምሰራውን ሥራ፣ ምንም በማላቻችለው የግል የፈጠራ ሥራዬን እየደጎምኩ እራሴን በራሴ እየደገፍኩ እሰራለሁ።

 በነገራችን ላይ ከምትበላውም ቢሆን ትቀንሳለህ። አሁን ‹‹ባሩድና ብርጉድ›› ላይ በመቶ ሺዎች ነው ያወጣሁበት፣ የማይመለስ። የካታሎጉን ህትመት ጨምሮ። ሆኖም፣ መንግሥት እስኪባንንና የሀገሩን ባህልና ሥነ-ጥበብ እስኪደግፍ ድረስ፣ በራስህ ትሞክራለህ። አንዳንድ ደጋግ ግለሰቦች አሉ ደግሞ ጥበብን የሚያግዙ። ለምሳሌ በካታሎግ ህትመት በከፍተኛ ጥራት ሰርቶ አታሚው ግማሹን ወጪ ‹‹እናንተ ሠዓሊዎች መታገዝ አለባችሁ›› ብሎ ደግፎኛል። በሌላ አገር እንዲህ ዓይነት ግለሰቦችና ኩባንያዎች እንዲህ ዓይነት እርዳታ ሲያደርጉ፣ መንግሥት ከታክስ ነፃ ያደርጋቸዋል። እዚህ ግን ይህ አሰራር ስላልተለመደ አታሚው በነፃ ሊያትምልህ ቢፈልግ እንኳ ታክስ እሱን ስለማይምረው ከፊሉን መክፈል ትገደዳለህ። ሆኖም እንዲህ ዓይነት ደጋግ ሰዎችን ያብዛልን እያልክ ሥራህን ትቀጥላለህ።

ታዛ፡- ከትራስህ ሥር አሊያም ዙሪያህን እንዲጠፉ የማትፈልጋቸው መጻሕፍት አሉ? ስለምን ርዕሰ ጉዳይ ነው በፍቅርና በጉጉት የምታነበው?

 በቀለ፡- ብዙ ናቸው። ለምሳሌ የሃሳብ መጽሐፎች አሉ። ለምሳሌ ‹‹ዘ አይዲያስ ኦፍ ፊውቸር›› ወደ ዐርባ ሃምሳ ምሁራን መጪው ዘመን ምን ይመስላል ብለው የተለያዩ ሃሳቦችን ያመላከቱበት አለ። እንዲህ ዓይነት መጻሕፍት ሃሳብ ይሰጡሃል፣ ሃሳብህን ያዳብሩልሃል፣ ያነቃቁሃል። በቅርብ ጊዜ የሞተው የሲኒማ ጥበብ ምሁሩ ፕሮፌሰር ተሾመ ኃይለገብርኤል የላከልኝ ነው- ከማረፉ በፊት። መጽሐፉ ያልዳሰሰው ነገር የለም፤ ይህ መጽሐፍ ከአጠገቤ አይርቅም። ሃሳብ ላይ የሚያተኩሩ፣ ሃሳብን የሚያብላሉ መጻሕፍት ይስቡኛል። ጥሩ የተፃፈ ባዮግራፊ (ግለ-ታሪክ)ና ሳይንስ ፊክሽን ይማርኩኛል። ጥበብ ላይ የተሰሩ ዘመናዊ ቲዎሪዎች፣ ዘመናዊ ሥነ-ጽሑፎች፣ የጥበብ ታሪኮች ደግሞ የመጀመሪያ ምርጫዎቼ ናቸው።

 ታዛ፡- ወደ ጥበብ ፈጠራ ስትገባ መነቃቂያህ መንገድ ምንድን ነው? አዳዲስ ሃሳቦችስ በምን ጊዜ ነው የሚመጡልህ?

 በቀለ፡- አሁን ከተወሰነ እድሜ በኋላ፣ ምንም መነቃቂያ አያስፈልግም። በእርግጥ ገና ሙያው ውስጥ ለመግባት፣ ለመጠንከር ነው መነቃቂያ (ኢንስፓይሬሽን) የምትፈልገው። አንድ ጊዜ ከገባህበት በኋላ ግን አንተ ትክክለኛ የጥበብ ሰው ከሆንክ ሃያ አራት ሰዓት ሥራህ ጥበብህ ውስጥ መኖር ነው። ሁልጊዜ እየሰራህ፣ ሃሳብ ፈጠራ እያብላላህ ነው የምትኖረው። ለመነቃቂያ የምትጠብቀው ጠዋትና ማታ የለም። ለምን መጸዳጃ ቤት አትሆንም ያለኸው በሥራህ ላይ ነህ፤ ከዛ ውጪ አይደለህም። ቀደም ሲል በአካባቢህ የምታየውን ነገር ከጥበብ አንፃር ትመለከታለህ፤ ሙዚዬም ገብተህ ትመለከታለህ። ጋለሪዎች ትፈልጋለህ፣ የጥሩ ጥሩ ሠዓሊዎችን ስቱዲዮዎች ትጎበኛለህ፣ በፈጠራ ለመነሳሳትና ለመነቃቃት። አንድ ጊዜ ከገባህበትና ከሰጠምክ በኋላ ግን ሁሌም እዛው ውስጥ ነህ።

ታዛ፡- በአለፈለገ የሥነጥበብ ት/ቤት መምህር ነህ፣ ዳይሬክተርም ነበርክ። የዚህ ሀገር የዕይታ ጥበብ ከየት ተነስቶ ወደ የት እየሄደ ነው ትላለህ?

 በቀለ፡- ተሰጥዖ አለ፣ ታሪክ አለ፣ ስቶሪ አለ፣ ጥያቄ አለ፣ ነገር ግን ህብር የለም። የተያያዘና በሲስተም የሚሄድ አይደለም። በጣም የሚገርመው እዚህ ሀገር ሁልጊዜ ተሰጥዖ አለ። ነገር ግን በመዋቅር የተደገፈ (ስትራክቸርድ) አይደለም። በደንብ የተያያዘ አይደለም። እንድንገለገልበት ሆኖ የተደራጀ አይደለም። እንደገና ደግሞ በአደባባይም፣ በትምህርት ቤትም ለዚህ መቶ ሚሊዮን ህዝብ ሊጠቅም እንደሚችል ሆኖ አይደለም ያለው። በግራፍ ብታወጣው ጨርሶ አይታይም። የለም። እና እንዲጠቅመን አድርገን ማደራጀት ያስፈልገናል። የሚጠቅመን በብዙ መንገድ ነው። መሠረታዊ ነው። እንዳልኩህ ሥነጥበብ መዝናኛ ብቻ አይደለም። መዝናኛ ቢሆንም ትልቁ

“በነገራችን ላይ ከምትበላውም ቢሆን ትቀንሳለህ። አሁን ‹‹ባሩድና ብርጉድ›› ላይ በመቶ ሺዎች ነው ያወጣሁበት፣ የማይመለስ። የካታሎጉን ህትመት ጨምሮ። ሆኖም፣ መንግሥት እስኪባንንና የሀገሩን ባህልና ሥነ-ጥበብ እስኪደግፍ ድረስ፣ በራስህ ትሞክራለህ”

ጉዳዩ እሱ አይደለም። አሁንም ያወቅንበት አልመሰለኝም፤ ብትንትን እንዳለ ነው ያለው።

 ታዛ፡- አንተ የት/ቤቱ ዳይሬክተር በነበርክበት ጊዜ እነዚህን ችግሮች ለማረቅና ለመቅረፍ ምን አስተዋጽዖ አበረከትክ?

በቀለ፡- በጣም ብዙ አስተዋጽዖ አድርጌያለሁ። ከነበረብን ችግር ተነስቼ ያልተሳተፍኩበት ትግል የለም። ትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ትምህርት ቤት እንዲሆን፣ ማደሪያ ዶርም እንዲኖረውና የትምህርት አሰጣጡ ለዓለም ክፍት እንዲሆን ከሚታገሉት ጋራ ከፊት በመሆን ብዙ አስተዋጽዖ አድርጌያለሁ። ይህን ስኬቴን ማየት ነው። ትምህርት ቤቱ የዛሬ ሃያ ዓመት ምን እንደሚመስል አይቶ ዛሬ ምን እንደሚመስል ማየት ነው እንግዲህ።

 ታዛ፡- አሁን ያለው የሥነጥበብ ትምህርት ሂደት የትኛውን የማስተማር መንገድ ነው የሚከተለው?

በቀለ፡- እንግዲህ በዚህ ዘርፍ የተጠናከረ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም ያለው አንድ ነው። ሌሎች እየተከፈቱ ነው። ግን ይሄ የባህል ጉዳይ ስለሆነ፣ የተሰጥዖ ጉዳይ ስለሆነ በአንድ ጊዜ ዝም ብለህ ትምህርት ቤት አታደርገውም። ልምድና ሲስተም መኖር አለበት። በዚህ አንፃር ስታይ አንድ ትምህርት ቤት ነው ያለው። በተለያየ አገር የተለያየ ትምህርት ቤት ሲኖር የተለያየ አስተሳሰብና ፍልስፍና፣ የተለያየ ዓይነት ቴክኒክ ይከተላል። ያ አማራጭ አለው። እዚህ ግን በአንድ ትምህርት ቤት ብዙ ነገር ማድረግ ትርፉ ውድቀት ነው የሚሆነው። ስለዚህ ሀሁ-ንም፣ ቀጥሎ ያለውን ፐፑ-ንም እዛው ውስጥ ስለሚማሩ፣ መሠረታዊ ነገሮችን ከዛው ጀምሮ፣ ከዚያ በኋላ ቀስ እያሉ፣ በሥነጥበብ ታሪክ ሃሳብ ውስጥ እያለፉ፣ የዘመኑን ሁኔታዎች፣ ዘመኑ የደረሰበትን መንገድ ደግሞ እንዲያውቁና ራሳቸውን እንዲችሉ መንገድ የሚቀይስ ፍልስፍና ነው። አንድ ትምህርት ቤት ሲሆን እንዲህ ማድረጉ ጠቃሚ ነው። መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በመመልከት። ነገር ግን በጊዜ ውስጥ አቋሙን እያስተካከለና እየለዋወጠ ሊሄድ ይችላል።

 ታዛ፡- እዚህ ላይ እንደ መምህር የአንተ አስተዋጽዖ ምንድን ነው?

 በቀለ፡- አንደኛ አርፎ ማስተማር። ስታስተምር ደግሞ የተቀጠርክበትን ኮንትራት መስመር መከተል ግድ ነው። እንደገና ደግሞ የምታምንበትን ነገር ለመጨመር የሚከለክልህ ነገር የለም። የምታምንበትን ስል የጎደለውን ነገር ከማንበብ፣ በዓለም ላይ ከመጓዝ፣ ሥነ-ጥበቡ የደረሰበትን ከፍታ ከመረዳት- ከመገናኘት፣ ከዚህ ተነስተህ ጎደለ የምትለውን ነገር ለማሟላት ራስን ዝግጁ ማድረግ፣ ተመልካችም፣ አስተማሪም፣ ሠዓሊም ራስን ከዘመኑ የጥበብ እንቅስቃሴ ጋር ማስተዋወቅ ያስፈልጋል። ዓለም ያለህባት ሠፈር ብቻ አይደለችም። ያለህበትም ሠፈር አንድ ሰሞን ከዓለም ተውሶ ያመጣው ነገር ነው ያለው። ስለዚህ እርሱን እንደ ሃይማኖት መያዝ ትልቅ ስህተት ነው። ሥነ-ጥበብና ሃይማኖት ይለያያል። ይሄኛው ዳይናሚዝሙ (ልውጥውጡ) እንደ ሳይንስ ፍልስፍናም ቢሆን፣ ከሳይንስም ጋር የተያያዘ ስለሆነ የልውጥውጡ ሂደት ፈጣን ነው። ስለዚህ ምንድን ነው ያፈጠነው? ምንድን ነው እየተደረገ ያለው? ምንድን ነው እያደረግኩ ያለሁት? የሚለውን እንደሌላው ሙያ በንባብም፣ በሥራም፣ በውይይትም፣ በጉዞም፣ በጉብኝትም፣ ራስን ከፍ ማድረግ፣ መረጃን ማደራጀት፣ እውቀትን ማደራጀት የግድ ነው። በዛ መሠረት ከዘመንህ ጋራ ትሄዳለህ፣ የዘመንህ ጥያቄ ይገባሃል፣ የዘመንህን ጥያቄ ትመልሳለህ። አለበለዚያ እዚህ እየኖርክ እንደሌለህ ትሆናለህ። ማንንም አትጠቅምም፤ ራስህንም። ስለዚህ ሁልጊዜ ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል።

ታዛ፡- በአሁኑ ጊዜ የሥዕል ገበያ እየደራ ነው ይባላል?

በቀለ፡- እውነት ነው። መሸጥ ከፈለክ ገበያው አለ። ገበያው ከድሮው በእጅጉ የተሻለ ነው። ገንዘብ ያለው ሰው እየተፈጠረ ሲመጣ፣ ገንዘቡን ከሚያውልበት አንዱ ሥነጥበብ – ሥዕል ነው። ከበፊቱ የተሻለ ቢሆንም አሁንም ገና የመቶ ሚሊዮን ጉዳይ አልሆነም። መቶ ሚሊዮን ህዝብ ባለበት አገር የሚገዛውን ያህል አይደለም ስዕል እየተሸጠ ያለው።

“ትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ትምህርት ቤት እንዲሆን፣ ማደሪያ ዶርም እንዲኖረውና የትምህርት አሰጣጡ ለዓለም ክፍት እንዲሆን ከሚታገሉት ጋራ ከፊት በመሆን ብዙ አስተዋጽዖ አድርጌያለሁ። ይህን ስኬቴን ማየት ነው” �

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top