ዘባሪቆም

ከዘፈኖቻችን

በልጅነቱ ወደ አሜሪካ ከመጣ አንድ የአጎቴ ልጅ ጋር በእድሜ እኩዮችና የልብ ጓደኛሞች ነን። እዚህ እንደማደጉ ቋንቋውን ያልረሳ፣ ወግና ባህሉን ያልሳተ ጥሩ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ከሚያለያየን ይልቅ የሚያግባባን ይበዛል። ከምንለያይባቸው ጥቂት ነገሮች መካከል አንዱና ዋንኛው የሙዚቃ ምርጫችን ነው። እኔ ረጋና ቆዬት ያሉ አገርኛ ዘፈኖችን ስመርጥ እርሱ ፈጠን ባሉ ዘመናዊ ሙዚቃዎች አብልጦ ይሳባል። ከከተማ ወጣ ባልንበት አንድ አጋጣሚ በየተራ ዘፈን እየመረጥን ስንጓዝ በጣም ከምወደው ድምፃዊ ዜማዎች አንዱን ከፈትኩ። “ሰርካለም እንዲያው ደ’ና ደ’ና (ሶስት ጊዜ)

ጀማመርነው እንጂ መች ዘለቅነው ገና፣

ሳብዬ ይሁን ደ’ና ደ’ና ((ሶስት ጊዜ))

ፍቅሩን አይንፈገን ሰላምና ጤና…”

በትዝታ የኋሊት ተጉዤ በተመስጦ አብሬ ሳንጎራጉር “ለስንት ሰው ነው እንዴ የሚዘፍነው?” ሲል አቋረጠኝ። የተለመደ ጭቅጭቁ ነው ብዬ በዝምታ ላልፈው እየፈለግኩ ወዲያው “እንዴት?” ብዬ ጠየቅኩት።

 “መጀመሪያ ላይ ሰርካለም ብሎ ሲደግመው ደግሞ ሳብዬ ይላል እኮ” አለኝ። ወደኋላ መልሼ ድጋሚ ሰማሁት። ቃል በቃል ሸምድጄ ስንት ዘመን ስዘፍነው የኖርኩት ዘፈን ውስጥ ልብ ያላልኩትን ነገር ስላሳየኝ ከመገረም ባለፈ ለርሱም ሆነ ለራሴ የምሰጠው ምላሽ ስላልነበረኝ በዝምታ መንገዴን ቀጠልኩ።

 በሌላ ቀን የዘፈን ‘ኮንሰርት’ ስንታደም ከሙዚቃ መሃል “የለውም አባይ” የሚለው የተለምዶ ጭፈራ ደራ። ዘፋኙ አገር መንደሩን እየጠራ ድፍን ኢትዮጵያ “የለውም አባይ” እያለ ሲያካልል ይሄው ነገረኛ ዘመደ- ጓዴ ወደ ጆሮዬ ጠጋ አለና “አባይ ምንድነው?” ሲል ጠየቀኝ። “አባይ ማለት ቃል-አባይ፣ በቃሉ የማይፀና ወይም ውሸታም ማለት ነው” ብዬ የቻልኩትንና የመሰለኝን ካብራራሁ በኋላ “ኢትዮጵያ ውስጥ ውሸታም የለም ወይ?” ብሎ እንዳይሞግተኝ ፊቴን በፍጥነት ወደ ጭፈራው ስመልስ “ተቀባዩ ‘አንች ወላዋይ’ የሚለውስ ለምንድነው?” ሲል ባላሰብኩት መንገድ አፋጠጠኝ። እውነትም አገር ምድሩን “የለውም አባይ” እያለ በሚያወድስ ዘፈን መሃል ‘አንች ወላዋይ’ የሚል ስድብ ምን ሲል ገባ? እያልኩ ከርሱ በፊት ለራሴ መልስ መፈለግ ጀመርኩ። በበኩሌ ይህን “የለውም አባይ” የሚል ዘፈን ስሰማ ሌላ ግርም የሚለኝ ነገር አለ። “የጎንደር ልጅ፣ የትግራይ ልጅ፣ የወሎ ልጅ፣ የኦሮሞ፣ የጎጃም ልጅ፣ የጉራጌ፣ የጋምቤላ፣ የሲዳሞ፣ ወዘተ ልጅ ‘የለውም አባይ’ በሚለው የጭፈራ ደምብ መሰረት ታዳሚው ለየትውልድና እድገት አካባቢው ድምፁን ያዋጣል። “የቦሌ ልጅ ሲባል ግን ከቦሌ ቀርቶ በቦሌ ያልመጣው ሳይቀር ባንድነት ጩኸቱን ሲያቀልጠው አዘውትሬ ታዝቤያለሁ። ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የተዋወቅኩት አንድ ፈረንጅ ኢትዮጵያዊ መሆኔን እንደነገርኩት “Are you from Addis too?” (አንተም ከአዲስ አበባ ነህ?) ሲል ጠየቀኝ። ለምን እንደዛ እንዳለኝ መልሼ ስጠይቀው መልሱ “That’s where every Ethiopian I met say they’re from” (የማገኘው ኢትዮጵያዊ በሙሉ ከአዲስ ነኝ ስለሚለኝ ነዋ) የሚል ነበር ።

 ስለዘፈን ግጥሞች ካነሳሁ ዘንድ እግረመንገዴን በሰማኋቸው ቁጥር ጥያቄ የሚያጭሩብኝን ጥቂት ስንኞች ልጥቀስ።

ጥያቄ 1. ቆየት ባለ አንድ ዘፈን ስማቸውን ያልያዝኩት ወንድና ሴት ድምፃውያን እንዲህ ሲሉ ይቀባበላሉ:-

(እሱ) “ፍቅርዬ”

(እሷ ) “ወይ”

(እሱ) “ፍቅርዬ”

(እሷ ) “ወይ”

(እሱ) “ፍቅር አይደለም ወይ፣ ወይ አትይኝም ወይ?”

 “ፍቅርዬ” ባለ ቁጥር ሳታሰልስ “ወይ” እያለች የምትቀበልን ትጉህ አጃቢ “ወይ አትይኝም ወይ?” ብሎ መውቀስ ሙያዊ አግባብ አለው?

ጥያቄ 2. በሌላ ቆየት ያለ ዜማ ደግሞ ድምፃዊቷ ወዳጇን:-

“ቁጭ በል ከሶፋው ሂድ ይመሽብሃል፣

በልብህ ውደደኝ ባይንህ ያውቁብሃል” ስትል ታግባባለች። በድብቅ ውደደኝ የሚለውን መልክት ለማስተላለፍ ቁጭ እንዲልም እንዲሄድም ባንድ ስንኝ የሚታዘዘው አፍቃሪ ምን እርምጃ እንዲወስድ ይጠበቃል?

ጥያቄ 3.

“ወዲያው የሚበራ ወዲያው የሚጠፋ፣

የወረት ፍቅር ነው የፍቅሮች ከርፋፋ”

ወዲያው በርቶ ወዲያው የሚጠፋን ፈጣን ነገር “ከርፋፋ” ማለት እንደምን ይቻላል?

ጥያቄ 4.

“እኔማ ያላንቺ መች ይሆንልኛል፣

ኑሮ እንደተራራ ገደል ሆኖብኛል”

ይሄኛውን እኔው ራሴ ልመልሰው:

እኔማ ያላንቺ መች ይሆንልኛል

ተራራና ገደል መለየት አቅቶኛል!

ቸር እንሰንብት! b_gfb_g��-J

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top