የታዛ ድምፆች

ተዋናይ ለሙያው ምን ያህል ርቀት ይሄዳል?

አንዳንድ ፊልሞች ላይ የማ ይታጡ ብሶቶች አሉ። ካ ሜራ ቆሞ፣ ተዋንያን፣ አዘጋጅና አ ምራች ተጨንቀው ከረፈደ በኋላ ደርሶ “ይቅርታ ጎበዝ ሌላ ቀረጸ ላይ ስለነበርኩ ነው፤ አሁን የትኛውን ክፍል ነው የምቀረጸው? መታ መታ አድርጌ ልሂድ፣ እነ እንትና ደግሞ ይጠብቁኛል” የሚል አለ። ጅልነት እስኪመስልባቸው ድረስ ህይወታቸውን ለፊልም የሚገብሩም አሉ። እንዲያው ይህም አለ እንዴ እንድትሉ ከኢንተርኔት የቃረምኩትን ላካፍላችሁ።

ሮበርት ደኒሮ የምር ታክሲ ሾፌር ሆኗል ሮበርት ደኒሮ

እውነት ፊልም ላይ የታክሲ ሾፌር ሆኖ ለመጫወት የታክሲ መንጃ ፈቃድ ያስፈልጋል? መኪና መንዳት እርግጥ ያስፈልጋል። ግን ታክሲ ላይ መሸቀል ከተዋናዩ ይጠበቃል? እርስዎን መጠየቄ ነው። ሮበርት ደኒሮ ታክሲ ድራይቨር በተባለው ፊልም ሹፌሩን ለመጫወት በሚገባ ሰልጥኖ የታክሲ ስራ ፈቃድ አውጥቷል። በቀረጻ መሀል እረፍት ሲሆን ኒውዮርክ ከተማ ውስጥ እየተዘዋወረ የታክሲ ስራ ይሰራ ነበር። ደኒሮ ቦክሰኛ ሆኖ ለተጫወተበት “Raging Bull” ለተሰኘው ፊልም ቦክስ መሰልጠን ብቻ ሳይሆን ቦክሰኛ ሆኖ ሚናውን በደንብ ለመወጣት 60 ፓውንድ (ከ27 ኪሎግራም በላይ) ክብደት ጨምሯል።

አን ሀታዌ ከ11 ኪሎ በላይ ቀንሳለች

 “Les Miserables” (መጽሐፉ “መከረኞቹ” እና “ምንዱባን” ተብሎ በሁለት ደራሲያን ወደአማርኛ ተተርጉሟል።) በተባለው ፊልም ውስጥ አንን ያዬ መከራዋ ይጋባበታል። ጭንቀቷ ጭንቀቱ ይሆናል። ወትሮም ቀጫጫ ትባል የነበረችው አን ይህችን ገጸ ባህሪ ለመጫወት የገብስ አጥሚት ብቻ እየጠጣች ከምግብ ተለያይታ በመክረም ከ11 ኪሎ በላይ ቀንሳለች። “ምን ላድርግ፣ ገጸ ባህሪዋ እንዲህ ነች” ትላለች። ሞት አፋፍ ላይ የቆመች እናት። የገጽ ቅብ ባለሙያዋ እና የፊልሙ አዘጋጅ ተይ እያሉ ቢመክሯትም አን ጸጉbን ሙልጭ አድርጋ ተቆርጣለች። “ህጻን ልጅዋን በህይወት ለማትረፍ ማንኛውንም መስዋእትነት የምትከፍልን እናት ህመሟን ለመረዳትና ለመጫወት ይህን ማድረግ ነበረብኝ” ብላለች። ይህ ጥረቷም የኦስካር ሽልማት አስገኝቶላታል።

ሂዝ ሌጀር ለአንድ ወር ከመኖሪያ ቤቱ አልወጣም

“The Dark Knight” በተባለው ፊልም ዘ ጆከር የተባለውን ገጸ ባህሪ ለመጫወት ሌጀር ቀወስ አድርጎት ነበር። ለወር ከቤት አልወጣም። የፊልሙ ቀረጻ ሲቃረብ መተኛት አቃተው። በቀረጻ ወቅት ማንንም ከባህሪው ውጪ አያናግርም ነበር። የሱ ተራ ባልሆነባቸው ቀናቶች ጭምር በቀረጻው አካባቢ እየተገኘ በሚጫወተው አስፈሪ ገጸባህሪ ሰዎችን ያስደነብር ነበር። ኤጭ አበዛኸው ቢባል ማንን ሰምቶ። ሌጀር ከፊልሙ ምርቃት በፊት በድንገት ሲሞት “የተጠናወተው ገጸባህሪ አለቅ ብሎት ነው ለሞት የተዳረገው” ተብሎ ተወራበት። በዚሁ ትወናውም ኦስካርን ጨምሮ በርካታ ሽልማቶችን ከሞት በኋላ አግኝቷል።

 ኬት ዊንስሌት እንደ ጀርመኖች መኮላተፍ ጀምራ በዛው ቀርታለች

በታይታኒክ ፊልም ውስጥ ባሳየችው ድንቅ ትወና ነፍሳችን ውስጥ የገባችው እንግሊዛዊቷ ኬት ዊንስሌት “The Reader” የተባለውን ፊልም ለመጫወት እንደ ጀርመኖች መኮላተፍ ነበረባት። ሆኖም በጣም አጥብቃ ይዛው ስለነበር በዛው ቀርታ ጉድ ሆናለች። ምሽት ላይ ልጆቿን ለማስተኛት ተረት ታነብላቸው ነበር። በዚያን ሰሞን ልጆቿ አልገባቸው ብሎ ሰነበቱ። 

ሺመልስ አበራ የአይን ብርሀኑን ሊያጣ ነበር

“ሰኔ 30” በሚባለው ፊልም ላይ ሺመልስ አበራ አንድ በበሽታ ምክንያት አይኑን የጋረደውን ገጸ ባህሪ እንዲጫወት ይመደባል። ሺመልሽ ይህን ገጸ ባህሪ አሳምሮ ተጫውቶታል ብለው የትወና አጋሮቹ መስክረውለታል። አንድ ቀን ግን በቀረጻ ወቅት ሺመልስ የዓይን ብርሀኑን ለመጋረድ የተገጠመለት ሌንስ ክፉኛ ያቃጥለዋል። ይህን አስታውቆ ሌንሱ ሲነሳለት ሺመልስ በጭለማ እንደተዋጠ ይቀራል። አዳሜ ደንግጦ ተbሩጦ የአይን ሀኪም ዘንድ ይወስዱታል። ትንሽ ቢቆይ በዛው ይቀር እንደነበር ሀኪሙ ከህክምና በኋላ አስታውቋቸዋል። ቴክኒካል የሆነ ስህተት ነው ሺመልስን ለዚህ ያበቃው። 

ሠአሊ ገጸ ባህሪን ለመጫወት ሠአሊ ሆኖ መገኘት

 ኤድ ሀሪስ

ብዙ ጊዜ ተዋናይ የሠአሊ ገጸባህሪን የሚጫወተው እንዴት መሰላችሁ? ከካንቫስ ጀርባ ተዋናዩ አንዴ እየተመሰጠ፣ ሲለው በብሩሹ ቀለም እያጠቀሰና ሸራው ላይ እየነካካ ልክ ስእል እንደሚስል ሰው ሲንቀሳቀስ ይታያል። ከዛም እጁ ብሩሽ ጨብጦ ቀለም እና ሸራ ሲያገናኝ በቅርበት ታያላችሁ። እጁ ግን የሱ ሳይሆን የሌላ የስእል አዋቂ እጅ ነው። ፊልም የሁለት ሰው አካል አንድ ያደርጋል።

 ኤድ ሀሪስ ግን ይህን አልመረጠም። በአሜሪካ የጥበብ ታሪክ ውስጥ በተለየ የአሳሳል ቴክኒኩ የሚታወቀውን ፖሎክ የተባለ ሠአሊ ለመጫወት ኤድ ይመደባል። ኤድ መጀመሪያ ያደረገው ስለፖሎክ የተሰሩ ጥናታዊ ፊልሞችን በመመልከት ሰአሊውን በጥንቃቄ ማጥናት ነበረ። እናም ኤድ የስእል ስቱዲዮ ገነባ። ከዚህ ቀደም ስእል ሞክሮ የማያውቀው ተዋናይ ፖሎክን ለመጫወት ሲል ራሱ ሠአሊ ሆኖ አረፈው። ፖሎክ ሌሎች እንደሚያደርጉት ስእል የሚሰራው ቀለም በብሩሸ እየቀባ እንዳይመስላችሁ። ቀለም እያፈሰሰ ወይም እየደፋ ነው የሚስለው።

ጃክ ኒኮልሰን የአእምሮ ህሙማንን ህክምና ቀምሷ

በቴያትር ጥበባት ውስጥ አንድ ተዋናይ የሚጫወተውን ገጸባህሪ ሀሳብ እና ስሜት ውስጡ በመፍጠር ተአማኒ የሆነ ትወና ለማሳየት የሚረዳው “ሜቶድ” የተባለ ስልት ይጠቀማል። ጃክ ኒኮልሰን በዚህ ቴክኒክ የሚችለኝ የለም ባይ ነው። ጃክ “One Flew Over the Cuckoo’s Nest” በተሰኘው ፊልም ውስጥ የአእምሮ በሽተኛ ሆኖ ተጫውቷል። እናም የገጸባህሪውን ህመም ለመታመም ሰውነትን ክፉኛ የሚያናውጠውንና ራስን ለመሳት የሚዳርገውን ECT የተባለ ህክምና ወስዷል።

የሚጫወቱትን ገጸባህሪ ሆኖ መቅረትም አለ!!

 ናኦሚ ራፓስ

ናኦሚ ራፓስ መሽቀርቀር እና መኳኳል የምትወድ፣ ውበቷን ለመጠበቅ መስታወት ፊት ሰአታትን የምታባክን ወጣት ነበረች። ታዲያ ይቺ ሽቅርቅር “The Girl with the Dragon Tattoo” በሚባል ፊልም ውስጥ አንዲት እኛ ዱርዬ የምንላት ዓይነት ገጸባህሪ እንድትጫወት ትመደባለች። ጸጉbን አሳጠረች፣ ጸጉbን አቀለመች፣ ቅንድቦቿን አነጣች፣ አፍንጫዋን በሳች። ይሄ ሁሉ የተሰጣትን ገጸ ባህሪ አሳማኝ አድርጋ ለመጫወት ነው። እናም ተሳካላት። እሷ ግን ከዚህ ፊልም በሁዋላ ያ ሁሉ መሽቀርቀር ቀርቶ ጠዋት ከእንቅልፍዋ ስትነሳ ያገኘችውን ለብሳ የምትወጣ ‘ኬሬዳሽ’ ሆና አረፈችው።

አድርያን ብሮዲ ቀን ከሌት ፒያኖ አጥንቷ

ይሄን ጭንቅና ጣር የበዛበት “The Pianist” የተባለ ፊልም አይታችኋል? አድሪያን ብሮዲ አጥንቱ ገጦ፣ ቆዳው አጥንቱ ላይ ተጣብቆ፣ ረሀብ፣ ድካም፣ ፍርሀትና ሽብር ሲንጠው ታዩታላችሁ። በሜካፕ ወይም በሆነ ጥበብ እንዳይመስላችሁ። ብሮዲ ይህን ፊልም እንዲጫወት ሲመደብ ቤቱን ለቀቀ፣ መኪናውን ሸጠ፣ ስልኩን አጠፋ፣ ሁለት ሻንጣ እና አንድ ኪቦርድ አንጠልጥሎ ወደ አውሮፓ ነጎደ። በሁለተኛው የአለም ጦርነት ጊዜ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ፍዳቸውን ይበሉ የነበሩ አይሁዶችን ያጠና ጀመር። ገጸባህሪውን ታማኝ አድርጎ ሊጫወተው የሚችለው በጥናቱ የደረሰበትን የአይሁዶችን ፍዳ እሱም ሲቀምስው እንደሆነ ብቻ ስለተረዳ ስቃያቸውን ለመሰቃየት፣ ስጋታቸውንና ሽብራቸውን ለመረበሽ ወሰነ። ስለዚህም በረሀብ መገረፍ ጀመረ። እናም ከክብደቱ ላይ 13 ኪሎ ቀነሰ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top