ጥበብ በታሪክ ገፅ

ሚሀይል ባቢቼቭ፣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ፓይለት

ስለ ሚሀይል ባቢቼቭ የሕይወት ታሪክ መፃፍ ስንጀምር፣ ይህ ሰው እንዴት የ መ ጀ መ ሪ ያ ው የኢትዮጵያ ፓይለት ሊባል ይችላል? እንዲያውስ ኢትዮጵያዊ ነው ወይ? የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ሚሀይል ባቢቼቭ ኢትዮጵያዊ መሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም እላይ ያነሳናቸውን ጥያቄዎች ለመመለስ ትንሽ ወደኋላ ሄድ ብለን የሩሲያ ጦር ሠራዊት መኮንን ስለነበረው አባቱ ስለ ኢቫን ባቢቼቭ አንዳንድ ነገር ማለት ያስፈልጋል።

 በ19ኛው ምዕተ ዓመት መጨረሻ ላይ ኢትዮጵያ ነፃነቷን ለማስከበር የሞት ሽረት ትግል በምታደርግበት ሰዓት ለኢትዮጵያ ድጋፍ ካደረጉ አገሮች መካከል ሩሲያ አንዷ ነበረች። በወቅቱም የዚህች አገር ዜጉች በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኢትዮጵያ ይመጡ የነበረ ሲሆን፣ ኢቫን ባቢቼቭ አንዱ ነበር። ኢቫን በመጀመሪያ (በ1896 ዓ.ም.) የሄደው ወደ ጅቡቲ እንደነበር የልጅ ልጁ አሌክሳንደር ባቢቼቭ ይገልጻል።

ባቢቼቭ ለምን ወደዚህ እንደመጣ ግልፅ ባይሆንም፣ ከእሱ በፊት ወደ አፍሪካ የመጣውንና ኖቫያ መስክቫ የተባለ የሩሲያ ቅኝ ግዛት በአፍሪካ ለማቋቋም አስቦ የነበረውን የኒኮንያ አሺነቭን አርአያ ተከትሎ ሳይሆን አይቀርም የሚል አስተያየት ይሰነዘራል። እሱም በጁቡቲ በነበረበት ወቅት ለሩሲያ የሚሆን መሬት እንዲሰጣቸው ከራሔታው ሱልጣን ጋር በግል ድርድር አድርጎ እንደነበር ይነገራል። ዳሩ ግን ይህ የተባለው ግዛት በፈረንሳይ ቁጥጥር ሥር ይገኝ ስለነበር ግንኙነታቸውን ሊያሻክረው እንደሚችል በመገመት የሩሲያም ሆነ የፈረንሳይ ባለሥልጣናት የባቢቼቭን ጥረት በበጎ ዓይን ስላላዩት ዕቅዱ ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም። በርግጥ ባቢቼቭ ይህን እርምጃ ከሩሲያ መንግስት ድጋፍ ሳያገኝ በራሱ ፍላጎት ነው የወሰደው ለማለት ያስቸግራል። ከዚህ በኋላ ባቢቼቭ ወደ አገሩ ቢመለስም፣ በሚቀጥለው ዓመት በ1897 ዓ.ም. እንደገና ወደ ጅቡቲ ይመጣል። በዚህ ወቅትም ወደ ኢትዮጵያ በመሄድ ላይ ከነበረው የንጉሡ አማካሪ ከኮንት ሊኦንትየቭ ጋር ይገናኛል። ይህም ግንኙነት የባቢቼቭን ሕይወት ፍፁም ይለውጠዋል። ባቢቼቭ በሊኦንትየቭ አቅራቢነት ከዐፄ ምኒልክ ጋር ለመተዋወቅ ዕድል ያገኝና በእሳቸው ትዕዛዝ ከሊኦንትየቭ ጋር ወደ ራሔታ ይላካል። ተልዕኮውን በተሳካ ሁኔታ ፈጽሞ ሲመለስም ዐፄ ምኒልክ “የሰለሞን ማኀተም”ን ሦስተኛ ደረጃ ኒሻን ሸለሙት።

 ከዚያም ከሩሲያ የጦር ሠራዊት ስንብት ጠይቆ ከለቀቀ በኋላ፣ ዐፄ ምኒልክ የመንገድና የተለያዩ ቴክኒክ ነክ ሥራዎች ኃላፊ አድርገው ይሾሙታል። እሱም ሥራውን በቅንነትና በትጋት በማከናወን በባለሥልጣናትም ሆነ በሕብረተሰቡ ዘንድ አክብሮትን ከማግኘቱም በላይ የፊታውራሪነት ማዕረግም ተሰጠው።ከዚያም ከወይዘሮ ተካበች ወልደፃድቅጋር ጋብቻ ፈጽመው፣ ሦስት ሴቶችናሁለት ወንዶች ልጆችን ወለዱ። ባቢቼቭ በዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት ምበመስራት ላይ እንደነበርና ከንጉሡም ጋር የቀረብ ግንኙነት እንደነበረው ይነገራል።

እንግዲህ የኢትዮጵያ አየር ኃይል መሥራችና በሶቪየት ሕብረት የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አንደኛ ፀሐፊ የነበረው ሚሀይል ባቢቼቭ፣ የዚህ ሩሲያዊና የኢትዮጵያዊቷ ተካበች ልጅ ነበር። ሚሀይል ወይም ሩሲያውያኖች እንደሚጠሩት ሚሻ የተወለደው በ1908 እ.ኤ.አ. ነበር። እሱም የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ካጠናቀቀ በኋላ በጦር ትምህርት ቤትውስጥ ገብቶ ትምህርቱን ቀጠለ።

ከዚያም ኢትዮጵያ አውሮፕላኖችን መግዛት ስትጀምር፣ በአውሮፕላንአብራሪዎች ማሰልጠኛ ገብቶ በ1930የመቶ አለቃ ሆኖ ተመረቀ። የጦር ትምህርቱንም በዚህ አላበቃም። በንጉሠ ነገሥቱ ትዕዛዝ ወደ ፈረንሳይሃገር ተልኮ በአየር ኃይል አካዳሚውስጥ ትምህርቱን ሲከታተል ከቆየበኋላ በክብር ተመርቆ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለስ በሻለቃነት ማዕረግ በመጀመሪያ የአውሮፕላን አብራሪዎች አሰልጣኝ በኋላ ደግሞ የማሰልጠኛ ትምህርትቤቱ አዛዥ ሆኖ አገልግሏል። የኢትዮጵያና ጣሊያን ጦርነት በተጀመረ ጊዜ ሻለቃ ባቢቼቭ የአገሪቷ የአየርኃይል አዛዥ ሆኖ የተሾመ ሲሆን፣ራሱ አውሮፕላን በማብረርም በጦርነቱ ውስጥ ተሳትፏል። በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ አየር ኃይል 19 ኋላቀር የሆኑ አውሮፕላኖች ብቻ የነበሩት በመሆኑ የኢጣሊያንን አየር ኃይል ለማቋቋም አልቻሉም። ባቢቼቭና ጓደኞቹ ግን አገራችውን ከጠላት ለመታደግ የተቻላቸውን ያደረጉ ሲሆን፣ ለፈፀሙት የጀግንነት ተግባርም ብዙ ኒሻኖችንና ሜዳሊያዎችን ተሸልመዋል። ከጦርነቱ በኋላ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአዲስ መልክ መቋቋም

“የኢትዮጵያና ጣሊያን ጦርነት በተጀመረ ጊዜ ሻለቃ ባቢቼቭ የአገሪቷ የአየር ኃይል አዛዥ ሆኖ የተሾመ ሲሆን፣ ራሱ አውሮፕላን በማብረርምበጦርነቱ ውስጥ ተሳትፏል”

ይጀምራል። አዳዲስ አውሮፕላኖች ይገዛሉ፤ተቋማትም ይጠናከራሉ። ከዚሁ ጎን ለጎንምየአገሪቷ የአየር መንገድ መቋቋም ይጀምራል። ባቢቼቭም በዐፄ ኃይለሥላሴ ትዕዛዝ የዚህበአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የአየር መንገድ ኃላፊ ሆኖ ይመደባል።

ባቢቼቭ ለአገሩ ለኢትዮጵያ አገልግሎትየሰጠው በወታደራዊ ዘርፍ ብቻ አልነበረም።የሩሲያ አብዮት በ1917 ሲቀጣጠል የተቋረጠውዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በ1943 እ.ኤ.አ.በኢትዮጵያና በሶቪዬት መካከል እንደገናሲጀመር፣ ዐፄ ኃይለሥላሴ ባቢቼቭን በሞስኮየኢትዮጵያ ኤምባሲ አንደኛ ጸሐፊ አድርገውልከውታል፤ ከ1946 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞየኤምባሲው ጉዳይ ፈፃሚ ሆኗል።

በዚሁ ሥልጣን ላይ እያለም በ1946 ሉድሚላኒስትሪንኮቫ ከተባለች ሩሲያዊት ጋር ተዋወቀ። እንደሚባለውም ፍቅራቸው የፀና ስለነበር በአጭር ጊዜ ውስጥ ጋብቻቸውን ፈጽመው የደስታ ሕይወታቸውን ቀጠሉ። ብዙም ሳይቆዩ ሚያዝያ 6 ቀን 1947 ዓ.ም. አሌክሳንደር የተባለውን የመጀመሪያ ልጃቸውን ወለዱ። እነኝህ ቀናትም በሁለቱ ግለሰቦች ሕይወት ውስጥ ልዩ ቦታ እንደነበራቸው ጥርጥር የለውም።

ነገር ግን፣ ይህ ደስታ ለረጅም ጊዜ አልቀጠለም። በጥር ወር 1948 እ.ኤ.አ. በቤተሰቡ ላይ ያልታሰበ መቅስፍት ይወርዳል፤ በሚሀይል ባቢቼቭ አንጎል ውስጥ ደም ይፈስና በሽተኛው በግራ በኩል ፓራላይዝድ ሲሆን፣ መናገርም ያቅተዋል። የሶቭዬት ሐኪሞች ባደረጉት ጥረት የሚሀይልን ሕይወት ለማዳን ቢችሉም፣ ቆሞ እንዲሄድና እንዲናገር ለማድረግ ግን አልቻሉም። በኢትዮጵያ የሚገኙት ዘመዶቹ ደግሞ ሚሀይልን ወደ ስዊድን ወስደው በታወቀው የነርቭ ሐኪም በፕሮፌሰር ክሮኔ ክሊኒክ ውስጥ እንዲታከም አድርገዋል።

የስዊድን ሐኪሞች ሚሀይል ቆሞ እንዲሄድና እንዲናገር አደረጉ። እሱም ህክምናውን ከጨረሰ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመለሰ። ነገር ግን በሕመሙ ምክንያት ከዚህ በኋላ ባቢቼቭ ወደ ዲፕሎማሲያዊ ሥራው ለመመለስ አልቻለም። እሱም ሞስኮ ትቷቸው የመጣውን ሚስቱን ሉድሚላንና ልጁን አሌክሳንደርን ሁለተኛ ሳያያቸው ታህሣሥ 23 ቀን 1964 እ.ኤ.አ. በተወለደ በ56 ዓመቱ አዲስ አበባ ውስጥ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።

 ይህ የኢትዮጵያን አየር ኃይልና አየር መንገድ በመመሥረት ከፍተኛ ሚና የተጫወተ ግለሰብ ሕይወት የተፈጸመው በዚህ ዓይነት አሳዛኝ ሁኔታ ነበር ማለት ይቻላል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ስለዚህ ጀግና ምንም የታወቀ ነገር አልነበረም ብንል ማጋነንን አይሆንም። ሚሀይል ባቪቼብ የተቀበረው በቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ውስጥ ሲሆን፣ ልጁ እንኳን መቃብሩን ሊያይ የቻለው ከዓመታት በኋላ በ2011 እ.ኤ.አ. ነው። ለዚህም የሩሲያ ቴሌቪዥንና በኢትዮጵያ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲና የሩሲያ የሳይንስና ባህል ማዕከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ መሆኑን ሳንጠቅስ አናልፍም።

አሌክሳንደር ባቢቼቭ ከቤተሰቡ ጋር የአባቱን መቃብር ለማየት በመጣ ጊዜ ልዩ ሥነ ሥርዓት ተዘጋጅቶና በርካታ ሰዎች ተጠርተው በመቃብሩ ላይ ፍትሃት ተደርጎለታል። ፍትሃቱንም ያደረጉት የቅድስት ሥላሴ ካቴድራል አለቃ አቡነ ጢሞቲዮስ ነበሩ። ከዚህም ሌላ አሌክሳንደርን የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ተቀብለው ያነጋገሩት ሲሆን፣ ከአየር መንገድ ባለሥልጣናትም ጋር ተገናኝቷል።

 ይህ አጭር ጽሑፍ እንደመነሻ ያገለግል እንደሆነ ነው እንጂ የዚህን ጀግና ሕይወት በዝርዝር የሚሸፍን አይደለም። ስለዚህም የኢትዮጵያ ጋዜጠኞችና ተመራማሪዎች ለዚህ ሰው ታሪክ ትኩረት እንዲሰጡት በማሳሰብ ይህቺን አጭር ጽሑፍ እንደመድማለን። ይህ ጽሑፍም የተዘጋጀው ልጁ አሌክሳንደር ስለ አባቱ የጻፈውን አጭር የሕይወት ታሪክ መሠረት በማድረግ ነው።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top