አድባራተ ጥበብ

መንግሥት፣ ቴያትር ቤቶችና የቴያትር ትምህርት ቤቶች

በዚህ በእኛ ዘመን የኢትዮጵያን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፌደራላዊ የመንግሥት ሥርዓት አወቃቀር አስተዳድራለሁ ብሎ ከሩብ ምዕተ ዓመት በፊት ሥልጣን ላይ የወጣው ኢሕአዴግ፣ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ ትውንና እይታዊ ጥበባት የሚቀርቡባቸውን ቴያትር ቤቶች በአግባቡ ከማሳነጽ ይልቅ፣ ለታላላቅ ስብሰባዎች የሚሆኑ አዳራሾችንና የሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየሞችን ሲያስገነባ ከርሟል። አንዳንድ የክልል መንግሥታትም እንዲሁ ያለበቂ ጥናትና ምርምር በተመሳሳይ ተግባር ላይ ተጠምደው ታይተዋል።

የዚህ መንግሥት መልካም ሥራዎች ከሆኑት አንዱ የዩኒቨርሲቲዎች መስፋፋት ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሀገሪቱ ብርቅዬ በነበረው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴያትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ይሰጥ የነበረው የቴያትር ትምህርት በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ተስፋፍቶ በመቀሌ፣ በወሎ፣ በወልቂጤ፣ በጎንደር፣ በጅማ፣ በአክሱም፣ በወልዲያ፣ በደብረማርቆስ፣ በአዲግራት፣ በአክሱምና በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ ይገኛል።

 በቅርቡ የትምህርት ክፍሉን ለመክፈት የሚታትሩ ሌሎች በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች መኖራቸውም ይታወቃል። የትምህርት ተቋማቱ መበራከት “እሰየው፣ ይበል” የሚያስብል ቢሆንም፣ ከላይ የተጠቀሱት ዩኒቨርሲቲዎች የቴያትር ጥበባት ትምህርት ቤት ምሩቃን እስከመቼ ድረስ ነው የቀበሌና የወረዳ የባህል ኤክስፐርት፣ የኮሙዩኒኬሽን ባለሙያ፣ ጋዜጠኛ፣ የህዝብ ግኝኙነት ባለሙያ ሲከፋም ስራ አጥ እየሆኑ የሚቆዩት!? እነዚህን ሥራዎች ለመስራትስ ለምን የቴያትር ጥበባትን ይማራሉ? የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን፣ የቋንቋና ፎክሎር ትምህርቶችን ቢማሩ አይሻልም ወይ!? … የሚል ጥያቄ ማንሳት እወዳለሁ።

 እስከማውቀው ድረስ የቴያትር ጥበባት ትምህርትን ለመቅሰም የሚመጣው ተማሪ በአብዛኛው የቴያትር ደራሲ፣ አዘጋጅ፣ ተዋናይ፣ ሃያሲ … የመሆን ጥልቅ ፍላጎት ሰንቆ ነው። ከዩኒቨርሲቲዎቹ “ብቁ” ሆኖ ተመርቆ ሲወጣ ግን የሚሰራው ሥራ እነዚህን ሳይሆን፣ እላይ የጠቀስኳቸውንና ለእለት ጉርሱ የሚሆኑትን ሥራዎች ነው። ይሄ ደግሞ መክሸፍ ነው – የትምህርት ቤቶቹም የምሩቃኑም! በርካታ ሥራዎች ሊሰሩ የሚችሉ የቴያትር ምሩቃን በየጥጋጥጉ “ለመኖር” በሚባል ፈሊጥ ከመክሊቶቻቸው ተራርቀዋል። በዚህ ደግሞ ከጎልማሳው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እስከ አዳዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች የቴያትር ትምህርት ክፍሎች ድረስ እንደከሸፉ ይሰማኛል።

 የከሸፉባቸው ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም፣ አንኳር አንኳር የምላቸውን እነሆ!

 ሀ. የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የቴያትር ጥበባት ትምህርት ክፍሎችን ሲያቋቁሙ፣ መንግሥትም ዩኒቨርሲቲዎቹ የሚያስመርቋቸው ባለሙያዎች የቀሰሙትን ዕውቀትና ክሂል የሚተገብሩባቸው በቂ የኢሕአዴግ ዘመን ቴያትር ቤቶች አለመኖራቸው ዋናው ነው። በሀገሪቱ ውስጥ በሥራ ላይ ያሉት ቴያትር ቤቶች አራት ሲሆኑ ባለሙያዎችን የሚያስመርቁ ዩኒቨርሲቲዎች ግን በርካታ ናቸው።

 ለ. የቴያትር ትምህርት ቤቶቹ በአብዛኛው ለቴያትር ትምህርት ብቁ ባልሆነ አደረጃጀት (ብቁ ባልሆኑ መምህራን፣ ቁሳቁሶች፣ አልባሳት፣ አዳራሾች…) መንቀሳቀሳቸው፣ የትምህርት ሥርዓታቸው ለ10 እና ለ15 ዓመታት ካለመሻሻሉ በላይ ቀኖናዊነት የሚጫናቸው መሆናቸው፣ እንደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተከታታይነት ያላቸው ምሁራዊ ውይይቶች (Intellectual Discourse) እና ሂሶች በወጉ የሚካሄድባቸው አለመሆናቸው።

“በአሁኑ ወቅት በሀገራችንበርካታ የቴሌቪዥንጣቢያዎች እየተቋቋሙበመሆኑ፣ የመድረክ ቴያትርንየሚሰሩ ብቻ ሳይሆን፣ለቴሌቪዥን ጣቢያዎቹየተለያዩ የጥበብ ሥራዎችንየሚያዘጋጁ፣ የሚተውኑ፣የሚፅፉ፣ የሚሂሱባለሙያዎችን ለማፍራትመሮጥ አለባቸው”

ሐ. የትምህርት ክፍሎቹ መንግሥት ቴያትርን ከበዓል ማድመቂያነትና ከፕሮፖጋንዳ መሣሪያነት ባሻገር ትኩረት እንዲሰጠው ለማድረግ ተቋማዊ ጫና መፍጠር አለመቻላቸው ዋና ዋናዎቹ ናቸው።

 ከላይ የዘረዘርኳችው ችግሮች አንዳንዶቹ በአዳዲሶቹ ዩኒቨርሲቲዎች የማይታዩ፣ አንዳንዶቹ እንደየሁኔታው በተለያየ መልኩ የምናገኛቸው ናቸው። ሆኖም ሁለት የሚያግባቡን ነገሮች አሉ።

 የትምህርት ተቋማቱ ሙያቸውን አስመልክቶ ተፅዕኖ መፍጠር፣ መንግሥትን መምራት፣ አቅጣጫዎችን ማሳየት፣ ሙያው በትኩረት ይተገበርበት ዘንድ ጉትጎታ ማድረግ፣ የቴያትር ፖሊሲ እንዲኖር፣ አዳዲስ ቴያትር ቤቶች እንዲከፈቱ ያለማሳለስ ጥያቄ ማቅረብ አለባቸው።

 የቴያትር ትምህርትን ያለብቁ መምህር፣ ያለ በቂና ምቹ አዳራሽ፣ ያለ አልባሳት፣ ያለመብራት፣ ያለ ብዙ ተጓዳኝ ነገሮች የሚያስተምሩበት ሁኔታ ሊቆም ይገባል። ሥርዓተ ትምህርታቸውንም በየጊዜው የመፈተሽና የመገምገም ሥራዎች ሊሰሩ ይገባል።

 በተለይ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በርካታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እየተቋቋሙ በመሆኑ፣ የመድረክ ቴያትርን የሚሰሩ ብቻ ሳይሆን፣ ለቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ የተለያዩ የጥበብ ሥራዎችን የሚያዘጋጁ፣ የሚተውኑ፣ የሚፅፉ፣ የሚሂሱ ባለሙያዎችን ለማፍራት መሮጥ አለባቸው።

ሥርዓተ ትምህርቱን ከዘልማዳዊው አካሄድ በመነጠል፣ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎችን መቆጣጠር የሚያስችሉ ትምህርቶችን ከብቁ ባለሙያ፣ መሳሪያዎች እና አደረጃጀቶች ጋር ማምጣት እንዳለባቸው ይሰማኛል።

 የቴያትር ትምህርት ቤቶች ሆይ ራሳችሁን ከመለወጥ በቀር አማራጭ የላችሁም! ስለሙያው ሳስብ ከእናንተ በላይ ተቆርቋሪ፣ ከእናንተ በላይ አለሁ ማለት ያለበት አካል ያለ አይመስለኝም። የአሳው ጭንቅላት እናንተ ናችሁ። በርቱ- ተበራቱ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top