የታዛ ድምፆች

ጥበብና ሥልጣኔ

የኢትዮጵያውያን የሕንፃ ጥበብ አሻራ፡

አ-ኣለፍ  መጀመሪያ

ኣለፍ -ኣ- ወይም አልፋ የመጀመሪያው ፊደል ነው። የፊደል ተራ በጥንታውያን ልሳናት ሲገለጽ በግእዝ -አ- በ- … በዕብራይስጥ አሌፍ፣ ቤት፣ ጋሜል… በዓረብኛ አሊፍ፣ ባ፣… በግሪክ አልፋ፣ ቢታ፣ ጋማ… በላቲን(ኖ) ኤ፣ ቢ፣ … የሚል ነው። በሁሉም ውስጥ “አ” ድምጽ መጀመሪያ ላይ ይገኛል:: በቅርጸ ፊደል ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ድምጹን ወክሎ ከተቀመጠው ፊደል የሚመሳሰል ፊደል ያለው በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። የዚህ ፊደል ትርጉሙ (የ) ቀደመ፣ ቀዳሚ (የ)ፊት ማለት ሲሆን በጥንታውያን ቋንቋዎች የፈጣሪን ቀዳሚነት ለመግለጽ ፊተኛው የሚል ትርጉም ያለው ስም (ስመ አምላክ) በመሆንም አገልግሏል። እኔ የመጀመሪያም የመጨረሻም “አልፋ” ና “ኦሜጋ” ነኝ እንዳለው። ይኸውም ቀዳማዊ ህልውናን የሚወክል “የህልውና” መግለጫ መሆኑን የሚያጠይቅ ነው። በግሪኩ ሐዲስ ኪዳን “አልፋ” ና “ኦሜጋ” የሚለው በግእዙ “አልፋ” ወ “ዖ” (ራዕ 1፡8) የተገኘው ከኦሪቱ የዕብራውያን ትርጉም አኽያ [ኣ]ሸር አኽያ“ (ዘፀ 3፡14) ያለና የነበረ ወደፊትም የሚኖር” ከሚለው ስለሆነ የመጀመሪያው ፊደል ቀዳማዊ የአምላክ ህልውናን ለማስተማር ጥቅም ላይ መዋሉ ታውቋል።

ሁለተኛው ፊደል “በ” ስሙ ቤት ትርጉሙ ማደሪያ ማለት ነው። በ-ቤት የሚለው ቃል የሚወክለው ማደሪያ ለሚያስፈልገው የሰው ልጅ መኖሪያነት ያገለገሉ እንደ ሕንፃ፣ ዋሻ፣ ፍልፍል መሬትና ዳስን (ድንኳንን) ሲሆን የቅርጸ ፊደሉ ተምሳሌት ማደሪያን ይወክላል። የግእዝ ቋንቋ ሁለተኛው ፊደል “ቤት” ነው። ምስጢሩን እና ሐተታውን ለጊዜው እንተወውና የፊደሉ መገኘት እንዴት እንደሆነ እንናገር። ቤት ቃሉ “ቤተ – አደረ” ከሚለው ዘር የተገኝ ነው። በሌላ በኩል ካለው የቋንቋ ፈጠራ ልምድ አንፃር መጀመሪያ “ቤት” ማደሪያ የሚለው ነባር ተገኝቶ፣ “ቤተ” አደረ የሚለው ዘር ከዚያ እንደወጣ የሚናገርም ይመስላል። ቃሉን በግእዝ፣ በአማርኛ፣ በዕብራይስጥ ቋንቋዎች በጥሬው ይጠቀሙበታል።

 ከጥንታዊው ሰው አኗኗር ታሪክ አንፃር የቤት ቅርጽ እንደ “በ” የተደፋ ኩባያ መስሎ የተሠራ ሲሆን በጥንቱ የግብፃውያን “ፒክቶግራፊ” እና የደቡብ ሴማዊ ቅርጸ ፊደል “በ” የሰውን መኖሪያ መስሎ የተቀረጸ ማደሪያውን የሚያመለክት የማደሪያ መጠሪያ ፊደል ነው። ስለዚህ የመጀመሪያው ሕንፃ ቤት ቅርጽ የ“በ” ፊደል ዓይነት ነው። በመሆኑም “ቤት” ማደሪያ ለሚለው ስምና ቤተ አደረ ለሚለው ግሥ መነሻ ብቻ ሳይሆን “በ” ለተባለው ቅርጸ ፊደልም መነሻ ነው። “በ” የተባለው ቅርጸ ፊደል የመጀመሪያው ቤት ቅርጽ በመሆኑም ይኽንኑ ቅርጽ አሁንም ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ተጓዦች፣ ጎብኝዎች፣ የመስክ ተመራማሪዎችና አርብቶ አደሮች ይጠቀሙበታል። እንደ ግእዝ፣ አማርኛና ትግርኛ ያሉ ቋንቋዎችም ይኽንኑ ፊደል ጥንታዊ ቅርጹን፣ ድምጹንና ትርጉሙን እንደጠበቁ ይገኛሉ።

በሀገራችን ሊቃውንት ትርጓሜ መሠረት በኦሪት አዳም ይመገበው የነበረውን ምግቡን፣ ከውድቀት በፊት የክብር ልብሱ ከውድቀት በኋላ የቁርበት (የቅጠል) ልብሱ ነገር ተጽፏል። ስለአኗኗሩ ግን በጥንታውያን ዋሻዎችና አለቶች ላይ ከተገኙ አሻራዎች ውጭ ሰፊ መረጃዎች የሉንም። ፈጣሪው እግዚአብሔር ቤት ሠሪ ዲዛይነር ነው። የሙሴን ቤተ መቅደስ ወርዱን፣ ቁመቱን፣ የሰሎሞንን ቤተ መቅደስ ዲዛይን የተናገረው ራሱ እግዚአብሔር ነው። አዳም ቤት የሠራው ከገነት ከወጣ በኋላ ሲሆን የቤቱም ቅርጽ “በ” ነው። ትርጉሙም ቤት ነው። የቅርጹም ምሳሌ የአዳም የትህትናው መግለጫ ነው። ቅርጽ -በ- የቆመ ዘንግ አንገቱን ዝቅ አድርጎ ከወገቡ ጀምሮ በቆመበት በ-ቤት ማደሪያ መጠን እኩሌታ ተደፍቶ መሬት የሚነካ ሰው ትመስላለች። ይኽም የአዳምን በበደሉ ፍጹም መጸጸት፤ በቆመበት መጠን (በስሕተቱ ልክ) ተደፍቶ/ተጎንብሶ ንሥሃ ለመግባቱ ምሳሌ ሲሆን ፈጣሪም የጸጸቱን ፍጹምነት አይቶ ማደሪያው የሰውን ሥጋ አድርጎና ተዋሕዶ አዳምን ወደቀደመ ክብሩ መለሰው ይላሉ።

ከመንፈሳዊው ትንታኔ ባሻገር በሥነ ጥበብ ታሪክ ዘገባ የጥንት አፍሪካውያን በቤት ጥበብ ቀዳሚ መሆናቸው በሰፊው ይነገራል። ኖኅ ስማቸው ሴም፣ ካም፣ እና ያፌት የሚባሉ ልጆች ነበሩት። የአፍሪካውያን አባት ኩሽ የካም ልጅ ሲሆን ናምሩድን ወለደ። እርሱም በምድር ላይ ኃያል ሆነ። … የግዛቱም መጀመሪያ በሰናዖር ሀገር ባቢሎን፣ ኦሬክ፣ አርካድ፣ ካልኔ ናቸው (ዘፍ 10፡ 8-11)። በዓለም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከድንጋይ፣ ከጡብና ከጭቃ ከተማ እንደሠራ የተጻፈለት ኃያል ገዥ የምሥራቅ አፍሪቃው ንጉሥ ናምሩድ ነው። ከምሥራቅም የተነሡት የኩሽ ልጅ የናምሩድ ሰዎች ከሰናዖር በኋላ በባቢሎን ትልቅ ከተማ ሠርተዋል። ለመሆኑ ምሥራቅ የተባለችው ሀገራቸው ማን ትሆን? ቅድመ ናምሩድ የነበሩት ጠበብት ነገሥታት ጥንት በአባይ ሸለቆ ከመነሻው እስከ መድረሻው የግብጻውያንና የተከታታይ

“ከእነዚህ ሥልጣኔ አሻራዎች እስከ አሁን ከፍ ብሎ የሚታየው ብቸኛ ምስክር ከሰሃራ በታች ሳይፈርስና መልኩል ሳይለውጥ በጽናት ቆሞ የሚገኘው የየሃ ቤተ መቅደስ ቅሪት/ አሻራ አንዱ ነው። የየሃ ቤተ መቅደስ ቅሪት ከአክሱም ከተማ በአድዋ በኩል 56 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኝ ጥንታዊ የሕንፃ ቅርስ ነው”

የአባይ ወንዝ ሥልጣኔ መሥራቾች ሲሆኑ እርሱም ከአባቶቹ ከአፍሪቃውያን በተማረው ጥበብ ባቢሎንንና አርካድን መሥርቷል። አባቶቹ የቅድመ ሳባ አፍሪካዊ ሥልጣኔ መሥራች ሲባሉ እርሱ በሜሶፖታምያ የተነሡት የደኀርት የአሶር፣ የፋርስ፣ የሱመር፣ የአርካድና መሰል ሥልጣኔዎች ሁሉ መነሻና መሥራች ሆነ። በዐባይ ሸለቆ ሥልጣኔ በቀይ ባሕርና በዐባይ ወንዝ መካከል የቅድመ ዳዐማት፣ የየሃ፣ የአክሱምና መሰል ሥልጣኔዎች ሲገኙ ለቅድመ አክሱም ሥልጣኔ መነሻም ናቸው። ከእነዚህ ሥልጣኔ አሻራዎች እስከ አሁን ከፍ ብሎ የሚታየው ብቸኛ ምስክር ከሰሃራ በታች ሳይፈርስና መልኩን ሳይለውጥ በጽናት ቆሞ የሚገኘው የየሃ ቤተ መቅደስ ቅሪት/አሻራ አንዱ ነው። የየሃ ቤተ መቅደስ ቅሪት ከአክሱም ከተማ በአድዋ በኩል 56 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኝ ጥንታዊ የሕንፃ ቅርስ ነው። የሃ ለአሁኗ ኢትዮጵያ የመጀመሪያ ሥልጣኔ ነውን? ወይስ የሌሎች የቅድመ የሃ ሥልጣኔዎች ተከታይ? ወይስ በሌላ ዓለም የተፈጠረ ሥልጣኔ ቅጅ? የሚሉትና መሰል ጥያቄዎች ገና ብዙ ሥራ የሚጠይቁ ጉዳዮች ናቸው። ይሁን እንጅ የሃ በታሪካዊ የአርኬዎሎጅ ጥናት ቅደም ተከተል ውስጥ በዓለም ደረጃ ከሚገኙ ታላላቅ የብሮንዝ ዘመን ሥልጣኔዎች የሚመደብ ሲሆን በምሥራቅ አፍሪካ እስከአሁን ተወዳዳሪ አልተገኘለትም። አሁን ገዝፎ ከሚታየው የየሃ ሕንፃ ጥበብና ካለበት አካባቢ በመነሣት በቅርብ ርቀት በርከት ያሉ የቅድመ የሃ፣ የየሃና ድኅረ የሃ የሥልጣኔ፣ የመንግሥት ሥርዓትና የሕዝብን አኗኗር የሚመሰክሩ ርስ በርስ ተያያዥነት ያላቸው መካነ ቅርሶች እንዳሉ የሚታወቅ ቢሆንም አሁን በቁፈራ የተገኙት በዚያው በየሃ አካባቢና አለፍ አለፍ ብሎ እስከ ውቅሮ አካባቢ የሚገኙት እንደ ምሳሌ ይወሰዳሉ።

የየሃ ሕንፃ ፍራሽ አሁን ባለው የዘርፉ ባለሙያዎች ስምምነት ከክርስቶስ ልደት ከ9ኛው እስከ 8ኛው መቶ ዓመታት በፊት እንደተሠራ ሲታሰብ የተሠራበት አገልግሎትም ለቤተ መቅደስ፣ ለአምልኮት እንደሆነ ይነገራል። ሕንፃው ወለሉ 14 (አሥራ አራት) ሜትር በ18 (አሥራ ስምንት) ሜትር ሲሆን (252 ካሬ ሜትር) ነው። ወደ ላይ ከፍታው 14 (አሥራ አራት) ሜትር ሲሆን ከአንደኛው የወለሉ ርዝመት ጋር በተመሳሳይ ስፍር የተለካ፤ በጥንቃቄና አስደናቂ በሆነ አቻነት የተቀረጹ ድንጋዮች የተገነባ ሕንፃ ነው። አንዳንዶቹ ድንጋዮች ርዝመታቸው እስከ ሦስት ሜትር የሚደርስ መሆኑን በጥሞና ለሚመለከት ያንን የሚያህል ድንጋይ እኩል በሆነና በተመጣጠነ መስመር መጠረቡ ብቻ ሳይሆን እነዚህን ፍጹም ተመጣጣኝ በሆነ ውበት የተቀረጹ ረጃጅም ድንጋዮች ታሳቢ በማድረግ የተሠራውን ግንባታ ሥልትና የገንቢዎቹንም መናበብ አብሮ ለማድነቅና ለመታዘብ ይቻላል።

እነዚህ ድንጋዮች በሚደራረቡበት ጊዜ ጠቢባኑ ገንቢዎች በዋናነት የተጠቀሙት የግንባታ ጥበብ የተመጣጠነ ዝብጠት ከመሬት 90 ዲግሪ ቀጥ አድርጎ በመገንባትና ዝመት እንዳይኖርና ግንቡ እንዲጸና ማድረግን ነው። ይሁን እንጅ ድርብርቡንም ሆነ የጎንዮሽ ድርደራውን ለማያያዣ ጥቅም ላይ የዋለው ንጥረ ነገር ምንድን ነው ብሎ ማሰብም ተገቢ ነው። በእርግጥም በሚያስደንቅ ሁኔታ አሥራ አራት ሜትር ከፍታ ያለው፣ በተመሳሳይና በባለሁለት መልከኛ ገጽ በጥንድነት የተሠራው ግንብ በውጭም ሆነ በውስጥ የላይኛው ገጹ ለማያያዣ የዋለውን ቁስ ምንነት በቀላሉ አይነግረንም። በዚህ ቦታ ከተሰዓቱ ቅዱሳን አንዱ አባ አፍጼ ቦታው እስከሚደርሱ ድረስ የብሉይ ኪዳን መሥዋዕት ተሰውቷል። በረጃጅምና በጥንቃቄ በተጠረቡ ማዕዘናቸው ፍጹም የተስተካከለ፣ መጠናቸው አቻ የሆነ፣ ርስ በርሳቸው በአስደሳች መስመር፣ ሥርዓትና፣ ተናባቢ ንድፎች በተገጣጠሙ መልከኛ ድንጋዮች የተገነባው ሕንጻ በአካበቢው የተደረጉ እጅግ አሰቃቂና ጅምላ ጥፋት ያካሄዱ ከዮዲት ጉዲት ጀምሮ፣ የግራኝንና የቱርክን፣ የጣሊያንን የከባድ መሣሪያ ጦርነቶች ሁሉ በተአምር አልፎ አሁን ድረስ የሦስት ሽ ዘመን የኢትዮጵያውያን የሕንጻ ሥልጣኔ ይመሰክራል። ከሁሉም ደግሞ በቅድመ ክርስትና የተሠራውን ሕንፃ ቅሪት ሳያፈርሱ፣ ነባሩን ሳያጠፉና ሳይደመስሱ ወይም ሳይለውጡ ከአምስተኛው/ስድስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የክርስትናን እምነት ሲያካሂዱ የነበሩት ኦርቶዶክሳውያን ካህናትና መነኰሳት በቅጥራቸው ጠብቀው ማቆየታቸው ያስደንቃል።

Ruins of the Yeha temple, Temple of the Moon in Yeha, Ethiopia. Yeha temple is one of the oldest standing in Ethiopia.

አሁን ባለውና በአካባቢው ተጠብቆ በቆየው የቃልና የጽሑፍ ትውፊት በሚለይ ሁኔታ የሚነገረው የዘመናውያኑ ተመራማሪዎች ስምምነት መሠረት ይህ የየሃ ሕንፃ “አልማቃሃ” ለተባለ የደቡብ አረብ (የአሁኑ የመን) ጣዖት የተገነባ ቤተ መቅደስ ነው የሚል ነው። ይህን ለማለት በቦታው ላይ የተፃፈ ጽሑፍ ወይም የሥዕል መግለጫ ኖሮ ሳይሆን በዚህ ጣዖት ስም በሌላ የዓለማችን ክፍል ለምሳሌ “በስርዋሕ” እና “አዋም” በተባሉ የማሪብ ቤተ መቅደሶች ከተገኘው ጋር በማመሳሰል የተሰጠ መላምት እንደሆነ ይነገራል። ይህ የምርምር መላምት ዘዴ/ስልት ዓለም አቀፍ ከመሆኑም ባሻገር በሥነ ጥበብና ኪነጥበብ ቅርሶች ጥልቅ ጥናትና ምርምር ውስጥ አንድ የታወቀ የምርምር ሂደት ነው። ሆኖም ከአካባቢው ነባራዊ ሁኔታና ካለው ሕዝባዊ ትውፊት ጋር በጣም የተራራቀ መላምት ሲሆን ደግሞ በደንብ ማጥናትና የመላምት ዛላዎችን አስፍቶ መንደፍ ይጠይቃል። ለጊዜው ብቻ ሳይሆን ከረጅም ዘመን ጀምሮ እንደሚታመነው ይህ ቤተ መቅደስ “መስዋእተ ኦሪት” የተሰዋበት እንደሆነ በአካባቢው ሲነገር ከመኖር በላይ በአጠገቡ በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ማብቂያና በስድስተኛው መጀመሪያ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ወደ ሀገራችን ከመጡት መነኰሳት አንዱና በየዓመቱ ግንቦት 29 ቀን መታሰቢያቸው የሚከበረው ጻድቅ አቡነ አፍጼ የመሠረቱት ገዳምና መዛግብተ ቤተ ክርስቲያን ከፃድቁ ገድል ጭምር ይህንኑ ታሪክ ይናገራሉ። የእንስሳት መስዋዕት ማቅረብ እንደሆነ በኦሪቱም የታወቀ ሥርዓት ነው፤ በዚህ ዓይነት የቤተ መቅደስ ውስጣዊ መዋቅርም በኦሪት ሥርዓት ውስጥ የደረጀ ታሪክ አለ። ስለዚህ የምርምር ዳራውን አስፍቶ ማየት ለሀገራዊ ምሁራን የሚጠቅም ይመስላል።

የየሃ ሕንፃ ብቻውን የቆመ አይደለም። በአካባቢው ሌሎች ተመሳሳይ የሥነ ጥበብ ይዞታ ያላቸው ልዩ ልዩ አገልግሎት የሚሰጡ ሕንፃዎች እንደነበሩ አሁንም የአርኬዎሎጅ ምርምር ይጠቁማል። እነዚህ መጠነ ሰፊ ፍራሾች ከነባሩ አቻ ሥልጣኔ ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ አጠቃላይ ገጽታቸው ምን ይመስላል የሚለው እጅግ ሰፊ ጥናት፣ ትንታኔና ሰፊ ትኩረት ይሻል። ለምሳሌ በዚሁ አካባቢ ካሉት መካነ ቅርሶች ውስጥ 46 በ46 ሜትር (2116 ካሬ ሜትር) ስፋት ያለውና 4.5 ሜትር ከፍ ብሎ የተሠራ መድረክ ያለውቤተ መንግሥት ይገኛል። በዚሁ ቤተ መቅደስ አጠገብ የተሠራና አሁን ፍራሹ የሚታየው ቤተ መንግሥት ዕድሜም ከዚሁ ቤተ መቅደስ ጋር አንድ ሲሆን የተሠራበት የሕንፃ ጥበብ ተመሳሳይ ነው።

ከዚሁ ብዙ ሳይርቅ ደግሞ አንድ የመቃብር ቦታ ይገኛል። ከዚህ የምንረዳው አሁን ትኩረት ተሰጥቶት የተገኘው ፍራሽን እንደጠቋሚ ተጠቅሞ ሰፊ ምርምር ቢደረግ የሃ የአንድ ከፍተኛ ሥልጣኔ ርዕሰ ከተማ፣ የመንግሥትና ሥርዓተ ማኅበር ማዕከል፣ የሥርዓተ አምልኮት፣ የመንግሥት አስተዳደርና የሕዝብ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ መናኸሪያ እንደነበር ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ ከሌሎች አብረው ከተገኙ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች ጋር በጋራ ሲተነተን የየሃን ሥልጣኔና የጥበብ አሻራዎቹን ምስጢር እጅግ የሚያጓጓ ያደርገዋል።

በየሃ በርከት ያሉ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶች ተገኝተዋል። አሁን እየተነጋገርን ያለው ስለሕንፃው ነው። ከሥነ ጽሑፍና ሥነ ጽሕፈት አሻራው በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ተንቀሳቃሽ ቅርሶችም ይገኛሉ። እውነተኛ ሀገራውያን የጥንታውያን ቅርሶች ምሁራን በዚህ ዘርፍ ቢሰማሩ እድሜያቸውን ሁሉ የማይጨርሱትን ምሥጢር ለዓለም ማስተላለፍ በቻሉ ነበር። ወደ ሀገራቸው ሄድ መጣ እያሉ ያጠኑት የምዕራቡ ዓለም ምሁራን ካስነበቡንና በየሃ አቡነ አፍጼ ገዳም አነስተኛ ሙዚየም በካህናቱ ጥንቃቄ ተጠብቀው ከተቀመጡት የድንጋይ ላይ ጽሑፎች፣ ልዩ ልዩ ቁሳቁሶች አንፃር የሃ አሁን ከምናወራለት ሀሳብ በላይ ጥልቅ እንደሆነ ነው። ሁለት ምሳሌዎችን ላቅርብ። የሥነ ጽሑፉ ዓይነት አንደኛ አሁን ከምንጠቀምበት ቅርጸ ፊደል ቀደም ብሎ፣ አሁን ለምንጠቀምበት ሥነ ጽሕፈት መሠረት የሆነ ቅርጸ ፊደል በየስባሪ ድንጋዮቹ ተቀርጾ እናገኛለን። ለማንበብ ስንሞክር ፊደሉ (አበገደው/አልፋቤቱ) በሁለት ጥንታውያን ቋንቋዎች አገልግሎት ውሎ እናገኘዋለን። ከእነዚህ አንዱ ግእዝ ነው። የሥነ ጽሑፎቹ ሥርዓተ ቋንቋ፣ የመልእክት ይዘትና የሚሰጡት አገልግሎት ደግሞ ለየብቻው የሚተነተን ነው። ሁለተኛው ምሳሌ የተገኙት ልዩ ልዩ የቤትና የአምልኮት ቁሳቁሶች ናቸው።

>
በይሃ የተገኙ የቤት ቁሳቁሶች እና ድንጋይ ላይ የተቀረፁ ጥንታዊ ጽሑፎች

 እነዚህ የወቅቱን አስተሳሰብ፣ የኑሮ ሁኔታ፣ የገበያና የማኅበራዊ ትሥሥር፣ የጠቢባኑን የዕውቀት ሽግግርና ማንነት የኪነ ጥበብና የዕደ ጥበብ ምርት ሂደት፣ የቁሳዊ ንጥረ ነገሮች ወይም የቅድመ ምርት ግብዓቶች አጠቃቀም፣ የውጭ ሀገር ግንኙነት የሚጠቁሙ ቅርሶች ናቸው። በሕንፃው ላይም ሆነ ከየቦታው ተለቃቅመው በተቀመጡት ቅርሶች በዋናው ሕንፃ ላይ ካሉት ቅርሶች መነሻነት የአምልኮቱን አፈጻጸም፣ የመሥዋዕቱን ድርጊት፣ ለመስዋዕት የዋለውን መባና ቁርባን፣ የሥርዓተ አምልኮቱን አፈጻጸም፣ የደም አቀራረብና የድኅረ መስዋዕት ሁናቴ፣ የምስዋዑ አቀማመጥና የዑደታቱ ማዕከል፣ በሙሉ ለመገመት የሚያስችል ቅርስ ነው። በአጠቃላይ የየሃ የጥበብ አሻራ ለብቻውም ሆነ አብረውት ከተገኙት ተያያዥ ቅርሶች አንፃር እጅግ ብዙ ሊያመራምር የሚችል ድንቅ፣ ረቂቅ፣ ምጡቅ ነው። የዚህን ቅርስ ይዞታ እስከ አሁን አስከብረው፣ ነባር ትውፊቱን ጠብቀው ያቆዩ የቦታው ሊቃውንት፣ ካህናት፣ መነኰሳትና ሕዝቡ ሊመሰገን የሚገባው ነው። የዚህ ታሪክ መጠበቅ ብቻ ሳይሆን በአግባቡ ተጠንቶ የሀገርን ገጽታ ለመገንባት፣ የቱሪስት መስህብ ለመሆንና በአካባቢውም ሆነ በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች ላሉ የዕውቀት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማት ልዩ የመስክ ምርምር ማዕከል ማድረጉ ደግሞ የሚመለከተው አካል ድርሻ ነው።

ቅርሶችን ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብ፣ ለማጥናትና ለማስተዋወቅ ጥቅም ላይ የሚውሉና እየዋሉ ያሉ በርካታ መንገዶች ሲኖሩ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ከዩኔስኮ (UNESCO) ጋርና ከመሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የሚደረጉ ጥረቶች ናቸው። የሃ እስካሁን በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንና በዓለም አቀፍ ምሁራን ከመተዋወቁና ከመጠናቱ ባሻገር የተቀናጀ የቅርስ ጥበቃ፣ እንክብካቤ፣ ማስተዋወቅና ድጋፍ የሚጠይቅ በዙሪያው ያሉ ቅርሶችን እስካሁን ጠብቀው ላቆዩት ነዋሪዎችም ድጋፍ ማድረግን የሚጠይቅ መካነ ቅርስ ነው።

የየሃንና ወደፊት የምናያቸውን የአክሱምና አካባቢው ኪነ ጥበባዊ ሐተታዎች በ1898 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ በዘመናዊ መንገድ ማጥናት የጀመሩት የጀርመን ተመራማሪዎች (የደች-አክሱም ስምሪት) ጥናት፣ የአኖ ሊትማንና የጥናት ቡድኑ፣ በኋላም በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ የቀጠሉት ምርምሮች ናቸው። በዚህም ስማቸውን ያልጠቀስናቸው እንዳሉ ልብ በማለት ከታወቁት ውስጥ ጣሊያናዊው ፕሮፌሰር ፋቶቢችና የሳቸው ቡድን፣ እንግሊዛዊው ፕሮፌሰር ዴቪድ ፊሊፕሰንና የሳቸው ጥናት ቡድን፣ የፈረንሳይ ተመራማሪ ቡድን እና የአንጀሊኒ ምልከታ፣ እንዲሁም ሞንሮሂ ግንባር ቀደሞቹ ናቸው። በውጭ ተመራማሪዎች ላይ ብቻ ተንጠልጥለን የቆየነውን ያህል በአሁኑ ዘመን በተለይ በመቀሌና በአክሱም ዩኒቨርሲቲዎች የሚደረጉት ጥረቶች ሊደገፉና ሊበረታቱ ይገባል። የሥነ ጥበባዊ ታሪክን የምርምር መንገድ በመከተልና ሀገራዊ ፋይዳውን በመቃኘት ምርምሮቹ ቢካሄዱና ትንተናዎቹ በራሳችን ባለሙያዎች እንዲሰጡ ዕድሉ ቢመቻች ድጋፍም ቢደረግ የበለጠ ውጤት ይገኛል። በተለይም የኢትዮጵያውያን የሥነ ጥበብ ቅርስ ምርምር ተመሰሳይ ከሆኑ የውጭ ሀገር ታሪኮች (ያውም ደቡብ አረቢያ (የመንን) ያማከለውን የአንድ አቅጣጫ ምልከታ) በመሻገር የውጩንም ከሌላው የአፍሪካ ሥልጣኔ ጋር፣ በተለይም ሀገራዊ ከሆነውና ካልተቋረጠው ሥልጣኔ ጋር የሚገናኝበትን የዕውቀትና የንድፈ ሐሳብ ተያያዥነት ማጥናት ያስፈልጋል። ከዚህም ጎን ለጎን ጥንታውያን የሕንፃና መሰል ጥበቦችን ከሀገራችን ትውፊትና የዕውቀት ውርስ እንዴት ማገናኘት እንዳለብን ማጥናቱ ለሀገራችን ዘላቂ ልማትና የታሪክ ምርምር፣ ለቱሪዝም መስፋፋትና የማይናወጥ ሥር ላለው አፍሪካዊ ማንነታችን ግንባታ እገዛ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top