ዘባሪቆም

የፍልስፍና መንገድ

አልፍረድ ኖርዝ ዋይትሄድ የተባለ ሰው “ፍልስፍና በነገሮች ወይም በሁኔታዎች በመደነቅ ነው የሚጀምረው” ይላል። እንደ እርሱ አባባል ከሆነ ይሄ በነገሮች ላይ የሚኖርን መደነቅ በፍልስፍና መንገድ ተጉዘህ ከመረመርከውና ካሰብከውም በኋላ የሚቀጥልና የበለጠ ጥልቀት የሚይዝ ነው። ስለዚህ፣ ፍልስፍና ማለት በነገሮችና በሁኔታዎች መደነቅ ማለት ሲሆን፣ በፍልስፍና መንገድ መጓዝ ማለት ደግሞ፣ ከአንድ መደነቅ ወደ ሌላ ጥልቅ መደነቅ እየተናጠሩ፣ ከአንድ ድንቅ የተፈጥሮ ሚስጥር መገለጥ ወደ ሌላ የመገለጥ ከፍታ እየወጡና እየወረዱ መንሸራሸር ማለት ነው። በዚህ መንሸራሸር ውስጥ ጥልቅ የመንፈስ እርካታ አለ። ከፍተኛ የሆነ መገለጥ አለ። ከነገረ-ዓለሙ (Cosmic nature) ጋር ውህደትና ስምምነት አለ።

እንደ ውቅያኖስ ተዝቆ ከማያልቀው የተፈጥሮ ድንቅ ተዓምራት፣ ከዚያ ውስብስብ ዓለም ምንጭ የሚቀዳ የዕውቀት ወሐዜ ወይን ጥጥት አድርገህ፣ እርክት ብለህ እንደገና የምትጓዝበት፣ እንደገና ሌላ የዕውቀት ምንጭ አግኝተህ አቅምህና እምነትህ በፈቀደው መጠን የምትጠጣበት፣ እዚያ ላይ እረፍት አድርገህ፣ ተደንቀህ፣ ተገርመህ እንደገና በማያቋርጥ ጉዞ ወደ ላይ፣ ወደ ከፍታ የምትወጣበት፤ እድሜህን ሙሉ፣ በውልደት ምክንያት ወደ ተለየህበት፣ ወደ መጣህበት ህላዌ እስክትመለስ ድረስ፣ ወደ ዘላለማዊ መኖሪያህ እስክትሰበሰብ ድረስ፣ ከዘላለማዊነት ጋር እስክትዋሃድና በዚያ ህላዌ እቅፍ ውስጥ እስክትኖር ድረስ በትልቅ መነሳሳት፣ በትልቅ ወኔ፣ በደስታ የምትጓዝበት መንገድ ነው።

 ይህ መንገድ ቁሳዊ ጥቅም፣ ዓለማዊ ሀብት ለማግበስበስ፣ ሆይ ሆይታና ዝና ለማትረፍ የሚፈልጉ ሰዎች የሚጓዙበት አይደለም። ምክንያቱም፣ እነዚህ ነገሮች በፍልስፍና መስክ ላይ የሚገኙ አይደሉምና። በፍልስፍና መንገድ ረጅም ርቀት ለመጓዝ እውቀት ላይ የተመሠረተ ትህትና ይጠይቃል።

በዚህ ጉዞ በራስህ ድካም፣ በፍለጋህ፣ ባገኘኸው እውቀት ወይም መገለጥ መደሰት እንጂ፣ ሌላ የምታገኘው፣ የምትጨብጠው፣ የምትይዘው ነገር የለም።

ይሄ መንገድ በምድራዊ እይታ፣ በተራ ሰው መነፅር ሲታይ የድህነት መንገድ ሊሆን ይችላል። እንዲያውም ይባስ ብሎ ብዙ ሰዎች በአኗኗርህ፣ በአስተሳሰብህ ሊያወግዙህ እና አቃቂር ሊያወጡልህ ይችላሉ። ምናልባት ጥቂቶች ሊያደንቁህ ይችሉ ይሆናል፤ እነዚህም ቢሆኑ ግን ሊከተሉህ አይችሉም። (ደግነቱ ፈላስፋ ተከታይ ኖረ አልኖረ የሚገደው ነገር አይደለም፣ እንዲያውም በአንድ ጊዜ ብዙ ተከታይ ያን ዕለት ነው መጠርጠር ያለበት)። በዚህ መንገድ መጓዝ ሸክሙ ፅኑ፣ መከራው ብዙ በመሆኑ፣ ደፍሮ የሚጓዝ ሰው አታገኝም። በዘመን ውስጥ አልፎ አልፎ የተጓዙ ሰዎችን ዳና ብቻ ነው የምታገኘው። መንገዱ ራሱ ለሁሉም ሰው ክፍት አይደለምና።

በዚህ ዓይነቱ መንገድ ላይ የሚጓዙት አዲስና የተሻለ መንገድ ለማግኘት፣ የተለየና አዲስ ነገር የማወቅ ጉጉት ያላቸው፣ ይህን ፍላጎታቸውንም ለማሳካት የቆረጡ ብቻ ናቸው። እንዲህ በመሆኑም ይህ መንገድ ወደ ገበያ ወይም ወደ ቤተ እምነት እንደመሄድ ማንም በቀላሉ የሚጓዘው አይደለም። በእውቀት ፍለጋ የተጉ፣ ጥቂት ጀግኖች፣ ደፋር ጠያቂዎች ብቻ የሚጓዙበት መንገድ ነው። ይህን መንገድ ነው እኔ የፍልስፍና መንገድ የምለው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የተባለውን ሁሉ በቀላሉ ማመን የሚቀለው ወይም የሚፈልግ ሰው አለ። ይህ ከምዕመናን ወገን ነው! አማኝ መሆን በራሱ ጥሩ ነገር ቢሆንም፣ ስለምታምነው ነገር አለመጠየቅና አለመመራመር ግን መንጋነት ነው። ስለሚያምነው ነገር ጥግ ድረስ ሄዶ የማይጠይቅ፣ በመንጋ አስተሳሰብ ውስጥ የሚኖር በቁጥር እንጂ በራሱ ሊገለፅ የማይችል ሰው ነው።

እንደዚሁም፣ ጥበብ የማትገለጥለት፣ ነገር ዓለሙ ሁሉ የተደፈነበት፣ በደመነፍስ የሚንቀሳቀስ፣ የሚኖር ሰው አለ፤ ለእርሱ ይሄ መንገድ ዝግ ነው። ጊዜያዊ ስሜቱን፣ የዕለት ተዕለት ፍላጎቱን ነውና የሚከተለው። ስጋዊ ረሀቡን ለማርካት ነውና የሚኖረው። ለዚህ ዓይነቱ ሰው የፍልስፍና እና የጥበብ መንገድ ዝግ ነው።

እነሆ ኦዜል በዚህ ከሁሉም መንገዶች በተለየና ፍፁም በሆነ የፍልስፍና መንገድ እየተመራመረ፣ እግረ መንገዱን የሚያጋጥመውን ሕፀፅ እየነቀፈ ይንሸራሸር ዘንድ መልካም ፈቃዱ ሆነ። ኦዜል ማለት ምንድን ነው? ኦዜልስ ማነው? ኦዜል በእብራይስጥ ቋንቋ መለኮታዊ ኃይል ማለት ነው።

በመሆኑም፣ ይህ መጠሪያ የእውቀት ስሜ ይሆን ዘንድ መርጨዋለሁ። በቤተክህነት ትምህርት የሆነ ከፍ ያለ የእውቀት ደረጃ ላይ ስትደርስ በፊት ትጠራበት ከነበረው የተለየ አዲስ ስም ለራስህ የምትሰጥበት ሁኔታ

“ጥበብ የማትገለጥለት፣ ነገር ዓለሙ ሁሉ የተደፈነበት፣ በደመነፍስ የሚንቀሳቀስ፣ የሚኖር ሰው አለ፤ ለእርሱ ይሄ መንገድ ዝግ ነው። ጊዜያዊ ስሜቱን፣ የዕለት ተዕለት ፍላጎቱን ነውና የሚከተለው። ስጋዊ ረሀቡን ለማርካት ነውና የሚኖረው። ለዚህ ዓይነቱ ሰው የፍልስፍና እና የጥበብ መንገድ ዝግ ነው”

አለ። ከዚህ ልምድ በመውሰድ እኔም የፍልስፍና አቋሜንና እምነቴን በዚህ መጠሪያ አንፀባርቅ ዘንድ መልካም ፈቃዴ ነው።

ኦዜል ከፈላስፎች ሁሉ፣ የፍልስፍና አባት የሆነውን ሶቅራጥስ በዋናነት የሚያደንቅ ነው። እርሱ ፍልስፍናን ወደ መሬት ያወረደ፣ ሰውኛ እንድትሆን፣ የሰውን ልጅ ጉዳይ፣ ኑሮና ሁኔታ እንድትፈትሽ፣ እንድታገለግል አድርጎ ለመጀመሪያ ጊዜ የገራት ሰው በመሆኑ ነው። ኦዜል ለዲዮጋን ሀሳቦችና አኗኗርም እንደዚሁ የተለየ ፍቅርና ቦታ፣ መደነቅና መገረም አለው። በእርግጥ ኦዜል የፈላስፋው ዘርዓያዕቆብ የመንፈስ ልጅ ነው። የሰው ልጅ አንድም በስጋ፣ አንድም በመንፈስ ይወለዳልና።

 “አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤ ጠይቁ ይመለስላችኋል” ይላል መጽሐፉ! በእርግጥ መጽሐፉ አይደለም ይህን ያለው፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ ነው። እኔ ደግሞ እላለሁ፤ ለማንኳኳትም በመጀመሪያ በሩን ማግኘት ያስፈልጋል። የጥበብን በር ያገኘ እርሱ የታደለ ነው። አይደለም የጥበብ በር ወደ ራሱ ቤት የሚወስደው መንገድ የሚጠፋበት፣ በውስብስቡ የሰው ልጅ ህይወት ሰክሮ፣ ተደናብሮ ወደ ገደል የሚጓዝ፣ በዚያ ምክንያትም የሚጠፋ ስንት ሰው አለ!

እነሆ የጥበብን መንገድ ፈልጎ ያገኘ እርሱ የታደለ ነው እላለሁ። ወደ ከፍተኛው እውነታ፣ ወደ ዘላለማዊነት የሚወስደውን መንገድ ጀምሯልና ነው።

በዓለም ላይ ብዙ ብዙ መንገድ አለ። መንገዱን ያገኘ ሰው ሁሉ ይጓዝበታል ማለት ግን አይደለም። ብዙ ሰው ዳና ባልወጣለት፣ ማንም ባልሄደበት ወይም በማይሄድበት መንገድ መጓዝ አይፈልግም። ይህም እሾህና መከራ እንዲያገኘው ስለማይፈልግ ነው። ስለዚህ የሰው እርጋጭ ምልክት ያለው፣ የተለመደ፣ የቀደሙ እግሮች ዳና ያለሰለሰውና ያሰፋው ጎዳና እንጂ መንገድ ባልወጣለት ወዴት እንደሚያደርስ በማይታወቅ መንገድ ላይ ለመጓዝ አይፈልግም። አንድም አቅጣጫ ስቼ እጠፋ ይሆን? ብሎ መጨነቅ ስለማይፈልግ ነው። አንድም ደግሞ ምቾት፣ ድካምና ሀሳብ የሌለበትን ጉዞ ማድረግ ስለሚመርጥ ነው። እርግጥ ነው፣ ብዙም ባልተለመደ መንገድ ስትጓዝ እሾህ ሊወጋህ ይችላል፣ አውሬ ወይም ሽፍታ ሊያገኝህ ይችላል፣ ልትጠፋም ትችላለህ። በእርግጥ በተለየ መንገድ ስትጓዝ ይህን ሁሉ አውቀህ፣ ተዘጋጅተህ ነው የምትጓዘው።

አንዳንዱ ሰው ህይወት በራሷ ጊዜ ወደ ዳንስ ቤት እንደምትወስደው፣ ሌላው ደግሞ ወደ ሀብት ማማ እንደምታወጣው፣ እንደዚሁም ሌላው ወደ ዓለማዊ ዝና እንደምትጎትተው፣ እኔ በብዙ የመከራ ማዕበል እየተገፋሁ ወደ እዚህ የፍልስፍና መንገድ ገባሁ።

ፍልስፍና ማንም የሚኖርበት ሕይወት አይደለም። ወደዚያ የሚወስደው መንገድም ወጣ ገባ ነው። ጥቂቶች ወደ በሩ መድረስ ቢችሉም፤ በሩ አይከፈትላቸውም። ወይም ራሳቸው በሩን አልፈው ለመዝለቅ አይችሉም፤ ይፈራሉና ነው።

አሁን በዚህ መንገድ እየተጓዝኩ ነው ብዬ አስባለሁ። መድረሻዬም አቅሜ እስከፈቀደ ድረስ ራስን ማወቅ ነው።

ከየት መጣሁ? ወዴት እሄዳለሁ? በሚለው ጉዳይ ላይ መመራመር ነው። ወደዚያ ለመግባት በር እያንኳኳሁ ነው። ይሄ ሁሉ የሆነው ግን እኔ ብቻ ስለፈለግኩ አይመስለኝም። በነገሮችና በሁኔታዎች ሠንሰለታዊ ግጥምጥሞሽ ውስጥ በተፈጠረ ተአምር እንጂ። የሆነ ሆኖ እዚህ ደርሻለሁ። ዕድለኛ ነኝ።

የጥበብን በር እያንኳኩ፤ በኳኳቴው እየተደሰቱ መኖር ራሱ ትልቅ ነገር ነው። መታደል ነው። በዚህም ጥልቅ ሀሴት አደርጋለሁ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top