ዘባሪቆም

የቤት ኪራይ ወጎች

1. ባንድ ወቅት ቤት ለመከራዬት ከደላላ ጋር አምስት ኪሎ አካባቢ ሄድኩ። ሰፊ ግቢ ውስጥ ያለች አንዲት አነስተኛ ክፍል ቤት እንደደረስን የእድሜ ባለፀጋዋ አከራይ ከእግር እስከራሴ ባትኩሮት እያጤኑ “ወንደ ላጤ ነህ?” ሲሉ ጠየቁኝ ።

 “አዎ ማዘር” ስል በትህትና መለስኩ።

 “ስራህ ምንድነው?”

 “አስተማሪ ነኝ ግን ደግሞ እማራለሁ” ከማለቴ ባግራሞት አንጋጠው እያዩኝ “ተምረህ ሳትጨርስ ነው ሰው ‘ምታስተምር? አይ የዘንድሮ ጉድ” አሉ።

 “እያሳደገ ነው፣ ለማሻሻል ነው ማዘር” ሲል ደላላው ጣልቃ ገብቶ መንገድ ላይ ሲያደርቀኝ የነገርኩትን ደግሞ መለሰ።

 “እሱን እናንተው ታውቁ!” አሉና የቤቱን ህገ ደምብ ማብራራት እንደጀመሩ ድንገት “ጫት ትበላለህ?” ሲሉ አፋጠጡኝ።

 “አይቅምም” አለ ለመመለስ እድል ሳይሰጠኝ። “ዋናው ነገር እሱ ነው፣ ጫት ካልበላህ ሌላ የሚያገናኘን ነገር የለም” አሉና አይናቸውን ከአፌ ላይ ሳያነሱ “ሲጃራስ ትጠጣለህ?” ከማለታቸው ደላላው አሁንም ፈጥኖ “ኧረ ጠላቱ! ጭስ በዞረበትም አይደርስ” ሲል አስረግጦ መለሰ። ከርሱ ስለኔ በርግጠኝነት መናገር በላይ የርሳቸው እሱን ማመን እያስገረመኝ ቀጣዩን ጥያቄ ስጠባበቅ “ሲጃራ ካልጠጣህ ምንም የሚያገናኘን ነገር የለም” አሉና መላ ሰውነቴን ‘ስካን’ የሚያደርጉ ይመስል ከከንፈሬ ወደ አንገቴ እየወረዱ “የቤንጤ ዘፈን ትሰማለህ?” ሲሉ አይናቸው ማተብ ፍለጋ መንከራተቱን ያስተዋለው ደላላ የሸሚዜን ቁልፍ ፈቶ ያንገቴን ሃብል እየሳበ “የማርያም ልጅ ነው! በሷ እንኳን ቀልድ አያውቅም” ሲል መሰከረ። “የቤንጤ ዘፈን ካልሰማህ የሚያገናኘን ነገር የለም” አሉ።

በተመሳሳይ ጓደኛ ካላበዛሁ፣ መብራት አብርቼ ካላመሸሁ፣ ካውያ ካልተጠቀምኩ፣ ወዘተ “የሚያገናኘን ነገር እንደሌለ” ካስረዱኝ በኋላ

“በተረፈ ቤቱ ቤትህ ነው” ሲሉ ቀጠሉ። “እንደ’ናትህ ቤት ቁጠረው፤ ከዚህ ቀደም የነበረው ተከራይ እንዳንተው ወጣት ነበር። ያገኘውን እንጃ ድንገት በጠና ታሞ በለጋ እድሜው ያልጋ ቁራኛ ሆነ”። ሰውነቴን አንዳች ፍርሃት ሲወረው ተሰማኝ።

“እኔ እናትህ እንዳብራኬ ክፋይ ሳልታክት ሳስታመው ከርሜ እጄ ላይ ካረፈ ገና ወሩ ነው።” ሲሉ በድንጋጤ ድርቅ አልኩ። “በሴት እድሬ እንዴት አርጌ እንደቀበርኩት ድፍን መንደሩን ብትጠይቅ ይነግርሃል” እያሉ ሲቀጥሉ ልቤ መምታቱን ለማረጋገጥ ደረቴን እየዳበስኩ ጉልበቴ ሳላውቀው ከድቶኝ ኖሮ አጎንብሼ ነበር።

“ያምሃል እንዴ ልጄ?” ሲሉኝ ከገባሁበት ድንጋጤና መታወክ ነቃሁ።

“ታሞ አያውቅም ማዘርዬ” አለ ደላላው “በሽታውን በልጅነቱ ነው የጨረሰው” ሲል ሳልወድ ፈገግ አልኩ።

“ጎሽ፣ ዋናው ጤና ነው!” አሉ አሮጊቷ። “ካልታመምክ የሚያገናኘን ነገር የለም የኔ ልጅ!”

“እሺ ማዘር ካልተያዘ ነገ እመጣለሁ!”- አልተመለስኩም፡፡

2. አሮጌው አውሮፕላን ማረፊያ (ኦልድ ኤርፖርት) አካባቢ ተከራይቼ እኖር የነበርኩበት ግቢ አከራዬ ከልጅ ልጃቸው ጋር ይኖራሉ። ልጅ ስለምወድ ከልጁ ጋር ወዲያው ተወዳጀን። ብዙ ጊዜ ቤቴ እየመጣ ይጫወታል። ፊደል መቁጠሪያ እድሜው ላይ ስለነበር የተፃፈ ነገር አያልፍም። በተለይ ግድግዳዬ ላይ የሰፈሩ ጥቅሶችን በገባ ቁጥር እንደዳዊት ሳይደግምቸው አይወጣም። አንድ ቀን ሲንደረደር መጥቶ “የሚረዳኝ የለምና ከኔ አትራቅ!” የሚለውን ጥቅስ “ረ” እና “ዳ” ን አጥብቆ ሲያነብ አስቤ የማላውቀውን ትርጉም አስታውሶ አስገረመኝ። ከጊዜ በኋላ እንደንባቡ ቁጥር መለማመድ ጀመረ። ቤቴ ውስጥ እንግዳ ካየ አንድ ባንድ በጣቱ ቆጥሮ ሲበር ቤቱ ይመለሳል። በዚህ ሁኔታ ሂሳብን ከስሌት ይልቅ የስለላ መሳሪያ በማድረግ የእንግዶቼን ብዛት ላከራዬ ሲዘግብ እንደነበር የደረስኩበት አያቱ መረጃ አጣቅሰው ባቀረቡብኝ የሰው ማብዛት ስሞታ ነበር።

3. አሜሪካ ከመጣ ቅርብ ጊዜ ከሆነው አንድ ወዳጄ ጋር የሚከራይ ቤት ፍለጋ አበሻ ሱቅ ውስጥ የተለጠፉ ማስታወቂያዎችን እያየን ስልክ እንደውላለን። መጀመሪያ የደወልንለት ሰው ቁጣ ባዘለ ድምፅ “ማስታወቂያው ላይ ቤቱ የሚከራየው ለሴት ነው ብያለሁ!” ሲል ጮኽ።

“ይቅርታ ጥድፊያ ላይ ሆኜ ልብ አላልኩም፣ የቦታውን ቅርበት ስለወደድኩት ምናልባት ሃሳብክን ከቀየርክ ብትደውልልኝ በጣም ደስ ይለኛል” አለ ጓደኛዬ በትህትና።

“የኔ ወንድም እኔ ሃሳቤን መቀየር አልችልም አንተ ከፈለ’ክ ፆታህን ቀይረህ መግባት ትችላለህ።” ስልኩ ተዘጋ። ቀጥሎ የደወለላቸው አከራይ:-

“ለስንት ሰው ነው የምትፈልጉት?” ሲሉ ጠየቁት።

“እኔና ባለቤቴ ነን” ሲል በትህትና መለሰ።

“ስራ ትሰራላችሁ?” ሲሉ በስልኩ ሌላኛ ጫፍ ያሉት አከራይ ድምፅ ለኔ ጭምር ይሰማኛል።

“ባለቤቴ ትሰራለች፣ እኔ ደግሞ ተማሪ ነኝ” አለ ወዳጄ ጨዋነት በተሞላና ያከራይ አንጀት በሚያለሰልስ ድምፅ።

“እንዴት እንዴት ነው ነገሩ?” የሴትዮዋ ድምፅ ይበልጥ ጎልቶ አስተጋባ።

“አንተ እየሰራህ እሷ ብትማር አይሻልም?” ሲሉ ተሳስቀን ሌላ ቁጥር መቃኘት ያዝን። st

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top