ስርሆተ ገፅ

የሙዚቃ መምህርቴ ተሰጥዖዬን አመላክታኛለች

ድምፃዊ እሱባለው ይታየው፣ በቅርብ ጊዚያት ውስጥ ለህዝብ ባቀረባቸው ሙዚቃዎች ጎላ ብሎ በመውጣት ላይ የሚገኝ ወጣት ድምፃዊ ነው። ከሰሞኑ ለህዝብ ያቀረበው ‹‹ትርታዬ›› አልበም ደግሞ የበርካታ ሙዚቃ አድማጮችን ውዴታ አትርፏል። የድምፃዊውን የሙዚቃ መንገድ ለመቃኘት የስርወተ-ገጽ እንግዳ አድርገነዋልና እነሆ፡-

ታዛ፡- እድገትህ እና ኪነት ያላቸው ተጣምሮ ምን ይመስላል?

እሱባለው ይታየው (የሺ)፡- ተወልጄ ያደግኩት አዲስ አበባ ከተማ፣ መርካቶ- ተክለሃይማኖት አካባቢ፣ በተለምዶ ሶማሌ ተራ ወይም አሜሪካን ግቢ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ውስጥ ነው። አካባቢው በርከት ያለ ሰው የሚኖርበት፣ ማህበራዊ ኑሮ ጎላ የሚልበት፣ ሃብታምና ደሃ ተቀላቅሎ የሚኖርበት፣ አብዛኛው የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ፣ ሙስሊም- ክርስቲያን በጋራ በፍቅርና በመተሳሰብ የሚኖርበት ስለሆነ፣ ለኪነጥበብ ሰው የሚሆን ብዙ ግብዓት አለው። አካባቢው ገና በልጅነትህ ብዙ እንድታውቅ ዕድል ይሰጥሃል። በዚህ የተነሳም የታላላቅ ድምፃውያንን ሥራዎች የማድመጥ ዕድሌ ሰፊ ነበር። ሙዚቃን አንተ ፈልገህ ከፍተህ ብቻ አይደለም የምታደምጠውና የምታጣጥመው። ጎረቤት ይከፍትልሃል፣ ቡና ቤቶች ይከፍቱልሃል፣ ሙዚቃ ቤቶች ከፍተው ያስደምጡሃል። እናም ሳታስበው በሆነ ጥበብ ውስጥ ቆስቆስ ያደርጉሃል። እኔም በዚህ ድባብ ውስጥ በማደጌ፣ ሙዚቃን በድምጽ ማንጎራጎር የጀመርኩት ገና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ እያለሁ ነው። አስታውሳለሁ፣ አንዋር መስጊድ ጎን በሚገኘው ደጃዝማች ዑመር ሰመተር ትምህርት ቤ ት (በ1996 ዓ.ም.) የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ ነው ክፍል ውስጥ ማንጎራጎር የጀመርኩት። በደጃዝማች ዑመር ሰመተር ት/ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የጀመርኩትን ማንጎራጎር (መዝፈን) ቀጥዬ፣ “ቺልድረን ኤይድ ኢትዮጵያ” (ቻዴት) በሚባል ዓለማቀፍ ግብረ- ሠናይ ድርጅት ክበብ ውስጥ መሳተፍ ጀመርኩ። ግብረ ሠናይ ድርጅቱ አንድ ትምህርታዊ የሆነ መልዕክት ለማኅበረሰቡ ማስተላለፍ ሲፈልግ፣ የሚጠቀምበት የኪነጥበብ ክበብ አለ – ቻዴት። በሥሩም የሙዚቃ፣ የቲያትር እና የውዝዋዜ ቡድኖች አሉ። እኔ ደግሞ እዛ ውስጥ በድምፃዊነት አገለግል ነበር። በተጓዳኝም በሌሎችም የሙዚቃ ክበባት ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። ከዛ በኋላ እየበረታሁ በመምጣቴ ወደ ህፃናትና ወጣቶች ቲያትር በድምጽ ተወዳድሬ ገባሁ። ህፃናትና ወጣቶች ቲያትር ለድምፃውያን በየወሩ አርባ ብር፣ ለተወዛዋዦች ደግሞ ሃያ ብር እየተከፈላቸው ነበር የምናገለግለው፡፡

 ታዛ፡- ህፃናትና ወጣቶች ቲያትር እንዴት ልትገባ ቻልክ?

እሱባለው ይታየው (የሺ)፡- ዘሪሁን አፈወርቅ የሚባል የባህል ሙዚቃ ተጫዋች አለ። በ1999 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ስዘፍን ያየኝና እድሜዬን አስተውሎ ‹‹ለምን ህፃናትና ወጣቶች ቲያትር አትሞክርም›› ብሎ ይዞኝ ሄደ። ከዛ እስቲ ሙዚቃ ተጫወት ተባልኩኝ። ያኔ አስራ አራት ወይም አስራ አምስት ዓመት አካባቢ ቢሆነኝ ነው። ተጫወትኩ፤ ድምፄን ወደዱትና በቃ ከዛሬ ጀምረህ መጥተህ መጫወት ትችላለህ አሉኝ። እና እዛ ስጀምር፣ በድምጽም ሆነ በውዝዋዜ መስክ ያሉት ልጆች የእድሜ እኩዮቼ ናቸው። ደስ አለኝ። ሌላ ቦታ ስትሰራ ግን የእድሜ እኩያህን አታገኝም፤ ትልልቅ ሰዎች ናቸው። ይሄ ለኔ ምቾትና ደስታ አይፈጥርልኝም ነበር።

ታዛ፡- ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ገብተህ ሙዚቃ ማጥናት ችለኃል?

እሱባለው ይታየው (የሺ)፡- ህፃናትና ወጣቶች ቲያትርን ሳልለቅ ተፈሪ መኮንን የሙዚቃ ትምህርት ቤት ገብቼ ሙዚቃ ማጥናት ፍላጎቴ ነበር። እና ምዝገባ መኖሩን ልጆች ነግረውኝ ልመዘገብ ስሄድ የአስረኛ ክፍል ውጤቴ እንደሚያስፈልግ እንኳ ግንዛቤ አልነበረኝም። በኋላ እዛ ልመዘገብ ስሄድ ‹‹ለመመዝገብ ይሄ፣ ይሄ ዶኩመንት ያስፈልጋል›› ሲሉኝ ተመልሼ ሄጄ የትምህርት ሠነዶቼን አቅርቤ ተመዘገብኩ። ከዛ በሙዚቃ ጥበብ ውስጥ ሳክስፎን ለሦስት ዓመት አጠናሁና ዲፕሎማ ያዝኩኝ። ከሳክስፎን ጎን ለጎን ደግሞ (ማይነር ኮርስ) የክራር ድርድር እማር ነበር።

ታዛ፡- ክራር ድርድር ምንድን ነው?

እሱባለው ይታየው (የሺ)፡- ክራር ድርድር እና ክራር ግርፍ የሚባል አጨዋወት አለ። ለምሳሌ ፋኖ አጨዋወትን ተመልከት፣ ልዩነቱ ይገባሃል። ክራር ድርድር ሲሆን- በእጅህ ብቻ ማለትም በጣትህ የላይኛውን ክፍል በመነካካት ብቻ ነው የምትጫወተው። ክራር ግርፍ ግን በሁለቱም ጥምረት የምትጫወተው የተለመደው የክራር አጨዋወት ነው። ስለዚህ እኔ የተማርኩት (ከሳክስፎን ቀጥሎ) ክራር ድርድር ነው።

ታዛ፡- ትርታዬ አልበምን በምን ያህል ጊዜ ዝግጅት ልታወጣ ቻልክ? ብዙ ድምፃውያን በአሁኑ ጊዜ አልበም መሥራት ከባድ ነው ሲሉ ይደመጣሉና?

እሱባለው ይታየው (የሺ)፡- ልክ ትምህርቴን እንደ ጨረስኩ ከተፈሪ መኮንንና ከህፃናትና ወጣቶች ቲያትር ለቀቅኩ። ምክንያቱም ተፈሪ መኮንን እያለሁ አንድ ጓደኛ ነበረኝ፣ ታምሩ አማረ ይባላል። አዲሱን አልበም የሰራልኝ ባለሙያ ማለት ነው። የሙዚቃ ቅንብሩን፣ ማዋሃዱን (ሚክሲንጉን)፣ ቀረጻውን ሁሉንም ማለት ነው። እና ከሱ ጋር ስንመካከር ካንተ ጋር መስራት እንችላለን አለኝ። አንዳንድ ሙዚቃዎችንም ትምህርት ቤት ሆኜ አሳየው ነበረ። የምሰራቸው ዜማዎች ደስ ይሉት ነበር። ከዛ ቀጥታ ወደ ስቱዲዮ ስራ ገባን ማለት ነው። የስቱዲዮ ውስጡን ሥራ በብርታት ስንሰራ ቆየንና በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ “ትርታዬ” አልበምን ማውጣት ቻልኩ።

ታዛ፡- የአሥረኛ ክፍል መልቀቂያ ውጤትህ ወደ መሰናዶ ትምህርት ያስገባህ ነበር?

እሱባለው ይታየው (የሺ)፡- አያስገባኝም ነበር። ወደ መሠናዶ ትምህርት አስገባኝም አላስገባኝም፤ ሃሳቤ የነበረው ተፈሪ መኮንን ገብቼ ሙዚቃ ማጥናት ነበር። በህይወቴ በጣም እመኘው የነበረው ነገር ይህ ነበር። ከዛ በቃ ትኩረቴ ሁሉ ስቱዲዮ ላይ ሆነ ማለት ነው። ሁሉም ነገሬ ይሄን አልበም ማሳካት መቻል ሆነ።

ታዛ፡- ከአልበምህ በፊት ነጠላ ዜማዎችን ለህዝብ አስደምጠህ ነበር፤ የነዚህ ሥራዎች መወደድ ብርታት ሆኖህ ነበር?

እሱባለው ይታየው (የሺ)፡- በደንብ። ስቱዲዮ ላይ እየሰራሁ፣ መጀመሪያ “ሆያ ሆዬ” የሚለውን ሙዚቃ ሰራሁ። ይህ ሙዚቃ ክሊፕም አለው። በሪከርድ ደረጃ የመጀመሪያ የሰራሁት ግን “ኢትዮጵያ” የሚለውን ሙዚቃዬን ነው። የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ማለት ነው። ይህም ሙዚቃ ክሊፕ ነበረው። ከዛ በኋላ “ሄሎ በይኝ” የሚለው ሙዚቃ ወጣ ማለት ነው። ሶስተኛ ላይ ነው “ሆያ ሆዬ” የሚለውን ያወጣሁት። በእርግጥ በደንብ የሰራሁት “ሆያ ሆዬ” የሚለውን ሙዚቃ ነው። ሌሎቹ ላይ ግን ምንም ተሞክሮ ስላልነበረኝ መለማመጃ ነው የሆኑት። “ሆያ ሆዬ”ን ሙዚቃ ከሰራሁ ከሁለት ዓመት እረፍት በኋላ “ማሬ ማሬ” የምትለው ሙዚቃ ወጣች ማለት ነው። “ማሬ ማሬ” ሙዚቃም በሰዎች ዘንድ በጥሩ መታየት ጀመረች። ከዚህ በኋላ በጣም ተበረታታሁ። የድምፄን ከለር ብዙ ሰው እንደሚወደው ከብዙ አድማጭ አስተያየት ተረዳሁ። የአድማጭ አድናቆትም ከዛ በኋላ ነው ከፍ ብሎ ማግኘት የጀመርኩት። ከዛ በመሐል ‹‹እኔ ነኝ ደራሽ ለወገኔ›› የሚለው ሙዚቃ ወጣ ማለት ነው። ይህ ደግሞ የበለጠ ወደ ህዝብ ጆሮ አደረሰኝ።

ታዛ፡የምትጫወታቸውን ዜማዎችና ግጥሞች የምትሰራው እራስህ ነህ?

እሱባለው ይታየው (የሺ) የሁሉም ዘፈኖቼን ዜማና ግጥም ራሴ ነው የሰራሁዋቸው። “እኔ ነኝ ደራሽ ለወገኔ” የተሰኘውንም ዜማና ግጥም ራሴ ነኝ የሰራሁት። ዜማውም በወቅቱ የዘውዲቱ ሆስፒታል የኩላሊት በሽታ ማጠቢያ ማሽን አስገብቶና በቦታውም ለኩላሊት ህክምና የሚውል ህንፃ ተሰርቶ ይመረቅ ስለነበር፤ ለዚህ ማህበራዊ ፋይዳ ሲባል ነው ዜማው የተሰራው።

ታዛ፡ወደ ሙዚቃ ህይወት አስገባኝ የምትለው መንደርደሪያህ ምንድነው?

እሱባለው ይታየው (የሺ) እኔ ዝንባሌዬን በቅጡ አላውቀውም ነበር። የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ስንማር የሙዚቃ ትምህርት (ኤስቴቲክስ) አለና፤ በዛ ክፍለ ጊዜ ለማርክ ብዬ የግድ ስዘፍን ነው ጎላ ብዬ ለመምህርቴ መታየት የጀመርኩት። እና የዛኔ የሙዚቃ መምህርታችን ወ/ሮ አይናለም ማሬ ግዴታ መምጣትና መዝፈን አለብህ አለችኝ። እኔ ደግሞ እቀር ጀመር። እሷ ሙዚቃ የሚሞክሩ ልጆችን ትመለምል ነበርና በግድ መምጣት አለብህ አለችኝ። እኔ ደግሞ እሷ በእኔ ላይ ያየችውን የሙዚቃ ተሰጥዖ (ችሎታ) እንደሷ ማየት ስላልቻልኩ፣ የመጀመሪያው ቀን ‹‹ክላስ ቀጣሁ››። ምክንያቱም ብዙም ፍላጎት አልነበረኝም ነበር። ከዛ ትረሳዋለች ብዬ ስገባ የሆነ ቀን አገኘችኝ። እናም ‹‹አንተ ልጅ ና ብዬህ ለምንድን ነው የቀረኸው?›› አለችኝ። እኔ ደግሞ አይን አፋር ነበርኩና መጥቼ ነበረ፣ ብዙ ሰው ስለነበረ ፈርቼ ተመለስኩኝ አልኳት። ከዛ በረንዳ ውጪ መዝፈን ቀረልኝና ክፍል ውስጥ ዝፈን አለችኝ። እንዲህ እንዲህ እያለች የሙዚቃ መምህርቴ ተሰጥዖዬን አመላክታኛለች።

ታዛ፡- የነማንን ሥራዎች ነበር በትምህርት ቤት የምትጫወተው?

እሱባለው ይታየው(የሺ)፡- ክፍል ውስጥ በምዘፍንበት ወቅት የቴዎድሮስ ታደሰን፣ የዳዊት መለሰን እና የሌሎች ድምፃውያንን ሥራዎች ነበር የምጫወተው። እነዚህ ድምፃውያን ለጆሮዬ በጣም ቅርብ የነበሩና የሚደመጡኝ ናቸው። ከዛ የሆነ ቀን ላይ ስሄድ የሙዚቃ መምህርቴ ህዝብ በተሰበሰበበት እንድዘፍን አደረገችኝ። በቃ እንደዛ ዓይነት ስሜት ተሰምቶኝ አያውቅም። በጣም ላቤ ሁላ በእጄ እየወረደ ነበር የዘፈንኩት። ሆኖም ከተጫወትኩኝ በኋላ፣ በጣም የሚያበረታታና የሚያጀግን ጭብጨባ ተለገስኩኝ። እና ከዛ በኋላ ዘፋኝ መሆን እንደምችል የሆነ የተስፋ ብልጭታ ይታየኝ ጀመር። ከዛ በኋላ በትምህርት ቤት የሙዚቃ ተሳትፎዬን አጠናከርኩ። መምህርቴንም አከበርኳት።

ታዛ፡- ከሀገር ውስጥ ሙዚቀኞች እነማንን ታደንቃለህ?

እሱባለው ይታየው (የሺ)፡- ከሴት ድምፃውያን፡- እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ)፣ አስቴር ዐወቀ፣ በዛወርቅ አስፋው፣ ዘሪቱ ከበደ፣ ከወንድ ድምፃውያን ደግሞ ጋሽ ጥላሁን ገሠሠ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ፣ ጋሽ ማህሙድ አህመድ፣ ምኒልክ ወስናቸው፣ ሙሉቀን መለሰ፣ ጋሽ ግርማ በየነ፣ ጋሽ ባህታ ገ/ሕይወት፣ ከዚህ ዘመን ድምፃውያን ደግሞ፡- ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)፣ ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ኢዮብ መኮንን፣ እና ሌሎችም ጥሩ ጥሩ ጥበብና ስሜት የሰጡኝን አደምጣለሁ። ከውጭ አገር ደግሞ የሜሎዲ ሥራዎች ስለሚማርኩኝ ለምሳሌ ዊትኒ ሂውስተን፣ ሴሊንዲዮን፣ አደል፣ ብርኖ ማርስ፣ ካሊድ፣ ብቻ መርጬ ሜሎዲ ሜሎዲ የሆኑ ሥራዎችን አደምጣለሁ።

ታዛ፡- በሀገር ውስጥ ከተሰሩ የሙዚቃ አልበሞች ሁሉ ሦስት አልበሞችን ብቻ ይዘህ ተሰደድ ብትባል የትኞችን ምርጥ ሦስት አልበሞች ትመርጣለህ?

እሱባለው ይታየው (የሺ)፡- ከባድ ጥያቄ ነው። ሆኖም በእኔ ምርጫ በአንደኛ ደረጃ የድምፃዊ ቴዎድሮስ ታደሰ ‹‹ዝምታ›› አልበም ምርጫዬ ነው። የእጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ‹‹ናፈቀኝ›› ዜማ ያለበት አልበም ደግሞ ሁለተኛ ምርጫዬ ነው። በሦስተኛ ደረጃ … እባክህ ሦስተኛው አልበም ቅልቅል ‹‹ኮሌክሽን›› ሥራዎች ይሁኑልኝ።

ታዛ፡- እሺ ይሁንልህ!

እሱባለው ይታየው (የሺ)፡- በዚህ አልበም ውስጥ የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ኦላን ይዞ››፣ የማህሙድ አንድ፣ የበዛወርቅ አንድ፣ የሙሉ ቀን አንድ፣ የኢዮብ መኮንን አንድ፣ የዘሪቱ አንድ፣ የናቲ ማንን አንድ፣ የአስቴር ዐወቀን የተወሰኑ ሥራዎች ለቅመን ለቅመን ኮሌክሽን አድርገን ማለት ነው። እነዚህ ሁሉ በእኔ የሙዚቃ ህይወት ውስጥ ቦታ አላቸው።

ታዛ፡- የኢትዮጵያ ሙዚቃ ካሉት ቅኝቶች ምን ያህሉን በአልበምህ እና በነጠላ ዜማዎችህ ላይ ተጠቅመህ ተጫውተኃል?

እሱባለው ይታየው (የሺ)፡- ሦስቱን ተጫውቼያቸዋለሁኝ። ማለትም፡- አንቺ ሆዬ፣ ትዝታ ማይነርና ትዝታ ሜጀር የሚባለውን ቅኝት ተጠቅሜ ተጫውቻለሁ። ጎላ ባይልም ባቲ ማይነርም አለ። ያው እንግዲህ እንደዛ ተጫውቼዋለሁ ብየ ባልደፍርም እንደ ናሙና ግን ሞክሬዋለሁ ማለት እችላለሁ። አምባሰል ቅኝትን ለወደፊት እጫወታለሁ ብዬ አስባለሁ። በአምባሰል ቅኝት ሰርቼው በአልበምም በነጠላ ዜማም ያልወጣ ሥራ አለኝ።

የሆነ ነገር ከተሰማኝና ልቤ የሆነ ነገር ካለኝ ነው የምሰራው። ማንኛውም ስሜት ከተሰማኝ ይሄንን ነገር ዜማ ማድረግ አለብኝ ወይም ደግሞ ግጥም ማድረግ አለብኝ ብዬ ነው የምሰራው።

ታዛ፡- ምን ያህል የዘፈን ግጥምና ዜማ ሰርተሃል?

እሱባለው ይታየው (የሺ)፡- እኔ ጋር ካሉት ከሆነ የምትጠይቀኝ አንድ መቶ ይሆናሉ። ማለት ግጥም ሃምሳ ዜማ ደግሞ ሃምሳ ማለቴ ነው። በኔ ድምጽ ብቻ ከአስራ ሰባት እሰከ ሃያ የሚሆኑት ወጥተዋል። በሌሎች ድምፃውያን ደግሞ አንድ ሃያ የሚሆኑት ወጥተዋል፤ ወይም በመውጣት ሂደት ላይ ናቸው።

ታዛ፡- ግጥምና ዜማ ስትሰራ ምንድነው የሚያነቃቃህ?

እሱባለው ይታየው (የሺ)፡- እውነት ለመናገር በምን እንደምነቃቃ አላውቀውም። እንደ ሁኔታው ነው። የሆነ ነገር ከተሰማኝና ልቤ የሆነ ነገር ካለኝ ነው የምሰራው። ማንኛውም ስሜት ከተሰማኝ ይሄንን ነገር ዜማ ማድረግ አለብኝ ወይም ደግሞ ግጥም ማድረግ አለብኝ ብዬ ነው የምሰራው። ስለዚህ ሁኔታዎች ናቸው ግጥምና ዜማ እንድሰራ የሚያደርጉኝ። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ ሥራ ተብዬ ርዕስ ተሰጥቶኝ በትዕዛዝ እሰራለሁ። በዚህ ጊዜ ሃሳቡን ትይዝና፣ ታሰላስልና ትሰራለህ። ለምሳሌ ሃሳቡ ስለትራፊክ አደጋ አሳሳቢነት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ከተለመደው አተያይ ወጣ ብለህ ልብን ሊነካ በሚችል ምልከታ ትሰራለህ። ካልሆነ ግን ለቀባሪው አረዱት ነው የሚሆነው። አይጥምም፣ ፋይዳ አይኖረውም።

ታዛ፡- የአንጋፋ ድምፃውያንን የዘፈን ግጥሞች ገልብጠህ ታጠና ነበር?

ድምፃዊ እሱባለው፡- አዎ! ይህን ማድረጌ ምን ሰጠኝ መሰለህ፣ በሂደት የራሴን አመንጭቼ እንድጽፍ አስችሎኛል። ህፃናትና ወጣቶች ቲያትር ሁልጊዜ ቅዳሜና እሁድ ፕሮግራም አለ። እና በሆነ ዓመት በዓል ደግሞ የሚቀርቡ ሥራዎች ይቀየራሉ። እና ለህፃናት የሚሆኑ ግጥሞች ሁሌ ትሰራለህ። መድረክ በተቀየረ ቁጥር ስትሰራ ሳታውቀው እያለማመደህ፣ እያለማመደህ ይሄዳል። እውነት ለመናገር ሥነ-ጽሑፉን አልተማርኩም። አንድ ሁለቴ ብቻ በሆነ ሥልጠና በተጓዳኝ ሰልጥኛለሁ። እንደገና በተፈሪ መኮንን ሙዚቃ ት/ ቤት የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሳለሁ በተጓዳኝ ተምሬዋለሁ። እርሱ የሆነ መሠረታዊ እውቀት ሰጥቶኛል።

ታዛ፡- በ‹‹ትርታዬ›› አልበም ላይ አንድ መሳጭ ሙዚቃ አለች በተምሳሌት ስለ ከበሮ፣ ስለ ዋሽንት፣ ስለ ክራር የምትዜም። እስኪ ይህን ግጥምና ዜማ እንዴት እንደሰራኸው ዓውዱን ንገረኝ?

እሱባለው ይታየው (የሺ)፡- በርግጥ ሃሳቡ ብዙ ጊዜ ውስጤ ይብሰለሰል ነበር። አንድ ቀን ሙዚቃ ስቱዲዮ ስገባ ዮሴፍ የሚባል ወዳጄ ኪቦርድ ሲጫወት ደረስኩ። እኔና እሱ ና እስኪ የሆነ ነገር እናድርግ ተባብለን እንደቀልድ ጀመርን። ዝም ብለን እያንጎራጎርን ሰራነው። ማለት ሃሳቡን መጀመሪያ አስቀመጥን። ከዛ ወደ ቤት ሄድኩ። ቤት ሄጄም ማታ ላይ እንደዚሁ የማንጎራጎር ልምድ አለኝ። የሰራኋቸውን ዜማዎች ሪከርድ አድርጌ እንደገና የመስማትና የማንጎራጎር። ከዛ ደጋግሜ ሰማሁት። ሁለት ተምሳሌቶች ብቻ ነበሩት፤ የከበሮውና የክራሩ ብቻ። ግጥሙ መጀመሪያ የሁለቱን ሃሳብ ነበር የያዘው። ከዛ ይህን ነገርማ በደምብ ይዤ ማጠናከር አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፤ የዛሬ አመት ከስድስት ወር አካባቢ ተጠናቀቀ። ቀጥታ ይሄ ሥራ አልበም ውስጥ መግባት አለበት ብዬ ሁላ እንድወስን ያደረገኝ ሥራ ሁኖ ወጣ። እንደነገርኩህ መጀመሪያ እንደቀልድ ዝም ብለን የጀመርነው ሥራ ነው። ብዙ ጊዜ ደግሞ የስሜት ስራዎች ናቸው የሚያሸንፉህና የምታስገባቸው። ሌላ እንደውም አንድ ሙዚቃ ነበር በጣም የምወደው እሱን ትቼ ነው ይሄን ሙዚቃ ያስገባሁት። ብዙ ሰው የወደደው በተለይ ሙዚቃ ሙያ ላይ ያለ ሰው በጣም ወዶታል።

ታዛ፡- አመሰግናለሁ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top