የታዛ ድምፆች

አሳሳቢው አሰባሳቢ ምንነት ሲቃኝ


የመጽሐፉ ርዕስ፡- ኢትዮጵያዊነት፣
አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት
የጽሑፉ ዓይነት፡- ፖለቲካና ወቅታዊ ጉዳይ
ጸሐፊው፡- ዩሱፍ ያሲን
የገጽ ብዛት፡- 437
ዋጋ፡- ብር 131.60
አሳታሚ፡- ኔባዳን አሣታሚ
ቅኝት፡- መኩሪያ መካሻ

በጦቢያ መጽሔት ዓምደኝነቱ የምናውቀው ሀሰን ዑመር የብዕር ስሙን እርግፍ አድርጎ ትቶ በቤት ስሙ መጥቶልናል – አዲስ መጽሐፍ ይዞ። ይህ መጽሐፍ ለኢትዮጵያ አንባቢዎች እንደ ልዩ በረከት የሚቆጠር ነው። “እኛ ኢትዮጵያውያን እንድንበታተን ሳይሆን አብረን እንድንኖር የተፈረደብን ህዝቦች ነን” ሲል፣ “ኢትዮጵያዊነት፣ አሰባሳቢ ማንነት በአንድ ሀገር ልጅነት”ን ጀባ ብሎናል።

 መጽሐፉ በውጭ አገር (አሜሪካ) በ2007 ዓ.ም. የታተመ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ከሁለት ዓመት በኋላ ኅዳር፣ 2009 ዓ.ም. ታትሟል። የውጪውና የኢትዮጵያው ርዕስ አነስተኛ ልዩነት ያሉት ሲሆን፣ “ኢትዮጵያዊነት” የሚለው ቁልፍ ቃል በቀዳሚ ርዕስነት ተመርጧል። ከሁሉም ግን የሀገር ውስጡ ህትመት ከውጩ የሚለየው በቃላት አንጣሪ (አርታዒ) ታሽቶና 35 ያህል ገጾች ተቀንሰውለት በመቅረቡ አንባቢ የደራሲውን ጥልቅና ምጡቅ ሀሳቦች በቀላሉ እንዲገነዘብ በማድረጉ አርታዒው አብዱልሐፌዝ መሐመድ በተጨማሪ ሊመሰገን ይገባል። ዩሱፍን ይበልጥ ልናመሰግን የሚገባን እኛ ኢትዮጵያውያን ላለፉት 50 ዓመታት ሲያነታርከንና ሳያግባባን የኖረን የብሔራዊ ማንነትንና ዜጋ ጉዳይ አበጥሮና ደቁሶ ስለሚያቀርብልን ነው። ዋና ጭብጡ የብሔረሰቦቿን የአብሮነት ቀመር ማፈላለጉና ማግኘቱ የማዕድ ቆፋሪን ድካም ያህል የተለፋበት ስራ ሆኖ ይታየኛል።

ደራሲው ከህይወት ልምዱም ሆነ ከተለያዩ ቋንቋዎች ማለትም፡- ከአማርኛ፣ ከእንግሊዝኛ፣ ከዓረብኛ፣ ከጀርመንኛ እና ከሌሎችም ቋንቋዎች ያካበተውን ዕውቀት መርምሮ ያቀረበልን በመሆኑ፣ ጥልቀትና ምጥቀቱ ይህ ቀረሽ አይባልም። ይህን መጽሐፍ ማንበብ ማለት ታሪክን፣ ማህበራዊ ሥነ-ልቦናን፣ የፖለቲካ ሳይንስንና ለመረዳት የሚያስቸግረውን ብሔራዊ ማንነት በአንድ ላይ ጨምቆ ያቀረበ በመሆኑ ሰፊ የዕውቀት ማሣነቱ አያጠራጥርም።

ዩሱፍ ከኢትዮጵያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ጀምሮ በኢትዮጵያ አብዮት ውስጥ በመሳተፍ፣ በህዝብ ድርጅት ጊዜያዊ ጽ/ቤትና በብሔረሰቦች ኢንስቲቲዩት እንዲሁም በዲፕሎማትነት በማገልገሉ የለማ አእምሮውን በዚህ መጽሐፍ ላይ ተጠቅሟል። ይህም ለአንባቢው እልፍኝ የማይችለው ድግስ ነው።

 ጸሐፊው “የዳር አገር ሰው” ከምንለውና ያውም ከኤርትራ አፋሮች አብራክ ከጢአ የተገኘ ምርጥ ኢትዮጵያዊ በመሆኑ የመሐሉ ሀገር ሰው እርስ በርስ ገመድ ሲጓተት ወይም ድንጋይ ሲወራወር ዩሱፍ ግን የሚጨነቀው ስለአሰባሳቢ ማንነት- ኢትዮጵያዊነት መሆኑ ለኢትዮጵያ ህልውና ለሚጨነቁ ሁሉ እንደ ዓላማ ሰንደቅ ከሩቅ የሚታይ ነው።

 ደራሲው የሚያስጨንቁ፣ የሚጎመዝዙ ዕውነታዎችን በምሳሌዎች፣ በዘፈን ስንኞች፣ በህዝባዊ አባባሎች እያዋዛ ስለሚያቀርብልን ፍሰቱ አይሰለችም። እርግጥ የማንነትን ጥያቄ ለመረዳት አስቸጋሪ ቢሆንም ጉዳዩ አዲስ አይደለም። ግሪኮች ከ429 ዓመተ- ዓለም ጀምረው አቅርበውልናል። እኛ ግን ላለፉት 50 ዓመታት ያህል ብንነጋገርበትም ልንስማማ አልቻልንም። ግሪኮች “የማንነትን” ጥያቄ በሶፎክልስ ቴያትር “በኤዲፐስ ንጉሥ” አማካይነት እንድንረዳ ለማድረግ ሞክረዋል። የቲያትሩ ጸሐፊ ለሀገሩ ህዝብ ማስተላለፍ የፈለገው ስለኩራትና የሥልጣን አደጋዎች ቢሆንም ዋና ትኩረቱ “ማንነት” ላይ ያነጣጠረ ነው። ኢዲፐስ የኮሪን ንጉሥና ንግሥት ልጅ ሳይሆን ማደጎ መሆኑን የኮሪን መልዕክተኛ ያረዳዋል። ትንሹ ልጅ ከቴብዝ በግ ጠባቂ እረኛ ተወስዶ ባይሰጥ ኖሮ እግረ-ዝሆኔው ኢዲፐስ በሕይወት አይተርፍም ነበር።

ከዚያም ኢዲፐስ ማን እንደሆንኩ ማወቅ አለብኝ ብሎ ይጠይቃል። ማንነትን መጠየቅ እጅግ አስፈላጊ ነገር ነው። ይህን የታሪክ እውነት ማንሳቴ የማንነት ጥያቄ ጥንትም ዛሬም እየተጠየቀ እንደሆነና ለመረዳትም አስቸጋሪ መሆኑን ለማሳሰብ ነው።

የእኛን ዩሱፍ ጨምሮ በብሔራዊ ማንነት ጉዳይ ላይ የጻፉት እነስሚዝ፣ ግራምቪ፣ ጎፍማንና ግሪንፊልድ የሚያነሱት ጥያቄ “ህዝቦች ለሀገራቸው፣ በተጨማሪም ለቤተሰባቸው፣ ለመደባቸውና ለኃይማኖታቸው ታማኝ የሚሆኑት ለምንድን ነው? መቼስ ነው ጤናማ የሆነ ብሔራዊ ማንነት ወደ መርዛማ ብሔርተኝነት የሚቀየረው? ለዘመናችን ግጭቶች ዘውጌነት እንዴት መነሻ ይሆናል? የቅኝ ግዛትና የብዝሃ-ዘውጌ ኢምፓየሮች ሲወድቁ ሀገራት እንደገና በአዲስ ዲዛይን (ሥሪት) ይፈጠራሉን? ሀገርስ ማለት ምንድን ነው? ለመሆኑ ብሔራዊ ማንነት ይገነባል? ይታለማል (imagined) ወይስ ቀድሞ የተፈጠረ (pre-existing) ክስተት ነው? ከሁሉም በላይ ዩሱፍ ከላይ የቀረቡትን ጥያቄዎች በተለያዩ መንገዶች ያነሳና አንድ ወሳኝ ጥያቄ ይጨምራል። “የኢትዮጵያዊነት ማጠንጠኛና ማሰሪያ መሠረታዊ ሕግ እንዴት መቆም አለበት?” ሲል ይጠይቃል። የዩሱፍ የማንነት ጥያቄ ነጽሮት ግልጽና ያልተወሳሰበ ነው። ስሚዝ፣ ሩስቶው ወይም ዶሽ ከሚተረጉሙትና ከሚሰጡት መስፈርት የተለየም አይደለም። ብሔራዊ ማንነት ታሪካዊ የሆነ ግዛት፣ የጋራ የሆነ ሥነ-ተረትና ታሪካዊ ትውስታዎች፣ የጋራ የሆነ ህዝባዊ ባህልና በተወሰነ ግዛት ውስጥ እየተንቀሳቀሱ የመስራት መብት የተጠበቀበት የጋራ ኢኮኖሚ አራቱ ዋነኛ መስፈርት ናቸው። ዩሱፍ ማንነት እንዴት እንደሚመጣና በምን ሁኔታ ልንተገብረው እንደምንችል እንደ ሥልጡን መካኒክ ፈታትቶ የሚያሳየን። አልፎ ተርፎም ዩሱፍ ኢትዮጵያን ካለ ብሔረሰቦቿ፣ ብሔረሰቦቿን ካለ ኢትዮጵያ ማሰብ አይቻልም። “ኢትዮጵያውያን አብረን እንድንኖር የተፈረደብን ሕዝቦች ነን” ሲል መፍትሔውን ራሳችን እንድንሻ ያሳስበናል። መጽሐፉ በ13 ሰፋፊ ክፍሎች የተሸነሸነ በመሆኑ አንባቢ በሰከነ አእምሮ ሊመረምረው ይገባል እላለሁ። ታሪክን በዛሬው መነጽር መመልከት የተዛባ ፍርድ የሚያሰጠን ነውና። ደራሲው “አብዛህነትን

መቀበል” አስፈላጊነቱን እያሳሰበ “አንድነት በእኩልነት” የሚለው መርህ ይበልጥ መሠረት እንዲይዝ ያስፈልጋል በማለት ይመክራል። ጽሑፉ ሠፊ ስፍራ ሰጥቶ ስለ አማራ፣ ኦሮሞና ትግራይ ልሂቃን ኃላፊነት ከማብራራቱም በላይ የኦሮሞ ብሔርተኝነት፣ የማንነት ፖለቲካና ተፈታታኝ ተግዳሮቶችን በዝርዝር ያቀርባል። ደራሲው ሳሙኤል ጆንሰን “ብሔርተኛነት የተረገሙ ወስላቶች መሸሸጊያ ነው” ያለውን ጠቅሶ ንጽሮታዊነታችንን እንድንሰጥ ነው ዩሱፍ የሚጠይቀው።

 ዩሱፍ የኦሮሚያንና የኦሮሞን ጥያቄዎች ሁነኛ ቦታ ሰጥቶ ይተነትናል። ሜጫና ቱለማ ከ1962 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ ከዚያም ኦነግ በ1973 ከተመሠረተና ፖለቲካዊ ርዕዮቱን በስሜትና በእንቅስቃሴ ማቅረብ ከጀመረበት

“ጋናውያን ናይጄሪያውያን ወይም ኬንያውያን ተዳቅለውም ቢሆን የብሪታኒያ ኢምፓየር ንጉሥና ንግሥቶች ለመሆን አልመው አያውቁም። የተዳቀሉ ኦሮሞዎች ግን የንጉሠ-ነገሥቱ ንጉሦችና ንግሥቶች ለመሆን በቅተዋል”

ጊዜ አንስቶ የኦሮሞ ብሔርተኝነት እንዴት እንደተፈጠረ ያሳየናል። የኦነግ ባህላዊ ገጽታና ወደ ፖለቲካዊ ማንነት ያደረገው ጉዞ ተፈታታኝ ተግዳሮቶች እንደገጠሙት ይተነትናል። ሰባት ልንወያይባቸው የሚገቡ አንጓ ችግሮችም ተዳሰውበታል። በተለይ በመጽሐፉ በግልፅ የተጠቀሰ ባይሆንም የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለው የቆየ ትስስር ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ያሳስባል። መረራ ጉዲና (ዶ/ር) በአንድ ወቅት እንደጻፈው የኦሮሞና የሌሎች ኢትዮጵያውያን ትስስር የደም ነው። እንደ ጋናና ናይጄሪያ ከቶ የሚታይ አይደለም። የእንግሊዟ ንግሥት ጋናዊ፣ ኬንያዊ ወይም ናይጄሪያዊ አላገባችም። የኢትዮጵያ ነገስታት ግን ኦሮሞዎችን አግብተዋል። ቴዎድሮስ፣ ምኒልክና ኃይለሥላሴ ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። በተመሳሳይ መልኩ ጋናውያን ናይጄሪያውያን ወይም ኬንያውያን ተዳቅለውም ቢሆን የብሪታኒያ ኢምፓየር ንጉሥና ንግሥቶች ለመሆን አልመው አያውቁም። የተዳቀሉ ኦሮሞዎች ግን የንጉሠ-ነገሥቱ ንጉሦችና ንግሥቶች ለመሆን በቅተዋል። ለዚህም ጥሩ ምሳሌዎቻችን ኢያሱ፣ ኃይለሥላሴ፣ የወሎው ንጉሥ ሚካኤልና የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሃይማኖት ናቸው። እስከዛሬም ድረስ በከፍተኛ የፖለቲካና ወታደራዊ ወንበር ላይ የተቀመጡት በርካታ ኦሮሞዎች መኖራቸውን መካድ አይቻልም። እርስ በእርስ እኔ፣ አንተ ትብስ ከመባባል ጃን ዛሆሪክ እንዳለው “ዲሞክራሲያዊ ሞዛይክ” መፍጠር ይኖርብናል።

ይህን መጽሐፍ በማንበብ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች፣ ልሂቃኖች፣ ዲያስፖራው የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን የሚሰሩ ሁሉ እንደ ዳዊት ሊደግሙት፣ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ እና ቅዱስ ቁርዓን ሊመረምሩት ይገባል። ኢትዮጵያዊ ዜግነት ስለመፍጠር መጣር አለብን ሲል ዩሱፍ ይመክራል።

ዩሱፍ ልንመልሳቸው የሚገቡ ጥያቄዎችን አልፎ አልፎ ጣል ያደርጋል። መጽሐፉን ካነበብን በኋላ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ እንሞክር። ያለፈን ታሪክ በዛሬ መነጽር ማየታችን ትክክለኛ ፍርድ እንዲኖረን ያደርጋል? ኢትዮጵያን ያለ ብሔረሰቦቿ፣ ብሔረሰቦቿን ያለ ኢትዮጵያስ ማየት ይቻላልን? ደራሲው አብረን ለመኖር የተፈረደብን ነን ይላል። ዕውን አብረን ለመኖር ተፈርዶብናል? የሙስሊም ወንድሞቻችን ሥፍራስ ኢትዮጵያ በምንላት ሀገር ውስጥ ምን መሆን አለበት? ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ማንነትን ለመገንባት ከልሂቃኖቻችን ምን ይጠበቃል? መልሱን ከመጽሐፉ ንባብ በኋላ፡፡

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top