አድባራተ ጥበብ

የጠቢባን ሮሮ

‹‹የተወሰኑ የመንግሥት ኃላፊዎችና የነጋዴዎች ጥምረት ችግር ጥሮብናል››

ኤሊያስ መልካ

ለቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ለማድረግ የወጣው ዓዋጅ (ቁጥር 410/1996) ስለ አስፈላጊነቱ ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶችን ያስቀምጣል። አንደኛው፣ ሥነጽሑፍ፣ ኪነጥበብና ተመሳሳይ የፈጠራ ሥራዎች የአንድን ሀገር ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ ልማትን በማፋጠን ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው የሚበረታቱበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው፤ ይላል።

ሁለተኛው፣ ሥነጽሑፍን፣ ኪነጥበብንና ተመሳሳይ የፈጠራ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ ለተዛማጅ መብቶች ሕጋዊ እውቅና መስጠትና ጥበቃ ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን አስቀምጧል። እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ሁለት ዓበይት ምክንያቶች ከዓዋጁ መጽደቅ ጋር ተዳምረው፤ ሥነጽሑፍና ኪነጥበብ ስላላቸው ፋይዳና ሊቀመጥላቸው ስለሚገባው የተጠቃሚነት የሕግ ማዕቀፍ ግልጽ እውቅና የሰጠ ነው- ዓዋጁ።

ሌላው የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ማሻሻያ ዓዋጅ ቁጥር 872/2007 ዓ.ም. የወጣበት መሠረታዊ ምክንያት፣ ባለመብቶች በተደራጀና በተጠናከረ አግባብ መብቶቻቸውን ማስተዳደር የሚችሉበት አመቺ ሁኔታ እንዲኖር ለማገዝ ነው።

 በዓዋጁ “ተዛማጅ መብት” ማለት፣ ከዋኝ፣ ድምፅ ‹ሪከርዲንግ›፣ ፕሮዲዩሰርና የብሮድካስቲንግ ድርጅት በሥራው ላይ ያለው መብት ነው።

 የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ዓዋጅና ማሻሻያ ዓዋጁን ወደ ሥራ ለማስገባት በተደረጉት ሂደቶች መነሻነት፣ በባለድርሻ አካላት የተለያዩ እምቅ ፍላጎቶች የተነሳ በተፈጠረ ውዝግብ፣ ጉዳዩ በበርካታ መገናኛ ብዙኃን የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ከርሟል። በዚህ ዘገባም በዓዋጁ በሰፈረው የማኅበራት አደረጃጀትና የጋራ አስተዳደር ምስረታና ተያይዘው በተነሱ ቅሬታዎችና ውዝግቦች ላይ የሚያተኩር ቃለ ምልልስ ይዘናል።

 እንደ ማሳያ እንዲሆንም በሙዚቃው ኢንዱስትሪ የተሰማሩ ባለሙያዎች ከሙያ ማኅበርና ከጋራ አስተዳደር ማኅበር ምስረታ ጋር በተያያዘ የገጠማቸውን ተደራራቢ ችግሮች ያካፍለን ዘንድ ታዋቂውን የሙዚቃ አቀናባሪ ኤሊያስ መልካን የዚህ ዕትም እንግዳችን አድርገነዋል። መልካም ንባብ

ታዛ፡ለቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ለማድረግ የወጣ ዓዋጅ አለ፤ የሙዚቀኛ ኮፒ ራይት ሶሳይቲን ለመመስረት ያቀረባችሁትን ጥያቄ ከዓዋጁ አንፃር እንዴት ነው የምትረዱት?

 ኤሊያስ መልካ፡- የወጣው ዓዋጅ የዓለም ዓቀፉን አሰራር ከግምት ያስገባ በመሆኑ መብታችንን የሚፃረር ድንጋጌ የለውም። በእኛ በኩል ጥሩ ዓዋጅ ነው። ለሁሉም የሙያ ዘርፍ ተገቢውን ሽፋን የሰጠ ዓዋጅ ነው። ሆኖም ወደ ሕግና ወደ አደባባይ መብታችንን ለማስከበር አቤት ለማለት የተገደድንበት ዋናው ምክንያት ዓዋጁ የሰጠንን መብት ለማስፈጸም ጥያቄ ስናቀርብ፣ ለአሰራር አመቺ አይደለም፤ በዓዋጁ መሠረትም አያዋጣችሁም ስለተባልን ነው። ዓዋጁ የተረቀቀው የዓለም ዓቀፉን አሰራርና ደንብ መነሻ በማድረግ እንደሆነ በርከት ያሉ ውይይቶች ላይ ስንሳተፍ የተገለጸ ጉዳይ ነው። እንዲሁም፣ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያለው አሰራርና ተሞክሮ የሚያሳየው ለምሳሌ በኬንያ፣ በናይጄሪያ፣ በጋና፣ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝና በሌሎች አገራትም እራሳቸውን የቻሉ የሙዚቃ ኮፒ ራይት ሶሳይቲ የሚባሉ አሉ። በእኛ ሀገር ሲደርስ በዓዋጅ ባይከለከልም፣ አስፈፃሚው የመንግሥት አካል የሙዚቃ ኮፒ ራይት ሶሳይቲ አትመሰርቱም የሚለን ከምን የሕግ መነሻ እንደሆነ ግልፅ አይደለም። ለምን?

ታዛ፡የሙዚቃ ኮፒ ራይት ሶሳይቲን እንዳትመሰርቱ የከለከላችሁ የመንግሥት አካል ማነው?

ኤሊያስ ፡- በተቋም ደረጃ የአዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤትና የሳይንስና ቴክሎጂ ሚንስቴር ሲሆኑ፣ በተጨማሪም የሙዚቃ ሥራዎችን የሚያሳትሙ፣ የሚያከፋፍሉና የሚሸጡ ነጋዴዎች ናቸው። እነዚህ ሦስቱ ጥምረት ፈጥረው ነው መቋቋም የለበትም የሚሉት። ለምን እንደሚከላከሉ በመከራከሪያነት የሚያቀርቧቸው ነጥቦች በየጊዜው ተለዋዋጭና አሳማኝ አይደሉም። በመጀመሪያ ያቀረቡት መከራከሪያ፣ ዓዋጁ የሙዚቃ ኮፒ ራይት ሶሳይቲ ብቻውን እንዲመሠረት ፈቃድ አይሰጥም የሚል ነበር። በእኛ በኩል ዓዋጁ የሚሰጠን መብት እንዳለ በተገቢ ሁኔታ አስረዳናቸው። ባቀረብነው የመከራከሪያ ነጥቦች መተማመን ላይ ደረስን። በተደረሰው የጋራ ግንዛቤና መተማመን ወደ ሥራ ለመግባት ስንንቀሳቀስ የያዙትን ድብቅ ፍላጎት ወደ ጎን ማድረግ ስላቃታቸው ወይም አበው እንደሚሉት “አዛኝ ቅቤ አንጓች” ሆነው፤ “ብቻችሁን ብትደራጁ ትጎዳላችሁ” ብለውን አረፉት። (ይህ የምልህ ሁሉ በድምጽና በቪዲዮ ሪከርድ የተደረገ በፋይል ያለ ነው።) በተደጋጋሚ የደረስንበት ስምምነት እየተቀየረ በመቸገራችን ፋይል ለመያዝ ተገደናል። እስካሁንም ድረስ በአዕምሯዊ ጥበቃ ጽ/ቤትና በነጋዴዎች መካከል ያለው ሕግን የተላለፈ ግንኙነት እልባት አለማግኘቱ እንቅፋት ሆኖብናል።

ታዛ፡- የሙዚቃ ኮፒ ራይት ሶሳይቲ ራሱን ችሎ ቢቋቋም በነጋዴዎቹ ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ምንድን ነው?

ኤሊያስ ፡- “ነጋዴዎቹ” ሲባል በተራ ንግድ አግባብ እንደሚቀመጠው አይደለም። ከፍ ባለ ደረጃ በማኅበር የተመሠረተው፣ መጠሪያውም “የኦዲዮ- ቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር” ነው የሚባለው። የዚህ አይነት መጠሪያ ስም ያለው ማኅበር በፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ ለተሰማሩ ድርጅቶች የሚሰጥ ነው። ይህም ሲባል፣ በፊልም ዝግጅት ውስጥ የፊልም ፕሮዲዩሰሩ ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ፤ ፊልሙም የሚጠራው በፕሮዲዩሰሩ ስም ነው። በፊልም ዝግጅት ውስጥ ስክሪፕት ጸሐፊው፣ ዳይሬክተሩ፣ የካሜራ ባለሙያው፣ የዜማ ደራሲው፣ የሜካፕ ባለሙያው፣ ተዋንያንና ሌሎች ሥራዎችን የሚሰሩ ባለሙያዎች ይሳተፋሉ። እነዚህ ባለሙያዎች ከፕሮዲዩሰሩ ጋር በሚያደርጉት ውል መሠረት ተከፋይ ይሆናሉ። አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ክፍያ አሰራር ስለሚስተናገዱ፣ ፊልሙን በተመለከተ ፕሮዲዩሰሩ የኢኮኖሚ መብት ባለቤት ይሆናል። የሙዚቃ ዝግጅት አሰራር ሂደት ግን ለየት ያለ ነው። በሙዚቃ አዘገጃጀት ሂደት፣ “የድምፅ ሪኮርዲንግ ፕሮዲዩሰር” ተብሎ ነው የሚጠራው። አንድ የባህል ሙዚቃ ለመስራት ያለውን ሂደት በምሳሌነት እንመልከተው። ይኸውም፣ ይልማ ገብረዓብ ግጥም ቢያዘጋጅልኝ፣ አበበ መለሰ ዜማ ቢደርስልኝ፣ ዳዊት ይፍሩ ቢያቀናብርልኝ፣ ማህሙድ አህመድ ቢዘፍንልኝ ብለው የሚያስቡት ባለሙያዎች ናቸው፣ የድምፅ ሪኮርድ ፕሮዲዩሰር ተብለው የሚወሰዱት። በእኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ ከላይ በሰፈረው መልኩ ሙዚቃን የሚያዘጋጁት ድምፃውያን ናቸው። ድምፃውያን ባይኖሩ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የሙዚቃ ካሴት አይዘጋጅም፤ አሳታሚም፣ አከፋፋይም፣ ሻጭም ባልነበሩ። ሙዚቀኞቹ ናቸው ፕሮዲዩሰሮቹ። የድምጽ ሪኮርዲንግ ሥራን የሚያመነጩትና ኃላፊነት ወስደው የሚሰሩት እነሱው ናቸው። በፊልሙም ቢሆን ፕሮዲዩሰር ማለት የኦዲዮቪዥዋል ሥራ ለመስራት ሃሳብ የሚያመነጭና ሥራውን በኃላፊነት የሚሰራ ሰው ነው። ፕሮዲዩሰር ሃሳብ ከማመንጨትና ከመፍጠር ጋር የተያያዘና ባለቤትነትን የሚያሳይ ትርጓሜ እንጂ በምንም መልኩ ፈጠራን ከማሳተም ጋር ተያያዥነት የለውም። ማሳተምም የፈጠራ ሥራ አይደለም። ፈጠራንም ማሳተም፣ ፈጠራ አይደለም። ከላይ በቀረቡት ትንተናዎች መሠረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት እንዲያውቁልን የምንፈልገው፣ በኢትዮጵያ የተቋቋመው የኦዲዮቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር፣ የኦዲዮቪዥዋል ፕሮዲዩሰር ያለውን ኢኮኖሚያዊ (የባለቤትነት) መብቶች በተመሳሳይ መልኩ በሙዚቃ ላይ ለመተግበር ያላቸውን ፍላጎት ነው። የኢትዮጵያ ኦዲዮቪዥዋል ማኅበር፣ በኢትዮጵያ የሙዚቃኢንዱስትሪ ውስጥ ከአሳታሚነት የዘለለ ሚና የለውም። አሳታሚ የሆነ አካል፣ የድምፅ ሪኮርዲንግ ሥራ ለመስራት ሃሳብ ያመነጨውንና ሥራውን በኃላፊነት ተከታትሎ የሠራውን አካል መብት ሊወስድ አይችልም። በየትኛውም የሀገሪቷ ሕግ አሳታሚ የአዕምሮ ፈጠራ ሥራዎችን መብት ሊወስድ አይችልም። በአሳታሚውና በፈጠራ ባለመብቶች መካከል ያለው ግንኙነት ተራ የንግድ ግንኙነት ብቻ ነው። ይኸውም፣ በተፃፈው የሕግ ስምምነት መሠረት ማሳተም፣ ማከፋፈልና መሸጥ ነው። ከባለቤትነት መብት ጋር ፈጽሞ አይገናኝም።

ታዛ፡- የኦዲዮቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር በዚህ ረገድ የሚያቀርቡት ሃሳብ በዓዋጁና በአመክንዮ ያልተደገፈ ነው ካሉ፣ ከመንግሥት አካላት ጋር ጉድኝት መፍጠራቸው ምን ትርፍ ያስገኝላቸዋል?

ኤሊያስ ፡- የአሳታሚዎቹን ፍላጎት ለማወቅ ቀላሉ መንገድ የኦዲዮቪዥዋል ፅንሰ ሃሳብ የሚቀመጠው፣ ከፊልም ጋር በተያያዘ ብቻ ነው። ፊልም ከሌለ ኦዲዮቪዥዋል የሚባል ነገር የለም። በአንፃሩ የድምፅ ሪኮርዲንግ የሚለው ፅንሰ ሃሳብ የሚገናኘው ከሙዚቃ ጋር ብቻ መሆኑን ልብ ይሏል። ስለዚህም፣ የአሳታሚዎች ማኅበር፣ የፊልምና የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን ጠቅልሎ ለመቆጣጠር በዓዋጅ ተነጣጥለው በግልፅ የተቀመጡ መብቶችን በአንድ ከረጢት ውስጥ ከቶ አላስፈላጊ የጥቅም ትስስር ለመፍጠር ከአንዳንድ የመንግሥት አካላት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ እየሰራ ይገኛል። በጣም አስደንጋጩ ነገር ደግሞ የሙዚቃ ሥራዎችን በማሳተማቸው ብቻ የፊልም ፕሮዲዩሰር ያለውን አይነት የባለቤትነት መብት ባልተገባ ቡድን ተደራጅተው ለመውሰድ መፈለጋቸው ነው። የማኅበራቸው ሥጋት መነሻም እኮ የሙዚቃ ኮፒ ራይት ሶሳይቲ ራሱን ችሎ ከተቋቋመ፣ ከኦዲዮቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር ስለሚወጣ የለመዱት ሕገ ወጥ ጥቅም ስለሚያመልጣቸው ነው። ይህ ከመሆኑ በፊት የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ላይ ተጠምደዋል።

ታዛ፡- በዚህ ደረጃ መብታችሁን ከተረዳችሁ፣ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥ የሆኑ የመንግሥት ተቋማትን እንዴት ማሳመን ያቅታችኋል?

 ኤሊያስ ፡- የማሳመን አቅም አይደለም ያጣነው፤ ጥቂት ግለሰቦችን ለመጥቀም የተቀመጡ የመንግሥት ኃላፊዎችን ነው ማሳመን ያቃታን።

ታዛ፡- የመንግሥት ኃላፊዎች በሕግ አግባብ አያስተናግዱንም እያልክ ነው?

ኤሊያስ፡- ምን ጥያቄ አለው፤ አዎ። ምክንያቱም መንግሥት ፖሊሲ ሲያወጣ ግለሰቦችን ማዕከል አድርጎ አይደለም። የፖሊሲ ውይይትም ሲደረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ እንዲሆኑ የሚፈለገው፣ የሚረቀው ፖሊሲ በዘርፉ ያሉ ጉዳዮችን በስፋትና በጥልቀት እንዲመለከታቸውና እንዲያካትታቸው ነው። ዓዋጅም እንዲሁ ነው፣ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ባለድርሻ አካላትን በሙሉ የመብታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው። ስለዚህም፣ አንድ የመንግሥት ኃላፊ ዓዋጁን ወደ አፈፃጸም ሲያወርደው፣ ሁሉም አካላት በተሰጣቸው መብት እንዲጠቀሙ የማድረግ ኃላፊነት አለበት። እንዲሁም፣ በምንም መመዘኛ መብትን በድርድር ወይም መብቶችን ጨፍልቆ አንድ ለማድረግ ወይም በተቀመጡ መብቶች ላይ የመንግሥት ኃላፊ አደራዳሪ ሆኖ ለመቅረብ አይችልም። በሕግ የተቀመጠን መብት፣ ለባለመብቱ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መስጠት ብቻ ነው ከአንድ የመንግሥት ኃላፊ የሚጠበቀው። በእኛ በኩል የገጠመን አስገራሚ ነገር ነው። የመንግሥት አካላት የተባሉት፤ “አንድ ብትሆኑ መልካም ነው፣ አንድነት ኃይል ነው፣ በጋራ ብትሆኑ ትጠቀማላችሁ” እያሉ በሕግ የተሰጡንን መብቶች እነሱ ወደፈለጉት ከረጢት እጃችንን ጠምዝዘው ለመክተት ሲተጉ ነው ያየናቸው። በእኛ በኩል በተደጋጋሚ የገለጽነው፣ መብታችንን የሚጨፈልቅ አንድነት አያስፈልገንም። አንድነት በሚል ሽፋን መብታችንን ጨፍልቃችሁ የአሳታሚ ማኅበሩን ለተቆጣጠሩት ነጋዴዎች ሲሳይ ልታደርጉን መፈለጋችሁ ትዝብት ላይ ከመውደቃችሁ ውጪ የምታመጡት ነገር የለም። ለከፍተኛ የመንግሥት አካላት አሳውቀን መብታችንን እናስከብራለን ብለናቸዋል። በጣም የሚገርመው ሙዚቀኛ ወይም ሠዓሊ ወይም ከኪነጥበብ ዘርፍ በአንዱ ባለሙያ ላልሆኑ ሰዎች የልብ ልብ ሰጥተው፣ በእኛ ላይ ከሳሽና ፈራጅ አለቃ አድርገው አስቀምጠዋቸዋል። አንዳንዶቹ ደግሞ የሌሉበት የኮሚቴ ሥራ የለም፣ በሽታም ይመስልሃል።

ታዛ፡- ፖሊሲው ሲዘጋጅ የመሳተፍ ዕድል አግኝታችሁ ነበር?

ኤሊያስ፡- ብትሳተፍም የተለየ ነገር አታመጣም። ድፍረት አይሁንብኝ እንጂ፣ በዚህ ሀገር ፖሊሲ ማርቀቅ፣ ዓዋጅ ማውጣት፣ የማስፈጸሚያ ደንብ ማዘጋጀት የሕፃን ልጅ ጨዋታ እስኪመስል ድረስ የምትታዘበው ነገር አለ። ለምሳሌ ባህልና ቱሪዝምን ብትወስድ አንዳንድ ሥራዎች የተወሰኑ ሰዎችን ለመጥቀም ሲባል የተቀመጡ ሕጎችን ጥሰው ሲሄዱ ታያለህ። ፖሊሲ ይረቀቃል … ዓዋጅ ይወጣል … የማስፈጸሚ ደንብ ይወጣል እየተባለ በየሆቴሉ ስብሰባ ትጠራለህ። በቅርቡ እንኳን ለአስራ ሰባት ቀናት ከአዲስ አበባ ውጪ የተጠራ ስብሰባ አለ። በስብሰባው ብትሳተፍም የተለየ ነገር አታገኝም። የተወሰኑ ሰዎች በ power point የተወሰኑ ነጥቦችን ያቀርባሉ። የተወሰኑ ተሳታፊዎች ሃሳብ እንዲሰጡበት ወይም ጥያቄ ካላቸው እንዲያቀርቡ ይደረጋል፤ ስብሰባው ይጠናቀቃል። አበል ይታደላል፤ አፅድቀው ይለያያሉ። አስፈላጊ ከሆነ የምናምን ተወካዮች ተብለው በራሳቸው መንገድ ኮሚቴ መርጠው አስወስነው ይበተናሉ። እግዚአብሔር ያሳይህ፣ በሥራ የተጠመደ ሰው ለአስራ ሰባት ቀናት ሥራውን ጥሎ ከአዲስ አበባ ውጪ ይሰበሰባል። በነዚህ አይነት ስብሰባዎች ላይ ዘወትር የሚሳተፉ የሚታወቁ ሰዎች አሉ። አብዛኛውን ጊዜ ሥራ የላቸውም። በሥራ በተጠመደው አካል ላይ ውሳኔ አሳልፈው ኮሚቴም ሆነው ተመርጠው ይመጣሉ። መንግሥት ካለበት ኃላፊነት አንፃር ከወሰድከው ግን የባለድርሻ አካላትን መብት በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ለማካተት መብቱ የሚገባቸው አካላት በሙሉ በስብሰባ ውስጥ ተሳታፊ መሆን አይጠበቅባቸውም። ምክንያቱም መንግሥት የሁላችንም ነው ብለው ስለሚያምኑ።

ታዛ፡- የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኮፒ ራይት ሶሳይቲ የጋራ አስተዳደር ማኅበርን በምን ዓይነት መንገድ ነው ያዋቀራችሁት?

ኤሊያስ ፡- በዓዋጁ ላይ የሰፈረው የጋራ አስተዳደር ማኅበር በሥሩ

“በኢትዮጵያ ውስጥ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ባለቤቶችና ዘርፎች ምን ያህል ናቸው? ሁሉንም መብቶችና ዘርፎች በአንድ ጨፍልቆ ማስተዳደሩስ የእነማን ፍላጎት ነው? በርግጠኝነት የመንግሥት ፍላጎት አይደለም። የተወሰኑ የመንግሥት ኃላፊዎችና የነጋዴዎች ፍላጎት ስለመሆኑ ግን ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው”

የሚያቋቁማቸው የዘርፍ ማኅበራት ቁጥር ከሦስት ማነስ የለበትም ሲል ደንግጓል። ይህ ሲሆን ብቻ ነው ማኅበሩ ሮያሊቲ (አስበ ድርሰት) መሰብሰብ የሚችለው። ከዚህ አንፃር ሙዚቃ የሚያካትተውን ስንመለከት ግጥም፣ ዜማ፣ ቅንብር፣ መከወንና ድምፅ ሪኮርድ ማድረግ አሉበት። ስለዚህ ሙዚቃ ተዛማጅ ነው፤ ከሦስት በላይ ዘርፎችም አሉት። ከዚህ በፊት የሙዚቀኞች ማኅበር ሁሉንም ዘርፎች አንድ ላይ አጭቆ የያዘ ነበር። አሁን እኛ በሦስት ዘርፍ አዋቅረነዋል። አንደኛው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ሥራ ከዋኞች ማኅበር፣ ሁለተኛው የኢትዮጵያ የሙዚቃ ሥራ አመንጪዎች ማኅበር፣ ሦስተኛው የኢትዮጵያ የድምፅ ሪኮርዲንግ ፕሮዲዩሰር ማኅበር ናቸው። ሦስቱም ማኅበሮች በፌደራል ደረጃ የተዋቀሩ በመሆናቸው ነው፣ የኢትዮጵያ ማኅበራት የተባሉት። በበጎ-አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት ኤጀንሲ በኩልም ሕጋዊ እውቅና አግኝተዋል። የጋራ አስተዳደር ማኅበር ማቋቋም ይችላሉ።

ታዛ፡- የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር “የኢትዮጵያ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር” የሚል ማኅበር ካቋቋሙ፤ በምን መልኩ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኮፒ ራይት ሶሳይቲ የጋራ አስተዳደር ማኅበር በተናጠል ሥራዎችን ሊያከናውን ይችላል?

ኤሊያስ፡- በነገራችን ላይ በዓዋጅ የተሰጡ መብቶችን በመጨፍለቅ የተካኑ ናቸው። የኦዲዮቪዥዋል አሳታሚዎች ማኅበር የሚባለው የድምፅ ሪኮርዲንግ ፕሮዲዩሰር የኢኮኖሚ መብቶችን እንዴት እንደጨፈለቀው ለማስረዳት ሞክሬያለሁ። የተወሰኑ አካሎችን ከሕግ በላይ የመጫን ፍላጎት ጥሩ ማሳያ ነው። የጋራ አስተዳደር ማኅበር አመሰራረት ላይም ተመሳሳይ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ጫና በስፋት ይንጸባረቅበታል። በቀላሉ ለማሳየት በኢትዮጵያ ውስጥ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ባለቤቶችና ዘርፎች ምን ያህል ናቸው? ሁሉንም መብቶችና ዘርፎች በአንድ ጨፍልቆ ማስተዳደሩስ የእነማን ፍላጎት ነው? በርግጠኝነት የመንግሥት ፍላጎት አይደለም። የተወሰኑ የመንግሥት ኃላፊዎችና የነጋዴዎች ፍላጎት ስለመሆኑ ግን ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው። የኢትዮጵያ የሙዚቃ ኮፒ ራይት ሶሳይቲ የጋራ አስተዳደር ማኅበር ከተመሠረተ ችግሩ ምንድን ነው? የሚለውን መመልከት ተገቢ ነው። ቡድንተኛ ውበችግር መልክ የሚያስቀምጠው፣ ሁሉም ተዛማጅ ዘርፎች የራሳቸውን የጋራ አስተዳደር ማኅበር ያቋቁማሉ። ይህ ሲሆን፣ “የኢትዮጵያ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር” በሚል ሽፋን ሥልጣኑን ጠቅልሎ የያዘው ቡድን ይበተናል። በተጨማሪም በሚመለከተውም በማይመለከተውም ሮያሊቲ በመሰብሰብና በማከፋፈል ያልተገባ ቡድንተኝነት ውስጥ ለመሰማራት የወጠኑት እቅድ ይከሽፋል። ከተራ የሙያ ሥልጠና እስከ ውጭ አገር ጉዞ በቡድን እየተደራጁ ሊሳፈሩበት ያቀዱት ማኅበር ከእጃቸው ያመልጣል። በሕግ አግባብ እንዲመራም ዕድል ይፈጥራል። ባለሙያዎች በዓዋጅ የተሰጣቸውን መብት እንዲያጣጥሙት በር ይከፍትላቸዋል። አንባቢያን እንዲገነዘቡት የምፈልገው የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ኮፒ ራይት ሶሳይቲ እንድናቋቁም ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ስምምነት ላይ የደረስነው ዓዋጁም መብቱን ስለሚሰጠን ነው። በጎን ግን የኢትዮጵያ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማኅበር ተቋቁሟል ይላሉ። ዓዋጁ ላይ የጋራ አስተዳደደር ማኅበሩ ሥልጣንና ተግባር ተብሎ የተዘረዘረውን ስትመለከተው የማይሰበስበው ሮያሊቲ የለም፤ ምክንያቱም ስያሜው የኢትዮጵያ የቅጅና ተዛማጅ መብቶችየጋራ አስተዳደር ማኅበር ስለሚል ነው። “የኢትዮጵያ” በሚል የወል ስም የሚሰጥም የሚወሰድም መብት የለም። መብት በዘርፍ፣ በሙያ ወይም በአደረጃጀት የሚሰጥ እንጂ በወል የሚሰጥ ነገር አይደለም።

ታዛ፡- አመሰግናለሁ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top