አድባራተ ጥበብ

የስም አወጣጥ ጥበብ በፊልሞቻችን

ዛሬ በየመንገዱ ላይ የማያጡት እለታዊ ክስተት የአዳዲስ ፊልሞች ፖስተር ነው:: ውብ ውብ የሆኑ ኮረዳዎች እና ወጣቶች የማይጠፉባቸው እነዚህ ፖስተሮች ብዙውን ጊዜ እጅግ ማራኪ የሆነ ርዕስ አላቸው:: በጣም ጠሪ፣ በጣም አጓጊ፣ በጣም ጋባዦች ናቸው:: በሀገራችን ፊልም ኢንዱስትሪ ውስጥ አንዱ ያደገ ነገር ይህ ፊልሞችን የመሰየም ጥበብ ነው:: ጥበብ ያልኩበት ምክንያት ርዕስ ማውጣት በጣም ከባድ ፈተና መሆኑን ስለምረዳ ነው:: የሚወጣ ርዕስ በአንድ በኩል የተሰራውን ፊልም ገላጭ እንዲሆን ሲፈለግ በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎችን የሚያጓጓ ሆኖ እንዲገኝ ያስፈልጋል:: ድርሰት ምጥ ነው እንደሚሉት ሁሉ ድርሰትን መሰየምም ፈተና ነው:: ሆኖም አሪፍ የፊልም ርዕስ አሪፍ ጋባዥ እንጂ አሪፍ ፊልምን አመላካች ላይሆን ይችላል:: በንጉሱ ዘመን አንድ የጊዜው ምሁር በርዕሱ ተስበው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴያትር አንድ ቴያትር ተመልክተው አልወደዱትም:: ታዲያ ንዴታቸውን አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ሲገልጹ የትችታቸውን ርዕስ እንዲህ አሉት ˝ስምን መልአክ ያወጣዋል˝::

እኔም እነዚህ ርዕሰ መልከ መልካም ፊልሞች እንዲህ እንዳይሆኑ ነው ምኞቴ:: ያላየዃቸው ፊልሞች ይበዛሉ:: ካየዃቸው መካከል እንደ ስማቸው አሪፎች የሆኑ እና ‘ስምን መልአክ ያወጣዋል’ የሚያስብሉ ይገኙባቸዋል::

የጣፋጭ ርዕሶች ብዛት እንደ ፊልሞቻችን ብዛት ነው:: ሁሉን መነካካት ይሆንልኛል ብዬ ስላልገመትሁ የተወሰኑትንና በወቅቱ ፈጥረውብኝ የነበረውን ስሜት ብቻ ለማንጸባረቅ እሞክራለሁ:: ወደፊት ወይ እኔ አክልበታለሁ ወይ እናንተ ትጨምሩበታላችሁ:: በርዕሱ ተማርከው የተመለከቱት ፊልም የቱ ነው? ርዕሱ ለምን ሳበዎት? የእኔን ስሜት ጥቂቶቹ ላይ እነሆ ላካፍላችሁ::

ወፍራም ዱርዬ

በርዕሳቸው ከማረኩኝ ፊልሞች አንዱ ነው:: ታዲያ እኔ የገባኝ ወፍራም ቢሏችሁ ወፍራም እንዳይመስላችሁ፤ ውፍርናው የዱሩዬነት ስልቱ ላይ ነው:: ብልጥ፣ የገባው፣ ለሌሎች ዱርዬዎች መልካም አርአያ የሆነ ይመስለኛል- ወፍራም ዱርዬ:: ታዲያ የዚህን ፊልም ርዕስ የፊልሙ ስክሪን ደራሲ እና አዘጋጅ የሆነው ህንዳዊው ዲፒ ሸንዲ ከሆነ እሱም ወፍራም ዱርዬ ሳይሆን አይቀርም:: አማርኛ መናገር ብቻ ሳይሆን በአማርኛችን ቅኔ መቀኘት ሳይችል አልቀረም::

አፋጀችን

ኢትዮጵያዊውን ባለቅኔና የኢትዮጵያ የተውኔት አባት ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴን ብዙዎች እናስታውሳለን:: ይህ ሰው ከማይጨው ጦርነት በኋላ ለሀገራቸው ክብርና ለባንዲራቸው የተሰዉ ሳይሆኑ ሌሎች በሀገሪቱ ላይ ሲገኑ በማስተዋሉ ብሶቱን አፋጀሽኝ የሚል ድራማ በመጻፍ ገለጸ:: በድራማው ላይ አፋጀሸኝ ኢትዮጵያን የምትወክል ገጸ ባህሪ ናት:: “አፋጀሽኝ” ዮፍታሄ ከጻፋቸው ተውኔቶች እጅግ ዝነኛዋ ነች:: እነዚህ ደግሞ ሽኝን በችን ቀይረው አፋጀችን ሲሉ ድንግጥ እንድል አደረጉኝ:: የጥንት የጠዋቱን ድራማ እንዳልሆነ ያስተዋልኩት ልብ ብዬ አተኩሬ ከተመለከትኩት በኋላ ነው:: ግን ቀልቤን እንድሰጣቸው፤ ማየት እንዲያምረኝ አድርገዋል። ደግሞም ማፋጀት ትልቅ የሆነ ተውኔታዊ ቃል ነው:: ከባድ የሆነ ብጥብጥ እና ግጭትን አመላካች ነው:: ማለትም የቀድሞውን ተውኔት ለማያውቅም ቢሆን አጓጊ ነው።

ቦንቡ ፍቅርሽ

ይህ የአንድ ዘፈን ርዕስ እንደነበር ነው የማስታውሰው፤ ትንሽ ላንጎራጉርላችሁ:: ቦንቡ ፍቅርሽ … አሃሃ … ሲፈነዳ … አሃሃ (አሃሃ የምትሉት እናንተ ናችሁ) ላንቺ ብዬ … አሃሃ … ገባሁ እዳ … አሃሃ በሰላ ጎራዴ አንገቴን መታሺው ገንዘቤ እስኪያልቅ ነው ለካስ የጠበቅሺው አንቺ ልጅ፣ ሰማሽ ወይ ከኔ ሌላ፣ ፈለግሽ ወይ ቦንብ የሆነ ፍቅር እንዴት ስክሪን ላይ ይገለጻል? ሳላየው አመለጠኝ:: ባያችሁት እቀናለሁ፡፡

ወንድሜ ያዕቆብ

ወንድሜ ያቆብ፣ ወንድሜ ያቆብ ተኛህ ወይ? ተኛህ ወይ? ደወል ተደወለ፣ ደወል ተደወለ ተነሳ! ተነሳ! ይህ የዛሬ ልጆች በየአጸደ ህጻናቱ እና ሙኣለ ህጻናት የሚዘምሩት ነው:: እኔ ግን በትዝታ የነጎድኩት ወደራሴ ልጅነት ነበር – ይህን የፊልም ርዕስ እንደተመለከትኩ። እኔ ህጻን ሳለሁ ወደ ትምህርት ቤት ሳመራ ከጓደኛዬ ቀድሜ ቤቱ ከደረስኩ ቤተሰቦቹ የውጪውን በር ስቆረቁር ከሚሰሙት ድምጽ ይልቅ የእኔን ቀድሞ መድረስ የሚረዱት እኔ በማሰማው መዝሙር ነበር። አንተ ጎበዝ፣ አንተ ጎበዝ ተነሳ ተማር፣ ተነሳ ተማር እንድትበላ፣ በወተት በማር እማማ እራበኝ፣ ይልቅስ ከማለት ብድግ ብሎ መሄድ፣ ወደ ትምህርት ቤት ታዲያ ያ ልጅ እኔ እንዳስጠነቀቅሁት ማር በወተት ስለመብላቱ እኔ አላውቅም:: ብቻ መልኩ ከአእምሮዬ ተፍቋል:: “ወንድሜ ያዕቆብ” ፊልም ምስጋና ይግባውና የልጅነት ትዝታዬን ኮርኩሮልኛል።

ባዶ ነበር

እንዴት ያለ ውብ ርዕስ ነው። ባዶ ነበር ማለት አሁን ሙሉ ነው ማለት ነው። ባዶ የነበረ ነገር ከምታስቡት ፍጥነት በላይ ሞልቶ ስታገኙት ደንግጣችሁ እንዴ! አሁንኮ ባዶ ነበር እንደምትሉት አይነት። ወይ ደግሞ እንዴ! አሁን ባዶ አልነበረም፤ ማነው ባንዴ የሞጀረበት እንደምትሉት ዓይነት። ግን ደግሞ እኔን ብዙ ነበር ያመራመረኝ ይሄ ርዕስ። ባዶ ማለት ምንም የሌለበት ነው ብለናል። ባዶ ነበር ስንል ግን ቀድሞ ባዶ የነበረ፣ አሁን ግን ያለው ማለታችን ነው። ታዲያ ከቃሉ ክብደት ጋር እኔ የተጓዝኩት ወደ ታላቁ መጽሀፍ ነበር። ታላቁ መጽሀፍ ምድር ባዶ ነበረች፣ ይልና ምንም አልነበረባትም ብሎ ይለጥቃል። እንግዲህ ይሄ በምድር ላይ ብርሀን ከመኖሩ በፊት፣ ጠፈር ከመኖሩ በፊት፣ ሰማይ ከመኖሩ በፊት፣ የብስ ከመኖሩ በፊት፣ ሰው ከመኖሩ በፊት ….ብዙ፣ ብዙ ነገር ከመኖሩ በፊት ማለት ነው። ታዲያ ምድር ባዶ ነበረች ብሎ በሃላፊ ግስ ሲያወራ ከባዶው ለጥቆ ኦናውን የሞሉትን ነገሮች እንደሚጠቅስ ግልጽ ነው። ባዶውን ለሚለጥቅ ነገር ባዶ ነበር አይባልማ። ታዲያ ይህ ፊልም ስለምን ያወራ ይሆን ብለን መደነቃችን አይቀርም።

የገጠር ልጅ

ጥሬ፣ ቅን፣ ንጹህ፣ እውነት እና እውነት ብቻ የሆነች፣ ፍልቅልቅ፣ የማይጠገብ የማይረሳ ፈገግታ፣ ሽቁጥቁጥ፣ ባለሙያ፣ ለሰው ተጨናቂ፣ ለስላሳ፣ የሚያውድ መአዛ … መልካም ነገሮችን ብቻ የተጎናጸፈች፣ ምቀኝነት፣ ተንኮል፣ ሸር ያልበከለው … እንዲያው ባጭር ቋንቋ የድንግል ውበት ባለቤት የሆነች ልጅ ነች በምናቤ የሳልኩት ይሄን ርዕስ እንደተመለከትኩ። ባሰብኩት፣ በምናቤ ባመላለስኩት ቁጥር ልምላሜ በሞላበት፣ አበቦች በፈኩበት፤ የንፋስ ሽውታ በሚያፏጭበት፣ የምንጭ ውሃ በሚንዶቀዶቅበት፣ ጸሀይ ወርቅ ቀለም በምትረጭበት በሜዳው፣ በገደሉ እምትፈስ፣ እምትቦርቅ፣ በአይኗ የምትሰርቅ፣ በፈገግታዋ የምትዋጋ ያልወፈረች፤ ያልቀጠነች፤ ያላጠረች፤ ያልረዘመች ኮረዳ ናት እኔ የታየችኝ። እኔ ይህን አልኩ እንጂ ይህቺን ኮረዳ ፊልሙ ላይ ታገኟታላችሁ ማለቴ አይደለም። አታገኟትም ማለቴም አይደለም። እኔ እንዲህ ጠርጥሬያለሁ ማለቴ ነው።

ሚስቴን ቀሙኝ

አንድ የምታውቁት ሰው ምን ልሁን? ሚስቴን ቀሙኝ ብሎ ቢያማክራችሁ ምን ትላላችሁ? ወንድ አይደለህም? አፍህን ሞልተህ ሚስቴን ቀሙኝ ትላለህ? ወንድ አሰዳቢ ይሉት ይሆናል። ወይ ደግሞ- ጅሎ እኔን ትጠይቀኛለህ? እኔ ምን እንድልህ ነው? ቅልቅል ጥራቸዋ! ወይ ደግሞ ሆሆ! ምን አይነት ዘመን ላይ ደረስን! ጠላቱን ገድሎ እንደመፎከር ጭራሽ ምክር ይጠይቀኛል! ወይ ደግሞ ችኩል ሀያሲ ይሆኑና ፊልሙን እንኳ ሳይመለከቱ ይሄሳሉ። በቃ እንደዚህ አይነት ነገር ነው የሚያስጠላኝ። ኢትዮጵያዊ ሆኖ እንዲህ ብሎ ምክር የሚጠይቅ ወንድ ይኖራል? የማይመስል ነገር ነው። እኔ ብዙ ብዙ ሀሳብ መጣ በአእምሮዬ። ለማወቅ ፊልሙን ማየት ነው ቢሉኝ እርስዎ ትክክል ነዎት።

አስረሽ ፍቺው

እንዴት ያለ ያበደ ርዕስ ነው!! ወትሮ ሃላፊነቱን ዘንግቶ የሚዝናና ሰው፤ ወይ ደግሞ ቤተሰቡን እየበደለ በየእለቱ የሚጎነጭ፤ ወይ ደግሞ መሻሻል እንዳለበት ዘንግቶ ጊዜውን ጊዜያዊ በሆኑ ነገሮች ላይ የሚያጠፋ ሰው ሲመከር አስረሽ ምቺው አበዛህ ነው የሚባለው። ጨዋታና ፈንጠዝያው ከመጠን አለፈ እንደማለት ነው። ህይወቱን ቁም ነገር አልባ አድርጎታል ማለት ነው። ግን አስረሽ ፍቺው ሲባል ምን ለማለት ነው? በእውነቱ ልገምተው ከብዶኛል። ቃል በቃል ልተርጉመው ካልኩ መጀመሪያ ጠፍሪው፤ በኋላ ልቀቂው ማለት ይሆንብኛል። ግን ይሄ የሰው ርዕስ አንኳሶ ማየት ሆነብኝ። ይህን ከማደርግ ስም አውጪውን እንዲያው በደፈናው “ዲንቅ” ነው ብለው ይሻለኛል።

ዴዝዴሞና

ይህ ፊልም የወዳጄ የማንያዘዋል ነው። ፊልሙ ለሕዝብ ይፋ ከመሆኑ በፊት ለአስተያየት ከተጋበዙት እድለኞች አንዱ ነበርኩ። ከማስታውሳቸው ነገሮች አንዱ ለዚህ ፊልም ተገቢ ግን ደግሞ ሳቢ ርዕስ ለመስጠት የነበረውን ጭንቀት ነው። እናም በመጨረሻ ይህ ውብ መጠሪያ ተገኘ። ሀገራችን ላይ ኦቴሎ ተውኔት ዝነኛ ስለነበር ዴዝዴሞናን ብዙ ሰው ያስታውሳታል። ድራማውን ላላዩም ቢሆን ዴዝዴሞና በወጣቶች የፍቅር ጨዋታ ውስጥ እንደ ሮሜዎና ጁሊዬት የምትገኝ ቅመም ነች። ዴዝዴሞናን የሚሰማ ሰው በአእምሮው ቆንጆ፣ ቅን፣ ቆራጥና ለፍቅር ሟች የሆነች ኮረዳ በምናቡ መሳሉ አይቀርም። በውይይትም ላይ ተስፋ ተደርጎ የነበረው ስሜት ይህ ነበር። ዴዝዴሞና ከወላጆቿ ፈቃድ አፈንግጣ፣ ከህብረተሰቧ አመለካከት ጋር ተጋጭታ ነጭ ሆና በእድሜ ብዙ የሚበልጣትን ጥቁር የወደደች እና ለፍቅር በፍቅረኛዋ የተሰዋች ኮረዳ ነች። እርሶስ ይህ ርዕስ ስቦት ነበር? ስቦት ከነበረስ ምን ነበር በአእምሮዎ የተቀረጸው?

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top