ጥበብ በታሪክ ገፅ

አባይን በጭልፋ

አባይ በይበልጥም በጥንታዊ ግሪኮች ከዚያም በሮማውያንና ግብፃውያን የሚቶሎጂው ዓለም ፍልስፍናና አስተሳሰብ ታሪኮች ተመዝግቦ ይገኛል። ምንም እንኳን አትዮጵያም በጥንታዊ ሥልጣኔ ከእነዚህ ሀገሮች እኩል የምትጠቀስ፣ በጥንታዊ የሚቶሎጂ ታሪኮችም እምብርት ሆና በእጅጉ የምትወሳና ጥንታዊ የጽሕፈት ሥርዓትና አጠቃቃም ቢኖራትም እንኳን ጥንታዊ የነገረ-መለኮት ፍልስፍናዋና ታሪኮቿ ተመዝግበው አይገኙም። በመሆኑም አባይን ርዕሰ- ጉዳይ በማድረግ በቀረበው በዚህ አጭር ፅሁፍ የማወሳቸው ፍሬ- ሀሳቦች በአብዛኛው በተጠቀሱት ሀገሮች ተመዝግበው የሚገኙ የሚቶሎጂ ታሪኮችን እንዲሁም “ዘመነ-ታሪክ” ከተሾመ ወዲህ በውጭ ጸሐፍት የሠፈሩ መረጃዎችን መሠረት በማድረግ ነው።

አባይ ጥንትም ዛሬም እንቆቅልሽ የጥንታዊት ግብፅ የሥነ-ኅላዌ ሚቶሎጂ ታሪኮች እንደሚተርኩት የአባይ መነሻ የዛሬዪቱ ሊቢያ ነበረች። በፓፒረስ ተጽፈው ሠፍረው የተገኙና ፕሊኒ የተረጎማቸው የጥንታዊ ግብፅ የሚቶሎጂ ታሪኮች እንደሚተርኩት አባይ (ናይል) ከሊቢያ ተነስቶ በምድር ውስጥ እየተጥመለመለ ወደ ደቡብ ከነጎደ በኋላ ከኢትዮጵያና ከግብፅ ኩታ-ገጠም ወሰን ሲደርስ ሞፊና ክሮፊ በተባሉ ሁለት ትይዩ ገደላማ ተራሮች መካከል በድንገት ምድሩን ፈንቅሎ ዲካውን ለማግኜት የማይቻል ሀይቅ ከሆነ በኋላ በሁለት ወንዞች ተከፍሎ አንዱ ወደ ግብፅ ሌላው ወንዝ ወደ ኢትዮጵያ መፍሰስ ይጀምራሉ። ወደ ግብፅ የሚሄደው እነሆ ከላይኛው ወደ ታችኛው ምድረ-ግብፅ እያጥለቀለቀ መፍሰሱን ይቀጥላል የሚል መላምትና እምነት እንደነበራቸው ሄሮዱተስ ካሰፈረው ጽሑፍ እንገነዘባለን።

በአንፃሩ ደግሞ ከ5 ሺህ ዓ.ዓ. አስቀድሞ ግሪካዊው ሄሶይድ፣ ከዚያም ኦቪድም ሆነ ቡልፊንችስ በጻፏቸው ሥራዎቻቸው የጥንታዊ ግሪኮች፣ ቀጥሎም፣ የጥንታዊ ሮማውያን የሚቶሎጂ እሳቤዎችና ታሪኮች የአባይ ምንጭ ኢትዮጵያ መሆኗንና በምድር ውስጥ ከቶም ይጓዝ እንዳልነበረ ይተርኩት ነበር። በእርግጥ ግሪኮች የአባይ ምንጭ መነሻው ከምድር ውስጥ መሆኑንና ይህ የሆነበትን መንሥዔ-ነገርም አምላከ ፀሐይ (ፌቦስ) ከኢትዮጵያዊቷ ክሌመን ከወለደው ከጀብደኛው ብላቴና ከፌጦን ጦሰኛ ድርጊትና ታሪክ ጋር በማያያዝ እንዲህ ሲሉ መለኮታዊም ዓለማዊም ትርጉም ይሰጡት ነበር። ይኸውም አምላከ- ፀሐይ (በጥንታዊ ግሪክ “ፌቦስ”) የፀሐይን ሠረገላ ልጓም ይዞ የኹረት መሥመሯን ሳይስት ከፍ ሳይል ወይ ዝቅ ሚዛን ጠብቆ የሚያዞራት ቢሻው እንደ ሰው በምድር እንደ እግዜር በሰማይ መኖር የሚችል ዲበ-ኩሉ

“በአጠቃላይ አባይ የተፈጥሮ ስጦታ፣ ለሚኖሩበት ሁሉ ሲሳይ፣ ፀጋ፣ በጥልቅ ሲታይ ደግሞ የተፈጥሮና የባህል ስንኝት ትእምርት ነው”

መለኮተ-ኃይል ነበር። ሥራውም ወደር የሌለው ንቃትንና ጥንቃቄን የሚጠይቅ ነበር።

ታዲያ ምን ይሆናል? አምላከ-ፀሐይ ከኢትዮጵያዊቷ ክሌመን የወለደው ልጅ ፌጦን አባቱ ማን እንደሆነ አያውቅም። ስሙ ማን እንደሚባል፣ የት እንደሚኖርና ሥራውም ምን እንደሆነ አያውቅም። እናቱ ክሌመንም አንድም ቀን አፏን ተስቶት ገልጻለት አታውቅም ነበር። የዕድሜ እኩዮቹ በየጨዋታው መሀል ‹አባትክን የማታውቅ›፣ ‹ከማን እንደተወለድክ የማታውቅ› እንዲህ እያሉ ያነውሩት፣ ያጣጥሉትና ያናንቁት ስለነበር ከፍተኛ የሥነልቡና፣ የዝቅተኝነትና የብቸኝነት ስሜት እያደረበት ከእኩዮቹ መራቅ አመጣ። በዚህ ሁኔታ ፌጦን ብቸኝነት እያደረበት፣ አእምሮው እረፍት እያጣ በመጣ ቁጥር ባሕርይው እየተለወጠ መጣ። በመሆኑም እናቱን ዘወትር “አባቴ ማን ይባላል?” “የት ነው የሚኖረው?” “ካልነገርሽኝ እራሴን እገድላለሁ” ምናምን እያለ ያስጨንቃት ጀመረ። ክሌመንም እናት ነችና በስጋትና በፍርሀት ተዋጠች። እናም እጇን ወደ ሰማይ ዘርግታ በጣቷ እያመለከተች ያውልህ “ፌቦስ” አለችና የአባቱን ማንነት ዘርዝራ ነገረችው። ፌጦን ለጊዜው ደስ አለው። ዳሩ ግን እናቱ የነገረችውን ሙሉ በሙሉ ለማመን ከራሱ ከፌቦስ ቃል ማረጋገጫ እስከሚያገኝ ልቡ ሊያርፍ አልቻለም። ምንም ቢሆን አምላክነት አለውና ወደ አምላከ-ፀሐይ፣ ወደ ፌቦስ፣ ተጉዞጥያቄውን አቀረበለት። ፌቦስም ከክሌመን የወለደው ልጁ መሆኑን አረጋገጠለት። ነገር ግን ፌጦን በደስታ ቢዋጥም ከጥርጣሬ ሙሉ በሙሉ ነፃ አልሆነም። ስለዚህ እውነትነቱን በገቢር ለማረጋገጥ ሲል ለአባቱ ተጨማሪ ጥያቄ አቀረበ። ይኸውም፡- “የፀሐይን ሠረገላ ለአንድ ቀን ስጠኝና ላዙራት፤ ይህን ካደረክ እውነትም አባቴ ነህ” አለው። ፌቦስ ግን በልጁ ልምድና አቅም ፈፅሞ ሊደረግ የማይችል ጥያቄ በመሆኑ እጅግ ተጨነቀ። ፌጦን ደግሞ “ይህ ካልሆነ እንዴት ላምን እችላለሁ” አለ። በዚህ ጊዜ ፌቦስን ታላቅ ፈተና ገጠመውና “ልሰጥህ እችላለሁ። ሥራው ግን እጅግ በጣም ከባድ ነው። አንተ ልጅ ነህ፤ ልምዱም፣ እውቀቱም፣ ድፍረቱም አይኖርህም። የአንዲት ቅፅበት ስህተት የዓለምን ዘላለማዊ ዕጣ ትወስናለች። ለዚህ አልበቃህም፤ ሌላው ይቅርና የፈጣሪ ኩሉ ዓለም የኃያሉ አምላክ የዚዎስ የበኩር ልጅ ኦሎምፐስም እንኳን ለቅፅበትም ቢሆን እንቅልፍ በዓይኑ ሳይዞር ሚዛን ሳያዛባ ጥንቃቄ በተሞላበት ሁኔታ የፀሐይን ሠረገላ መሥመር ጠብቆ ለአንድ ቀን ሊያዞራት አይችልም” ሲል አስረዳው። ፌጦን ግን የሥራውን ኃያልነትም፣ ምክሩንም አልተቀበለም። “እኔ እንኳን እችላለሁ። አልሰጥህም ካልክ በእርግጥም አባቴ አለመሆንክን ያረጋግጥልኛል” በማለት ተስፋ መቁረጡን ነገረው።

 የፈሩት ይደርሳል፤ የጠሉት ይወርሳል። የማይሆን ነገር ሊሆን ነው። ፌቦስ ከብዙ ጭንቀት በኋላ “ቃሌን ካላመንክ እሽ ያውልህ። ግን አሁን የምነግርህን በጥንቃቄ አዳምጥ። መሥመሩን እንዳትለቅ፤ ሚዛን እንዳታፋልስ ተጠንቀቅ። ሠረገላው ከመሥመሩ ወጥቶ ከፍ ካለ ዓለም በጨለማ ትዋጣለች፤ ትናወጣለች፤ ከመሥመሩ ዝቅ ካለ ዓለም ትቃጠላለች፤ ትጠፋለች። መሥመሩን መጠበቅ እንጂ የምትይዝ የምትጨብጠውን እንዳታጣ አትደንግጥ” ብሎ ሰጠው። ፌጦን በሲቃ ተሞልቶ ከሠረገላው ወጣ። ጥቂት እንደሄደ ግን ሠረገላው ሲያረገርግ በድንጋጤ ተውጦ የሚይዘውን የሚጨብጣውን አጣ። ሠረገላው መሥመሩን ሥቶ ወደ ታች እየሠረገ ሄደ። ፌጦን ከድንጋጤ ብዛት ልጓም መዘወሩን ለቀቀው፤ ከዚያም ተስፈንጥሮ ወደቀ። የእርሱ ጉዳይ በዚሁ አከተመ። ጦሱ ግን ለዓለም ተረፈ። ዓለም በፀሐይ ግለት፣ በእቶን፣ መቃጠል ጀመረች። ውቅያኖስ፣ ሐይቆችና ወንዞች መትነን ጀመሩ። በዚህ ጊዜ አባይ ተኖ ከማለቁ በፊት ውሀውን መልሶ ራሱን ወደ ምድር ውስጥ ቀበረ። እናት ምድርም ፍጡራን ሁሉ በእቶን ከምድረ-ገጽ ዘራቸው እንዳይጠፋ እጆቿን ዘርግታ ወደ ፌቦስ ተጣራች። ዚወስንም ተማፀነች። ፌቦስም ሠረገላውን በፍጥነት ተቆጣጠረ። … በአጭሩ ወደተነሳንበት ሀሳብ ስንመለስ ጥንታዊ ግሪኮ- ሮማውያን አባይ ራሱን የቀበረበትን ምክንያት ከላይ በአጭሩ ከተገለፀው ከፌጦን የሥነ-ኅላዌ ታሪክ ጋር በማያያዝና ከዚያ ጊዜ ወዲህም ራሱን ከቀበረበት መንጭቶ መፍሰሱን ቀጥሎ እንደሚገኝ ይተርኩ ነበር ማለት ነው።

አባይ በግሪኮ-ሮማውያን የሚቶሎጂ ዓለም የጤንነት፣ የፈውስ አብነት ነው። የግሪክ አማልዕክት ጤና በሠረቁ ቁጥር ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በአባይ ውሀ ተጠምቀው፣ ፈውስ  እንገነዘባለን። ለዚህ የውቢቷን የአዮን ታሪክ እንደ ምሳሌ ማውሳት እንችላለን። አምላከ ዚዎስ አዮን ቅምጥ አድርጎ ባበደ ጊዜ ሚስቱ ሄራ በቅናት ተቃጥላ እርሷም በአምላክነቷ ቅጣት አዘዘችባት። ቅጣቱም ቀን ከሌት እረፍት የሚነሳ፣ የማያስቀምጥ፣ የማያስተኛ፣ መውጫ መግቢያ የሚያሳጣ ተናዳፊ የተርብ መንጋ ነበር። አዮ በዚህ ምክንያት በዱር በገደል፣ በሸለቆ በተራራ፣ እየባከነችና እየተንከራተተች ሳለች ከአማልዕክት ወገን ለሰው ልጆች ሁሉ በርኅራሄውና በተቆርቋሪነቱ አርአያ ትእምርትነቱ ምሳሌ ተደርጎ በሀሳብ ታሪክ የሚጠቀሰው ፕሮሚቲዩስ ወደ ኢትዮጵያ ሄዳ በአባይ ውሀ እንድትታጠብ መከራት። አዮም ፕሮሚቲዩስ በነገራት መሠረት ወደ ኢትዮጵያ መጥታ በአባይ ውሀ ከታጠበች በኋላ የዚወስ ሚስት ሄራ ካዘዘችባት የተርብ ፍዳ መላቀቋን እንረዳለን። ሆመርም እንደዚሁ ኤሊያድ በተሰኜው ክላሲካል መጽሐፉ ውስጥ ኃያሉ አምላከ ዚዮስ አማልዕክቱን ሁሉ አስከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የፌስታ በዐል ለመካፈል፣ ለፈውስና ለእረፍት መሄዱንና ከ12 ቀናት በኋላ መመለሱን ይተርካል።

አባይ ሰማያዊም-ምድራዊም ኃይል ነው የሥልጣኔ ምንጭ ብቻ ሳይሆን የሚቶሎጂ ኮስሞሎጂያዊ አውታረ-ሀሳብም ሆነ የሥነ- መለኮት ወይም የእምነት ማዘንገጊያ-ማጠንጠኛ ዛቢያ ጭምር ነው። እንደ ኢትዮጵያ ሜርዌ ሁሉ የግብፆች ጥንታዊ ሥልጣኔ ከአባይ ጋር የተቆራኜ ሕይወት ያፈራው ትሩፋት መሆኑ በጸሐፍት ዘንድ ብዙ ተዘክሯል። የዘመንና የቀን አቆጣጠር፣ የስሌትና የአስትሮኖሚ ዕውቀት፣ የመስኖና የምህንድስና ጥበብ፣ የእምነትና የሥነምግባር ሕግጋትና ደንቦች፣ የፍልስፍና ፈሊጥና አድማስ፣ በአጠቃላይም የመንፈሳዊና ቁሳዊ ብሂል፣ ወዘተ. ሁሉ ከናይል ጋር በእጅጉ የተቆራኙ ናቸው። የእነዚህ ነገሮች የሥርፀት ደረጃ ልዩነት ሊኖረው ቢችልም ሁለቱን ጥንታዊ ሀገሮች የሚያመሳስሉ ጉዳዮች ናቸው ቢባል እውነት ይሆናል። አባይ በሁለቱም ሀገሮች መለኮታዊነት ነበረው፤ አለውም። ለምሳሌ የጥንቱን የግብፁን አምላከ “ሀፒ (አፒ)” እና የኢትዮጵያውን “ግዮን” እናስተያይ። በስም የተለያዩ ቢሆኑም እነዚህ ሁለቱ የአባይ መንፈሳዊ ኃይሎች ናቸው። “ሀፒ” በበሬ ይመሰላል። “ግዮን” በረቂቅነት። “ሀፒ” ቀለሙ ጥቁር ቦቃ፣ ከጎኑ ነጭ ያልቆነጀች የጨረቃ ምልክት ያለውና ከምላሱ ላይ ደግሞ የጢንዚዛ ምልክት ያለው መሆን አለበት። ይህ ከብት አምላከ ናይል በውስጡ ያደረበት ነው። ከብቱ ከየትም ተፈልጎ ለራሱ በተሠራ ቤተ- መቅደስ ውስጥ በእንክብካቤ ተይዞ፣ ተቀልቦ፣ ግብር ተቀብሎ፣ ሀፒ ሆይ አንተ ታውቀለህ ጠብቀን ተብሎ፣ ሥርዓተ-ቅዳሴ ተሟልቶለት የሚመለክበት ከብት ነው። በከብትነቱ ብቻ ሳይሆን በአምላክነቱ የሚገበርለት ነው። ሀፒ የናይል፣ የፀሐይ አምላክ የ‹ራ› (ቆይቶም የ‹ኦሲሪስ›) እና የእናት ምድር የ‹ኑት› – የእነዚህ የሰለሥቱ ተዋህዶ-አምላክ – ተደርጎ ይታመንበት ነበር። የተዋህዶነቱ አርአያ ትእምርነት ወይም ምሳሌነት እርጥበትን፣ ርቢን፣ የምርት መትረፍረፍን፣ ሲሳይን፣ ሕይወትን፣ ጤንነትን፣ ሰላምን፣ ደስታን፣ ወዘተ. አጭቆ የያዘ ነው።

 የአባይን መንፈስ “ግዮን”ን ስናይ ደግሞ ከዚህ እምነት በብዙ የተለየ አይደለም። ‹ግዮን›ን የአባይ ተለዋጭ ስም አድርገው የሚጠቅሱት አሉ። በመጽሐፍ ቅዱስም በዚሁ ስያሜ በመጥቀስ ግዮንን ከዓለም አምሥቱ ታላላቅ ወንዞች አንዱ ተደርጎ ይታያል። ከፎክ ወይም ከትውፊታዊው እምነት አስተሳሰብ አንፃር ግን ግዮን የአባይ አምላክ ነው። የአምላክነቱ ምሳሌነትም እርጥበትን (ዝናብን)፣ የሕይወት መቀጠልን (ርቢን)፣ ሲሳይን፣ ጥጋብን፣ ልግሥናን፣ ደኅንነትን፣ ሰላምን፣ ተስፋን፣ ወዘተ. የያዘ ነው። የተወለደው እንዲያድግ፣ የተዘራው እንዲበቅል፣ የበቀለው እንዲያፈራ የሚያደርግ መንፈሳዊ ኀይል ተደርጎ ይታመንበታል። እሱን ደስ ሲለው ደስ ያሰኛል። ስለዚህ ደስ ይለው ዘንድ በአብዛኛው መስከረም ከጠባ በኋላ በየዓመቱ አደይ አበባ የመሰለ ቡላ ወይም የጭስ አባይን ፏፏቴ የመሰለ ዳመናማ (ሰሳ) ቀለም ያለው ከብት መስዕዋት ይደረግለታል። ይቋደሳል። አማንያንም ቅርጫውን ይካፈላሉ። ቂም በቀል የገቡ ሰዎች ጠባቸውን “እንደ ጋጃ ይንፈስ እንደውሀ ይፍሰስ” ብለው ይታረቃሉ። ግዮን ጥቁር ቀለም ያለውን ከብት ደም በመስዋዕትነት አይቀበልም። ዛጎላ ወይ እንደ ‹ሀፒ› ከግንባሩና ከጎኑ ነጭ የጣለበት ጥቁር ቦቃም ቢሆን አይስማማውም። ከእምነት ይዘቱ አኳያ ግን የእኛው ‹ግዮን› ከግብፆቹ ‹ሀፒ› የተለየ አለመሆኑን እንገነዘባለን ማለት ነው።

አባይ የጥንታዊ ሥልጣኔ (የባህል) ምንጭና የሚቶሎጂ ምህዋር ብቻ ሳይሆን በታሪክ፣ በተለይም በጥንታዊት ኢትዮጵያ መልክዓ- ምድራዊ ለውጦች ላይ ግዙፍ ተፅዕኖ ያስከተለ የፖለቲካ አዙሪት ጭምር ነው። በጥንታዊ  ፀሐፍት ማስታዎሻዎች እንደሠፈረው በአጭሩ ይህን ይመስላል። በ250 ዓ.ዓ. ገደማ ስትራቦ እንደፃፉት ከክርስቶስ ልደት በፊት በ300 ዓ.ዓ. የግብፅ ንጉሥ ፕቶሎሚ የአባይን ምንጭ እርግጠኛ ቦታ ለማወቅ ጦር ይዞወደ ኢትዮጵያ ድንበር በገባ ጊዜ በሜርዌው መንግሥት ጦር ተመትቶና ተበታትኖ ለመመለስ ተገደደ። ከዚያም በኋላ ጥንታዊ ሮማውያን ኃያልነትን አግኝተው ዓለምን ጠቅለው የመግዛት ህልም አደረባቸው። ይህንም መለኮታዊ ተደርጎ እስከመታየት ደርሶ በነበረው በአውግስጦስ ቄሣር ዘመነ-መንግሥት ግብፆችንና ሊቢያውያንን በቁጥጥራቸው ሥር አውለው ቅኝ መግዛት ቀጠሉ።

በዘመኑ የኢትዮጵያ ግዛት ከግብፅ ይዋሰን ስለነበረ ኢትዮጵያውያን ብርቱ ሥጋት አደረባቸው። አውግስጦስ ቄሣር የአባይን መነሻና የተፋሰሱን ገጽታ ለማወቅ እጅግ ይጓጓ ስለነበር በዘመኑ ጂኦግራፊ የተሻለ እውቀት የነበረውን ፊሊጶስ የተባለ ጣሊያናዊ ይህን

“ቂም በቀል የገቡ ሰዎች ጠባቸውን “እንደ ጋጃ ይንፈስ እንደውሀ ይፍሰስ” ብለው ይታረቃሉ። ግዮን ጥቁር ቀለም ያለውን ከብት ደም በመስዋዕትነት አይቀበልም። ዛጎላ ወይ እንደ ‹ሀፒ› ከግንባሩና ከጎኑ ነጭ የጣለበት ጥቁር ቦቃም ቢሆን አይስማማውም”

ተግባር እንዲፈፅም አዞት ወደ ግብፅ መጥቶ ዝግጅት ያደርግ ነበር። በኢትዮጵያውያን በኩል ይበልጥ ሥጋቱን ያባባሰው ግብፅን ያስተዳድር የነበረው የቄሣር እንደራሴም ፊሊጶስ የቄሣሩን ምኞት በተሳካ ሁኔታ ይወጣ ዘንድ አስፈላጊውን አሟልቶ ጥቂት ሰዎች አብረውት እንዲሄዱ መድቦለት የአባይን መነሻና ተፋሰስ ለማሰስ የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ ጉዞውን በቀጠለበት ጊዜ ነበር። ያን ጊዜ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ከተማ ሜርዌ ነበረች። በትረ መንግሥቱም የሕንደኬ ሥርወ-መንግሥት አንዱ በነበረው ንጉሥ የሚተዳደር ነበር። የሕንደኬው ንጉሥ ፊሊጶስን ከእነተከታዮቹ አግቶ ካቆያቸው በኋላ አስጠንቅቆ ወደመጡበት መለሳቸው። የፊሊጶስ ተልዕኮ የነበረውን ሥጋት ይበልጥ በማጠናከሩ የኢትዮጵያው ንጉሥ ጦሩን አደራጅቶ አውግስጦስ ቄሣርበቅኝ ግዛት ሥር ያዋላትን ግብፅ በመውረር ከላይኛው እስከ ታችኛው ግብፅ፣ እስከ ሜዲትራኒያ ጫፍ፣ እስከ መምፊስ ድረስ፣ በአጭር ጊዜ ለመቆጣጠር ቻለ። በየከተሞች የቄሣር ሀውልቶች ተተክለው ነበርና የሕንደኬ ሠራዊት ሀውልቶችን ነቃቅሎ በማፈራረስ አወደማቸው። በእርግጥ ድርጊቱ ከሮማውያን፣ ከዚያም አልፎ ተርፎ በአውሮፓውያን ዘንድ ኃያል የዓለም ገዥ ተደርጎ ይታሰብ የነበረውን የቄሣርን ገናናነት አውርዶ ትቢያ ላይ የጣለ፣ ክብርና ዝናውን በመግፈፍ ዕርቃኑን ያስቀረ ታሪካዊ እርምጃ ነው። ይሁንና የኢትዮጵያው ንጉሥ ይህን የመሰለውን ርምጃ ከወሰደ በኋላ ወደ ሜርዌ፣ ወደ ቤተ-መንግሥቱ፣ ተመለሰ።

አውግስጦስ ቄሣር ድርጊቱን እንዳወቀ ይቅርታ አልጠየቀም፤ ወቀሳም አላቀረበም፤ የአፀፋ ርምጃም ለመውሰድ አልፈለገም። እርግጥ ነው፤ የሜርዌው መንግሥት ኃያል መንግሥት እንደሆነ፣ ኢትዮጵያውያንም ብርቱ ተዋጊዎች እንደሆኑ፣ ከታሪክ ጠንቅቆ ያውቃል። የአሁኑ ድርጊትም ይህንኑ ያስመሰክራል። ከዚህም በተጨማሪ የታላቁ እስክንድር ግሥጋሤና የድል ዜና አሳሳቢ እየሆነ ከመጣበት ሁኔታ ጋር ተዳምሮ “የወዳጅነት ትብብር አጥብቆ የሚሻ” ከመሆኑ በስተቀር በመልእክተኛው በኩል ለኢትዮጵያው ንጉሥ ያስተላለፈው ሌላ ቃል እንዳልነበር መረጃዎች ያሳዩናል።

ቢሆንም ውሎ አድሮ አፀፋው መልኩን ቀይሮ መከሰቱ አልቀረም። ሤራውና አፀፋውም ይህን ይመስላል። ግብፅን ያስተዳድር የነበረው የቄሣር እንደራሴ ከጥቁር አባይ ምዕራብ በኩል ይኖሩ የነበሩ የአካባቢውን ተወላጆች በማስተባበር፣ በመደገፍና በማሰማራት ኑባ የተባለችውን ጥንታዊ ከተማ ያለማቋረጥ በተከታታይ እንዲወጓት በማድረግ ከኢትዮጵያ ቁጥጥር ውጭ እንድትሆን አደረጓት። ችግሩ በዚህ አልተገታም። ከዚያ ወዲህ የሜርዌ መንግሥት እረፍት አጣ። ፕሮፌሰር ዊንድሶር እንዳሠፈረው ደግሞ ኑባ ከሜርዌ መንግሥት እጅ ከወጣች በኋላ ማዕከላዊቷ የሜርዌ ከተማም ከየአቅጣጫው በተለይም ከኑባ በኩል ይሰነዘሩ በነበሩ ተደጋጋሚ ጥቃቶችና ዘረፋዎች ሰላም እያጣች በመምጣቷ ወደ ቤጋ፣ ከዚያም ወደ ሳባ፣ በመጨረሻም ወደ አክሱም መዛወሯን ይናገራል። ይህ ሁሉ ሆኖ ከኑባም፣ በኋላም ከሜርዌም፣ ከቤጃም ጭምር በአክሱም መንግሥት ላይ፣ በአጠቃላይም እያደር ግዛቷ እየጠበበ በመጣችው ኢትዮጵያ ላይ፣ ይሠነዘሩ የነበሩ ጥቃቶች ለአንዴም ለሁሌም ስሟን ብቻ ይዛ እስከምትቀር ፍርስራሽ እስከሆነችበት ጊዜ ድረስ አላቆሙም ነበር። ከዚያስ ምን ሆነ? ለአንባብያን እተወዋለሁ።

በአጠቃላይ አባይ የተፈጥሮ ስጦታ፣ ለሚኖሩበት ሁሉ ሲሳይ፣ ፀጋ፣ በጥልቅ ሲታይ ደግሞ የተፈጥሮና የባህል ስንኝት ትእምርት ነው። እና አባይ ለእኛ ስማችን ነው – ኢትዮጵያችን!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top