ጥበብ በታሪክ ገፅ

ጥምቀት በጎንደር

በሁሉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ የጥር ወር የሚታወሰው በዓለ ጥምቀት የሚከበርበት በመሆኑ ነው። ጥር 10 ባሕር መጥረጊያ ወይም ከተራ ወይም ዋዜማ ተብሎ ይታወቃል። ጥር 11 በዓለ ጥምቀት የሚከበርበት ዕለት ነው። በሊቃውንት ስምምነት ጥር 12 ቃና ዘገሊላ፣ ጥር 15 ቂርቆስ፣ ጥር 18 ሰባር አፅሙ፣ ጥር 21 አስተርእዮ ማርያም፣ ጥር 24 ቤተልሄም፣ ጥር 25 መርቆርዮስ ሲሆኑ በእነዚሁ ቀናት እንደ ጥር 11 ቀን ሁሉ ታቦታቱን ወደ ጥምቀተ ባሕር በማውረድና ፀበል በመረጨት የዕድሜና የፆታ ልዩነት ሳይኖር ሁሉም በጋራ ያከብሩታል። ይህችም ጽሑፍ ከዓመታት በፊት በዓለ ጥምቀትን በጎንደር ከተማ ከነዋሪዎቹ ጋር ሳከብር ያየሁትን ለአንባቢያን ለማካፈል የተዘጋጀች ነች።

ጎንደር ከምትታወቅባቸው አያሌ ነገሮች መካከል አንዱ በተወሰነ ቦታ ብዛት ያላቸው አድባራት መኖራቸውነው።  ለዚህም  ነው የአካባቢው ተወላጆችና  ነዋሪዎች መረግረጊያ / መኩራሪያ/ “ኧረ በአርባ አራቱ” የሚል የሆነው።

ጥር አብቶ በየካቲት እስኪተካ የተለያዩ ታቦታት በጎንደር ከተማና አካባቢዋ ይነግሣሉ። ንግሠትን ለማክበር የሚወጣው ህዝብ ለጎንደር ከተማ ድምቀትንና ውበትን ይሰጣታል። ታቦታቱ ከሚነግሡባቸው ቀናት መካከል በዓሉ የሚከበርበትን ዋዜማ ዕለት መመልከቱ በጎንደር ከተማና አካባቢ ስለሚገኙ አድባራት በዓለ ጥምቀት የተወሰነ መረጃ ሊሰጥ ይችላል።

እንደሌሎች አካባቢዎች ሁሉ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎችም የጥምቀትን በዓል የሚጠባበቁት በጉጉት ነው። አዳዲስ ልብስና ጫማ ይገዛሉ። አዳዲስ ልብስና ጫማ መግዛት ያልቻሉም ያላቸውን ያጥባሉ፣ ይተኩሳሉ። በተጨማሪም ሴቶች እጅና እግርን ለማቅላት የሚያገለግል እንሶስላ ይገዛሉ። የተለያየ ዓይነት ቁንዳላ (ሹርባ) ይሰራሉ።

 ከየቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ በመውጣት ረዥሙን ጎዳና ተከትለው ፋሲለደስ ተብሎ ወደ ሚታወቀው ጥምቀተ ባሕር ለሚወርዱት ታቦታት ነጋሪት ሲጎሰም፣ የወጣቶች የሆታ ሁካታ፣ የሴቶች እልልታና የሕፃናት ጭፈራ ሲሰማ እጅግ ይማርካል። በያሬድ ማኅሌት ከሚያሸበሽቡት ቀሳውስትና ካህናት ኋላ ኋላ መነኩሴዎችና እናቶችም፣

በህይወት ያግባህ በህይወት፣

ያገራችን ታቦት።

እጣን እጣን ይሸታል መሬቱ /2/

ቅዱስ ሚካኤል ያረፈበቱ።

ማር ይፈሳል ጠጅ /2/

በአርባ አራቱ ደጅ።

የሚሉትንና ሌሎችንም የታቦት ሙገሳ ግጥሞች እየደረደሩ ያጅባሉ። ወጣቶች ደግሞ፣

እንኳን ለሚካኤል ለታዳጊው ጌታ፣

ይዘፈን የለም ወይ ለቀይ ጋለሞታ።

እያሉ ሆታውን በማቅለጥ ታቦቱን የተሸከሙትን ቀሳውስት ፍጥነት ለመግታት ይሞክራሉ። ይህንን የሚያደርጉበት ምክንያት ለታቦቱ ያላቸውን ፍቅር በጭፈራ ለመግለፅና ታቦቱ ከሚያድርበት ቦታ ቶሎ ደርሶ ጭፈራቸው እንዳይቋረጥ በማሰብ ይመስላል። ይህ ግን እነሱ እንደፈለጉት ላይሆን ይችላል። ምክንያቱም ፖሊስ እየተከተለ ቶሎ ቶሎ እንዲሄዱ ይገፋቸዋልና ነው። ለእይታ አመቺ ነው ብለን ከቆምንበት ቦታ ታቦታቱና አጃቢዎቹ እየራቁ በመሄዳቸው ከኋላ ኋላ መከተል ጀመርን። ብዙም ሳንሄድ አጣጣሚ ሚካኤልን፣ እልፍኝ ጊዮርጊስንና መድኃኔዓለምን ይዘው ከመጡት ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና መነኮሳት እንዲሁም ከአጃቢዎቹ ጋር ተገናኘን። የሦስቱ ታቦታት አጃቢዎች ከተገናኙበት ቦታ ላይ ለጥቂት ጊዜ ቆም በማለት ሊቃውንቱ መረግድና ሽብሸባ ሲያደርጉ ሌሎቹ ደግሞ የሚችሉትን የጥምቀት ዘፈን ሲዘፍኑ ቆይተው ጉዟችንን ወደ ጥምቀተ ባሕሩ ቀጠልን። በዚህ ጊዜ እንደታቦታቱ ቁጥር ሁሉ የአጃቢዎቹም ቁጥር እጅግ ጨምሮ ነበር። በዚህ ታቦት የማውረድ ሥነ-ሥርዓት ላይ የሚገኝ ምዕመን ሁሉ ግጥሞችን በመደርደርና እስክስታ በመውረድ ስሜቱን ሲገልፅ ይታያል። እነ እሙሃይም የለበሱትን ጋቢ ወገባቸው ላይ አደግድገው ሲወሳወሱ ሌሎች ደግሞ ከግራ ቀኝ ትከሻቸው ጋቢያቸውን ሳያወርዱ እስክስታውን ያስነኩታል።

ምንም እንኳ ለታቦት ሙገሳና መማፀኛ የሚደረደሩ ግጥሞችን የሚያቀነቅኑ እናቶችና ቤተሰቦቻቸው ከግብርና ሙያ የራቁና በተለያየ የሥራ መስክ የተሠማሩ ቢሆኑም የገበሬ ሚስቶች ለባሎቻቸው የሚደረድሩትን ግጥም እንዲህ በማለት ያቀነቅናሉ። ከዚያው ማርልኝ ያን ወለላ /2/ ዓመት ጥሮ ግሮ ሳይለምን አይበላ። ከዚያው ማርልኝ ያን ገበሬ /2/ ይዤው እንዳልመጣ ይጠብቃል በሬ። ከዚያው ማርልኝ ያንን ምቹ /2/ ይዤው እንዳልመጣ ከብቶቹ ልጆቹ። የግጥሙንና የዜማውን ስልት በመከተል ለአገር አንድነትና ለወገን ደህንነት ለዘመተው ወታደርም፤ ከዚያው ማርልኝ ያን ወታደር /2/ ይዤው እንዳልመጣ ይጠብቃል አገር። ይዤው እንዳልመጣ ያስከብራል ድንበር። በማለት በዕለቱ የነገሠውን ታቦት ይለምኑለታል፡፡

አንዳንዶቻችን እንዲያው ለመሆኑ ዐፄ ፋሲል የራሳቸው የመዋኛ ቦታ አሠርተው ነበር ወይ? ብለን መጠየቃችን አይቀርም። ለዚህም መልሱ ብዙ ድልድዮችን ያሠሩ፣ ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያለው ቤተ-መንግሥት ያስገነቡና ብዙ አድባራትን ያሳነፁ ንጉሥ መዋኛ ማሠራት ይሳናቸዋልን? ነው።

የዐፄ ፋሲል መዋኛ ከቤተ መንግሥታቸው በስተ ምዕራብ በግምት ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ቀሃ ወንዝ አጠገብ የሚገኝ ነው። ይህ ቦታ የተመረጠበት ምክንያት የመዋኛውን ቦታ የሚሞላ ውሃ ከቀሃ ወንዝ ለማምጣት በማሰብ ይመስላል። በመሆኑም ከቀሃ ወንዝ በመስኖ መልክ ተጠልፎ የሚመጣው ውሃ ለመዋኛ ተብሎ ከተከለለው ግቢ እስኪገባ ድረስ ሲፈስ ይታያል። ወደ ግቢ ከገባ በኋላ ግን በዘመኑ ከሸክላ በተሠራ ቱቦ መሰል ነገር በመሬት ውስጥ ለውስጥ ወደ መዋኛው ባሕር ይፈሳል። አሁን አሁን ግን የቀሃ ወንዝ ውሃ እየተመናመነ በመምጣቱ የከተማው ምክር ቤትመዋኛውን በቧንቧ ውሃ ለመሙላት ተገዷል። በጥድ፣ በወይራና በዋርካ ዛፎች የተከበበው የዐፄ ፋሲል መዋኛ ከርቀት ሲመለከቱት በአፀድ የተከበበ ቤተክርስቲያን ይመስላል።

 የመዋኛውን ባሕር ጥልቀት፣ ስፋትና ርዝመት በትክክል ለመናገር ቢያስቸግርም ከአንዳንድ ዘመናዊ መዋኛዎች የሚያንስ አይደለም። ይኸው መዋኛ ዙርያው ክብ ደረጃ ሲኖረው ወለሉ በድንጋይ ንጣፍ፣ ግድግዳው ደግሞ በድንጋይና በኖራ መሰል ነገር የተሠራ ነው። ምንም እንኳን ወለሉ በድንጋይ የተነጠፈ ቢሆንም ውሃ በሚሞላበት ጊዜ ድፍርስ መሆኑ አይቀርም። ወለሉም ሆነ ግድግዳው በነፋስ ከሚመጣ አቧራ ነፃ አይሆንምና። ንፁህ የመዋኛ ውሃ ለማግኘት ደጋግሞ ማጠብን ይጠይቃል። ወደ መዋኛው ባሕር ለመግባትም ሆነ ለመውጣት የሚያገለግል ደረጃ አለ። እንደ ዘመናዊ መዋኛዎች ሁሉ አገልግሎት የሰጠ ውሃ የሚፈስበት ሽንቁርም በስተ ደቡብ ይገኛል።

በስተ ሰሜን በኩል ከመዋኛው ባሕር ግድግዳ ጋር ተያይዞ የተሠራ ባለ ሦስት ፎቅ ሕንፃ አለ። የሕንፃው የመጀመሪያ ክፍል ለመዋኛ በተቆፈረው መሬት ላይ የተመሠረተና ውሃው እስከ ሁለተኛ ፎቅ የሚደርስ በመሆኑ ለመኖሪያ እንዲያገለግል ሆኖ የተሠራ አይደለም። ውሃ ሲሞላ የመዋኛው ቦታ በውሃ ሊሸፈን ስለሚችል በቤት ግድግዳ መልክ የተሠራ ካለመሆኑም በላይ ከትልቅ ወንዝ ላይ የተሰራ ድልድይን ለመደገፍ ከውሃው ውስጥ ተመሥርተው የወጡ ምሰሶዎችን ይመስላል። በስተ ሰሜን በኩል ባለው የመግቢያ በር እንደገቡ ሁለተኛው ፎቅ ከክልሉ መሬት እኩል ስለሆነ ወይም የመጀመሪያ ክፍል (first floor) እንደምንለው በመሆኑ ለመግባት ደረጃ መውጣት አያስፈልገም። ይልቅስ ከመሬት ወለል ጋር የተያያዘ በመሆኑ ድልድይ ይመስላል።

ጥምቀተ ባሕሩ ባለበት ግቢ ተገኝተን፣ የወጣቶችን እስክስታ ተመልክተን፣ የመዋኛውን ቦታ ቃኝተን፤ ዋናተኞችን አይተን፣ የታቦታቱን አደራ ለቀሳውስቱ፣ ካህናቱና መነኮሳቱ ሰጥተን ለሚቀጥለው ቀን ቀጠሮ በመያዝ የጥምቀትን ዋዜማ በዚህ አጠቃለን ወደ ቤታችን ተመለስን። በማግስቱ ጠዋት የቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት አብቅቶ፣ ፀበል ተረጭቶ፣ ታቦታቱ ካደሩበት የዐፄ ፋሲል ባለ ሶስት ፎቅ መዋኛ ሕንፃ እየወረዱ የግቢውን በር ትተው ወደየመጡበት መጓዝ ጀመሩ። በዋዜማው ከተገኘው ይልቅ በዕለተ ጥምቀቱ የተገኘው ሕዝብ በእጅጉ ይበልጣል። እንደ ዋዜማው ሁሉ ትኩረቴን የታቦታት ሙገሳ ግጥሞችን በሚደረድሩት መነኩሴዎችና እናቶች ላይ አድርጌያለሁ። እነሱም ከታቦታቱ ኋላ ኋላ እየተከተሉ፣

 እጣን እጣን ይሸታል መሬቱ /2/

መድኃኔዓለም ያደረበቱ።

እየው ባርኮ ሲሸሽ፣

መድኃኔዓለም በሻሽ።

እየው ባርኮ ሲነሣ፤

ጊዮርጊስ ነው አንበሳ።

በማለት ያመሰግናሉ። በበዓለ ጥምቀቱ የተገኙት እናቶች ለበዓሉ ብለው ፀጉራቸውን በተለያየ የሹርባ አሠራር ተሠርተዋል። አንዳንዶቻችን ለመሆኑ የሹርባ ዓይነቶች ምን ምን ናቸው? ብለን መጠየቃችን አይቀርም። በአካባቢው በባህላዊነታቸው የሚታወቁት የሹርባ ዓይነቶች አለባሶ (ድርብ)፣ ስንቅር፣ ግልብጭ (እልም ያለ ቀጭን)፣ ግጫ፣ ሳዱላ፣ ጋሜና ቁንጮ ናቸው። ከነዚህ ሌላ ሕዝብና መንግሥት፣ አሳ፣ ጨረቃ፣ አፖሎ የሚባሉ ዘመን የወለዳቸው የሹርባ ዓይነቶችም አሉ።

እንደ ሹርባው ሁሉ የለበሱት

ቀሚስ የጥልፍ ዓይነትም ብዙ ነው።

“ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ”

እንዲሉ ያላቸውን የጥበብ ዓይነት

የሚያሳዩበትም ነው። በጥልፍ ሙያቸው የታወቁት አቶ ገበየሁ ገሥጥ ዓይነቶቹን የሃገር ባህል፣ ስንዴ፣ ጉብጉብ፣ ፍቅር ቁርጥ፣ ላሊበላ፣ ፋኖ፣ (ቆለኛ ወይም ባለ ክታብ ተብሎም ይጠራል) ሳተላይት፣ ሞረድ፣ ተመሳሳይ፣ መጋዝ፣ ማርዳ፣ ጄትና አበባ በማለት እስከ ዐሥራ ሦስት ቆጥረውልኛል። ይህ ዝርዝር የራያ ጥልፍ ተብሎ የሚታወቀውን አይጨምርም። ፋኖ በሚባል የሚታወቀው የጥልፍ ዓይነት ሦስት የተለያየ መጠሪያ እንዳለው ሁሉ ማርዳ የሚባለው የጥልፍ ዓይነትም ቅጥያ እየተጨመረለት ጉርድ ማርዳ፣ ንቅስ ማርዳና ሸረሪት ማርዳ እየተባለ ይጠራል። ከዚህ በላይ በተዘረዘሩት የጥልፍ ዓይነቶች ውስጥ ይካተት አይካተት ባላውቅም የአካባቢው ነዋሪዎች “ወፍ እግር” እና “ሰንሰለት” የሚባሉ የጥልፍ ዓይነቶችም እንዳሉ ሲናገሩ ሰምቻለሁ።

 እንደኔ ላለ የጥልፍ ጥበብን በሚገባ ማወቅ ቀርቶ ጎልቶ የሚታይን የጥልፍ ልዩነት ትኩረት ሰጥቶ ለማያውቅ ከላይ የተዘረዘሩትን የጥልፍ ዓይነቶችና ልዩነታቸውን ለሌላ ሰው መግለፅ እጅግ አስቸጋሪ ይሆንበታል። በእርግጥ የራስን ባህላዊ ልብስ ዓይነት ጠንቅቆ

“በበዓለ ጥምቀቱ የተገኙት እናቶች ለበዓሉ ብለው ፀጉራቸውን በተለያየ የሹርባ አሠራር ተሠርተዋል። አንዳንዶቻችን ለመሆኑ የሹርባ ዓይነቶች ምን ምን ናቸው? ብለን መጠየቃችን አይቀርም። በአካባቢው በባህላዊነታቸው የሚታወቁት የሹርባ ዓይነቶች አለባሶ (ድርብ)፣ ስንቅር፣ ግልብጭ (እልም ያለ ቀጭን)፣ ግጫ፣ ሳዱላ፣ ጋሜና ቁንጮ ናቸው።”

ማወቅ አስፈላጊ ነው። በተለይም የሥዕል ባለሙያዎች ልዩነታቸውን ማወቃቸው ለሙያቸው ጥራትና ብቃት እንዲሚረዳቸው አምናለሁ። እስኪ ስለ ጥቂቶቹ ልንገራችሁ፡-

ፍቅር ቁርጥ የሚባለው የጥልፍ ዓይነት ከላይ ወደ ታች የሚወርደው ጥልፍ ከሁለትና ሦስት ቦታ ላይ ሳይያያዝ ወይም ክፍተት ኖሮት የሚወርድ ቀጭን ጥልፍና ከሁለትና ሦስት ቦታ ላይ በመስቀል ቅርፅ የተጠለፈ ጌጥ ያለው ነው። በስተኋላ ደግሞ ከዐንገትዬ ወረድ ብሎ ከወገብ በላይ በሚያርፈው ልብስ ላይም የመስቀል ቅርፅ ያለው ጥልፍ ይደረግበታል።

ፋኖ (ቆለኛ ወይም ክታብ) የሚሉት ደግሞ ከላይ ወደ ታች ከዐንገት ወደ ጀርባ የሚወርድ ጥልፍ ቢኖረውም በግራ ቀኝ ጡት ላይ የሚያርፈው ልብስ ላይ ስፋት ያለው ክብ መሰል የጥልፍ ንቅስ መኖሩ ልዩ ያደርገዋል።

ሳተላይት የሚሰኘው የጥልፍ ዓይነት በአብዛኛው ስፋት ያለው በመሆኑ የራያ ጥልፍ ተብሎ ከሚታወቀውጋር ይወዳደራል። በቀሚሱ መጨረሻ ዙርያውን አነስተኛ የመስቀል ቅርፅ ያላቸው ጥልፎች ይታያሉ። እነዚህንም ዙርያ ጥልፍ ይሏቸዋል። ከላይ ከተዘረዘሩት የጥልፍ ዓይነቶች በተጨማሪ በብዙ ቦታዎች የሚታወቀውን የራያ ጥልፍ ገበያ አምጥቶት ለጥምቀት በዓሉ የለበሱት ሴቶች ቁጥር ብዙ ነበር።

ስንቅር በሚባለው የሹርባ ዓይነት ፀጉራቸውን ተሠርተው፣ ፈርጥ ጨምረው ራሳቸውን በቀልቤ (ሻሽ) ሸብ አድርገው በፍቅር ቁርጥ የጥልፍ ዓይነት ካጌጠው ቀሚሳቸው ላይ ቀጭን ኩታቸውን (ሞራቸውን ወይም ዐይነበጓቸውን) ደርበው እግራቸውንም ሆነ እጃቸውን በእንሶስላ አቅልተው ባማረው ተረከዛቸው ላይ ያረፈው የአልቦ ጌጥ ተዳምሮ የጎንደር ሴቶችን ውበት አጉልቶታል።

 የገጠሩን ባህል እንደጠበቁ የያዙት ደግሞ ረዥሙ ቀሚሳቸው አገር ባህል በሚሉት የጥልፍ ዓይነት ያጌጠ ከመሆኑም በላይ ሙሉ እጅጌ ያለው በመሆኑ እስከ እጃቸው መዳፍ አጥልቀው ከእጅጌው ጫፍ ላይ ካለው ጥልፍ ጋር ተያይዞ በተተከለው “ወቶ ማቲክ” ቆልፈውታል። ልብሱ በዘመናዊ የሴቶች ልብስ አሰፋፍ ያልተሰፋ በመሆኑ ወገብ ላይ ማቆሚያ ወይም መሰብሰቢያ ነገር የግድ አስፈልጎታል። በመሆኑም በትፍትፍ (በተለያየ ጥለት ባጌጠ) ሙሉ ውርድ መቀነት ሸብ አድርገው በአልቦ ለአጌጠው እግራቸው የሚስማማ ጫማ ተጫምተዋል። እዚህ ላይ ስለ በዓለ ጥምቀት አክባሪዎች መናገሩን አቁመን፤ ስለ አከባበሩ ሥነ ሥርዓት ማውጋታችን እንቀጥል።

 ከፊት “ሆ” በሚሉት ወጣቶች፣ ከኋላ በመነኩሴዎችና እናቶች የሚታጀበው ታቦት ጉዞው ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ቀጥሏል። ቄሶችና ካህናት ፅላት የተሸከሙትን ቄሶች ክብብ አድርገው ያዘግማሉ። ሰፋ ያለ ቦታ ሲገኝም ጉዟቸውን አቁመው ዝማሜውን፣ መረግዱን፣ ማስረገጡንና ማሸብሸቡን በከበሮ ታጅበው ያቀልጡታል። በዚሁ የእረፍት ማድረጊያ ቦታ መነኩሴዎችና እናቶች ግጥም በማውረድና እስክስታ በማለት ለታቦታቱ በረከት ያቀርባሉ። ከወጣቶች ብዙዎች ክብ ሠርተው “ሆ” ይላሉ። ሌሎች ደግሞ “ሰይ ሰይ” ይጫወታሉ። ይህ “ሰይ ሰይ” የሚባለው ጨዋታ “ምክቶሽ” ብለን ከምንጠራው ራስን ከዱላ በዱላ መከላከል ጋር ይመሳሰላል።

“ሰይሰይ” የሚጫወቱት ብዙ ጊዜወጣቶች ናቸው። ሰፋ ያለ ቦታ ላይ ወጣቶች ክብ ሰርተው ይቆማሉ። በዕድሜያቸው ወይም በጉርምስናቸው ተመጣጣኝ የሆኑ ሁለት ወጣቶች ለዚሁ ተብሎ ወደ ተተወው ቦታ ይገባሉ። ከዚያም በቁመታቸው ልክ ከመሬት ከፍ አድርገው ዱላዎቻቸውን አነካክተው ይቆዩና ቀስ ብለው ጨዋታውን ይጀምራሉ። ቀስ ብሎ የተጀመረውን ዱላ አንደኛው ወደ ሌላኛው ሰውነት ማስጠጋትና መከላከል በጣም እየፈጠነ በመሄድ ለዓይን ክትትል የሚያስቸግርበት ደረጃ ላይ ይደርሳል። በዚህ ጊዜ አንደኛው ቀልጣፋ ሆኖ ሌላኛው ዳተኛ ከሆነ ቀልጣፋው ዳተኛውን ይመታዋል። የሚመታውም ከጉልበት በላይ ከትከሻ በታች ነው። አመታቱም በቅልጥፍና እኔ እበልጥሃለሁና ንቃ ለማለት ይመስላል። ተመቺው በመመታቱ ተቆጥቶ ከጨዋታው በማለፍ ወደ ጠብ አያመራም። የሁለቱ መሸናነፍ የሚለካው በዚሁ በመሆኑ ተሸናፊውን በመተካት አሸናፊውን ለመግጠም “ችሎታ አለኝ” የሚል ክብ ሠርተው ከቆሙት ወጣቶች መካከል አንዱ በራሱ ፍላጎት በመምጣት ይገጥመዋል። አንዳንድ ጊዜ ሁለቱም መሸናነፋቸውን ለተመልካች አሳውቀው ቦታውን ለሌሎች ይለቃሉ።

ታቦታቱ ጉዟቸውን ሲቀጥሉ ከኋላ ሆነው የሚያጅቡት እናቶች የተጓዙበት መንገድ ለከርሞ እሾኽና እንቅፋት እንዳይኖረው በመመኘት፡- ላሎ መንገዱን አለስልሰው ከርሞ ይመጣል ያልሞተ ሰው። ከርሞ ይመጣል ያደረሰው። ይላሉ። ለሚቀጥለው ዓመት በሰላም እንዲያደርሳቸውም፡- እስኪ ዓመት ድገመኝ ጌታዬ ላመት ካደረስከኝ እኔ ምንተዳዬ። በማለት በዕለቱ የነገሠውን ታቦት ይለምናሉ። በዕለተ ጥምቀት ያልዘፈነች ሴት የታቦት ሙገሣና መማፀኛ ግጥሞችን በምትደረድረው መወቀሷ አይቀርም። ብዙዎቹ ለዓመት ያደረሳቸውን ታቦት በማመስገን በድምፃቸው ግጥም በማውረድ (በመደርደር) እና በመቀበል፣ በዐንገታቸውና በትከሻቸው እስክስታ በመውረድ ስሜታቸውን ሲገልፁ፤ አንዳንዶቹ ለዚያ ቀን የተሠሩት ሹርባ፣ ዐዲሱ ወይም የክት (ታጥቦ ወይም ተቀምጦ የነበረው) ልብሳቸው እንዳይበላሽ በጥንቃቄ በመራመድ የሌሎችን ስሜት አገላለፅ ይመለከታሉ። ይህንን ድርጊታቸውን የተገነዘቡ ግጥም አውራጆች በገለልተኝነት የሚመለከቷቸውን ፡-

ያሁኑ ኩራት ለምን ነው፣

የዛሬው ኩራት ለምን ነው፣

ሁሉም የተሠራው ለዐፈር ነው፣

እሱ አይደለም ወይ ባለቤቱ /2/

ቀጭን ኩታ ለብሶ፣ ምንድነው ኩራቱ።

በማለት የእነሱ ታዳሚዎች እንዲሆኑ ያደርጋሉ። እነዚህንም እንደ ሌሎች በእስክስታ፣ በእልልታ፣ በጭብጨባ በዓሉን እንዲያደምቁ ለማድረግ፤

ኧረ ተይ እሙሃይ ተነሺ /2/

መድኃኒዓለም ቆሞ ምነዋ ዝም አልሺ።

በማለት ይቀሰቅሳሉ። በዚህ የመቀስቀሻ ግጥም አማካይነት ተሳትፏቸውን ያላሳዩ ከሆነ ግን ሰብዕናቸውን የሚዳፈር ግጥም እንዲህ በማለት ይገጥማሉ።

ምነዋ እሙሃይ ዝም አልሺ /2/

ዋንጫ ጠላ ቢሆን አይለፈኝ ባልሺ።

ይሏቸዋል። ቅስቀሳውና ጉንተላው የበረታባቸው መነኮሳት የሚችሉትን ያህል ለመሞከር ወደ ዘፈኑ ጎራ በመቅረብ በእልልታና በጭብጨባ ከአውራጅ የሚደረደረውን ግጥም ይቀበላሉ። አንዳንዶችም ጋቢያቸውን ከትከሻቸው ወረድ አድርገው ወገባቸው ላይ በማደግደግ የጎንደሬ ባህል የሆነውን ለእስክስታ መዘጋጀትን የሚገልፀውን ውስዋሶ ጉልበታቸውን አጠፍ በማድረግ ወደ መሬት ወረድ እያሉ መወሳወስ ይጀምራሉ። በዚህ ጊዜ ጉልበታቸው የደከመ፣ ወገባቸው በእድሜ መግፋት ምክንያት አልታዘዝ የሚላቸው አይመስሉም። የእናትነት እንቅስቃሴያቸው ስሜትን ወጥሮ በመያዝ እድምተኛ ያደርጋል እንጂ። ታድያ አውራጇ ግጥም ስትደረድር ትቆይና ለእስክስታ መዘጋጀታቸውን ላሳወቁት መነኩሴዎች ተራውን ትለቃለች። በዚህ ጊዜ የሚችሉትን የተለያየ የእስክስታ ዓይነት ጀመር ተው፣ ጀመር ተው ያደርጋሉ። ችሎታቸውን ይበልጥ ሊያወጡ የሚችሉት የእስክስታው አጃቢዎች ድምቀት ሲታከልበት መሆኑን የተረዱ ግጥም አውራጆችና ተቀባዮች፡-

እሙሃይ ባለ አበባ፣

በላይ ቆብ በታች ድባ።

በማለት ይበልጥ እንዲንቀሳቀሱ ያደርጓቸዋል። በበዓለ ጥምቀቱ ላይ የተገኙት መነኩሴዎች እና እናቶች በፍላጎት ተነሳስተው፣ በአሽሙር ተጎንትለው፣ በመወድስ ተቀስቅሰው ለታቦታቱ ተገቢውን ክብካቤ ሲያደርጉ በተለያየ ምክንያት ታቦት ለማጀብ ያልመጡትን ሰዎች እኩይ ተግባር እንደፈፀሙ በመቁጠር፤

ዲያብሎስ ሞተ አሉ ከነ ሚስቱ፤

ተዝካሩን ያወጡለት እዚህ ያልመጡቱ።

መልካም ገበያ ቀረብሺ /2/

ቡናውና ቁርሱ ይቀራል ብለሺ።

ያ የማልዳው ፍትፍት ይቀራል ብለሺ።

ወይ እንደኔ ማልደሽ በመጣሺ።

ከቤት ይውላል ሞኛ ሞኙ /2/

እናትና ልጁ አንድ ላይ ሲገኙ።

በማለት ይተቻሉ። በበዓለ-ጥምቀቱ ላይ ለተገኘው ደግሞ፡-

መልካም ገበያ ገበየነ /2/

እናትና ልጁን አንድ ላይ ዐየነ።

አለቀሰ አሉ ዲያብሎስ /2/

ትንሹ ትልቁ ግሸን ላይ ሲደርስ።

አሞራ በሰማይ ሲያይህ ዋለ /2/

የጊዮርጊስ ነው እያለ።

አሞራ በሰማይ ሲያይሽ ዋለ /2/

የተክልዬ ናት እያለ።

ያገራችን መምህር፣

ቅኔው ሲያምር።

ያገራችን ደብተራ፣

ቅኔ ሲመራ።

ወፌ ብር በይ /2/

ቄሱም ዘመናይ።

ወፌ ብር በይ /2/

ዲያቆኑ ዘመናይ።

እንዲህ እንዲህ እየተባለ መስቀል አደባባይ ደረስን። ይህ ቦታ አንድ ላይ ከጥምቀተ ባህሩ ተነስተው ሲመጡ የነበሩ ታቦታት ወደየአጥቢያቸው የሚወስደውን ጎዳና ይዘው ለመሄድ የሚለያዩበት ነው። እዚህ ቦታ ላይ ከግማሽ ሰዓት በላይ በመቆየት ሊቃውንቱ በያሬድ ዝማሬ፣ ወጣቶች በሆታ፣ መነኩሴዎች እና እናቶች በታቦት ሙገሳ ግጥም ሲያስተጋቡ ከቆዩ በኋላ ፀጥ እንዲሉ ተደርጎ አቡኑ በዓለ ጥምቀቱን አስመልክተው ንግግር አደረጉ። የማሳረጊያው ንግግር እንዳበቃ እልልታው ከየአቅጣጫው ተስተጋባ። ከዚያም ታቦታቱ ወደየአጥቢያቸው የሚሄዱበትን አቅጣጫ ይዘው ጉዞ ሲጀምሩ የተለያየ ቡድን ፈጥረው ይጨፍሩ የነበሩት አቅራቢያቸው የሆነውን ታቦት አጅበው ጉዞ ቀጠሉ። እኛም የመድኃኒዓለምን ታቦት ተከትለን በመሄድ ከቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ደረስን። ወደ ቅጥር ግቢው ስንገባ አጃቢዎቹ ፀሐይ ሲመታቸው የዋለ፣ መንገድ ያንገላታቸው፣ ጭፈራ ያደከማቸው አይመስሉም ነበር። ስለት ያለባቸው የተሳሉትን የማስቀደሻ ግብር ተሸክመው ግጥም ያወርዳሉ፤ በዐንገታቸውና በትከሻቸው እስክስታ ይወርዳሉ። ሌሎች ደግሞ የተሳሉትን ጥላ ተሰብስበው በሚዘፍኑት እናቶች መካከል ሲዘረጉት እልልታው ይቀልጣል።

ኧረ እሰይ ስለቴ ሰመረ /2/

አምና ይኸን ጊዜ ተስዬ ነበረ።

እያሉ ጥላቸውን እንደዘረጉ ወደ እስክስታው መሃል በመግባት ኩታቸውን ከትከሻቸው ሳያወርዱ ትከሻቸውን ሲያርገፈግፉት እስክስታ የጎንደሬዎች ብቻ ስጦታ ይመስላል።

“ቅስቀሳውና ጉንተላው የበረታባቸው መነኮሳት የሚችሉትን ያህል ለመሞከር ወደ ዘፈኑ ጎራ በመቅረብ በእልልታና በጭብጨባ ከአውራጅ የሚደረደረውን ግጥም ይቀበላሉ። አንዳንዶችም ጋቢያቸውን ከትከሻቸው ወረድ አድርገው ወገባቸው ላይ በማደግደግ የጎንደሬ ባህል የሆነውን ለእስክስታ መዘጋጀትን የሚገልፀውን ውስዋሶ ጉልበታቸውን አጠፍ በማድረግ ወደ መሬት ወረድ እያሉ መወሳወስ ይጀምራሉ”

በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ የታየው ዐዲስ ነገር ወጣት ሴቶች “የልጃገረዱ ሊታይ ነው ጉዱ” እንደተባሉ ሁሉ የራሳቸውን ቡድን ፈጥረው እንደፈለጉት በሚታዘዝ ሰውነታቸው የሚያሳዩት እስክስታ ነበር። አጎጠጎጤያቸውም የጡት ማስያዣ ድጋፍ ሳያስፈልገው እንደሚዋጋ ቀንድ ወደ ፊት በመቆም ለእስክስታው የበኩሉን አስተዋፅኦ ሲያበረክት ታይቷል።

 ይኸው ደረትሽ ነው ያጣላው ሰውን፣

 እስኪ ሸፈን አርጊው ያጡት እንደሆን።

 ተብሎ የተገጠመው በእንዲህ ዓይነት አጋጣሚ ይሆን? በሌላ በኩል ደግሞ፤

 ሸማኔ ሲሠራ ይላል ቀለም ቀለም፤

የደረቷ ክፋት ጡት አላበቀለም።

 ሊባሉ የሚችሉ ወጣት ሴቶችም ለእስክስታቸው የጡት ታዳሚነትን አጥተው ታይተዋል። የእስክስታው ዓይነት ብዙ በመሆኑ እያንዳንዱን የእስክስታ እንቅስቃሴ ወረቀትና ብእር አገናኝቶ በትክክል ለመግለፅ አስቸጋሪ ነው። በጣም ጥቂቱን ለመግለፅ መሞኮር ግን ይቻላል። በመሆኑም አንዳንዶች ትከሻቸው ሳይንቀሳቀስ ዐንገታቸውን ወደላይና ወደፊት ሳብ ሳብ በማድረግ ወደ ግራ ቀኝ ትከሻዎቻቸው በማንቀሳቀስ የዐንገት ላይ እስክስታ የሚሉትን ያሳያሉ። ጡቶቻቸውን ብቻ ወደ ላይ በማዘለልና ወደ ጎን በማንቀሳቀስ የጡት እስክስታ ይወርዳሉ። ደረት ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሌሎች ዐንገታቸውንና ትከሻቸውን በማስተባበር የእስክስታውን እንቅስቃሴ ሲያሳምሩ፤ አንዳንዶች እጆቻቸውን ግራ ቀኝ ዳሌያቸው ላይ በማሳረፍ የዐንገታቸውንና የትከሻቸውን እንቅስቃሴ ያሳያሉ። ሌሎች ደግሞ ለእስክስታ መውረጃ ያደገደጉትን ኩታ ጫፍና ጫፍ በግራ ቀኝ እጃቸው በመያዝና ትከሻቸውንና አንገታቸውን ወደ ላይ ከፍ ከፍ በማድረግ የእንቅስቃሴው ታዳሚ ያደርጋሉ። ቆመው የጀመሩትን እስክስታ ጉልበታቸውን እጥፍ በማድረግ ወደ መሬት ዝቅ ዝቅ እያሉ እስክስታውን የሚያርገፈግፉም ነበሩ።

በመሆኑም ትከሻቸውንና ዐንገታቸውን ፍጥነት ባለው ሁኔታ ወደ ተለያየ አቅጣጫ ያወዛውዙታል። እንቅስቃሴያቸው ወደተቃራኒ አቅጣጫ በመሆኑም “አየሁሽ አየሁሽ” ወይም “አየሁህ አየሁህ” የሚባለውን የሕፃናት ድብብቆሽ ጨዋታ የሚጫወቱ ይመስላሉ። ክብ ክብ ሰርተው ሲጨፍሩ ሴትና ወንድ ተጣምረው በመግባት “እኔ አሸንፍ” “እኔ አሸንፍ” በሚል እልህ የገጠሙ ይመስሉ ነበር። ሌላ ቦታ ላይ ደግሞ እስክስታ ልውረድ ባዩ በመብዛቱ አንድ ጊዜ እስክስታ መውረድ ከጀመሩ ግጥም አውራጇ/ጁ/ ለአንድ ጊዜ እስክስታ እንዲመታ ካደረገ/ች/ በኋላ ለእስክስታ መውረጃ በተተወው ቦታ ላይ እየተወሳወሱ በመቆየት ትከሻን አሳርፎ እንደገና እስክስታ መቀጠል አይቻልም። መሃል ወርደው እስክስታ የሚወርዱትን አስወጥቶ ሌሎች ወደ መድረኩ እንዲገቡ የሚያስተናግድ በእድሜም ሆነ በሰውነት ጥንካሬ ከሁሉም የተሻለ ሰው ስላለ እነሱ ካልወጡ ገፍትሮም ቢሆን ያስወጣቸዋል። ይህ የሚደረግበት ምክንያት ሁሉም እስክስታ ለመውረድ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ስላለ እንዲዳረስ በማሰብ ይመስላል።

በቤተክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ የነበረው ጭፈራ እንዲቆም ተደርጎ ቡራኬ ከተሰጠ በኋላ ታቦት ወደ መቅደስ ሲገባ መነኩሴዎች እና እናቶች ደስታቸውን በእልልታ ገለፁ። ሁለት ቀናት ታቦቱን እየከበከቡና የሙገሳ ግጥሞቻቸውን እየደረደሩ ወደ ቤተመቅደስ እንዲገባ ያደረጉት መነኩሴዎች እና እናቶች፡-

ከርሞ እንገናኝ ላመት /2/

እናንተም ሳትሞቱ እኛም ሳንሞት።

በማለት የመሰነባበቻ ግጥም አሰምተውና የታቦት ሙገሳ ዘፈኑን አቁመው፤ ግማሾቹ ወደየቤታቸው ሲሄዱ የተወሰኑት ደግሞ የታቦት ሙገሳ ግጥም በመደርደርና እልል በማለት የደረቀን ጉሮሮ ለማራስ፣ በጠራራ ፀሐይ የደከመን ጉልበት ለማበረታታት መክፈልት ለማድረግ ወደ ተዘጋጀላቸው ደጀሰላም አመሩ። የወጣቶቹ ዘፈንና ጭፈራ ግን እንደተጋጋለ ቀጠለ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top