ከቀንዱም ከሸሆናውም

የጎዳናው አዝናኝ

ራሱን “አርቲስት ፈላስፋው” ብሎ ይጠራል፤ በዙሪያው ያሉ ሁሉ ይህንኑ ተቀብለውና ለሌላውም አቀብለው “አርቲስት ፈላስፋው” ብለው ይጠሩታል። “አቤት! ምን ልታዘዝ ይላል?” ክራሩን እየመታና እያቀነቀነ- በዜማ። ለራሱ ዘና ብሎ ዙሪያውን- በአደባባይ፣ በጎዳና ያለ መጪና-ሂያጁን፣ ወጪ- ወራጁን ሁሉ ዘና ያደርጋል።

 “ዲጄው! የዓሊ ቢራን፣ አንድ ሙዚቃ ልቀቅብን እስቲ” ይለዋል አንዱ መንገደኛ።

 “ምን ጣጣ አለው! አንድ ነጠላ ዜማ ይለቀ-ቀ-ቀቃል” ይላል በአማርኛ፤ በራሱ የአነጋገር ዘዬ። ከዚያም ቋንቋውን ወደ ኦሮምኛ ለውጦ የተወሰኑ ቃላት ይናገራል፤ ለጥቆም፣ ራሱ- ራሱን ማስተዋወቅ ይጀምራል። “እኔ ፈላስፋው አርቲስት ነኝ! ከራሴ ኤፍ ኤም ራዲዮ ጣቢያ፣ ከግሌ ስቱዲዮ፣ የሚተላለፍላችሁ ዝግጅት- በኔ በራሴ ከዚሁ- ከአለሁበት የቀጥታ ሥርጭት ነው፤ የራ-ሴ ራዲዮ።” ይህንኑ ፍሬ-ሃሳብ በሌላኛው የሀገር ውስጥ ቋንቋ ይደግመዋል።

የዓሊ ቢራን ዘፈን በራሱ አዝናኝ ለዛ መጫወት ይጀምራል። እናንተ (አድማጭ-ተመልካች) በሙዚቃው ስምጥ ብላችሁ አንደበቱ ላይ ጆሯችሁን ስታጣብቁ፣ ሳታስቡት በዜማ እጥፍ ይልና የጋሻው አዳልን ወይም የእሳቱ ተሰማን ወይም የዚኒት ሙሃባን የቆየ የአማርኛ ሙዚቃ ይቀላቅልበታል። እንዴ ምን ዓይነት የሙዚቃ ሽግግር ነው? ወዴት ወዴት? ብላችሁ ግር ስትሰኙ ደግሞ የኪሮስ ዓለማየሁን የቆየ የትግርኛ ጨዋታ ያስገባበትና በጥበብ ይዟችሁ ይነጉዳል። እሺ ይሁና ብላችሁ በዚህ ዜማ ሰውነታችሁ ሞቅ ሲል ደግሞ፣ ሌላ የዓሊ ቢራን ወይም ድሮ በኢትዮጵያ ራዲዮ ይደመጥ የነበረ የሶማሌኛ ዘፈን መዝጊያ አድርጎት እርፍ።

የፈጠራ ጥበቡ ድንቅ ብሎዎት ሆ ብለው ሳቅ- በሳቅ ይሆናሉ። ይህን የሙዚቃ ቅንጭብጭብ ወይም የሙዚቃ በየዓይነቱን ስምም አድርጎ በራሱ ለዛ (ትንሽ ሸፈፍ አድርጎ) ስለሚያቀርበው፣ በዙሪያው ያለውን ሰው አትኩሮት በቀላሉ ያገኛል። እናም በዚህ በፈጠረው ሥሙር የተግባቦት ክህሎት፣ የማስታወቂያ መልዕክታቸውን ለውሱን ማኅበረሰብእንዲያስተላልፍላቸው የተነጋገራቸውን ድርጅቶች ወይም ተቋማት ማስታወቂያ ወደ ሚፈለገው ታዳሚ በቀላሉ ያስተላልፋል። ከዚያም “ምርትዎን፣ አገልግሎትዎን በኔው በራሴ ተንቀሳቃሽ ራዲዮ ጣቢያ ያስተዋውቁ“ ሲል የራሱን ሰበር ማስታወቂያ ይለቃል። እናም ወደ ዋዛና ቁምነገር ይገባል። ያልተለመዱ ሁኔታዎችን አቀናብሮና ዜና አድርጎ ያወራል። ግማሽ እውነት፣ ግማሽ ውሸት የሆኑ ዜናዎችን ቀላቅሎ ያወራል፤ የግሌ በሚለው ራዲዮ ጣቢያው።

“የጎዳናውን አርቲስት” ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከትኩት ከሁለት ሳምንት በፊት ብሔራዊ ቴአትር፣ አንድ የአዘቦት ቀን ቴአትር ለመመልከት ወረፋ ላይ በነበርኩበት ጊዜ ነበር። የራፐር ዓይነት ኮፍያ አናቱ ላይ አጥልቆ፣ ስካርቭ የሚያህል ከረባት አድርጎ፣ ትልቅ ጥቁር መነጽር አፍንጫው ላይ ሰክቶ የተሰለፈውን ሰው እየዞረ ሲያዝናና።

ከአንደበቱ የሚወጣውን ዜማ እና መልዕክት የሚያጎላለት አነስ ያለች ዘመናዊ ‹ስፒከር› (ልክ እንደ ማይክል ጃክሰን) ከጆሮው ላይ ተሰክታ፣ ከከንፈሩና ከአገጩ መካከል ውላለች። በወገቡ ላይ በታጠቃት ትንሽዬ የፀሐይ ኃይል መጠቀሚያ (ሶላር ኢነርጂ) መሳሪያ የምትደገፍ ክራር ይዞ በጣቶቹ ይገርፋል። ቀደም ባለው ጊዜ ጋዜጠኞች ድምፅ የሚቀዱበትን ትንሽ ቴፕ (ካሴት)

ከ“ጎዳናው አርቲስት ” ጋ ጠጋ

ብሎ ለማውራት ትንሽ ትዕግስት

ይጠይቃል። እርሱን እንደ ራሱ- እንደ

ባህርይው መረዳትንና መቀበልን ግድ

ይላል። ካልሆነ ግን ትንሽ አዎንታዊ

አፈንጋጭ ሰው ይመስለኛል

በሽንጡ ላይ እንደ ሽጉጥ ታጥቋል። እናም እኒህን መሳሪያዎች አቀናጅቶ የሰራውን ተንቀሳቃሽ ‹‹ስቱዲዮ›› ታጥቆ፣ ሰው ሰብሰብ ባለበት ቦታ ሁሉውል የገባለትን ድርጅት ወይም ተቋም መልዕክት ያስተላልፋል። ይዘፍናል፣ ቀልድ ያቀርባል። ለራሱ ዘና ብሎ በዙሪያው ያሉ ሰዎችን ሁሉ ዘና ያደርጋል።

ከ“ጎዳናው አርቲስት” ጋር ጠጋ ብሎ ለማውራት ትንሽ ትዕግስት ይጠይቃል። እርሱን እንደ ራሱ፣ እንደ ባህርይው መረዳትንና መቀበልን ግድ ይላል። ካልሆነ ግን ትንሽ አዎንታዊ- አፈንጋጭ (Postive Deviance) ሰው ይመስለኛል። በብሔራዊ ቴአትር አዳራሽ ሰልፍ ላይ ያለውን ማኅበረሰብ ሲያዝናና እንደተመለከትኩት ጠጋ ብዬ ተዋወቅኩት። ስልክ ቁጥር ተለዋወጥንና በማግስቱ ቢሯችን ተገኝቶ እንግዳዬ እንዲሆን ጋበዝኩት።

“ማን ልበል?” አልኩት፤ ዘና ብሎ ቢሮውን ሲቆጣጠረው።

“አርቲስት ፈላስፋው ዲዮጋን እባላለሁ። እናት አባቴ ያወጡልኝን ሥም ከሆነ ሚሊዮን ታመነ። “አርቲስት ፈላስፋው” ብትለኝ ግን እመርጣለሁ፤ ቅጽል ስሜን በጣም ነው የምወደው።”

(በመሐል ክራሩን እየመታ መዝፈን ጀመረ፤ ዙሪያውን ባለ ሰው ላይ ለሚፈጥረው የድምጽ ጫና ጣጣም የለው።:)

“ሥራህ ምንድን ነው ወዳጄ?”

“አዝናኝ ነኝ፣የማስታወቂያ ባለሙያ ነኝ፣ ራሴ የፈጠርኳት ሜድ ኢን እዚችው ተንቀሳቃሽ ስቱዲዮ አለችኝ። እያዝናናሁ መልዕክት አስተላልፋለሁ። በሚፈልጉት ቦታ እየተዘዋወርኩ ማስታወቂያ የምሰራላቸው ድርጅቶችአሉ፤ ድጋፍ ያደርጉልኛል። መኪና አስመጪዎች፣ መኪና አከራዮች፣ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ አስመጪዎች፣ ፋብሪካዎች፣ ነዳጅ ማደያዎች ወዘተርፈ”

“ይሄን ስራ ከጀመርክ ምን ያህል ጊዜ ሆነህ?”

“በትንሹ ሁለት ዓመት ይሆነኛል።”

“ቀደም ሲል በምን ሙያ ነበርየምትተዳደረው?”

“ሁለገብ ነገሮችን እሰራለሁ። ሙያ አልፈራም፤ ኤሌክትሪክ እሰራለሁ፣ ሊሾ እለጥፋለሁ፣ ቧንቧ እሰራለሁ፣ መፋታት የሚፈልግ ባለትዳር ካለ አፋታለሁ፤ ሁለገብ ባለሙያ ነኝ።

“የኪነጥበብ ዝንባሌ አለህ? ስመለከትህ ትሞዝቃለህ። በዘፈን ትዘብታለህ? ትቀልዳለህ?”

“ከመጀመሪያ ጀምሮ የታሸሁት በኪነጥበብ ሙያ ስለሆነ እኮ ነው ሁለገብ ተዋናይ የሆንኩት። ዓለም ቴአትር ናት፣ ዜጎቿም ተዋናይ ናቸው ሲባል አልሰማህም? በሁሉም ዘርፍ እየተወንኩ ነው የምኖረው። ክራር እጫወታለሁ፤ የኪነ-ጥበብ አንዱ ክፍል ደግሞ “ፊሎሶፊ” ነው። ፍልስፍናን እኖረዋለሁ። ነገሮችን በራሴ አንግልና እይታ ነው የምመለከታቸው። ምንም ነገር አላካብድም። ህይወትን ቀለል ነው የማደርጋት (ቃለ-ምልልሱን አቋርጦ ደግሞ ይዘፍናል፤ ይቀልዳል) ከሰው ጋርም ሆነ ከእንስሳ ጋር ተግባቢ ነኝ። ግን ሁለቴ ሰላምታ አይመቸኝም። ሰላምታ ማብዛት ሠላም ላይሆን። ውሸት ማውራት አይመቸኝም። ደግሞ እውነት ካወራህ እውነት አወራህ ነው- በቃ። መሃላ ምን ያደርጋል? ትርፍ ነው፣ አያስፈልግም።”

“ህዝብ በተሰበሰበበት ቦታ ላይ ነው ማስታወቂያ የምትሰራው?”

“በመንገድ ላይም እሰራለሁ። ድርጅቶቹ መኪና ካቀረቡ አሊያም ከተኮናተሩ በመኪናም ዘና ብዬ እየዞርኩ ፈሳሽ መጠጥ በ‹ስትሮው› እየሳብኩ እሰራለሁ። በእግር እየዞርኩም እሰራለሁ።” “ብሔራዊ ቴአትርስ ምን እየሰራህ ነበር?” “ወደ ቤት እየገባሁ ስለነበር በእግረ መንገድ የራሴን ራዲዮ ጣቢያ ለምን አላስተዋውቅም በሚል ነው። ሰው ሰብሰብ ብሎ ሳይ ይመቸኛል። ፈታ አደርጋቸዋለሁ።”

“የራዲዮ ጣቢያህ ፍሪኮንሲ በስንት ላይ ይገኛል?”

“ፍሪኮንሲው ስልክ ቁጥሬ ነው። እኔ በሄድኩበት ቦታ ሁሉ ተደማጭ ነው ጣቢያዬ።” “ባለ ትዳር ነህ ወይስ ወንደላጤ?” “በቅርቡ ለምታገባኝ ሴት በግልጽ ጨረታ ራሴን አቅርቤያለሁ። የማይመለስ መቶ ሺህ ብር ቢቀርብልኝ ደስ ይለኛል፤ ግን ጨረታውን የመሰረዝ መብቴ ተከብሮ ነው።”

“ሰፈርህ የት ነው?”

“አሁን የምኖረው አዲስ ከተማ ነው። ትውልዴ ግን ‹‹ሜድ ኢን›› ጨርቆስነው። ልጅነቴ እዛ ነው ተሟጦ ያለቀው። ከዛ በ‹‹ስኮላርሺፕ›› በተለያዩ ሠፈሮች ኖሬያለሁ፤ ለምሳሌ ሳሪስ። ተባራሪ ነው-ኑሮዬ። አየር ባየር ነውየምኖረው።”

“ተንቀሳቃሽ ራዲዮ ጣቢያህ ከማስታወቂያ ገቢ በተጨማሪ የሚያስገኝልህ ሌላ ገቢ አለ?”

“በተሰጥኦዬ ዝም ብሎ ማወዣበር ነው የምሰራው። ደስ የሚልህ ነገር መደበኛ (ፎርማል) ነገር የማይወድ ብዙ ሰው አለ የተሰላቸ። እና እነሱ ያሳዝኑሃል። የተለመደው ነገር ሁሉ የሰለቸው ህዝብ በከተማው ውስጥ በዝቷል። አሁን በትክክል ብትዘፍን የሚጠላህ ሰው አለ የማያደንቅህ። ኧረ እንደውም ተነስቶ ልፈንክትህ የሚል አለ። ብዙ ሰዎች “አንተ እያሾፍክ፣ እያላገጥክ፣ ሙድ እየያዝክ ለመኖር ነው ወደዚች ምድር የመጣኸው” ይሉኛል። ካሳንችስ ብትሄድ አይለቁኝም። ስታዲዮም ብትሄድ አይለቁኝም፣ ሳሪስ ብትሄድ አይለቁኝም፤ መርካቶ አይለቁኝም። በግብዣ ያጣድፉኛል። እኔም ዘና አደርጋቸዋለሁ። ሰው ፈታ ማለት አለበት። ሰውን ሳዝናና ራሴም ተዝናንቼ በሰላም ቤቴ እገባለሁኝ።”

(ክራሩን እየመታ መዝፈን ጀመረ። አሁን ደግሞ በሙዚቃው ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ ነጉዷል።) ከፈላስፋው ጋር ጭውውታችንን በማገባደድ ላይ ሳለን፣ “ማኔጂንግ ዳይሬክተሬንና ጠባቂ ጋርዴን ላስተዋውቅህ” አለኝና አቶ ዳግም አማረ የተባለ ሰው አስተዋወቀኝ። “ይህ ሰው አመጋገቤን፣ አለባበሴን፣ አዋዋሌን ሁሉ ነው የሚቆጣጠርልኝ። እንደገና ደግሞ የቤት መኪናውን አቅርቦልኝ ሾፌሬም ሆኗል” አለኝ።

አቶ ዳግምን ከፈላስፋው ጋር እንዴት ተዋወቃችሁ ስል ጠየቅኩት።

“ፈላስፋው ሳሪስ አካባቢ ያለውን ማኅበረሰብ በማዝናናት ላይ ሳለ ተመለከትኩት። ሰው ይስቃል፣ ከመኪናዬ ወርጄ ተመለከትኩት አዝናናኝ። የሚዘፍናቸውን ዘፈኖች ከዋናዎቹ ዘፋኞች ለወጥ አድርጎ ስለሚዘፍንና አንዱን ዘፈን ከአንዱ እያያያዘ ስለሚኮምክ ያዝናናል። እንዲህ የሚያዝናና ሰው ገጥሞኝ አያውቅም። እና ይሄ ልጅ አጋዥ ቢያገኝ፣ ብዙ ይሰራል ብዬ አሰብኩና አነጋገርኩት። ተግባባን፣ እነሆ አብረን መሥራት ከጀመርን አንድ ዓመት ሆነን። ለእኔም የገቢ ምንጭ ጨመረልኝ። እሱንም አበረታሁት፣ ከድርጅቶች ጋር እየተነጋገርን ሥራችንን ከፍ አደረግነው። ሁለታችንም ተጠቃቀምን። ቀደም ሲል በመኪናዬ ሀገር የሚጎበኙ ሰዎችን ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ ነበር ሥራዬ። አሁን ግን የፈላስፋው ማኔጀር፣ ጓደኛ፣ ሾፌር ሆኜ አብረን እንሰራለን። ቀደም ሲል ትንሽ ሰርቶ አንድ ቦታ ድራፍት- ቢራ ሲጠጣ ነበር የሚውለው። አሁን ሁሉን ነገር በወጉ ነው የሚያደርገው። መጀመሪያ ሥራ እንደሚቀድም ተስማምተናል፤ ብዙ ስፖንሰሮች አግኝተናል። ኖክ በየሳምንቱ የምንቀሳቀስበትን የነዳጅ ኩፖን ፈቅዶልን እንቀዳለን። እኛም በምትኩ በምንሄድበት ቦታ ሁሉ እያዝናናን የማስታወቂያ ሥራ ለድርጅቱ እንሰራለን። በዚህ ሥራ ሁለታችንም ውጤታማ ሆነናል።” በዚሁ ከፈላስፋውና ከማኔጀሩ ከአቶ ዳግም ጋር ያደረግነውን ውይይት አጠናቀን ተሰነባበትን። q'(U]��l��

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top