አጭር ልብወለድ

“ወይነዶ!”

የባህር ማዶ ወግ

ይህቺ ሊዛ የሚሏት፣ አብራኝ የምትሠራ አሜሪካዊት፣ ሁኔታዋ አይጥመኝም። እንደው ነገረ ሥራዋ

አይገባኝም። ምን እንዳደረግኳት ወይ በምን እንዳስቀየምኳትም አላውቅም። ብቻ አልፈቀደችኝም። ውቃቢዬ አላማራትም። ወይም ላለዝበውና ኮከባችን አልገጠመም። እግዜር ደግ ነው አለቃዬ አይደለችም። እንጂ አቃጥላ በገደለችኝ ነበር። ታዲያ በጨዋታ መሃል ይህን ያነሳሁለት አንድ ባልደረባዬ፣

“ቅረባት፣ ዋናው መፍትሄ ጠላትንምቢሆን ቀርቦ ወዳጅ ማድረግ ነው” አለኝ።

እንዴት አድርጌ? ሲፈጥራት ነፋስ ናት። ከነፋስ ጋር ወዳጅ መሆን ይቻላል? አሁን እዚህ አይተዋት በደቂቃ ውስጥ እላይኛው ፎቅ የምትገኝ። ከራሷ የተጣላች የሚሏት አይነትም ናት። እኔ ደግሞ ቀስ ያልኩ፣ ቁጥብ፣ ድምፄ የማይሰማ፣ መኖሬና አለመኖሬ በዳሰሳ የሚለይ ነገር ነኝ።

ብቻ ትመጣና ምን እየሠራሁ እንደሆነ አይታ ትሄዳለች። ከዚያ ‘እንዲህ ያለ ድረ-ገጽ ከፍቷል፣ እንዲህ የመሰለ ሙዚቃ ያዳምጣል’ እያለች ታወራለች። ታስወራለች። በምሳ ሰዓት ደግሞ ‘ዳይት’ ላይ ነኝ እያለች አፕል በስፕራይት የምታወራርደው ሰው ከስብሰባ የተራረፈ የነፃ ምግብ ካገኘች አጠገቤ ተቀምጣ ታሻምደዋለች።

 እኔ ፊት ስትሆን “Your food smells good” (ያንተው ምግብ ደግሞ ያውዳል ጃል!) ትለኛለች። እኔም አንዳንዴ ቅመሺው እያልኩ እጋብዛታለሁ። አንድ ሁለቴ ጎራርሳ፣ ወጥ የነካኩ ጣቶቿን ላልሳ ታንኪው ብላኝ ትሄዳለች። አለፍ ስትል ደግሞ ‘ለሶስት ሰው የሚበቃውን ምግብ ብቻውን ጭጭ ያደርገዋል’፣ ምናምን እያለች ታወራለች። ደግነቱ አሜሪካውያን ምስጢር እሚባል ነገር ስለማያውቁ ወዲያው ነው አምጥተው የሚነግሩኝ። ድንገት ሃገሬን የሚመለከት ክፉ ዜና (መቼም በጎ በጎውን አይፅፉት) በጋዜጣ ወጥቶ ያየች እንደሆነ ደግሞ የሃዘኔታ በሚመስል ግን ውስጡ ተንኮል ነገር ባዘለ ቃና፣ “Have you seen this?” (ይህን ነገር ተመልክተኸዋል?) ብላኝ ታልፋለች። ወይም ደግሞ “I’m so sorry there is no good news” (አዝናለሁ፣ ቸር ወሬ አይደለም) የሚል ማስተዛዘኛ መሰል ነገር ጣል ታደርጋለች። አንዳንዴ ጋዜጣው ከእሷ በላይ ያናድደኛል። እነዚህ ያደገው ዓለም ጋዜጠኞች የወሬ ጥማታቸው፣ አለቃቀማቸውና አሠረጫጨታቸው ይገርመኛል። አፍሪካ ውስጥ ሲሆን ግን ሰው ካልሞተ፣ ወይ አገር ካልተቃጠለ፣ ወይ ችጋር ካልገባ፣ ወይ እርስ በርስ ካልተጋደልን ሌላው ነገር አይጥማቸውም። ‘ታሰረ’ ያሉትን ሰው ሲፈታ ወሬውን አያነሱትም። ፈረሰ ያሉት ድልድይ ሲታነፅ፣ ተናጋ ያሉት መንግስት ሲፀና በዘገባቸው አይጠቅሱትም። ጭራሽ አያስታውሱትም። እርግጥ ነው እኛም እንመቻቸዋለን። ዜናውን እንደሚፈልጉት አድርገን በተግባር እንሠራላቸዋለን።

ወደቀደመ ጉዳያችን ስንመለስ፣ ይህቺው ሰው አንዳንዴ፣ በተለይ ሰኞ ሰኞ፣ የእረፍት ጊዜዬን የት እንዳሳለፍኩ፣ ምን እንደሠራሁ፣ ምን እንደበላሁ ትጠይቀኛለች። የዚህ ሁሉ ምክንያቱ ስለእኔ ግድ ኖሯት ሳይሆን “አንቺስ?” እንድላት ነው። ከዚያ በኋላ ምን አይነት ፊልም እንዳየች፣ ከማን ጋር የት እንደዋለች፣ ምን እንደበላች፣ አዳሯንና አስተዳደሯን ሳይቀር ትነግረኛለች። በዚያውም ስለጎበኘቻቸው የመካከለኛውና ሩቅ ምሥራቅ መብል ቤቶች ትተርክልኛለች። ወደ ኢትዮጵያ ምግብ ቤት ሄዳ ለመመገብ ሃሳብ እንዳላትም ትጠቁመኛለች። አንድ ቀን እንደ ደህና ወዳጅ እጇን ትከሻዬ ላይ ጣል አደረገችና፣ “Which Ethiopian restaurant do you recommend?” አለችኝ። (ወደየትኛው ያበሻ ምግብ ቤት ብሄድ ይሻላል ትላለህ? እንደማለት።) እንደተለመደው ምን አይነት ምግብ እንደምትፈልግ፣ ጥብሳ ጥብስ ወይ የፆም ዘር -እነሱ ቬጄቴሪያን የሚሉትን- ከጠየቅኩ በኋላ ቀድመው ባሳቤ የመጡትን ነገርኳት።

በሳምንቱ ባንደኛው ያበሻ ምግብ ቤት በልታ ኖሮ ስትሮጥ እኔ ዘንድ ትመጣለች። ለካንስ ዘፈንና ጭፈራም አጋጥሟት ስለሱ ልታወራ ከጅላ ኖሯል። እኔ ደግሞ አስቸኳይ ሥራ ይዤ ብዙም አላዳነቅኩላትም። ሆኖም እሷን በጣም የሳባት ወንድና ሴት ጥንድ ጥንድ ሆነው አልፎ አልፎ አገጭና አገጫቸውን እያነካኩ የሚጫወቱበት “ሌምቦ” የሚሰኘው የሲዳማ ብሔረሰብ ጨዋታ ኖሯል።

ከዚያ “ይኸውልህ እነዚህ ደግሞ ብላቸው ብነግራቸው ምንም አልገባቸው አለ። እስቲ እባክህ እኔና አንተ እየጨፈርን እናሳያቸው” ትለኛለች። በልቤ ‘ሞኝሽን ፈልጊ፣ ደሞ ሃራስመንት ምናምን ብለሽ ከሥራዬ ልታስወጪኝ ነው’ ብዬ ዝም አልኩ።

 ሌሎች ባልደረቦቼ ግን የአይን አፋርነት ነገር መስሏቸው ‘እባክህ እባክህ’ እያሉ ተረባረቡብኝ። በሌላ በኩል እኔም ብሆን እንዲሁ በቴሌቪዥን ከማየቴ በቀር ሞክሬው ስለማላውቅ ተቸገርኩ። ‘ዩቲዩብ’ ላይ ገብቼ እንዳልፈልግ እንኳ ፋታ ነሱኝ። በቃ ወጥረው ሲይዙኝ ጊዜ ተነሳሁና እጅና እጇን ይዤ፣ አገጬን አገጯ ላይ ተክዬ ከፍ ዝቅ ላደርጋት ሞከርኩ። ብዙዎቹን ሳይታሰብ አዝናናቸው መሰል ጭብጨባ

በቴሌቪዥን ከማየቴ በቀር ሞክሬው ስለማላውቅ ተቸገርኩ። ‘ዩቲዩብ’ ላይ ገብቼ እንዳልፈልግ እንኳ ፋታ ነሱኝ። በቃ ወጥረው ሲይዙኝ ጊዜ ተነሳሁና እጅና እጇን ይዤ፣ አገጬን አገጯ ላይ ተክዬ ከፍ ዝቅ ላደርጋት ሞከርኩ

ቢጤ ተሰማ። ያን የሰሙት ደግሞ እንደተለመደው ‘የመልካም ልደት’ ሆታ ነገር መስሏቸው ሊያዳንቁ፣ በእግረ መንገድም ከጠበል ጠዲቁ ሊቋደሱ፣ ከየክፍላቸው እየወጡ መጡ። ነገሩን ሲያውቁ ደግሞ እንደገና እንድናሳያቸው መማፀን ያዙ።

እመቤቲት አንድ ልዩ ግኝት እንዳበረከተች ሁሉ በኩራት መንደርደሪያውን ከሰጠች በኋላ እንደገና ከፍ ዝቅ ብለን አሳየናቸው። እንደገናም ተጨበጨበ። በመሃሉ አደነቃቅፎን ከንፈር ለከንፈር ብንገናኝም ቶሎ ብዬ ሸተት አልኩ። ከዚያ በኋላ ምን አለፋችሁ ወሬውን ለቢሮው ሠራተኛ ሁሉ ለማዳረስ ሰላሳ ደቂቃ እንኳ አልፈጀባትም። በ”Power point” ማቅረብ ነው የቀራት። በዚያ ላይ በኬነዲ ሴንተር ትርኢት ያቀረበች ይመስል ኩራቷ ጣራ ደረሰ።

አንዷ ተንኮለኛ ደግሞ እኔን ለማስደንገጥ ይሁን እሷን ለማስደሰት በዚያው የፈረደበት የእጅ ስልክ ፎቶ አንስታን ኖሯል። በማግስቱ ቢሮዬ ገብቼ ኢሜሌን ስከፍት “Kissing while dancing” (“እየደነሱ መሳሳም” ወይም “እየተሳሳሙ መደነስ” እንደማለት) የሚል ርዕስ የሰጠችውን ፎቶ ልካልኛለች። ይህቺው ሰው ለካንስ ፎቶውን ለብዙ ሰው በትናው ኖሮ በመንገድ ላይ የሚያገኙኝ ባልደረቦቼ ሁሉ ‘ከሊዛ ጋር ቆንጆ ዳንስ አሳያችሁ አሉ፣ የሚቀጥለው ፕሮግራማችሁስ መቼ ነው?’ ይሉኛል። ልክ ኮንሰርት ያቀረብን ያስመስሉታል። ስቄ አልፋለሁ። ሲደጋገም ግን አናደደኝ፣ አስጠላኝም።

አንድ ቀን በጣም ወዳጄ የሆነ፣ መሥሪያ ቤቱን ያስለመደኝ ማለት ይቻላል፣ ጥሩ ሰው “ይኼ ነገር እውነት ነው እንዴ?” ሲል ይጠይቀኛል።

“ምኑ?”

“ሊዛ የነገረችኝ?”

እጢዬ ዱብ አለ። አሁንም አልተወችኝም ማለት ነው?

“ኧረ ዝም ብላ ነው የምትቀባጥረው!”

“ኖኖ እንደዚህ ባለ ታለንትህን (ችሎታህን) በሚያሳይ ነገር ላይ አይን አፋር መሆን የለብህም። ይህ በጣም ጥሩ ዕድል ነው። በነገራችን ላይ በዓመታዊ ስብሰባችን ላይ ሁሉ ይቅረብ እየተባለ ነው።” “ምን?” ‘እስቲ እንግዲህ የት አባቴ ልሂድላት?’ አልኩ በሆዴ። ወዲያው ግን ሃሳብ መጣልኝ።

“እንዴ ይህን ያህል የሰዎችን ስሜት የሳበ ከሆነና ማኔጅመንቱም ከተስማማበት ለምን ዋናዎቹን ባለሙያዎች ተኮናትረን አናመጣቸውም? ችግር የለውም፣ እዚሁ ዋሺንግተን ዲሲ ነው ያሉት። እንደውም ሌሎች ግሩም ግሩም የሆኑ ጨዋታዎችንም አብረው ያቀርባሉ። በዚያ ላይ እንዲህ ያለ የባህል ትርኢት በአልባሳትና በቁሳቁስ ተሟልቶ ሲቀርብ ነው ድንቅ የሚሆነው”።

“በዛ ደረጃ ለማቅረብ ፕላን ማድረግ ይጠይቃል። ከጊዜ፣ ከገንዘብ፣ ምናልባትም ከቦታ አንፃር ማለቴ ነው። በዚያ ላይ የእናንተው እንደ “Fun stuff” (ቀልድ ነገር) ነው የተወሰደው።”

ምንድነው? ምን አይነት ወሳኝ ሰው ቢኖራት ነው ይህን ያህል እሷ ያለችው የፈቀደችው የሚፈፀምላት? እንዴ! እኔስ አልጠየቅም? የእኔስ መብት አይከበርም? አልፈልግም አልኩ። አሁን ደግሞ በተለያዩ ሰዎች፣ በተለይ በማከብራቸው ወዳጆቼ ያስጠይቁኛል። በቃ ያን ቀን ወይም ሳምንት ታመምኩ ብዬ ቤቴ እውላለሁ። ወይም እረፍት (ቫኬሽን) እወጣለሁ ብዬ ወሰንኩ። ምሳ ሰዓት ላይ ሁኔታውን ላንድ ቅርቤ አጫወትኩት።

“አሪፍ ነዋ!” አለኝ።

“አንተ ደግሞ ምኑ ነው አሪፉ? እኔ አልፈልግም። ከዚያ ሁሉ ሰው ፊት ቆሜ አልደንስም። እሷ ስለወደደች እኔ መገደድ አለብኝ?”

“I see፣ አይናፋርነት ካለብህመፍትሄውን ልንገርህ?”

“እሺ፣ ብቻ ‘ጠጥተህ ና’ እንዳትለኝ።”

“ኖኖኖኖ!”

“ታዲያስ?”

“ከፈለግክ ብቻችሁን ሆናችሁ ትሠሩትና የ”PR & C” (የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን) ሰዎች በቪዲዮ ይቀርፁታል። ከዚያ ኮንፈረንሱ ላይ ይለቁታል።”

“የማይቀርልኝ ከሆነ፣ መቼስ በአካል ወጥቶ ከመወዛወዝ በፊልም መታየቱ እንደሚሻል ጥርጥር የለውም” ብዬ ተስማማሁ። ግን አንድ ነገር ብልጭ አለብኝ። ምነው ያን ‘ሰለሜ’ የተሰኘ ባህላዊ የደቡብ ጨዋታ አይታልኝ መጥታ በሆነ ኖሮ! ጅራፍ ቢጤ ፈልጌ በዚያ ሾጥ እያደረግኩ አዘፍናት ነበር።

ወይ ነዶ!

ጥር 2005 ዓ.ም.

ዋሺንግተን ዲሲ

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top