ከቀንዱም ከሸሆናውም

አጫጭር ቀልዶች

በቀድሞው የካቲት መጽሔት “የአነጋገር ለዛ” የሚባልና ከባህልና ከወጋችን ጋር የተያያዙ ቀልዶችና ጨዋታዎች የሚቀርቡበት አምድ ነበር። በዚያ አምድ ላይ ስራዎቻቸውን ከሚያቀርቡ ባለሙያዎች አንዱ ሁለገቡ የቴያትር ሰው ፍሥሐ በላይ ይማም ነበር። ፍሥሐ እነዚያን ጨዋታዎች ባብዛኛው የሚለቅመው ከወላጆቹ በተለይም ከአባቱ ስለነበር ከስሙ ቀጥሎ የአባቱን ሙሉ ስም የሚጽፈውም ለዚሁ ነበር። ለዛሬ በ1980ዎቹ መጀመሪያ ላይ ከፍ ብለን በጠቀስነው መጽሔት ከወጡት የፍስሐ በላይ ይማም ሥራዎች መካከል የተወሰኑትን ትዝናኑባቸው ዘንድ መርጠንላችኋል።

መነኩሴና ሽፍታ

ወሎ ውስጥ መነኩሴ ከሚባለው አገር ተዛውሮ ሽፍታ በሚባል አገር የሚኖር ሰው ለምስክርነት ፍርድ ቤት ተጠርቶ ይቀርባል። ከዚያም ዳኛው ስሙን መዝግበው አድራሻውን ይጠይቁትና፣

“በመጀመሪያ መነኩሴ ነበርኩ። አሁን ሽፍታ ነኝ” ሲላቸው ተገርመው፣

“ምነው የፊቱን ኋላ ማድረግህ?” አሉት ይባላል።

ክፍቱን ሲገኝ

እናት ውሻ ልጇን ቡችላዋን ትጠራና ትመክራለች።

“ልጄ ስማችን እልም ብሎ ጠፋ። እባክሽ ታሁን ወዲያ እንዳትሰርቂ። ተሰው ሌማት ተሰው ድስት ድርሽ እንዳትይ አደራ”

“እሺ እንዳልሽ አደርጋለሁ። ግን ተከፍቶ ሳገኝስ?”

“ክፍቱን ሲገኝማ ግድየለም። አፍሽ ላይ እስከሚያስቀምጡት ልትጠብቂ ነው እንዴ?”

ምልልስ

አንዲት ምንም አይነት የገቢ ምንጭ የሌላት ሴት ከአንድ ልጇ ጋር ክትት ብላ መኖሯ ጎረቤቶቿን ያስደንቃቸዋል። ጦም አዳሪ አለመሆኗ እንቆቅልሽ ሆኖባቸው ከሚኖሩ ጎረቤቶቿ ጋር ትጋደዳለች፤ በወንፊቱ፣ በሰፌዱ፣ በሙቀጫው፣ በእሳት መጫጫሩ፣ ወዘተ. ከጎረቤቶቿ ጋር ትገናኛለች። ከዕለታት አንድ ቀን ልጇን እሳት ጭሮ እንዲያመጣ ትልከዋለች። ምጣድና ድስት ጥዳ ከልጇ ጋር ለመቅመስ። ታዲያ ልጁ ገል አንጠልጥሎ ወደ ጎረቤት ይበራል።

“እናቴ ስትል፣ እሳት ጭረሁ ላኩልኝ”

“ደሞ ለእሳቱ? ጫርና ውሰድ። እንዲያው ለመሆኑ የምትበሉትን ከዬት እያመጣችሁ ነው?”

“ተበድረን”

“ኧረ! ታዲያ ከዬታችሁ ትከፍላላችሁ?”

“ተበድረን”

“ይኼማ በማመላለሱ ካልተቸገራችሁ ዕዳ የለባችሁም።”

የደራና የኮራ

ራስ ሚካኤልና ራስ ወሌ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በሚል እርስ በእርሳቸው ይፎካከሩ ነበር ይባላል። በአንድ ወቅት የራስ ሚካኤል መልዕክተኛ ወደ ራስ ወሌ ዘንድ ይሄዳል። ራስ ወሌም የራስ ሚካኤልን መልዕክት ይቀበሉና መልዕክተኛው ግብር ተጥሎ እንዲጋበዝ ካደረጉ በኋላ አንዳንድ ጥያቄዎች ያቀርቡለታል።

“ስማ እንጂ ወዳጄ፣ ተናንተና ተኛ ቤት የቱ ይበልጣል?”

መልዕክተኛውም የእልፍኛቸውን ጣራና ግድግዳ መልከት መልከትያደርግና

“የእኛ ቤት ደራ ሰፋ፣ የእናንተ ቤት ደግሞ ኮራ ያለ ነው”

ብሎ ሲመልስላቸው ራስ ወሌ ደስ ብሏቸው ሽልማት ሰጥተው ያሰናብቱታል። መልዕክተኛው ከሄደ በኋላ ለመኳንንቶቻቸው ሁኔታውን ያጫውቷቸዋል።

“አያችሁ ራስ ሚካኤልን እንደምበልጠው፣ የገዛ አሽከሩ መሰከረበት።”

“ጌታዬ ተመሰደብዎ መሸለምዎ ገረመን”

“እንዴት?”

“ቤታችሁ መኩራት ብቻ ነው እኮ ነው ያለዎት”

“እንዲያ ኖሯል? ወይኔ ልውጡ!”

የዓይን ማረፊያ

አንድ ሰው በጠና ታሞ ከቤቱ ተኝቶ ጎረቤትና ዘመድ አዝማድ እየተመላለሰ ይጠይቀዋል። አንድ ቀን ህመሙ በርትቶበት በጣር ሲሰቃይ በቤቱ ሙሉ የተቀመጡት ጠያቂዎቹ ከንፈራቸውን እየመጠጡ ያላዝናሉ። በሽተኛውን እየተመለከቱ አስተያየታቸውን ይናገራሉ። ሕመምተኛው ልጆቹን ሲመለከት፣ “ልጆቹን እየተሰናበተ፣” ሚስቱን ሲያይ “ሚስቱን እየተሰናበተ፣” “ቤቱን፣ ጣራውን፣ ግድግዳውን” ወዘተ. እየተሰናበተ ነው እያሉ አይኑ ያረፈበትን ነገር ሁሉ እየተከታተሉ ሲያስቸግሩት እንደምንም ተጣጥሮ አንዲት አረፍተ ነገር ይተነፍሳል።

“እ-ባ-ካ-ች-ሁ ለአይኔ ማረፊያ ቦታ ስጡት።”

አማ?

   አማ የሚባሉት ሳይንቴ አሽከራቸውን ይጠሩና የሚወዷትን የጭን በቅሏቸውን “መንገድ አሳያት” ብለው ይሰጡታል። ታጅባ በቤት ውስጥ ስለቆየች እግሯ እንዲፍታታ፣ ስግረቷን እንዳትረሳ ጋልቦ እንዲሞክራት ያዘዙት አሽከር በቅሎዋን እየሳበ ወስዶ መስቀለኛ መንገድ ላይ ሲደርስ “ይሄ የእከሌ አገር መንገድ፣ ይሄኛው የእከሌ፣ ያኛው ደግሞ የእከሌ መንገድ ነው … ባሰኘሽ ንጎጂ” ይልና በቅሎዋን ይለቃታል። በቅሎዋም አንደኛውን ጎዳና ይዛ ገና መፈንጠዝ ስትጀምር ከጥሻ ውስጥ ጅብ ዘሎ ይወጣና ሆዷን ዘንጥሎ ይጥላታል። አሽከርዬውም ተመልሶ ይመጣና ሁኔታውን ለጌታው ይነግራቸዋል።

“እህ መንገድ አሳየሃት?”

“ያገሩን ሁሉ ጎዳና ቆጥሬ አሳይቻት ነበር፣ ከእጄ ገና ሳትወጣ ጅብ

ተቀብሎ ጣላት።”

“አማ?” – (በስማቸው ‘አማ ይሙት!’ ብሎ በመሃላ እንዲያረጋግጥ)

“እንዴት ያማል ጌታዬ? ቀልበው የላኩለትን በቅሎ እያመሰገነ ነው የዘነጣጠላት”።

የባቄላ ግምብጥ

በግንቦት ሀሩር (በጋ) ዝንጀሮ ታማ ትተኛለች። የሚያስታምማት አባቷ የሚያስፈልጋትን እንድትነግረው ይጠይቃታል፣ እየደጋገመም ይወተውታታል።

“ልጄ ምን አማረሽ? አባትሽ እያለሁ ምን ቸግሮሽ? ያሰኘሽን ንገሪኝ።”

“ንገሪኝ ካልክማ ውል ውል እያለ አይኔ ላይ የሚንከራተት ነገርአለ።”

“እኮ ምንድን ነው?”

“ግምብጥ የጎመራ የባቄላ እምቡጥ”

“ተይው ልጄ! ይህንንማ አምና በግንቦቱ አክስትሽም እያማራት ነው የሞተችው።”

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top