ጥበብ በታሪክ ገፅ

ገዢዎቻችን እነማን ነበሩ?

መጀመሪያ ደርግ፣ ቀጥሎ ኢሕአዴግ የሀገሪቱን ሥልጣን እስከያዙበት ዘመን ድረስ ኢትዮጵያን ይገዙ የነበሩት፣ “እግዚአብሔር የምድር ላይ ክርስቲያናዊት መንግሥቱን እንድንጠብቅለት ኃላፊነት የጣለብን የዳዊት የሰሎሞን ቤተ ሰብ ነን” የሚሉ ንጉሣዊ ገዢዎች ነበሩ። ሦስቱም ገዢዎች (ማለት፣ ንጉሣዊው፣ ደርግ፣ ኢሕአዴግ) ሁሉም የሚታሙበት ወንጀል ሲኖራቸው፣ ከአሁኖቹ በቀር ማናቸውም ኢትዮጵያን ወደብሔር ፖለቲካ አልወሰዷትም። በተለየ ዛሬ በአማራነት የሚታማው ንጉሣዊ ቤተሰብ ደጋፊዎቹን የሚመለምለው በታማኝነት ጥቅም ከሚካፈሉ ኢትዮጵያውያን ውስጥ እንጂ ከእገሌ ወገን ብሎ አልነበረም። ሰሎሞናዊው ቤተ መንግሥት ከየትኛውም ጎሳ የተመለመሉ ችሎታ ያላቸው ጥቅመኞች መዶለቻ እንጂ የጎሳ ወገንተኝነት ቦታ አልነበረም። መንግሥቱ ግን ከአክሱም ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ያቋቋሙት የክርስቲያን ቤተ ሰቦች ስለነበሩ ዋናዎቹና ካህናቱ ሁል ጊዜም ክርስቲያኖች ነበሩ። የጎሳ ልዩነት ግን፣ በተለየ በትግሬዎች፣ በአማሮች፣ በጉራጌዎች፣ በሲዳማዎች፣ በአገዎች፣ በጋፋቶች፣ በኦሮሞዎች መካከል ምን ጊዜም አልነበረም። ደማቸው ከሁሉም ይጠቅሳል። ብዙዎች ጎሳዎች የጠፉት ተገድለው ሳይሆን በባህል አማሮችና ኦሮሞዎች ሆነው ነው። ይኸንን እውነታ በብዙ አጋጣሚ በማስረጃ ተችተነዋል ። ሆኖም፣ ብዙ ሰዎች፣ በተለየም የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግምባር (የኦነግ) ሰዎች፣ የማይናጋ ሃይማኖት-መሰል የታሪክ እምነት ስላላቸው እምነታቸውን የሚያናጋ እውነታ በምንም አነጋገር፣ በምንም ማስረጃ ቢቀርብላቸው ሊቀበሉት አይፈልጉም። ትግሉን በፖለቲካ ላይ ሳይሆን፣ በሌለ ብዙ ዘር፣ በሌለ አንድ ጎሳ፣ በሌለ አንድ ባህል ላይ እንዲያተኩር ያደርጋሉ።

የንጉሣዊ ቤተ ሰቦች የሚገዙትና የሚያጋዟቸውን መኳንንት የሚመለምሉት በአገልግሎትና በታማኝነት እንጂ በጎሳ እንዳይደለ የአፄ ቴዎድሮስ፣ የአፄ ዮሐንስ፣ የአፄ ምኒልክ፣ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ደም እና የመኳንንቶቻቸው ታሪክ ቢመሰክርም፣ ብዙ ጊዜ በማስረጃነት የሚጠቀሰው የአፄ ኢዮአስ ማንነት ነው። ግን የዚህ ንጉሥ ታሪክ የተመዘገበው በግዕዝ ስለሆነ፣ የንጉሡን የአነሣሥ ታሪክ እንኳን ብዙ ሰው አያውቀውም። ስለዚህ እውነታው እንዳለ ሆኖ፣ ዕውቀት ለሚፈልግ ጥቅሙ ስለታየኝ፣ ከንጉሡ ታሪክ ውስጥ ከመነሻው ላይ ቀንጠብ አድርጌ ለአማርኛ እንዲመች እያደረግሁ፣ ለጊዜው የማያስፈልጉ መሥመሮችንም እየዘለልኩ እንደሚከተለው ተርጒሜዋለሁ።

የዛሬ ሁለት መቶ ስልሳ ሶስት ዓመት የሆነውን ስናጠና፣ ንጉሥ ሲሞትና ምትኩ አልጋ ሲወርስ ምን እንደሚደረግ፣ ጸጥታ እንዳይደፈርስ ምን ዓይነት ጥንቃቄ እንደሚወሰድ፣ መኳንንቱ እነማን እንደነበሩ፣ ሥልጣን ከእጃቸው እንዳትወጣ እንዴት ነቅተው እንደሚጠብቁ፣ ታሪክ ጸሐፊው ከግዕዝ እየወጣ ወደአማርኛ ለመሄድ እንዴት እንደሚገደድ ለማየት አጋጣሚው ዕድል ይሰጠናል፤

ሰኔ 21 ቀን፣ ኃሙስ ዕለት [1747 ዓ.ም.]፣ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ በዓል ዕለት ማለት ነው፣ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አድያም ሰገድ ኢያሱ አረፈ። በዚህ ጊዜ (አብራው ትገዛ የነበረችው) እናቱ ንግሥት ብርሃን ሞገሳ (1) እሪ አለች።  “ወዮልኝ ልጄ፣ ፍቅሬ ሆይ፤ ወዮልኝ የዓይኔ ብርሃን ሆይ፤ ወዮልኝ የልቤ ደስታ ሆይ!” እያለች አለቀሰች። እንዲህ ትል የነበረው ደረቷን እየመታች፣ የራሷን ጠጉር እየነጨች፣ ከመሬት እየወደቀች ነበር። እንዲህም አለች፤

የላስታን ዓቀበት ያለፈረስ ያለበቅሎ የወጣህ፤
እንዴት በፈትል ገመድ ታሰረ እግርህ።
የሄድክ ሆይ፣ እስከ ምድረ ዋግ፤
ልታጠፋ ጠላትን (ያንን) ጠባየ ፀዋግ (2) ።
የሄድክ ሆይ፣ እስከ ምድረ ዶባ፤
ግብር ልትቀበል ከሕዝቧ ።
የሄድክ ሆይ፣ እስከ ምድረ ወፍላ፤ ለመውጋት …፤
ድንኳንክን የተከልክ በመሃከሏ ።

ደግሞም እንዲህ ትል ነበረ፤ “እንደዚህ አልጋ ላይ ተጋድመህ ከማይህ ሞቶ መቀበር ይሻለኝ ነበረ።” ዘመዶቿ ጩኸቷን በግድ አስተዋት ። “ከእንግዴህ ወዲያስ የሚሻለው ለእኛም ለዓለምም የሚበጀውን ምክር መመካከር ነው” አሏት። ከዚያ በኋላ፣ ንግሥት ምንትዋብ አሳላፊ እሸቴን (ጠርታ)፤ “ራስ ወልደ ልዑልን ጥራው” አለችው። ራስ ወልደ ልዑል በታላቅ ግርማ መጣ። መስቀል ግምብ ወደሚባለው ቤተ መንግሥት ሲገባ፣ ንጉሥ ኢያሱን አርፎ አገኘው። ደግሞ ደጅ አዝማች ጌታን፣ ደጅ አዝማች አውሳብዮስን፣ ደጅ አዝማች ማሞን አስጠራቻቸው። መጡና አይተው እንደሞተ ተረዱ። በእናቱና በዘመዶቹ ማህል ትልቅ ዋይታና ሰቆቃ ሆነ፤ ልክ (ወንጌላዊው) ዮሐንስና እመቤታችን ማርያም ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ የተሰቀለ ዕለት ዋይታ እንደሆነባቸው ።

በዚህ ጊዜ፣ ራስ ወልደ ልዑል እኅቱን ንግሥት ብርሃን ሞገሳን እንዲህ ብሎ ጠየቃት፤ “(ንጉሡ) በሕይወቱ ሳለ፣ ከ፫ቱ ልጆቹ፣ ከአቤቶ ዓፅቁ፣ ከአቤቶ ኃይሉ፣ ከአቤቶ ዋዩ፣ አልጋውን የሚወርሰው ማንኛው እንደሆነ ምን ነገር ነገረሽ?” (ዋዩ) የወሎ አሚጦ [ኦሮሞ] ልጅ፣ የሉባውና የዱላው እኅት ከሆነችው ከእመቤት ወቢ የተወለደው ኢዮአስ የተባለው ነው። ንግሥት ለወልደ ልዑል እንዲህ ብላ መለሰችለት፤ “ከዳዊት እስከ አሁን እንደነበሩ ንጉሦች አባቶቼና ዘመዶቼ በሞት ከቀደምኩሽ ልጄን ኢዮአስን አንግሺው፤ ምክንያቱም ያዕቆብ ልጁን ዮሴፍን ይወደው እንደነበረ፣ ዳዊት ዮናታንን ከአቢሳ አብልጦ ይወደው እንደነበረ፣ እኔም ከሁለቱ ልጆቼ አብልጨ እወደዋለሁ” ብሎኝ ነበር። ራስ ወልደ ልዑልና ዘመዶቿ፤ “ንጉሠ ነገሥት ኢያሱ እንዳለው ይሁን” አሏት። ሐሳቡን ወደዱት፤ ምክንያቱም ንጉሣቸው ብቻ ሳይሆን፣ ሰሎሞን ሠራዊቱ ይወደው እንደነበረ ያፈቅሩት ነበረ።

ከዚህ በኋላ፣ ራስ ወዳጄንና ባላምባራስ ዱሪን አስጠራቻቸው። ይህ ሁሉ ሲሆን ከቤተ መንግሥቱ ውስጥ የሚላላኩ ባለሟሎች ነበሩ፤ እነሱም የሻለቃ ወልደ ሐና፣ የሻለቃ አርማስቆ፣ የሻለቃ ገርቢና፣ ነጋድራስ ጌርጊስ ነበሩ። (ነጋድራስ ጌርጊስ) ንግሥት ወለተ ጊዮርጊስ የምታደርገውን እስክታደርግ ድረስ የቤተ መንግሥቱን በሮች በብረት መቀርቀሪያ ዘግቷቸው ነበር። በዚያ ጊዜ ንግሥቲቱ አሳላፊ እሸቴን፣ ራስ ወዳጄ በበቅሎ ቤት ባለበትና እነዚህ ቀደም ብለን የዘረዘርናቸው ባለሟሎች ባሉበት እንዲህ ብሎ እንዲነግራቸው አዘዘችው፤

እነሆ ድምፁ በአራቱ መዓዝነ ዓለም ባሉ ሕዝቦችና ነገዶች ዘንድ እንደመብረቅና እንደነጐድጓድ የሚሰማው፣ የምታፈቅሩት ንጉሣችሁ ኢያሱ አድያም ሰገድ አርፏል። እንግዴህ፣ ስለሚነግሥላችሁና እንደ ልጄ እንደ ኢያሱ በየጠባያችሁ ስለሚያሳድራችሁ (ንጉሥ) ምከሩ። እንዲሁ ስል የልማድ ያህል ተናገርኩ እንጂ፣ እንደ እውነቱ ከሆነስ እንደልጄ እንደ ኢያሱ የሚሆንስ አይገኝም።

ለንግሥት ምንትዋብ እንዲህ ሲሉ መልስ ሰጧት፤

ንጉሡ በቃሐ በነበርን ጊዜ እንዲህ ሲል አጫውቶናል፤ “ስሞት ምን ታደርጋላችሁ? መቸም የኖረ ሰው ሞትን ሳያያት አይቀርም።” እኛም በአንድ ቃል፣ “አንተ ከሞትክ እረኛ እንደሌላቸው በጎች እንበተናለን፤ ልክ መጽሐፉ፣ እረኛውን እገድለዋለሁ፤ የበጎች መንጋዎቹም ይበተናሉ እንዳለ” አልነው። ንጉሥ ኢያሱ ይኸንን ሲሰማ፣ “እንዲህ ያለ ነገርስ ጥሩ አይደለም፤ (መጽሐፉ እንደሚለው) ዮዳሔ የሰባት ዓመቱን ልጅ ኢዮአስን እንዳነገሠው እናንተም ልጄን ኢዮአስን አንግሡት” አለን።

አሳላፊ እሸቴ ይኸንን ስምቶ ወደንግሥት ብርሃን ሞገሳ ዘንድ ሄዶ ራስ ወዳጄ፣ ባላምባራስ ዱሪ፣ የሻለቃ ወልደ ሐና፣ የሻለቃ አርማስቆ፣ የሻለቃ ገርቢ የነገሩትን ሁሉ ነገራት። ይኸን ሲነግራት፣ “ለኔም የነገረኝ ይኸንኑ ነው፤ ያዘዛችሁን ፈጽሙ። እኔ ግን ከአሁን ወዲያ የሰማዩን መንግሥት እንጂ የዚህን የኃላፊ ዓለም መንግሥት አልፈልግም አለች ብለህ ንገራቸው” ብላ አሳላፊ እሸቴን አዘዘችው። ሄዶ ለላኩት ነገራቸው። ሰምተው፣ “መንግሥቱን እለቃለሁ፤ በዚህ ዓለም አልኖርም” በማለቷ ሲተክዙ፣ ኢዮአስን ስለማንገሥ ጉዳይ ንጉሠ ነገሥት ኢያሱ ቀደም ብሎ የነገራቸው ከእሷ ቃል ጋር አንድ በመሆኑ ተደሰቱ። ንግሥት ወለተ ጊዮርጊስን ግን መንግሥት ያለ እሷ ስለማይጸና፣ እንዳይለቋት፣ አቤቶ ኢዮአስን እንዲያነግሡ ሁሉም በኲርዓተ ርእሱ (3) ሥዕል ተማማሉ።

ከዚህ በኋላ መኳንንቱንና የፍርድ ሊቃውንቱን (4) ሁሉ ጠሩና እያንዳንዱን ለየብቻቸው አስማሏቸው። መኳንንቱና ሊቃውንቱ ደግሞ ተራቸውን ዘመዶቿን እነራስ ወልደ ልዑልን፣ ደጅ አዝማች ጌታን፣ ደጅ አዝማች አውሳብዮስን፣ ደጅ አዝማች ማሞን፣ አሳላፊ እሸቴን፣ የሻለቃ ክንፉን፣ አቤቶ የማርያም ባርያን፣ አቤቶ ወልደ ሚካኤልን፣ ሌሎችንም በቤተ መንግሥት የሚኖሩ የቅርብ ዘመዶቿን አስማሏቸው። ንግሥት ብርሃን ሞገሳ ገዳም እንዳትገባ እንዲጠብቋት አደራ አሏቸው።

መኳንንቱና ዘመዶቿ በመሐላ አንድ ከሆኑ በኋላ፣ ባላምባራስ ዱሪንና ዞጌ ያቦ ባርያን ሕፃኑን ኢዮአስን ከእናቱና ከአሳዳጊው ጋር በጥድፊያ እንዲያመጡት ተወልዶ በካህናቷ ጸሎት ወደ አደገባት ደብረ ፀሐይ ወደምትባለው ወደ ታቦተ ቊስቋም (5) ላኳቸው። አምጥተው ከመሰሪ (6) አስገቡት። ከዚያ በኋላ ከመሰሪ አውጥተው ወደ መናገሻ ግምብ አውጥተው ከፍ ካለ የወርቅ ዙፋን ላይ አስቀመጡት፤ ዓይን የሚማርክ የመንግሥት ልብስ አለበሱት፤ ዘውድ ጠባቂው ነጋድራስ ጌርጊስ ዘውዱን ይዞ መጣና እንደ ሕጉና እንደሥርዓቱ አነገሡት።

ከዚያ በኋላ አሳላፊ እሸቴ መኳንንቱን፣ ሊቃውንቱን፣ አዛዦቹን የየቤተ ክርስቲያኖቹን ሊቃውንት የጨዋ ልጆችን ሁሉ መጥተው እጅ እንዲነሡ ጠራቸው። እጅ ነሡ፤ “ንጉሥ ሆይ፣ ለዘላለም ኑር” አሉ። ደጃዝማች ጌታ ከመኳንንቱና ከሊቃውንቱ ጋር ወጥቶ፣ ከዓዋጅ መንገሪያው አደባባይ ማህል ቆመ። ሕግ ጠባቂዎች (7) ሲመጡ እንዲህ የሚል ዓዋጅ ተነገረ፤

እነሆ ንጉሠ ነገሥት ኢያሱ አርፏል፤ በሱ ቦታ ልጁ ንጉሠ ነገሥት ኢዮአስ ነግሧል፤ የሞትንም እኛ ነን፤ ያለነውም እኛ ነን፤ [ስለ ሞትን እንዘን፤ ስለነገሥን እንደሰት።]

ዓርብ ዕለት በጠዋት መኳንንቱ፤ ሊቃውንቱ፤ ሠራዊቱ፤ ሴት ወይዘሮዎቹ እና የግቢው ሰው ሁሉ ተሰብስበው ከፍ ያለ ልቅሶ አለቀሱ። ከዚያ ወደአደባባይ ወጥተው፡ የሞተውን ንጉሥ ምስል ሠሩ።

ወምበዴ የሚባለውን በቅሎውና ሎላ እና ሳልዳ የሚባሉትን ሁለቱን ፈረሶቹን በንጉሥ ልብስ አስጌጧቸው። ትልቁና ትንሹ ሁለቱ ጃንጥላዎች ተያዙ። አንድ አምበል ከፈረስ ላይ ወጣ። ሰንደቅና ነጋሪት ከሌሎች ሕግ ጠባቂዎች ጋር ወጡ። መጀመሪያ ነፍጠኛ እመካበቢያ ድረስ ወጣ፤ ቀጥሎ ከምስሉ ቀደም ብሎ ሰይፈ እጃግሬ ወጣ፤ ከምስሉ ከተል ብሎ ጋሻ እጃግሬ ወጣ። ከዚያ መኳንንቱ የኀዘን ልብስ ለብሰው ተከተሉ። በማህላቸው ደጅ አዝማች ጌታ፣ ደጅ አዝማች አውሳብዮስ፣ ደጅ አዝማች ማሞ፣ አሳላፊ እሸቴ አሉ። በወይዛዝርቱና በደረባ ቤት ማህል ከፍ ያለ ጩኸት ሆነ። የንጉሠ ነገሥቱ እናት ይቴጌ ምንትዋብ ከእናቷ ከወይዘሮ እንኰየ፣ ከብዙ የሴት ዘመዶቿ፣ ከአምቻዎቿ፣ ከይቴ አግሮዶች ጋር ኀዘን ጸናባት። በኀዘን ዜማ (በአማርኛ) እንዲህ እያሉ አለቀሱ፤

አያ በሰቀላህ ወሀ ሞላ፤ በሰቀላህ ወሀ ሞላ።
የተራበ ዘመድ እንዳይበላ።
ወይ እርሱ ሳለ ቀሊል ኢያሱ ለጋሱ።
አንት የወፍላ ንጉሡ።
እንዘን፣ አብረን አድገናል፤ አብረን እናልቅስ፤ አብረን በልተናል።
ከዝያ ሰው፣ የጌታ ባልንጀራ፤ ሞቴን ያድርገው ካንተ ጋራ።
ካንተ ጋራ ሞቴን ያድርገው።

ደግሞ የንጉሥ ኢያሱ ሎሌዎች (በአማርኛ) አለቀሱ፤

ተያይዘው አንገት ላንገት፤
ቢሞትባቸው ድንገት፤
“አለ፣ አለ” ሲሉት።
የለመዱ ሹመት፤
ያልተሾሙ በከብት፤
ከፍ፣ ከፍ ያሉም በጒልት።

ይኸንን ለቅሶ ያየና የሰማ ከጐንደር እስከ ምድር ወሰን፣ እስላም፣ አምሐራ፣ ቅማንት፤ ፈላሻ፣ ወታደር በጋሻ፤ መነኲሴ በዋሻ፤ ነጋዴ ሰው ሳይሻ፤ የሚሄድ በጣቻ ስቅስቅ ብሎ አለቀሰ።

ቅዳሜ ዕለት ሰኔ 23 ቀን ደጃዝማች ወረኛ ጐንደር ገባ፤ ንጉሠ ነገሥት ኢዮአስና ንግሥት ምንትዋብ ከመኳንንቱ፣ ከሴት ወዛዝርቱ፣ ከሌሎቹም ሠራዊት፣ ማለት፣ ከኒሳ፣ ትግሬ፣ ላስቴ፣ እጃግሬ፣ ጋሻ እጃግሬ፣ ግምጃ ቤት፣ ሰይፍ እጃግሬ ጋር በመሰሪ መከታ ነበሩ። ካለፈው የሚበልጥ ትልቅ ለቅሶ ሆነ። ባለሟሎቹ የሻለቃ ወልደ ሐና፣ የሻለቃ አርማስቆ፣ የሻለቃ ገርቢ፣ የሻለቃ ቶማ፣ የሻለቃ መርዱ ትግሬ፣ የሻለቃ ፋሬስ ክንፉ፣ የሻለቃ ከብቴ -ትርፍ ስሙ በሬ በላ- አሳላፊ እሸቴ፣ አሳላፊ ክንፉ፣ አሳላፊ ገብረ መስቀል፣ አሳላፊ ተስፋ፣ አሳላፊ ላፍቶ ጎቱ አውዶክዮስ፣ አሳላፊ ያሬድ እሸቴ ማሞ፣ አቤቶ የማርያም ባርያ፣ ዞጌ ያቦ ባርያ፣ ቢሶሪስ ገብሩ፣ አቤቶ ወልደ ሚካኤል፣ እማያ ኮቾ፣ ግራና ቀኝ ቆመው (በአማርኛ) እንዲህ እያሉ በኀዘን ዜማ አለቀሱ፤

እንዴት ዋላችሁ፤ ሳትዋጉ ድል ተነሣችሁ።
በጎም አልዋልነ፤ ሳንዋጋ ድል ተነሣነ።

በዚያ ጊዜ ግማሹ ጋሻና ጦር ይዟል፤ ግማሹ ሰይፍ ይመዛል፤ ግማሹ ጠመንጃ ያንጐደጒዳል፤ ግማሹ ቀስት ይወጥራል፤ ግማሹ ፈረሱን የጦር ልብስ እያለበሰ ጎምለል ጎምለል ይላል። ደጃዝማች ወረኛ ይኸን ሁሉ ሲያይ ከተቀመጠበት የሰቅሰቅ አሸዋ ብድግ ብሎ አብሯቸው አለቀሰ። የንጉሠ ነገሥት ኢያሱ ወዳጅ ስለነበረ፣ ከዳሞትና ከጃዊ ጋር ሆኖ ኀዘን በረታበት። ዳሞትና ጃዊ [ኦሮሞና] መጫ (8) ናቸው።

ሰኞ ዕለት፣ ሰኔ 25 ቀን፣ ንጉሡ አጃሌ ግምብ ከሚባለው ቤተ መንግሥት ገባ። አቡነ ዮሐንስ፣ እጨጌ ኤዎስጣቴዎስ፣ የደብረ ሊባኖስ ካህናት (9) በአንድነት አብረዋቸው ሲገቡ፣ ንጉሥ ኢዮአስን፣ አጃሌ ግምብ ውስጥ ከንግሥት ወለተ ጊዮርጊስ፣ ከመኳንንቱ፣ ከፍርድ ሊቃውንቱ፣ ከዓቃቤ ሰዓት ኢዮብ ጋራ ሆነው አገኟቸው። ጳጳሱ አቡነ ዮሐንስ፣ “ዘውዱን ሜሮን እንድቀባው አምጡ” አሉ። ሜሮን ንጉሥ የሚቀባበት ነው። ነጋድ እራስ ጌርጊስ ዘውዱን አመጣ። ጳጳሱ ንጉሥ ኢዮአስንና ዘውዱን በመስቀል ምልክት ቀባቸው። አክሊሉን ራሱ ላይ ደፍቶለት ለንግሥ የሚገባውን ጸሎት ጸለየ።

ማብራሪያ፤

1. ንግሥት ብርሃን ሞገሳ፣ ንግሥት ወለተ ጊዮርጊስ፣ ንግሥት ምንትዋብ የአንድ ሰው የዘውድ ስም፣ የክርስትና ስም፣ የዓለም ስም ናቸው። አገር የሚገዙት በሥርዓት ዘውድ የጫኑ ንጉሥና ንግሥት ነበሩ፤ ንግሥት የምትሆነው የንጉሡ ሚስት ብትሆንም፣ የንጉሡ እናት የምትሆንበት አጋጣሚም ይኖራል።

  1. “ጠባየ ፀዋግ” ማለት “ጠባየ ጠማማ” ማለት ነው፤ እቦታው ያልተረጐምኩት፣ ግጥሙን እንዳያበላሽ ነው።
  2. “ኲርዓተ ርእሱ” ሥዕል የሚባለው ኢየሱስ አይሁድ የሾህ አክሊል ጭነውበት የተሣለው ሥዕል ነው። ረጅም ታሪክ አለው።
  3. “የፍርድ ሊቃውንት” የሚባሉት በዳኝነት ጊዜ ፍርዱ ሕግ የተመረኮዘ እንደሆነ የሚያረጋግጡ የሕግ ተርጓሚዎች ናቸው።
  4. “ታቦተ ቊስቋም” ጎንደር ከተማ ውስጥ ንግሥቲቱ (ምንትዋብ) ያሠራችው ቤተ ክርስቲያን ነው።
  5. “መሰሪ” የአዳራሹ ስም ነው።
  6. “ሕግ ጠባቂዎች” የቤተ መንግሥቱን ሥርዓት የሚቆጣጠሩ፣ የሕጉ ቅጂ በእጃቸው ያለ ሊቃውንት ናቸው።
  7. “ዳሞትና ጃዊ [ኦሮሞ] ና መጫ ናቸው” የሚለው አነጋገር የሚያመለክተው፣ ኦሮምኛ የሚናገረውን ሁሉ ኦሮሞ ይሉት እንዳልነበረ ነው፤ ምክንያቱም ጃዊም መጫም ቋንቋቸው ኦሮምኛ ነው።
  8. የደብረ ሊባኖስ መነኮሳት በንግሡ በዓል ላይ የተገኙት ለበዓሉ ሲባል ከሸዋ ድረስ መጥተው አይደለም። አፄ ሱስንዮስ ካቶሊክ ሲሆን ደብረ ሊባኖስን አዘዞ (ጐንደር አጠገብ) አዛውሯት ነበርና ካህናቱ የመጡት ከአዘዞ ነበር።
  9. ታሪክ ጸሐፊዎቹ የሃይማኖት መጻሕፍት ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ምሳሌ መጥቀስ ይቀናቸዋል።
  10. ዘር የትም መሬት ላይ ቢዘራ ምርቱ ዘሩን እንጂ መሬቱን እንደማይመስል፣ ንጉሡ ከየሴቱ የሚወልዳቸው ልጆች ሁሉ ንጉሥ ለመሆን የሚበቁ የሰሎሞን ዘር ነበሩ።

 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top