ጣዕሞት

ብሔራዊ የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ ሊካሄድ ነው

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴያትር አዳራሽ ብዙኅን የሚሳተፉበት ብሔራዊ የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ ሊካሄድ መሆኑን አዘጋጆቹ ለዝግጅት ክፍላችን አስታውቀዋል።

የመጻሕፍት ዐውደ-ርዕዩ ከታህሳስ 20 ቀን ጀምሮ እስከ ታህሳስ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ የሚቆይ ሲሆን “ከአስተዋይ ሰው ጀርባ መጻሕፍት አሉ” በሚል መሪ ቃል የሚዘጋጅ ነው ተብሏል።

የሰው ልጅ አካላዊ እድገቱ ተጠብቆ እንደሚያድገው ሁሉ፤ በማስተዋልና በጥበብ ታንፆ እና ተኮትኩቶ እንዲበለፅግና ፍሬያማ ሆኖ ለራሱና ለወገኑ ውጤታማ እንዲሆን መጻሕፍት አዕምሮአዊ ሥንቁና ትጥቁ በመሆናቸው መሪ ቃሉን መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ሲሉ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።

የዐውደ-ርዕዩ መካሄድ አንባቢን ለማበረታታት፣ ወጣት አንባቢያንን ለመደገፍና ወጣቶችን ከመንገዳቸው ከሚጎትቱ አልባሌና ጎጂ ተግባራትና ሥፍራዎች ታድጎ በዕውቀትና በጥበብ ዓለም መሰማራት እንዲችሉ ማገዝን ዓላማ አድርጎ የሚዘጋጅ ነው ተብሏል።

ከታህሳስ 20 ቀን ጀምሮ በብሔራዊ ቴያትር ጋለሪ የሚጀመረው ዐውደ- ርዕይና የመጻሕፍት ሽያጭ መንፈሳዊ፣ ዓለማዊና ለተማሪዎችና መምህራን አጋዥ የሆኑ፤ እንዲሁም የመጻሕፍት ወዳጆች በየፍላጎታቸው የሚመርጧቸውን ከድሮ እስከ ዘንድሮ ያሉ መጻሕፍት ያካተተ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

ዓውደ- ርዕዩ ከ20 – 50 በመቶ ቅናሽ እንደሚደረግበት የጠቀሱት አዘጋጆቹ፣ በዘጠኝ ቀናት ቆይታው ለመጻሕፍት አንባቢያን ከቅናሹ በተጨማሪ ለወዳጆቻቸው የሚያበረክቱት ነጻ የመልካም ምኞት መግለጫ ካርድ ከመጻሕፍት ጋር በሽልማት እንደሚቀርብም ተናግረዋል።

በራሳቸው በመጻሕፍት አቅራቢዎችና ደራሲያን በኩል የሚዘጋጀው ይኸው የመጻሕፍት ዐውደ-ርዕይ እና ሽያጭ ፈላጊውን ከተፈላጊው ጋራ ድልድይ ሆኖ የሚያገናኝ ነው ብለዋል።

በአደጉት አገራት ይህ ዓይነቱ ተግባር በራሳቸው በመጻሕፍት አቅራቢዎች በኩል የሚተገበር ሲሆን፤ ሁኔታው ራሱን የቻለ ኢንዱስትሪ ሆኖ እንዲበለጽግና ዘርፉም ራሱን ችሎ እንዲቆም ከማገዙ በላይ፤ የመጻሕፍት አሳታሚዎችና አከፋፋዮች በመተባበር ሊሰሯቸው የሚገባቸውን ሥራዎች ለመመካከርና ለመደጋገፍ ሁነኛ አጋጣሚን ያመቻቻል።

ከገበያ የጠፉትን፣ የቆዩትንና በቅርብ ጊዜ ለህትመት የበቁ ልዩ ልዩ መጻሕፍትን በቀጥታ ከአቅራቢዎቹ እጅ ለማግኘት ዕድል የሚፈጥርላቸው እንደሆነ አዘጋጆቹ ከአስራ አንድ በላይ የሆኑ የመጻሕፍት አቅራቢዎች ገልጸዋል።አንባቢያን ከታኅሳስ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በብሔራዊ ቴያትር ጋለሪ እየተገኙ መስተናገድ እንደሚችሉም የዝግጅቱ ዋና አስተባባሪ አቶ በፍቅሩ ዳኛቸው ተናግረዋል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top