ጣዕሞት

“ጊዜ ቢነጉድም” አልበም እየተደመጠ ነው

ጌዲን እንደዋዛ እና ዜማ አማን አልበም በገበያ ላይ ዋሉ

የድምፃዊት ሚካያ በሀይሉ “ጊዜ ቢነጉድም” አዲስ አልበም፣ በጆሮ ገበያ ውስጥ በመደመጥ ላይ ነው። ድምፃዊቷ በህይወት በነበረችበት ጊዜ ዘጠኝ አዳዲስ የሙዚቃ ግጥሞችንና ዜማዎችን ደርሳ፣ለአዲስ አልበም ዝግጁ አድርጋ ተጫውታ ነበር። ሚካያ ያሰናዳቻቸው የሙዚቃ ሥራዎች ተሰባስበውና የሁለት ተጋባዥ ድምፃውያን ሦስት ሥራዎች ተካተውበት ነው አልበሙ የቀረበው።

ድምፃዊ ሚካያ የዘፈን ግጥሞችና ዜማዎችን በመድረስ የተካነች፣ ለጆሮ የሚስማማ ጥዑም ድምጽ የነበራት፣የሙዚቃ ድንቅ ተሰጥዖ ባለቤት፣ ለጥበብ የማለለች፣ በኪነጥበብና በሥነጽሑፍ እውቀት የዳበረች ድምፃዊት ነበረች ሲሉ የጥበብ ባለሟሎች ያሞካሿታል።

ድምፃዊት ሚካያ በሀይሉ፣በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማታው የትምህርት ክፍልበኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ጽሑፍ ተምራ በ1996 ዓ.ም.የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀብላለች።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታዋየሰራችው የመመረቂያ ጽሑፍ በዩኒቨርስቲው ቤተመጻሕፍት የሚቀመጥ ድንቅ ሥራ ሆኗል። ሚካያ በወቅቱ የሰራችው ጥናት‹‹አስቴር ዐወቀ የተጫወተቻቸው የሶስና ታደሰ የዘፈን ግጥሞች›› (Lyrics) ላይ ሲሆን ያቀረበችው በሳል ትንተና የጥበብን ባህላዊና ማህበራዊ ፋይዳ ያመላከተችበት ነው።

ሚካያ በሀይሉ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ካገኘች በኋላ ለሁለት ዓመታት ያህል በ‹‹ስኩል ኦፍ ቱሞሮው›› እና ‹‹አዲስ ኢንተርናሽናል›› ትምህርት ቤቶች በመምህርfትነት አገልግላለች።

በ1999 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የመጀመሪያ አልበሟን ‹‹ሸማመተው›› ለማውጣት ችላለች። ከዚህ በኋላ ህይወቷ እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በሀገር ውስጥና በውጪ አገራት መድረኮች የመጫወት እድሎችን አግኝታለች። በ2001 ዓ.ም. የሴት ልጅ እናት ለመሆን የበቃች ሲሆን፣ ደስታዋን በጥበብ ሥራዋ ላይ በማንጸባረቅ በበሳል የዘፈን ግጥምና ዜማ አድርጋ “እሹሩሩ እናቴ” በሚለው ዜማ እናቷ ለእርሷ ያላቸውን ፍቅር፣ ልጇን ከወለደች በኋላ በቅጡ መረዳቷን ገልፃ የእናት ፍቅር እንደ ጅረት ውኃ ከላይ ወደታች የሚከፈል (የሚፈስ) መሆኑን በዜማ ነግራናለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የድምፃዊ ጌዲዮን ዳንኤል አልበም ‹‹ጌዲን እንደዋዛ›› በገበያ ላይ ውሏል። ድምፃዊው በጤንነት መጓደል ሳቢያ ለዓመታት የሙዚቃ ሥራውን አቋርጦ እንደነበር ይታወቃል።

ድምፃዊ ጌዲዮን፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ጤናው በመስተካከሉ ወደ ሙዚቃው ዓለም ዳግም ተመልሶ በሳል ሥራዎችን ይዞ ለመቅረብ ሲተጋ መቆየቱን የሙያ አጋሮቹ ገልጸው፣ አልበሙ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎችን በልዩ አቀራረብ ማምጣቱን ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ዜና፣ ‹‹ዜማ አማን›› ቁጥር ሁለት የተሰኘ የአምስት ድምፃውያን ሥራዎች ስብስብ (ኮሌክሽን) በገበያ ላይ ዋለ።

ታዋቂው ድምፃዊ ሀይለየሱስ ግርማ፣ ሳሚ በየነ፣ አንተነህ ወራሽ፣ ፅላት ገዝሙ እና ያሬድ በላይ ናቸው አንድ የጋራ አልበም ለጆሮ ገበያው ያበረከቱት። አልበሙን ዝግጁ አድርጎ ያቀረበው ደግሞ አማኑኤል ይልማ ነው።

‹‹ዜማ አማን›› ቁጥር አንድ የጋራ አልበም ከዓመት በፊት ለገበያ እንደቀረበ ይታወሳል።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top