ማዕደ ስንኝ

ፍለጋ

ፍለጋ

በሁኔታ
በጊዜ
በቦታ
ያልተፈታ፤
በደመ ነፍስ ያልተመራ።
በምናልባት (?)
በይሆናል (!)
ያልተሽሞነሞነ።
ፊደል ከቃላት
ያልዘባረቁበት።
ከመሄድ
ከመምጣት፣
ከትናንት
ከነገ፣
ያልተገመደ።
በነገሮች ፈትል
በቅጥነት በውፍረት
ያልተሸመነ።
እንዲሁ …
ከፍጥረቱ
ከፈጣሪው፣
ለይስሙላ
በልማድ፣
ሳይጣበቅ፤
ሳይጠብቅ
ሳይላላ፤
መወላወል
መሄድ መምጣት፣
ያልሰለጠነበት።
በተቃራኒ ቃላት
በዝብርቅርቅ ማንነት
ልቡ ያልተፈታው።
ወደድኩሽ
ወደድኩህ
ስሜቱን ያልከዳው።
በውሰት ማንነት
በዝብርቅርቅ ቃላት፣
ግራ በሚያጋባ
ጉራማይሌ አንደበት፤
በአንድ አፍ ሁለት ምላስ
ያልሆነ።
ለእውነት፣
ስለ እውነት
በውበት የኖረ፤
እሱ ነው፣ የኔ!
መሄጃ ትልሜ
መድረሻ ግቤ።

ፍለጋ

አንድ
ሁለት
ሦስት
አራት
አምስት
አሥር ሰው፤
ቁልቁል የሚደመር፣
ሽቅብ የሚካፈል
የበዛበት ምድር፤
ፍቅር
በጥላቻ፤
ሠላም
በሁከት፤
እርጋታ
በወከባ፤
የተጣፋ የተጥፋፋ
ህይወት።
ሰምቶ ማዳመጥ
አይቶ መመልከት
ተነጋግሮ መግባባት
የጠፋበት ዘመን።
ጭንቀት
ከእረፍት፣
ጉራማይሌ
የሆኑበት
ህይወት፤
መታተር መሰልቸት
መልፈስፈስ መጠንከር
የተምታቱበት፣ የተማቱበት፤
ዝርክርክ
ህይወት፤
ውጥንቅጥ
ህይወት፤
ከንቱ ድካም የበዛበት፤
እርጋታ ወእርካታ የጠፋበት
የኛ ዘመን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top