በላ ልበልሃ

መገዳደል የፖለቲካ ባህላችን አካል

ሰሞኑን ከአንድ ወዳጄ ጋር ስለ ፖለቲካዊ ባህል ስንጨዋወት አባባሉ አስደነገጠኝ። እንዲህ አለ፡- “ኢትዮጵያ ምን የፖለቲካ ባህል አላትና ነው ስለ ፖለቲካ ባህላችን የምታወራው?” አለኝ። ሁኔታው ባያስከፋኝም አስደመመኝ። ጉዳዩን እንዳሰላስለውም ገፋፋኝ። የፖለቲካ ባህል ባላደገባት ሃገራችን ይህ ጉዳይ መነሳቱ አላስከፋኝም። ለአንድ ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚኖር ሰው “የፖለቲካ ባህል” የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ በጥሬው መረዳት ያስቸግረዋል። ብርቅርቅነት ያለው ቃል በመሆኑ ነው በቀጥታ የማይጨበጠው። የፖለቲካ ባህል ከፖለቲካ ድርጊቶች (manners) የሠፋ ነው። ኢትዮጵያ በረዥም ዕድሜዋ ባህር የሆነ አዝጋሚ ለውጥ ተመልክታለች። ዳሩ ግን ከንጉሣውያኑ ልማዳዊ የፖለቲካ ባህል ገና አልተላቀቀችም። ከኢትዮጵያ አብዮት ጋር አዲስ ፖለቲካዊ ባህል ብልጭ ያለ ቢሆንም በሚገባ አልፈረጠመም። አሳታፊ ፖለቲካዊ ባህል (participatory political culture) ሆኖም አልዘለቀም።

ከኢትዮጵያ አብዮት ጋር ድንገት ደራሽ የሆነው ደርግ መሠረታዊ የመሬት ስሪት ለውጥ አድርጓል። አንዳንድ አብዮታውያንም ብዙዎች ለዘመናት የታገሉለትን መሬት “የህዝብ” ሃብት አድርጓል ብለው አምነዋል። በትክክለኛ ትርጉሙ ከተመለከትነው ግን አዋጁ መሬትን የህዝብ ሳይሆን የመንግሥት ነበር ያደረገው። ሕዝብም አልን መንግሥት ርምጃው ግን ሥር-ነቀል ነበር። በዚሁ ርምጃም አያሌ ተራማጅ ወገኖች የታገሉለት የዘመናት ጥያቄ መልስ በማግኘቱ በጥቂቱም ቢሆን የሃገሪቱ ፖለቲካ ነጽሮታዊ አቅጣጫን (paradigm shift) ይዟል። በወቅቱም እንደ ኢሕአፓ ያሉ ድርጅቶች ዋነኛ የመታገያ አጀንዳቸውን እንዲያጡ አድርጓል ተብሏል። ክፍሉ ታደሰ እንደከተበው የዚህ አዋጅ መውጣት በግራ ዘመሙ የፖለቲካ ጎራ ላይ ፈተናዎችን ደቅኗል። በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የመደብ ቅራኔውንና የትግሉን ግለት አብርዶ እንዲደበዝዝ ወይም እንዲድበሰበስ አድርጓል።

በ1957 ዓ.ም. ፊት ለፊት የቀረበው የተማሪዎች ጥያቄና ዋነኛ አጀንዳ “መሬት ላራሹ” ነበር። ከ10 ዓመታት የትግል ውጣ ውረድ በኋላ ግን በዘመነ ደርግ ተግባራዊ ሆነ። የካቲት 25 ቀን፣ 1967 ዓ.ም. የመሬት አዋጅ ሲታወጅና በዚያ አስገምጋሚ ድምጹ አሰፋ ይርጉ በሬድዮ ሲያውጀው ገበሬውም፣ ባለመሬቱም ደንግጠው ነበር። እኔ እንኳ እንደማስታውሰው በወቅቱ በጅማ ዞን ሰፊ የቡና መሬት የነበራቸው ዳምጠው አዱኛ የተባሉ ከበርቴ በድንጋጤ ልባቸው ቆሞ ቤተሰባቸው በሃዘን ሲዋጥ፤ ገበሬዎች ግን ጮቤ ይረግጡ እንደነበር እስካሁን እንደ መድረክ ቴያትር ሆኖ ይታየኛል። ከዚሁ አዋጅ ጋር የንጉሡ ዋነኛ የፖለቲካ ሥርዓት አልጋና-ሸንኮር የሆነው መሬት ሲወረስ ሥርዓቱ አከተመ። አፈር ገፊውን እንደ መዥገር ተጣብቆ ደሙን ይመጠው የነበረው የመሬት ሥሪትና ሙግት እስከ ወዲያኛው ፋይሉ ተዘጋ።

አሸናፊው ኃይል ግን ዘገሩን እንደነቀነቀ ቀጠለ። “አሸናፊ ኃይል ሁሉንም ይወስዳል” (winner takes it all) የሚለው የፖለቲካ ብሂል ሀገሪቱን ሲዘፍቅ ኖሯል። ከአብዮቱ ግፊት ጋር የወታደሩ ክፍል (ደርጉ) ወደ ካምፓችን እንመለሳለን እያለ ሲያስመስል ቢቆይም ሥልጣን ጣመችው። የአገዛዙን ልጓም ህዝቡ ላይ አጠበቀ። ዕመቃውን አጠናከረ።

በአፍሪካ እንደ ሊዮፖርድ ሴዳር ሴንጎር፣ አህማዱ አሂጆ፣ ጁሊዬስ ኔሬሬና ስዌር አልዳሃብን የመሳሰሉ ቅን የአፍሪካ ልጆች “ሥልጣን ምን ተዳዬ” በማለት ዙፋን ጠል ሆነው ሥልጣንን ወደ ህዝብ መልሰዋል። ዳሩ ግን ለሥልጣን አይደለም ከካምፔ የወጣሁት ሲል የነበረው ደርግ፣ አዲስ ግን ደግሞ ኋላቀር ፖለቲካዊ ባህል (neo-parochial political culture) አንግቦ ተገኘ። ሰኔ 21 ቀን፣1966 ዓ.ም. ራሱን “ደርግ” በማለት ህዝባዊ አብዮቱን አጨናገፈ። ሆኖም ግን ጉዞው አልጋ በአልጋ አልሆነለትም። በጉልበት ራሱን “አንቱ” ያለው የደርግ ቡድን ከራሱ የጦር አባላት ሳይቀር ተቃውሞዎች እየተነሱ ይለበልቡት ጀመር። በተለይ በንዑስ የደርግ አባላትና በዋናው የደርግ አባላት መካከል መከፋፈልና ንትርክ ነገሠ። በሰለጠነ መንገድ መወያየት አክትሞለት በ1967 ዓ.ም. “ሚናህን ለይ” የሚል አዲስ ፈሊጥ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ምህዳር ላይ ብቅ አለ። ከሁሉም በላይ ጠንካራ ተቃውሞ የገጠመው ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበር ሲሆን ከ“ጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት ይቋቋም!” ጥያቄ ጋር አፋጠጡት። ደርግ ይህን ጥያቄ ለመፍታት አቅሙም፣ ችሎታውም አልነበረውም። በተለይ በደርጉ ላይ የፊውዳሉ ሥርዓት ጋሻ ጃግሬዎች የሚያደርሱበት ተቃውሞ እንዳለ ሆኖ ተራማጅ ከተባሉት ኃይሎችም ተቃውሞና ውግዘቶች ሳያባሩ ይዘንቡበት ነበር። እነዚህም ኃይሎች ቢሆኑ ከደርግ የተሻሉ ነበሩ ማለት አይቻልም። ተቃዋሚነታቸው ደርግ ላይ ብቻ ያነጣጠረ ሳይሆን እርስ በርስ መነጫጨታቸውን ቀጠሉ። “ሪቮና ሳቦተር” እየተባባሉ ሲካሰሱና ሲነካከሱ ቆዩ። የፖለቲካውን አየርም በከሉት።

ዲሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ባህልን ሊላበስ የማይችለው ደርግ አማቂና ጨፍላቂ የመንግሥት ሥልጣኑን ለማጠናከር ሲል “ይህ አዋጅ እስኪነሳ ድረስ ኢትዮጵያ ትቅደም የሚለውን ዓላማ የመቃወም፣ አድማ የማድረግ፣ ሥራ ማቆም፣ ያለፍቃድ ሠላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማድረግ፣ በጠቅላላ የህዝቡን ፀጥታና ሰላም የሚነሳ ተግባር መፈፀም ክልክል ነው” እያለ፣ የፍየል ወጠጤን እያዘፈነና የሞት ደወል እየደወለ አማቂነቱን ህጋዊ አደረገ።

እስረኞቹን አስሮ በመጠባበቅ ላይ ያለው ጦርም የዶሮ ወጥና ፍትፍት ማሽተትና
መፈተሸ ሰለቸኝ እያለ ስሞታውን እያቀረበ ነው በሚል ሰበብ የንጉሡ ባለ ሥልጣናት ተረሽነው በአንድ ጉድጓድ ውስጥ
እንዲከተቱ አደረገ

የመጀመሪያው አሸማቃቂ ርምጃ የተወሰደው ደርግ ራሱ መርጦ ባስቀመጣቸው በጀኔራል አማን ሚካኤል ዓንዶም ላይ ሆነ። አልፎ ተርፎም ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ እንደሚነግረን ሻለቃ መንግሥቱ “ጦሩ እንዴት አስራችሁ ትቀልባላችሁ በማለት ወቀሳ እየሰነዘረብን ነው። እስረኞቹን አስሮ በመጠባበቅ ላይ ያለው ጦርም የዶሮ ወጥና ፍትፍት ማሽተትና መፈተሸ ሰለቸኝ እያለ ስሞታውን እያቀረበ ነው” በሚል ሰበብ የንጉሡ ባለ ሥልጣናት ተረሽነው በአንድ ጉድጓድ ውስጥ እንዲከተቱ አደረገ። በዕለተ እሁድ ኅዳር 15 ቀን፣ 1967 ዓ.ም. ጠዋት የኢትዮጵያ ህዝብ ከእንቅልፉ ሲነሳ በገዛ ሬዲዮው መርዶውን ሰማ። ድንጋጤ ኢትዮጵያን የጨው አምድ አድርጎ አስቀራት።

ከዚያ በፊት ኅዳር 13 ቀን፣ 1967 ዓ.ም. የወጣውና ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማሪያም በፊርማው ትእዛዝ የሰጠበት ደብዳቤ “በዋናው ከርቸሌ ለ54 ሰው በዶዘር ጉድጓድ እንዲቆፈር ሆኖ ከተራ ቁጥር አንድ እስከ 54 ያሉት ከፍተኛ የሲቪልና የጦር ባለ ሥልጣናት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ከእስረኞች ተለይተው ለብቻ እንዲቆዩ፤ ከለሊቱ 8፡00 (0200) ሰዓት በወታደራዊ መኪናዎች ወደ ዋናው ከርቸሌ ተወስደው በአንድ ላይ በጥይት ተደብድ[በው] እንዲገደሉ እናስታውቃለን” ይላል። ይህም ሻለቃው ደርጉ ኅዳር 14 ቀን ከመሰብሰቡ አንድ ቀን በፊት እርምጃው እንዲወሰድ በፊርማው ትዕዛዝ ማስተላለፉን ያሳያል።

“የፍየል ወጠጤ፣ ትከሻው ያበጠ፣ ልቡ ያበጠበት እንዋጋ ብሎ፣ ለነብር ላከበት፣ የማትረባ ፍየል፣ ዘጠኝ ትወልዳለች ልጆቿም ያልቃሉ፣ እሷም ትሞታለች” የሚለው የይርጋ ዱባለ ዘፈን የኢትዮጵያን የአየር ሞገድ በሰቆቃና በሽብር ናኘው። ከዚህ በኋላ የፖለቲካ መድረኩ ሁሉ የፉክክር፣ እኔ እበልጥ የማለት፣ የመነጋገር ሳይሆን የመገዳደል ፖለቲካ ሆነና የኢትዮጵያን  አድባር ቆሌ አሳጣው። ሀብታሙ አለባቸው እንደፃፈው ደርግ በሃገራዊ አንድነት ፕሮጀክት “አጥንትና ጉልጥምት” ኢትዮጵያን ለመፍጠር አልታገዘም ሲል የደርግ የፖለቲካ ህይወት ፍሬ አልባ መሆኑን ያሰምርበታል።

 የመጠፋፋት ፖለቲካ (ኢሕአፓ፣ መኢሶንና ደርግ)

ሳይንቲስት አንድሬ ሳክሮቭ “በኬጂቪ ፋይል” መጽሐፉ ያወሳውን ጉዳይ እዚህ ላይ መጥቀስ ያስፈልጋል። ሰውዬው ብሩህና ስሑል መስተሃልይ (የለማ አእምሮ) አለውና አንድ ጠቃሚ አስተምህሮ አስተላልፎልናል። እንዲህ ይላል፡- “አምባገነናዊ የፖሊስ ስርዓት ሲፈጠር ለሀገር አደገኛ ይሆናል። የስታሊን፣ የሂትለር፣ የማኦ ዜዱንግ አምባገነናዊ የፖሊስ ስርዓት ከተፈጠረ ለአንድ ሀገር እጅግ አደገኛ ነው። በጀርመን ናዚዝም ለአሥራ ሁለት ዓመታት ዘልቋል፣ ስታሊኒዝም በሶቪዬት ሕብረት በዚህ ጊዜ በእጥፍ ተንሰራፍቷል። ሁለቱም ሥርዓቶች የጋራ የሚያደርጓቸው ብዙ ነገሮች አሏቸው። በእርግጥ አንዳንድ ልዩነቶች ታይተውባቸዋል። ስታሊኒዝም ግን የተደራጀ ግብዝነትና (ሂፓክራሲ) ዴማጎጂያዊ መልኩን አሳይቷል። ያራመደው ፕሮግራም እንደ ሂትለር ሰው በላ ሳይሆን ተራማጅ፣ ሳይንሳዊና ህዝባዊ የሆነውን የሶሻሊስት ርዕዮት ሲሆን፣ በህብረተ-ሰቡ ውስጥ ተቀባይነት ያገኘውን ግን ደግሞ፤ ለሰራተኛው መደብ የማታለያ ጭንብል እያሳየ የምሁሩን ፈርጣማነት ለማዳከምና በሥልጣን ትግል የሚፎካከሩትን ለመድፈቅ ተጠቅሞበታል ሲል ያስነብባል።” በኢትዮጵያ የሆነው ደግሞ ሳካሮቭ ከሚለው የባሰ ነው። ስታሊኒዝምንና ማኦይዝምን ምሁሩ ወገን በካባነት በመደረብና ደርግ ጭምር ይህንኑ በቀጥታ እንዲደርብ በማድረግ ፖሊሳዊ መንግሥትነቱን አጠናከረው። ከጠመንጃ በስተቀር ሌላ መሣሪያ መጠቀም የማያውቀው ደርግ፣ የስታሊንና የማኦን በትር ተጠቅሞ በፈርጣማ ክንዱ ደቆሳቸው።

በዚህ የመገዳደል ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚወስዱት ኢሕአፓና መኢሶን ናቸው። በእርግጥ ኢሕአፓና መኢሶን የኢትዮጵያ ልማዳዊ ፖለቲካዊ ባህል እንዲለወጥ ጥረት ያደረጉ፤ የዚያ ትውልድ ምርጥ ፍሬዎች ቢሆኑም የሚወቀሱበት ብዙ ጉዳዮች አሏቸው። ከሁሉ በፊት በሰለጠነ መንገድ ለሃሳብ መለያየት ቦታ አለመስጠታቸው ተጠቃሽ ይሆናል። ሙት ወቃሽ ለመሆን አልፈልግም። ሆኖም ግን የታዩባቸውን ፖለቲካዊ ችግሮች መመልከት አስፈላጊ ይመስለኛል።

ደርግ ከምሁራኑ የስታሊንና የማኦን በትር ከተቀበለ በኋላ የህዝብ ድርጅት ጽ/ቤትን አቋቁሞ ለሁሉም ተራማጆች ጥሪ አድርጎ ነበር። አንዳርጋቸው አሰግድ እንደፃፈው መኢሶን ሂሳዊ ድጋፍ በሚል ከሚያዚያ 1968 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ደርግ ተለጠፈ። ኢሕአፓ ግን ጥሪውን አንቀበልም በማለት አፈነገጠ። እነዚህ ሁለት ቡድኖች በአብዮተኝነት የሚታወቁ ናቸው። ሽመልስ ተክለፃድቅ በአንድ ወቅት ሲጽፍ እነዚህ ቡድኖች “ማንኛቸውም የኅብረተ- ሰብ ጉዳዮችን የሚገነዘቡት ከመደብ አንፃር ነው። ቆምንለት ከሚሉት መደብ/ ክፍል (ብዙ ጊዜ ገበሬውና ሰፊው ህዝብ) የማይስማማ የመሰላቸው ሃሳብም ሆነ ሌላ ወገን ካለ በጠላትነት ይፈርጃሉ” ሲል ገልጿል። በዚህ ጽሑፍም ከመደብ አንፃር ሲፋለሙ የቆዩትን የፖለቲካ ቡድኖችን (ኢሕአፓንና መኢሶንን) ብቻ እንመለከታለን። በሚቀጥለው ዕትም ዘውጌ ፖለቲካና መገንጠልን የሚያራምዱት ወገኖች የትኩረታችን አቅጣጫ ይሆናሉ።

ከሁሉም በላይ ኢሕአፓ ያበላሸው ነገር ድርጅታዊ ነፃነቱን አስጠብቆ እንደ መኢሶን ሁሉ የህዝብ ድርጅትን አለመቀላቀሉ ፖለቲካዊ ስህተት ነበር ሲሉ ብዙ ፖለቲከኞች ይተቻሉ። መኢሶንና ኢሕአፓን ዓይንና ናጫ ያደረጋቸው መኢሶን ህዝቡን ማንቃትና ማደራጀት ይቀድማል ሲል፤ ኢሕአፓ ግን በመጀመሪያ ስልጣን፣ ከዚያም አብዮት ማካሄድ የሚለውን መስመር መከተሉ እንደነበር ተሂሷል። እንደ ባህሩ ዘውዴ እምነት መኢሶኖች ኢሕአፓን በክፉ ዓይን እንዲመለከቱት ካደረጋቸው ምክንያቶች አንዱ ተሸቀዳድሞ ራሱን “የላብ አደሩ ፓርቲ ነኝ” ብሎ ማወጁ ነው። የኢሕአፓን ያህል ሰርገው ለመግባት ያልቀናቸው እነዚህ ቡድኖች ኢሕአፓን “የጅብ ችኩል ቀንድ ይነክሳል” ብለው አጣጣሉት። እንደ አጣጣሉትም አልቀረ በገቢርም ዕውን ሆነ።

መኢሶንና ኢሕአፓ የሚተዋወቁ ምሁራንን ሰብስበው የያዙ ሆነው ልዩነቶቻቸውን ግን በሰለጠነ ፖለቲካዊ ዘዴ (ባህል) ለመፍታት አለመሞከራቸው እስከ ዛሬም ድረስ አስገራሚ ድርጊት ሆኖ ዘልቋል። ልክ ከዚህ ቀደም ያነሳናቸውን አይነት ንጉሣዊና መኳንንታዊ አስተሳሰብ በመያዝ አንዱ በአንዱ ላይ የበላይነትን ለመቀዳጀትና የሥልጣን ባለቤት ሆነው ለመውጣት ተፋለሙ። ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብርን የፖለቲካ መፍቻ መሣሪያቸው አደረጉት።

የቀይ ባንዴራ (በኋላ የኢትዮጵያ የኮሚኒስት ፓርቲ) መሥራች የሆነው አሰፋ እንደሻው ስለ ኢሕአፓ ፖለቲካዊ ስህተት ሲያወሳ “ኢሕአፓ በጀብደኞች አመራር ሥር ወድቆ ከከተማ ሳይወጡ ከጀብሃ በተመፀወቱት ሽጉጥ የቀበሌ መሪዎችንና ካድሬዎችን ጭንቅል፣ ጭንቅል እያሉ ከደርግ ላይ ሥልጣን ለመቀማት ሲራወጡ ትጥቃቸው ተፈትቶ ድርጅቱን የዶግ አመድ ማድረጋቸው ሁላችንን የደርግ ተቃዋሚዎች ጎዳን” ሲል የኢሕአፓን ጥፋት ዘርዝሯል።

የኢሕአፓ አመራር የኢትዮጵያ ጠላት ከሆነው ጀብሃ ጋር ወግኖ የትግል ስልት መቀየሱ፣ የኢኮኖሚ አሻጥር መፈፀሙ፣ ባንዳ ምሁራን ብሎ የዩኒቨርሲቲ የቅርብ ጓዶቹን በመምታት ከውይይትና ፉክክር ይልቅ በአቋራጭ ሥልጣን ለመንጠቅ መቋመጡ በአሁኑ ወቅት ወደ ኋላ መለስ ብለው ሲመለከቱት የሚቆጭ ነው። በተማረ ኃይል የሚመራ ቢሆንም፣ ይህ የተማረ ኃይል አዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ ማምጣትና ከቀድሞዎቹ ንጉሣዊና መሣፍንታዊ ኃይሎች የፖለቲካ ባህል በተለየ ሁኔታ ማሰብ ሲገባው ያንኑ መንገድ መድገሙ የሚገርም ሆኗል። “እናሸንፋለን” እና “እናቸንፋለን” በሚሉ ተራ ቃላት ሳይቀር ጎራ ለይቶ መቆራቆሱን ዛሬ ላይ ሆነን ስንመለከት ምን ነክቶን ነበር? ያሰኛል። ብርሃነ መስቀል ረዳ “ሽብርን እንደ መሠረታዊ የትግል ዘዴ በቲዎሪና በተግባር የወሰደው ራሱ ክሊኩ ስለሆነ በሽብር ምክንያት ላለቁት በመጀመሪያ ደረጃ ተጠያቂው የኢሕአፓ ክሊክ ነው” ሲል ራሱ አምጦ በወለደው ድርጅት ላይ ፍርዱን ሰጥቷል።

በቀልን በበቀል ለመለወጥና ደምን በደም ለማጠብ የኢሕአፓው ነጭ ሽብር በቀይ ሽብር ተለውጦ በመኢሶንና በደርግ ከፍተኛ አመራሮች ቅንብር ተካሄደ። የፖለቲካ ባህላችን በቀለኛ ነውና የግፍ ፅዋውን ማንሳት ቀጠለ። ብዙዎች እንደሚሉት ከዶክተር ፍቅሬ መርዕድ ግድያ በኋላ እነ ኃይሌ ፊዳ፣ ነገደ ጎበዜ፣ ሠናይ ልኬ (መኢሶኖች)፣ ኮሎኔል ተካ ቱሉ፣ ኮሎኔል ተስፋዬ ወ/ ስላሴ፣ ኮሎኔል ስዩም መኮንን (ደርጎች) ስብሰባ አድርገው ለቀይ ሽብር በሩን ከፈቱ። ከመነጋገር ይልቅ መተላለቅን ተከተሉ። ሽብር አገሪቱን አፍኖ አናወጣት። ወንድም ከወንድሙ፣ አባት ከልጁ ጋር ተገዳደሉ። በሃገሪቱ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የሃዘን መርግ በእያንዳንዱ ቤት ላይ ወደቀ። እናቶች የሀዘን ማቅ ተከናነቡ። መተማመን ጠፋ፣ በ“ዲሞን በዲሞትፈር!” ፉከራ፣ በመንጥር ዘመቻ ጉልበት ምንጠራና ነፃ እርምጃ እየተወሰደ የሰው ነፍስ ከውሻ ነፍስ ያነሰ ሆነ።

ከመጋቢት 30 ቀን፣ 1970 ዓ.ም. በኋላ ቀይ ሽብርም ሆነ ነፃ እርምጃ በአራማጆቹ ቀጭን ውሳኔ እንዲቆም ተደረገ። ከዚህ በኋላ ሃገሪቱ በስታሊናዊ ፈርጣማ ክንድ ሥር ስትደቆስ ቆየች። ሊዮ ቶልስቶይ “እያንዳንዱ ሰው ዓለምን ስለመለወጥ ያስባል፤ ራሱን ግን ለመለወጥ አያስብም” (Everyone thinks of changing the world, but no one thinks of changing himself) ያለው እዚህ ላይ ይጠቀሳል። የኢትዮጵያ መሪዎች እንዲህ ዓይነት ተመሳሳይ አስተሳሰብ ነበራቸው። ኢትዮጵያን ለወጥን ብለው ያስባሉ፤ እነሱ ግን አልተለወጡም። ለኢትዮጵያ ቆምን ይላሉ፤ ኢትዮጵያን ግን በግንባሯ እየደፉ ዳዴ ያስኬዷታል። ራሳቸውን መልሰው ማየት በጀመሩ ጊዜ ከእግራቸው ሥር የቤተመንግስታቸው ወላንሳ ተጎትቶ ይነሳል። እነሱም ይወድቃሉ።

በኢትዮጵያ የሶሻሊስትና ብሔርተኛ- ነጽሮት (ፓራዳይም) ከ1966 ዓ.ም. ወዲህ ዋነኛው የፖለቲካ አንቀሳቀሽ ኃይል ሆኖ ቆይቷል። እንደ ዐረቡ የሶሻሊስት ብሔርተኛ ነጽሮት ግን ጉልበት አልነበረውም። ከ1950- 1970ዎቹ የቆየው የዐረቡ ዓለም ነጽሮት በግብፅ፣ በሶሪያና በኢራቅ በባህላዊ ተቋማቱ ውስጥ ዋነኛ አንቀሳቃሽ ሞተር ነበር። በተለይም በምሁራን ማለትም በጋዜጠኞች፣ በደራሲያን፣ በዩኒቨርሲቲ መምህራን ዘንድ ሥሩን ሰድዶ ቆይቷል። ተቀባይነትም አግኝቷል። እንደነ አብደል ናስር ባሉ ተሰሚ ሰዎች ብሔራዊ ማንነትን አጠንክሮ ወጥቷል። የኢትዮጵያው ሁኔታ ግን የተገላቢጦሽ ነበር። ደርግ እንኳን ብሔራዊ ማንነትን ለማጠናከር ቀርቶ የራሱን መንግሥታዊ ህልውና ሳያስጠብቅ እስከ ወዲያኛው አሸልቧል።

እነ ኮሎኔል መንግሥቱና ቡድናቸው ስለ ተማከለ አመራርና አገራዊ አንድነት በመስበካቸው ብሔረ- ኢትዮጵያን የመገንባት ተልዕኮን ለመፈፀም አልቻሉም። እንደ ሀብታሙ አመለካከት “የተሳካ የብሔረ- ኢትዮጵያ ግንባታ ተልዕኮ በቀጥታ የጄኔራሎች ተግባር አይደለም። በተቃራኒው ከፍ ያለ የመሪዎች ብቃትና ችሎታ፣ አርአያነትና ታጋሽነት፣ የፖለቲካ ፈቃደኝነትና ብልህነት … በእጅጉ የሚጠይቃቸው ግብአቶች ናቸው” ሲል ያስቀምጣል። ታዲያ ደርግ እንኳን እጅግ አስቸጋሪውን የብሔረ – ኢትዮጵያን ተልዕኮ ሊፈፅም ቀርቶ ተለምዷዊው የፖለቲካ ባህላችን ዋጋ ቢስ ሆኖ እንዲጨረማመት አድርጎ አልፏል። አዎ አልፏል። ግን አልፏል እያልን በ”ዝም አይነቅዝም” ብሂል አናዘግምም። “ያሳዝናል” እያልን ያለፈ አዳፋ ታሪካችንን አናዳፍነውም፤ ልንመክርበትና ልንከራከርበት ይገባልና።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top