ታዛ ስፖርት

‹‹ፌር ፕሌይ›› (ስፖርታዊ ጨዋነት) የሚባል መርህ በሁሉም አካላት ተጥሷል፡፡››

ታዛ፡- በሀገራችን የእግር ኳስ ጨዋታና የድጋፍ አሰጣጥ ዘዬው ከየት ተነስቶ የት ላይ ደርሷል?

ኢብራሂም ሃጂ፡- አጀማመሩ ጥሩ ነበር። የአፍሪካ ዋንጫ ሲቋቋም፣ ኢትዮጵያ ከመስራቾቹ አንዷ ነበረች። የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ዋንጫም ሲመሰረት እንደዚሁ። ስለዚህ ኢትዮጵያ ከቀዳሚዎቹ አንዷ ነበረች ማለት ነው። ምንም እንኳን የአንደኛውንና የሁለተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ባናገኝም፣ ሦስተኛውን የአፍሪካ ዋንጫ በ1954 ዓ.ም. ጥር ወር ላይ እዚሁ በሀገራችን አዘጋጅተን አስቀርተናል። በዛን ጊዜ እንዳውም ለአራተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ቡድናችን ወደ አዘጋጇ ጋና ከመሄዱ በፊት ወደ ሴኔጋል ጎራ ብሎ የወዳጅነት ግጥሚያ አድርጎ ይመለስ ነበር። ያኔ በአፍሪካ አገራት “የእግር ኳስ ጥበብን ማየት ከፈለጋችሁ የኢትዮጵያን ብሄራዊ ቡድን ጋብዙ” እስከመባል የተደረሰበት ጊዜ ነበር። አራተኛውም የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ጥሩ ነበርን። ስድስተኛውንም የአፍሪካ ዋንጫ ስናዘጋጅ የኳስ ደረጃችን እንዲሁ ጥሩ ነበረ።

ታዛ፡- ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫን ስንት ጊዜ አዘጋጅታለች?

ኢብራሂም ሃጂ፡- ሦስት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫን አዘጋጅታለች። በ1954 ዓ.ም. 3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅታ አስቀርታዋለች። በ1960 ዓ.ም. 6ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጅታ አራተኛ ወጣች። በ1968 ዓ.ም. 10ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ብታዘጋጅም በዛን ጊዜ ጥሩ ብቃት ላይ አልነበርንም። ከምድብ እንኳን ማለፍ አልቻልንም ነበር። በዚህ ወቅት ጨዋታው በአዲስ አበባ እና በድሬዳዋ ነው የተደረገው። በሁለተኛው በአስመራና በአዲስ አበባ ነበረ።

ታዛ፡- ብሄራዊ ቡድኑ እየተዳከመ የመጣው ለምንድን ነው?

ኢብራሂም ሃጂ፡- በወቅቱ ብሄራዊ ቡድኑ ጥሩ ተዘጋጅቶ ነበር። ግን ምድብ ማጣሪያውን እንኳ ማለፍ አልቻለም። የሚገርምህ ነገር በሦስተኛው የአፍሪካ ዋንጫ እነ ሉቻኖ፣ እነ መንግስቱ ወርቁ እና ዘመነኞቻቸው ነበሩ። በአራተኛውም፣ በአምስተኛውም፣ በስድስተኛውም እነሱው ናቸው። በወጣቶች አልተተኩም። ሱዳን ባዘጋጀችው 7ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ አንድም ነጥብ ሳያገኙ ተመለሱ። ተዳክመዋል። ይህ ምን ያሳየናል? ተተኪ አለመኖሩን። በዚያ ላይ በሁሉም ስፖርቶች ደካሞች ነን ማለት ትችላለህ። ተተኪ ላይ ትኩረት የለም። ባለው ብቻ እስከመጨረሻ መሄድ ነው የተለመደው።

በዓለም ላይ ከአስራ ሰባት ዓመት በታች፣ ከሃያ ዓመት በታች ተብሎ የሚዘጋጅ ውድድር አለ። ዓላማውም ሀገሮች ተተኪ ስፖርተኞችን እንዲያገኙ ለመርዳት ተብሎ ነው። እኛ ጋ ግን ትኩረት ስላልተሰጠው በዚህ በኩል ምንም የለንም። አሁንም ይሄ ችግር እንደቀጠለ ነው። ጠንካራ ክለቦች በሌሉባት ሀገር፣ ጠንካራ ብሄራዊ ቡድን ልታገኝ አትችልም። በዚህ ላይ አሰልጣኞችና የክለቦች አመራሮች ትኩረታቸው አዲስ አበባ ላይ ብቻ መሆን የለበትም። የእግር ኳስ ፌዴሬሽንም በመላ ኢትዮጵያ ተተኪ ወጣቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት።

ሚዲያውም ለሀገር ውስጡ ስፖርት ትኩረት ሰጥቶ መስራት አለበት። አሁን እነ ፔሌ፣ እነማራዶና ሲናገሩ ሚድያ ባይኖር ኖሮ እኛ እዚህ ባልደረስን ነበር  ይላሉ። የኛ ሚድያ ለሀገር ውስጥ ጨዋታና ለሀገር ልጅ ትኩረት አይሰጥም። አንድ ሚሊዮን ብር ከምትሰጠኝ የኔን ፎቶ ጋዜጣ ላይ ባይ፣ የኔን ስም በሬድዮ ብሰማ፣ ራሴን በቴሌቪዥን ባይ፣ እርካታው ከፍተኛ ነው። ለበለጠ ውጤት ያነሳሳኛል። ግን እኛ ሀገር የዚህ ዓይነት ነገር የለም። በዚህ ምክንያት ጎበዝ የሆኑ ተተኪ ተጫዋቾችን ማግኘት አልቻልንም። በጥረቱ የወጣውን ብቻ ነው በክለብም፣ በብሄራዊ ቡድንም ተሻምተን ይዘን የምንጓዘው። ውጤት ግን የለውም። እግር ኳስ ተዳክሟል። ከስሟል። በአፍሪካ ዋንጫ ውጤታችንን ስትመለከተው ቁልቁል ነው የወረደው።

ከአስረኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ፣ ከኋላችን ተነስተው የቀደሙን አገሮች ብዙ ናቸው። ምክንያቱም እኛ ከሰባተኛው የአፍሪካ ዋንጫ በኋላ፣ በአስረኛው አዘጋጅ ሆነን፣ በአስራ ሶሥተኛው ጊኒን ከሜዳ ውጪ በነበረን የጎል ብልጫ (አድቫንቴጅ) አሸንፈን ሊቢያ ላይ ተካፍለን ነበር። ከዚያ ከ31 ዓመት በኋላ ነው በደቡብ አፍሪካ የተካፈልነው። ያውም ለዚህ የበቃነው ከቤኒን ጋር በሃገራቸው 1 ለ 1 እኩል ወጥተን፣ እዚህ ዜሮ ለዜሮ አቻ በመውጣታችን አሁንም ከሜዳ ውጪ ባገኘነው የጎል ብልጫ ነው። ከሱዳን ጋር በሃገራቸው አምስት ለሶስት ተሸንፈን፣ እዚህ ሁለት ለዜሮ በማሸነፋችን በድምር ውጤት አምስት ለአምስት ብንሆንም በሰው ሀገር ከፍ ያለ ቁጥር ያገባ የተሻለ ዕድል ስላለው ነው ያለፍነው። እንጂ ብቃት ያለው ቡድን ሰርተን አይደለም። ደግሞስ ቤኒን እና ሱዳን በአፍሪካ ዋንጫ ምን ቦታ አላቸው? ምንም የላቸውም።

ከ31 ዓመት በኋላ ሄደን ተካፍለን ከአስራ ስድስት አገሮች አስራ ስድስተኛ ነው የወጣነው። በደቡብ አፍሪካ የቻን ዋንጫ ላይም እንዲሁ ከአስራ ስድስት አገሮች አስራ ስድስተኛ ወጣን። አንድ ጎል እንኳ ሳናስቆጥር፣ አንድ ነጥብ ሳናገኝ መጣን። ውጤቱ ነው እንዲህ የሚናገረው። ይሄ የእግር ኳሳችን ውድቀት ነው። ታዛ፡- የኢትዮጵያውያን የእግር ኳስ ድጋፍ አሰጣጥ ባህልስ ምን ይመስላል? ኢብራሂም ሃጂ፡- እኔ ድሬዳዋ ነው ተወልጄ ያደግኩት። ትላልቅ ክለቦች ነበሩ (ጨርቃ ጨርቅና ኢትዮ- ሲሚንቶ)። ሁሉም የሚደግፈውን ቡድን ይደግፋል እንጂ የተጣላንበትን ጊዜ አላስታውስም። ስንሸነፍ እናለቅሳለን። ንዴታችንን በዚህ ነው የምንወጣው። በወንበር በመፋለጥ፣ በመስበር ንዴታችንን አንወጣም።

በኃይለሥላሴ ጊዜ ይኸውልህ ፖሊስ “ኦሜድላ”፣ አየር ሃይል “ንብ”፣ ክቡር ዘበኛ “መኩሪያ”፣ ምድር ጦር “መቻል” ይባሉ ነበር። ተመልከት ስምም፣ ወታደራዊ ልብስም ቀይረዋል። ለምንድን ነው? ወታደሩ በወታደርነቱ መጥቶ ከሲቪል ጋር እንዳይጋጭ። እንደዛም ሆኖ ግን ግጭቱ ስለነበረ፣ ለብቻው ተነጥሎ ወጥቶ ነበር። በደርግ ጊዜ ነው የተመለሱት።

ያኔ ኤርትራና ኢትዮጵያ አንድ በነበሩበት ጊዜ እነ ሀማሴንና አካለ ጉዛይ የሚባሉት ቡድኖች በጎሳ የተደራጁ ስለሆነና ይህም ለእግር ኳስ እድገት ጥሩ ስላልሆነ፣ ስማቸውን እንዲቀይሩ ተደረገ። ለምሳሌ ሀማሴን- በ”አስመራ” ተቀየረ። ብዙ በጎሳ የተደራጁ ቡድኖች ስማቸው ወደ “ቀይባህር”፣ “ኤሌክትሪክ” እና “ቴሌ”፣ መለወጡን አስታውሳለሁ።

አሁንም ድጋፍ አሰጣጡ ወደ ጎሳ እየሄደ ነውና ማህበራዊ እንዲሆን መሰራት አለበት። ሰው የፈለገውን ቡድን መደገፍ እንዲችል። ያ ደግሞ ጥሩ ነው። አንድነት ያመጣል፣ ያፋቅራል።

በውጪ አገሮችም ስናይ ክለቦች በጎሳ አይደራጁም። በከተማ ወይም በሌላ ማህበራዊ መሠረት ነው የሚደራጁት። በተፈጥሮ ስፖርት በተለይ ደግሞ እግር ኳስ ‹‹አክሽን›› አለው። ያ ‹‹አክሽን›› ደግሞ ‹‹ሪ-አክሽን›› አለው። ቲፎዞው ወዲያው ነው ‹‹ሪ-አክት›› የሚያደርገው።

ታዛ፡- ለምንድን ነው የደጋፊ ሁከትና ግጭት የተበራከተው?

ኢብራሂም ሃጂ፡- አሁን ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› አይነት ነገር ነው ያለው። ሁሉም በምንም መንገድ ዋንጫውን ብቻ ይፈልጋል። ጊዜያዊ እርካታ ብቻ። ጊዚያዊ ስም አግኝቶ ለእገሌ ቡድን ዋንጫ አስገኝቻለሁ ለማለት። ‹‹ፌር ፕሌይ›› (ስፖርታዊ ጨዋነት) የሚባል መርህ በሁሉም አካላት (ቡድኖች፣ አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ የቡድን አመራር አባላት) ተጥሷል። በምንም መንገድ ይሁን ጊዜያዊ ውጤት ብቻ ይፈለጋል። ይሄ ስሜት ደጋፊውም ላይ እንደ ወረርሽኝ ተጋብቶበታል። ስለዚህ በተራ ነገር ይጋጫል።

ታዛ፡- የስፖርት ጋዜጠኞች እንዴት መዘገብ አለባቸው?

ኢብራሂም ሃጂ፡- እኛ አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ወግኖ ከፃፈ በኤዲቶሪያል ስብሰባ ላይ እናጋልጠዋለን። ወግኖ ከፃፈ ቲፎዞ ነው ማለት ነው። ደጋፊ ነው ማለት ነው። ደጋፊ ከሆነ ደግሞ አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ከእውነት፣ ከትክክለኛነት ሊነጠል ይችላል። ዘገባ ደግሞ በእውነትና በመረጃ (ፋክት) ላይ መመስረት አለበት። ካልሆነ የግል አመለካከት (ኦፒኒየን) ነው የሚሆነው። እኔ ስለ ጋዜጠኝነት ስማር እድሜው ከሰላሳ ስድስት ዓመት እስካላለፈ ድረስ ለአንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ዋና አዘጋጅነት አይሰጥም ይላል። አሁን እንዴት ነው? ስንቱ ተምሮና አውቆ ይሰራል? ዘርፉን መመልከት ነው።

ታዛ፡- የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ምን መስራት አለበት?

ኢብራሂም ሃጂ፡- የፌዴሬሽን ህዝብ ግንኙነት ከሚሰራው ትልቅ ስራ አንዱ ምንድን ነው ደጋፊውን ማረጋጋት ነው። ተጫዋቾችንም ንቃትን በመፍጠርና በሕግና በደንብም ፈር ማስያዝ ነው። ግን በዚህ በኩል ሲሰራ አታይም። በሰባዎቹ መጨረሻ አካባቢ የ‹‹ፌር ፕሌይ ብሄራዊ ኮሚቴ›› ነበር። እኔም እዛ ውስጥ ተመርጬ እሰራ ነበር። ምንድን ነው የምናደርገው ማስተማር ላይ እንሰራ ነበር። ‹‹ፌር ፕሌይ›› ምንድን ነው? ድጋፍ እንዴት ይሰጣል? ውድድር እንዴት ይካሄዳል? ወዘተ. በሚል በጋዜጦች እንጽፋለን። በራዲዮና በቴሌቪዥንም እናቀርባለን። ደጋፊ ይማራል፣ መረጃ ያገኛል።

ታዛ፡- አመሠግናለሁ!

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top