ጥበብ በታሪክ ገፅ

ፊሊፕ ካፕላን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የባህል ማዕከል ግንባር ቀደም መስራች

1950ዎቹ መጀመሪያ አጋማሽ በአገራችን ሁለት መደበኛ ቤተ-ተውኔቶች 950ዎቹ መጀመሪያ ብቻ ነበሩ፡- የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ቴያትርና የሀገር ፍቅር ቴያትር። በነዚህ ዓመታት፣ እንደ ፍራንሲስ ዘልቬከርና አሌክሳንደር ሀገር ባሉ ድንቅ የቴያትር ጠቢባን የብቃት ደረጃቸው ከፍተኛ የሆኑ ተውኔቶች ተደርከዋል። ይሁንና ጥበቡ እጅግ ውስን ለሆነ የህብረተ-ሰብ ክፍል ብቻ ነበር ይቀርብ የነበረው የዚህ የውስንነት ግፊት በአንጻሩ የሌላ ስነ-ጥበብ ማዕከልን መፍጠር አስፈላጊነት በመጫሩ፤ ቀድሞ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ውስጥ በክበብ ደረጃ የተጀመረው የስነ- ጥበብ እንቅስቃሴ ከቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መቋቋም በኋላ ጎልብቶ ወደ ኪነ-ጥበባት ወቴያትርመመስረት ተሸጋገረ። ይህ ተቋም በአዲስ አበባ ውስጥ እንደ ሶስተኛ የስነ-ጥበብ ተቋም ተጨማሪ አማራጭ ሆኖ በቅርበት ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች፣ በርቀት ደግሞ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችና ምሁራን ስነ-ጥበባትን ያቋድስ ነበር። በዚህም ኪነ-ጥበባት ወቴያትር ለዛሬው የባህል ማዕከል መሰረት በመሆን የታሪክ አካል ሊሆን በቅቷል። ይህንን ማዕከል በመመስረትና በመምራት ሂደት የተለያዩ ጠቢባን የተሳተፉ ቢሆንም የጎላውን ሚና የተጫወተው አሜሪካዊው ዶ/ር ፊሊፕ ካፕላን ነበር። ታሪኩን በዝርዝር እንመልከት፡-

የዛሬው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ በአሁኑ የአራት ኪሎ ሳይንስ ፋኩልቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ተብሎ በ1942 ዓ.ም. እንደተመሰረተ፤ የኮሌጁ ተማሪዎች ማህበራቸውን ሲያደራጁ የአእምሮ ማስፋፊያና ማደራጃ ክበብን በሥሩ አቋቋሙ። ይህ ክበብ የኮሌጁንና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን እንዲሁም የውጭ እንግዶችን በማስተባበር ከቅጥር ግቢው ውጭ ያለው ሕብረተ-ሰብ ጭምር ስነ- ጥበብ ነክ ጉዳዮችን እንዲቋደስ ያደርግ ነበር። ዝግጅቶቹ የሚቀርቡትም ድሮ ሲኒማ ካምቦኒ በመባል ይታወቅ በነበረው አዳራሽ (አሁን የሳይንስ ፋኩልቲ አዲሱ የመማሪያ ሕንፃ በተሰራበት) ውስጥና በሜዳ ላይ ነበር።

ድራማዎች ከተፈሪ መኮንን፣ ከኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ ከምኒልክ፣ ከዊንጌት 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ይመጡ በነበሩ ተማሪዎች ጭምር ይሰሩ ነበር። እኚህ ክንዋኔዎች ባብዛኛው ይፈፀሙ የነበሩት በየዓመቱ በሚከበረው የኮሌጅ ቀን ነበር። ዩኒቨርሲቲ ኮሌጁ ዕድገት አግኝቶ፤ ታህሣሥ 9 ቀን 1954 ዓ.ም. ንጉሠነገሥቱ ባስረከቡት የ6ኪሎ ቤተ-መንግሥታቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተሰኝቶ ተመረቀ። ቀድሞ የልዑል ሳህለሥላሴ መኖሪያ የነበረውና ኋላ የህግ ፋኩልቲ ቤተ-መጻሕፍት የሆነው ሰፊ ክፍልም ለስነ-ጥበብ እንቅስቃሴ እንዲውል መደበ። አሜሪካዊው ሊንደን ሌቪት ተማሪዎችን በማስተባበር እንቅስቃሴ እንደጀመረ ብዙም ሳይቆይ በዚያው ዓመት ከአሜሪካን ከመጡት ሁለት የቴያትርና የሙዚቃ ሊቃውንት ጋር በመሆን በአገራችን የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ የሚኖረውን ተግባር ፈፀሙ። የቴያትሩ ሊቅ ዶ/ር ፊሊፕ ካፕላን ነበር።

ዶ/ር ፊሊፕ ካፕላን፣በአሜሪካን አገር በዌስት ቨርጂኒያ ውስጥ ቻርልስተን በምትባል ስፍራ በ1917 እ.አ.አ (በ1909/10 ዓ.ም.) ተወለደ። የዶክትሬት ዲግሪውን ከዴንቨር ዩኒቨርሲቲ ተቀበለ። በማናቲ መለስተኛ ኮሌጅ ንግግር እና ድራማን አስተምሯል።ለስምንት ዓመታት የማርሻል ኮሌጅ ቴያትር ዳይሬክተር ሆኖም ሰርቷል። ፈረንሳይ ውስጥ ምርምር ለማድረግ ለፉልብራይት ፌሎውሺፕ የገንዘብ ድጋፍ በጠየቀበት ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ሄዶ በቀ.ኃ.ሥ.ዩኒቨርሲቲ እንዲያስተምር አማራጭ ስለቀረበለት፣ ነፍሰ-ጡር ባለቤቱን ፍራንሲስንና ልጁን ጃንን አስከትሎ አዲስ አበባ በመምጣት በ1954 ዓ.ም. የዩኒቨርሲቲ ስራውን ጀመረ። ከማስተማሩ በተጨማሪ በቀ.ኃ.ሥ.ቴያትር ውስጥ አገልግሎት ለማበርከት ጥያቄ አቀረበ። ይሁንና በጥርጣሬ አይን ታይቶ አመኔታን ባለማትረፉ ለጥያቄው አዎንታዊ ምላሽ ሊያገኝ አልቻለም ነበር። ስለዚህም፣ ሊንደን ሌቪት በአሁኑ የህግ ፋኩልቲ ውስጥ ከጀመረው የጥበብ እንቅስቃሴ ጋር ራሱን በማዋሀድና ተማሪዎችን በመሰብሰብ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የድራማ ማህበረ-ሰብ የሚባል ክበብ መስርቶ የቴያትር ልምምድና አቅርቦት ጀመረ። በአንድ ዓመት ውስጥ ተደናቂ የሆኑትን ¾Plautus’ Comedy of Love – (The Braggart Soldier)፣ My Three Angeles፣ የቴነሲ ዊልያምን The Glass Menagerie፣ የፀጋዬ ገብረመድህን Theodrosን በላቀ የቴያትር ክሸና ደረከ። የግሪኩ ቧልታይ የፕላውተስ የእንግሊዝኛ ቅጂ ቢሆንም ከአማርኛ ጋር እያዳቀለ በማቀናበሩ፣ ቁጥሩ ያመዝን የነበረው የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የሆነው ተደራሲ በቀላሉ ገብቶት ይስቅና ያጨበጭብ ነበር

ካፕላን የደረካቸውን ድራማዎች ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ ልዑላን ቤተሰቦች፣ መሳፍንቱና መኳንንቱ በራስ መኮንን አዳራሽ ተገኝተው ያዩ ነበር ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈለትንና ከንጉሠ-ነገሥቱ ጋር እስከ መጨባበጥ ያደረሰው ግን በእንግሊዝኛ የቀረበው የፀጋዬ ገብረመድህን የቴዎድሮስ ተውኔት ነበር። ካፕላን ቀደም ሲል ቀ.ኃ.ሥ.ቴያትር ውስጥ በቀጥታ ለመሳተፍ የነበረውን ፍላጎት በእጅ አዙር በማርካት ሂደት ላይ ነበር የቴዎድሮስን ተውኔት አቅርቦት እጅግ ከላቀ ደረጃ ያደረሰው። በ1953 ዓ.ም.ከአሜሪካው የኖርዝ ዌስተርን ዩኒቨርሲቲ በቴያትር ጥበብ ኤም.ኤ.ዲግሪውን ይዞ የተመለሰው ተስፋዬ ገሠሠ በቀ.ኃ.ሥ.ቴያትር ተቀጥሮ ስለነበረና ተስፋዬንም ረዳት ደራኪው አድርጎት ስለነበረ ካፕላን የቀ.ኃ.ሥ.ቴያትርን ትብብር ማግኘቱ ተሳክቶለታል

በዚሁ ሳቢያም የቀ.ኃ.ሥ.ቴያትር ባልደረባ የሆነው ፀጋዬ ደባልቄ የመክፈቻ ሙዚቃውን ሲያቀርብ ለማ ገብረሕይወት እንደ ሰላይና ፎካሪ፣ ተስፋዬ ገሠሠ እንደ መልዕክተኛ፣ ላቀው አበበ እንደ ባለ ዋሽንቱ እረኛ፣ ሌሎችም እንደ ሰርገኛ እና ታዳሚ ተውነዋል። አብሮት የመጣው የፉል ብራይት ባልደረባው የሙዚቃ ሊቅ ግብፃዊ-አሜሪካዊው ዶ/ር ሀሊም ኤልዳብ ግብአተ-ድምፁንና ሙዚቃውን፣ ግብአተ-ብርሀኑን ደግሞ ፕሮፌሰር ሮይ ሎሬንስ፣ አልባሳቱን ባለቤቱ ፍራንሲስ ካፕላን፣ የአስተዳደር አስተባባሪነቱን ዶ/ር ሊንደን ሌቪት አከናውነዋል። በትወናውም ፕሮፌሰር ሬቨን ሮበርት እንደ ካፒቴን ካሜሩን፣ ኬኒያዊው ተማሪ ኤኛ መዋኒኪ እንደ አሽከር ተውነዋል። አፈወርቅ ተክሌ የትዕይንቱን ዲዛይን፣ አማረ ተፈሪ መስተንግዶውን፣ ተፈሪ ብዙአየሁ የማስታወቂያ ሀላፊነትና አቅርቦት አስተባባሪነትን፣ በትወናውም ሰላሙ በቀለ እንደ ካሣ፣ ሂሩት በፍቃዱ እንደ ካሣ እናት- አትጠገብ፣ ተኰሂ ቦጎሲያን (አርመናዊት በእንግሊዝ አገር የታወቀች ተዋናይት) እንደ ንግሥት መነን፣ ዘርአብሩክ አበራ እንደ ራስ አሊ፣ ጥሩወርቅ ደስታ እንደ ልዕልት ተዋበች፣ ዮናስ አድማሱ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ተፈሪ ብዙአየሁ እንደ ደጃች ወንድይራድ፣ መኮንን ደለለ እንደ ገልሞ፣ የማነ ገብረሚካኤል እንደ ገብርዬ፣ ተመስገን ኃይሌ እንደ ህፃኑ ምኒልክ፣ ሶፍያ ይልማ እንደ ወይዘሮ ጥሩ ወርቅ፣ ስንታየሁ ሳህሌ እንደ ዓለማየሁ ቴዎድሮስ፣ ተሾመ ኃይለማሪያም እንደ ትሩባዶር የተጫወቱ ሲሆን አባተ መኩሪያም ቃላት ጠቋሚ (ፕሮምፕተር) ነበር።

ድራማው እንዳለቀ፣ ንጉሠ-ነገሥቱ ደራኪውን ካፕላንን ተቀብለው የእጅ ሰላምታ አቅርበውለታል። ሁለቱም የፈረንሳይኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች ስለነበሩ በዚሁ ተግባብተው፣ ጥበቡ በተጠናከረ መንገድ መቀጠል እንዳለበት ካፕላን ያሳመናቸው ጃንሆይ 30 ሺህ ብር ለግሰው የግብር ቤት የነበረው ወደ ቴያትር አዳራሽነት እንዲለወጥና አንድ የስነጥበብ ማዕከል እንዲቋቋም መመሪያ ሰጥተዋል።

የፊሊፕ ካፕላን ፌሎውሽፕ ለአንድ ዓመት ከታደሰለት በኋላ ከ1955 ክረምት ጀምሮ ተስፋዬ ገሠሠ በዩኒቨርሲቲው እንዲቀጠር አስደረገ። ከኤልዳብና ከተስፋዬ ገሠሠ ተጋግዞም ግብር ቤቱን ቤተ ተውኔት አስመሰለው። አዳራሹም (የአሁኑ የባህል ማዕከል) ቤተ ኪነ-ጥበባት ወቴያትር ተብሎ ተሰየመ። ፊሊፕ ካፕላን ዳይሬክተር ሆኖ ተመደበ። በሱ ስር በስራ አስፈፃሚነት ተስፋዬ ገሠሠ የአማርኛው ቴያትር እና ስነ-ጽሑፍ ሃላፊ፣ ዶ/ር ሊንደን ሌቪት ዋና አስተዳዳሪ፣ ዶ/ር ሀሊም ኤልዳቭ የሙዚቃና የዳንስ ሃላፊ፤ ዶ/ር ማርከስ አንደርውድ ዋና ፀሐፊ፣ ማርሻል ክላውስ የሂሳብ ሹም ሆኑ። ፀጋዬ ገብረመድህንና መንግስቱ ለማን በቴያትር አማካሪነት፣ አለ ፈለገሰላምንና አፈወርቅ ተክሌን በሥዕል አማካሪነት፣ ፀጋዬ ደባልቄንና አሸናፊ ከበደን በሙዚቃ አማካሪነት፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራኑን ዶ/ር ሪቻርድ ፓንክረስትንና ሚስተር ፖት ሀንተንን በስነ-ጽሑፍ አማካሪነት አደራጅቶ አዳዲስ ስነጥበባዊ ጅማሮዎችን አከናውኗል። በሱ አመራር የሥዕልና ስነጽሑፍ ሲምፖዚየም ተዘጋጅቶ ፀጋዬ ገብረመድህን ስለቴያትር፣ መንግስቱ ለማ ስለስነ-ግጥም፣ ገብረክርስቶስ ደስታ ደግሞ ስለስነ-ስዕል እንዲናገሩ አድርጓል።

በዚሁ አዳራሽ ታዋቂ የሆኑ በርካታ የአውሮፓ፣ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ተውኔቶች ተደርከዋል። ተስፋዬ ገሠሠ ሮሜዎና ዡሊዬትን፣ አቶ በላይነህን፣ እናትና ልጆችን፣ ያላቻ ጋብቻን (ጃንሆይ በተገኙበት) ሲደርክ ፊሊፕ ካፕላን በመቸት ዲዛይን፣ በመብራትና ድምጽ ግብአት አስተዋጽኦ አበርክቷል። ራሱም የሳሙኤል ቤኬትን Waiting for Godot፣ የአልቢን The Zoo Story፣ እና Who is Afraid ofVirginia Woolf? በተማሪዎችና ውጭ ሰዎች ደርኮ ለህዝብ አሳይቷል። የተወሰኑ ተማሪዎችን በማስተባበር አብሮ አዳራሽን ያጸዳና የመድረክ ትዕይንቱን እያነጠ ነበር ድራማዎችን ያቀርብ የነበረው። እንደ አባተ መኩሪያ ደበበ እሸቱ፣ ወጋየሁ ንጋቱና ተፈሪ ብዙአየሁ ላሉ ተዋንያን የመድረክ ረዳቶች 50 ብር የኪስ ገንዘብ ያሰጥም ነበር።

ፊሊፕ እስከ 1956 ዓ.ም. መጨረሻ ከሰራ በኋላ ልጆቹን ጃንን፣ መሊሳ አዲስን (አዲስ አበባ የተወለደችውን)፣ ባለቤቱን ፍራንሲስን ይዞ ወደ አሜሪካ ፍሎሪዳ ተመለሰ። ከዚያም የጥቁሮች ሜቶዲስት ተቋም በሆነው ቩርሂስ ኮሌጅ በእንግሊዝኛ መምህርነት ተቀጠረ። እሱ ያስተምርበት በነበረው በጥቁሮች ትምህርት ቤት ውስጥ ልጁ መሊሳ ብቸኛዋ ነጭ ተማሪ ነበረች። ያኔ በእንዲህ ዓይነት ህይወት ውስጥ በአሜሪካ መዝለቅ እጅግ ከባድ ነበር። በኋላ በጁን 1969 ጆርጂያ በሚገኘው በፎርት ቫሊ ስቴት ኮሌጅ ስራ አገኘ። ወደዚያ ከመሄዱ በፊት ዘመድ ለመጠየቅ ካሊፎርኒያ ወደ ሚገኘው ኦክላንድ ቤተሰቡን ይዞ ሄደ። ያኔ ጠንካራ የ52 ዓመት ጎልማሳ ነበር። ወደ መዝናኛ ሄዶ ልጁ መሊሳን በመናፈሻ ውስጥ እያጫወተ ሳለ አንድ ፖሊስ ወደ ካፕላን ሄዶ፣ “ከመጠን በላይ በአካባቢው በመዘዋወር ልታይ ልታይ እያልክ ሰላም ነስተሃል” በማለት እጁን በብረት ሰንሰለት አሰረው።

ያኔ የስድስት ዓመት የነበረችው ልጁ መሊሳ አዲስ፣ ስለዚያን ጊዜ ስታስታውስ “ካፕላን መኪና ውስጥ በመራገጥና በመጮህ ያውክ እንደነበረ ፖሊሱ ውሸቱን ሪፖርት አደረገ። ወደ እስር ቤት ሲወስዱት እኔ አብሬው መኪና ውስጥ ነበርኩኝ። በጨዋነት ተቀምጦ እኔን ለማረጋጋት ምንም ነገር እንዳልሆነ ለማስመሰል በአይኑ ይጠቃቅሰኝ ነበር እንጂ የተባለውን አልፈጸመም።” ብላለች። ካፕላን ከሶስት ቀን በኋላ አእምሮውን ስቶ ሞተ። የሬሳው ምርመራ ራጂ ሲታይ ሰውነቱ ቆሳስሎ እንደነበረ አመልክቷል። በአሰቃቂ ህልፈቱ ምክንያትቤተሰቡ ፖሊሱ ላይ ክስ ቢመሰርትም የተፈፀመው ወንጀል ተክዶና ተድበስብሶ፣ የሁለት ሺህ አምስት መቶ ዶላር ካሳ ብቻ ነበር የተፈረደላቸው። የካፕላን ባለቤት ግን ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለየችበት ደቂቃ ድረስ ቼኩን አልመነዘረችውም።

ተማሪዎቹ እና የስራ ባልደረባዎቹ፣ እንደ ካፕላን ያለ እጅግ ተወዳጅና የሚያስገርም መምህር አጋጥሟቸው እንደማያውቅ፣ የማስተማርና የቴያትር አቅርቦት ጣምራ ችሎታው፤ አሉ ከሚባሉት ጥቂት ድንቅ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ዘንድ እንኳ ተዘውትሮ የሚገኝ እንዳይደለ፤ በእንዲህ ያለው ብርቅና የሚያስገርም የችሎታ ጥምረት ላይ ትህትናና ልባዊ የማነቃቃት ስብዕናው ተደማምሮ፣ ከፍተኛ አክብሮትንና አድናቆትን ሊያተርፍለት እንደቻለ በመጽሔቱ መስክረውለታል።

ልጁ መሊሳ አዲስ፣ የዛሬ አራት ዓመት ገደማ ወደ ተወለደችበት አዲስ አበባ መጥታ ስለ አባቷ ብዙ ቁምነገር ልትረዳ ችላለች። የተሰማትን ስሜት ስትገልፅም “እኔ አሁን ወደ ሙሉዕነት እንደ ተሸጋገርኩ ነው የሚሰማኝ። ልቤ ከምንጊዜውም በላይ ደስተኛ ሆኗል። ፊሊፕ እና ፍራንሲስ በአካል እዚህ ባይገኙም በመንፈስ እዚህ እንዳሉ እርግጠኛ ነኝ።” በማለት ተናግራለች። ወደ አገሯ እንደ ተመለሰች ብዙም ሳትቆይ ከዚህ ዓለም ተለይታለች። ጠቢብ ስለነበረችም እንደ አባቷ ታሪኳ በአሜሪካ መፅሔቶች ተዘግቧል።

ዶ/ር ፊሊፕ ካፕላን ለአገራችን ስነ- ጥበብ እድገት ያበረከተውና፣ ከዚህም ጋር በተያያዘ ለሰው ልጅ እኩልነት የከፈለው የህይወት መስዋዕትነት እጅግ የላቀ ሰብዕናውን በአክብሮት ሊያዘክር የሚገባ ነው።

 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top