ታዛ ስፖርት

“ዳኞች ተጫዋቾቹን ሥርዓት ካስያዙ ደጋፊው የውክልና ግጭት ውስጥ አይገባም”

ታዛ፡- በአዲስ አበባ ስታዲዮም የእግር ኳስ ጨዋታ ሲኖር በመታደም፤ የኢትዮጵያ ቡና ክለብ ግጥሚያ ሲኖረው በደጋፊነትና በአስጨፋሪነት ምን ያህል ጊዜ አገለገልክ?

አዳነ ሽጉጤ፡- በ1989 ዓ.ም. መጨረሻ አካባቢ ነው በአዲስ አበባ ስታዲዮም መታደም የጀመርኩት። ወደ 20 ዓመት ሆኖኛል።

ታዛ፡- ባለፉት ሃያ ዓመታት ስታዲዮም ውስጥ በደጋፊነትና በአስጨፋሪነት ሚናህ ምን ታዘብክ?

አዳነ ሽጉጤ፡- ቀደም ባሉት ጊዜያት በደጋፊዎች መካከል ጥሩ የሆነ የመከባበር ሁኔታ ነበር። ስታዲዮም የሚገቡት ሰዎች ትላልቅ ሰዎች ናቸው። አሁንም አልፎ አልፎ አሉ። በዛን ጊዜ የነበሩት ተወዳዳሪ ክለቦችም፡- መቻል፣ ጊዮርጊስ፣ ቡና፣ መድኅን፣ መብራት ኃይል እና ሌሎችም ነበሩ። ያኔ ትንሽ የመቻል ደጋፊዎች ያስቸግሩ ነበር። ያም ሆኖ ግን፣ ደስ የሚል የድጋፍ ድባብ ነበር። ያ ጊዜ የሚያምር ነበር። ይናፍቃል። ከብሽሽቅ የዘለለ ብዙ ነገር አልነበረም።

ታዛ፡- በዚያን ጊዜ የአኅጉር አቀፍ (የመላ አፍሪካ ክለቦች) ጨዋታ ሲኖር ደጋፊዎች ይለያዩ ነበር? የተፎካካሪ ክለብ ደጋፊዎች የእንግዳውን ቡድንስ ይደግፉ ነበር?

አዳነ ሽጉጤ፡- ኧረ በፍጹም! አይለያዩም ነበር! በአንድነት፣ በኅብረ- ዝማሬ ነበር የሀገራቸውን ክለብ የሚደግፉት።

ታዛ፡- ከቅርብ ጊዜ ወደህ ምን አዲስ ነገር ተከሰቶ ነው ሁከትና ግጭት የበዛው?

አዳነ ሽጉጤ፡- አላስፈላጊ ነገሮች እየመጡ ነው። ሜዳ ውስጥ እየገቡ መበጥበጥ፣ እንደገና ከሜዳ ውጪ አጉል ነገሮች እየተደረጉ ነው። እኛ አሁን የያዝነው ነገር ቢኖር ይሄን የሁከትና የግርግር ሁኔታ ለመለወጥና ለመቅረፍ ጥሩ ጥሩ ህብረ-ዝማሬዎችን እያጠናንና እያስጠናን፣ የተለያዩ የአደጋገፍ ሁኔታዎችና ጭፈራዎች ተጀምረዋል። ወጣቶች ናቸው ይሄን የጀመሩት። አንድ ዓይነት ህብረ-ዝማሬ አድርገው የሚያስዘምሩ። የተለያዩ ድባቦችን የሚያሳዩ። ጥሩ ጥሩ ልጆች መጥተዋል። ይህ የሚደረገው ደጋፊውን ወደ ፍቅርና ሰላም ለመመለስ ነው። አንድነቱ ጋ ማተኮር እንዲቻል ነው። ዞሮ ዞሮ አንድ ጠንካራ ብሔራዊ ቡድን ለማውጣት ነው የምንጫወተውም የምንደግፈውም። ትልቁ ቁም ነገር በዓለማቀፍ ደረጃ ብቁ እና ጠንካራ አስራ አንድ ተጫዋቾችን ለማውጣት ነው። ለኤልፓም ተጫወትክ፣ ለደደቢት፣ ለባንክም ተጫወትክ ለጊዮርጊስ ወይም ለኢትዮጵያ ቡና፣ ዞሮ ዞሮ ሀገርን የሚወክሉ አስራ አንድ ጠንካራና ጎበዝ ተጫዋቾችን ለማውጣት ነው። ያ ነው ቁም ነገሩ።

ታዛ፡- ግጭት እየተፈጠረ ያለው በየትኞቹ ክለቦች ደጋፊዎች መካከል ነው?

አዳነ ሽጉጤ፡- ይበልጥ ግጭት እየተፈጠረ ያለው ክልል ላይ ነው። እንደምታውቀው ክልል ላይ የሚገኙት ብዙዎቹ ስታዲዮሞች አጥር እንኳ የላቸውም። ለምንም ነገር ክፍት ናቸው። ስለዚህ ጥቂት ግለሰቦች በተናገሩት ግጭቱ በቀላሉ ከአንዱ ወደ ሌላው እየተሻገረ፣ መወራወርና መጣላት ይከሰትና የሁለት ልጆች ወይም የጥቂቶች ግጭት የሁለት ቡድን ደጋፊዎች ይሆናል። በሌላ በኩል የዳኛ ስህተት ተበራክቷል። ብዙ ጊዜ ለደጋፊዎች ግጭት የዳኞች የተሳሳተ ውሳኔ ብዙ ሁከት፣ ግርግርና ጸብ ሲያስከትል ተመልክተናል። እንዲህ ዓይነት ግጭቶች ብዙውን ጊዜ በክልል የደርሶ መልስ ጨዋታዎች ወቅት ነው የሚከሰቱት።

በአዳማና ቡና ደጋፊዎች መካከል ግጭት ሲፈጠር በቦታው ነበርኩ። መጀመሪያ የቃላት ጦርነት ተነሳ። አለመግባባት ተፈጠረ። ከዚያ የሆነ ነገር በሃይላንድ እየሞሉ መወራወር ተጀመረ። ሁከት ተፈጠረ። ይኸው ነው።

ታዛ፡- ለግጭት መነሻ ናቸው የምትላቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

አዳነ ሽጉጤ፡- ብዙ ጊዜ ስታዲዮም ውስጥ በደጋፊዎች መካከል ጠብ የሚያስነሳው የዳኛ የውሳኔ ስህተት ነው። አንድ ተጫዋች ሜዳ ውስጥ ጥፋት ሲፈጽም ዳኞች ቶሎ ብለው ትክክለኛውን እርምጃ ካልወሰዱበት፣ ደጋፊው የመጠቃት ስሜት ይሰማውና በንዴት ለግጭት ይነሳሳል። ለምሳሌ ሪጎሪ (ፔናሊቲ) ሊያሰጥህ የሚችለውን ዕድል ዳኛው በስህተት ሊከለክልህ ይችላል። ለዳኛው የማይታየው ለደጋፊው ሊታይ ይችላል። ዳኛ ፍፁም አይደለም፤ እንደ ማንኛውም ሰው ይሳሳታል። ግን ለሁሉም እኩል ሚዛናዊ ቢሆን ጥሩ ነው። በውጪ አገር እንደሚሆነው በካሜራ ቢታገዙ ደግሞ እጅግ በጣም ጥሩ ነው። ምክንያቱም ሁልጊዜም ጠብ የሚነሳው ሜዳ ውስጥ በሚታይ ስህተት መነሻነት ስለሆነ ነው። ከሜዳ ውጭ ያለው አለመግባባት ያን ያህል አይደለም። በአንድ አስጨፋሪ አንተም ተው፣ አንተም ተው ብለህ የምታስቆመው ነው።

እኔ በማስጨፍርበት ጊዜ ስድብ እንኳን ሲያነሱ ተው ነው የምለው። መሃል ገብቼም እገላግላለሁ። ጠብ እርስ በርስ ውስጥም እኮ አለ። ከተቃራኒ ክለብ ጋር ብቻ አደለም። ያንን ግን የምታስጥለው በምክንያት ነው። ባለህበት ቦታ ሆነህ አንተም ተው አንተም ተው ብለህ አስታርቀህ መለያየት ነው። እንደ ዛሬው ነገሮች ሳይከፉ ሚስማር ተራ እያስጨፈርኩ ከዛ ወጥቼ የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ባሉበት ካታንጋ ገብተን ‹‹እናንተም ተው፣ እነርሱን አስቁመናል›› በሚል ገና ግጭቱ በቃላት ደረጃ እያለ እናስቆም ነበር።

ሌላው ደግሞ፣ ደጋፊው የቃላት ጦርነት እንደሚያደርገው ሁሉ በተጫዋቾች መካከልም የቃላት ግጭት አለ። በዚህ ጊዜ ዳኞች ተጫዋቾቹን ጠርተው ካላስጠነቀቁና ገደብ ካላስያዙ የእነርሱ ግጭት ወደ ደጋፊዎቻቸው ይዞርና የደጋፊ ግጭት ይፈጥራል። ዳኞች ተጫዋቾቹን ሥርዓት ካስያዙ ደጋፊው የውክልና ግጭት ውስጥ አይገባም።

ታዛ፡- የቡና ደጋፊ ባህሪ ምን ይመስላል አንተ ስትመለከተው?

አዳነ ሽጉጤ፡- የቡና ደጋፊ እኔን ጨምሮ ክለቡን እንደሚወድና

እንደሚያከብር አውቃለሁ። በክለቡ ደስተኛ ነው። ክለቡ በጨዋታ ተበልጦ ከተሸነፈ በስፖርታዊ ጨዋነት አጨብጭቦ የሚወጣበት ጊዜም አለ። ያው አንዳንዴም ያልተፈለጉ ነገሮች ይከሰታሉ። ሁሉም ደጋፊ አንድ ዓይነት አይደለም። ከእኛም ስህተት የሚሰራ ይኖራል። እየመከርክ እየገሰጽክ ትሄዳለህ። ሌሎች ክለቦችም እንዲህ ቢያደርጉ ለስፖርታዊ ጨዋነት ጥሩ ነው።

ታዛ፡- ብጥብጡና ሁከቱ ለምን የጨመረ ይመስልሃል?

አዳነ ሽጉጤ፡- እልህ መሰለኝ፤ መሰላቸት። ተጫዋቾቹ ኳስ ጨዋታውን ሲገድሉበት ኳሱን ትቶ እርስ በእርሱ መታገል ጀመረ። አሁን ይህን የመሰለ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር የኳስ ፍቅር ያለው ሀገርና ህዝብ እንዴት ሆኖ ነው አገርን የሚወክሉና ባንዲራ የሚያውለበልቡ 11 ጎበዝ ተጫዋቾች የሚያጣው? ለክለቦች ብቁ የሚሆኑ ተጫዋቾች እንዴት ይጠፋሉ? ያስገርማልም፣ ያሳዝናልም።

አሁን በቅርቡ ቡና እና ቢራ ሲጫወቱ የተረበሸው ካታንጋ ላይ ነው። እንዳየኸው ሌላው ቦታ ላይ ሰላም ነው። አሁን ካታንጋ ላይ በተነሳው ረብሻ ሙሉ የቡናን ደጋፊ ልትወቅስ ይገባል? አይገባም። ወይም ሙሉ የጊዮርጊስን ደጋፊ ልትወቅስ ይገባል? አይገባም። መውቀስ የሚገባህ እዛ ቦታው ጋ ያለውን ደጋፊ ነው። ጠቡ ለምንስ ተነሳ? ኳሱስ እሚረባ ነበር ወይ? ያ ጨዋታ እንኳንስ ጠብ ልታስነሳበት ይቅርና ክብሪትም የሚያስጭር ጨዋታ አልነበረም።

ታዛ፡- ኳስ ጨዋታ ሲኖር ትኬት ለመቁረጥ ረጃጅም ሰልፎች አሉ፤ በዚህ ወቅት መጠጥ ጠጥቶ የሚገባው ደጋፊ ብዙ ነው ይባ ክለቦችም እንዲህ ቢያደርጉ
ለስፖርታዊ ጨዋነት ጥሩ ነው።

ላልና ይህስ ግጭቱን አያባብስም? አዳነ ሽጉጤ፡- ምንም ችግር የለውም። እኔ እኮ ቡድኔን ለመደገፍ ሶስት አራቴ ውጭ አገር ሄጃለሁ። የፈለግከውን ምግብ እየበላህ፣ የፈለግከውን መጠጥ እየጠጣህ ነው የምታየው። አንደኛ ነገር ስታዲዮም ውስጥ ምን አለ? ውሃ እንኳ የለም፤ የምትበላው ነገር የለም። ሰዓቱ እስኪ ደርስ ውጪ ተጠቅመህ ነው የምትገባው። እና ጨዋታ ተጀምሮ እስኪያልቅ ሳትበላ ሳትጠጣ ልትውል ነው? ወረፋ እንኳ ሁለት ሶስት ሰዓት ትጠብቃለህ። ለአስር ሰዓት ጨዋታ ስድስት ሰዓት ገብቶ የሚጠብቅ አለ። እስከ አስራ ሁለት ሰዓት የሚበላው ነገር የለም። ውጪ በልተህ ተዝናንተህ መግባት ነው እንጂ ስታድዮም ውስጥ ምንም ነገር የለም። ውስጥ ገብተህ እኮ ፀሐይ ነው የሚያሳርርህ። ለሞተ ኳስ ደግሞ ምንም ሳትበላ ትገባለህ እንዴ? ጨጓራ በሽታ! የክለቡ ጨጓራ በሽታ አለ። እንደገና በርሃብ ደግሞ ሌላ ጨጓራ!?

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top