ታዛ ስፖርት

“ደጋፊው ከሚጋጭ ቢዝናናበት የኳስ ደረጃችንን በጋራ ለማሻሻል እንችላለን ”

ታዛ፡- በአዲስ አበባ ስታዲዮም የእግር ኳስ ጨዋታ ሲኖር በመታደም፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ ግጥሚያ ሲኖረው በደጋፊነትና በአስጨፋሪነት ምን ያህል ጊዜ አገለገልክ?

ይድነቃቸው አሸናፊ (አቸኑ)፡- በአስጨፋሪነት የቆየሁበት ዘመን 29 ዓመት ይሆናል። ከልጅነቴ ጀምሮ ያደግኩበት ነው።

ታዛ፡- ቀደም ሲል የነበረው የድጋፍ ባህል እንዴት ነበር? አሁንስ?

ይድነቃቸው አሸናፊ (አቸኑ)፡- ቀደም ሲል የነበረው የደጋፊ ስሜትና አሁን ያለው የደጋፊ ስሜት በጣም የተለያየ ነው። የበፊት ደጋፊዎች ኳስን ሜዳ ውስጥ አይተው፣ ድጋፉን እዛው ሜዳ ውስጥ ጨርሰው ከሜዳ ውጭ ግን ጓደኝነታቸው ነው የሚቀጥለው። ደግሞ ለሚቀጥለው ግጥሚያ ይዘጋጃል በሠላም- በፍቅር።

በመካከል ደግሞ የተለያዩ አምባጓሮዎች መፈጠር ጀመሩ። የተለያዩ የድንጋይ ውርወራዎች ብልጭ ድርግም የሚሉ ነበሩ። እነዚህ የስታዲዮም አምቧጓሮዎች መቆም ባለመቻላቸው በእድሜ ተለቅ ያሉ፣ ሴቶች እና ልጆች ደጋፊዎች ከስታዲዮም ራቁ። ከዛ በኋላ ደግሞ አሁን በተሻለ ሁኔታ ያደጋገፍ ዘዬዎች ተቀይረው፣ ሁሉም ለድጋፍ በሚጓጓበት ጊዜ አላስፈላጊ ግጭቶች እየተፈጠሩ ነው።

ታዛ፡- ግጭት እየተፈጠረ ያለው በየትኞቹ ክለቦች ደጋፊዎች መካከል ነው?

ይድነቃቸው አሸናፊ (አቸኑ)፡ – ብዙውን ጊዜ ጊዮርጊስ ከቡና ጋር በሚጫወትበት ሰዓት ነው ግጭቱ የሚነሳው። እነዚህ ግጭቶች የሚፈጠሩበትም ምክንያት አንደኛ ለውጤት ከመጓጓት የተነሳ፣ ሁለተኛ የደጋፊዎች ያለመሸነፍ ስሜት ነው የሚመስለኝ። ሶሥተኛው ሜዳ ውስጥ የሚያጋጥሙ ነገሮች በተለይ ዳኞች የውሳኔ ስህተቶችን ሲፈጥሩ ተጫዋቾች በደጋፊዎቻቸው ለመወደድ ሲሉ የዳኞችን ውሳኔ ያለመቀበል ዝንባሌ ያሳያሉ። ሜዳ ውስጥ የሚፈጠሩት ትዕይንቶች ደግሞ ደጋፊውን በቀላሉ ወደ ፀብ ይከቱታል። በተጨማሪም ከመጠን በላይ የሆነ አልኮል ጠጥቶ ወደ ስታዲዮም መግባቱ ያባባሰው ይመስለኛል።

ታዛ፡- ክልል ላይ የሚፈጠሩት ግጭቶችስ መነሻቸው ምንድን ነው?

ይድነቃቸው አሸናፊ (አቸኑ)፡- ክልል ላይ የሚፈጠሩ ግጭቶች መነሻቸው አንደኛው በዳኝነት ስህተት ነው። የክልል ቡድኖች ወደ አዲስ አበባ መጥተው ሲጫወቱ አንድ ቦታ ላይ ችግር ከተፈጠረ፣ ወደ ክልል በምትሄድበት ሰዓት በቃ ለአጸፋ መልስ ዝግጁ ሆነው ይጠብቁሃል። እንደ በቀል አድርገው ያዩታል ማለት ነው።

በእግር ኳስ ጨዋታ የሰው ልጅ ህይወት መጥፋት የለበትም። የሰው አካል መጎዳት የለበትም። እግር ኳስ መዝናኛ እንጂ የመደባደቢያ መስክ አይደለም። በአጠቃላይ ስፖርት መዝናኛ እንጂ መጣያ፣ የጎሪጥ መተያያና እየጠበቁ ወንጀል የሚሰራበት መሆን የለበትም።

ታዛ፡- የጊዮርጊስ ደጋፊዎች ሁኔታና ባህርይስ እንዴት ነው?

ይድነቃቸው አሸናፊ (አቸኑ)፡ – ክለቤ ውስጥ ምንም ስህተት የለም ማለት አልችልም። ከጥሩ ስንዴ መሐል እንክርዳድ እንደማይጠፋ ሁሉ ጥፋተኞች ሊኖሩ ይችላሉ። ሆኖም ብዙኀኑ የኛ ደጋፊ በጸብና ሁካታ አያምንም። ለስህተት የሚጋብዝ ነገር የሚሰሩ ደጋፊዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እነሱንም በክለቡ መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ከአባልነት እስከ ማገድ ይኬዳል። ካልሆነም ለሕግ በመስጠት የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ጀምረን ነገሮች እየተስተካከሉ መጥተዋል። ስለዚህ የሁሉም ክለብ ደጋፊዎች በእንደዚህ ዓይነት መንገድ ቢጓዙ ፀብ አጫሪ የምንላቸውን ነገሮች የሚፈጥሩ አካለትን መቆጣጠር ይቻላል።

ታዛ፡- ሥርዓት ያለው አደጋገፍ ለማስፈን ምን እየሰራችሁ ነው? ይድነቃቸው አሸናፊ (አቸኑ)፡ – እነዚህ አዳዲስ የድጋፍ ዘዬዎች የተቃራኒ ክለብ ደጋፊዎችን በማይነካ መልኩ ክለባችንን የምናበረታታባቸው፣ ብዙ የጋራ ዝማሬዎችን አዘጋጅተናል። ዝማሬዎቹ በመቀባበል የሚቀርቡ ሲሆን ጭብጨባ፣ ጭፈራ እና ውዝዋዜም አላቸው። ይሄ አደጋገፍ የሌላን ቡድን ስም ሳናነሳ፣ 90 ደቂቃውን የራሳችንን ቡድን የምናበረታታበትና የምንደግፍበት ስልት ነው። አሁን ዝግጅቱን በማጠናቀቅ ላይ ነን። ሌላው ቡድንም ከኛ እንዲማርና ተሞክሮ እየወሰደ እንዲጓዝ ነው ምኞታችን።

ታዛ፡- የሀገር ውስጥ የእግር ኳስ ቡድኖችና ብሔራዊ ቡድን ያለበትን ደረጃ እንዴት ትገመግመዋለህ?

ይድነቃቸው አሸናፊ (አቸኑ)፡- በሀገራችን እግር ኳስ እያደገ ነው ለማለት አልደፍርም። የተጫዋቾች ክፍያ ገንዘቡ ነው ያደገው። የተጫዋቾች ህይወት ብቻ ነው የተቀየረው። በብሔራዊ ቡድን ደረጃ ስንሄድ ደግሞ እድሜ ለአቶ ሰውነት ቢሻው ከ31 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ አሳልፎ ነበር።

ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ደግሞ ዳር የደረስንበት ጊዜ ነበር። ሆኖም ውጤት ሳይሳካልን ቀረ። ከዛ ውጪ ግን ክለቦች ጠንካራ አይደሉም። ሁልጊዜ የኢትዮጵያን ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ የሚበላው ጊዮርጊስ ነው። ጊዮርጊስን አሸንፎ ዋንጫ መብላት ያልቻሉ ቡድኖች ባሉበት የውድድር ፕሮግራም ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ለአፍሪካ የክለቦች ሻምፒዮና ደርሶ ውጤት እንዲያመጣ መጠበቅ ማለት የማይታሰብ ነው። ለምን ፉክክሩ መጀመሪያ እዚህ ሀገር ውስጥ የለማ።

ታዛ፡- ታድያ እግር ኳሱ እንዲህ በወደቀበት ደረጃ የደጋፊ ግጭትና ሁከት ከየት መጣ?

ይድነቃቸው አሸናፊ (አቸኑ)፡- አንደኛ በኳሱ መሰላቸት ነው። እንደገና ደግሞ በደጋፊ መካከል የአልሸነፍ ባይነት ነገር አለች እንጂ የሀገራችን እግር ኳስ የሚያደባድብበት ደረጃ ላይ አይደለም። ግን ያው ሰው ባለው ነው የሚዝናናው። ደጋፊው በኳስ ከሚጋጭ ቢዝናናበት የኳስ ደረጃችንን በጋራ ማሻሻል እንችላለን።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

በብዛት የተነበቡ

To Top