በላ ልበልሃ

የፖለቲካ ባህላችን ህመምና የንጉሱ አወዳደቅ

“ገለባ ሁነህ እሳትን ቆየው”

የ ፖለቲካ ባህል፣ ከፖለቲካ ተቋማትና ከሚከሰቱ ፖለቲካዊ ውጤቶች ጋር ያለው ትስስር ውስብስብ መሆኑን ተረድተናል፤ ብልቶቹም ድርብርቦች መሆናቸው ይታወቃል። ሌላው ቀርቶ “ፖለቲካዊ ባህልን በትክክልና በግልፅ ማስቀመጥ ይፈትናል። ለተለያዩ ትርጉሞችም የተጋለጠ ነው” ሲል በአረብ አገራት ፖለቲካዊ ባህል ላይ ጥናት ያደረገው ፖል ሳሬም ያስረዳል።

የኢትዮጵያ የሰሜኑ የፖለቲካ ባህል ከመካከለኛው ዘመን የዘርአ ያዕቆብ (1434-68) የንጉሶች ፈላጭ ቆራጭነት እስከ አፄ ኃይለሥላሴ መጨረሻ ዘመን ድረስ ዘልቋል። ኢትዮጵያ ለዕድገትዋና ለዴሞክራሲዋ መሠረት ሊሆናት የሚችለውን የአውሮፓውያን ዓይነት ማግና ካርታ (የነጻነት ቻርተር) ወይም የቡርዧ ዴሞክራሲያዊ አብዮትን ሳታገኝ በመቅረቷ የፖለቲካ ባህልዋ ስንኩል ሆኖ ቆይቷል። በተወሰኑ የታሪክ ኹነቶች ሥልጣንን ለአካባቢ ገዥዎች ማደላደል አልታየም ማለት ግን አይደለም። አፄ ዮሐንስም ሆኑ አፄ ምኒልክ አድርገውታል። አፄ ዮሐንስ ለጎጃሙ ንጉስ ተክለሃይማኖትና ለአፄ ምኒልክ አካባቢያዊ ግዛትን ሲያደላድሉ፤ ምኒልክ ደግሞ በተራቸው አካባቢውን ለሚገዙ ተወላጆች ሥልጣን ሰጥተዋል። በዚህ ረገድ የሌቃ-ለቀምቱ ኩምሳ ሞረዳ፣ የጂማው አባ ጅፋር፣ የአሶሳና ቤኒሻንጉሉ ሼህ ሆጀሌ አል-ሀሰን፤ የአውሳው ሀንፍሬና የጉባው ሃምዳን አቡ ሾክ ይጠቀሳሉ። ዳሩ ግን እነዚህ ሁሉ ራስን የማስተዳደር ግዛቶች በአፄ ኃይለሥላሴ እንዲቀሩ ተደርገው በንጉሱ ፈርጣማ እጅ ሥር ወደቁ። ማዕከላዊነት ይበልጥ ኢትዮጵያን ጨምድዶ ያዛት። ይህ በመሆኑ ምን ተፈጠረ? እስቲ የዚህን ወቅት ፖለቲካዊ ባህል ቅርጽ አልባነት (Formlessness) ቀጥለን እንመልከት።

በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመን በነበረው የፖለቲካ አይዲዮሎጂ አማካኝነት ሲንፀባረቅ የነበረው ፖለቲካዊ ባህል በፖለቲካዊ አስተሳሰብ ላይ ያለውን ተፅዕኖ ለማየት እንሞክር። በሀገራችን ጉዳይ “ይመለከተናል” የሚለው አስተሳሰብ መበልፀግ አለበት። በመንግሥት ጉዳዮች ላይ የእኔነት ስሜት ካላሳደርን በቀር መንግሥት በትክክል ስለመራመዱ መገንዘብ ያስቸግረናል የሚል እምነት አለኝ። ምንም እንኳ የምንነጋገርበት ታሪካዊ ዳራ ያለፈና ያለቀለት ቢሆንም እንኳ፣ ያለንበትን ፖለቲካዊ ባህል ለመመዘን መነሻ መሠረት ይሰጠናል ብዬ አምናለሁ። ብዙ የዘርፉ ጸሐፍት እንዳሳሰቡት እውነተኛ ዴሞክራሲ የሚወሰነው ሀገሪቱ ባላት የፖለቲካ ባህል ዕድገት ነውና። ፕሌቶ “በመንግሥትህ ጉዳዮች ላይ ፍላጎት ካላሳየህ፤ በቂሎች አገዛዝ ሥር ለመውደቅ ትገደዳለህ” (If you do not take an interest in the affairs of your government, then you are doomed to live under the rule of fools) ያለውን ታላቅ አባባል እዚህ ላይ ማስታወስ ሳይገባ አይቀርም።

በዘመነ አጼ ኃይለሥላሴ፣ ካለፉት መንግሥታት ይልቅ ዜጎች ማዕከላዊ መንግሥቱን አውቀው በሕገ-መንግሥት ጥላ ሥር ለመጀመሪያ ጊዜ ከጥንታዊ ፖለቲካዊ ባህል ወደ ዜጋ (subject) ፖለቲካዊ ባህል ደረጃ የተሸጋገሩበት ጊዜ ነበር ልንል እንችላለን። ይህ ማለት ዜጎች በአንድ የተማከለ ፖለቲካዊ አስተዳደር ሥር ማዕከላዊ መንግሥቱን አውቀውና ለመንግሥቱ ውሳኔዎች መገዛት የጀመሩበት ዘመን መሆኑ ነው። አገዛዙ ከላይ ወደ ታች የሚፈስ የጌታና የሎሌ ግንኙነትን የሚከተል እንደነበር ይታወቃል። ኢትዮጵያውያን ነን ብለው የሚቀበሉ ዜጎች ህይወታቸው በመንግሥት ፖሊሲዎች ተፅዕኖ ሥር በቀጥታ እንደሚወድቅ ይገነዘባሉ። ገላውዲዮስ አርአያ እንደሚለው እነዚህ የህዝብ ክፍሎች መሠረታዊና መካከለኛ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ናቸው። በተጨማሪ ይህ ክፍል፣ መንግሥት ወሳኝ አካል (authority) እንዳለው ቢረዳም፣ ሚናውንና ፖለቲካዊ ሂደቱን በትክክል ሊገነዘቡ የሚችሉ ናቸው ይላል።

አልጋ ወራሽ ተፈሪ፣ በደጋፊዎቻቸው አማካኝነት በዘዴና በስልት ሥልጣናቸውን ካደላደሉ በኋላ የፖለቲካው ወንበር ላይ ያለተቃውሞ አልተቀመጡም። በየአቅጣጫው የተቃውሞ እሳት ይነሳባቸው ጀመር። የአልጋ ወራሽ ተፈሪ ስልታዊ  ፖለቲካዊ አካሄድ ያስፈራቸው ወግ አጥባቂ ቡድኖች እጃቸውን አጣጥፈው አልተቀመጡም። በተለይ ከውጭ አገር ዜጎች ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መፍጠራቸው የፖለቲካ ሥልጣን ክንዳቸውን ለማጠናከር ረድቷቸዋል። በአንጻሩ ደግሞ በመሳፍንቱና በመኳንንቱ ዘንድ ቅሬታን ፈጥሯል። በአፍቃሬ ፈረንጅነት፣ በካቶሊክነት፣ አገር በመሸጥና አልፎም ተርፎም “ተፈሪ እና የሸዋ ተከታዮቹ የውሻ ሥጋ ይበላሉ” እስከሚል ክስ ወረደባቸው።

(ጽንሖ ለእሳት ከዊንከ ብርዓ)

ተፈሪ ግን ይህንን ክስ እንዲህ በዋዛ አልተመለከቱትም። ሰላማዊ ውይይት ወይም ድርድር ሳይሆን የፈረጠመውን ጡንቻቸውን ማሳየት አስፈለጋቸው። በአማፂው የንግስት ዘውዲቱ ባለቤት በራስ ጉግሳ ወሌ ላይ የአውሮፕላን ቦምብ በማዝነብ ፀጥ ለጥ አደረጓቸው። ኃይልና ጉልበት የፖለቲካው መነጋገሪያ ሆነ። የባለቤቷ በዚህ ሁኔታ መውደቅ ያስደነገጣት ንግሥት ዘውዲቱም ልቧ ቆሞ እስከ ወዲያኛው አሸለበች። ተፈሪ ንጉሥ ከተባሉ በኋላ የጋዜጦች የመፃፍ ነፃነት እንኳ ኮስሶ ከ1921 በኋላ ወደ አወዳሽነት ዞሩ። እነሆ እስካሁንም ድረስ የኢትዮጵያ ጋዜጦች በአዝማሪነታቸው ቀጥለዋል። ይህም እንዲሁ በድንገት የመጣ ሳይሆን ነባሩ ፖለቲካዊ ባህላችን ያሳደረውን ተፅዕኖ ያሳያል።

የራስ ተፈሪ ፖለቲካዊ ብልጥነት እንዲህ በቀላሉ እንደማይታይ ብርሃኑ ድንቄ ሲጽፍ፣ “ራስ ተፈሪ ሰው አያምኑም፤ በቀላሉ የሰው ምክር አይከተሉም። ወሬ ከማንም ሰው መስማት ይፈልጋሉ። እንደሚቀናቸው ካላመኑ በቀር አንድ ነገርን ለመጀመር ያመነታሉ። በሴትና በመጠጥ አይታለሉም” ብሏል። የአጼ ኃይለሥላሴ ፍፁማዊና መለኮታዊ አገዛዝ ያስገኘው አዲስ ነገር በ1923 ዓ.ም የመጀመሪያውን፣ በ1948 ዓ.ም ደግሞ የተሻሻለውን ሕገ-መንግሥት ማምጣቱ ነው። ሕገ-መንግሥቱ በንጉሡና በመሳፍንቱ መካከል ያለውን የሥልጣን ሚዛን የሚደነግግ ሲሆን፣ ባህሩ ዘውዴ እንደሚለው “የህዝቡን መብትና ግዴታዎች የሚገልጹ አንዳንድ አንቀፆች የገቡትም እንዲህ አይነት አንቀፆች የሌሉትን ሕገ- መንግሥት ሰው ፊት ማቅረብ ስለማይቻል ይመስላል” ሲል ለይስሙላ እንደቀረበ አትቷል።

“ተፈሪ ንጉሥ ከተባሉ በኋላ የጋዜጦች የመፃፍ ነፃነት እንኳ ኮስሶ ከ1921  በኋላ ወደ አወዳሽነት ዞሩ። እነሆ እስካሁንም ድረስ የኢትዮጵያ ጋዜጦች በአዝማሪነታቸው ቀጥለዋል”

ለይስሙላነቱ እንዲሁ የተፈጠረ አልነበረም። የዚያን ወቅት የፖለቲካ ባህል አስተሳሰብ ስንኩል መብት እንዲሰጥ ሆኖ በመታሰቡ ሕገ-መንግስቱን ሽባ ያደረገ ነበር። የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት መሳፍንት እና መኳንንት ሲሆኑ፣ እነሱም በቀጥታ በንጉሠ-ነገሥቱ የሚሰየሙ ናቸው። የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላቱ ደግሞ ለይስሙላ በህዝቡ የሚመረጡ የመሬት ከበርቴዎች ነበሩ። እኔ እንኳ በልጅነቴ የማውቃቸውና ለሊሙ አውራጃ እንደራሴነት የተወዳደሩት ራቢያ አብዱልቃድር የባላባት (ቆሮ) ልጅ ነበሩ። ዴሞክራሲ ላልተማረውና ተራው ህዝብ በሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ቦታ አልነበረውም ተብሎ ይታሰባልና ላልሰለጠነ ህዝብ አይበጀውም በሚል ቦታ አላገኘም። ይህም የኋላ ኋላ ዳፋው ለንጉሱ ውርደትና ውድቀት በር ከፈተ።

በአጼ ኃይለሥላሴ ላይ የመጣው የመጀመሪያው የፖለቲካ ሥልጣን ችግር በንጉሡ “የራስክን አድን” መርህ የመጣ ነው። የመንግሥታትን ሰላምና ፀጥታ

ለማስከበር ኮሌክቲቭ ሴኩሪቲ መድህን ነው ብሎ ከማሰብ የመነጨ ይመስላል። ንጉሱ በጦር ሜዳ ሲሸነፉ እንደተመከሩት ወደ ጎሬ ሳይሆን ወደ አውሮፓ ነበር ያቀኑት። ይህን በማድረጋቸው ንጉሡ በኢትዮጵያ ታሪክ አንድ ትልቅ ጠባሳ አሳረፉ። ለመጀመሪያ ጊዜ (በዓለም ሳይሆን አይቀርም) የስደት ምርጫ ያጋጠመው ንጉሠ-ነገሥት ኃይለሥላሴ ሆኑ። ምንም እንኳ የጣሊያን ፕሮፖጋንዳ ክፍል “ኃይለሥላሴ ጊዜውን በለንደን ከቆነጃጅት ጋራ ከማሳለፍ በቀር ለአገሩ አሳብ የለውም” የሚል ጽሑፍ እያሰናዳ ቢበትንም የኢትዮጵያውያን አእምሮ ግን ለፕሮፖጋንዳው የተዘጋጀ አልነበረም። ንጉሡን ከውስጡ አላወጣም። በጣሊያን ፕሮፖጋንዳ ክፍል ይሰሩ የነበሩ እንደ ነጋድራስ አፈወርቅ ያሉ ኢትዮጵያውያን ለንጉሡ አጎብዳጅ እንዳልነበሩ ሁሉ፤ አሁን ደግሞ ሦስት መቶ ስድሳ ዲግሪ ዞረው የጣሊያን አሽቀባጭ ሆኑ። ይህም የነበረው የፖለቲካ ባህል አካል እንደነበር መካድ አይቻልም። በኋላም በ1933 ዓ.ም የነፃነት መመለስ ኢትዮጵያውያንን ለሦስት ወገን ከፍሎ እንደነበር የተለያዩ የታሪክ ጸሐፍት ገልፀውታል። ስደተኛ፣ አርበኛና ባንዳ በሚል። ለዚህም ነው በወቅቱ፡-

“ባንድ ወገን ‘ሶልዳቶ’ ሲረግጠኝ በጫማ፣
ባንድ ወገን አርበኛ ንብረቴን ሲሻማ፣
ስደተኛ መጣ ፋንታውን ሊቀማ።
ኡኡ ብል፣ ኡኡ ብል፣ ማነው የሚሰማ?

የሚል ግጥም በአደባባይ ሲሰማ የቆየው። ይህ ግጥም የህዝቡን መብገንና የውስጥ ቁስል የሚገልፅ ይመስለኛል። በአጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያ ከአድዋ በኋላ ሁለተኛውን የጦርነት ዳፋ እንድትሸከም ያደረጋት በቤተ-መንግሥቱ የፖለቲካ ኩሽና ውስጥ የተካሄደው ቅጥ ያጣ ሽኩቻ፤ በወታደራዊ ኃይል ጠንክሮ አለመገኘትና የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲያዊ ጡንቻ መላላት እንደሆነ ግልፅ ሊሆን ይገባል።

ሀገሪቱ ከጣሊያን አገዛዝ ነፃ ብትወጣም፣ ሌላው ገዢ ደግሞ ንጉሡን አስከትሎ መጣ- እንግሊዝ። ጣሊያኖች ትግራይንና ኤርትራን በአንድ አስተዳደር አጣምረው ይገዙ ነበርና እስከ 1934 ዓ.ም ትግራይን ወደ ንጉሡ አልመለሱም። እንግሊዞች አስተዳደራቸው

ሞግዚታዊ ሆኖ በመንግሥት ፀጥታና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጣልቃ እየገቡ ለንጉሡ የጎን ውጋት ሆነው ቆዩ። አልፈው ተርፈውም ኤርትራን “የጠላት ግዛት” በማለት በራሳቸው አስተዳደር ሥር ጠቅልለው ያዙ። አሜሪካኖችም እንደ ቃል ኪዳን አገር አባልነታቸው የተወሰኑ ወታደሮቻቸውን በኤርትራ አሠፈሩ። ኤርትራውያኑ ከነዚህ ሁኔታዎች ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ከጣሊያኖች ዘመን በተሻለ አግኝተዋል። ሦስት የተለያዩ መንግሥታት ማለትም ግብፅ፣ ጣሊያንና ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ባቀረቡት መሠረት ብዙ ፖለቲካዊ ውዝግቦች ተካሄዱ።

በዚህ መሐል በተለይ የግብፅ መንግሥት ለራሱ ጥቅም የቆሙ ደጋፊ ፓርቲዎችን በማደራጀት ለዘለቃው የሚሆኑ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን አጠመደ። ሄንዝ እንደሚለው በ1943 ዓ.ም ጉዳዩ ለተባበሩት መንግሥታት ቀርቦ ኤርትራ ውስጣዊ ፖለቲካዊ ነፃነቷ ተጠብቆ የኢትዮጵያ ፌደራል አሐድ ሆነች። ኤርትራ ገና ፖለቲካዊ ባህሏ ካልዳበረው (parochial culture) ኢትዮጵያ ጋር ስትዋሃድ ለአጼ ኃይለሥላሴም ሆነ ለደርግ መንግሥት መውደቅ ዋና ምክንያት የሆነው እሳት ተጫረ። የአጼ ኃይለሥላሴ መንግሥት ፖለቲካዊ ባህል ከኤርትራ ዴሞክራሲያዊ ልምድ (የሠራተኛ ማህበራት፣ የፕሬስ ነፃነትና የሲቭል ማህበራት መብቶች ወዘተ.) ጋር ተላተመ። ትራቫስኪ “ኢትዮጵያ ኤርትራን በቁጥጥር ሥር ካዋለች የኤርትራውያን ቅሬታ ከሀዘኔታ ጋር ተዳምሮ ሊቀሰቅስና ወደ አመጽ ሊያመራ ይችላል፤ አመፁ ከውጭ በሚገኝ ድጋፍ ኤርትራንና ኢትዮጵያንም ጭምር ሊያምስ ይችላል” የሚለው ግምቱ ዕውን ሆነ። ገብሩ አስራት በጽሑፉ ሲያስታውስ “አጼ ኃይለሥላሴ ያን ሁሉ ለፍተው በ20ኛው ክፍለ ዘመን ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጉትን የፖለቲካ ማሻሻያዎች ከማድረግ ይልቅ ወደ ኋላ የሚጎትቱ እርምጃዎች በመውሰዳቸው ደጋፊዎቻቸው የነበሩትን ኤርትራውያን በሙሉ እያስከፉ ሄዱ” ብሏል።

“ኢትዮጵያ እኮ ህያው ነች፣ እኛ ሁላችንም ዐላፊዎች ነን። ኢትዮጵያ ግን አታልፍም። እስቲ ይመልከቱ! ዐፄ ምኒልክ ዛሬ የት ናቸው? አባትዎ ራስ መኰንን የት አሉ? ሌሎችስ ታላላቆችና ገናናዎች የነበሩት ሁሉ የት ናቸው? ኢትዮጵያ ግን አለች። ወደፊትም ትኖራለች”

ተክለሐዋርያት ስለ ሥልጣን ጭንቅላት በጥባጭነት ሲጽፉ “አረቄ ጠጥቶ የማይሰክር ተየት ይገኛል? ዘውድ፣ ዙፋን ከአረቄ አሥር እጅ የባሱ አስካሪዎች ናቸው። አስካሪነታቸው ንጉሥ ለተባለው ሰው ብቻ አይደለም። ለባለሟሎችም፣ ለዘመነኞችም ነው። ህዝቡንም ጭምር ለማስከር እንዲችሉ ተደርገው ተሰናድተዋል። የአረቄ ስካር በቶሎ ይበርዳል። የዙፋንና የዘውድ ስካር ለመቼም አይበርድ” ሲሉ የሰላ ትችታቸውን ሰንዝረዋል።

ኤርትራውያን ብቻ አይደሉም በንጉሣዊው አገዛዝ የተከፉት። የከተማውም፣ የገጠሩም ህዝብ ማመፅ ጀመረ። ከነዚህም ውስጥ የቀዳማይ ወያነ አመፅ፣ የጎጃም ገበሬዎችና የባሌ ኦሮሞዎች አመፆች ተጠቃሾች ናቸው። አጼ ኃይለሥላሴ ቀድሞ የነበረውን ፖለቲካዊ ባህል ሳያሻሽሉ በመቀጠላቸውና አዳዲስ ዴሞክራሲያዊ ርምጃዎችንም ለመውሰድ የፊውዳልና የንጉሣዊነት ባህርይ ስለማይፈቅድላቸው ሥልጣኔን ያስጠብቅልኛል ብለው ያቋቋሙትን የጦር ኃይል አመጽም አስነሳባቸው። ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ “የጦር ሰው ፖለቲካን መልመድ ወላዋይነትን ያስከትላልና ኃሳቡን መግታት አለበት” እያሉ ለሠራዊቱ በየጊዜው ቢደሰኩሩም ጆሮ የሚሰጣቸው አልተገኘም። የክብር ዘበኛ ጦር በ1953 ዓ.ም የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አደረገ። ከዚህ ጊዜ በኋላ የተማሪው እንቅስቃሴ እየጋለና እየፋመ ንጉሡን ፋታ ነሳ። ተማሪው “በክሮኮዳይልስ” ቡድን ተንኳሽነት በትዕይንተ-ህዝብ ታጅቦ “መሬት ላራሹ፣ ፍትህ ለህዝቡ፣ ፋኖ ተሰማራ፣ የዲሞክራሲ መብቶች ይከበሩ!” ወዘተ. በሚሉ መፈክሮች የአጼውን መንግሥት አርበደበደው።

የወሎ ቦረና ተወላጅ የሆነውና ከአማራው አብራክ የተገኘው ዋለልኝ መኮንን የጆሴፍ ስታሊንን የብሔረ-ሰቦች ጥያቄ በግርድፉ በማንሳት “በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ብሔረሰቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብት እንዲታወቅ” የሚለው ጽሑፉ የተማሪውን ልብ ማረከ። የኤርትራ ተቃዋሚ ኃይሎች እንቅስቃሴ ዕውቅና እንዲያገኝ ጽሑፉ የራሱን አስተዋፅኦ አድርጓል። አልፎም ተርፎም የቀዳማይ ወያነ ታሪክ የለኮሳቸው የትግራይ ተማሪዎች ማህበር ገስገስቲ ብሔረ ትግራይን (ማገብት) ሲመሰርቱ፣ የኦሮሞ ተማሪዎችም ተመሳሳይ መስመር ተከተሉ። በ1960 ዓ.ም መኢሶን በጀርመን ሃምቡርግ ከተቋቋመ በኋላ በ1961 ዓ.ም አውሮፕላን ጠልፎ ከሀገር ከወጣውና በአልጀሪያ ከሚገኘው የኢያሱ አለማየሁና የብርሃነ መስቀል ረዳ ቡድን ጋር ግኑኝነት መሠረተ።

ሆኖም፣ የፖለቲካ ባህላችን በሽኩቻና በጥርጣሬ የተሞላ በመሆኑ ወጣቱንና የተማረውንም ኃይል እንደ አባቶቹ ያለመስማማትና ያለመግባባት ጎርፍ ጭልጥ አድርጎ ወሰደው። መኢሶንና የኢትዮጵያ ህዝቦች አርነት ድርጅት (ኢሕአድ፣ በኋላ ወደ ኢህአፓ ያደገው ቡድን) ተለያይተው ተቋቋሙ። ከጥቂት ዓመታት በኋላም በሚሰቀጥጥ ሁኔታ እርስ በርሳቸው ተበላሉ። የሥራ ማቆም አድማዎችና ሰላማዊ ሰልፎች የአጼውን መንግሥት ማናጋታቸውን ቀጠሉበት። አዲስ የፖለቲካ ባህል ለውጥ በኢትዮጵያ አየር መንፈስ ጀመረ።

የንጉሡ የቅርብ ወዳጅና አማካሪ የሆኑት ተክለሐዋሪያት፣ የፖለቲካው ነፋስ አመጣጥ ስላሰጋቸው ለንጉሡ፡- “እንግዲህ እኛ በቃን፣ አረጀን፣ ሥራውን ለተተኪዎች ለቀን እርስዎና እኔ አበባችንን ብንተክል፣ አትክልታችንን ብንኮተኩት ይሻላል” ብለው ቢነግሯቸውም፣ ከንጉሱ ይሁንታን አላገኙም። ምክር ያልመለሰው መከራ መቀበሉ የማይቀር ነውና ደርግ መከራውን እንዲቀበሉ አደረገ። እንዲህም ሆኖ የህዝቡን ስሜትና የወታደሩን ቅሬታ ያነገበ ወታደራዊ ኮሚቴ (ደርግ) ሰኔ 21፣ ቀን 1966 ዓ.ም ተቋቁሞ ህዝባዊ ትግሉን ነጠቀ። እመቃን አስፋፋ። ራሱን ለዙፋን ያዘጋጀው የደርግ ኃይል ፖለቲካዊ ገመዱን በንጉሡ መንግሥት ላይ እያጠበበና “ያለምንም ደም ኢትዮጵያ ትቅደም፣ በቀና መንፈስ ግን እንከኗ ይውደም” እያለ በመዘመር ዙፋኑን ገዘገዘው። ሌተናል ኮሎኔል ፍስኃ ደስታ እንደገለፀው ሻለቃ ደበላ ዲንሳ የደርጉን ትእዛዝ ለንጉሱ እንደሚከተለው አነበበ፡-

“ምንም እንኳ በኢትዮጵያ ታሪክ ለረጅም ጊዜ የኖረውን ዘውድ ህዝቡ በቅን ልቦና የአንድነት ምልክት ነው ብሎ የሚያምንበት ቢሆንም፣ ከሃምሳ ዓመት በላይ ከአልጋ ወራሽነት ጀምረው ሀገሪቱን ሲመሩ ከህዝብ የተሰጠዎትን ክቡር ሥልጣን አለአግባብ በልዩ ልዩ ዘዴ ለራስዎ እና በአከባቢዎ ለሚገኙት ቤተሰቦችዎና ለግል አሽከሮችዎ ጥቅም በማዋል አሁን ሀገሪቱ ካለችበት ችግር ላይ እንድትወድቅ ከማድረግወ በላይ ዕድሜዎ ከ82 ዓመት በላይ በመሆኑ በአካልም ሆነ በአእምሮ በመድከምዎ ከእንግዲህ ወዲህ ይህን ከፍተኛ ኃላፊነት ሊሸከሙ አይችሉም” ሲል አነበበ።

ንጉሡም በጥሞና ካዳመጡ በኋላ “ለአገር በጎ አስባችሁ ከተነሳችሁ የአገርን ጥቅም ከራስ ጥቅም ማስቀደም አይቻልም። እኛ እስከዛሬ አገራችንና ህዝባችንን አቅማችን በፈቀደውና በምንችለው ሁሉ አገልግለናል። አሁን ተራው የእኛ ነው ካላችሁ ኢትዮጵያን ጠብቁ” ብለውና እንባቸውን ረጭተው ዙፋናቸውን አስረክበው በሰማያዊ ቮልስ መኪና ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ተወሰዱ። በርካታው ወገን በእሳቸው ስም እየማለ እንዳልኖረ፤ “እኔ ያንተ አሽከር! ያንተ ቡችላ! ፀሐዩ ንጉሥ!” እያለ እንዳላጎበደደ፣ “ሌባ! ሌባ!” እያለ በመጨረሻ ሸኛቸው።

የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ባህል እንዲዳብር መንገድ ባለመክፈታቸው መጨረሻቸው እንዲህ ሆኖ ቀረ። ዲፕሎማቱና የፖለቲካ ሰው የነበረው ብርሃኑ ድንቄ እንደሚለው አንድ የአገር መሪ “ዘላቂ ዓላማ፣ የተጣራ ፕሮግራም፣ ታማኝ ደጋፊዎች፣ ጠለቅ ያለ ርዕይ ወይም vision እንዲኖረው ያስፈልጋል። አጼ ኃይለሥላሴ ግን ይህ ሁሉ ስለሌላቸው ከእርሳቸው እድሜ አልፈው በኢትዮጵያ ወደፊት የሚደርሰውን ለማየት አልሞከሩም ማለት ይቻላል” ሲል በቁጭት ገልጿቸዋል።

ተክለሐዋርያትም፤ “አንድ ቀን ስንነጋገር [ጃንሆይ] እንዲህ አሉኝ” ይላሉ። “አንተ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የምትለው፣ ኢትዮጵያ ያለ እኔ ምንም አይደለችም፣ ዕድልዋ ከኔ ጋር የተሳሰረ ነው። እኔ ነኝ የማደርሳት። ካለኔ ትኖራለች ብለህ አታስብ” እንዳሏቸው አባቱ ያጫወቱትን ግርማቸው በፊታውራሪ ተክለሐዋርያት መጽሐፍ መግቢያ ላይ ጠቅሶታል። በመቀጠልም፣ ተክለሐዋርያት በንጉሡ አባባል እንዴት እንደተገረሙና እንደተበሳጩ ገልጾ “እንዴት እንደዚህ ያስባሉ፣ ኢትዮጵያ እኮ ህያው ነች፣ እኛ ሁላችንም ዐላፊዎች ነን። ኢትዮጵያ ግን አታልፍም። እስቲ ይመልከቱ! ዐፄ ምኒልክ ዛሬ የት ናቸው? አባትዎ ራስ መኰንን የት አሉ? ሌሎችስ ታላላቆችና ገናናዎች የነበሩት ሁሉ የት ናቸው? ኢትዮጵያ ግን አለች። ወደፊትም ትኖራለች”፣ እንዳሏቸው ግርማቸው ጽፏል።

የንጉሡ መጨረሻም ተዋርዶ መሞት ብቻ ሆነ። ያሳዝናል። አዎ! የኢትዮጵያ ፖለቲካ በእጅጉ ያሳዝናል። ኢትዮጵያ ግን አለች፣ ብዙ ንጉሦቿ ከማይወጡበት የጠበበ ጉድጓድ ወጥተው ነፍስ ሊዘሩ አልቻሉም። ንጉሦችና ባለጊዜዎች ከጥፋት የሚደርሱት በከንቱ ውዳሴና በከንቱ ትምክህት ነው። ጃንሆይ መታበያቸው ይዞአቸው ገደል ወረደ። ጃንሆይ ገለባ ሁነው የደርጉን እሳት ጠበቁ። አፄ እስክንድር “ገለባ ሁነህ እሳትን ቆየው” (ጽንሖ ለእሳት ከዊንከ ብርዓ) ያለውም በእሳቸው ስህተት ተፈፀመ።

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top