ጣዕሞት

‹‹የፑሽኪን አያትና የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት አዛምዶናል›› (አሌክሲ መሉይኮቭ)

‹‹የአሌክሳንደር ፑሽኪን አያትና የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት በኢትዮጵያና በሩሲያ መካከል በተለይ የሚያስተሳስሩን ማኅበራዊ ኹነቶች ናቸው›› ሲል ፒያኖ ተጫዋቹ ሩሲያዊ አሌክሲ መሉይኮቭ ለዘጋቢያችን ተናግሯል።

የሩሲያ ኤምባሲ ‹‹ብሄራዊ የአንድነት ቀን››ን በማስመልከትና የአዲስ አበባና የሴንት ፒተርስበርግ ከተሞችን እህትማማችነት ምክንያት በማድረግ የሩሲያ የሳይንስና ባህል ማዕከል (ፑሽኪን አዳራሽ) ከሩሲያ በመጡ ወጣት ሙዚቀኞች ኮንሰርት ባቀረበበት ወቅት ነው ይህን የተናገረው።

የ27 ዓመቱ ፒያኖ ተጫዋች አሌክሲ መሉይኮቭና የ25 ዓመቱ ሳክስፎን ተጫዋች ቭላድሚር ህስታይንዘር የተለያዩ የምዕራባውያን ሙዚቃ አቀናባሪዎች የፃፏቸውን ዘመናዊና ክላሲካል ሙዚቃዎች ተጫውተዋል። ፒያኖ ተጫዋቹ አሌክሲ ለታዛ መጽሔት  ዘጋቢ ሲገልጽ፣ ‹‹ወደ አፍሪካ ስመጣ ይሄ የመጀመሪያዬ ነው። ከአሌክሳንደር ፑሽኪን በስተቀር የሩሲያ ደራሲያን በኢትዮጵያ ውስጥ ጎልተው መታወቃቸውን አላውቅም ነበር። ለካስ ብዙ ደራሲዎቻችን እዚህ ይታወቃሉ›› ብሏል። ‹‹እኛ ሩሲያውያን የደራሲዎቻችን፣ የሙዚቀኞቻችን፣ የሠዓሊዎቻችን በአጠቃላይ የሥነጥበብና የባህል አምባሳደሮቻችን ሥራቸውና ግለታሪካቸው በትምህርት ካሪኩለማችን ውስጥ ስለሚካተት ከልጅነታችን ጀምሮ ጠንቅቀን እናውቃቸዋለን። የፑሽኪንን፣ የቶልስቶይን፣ የዶስቶዮቭስኪን፣ የጎርኪን፣ የጎጎልን፣ የሌርሞንቶቭን፣ የአንቷን ቼሆቭን ወዘተ. ሥራዎች ገና በልጅነት ነው የምናነበው›› ብሏል። ‹‹የታዋቂው ሩሲያዊ ባለቅኔ የፑሽኪን አያትና የኦርቶዶክስ ክርስትና ሩሲያን እና ኢትዮጵያን በደንብ የሚያስተሳስሩ ኹነቶች ናቸው። ፑሽኪንና ኦርቶዶክስ ክርስትና በተለይ አዛምደውናል›› ብሏል ፒያኖ ተጫዋቹ አሌክሲ።

 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top