በላ ልበልሃ

የተማሪው ትግልና የአብዮቱ ደመና

የ ፖለቲካ ባህላችን ተቃርኖ መንተክተክን አላቆመም። የፖለቲካ ሥርዓቱ በተለወጠ ቁጥር እስካሁን ዘልቆ የመጣው የፖለቲካ ባህል የዓይነት ለውጥ ፈጽሞ አላሳየም። በ1960ዎቹ የታየው የተማሪዎች እንቅስቃሴና የደርግ ዘመኑ ፖለቲካዊ ባህላችን በቅርበት ሊተኮርበት የሚገባው ነው። ቀደም ሲል በታዩት ሥርዓተ-መንግሥታት የፖለቲካ ባህላችን መቻቻል የሌለበት ጥንታዊ (parochial) እንደነበር በዝርዝር ተመልክተነዋል። አሁን ደግሞ በ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የነበረው የፖለቲካ ባህላችን ውስጣዊ ተቃርኖ ምን ይመስላል? የሚለውን ማየት ተገቢ ይሆናል።

ፈላስፋው ፍሬድሪክ ሄግል በህይወት ዘመኑ የታዘበውን ሲገልጽ “ታሪክ የሚያስተምረን ነገር ቢኖር አገራትም ሆኑ መንግሥታት ከታሪክ ምንም ነገር አለመማራቸውን ነው” ብሎ ነበር። “ኢትዮጵያውያን ነን” ብለን የምናስብ ወገኖችም ይህ አባባል አእምሮአችንን ሊያናውጠው ይገባል ባይ ነኝ። ሀገራችንም ሆነ የተመለከትናቸው መንግሥታት ካሳለፉት ታሪክ የማይማሩ ከሆነ የሀገርና የመንግሥት ውድቀት ሥር የሰደደ ይሆናል።

በሀገራችን የቆየ ልማድ አለ። አንድ መንግሥት ሲወድቅና ሌላው ሲተካ የፖለቲካ ባህሉን ለውጥ መመዘን ያለና የተለመደ ይመስለኛል። ይህን ለማድረግ ደግሞ ከመጽሐፍ ማንበብ ብቻ ሳይሆን የዓይን ምስክር መሆን የበለጠ ጠቃሚነት አለው። የ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴና ከዚያም በኋላ የህዝባዊውን አብዮት የነጠቀውን የደርግ ኃይል በዕድሜ ልምዳችን የምናውቃቸው በመሆኑ የተሻለ ግምገማ እንደሚኖረን እርግጠኛ ነኝ።

እንግዲህ ያሳለፍነውን እውነታ በአግባቡ የምንመዝን ከሆነ ፈሪሳውያንን አንሆንም። የተማሪው እንቅስቃሴ በአብዛኛው በውጫዊ ኃይል የተገፋ እንቅስቃሴ ነበር። በተቻለ መጠን አብዮታዊነትን ታጥቆ የተነሳ ኃይል ሆነ። በበርናንድ ሾው አገላለፅ “አብዮቶችና አብዮታውያን የጭካኔን ሸክም አቃለው አያውቁም፤ ግን ወደ ሌላው ትከሻ ያዛውሩታል” ያለውን እዚህ ላይ ማስታወስ ይገባል።

ቀደምቶቹ የኢትዮጵያ የለውጥ ሐዋሪያት የሀገሪቱ የፖለቲካ ባሕል እንዲለወጥ የተቻላቸውን ለማድረግ ጥረዋል። እነ ፊታውራሪ ተክለሃዋሪያት፣ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ ታከለ ወ/ሃዋሪያት፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ፣ አፈወርቅ ገብረየሱስ፣ አጽመ ጊዮርጊስ፣ ሀዲስ ዓለማየሁ ወዘተ. ዋናዎቹ የለውጥ ሐዋሪያት በመሆን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ባህላዊ አድማስ እንዲሰፋ ጥረዋል።

ከዚህ በኋላ በእነ ጄነራል መንግሥቱ ነዋይ የተካሄደው የለውጥ አመጽ የወጣቱን ትውልድ አመለካከት በእጅጉ ቀይሮታል። የሥርዓቱ ቁንጮ ባለ ሥልጣን የነበሩት ጄኔራል አቢይ አበበ ሳይቀሩ “አውቀን እንታረም” በሚለው መጽሐፋቸው “ዋይ፣ ዋይ ከማለት በፊት መወያየት ቢቀድም ብዙ ክፉ ነገሮች አይደርሱም፣ እርስ በርስም መግባባት ከኖረ በህብረት ለመሥራት አያዳግትም። … እስካሁን እየተራመድንም፣ እየዘለልንም አልፈን ይሆናል፤ አሁን ግን መሸጋገሪያ ድልድያችንን አጥብቀን መገንባት አለብን” በማለት አስጠንቅቀዋል፣ መክረዋል። ግን ምክሩ ሁሉ በገዢዎች ዘንድ ተደማጭ ባይሆንም ለተማሪው ግን የአዲስ አመለካከት አድማሱን አስፍቶለታል።

በ1960ዎቹ በኢንዶኔዥያ፣ በቬንዝዌላ፣ በጃፓንና በደቡብ ኮሪያ የተማሪዎች እንቅስቃሴ በመፋፋሙ በተጠቀሱት አገራት የመንግሥት ለውጥ ሊመጣ ችሏል። የግብፅ ተማሪዎች የእንግሊዝ ኮሎኒያሊስቶችን በመዋጋት ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍለዋል። በግብፅ በ1952 እ.ኤ.አ. ለተካሄደውና ናስርንና ጓዶቹን ለሥልጣን ላበቃው አብዮት ዋነኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ነበሩ- ተማሪዎች። የግብፁ እንቅስቃሴ ለሌሎች የአፍሪካ ተማሪዎች ሁነኛ መንደርደሪያ ሆኖ እንደነበር ማስታወስ ይቻላል። የአፍሪካ ተማሪዎች በመጀመሪያው ትግላቸው መነሻ ያደረጉት ፖለቲካዊ ትግሉን ሳይሆን ማህበራዊና ባሕላዊ ትግሎችን ነበር። በተለይ በፍራንኮፎንና በማግረብ አገራት የነበረው ትግል ፀረ- ኮሎኒያሊዝም ከመሆኑም በላይ ከፈረንሳይ ኮሙኒስት ፓርቲ ሙሉ ድጋፍ ያገኙ እንደነበር የእነ አልጀሪያና የሌሎች የምዕራብ አፍሪካ አገራት ታሪኮች ይመሰክራሉ።

በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ሥር የነበሩት የአፍሪካ ሀገራትም የተማሪዎች እንቅስቃሴ በናይጄሪያ፣ በጋምቢያ፣ በጋና (በጎልድ ኮስት)፣ በሴራሊዮን ተፋፍሞ ቀጥሎ ነበር። ባህሩ ዘውዴ እንደሚለው የተማሪዎቹ እንቅስቃሴ ሁለት መልክ ነበረው፤ ርዕዮተ-ዓለማዊና ብሔርተኛነት። በአብዛኛው ሁኔታ ግን ግራ-ቀደም እንደነበር ባህሩ ጽፏል። ይህም ሁለት መንታ አመለካከት መያዝ የውጭ አገር ተማሪዎችን ትግል በተምሳሌትነታቸው እንዲከተሉ አድርጎታል። በተለይም የኩባ፣ የቪዬትናም ተማሪዎች ትግል በወቅቱ የብዙ አፍሪካ ሀገራትን ተማሪዎች ቀልብ የሳበ እንደነበር አይካድም። በአብዮታዊነቱ በተማሪዎች ዘንድ ዋነኛ ተምሳሌት የነበረው ቼ ጉቬራ በየትግል መድረኩ ዋነኛ ቀልብ ሳቢ ነበር። ኖኦም ቾምስኪ ማህበረሰባችን በእጅጉ የሚሻውን ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚችለው የተደራጀ፣ ዕውነተኛና ተነሳሽነት ያለው የተማሪዎች እንቅስቃሴ መሆኑን በእርግጠኝነት ጽፎ ነበር። በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ይህ ሲተገበር አልታየም።

የዓለም አቀፍ ተማሪዎች እንቅስቃሴ መጋምና በሀገር ውስጥ በ1953 ዓ.ም የተካሄደው በጄኔራል መንግስቱ ነዋይ የተመራው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ጭንቅላት ውስጥ አንድ ጥያቄ አጫረ። ይህም ጥያቄ ለካስ “ፀሐዩን ንጉሥ” ከሥልጣን ማፈናጠር ይቻላል የሚለውን አንድምታ አሳደረ። ለዚህም ነው በ1960ዎቹ መጨረሻ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጆች የየራሳቸውን የተማሪዎች ማህበር ለማቋቋም የበቁት። ከማህበራቱ መssም ጎን ለጎን ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የከፍተኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመከታተል የመጡ ተማሪዎች የፖለቲካ ልምድም ለኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ መበልፀግ አስተዋፅኦ አድርጓል።

ቀስ በቀስም የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ማህበር አመራር “አዞዎቹ” (ክሮኮዳይልስ) ተብለው በሚታወቁ ግራ-ቀደም ተማሪዎች እጅ ወደቀ። እነዚህ አዞዎችም “ተሰዓቱ ቅዱሳን” (ዘጠኙ ቅዱሳን) ተብለው የሚታወቁ ናቸው። በኋላም አብዛኞቹ የኢህአፓ መሪዎች ሊሆኑ ችለዋል። እነሱም ብርሃነ መስቀል ረዳ፣ ዘርኡ ክሕሸን፣ ገብሩ ገብረወልድ፣ ኃይሉ ገብረዮሐንስ፣ ታዬ ጉርሙ፣ ስዩም ወልደ ዮሐንስ፣ ዮሐንስ ስብሃቱ፣ ሚካኤል አበበና ሃብተጊዮርጊስ ሙላት ነበሩ። እነዚህ ግራ-ቀደሞች ፀረ-አሜሪካ እንቅስቃሴና መሬት ላራሹ የሚለውን መፈክር በማንገብ በ“ኒውስ ኤንድ ቪውስ” ጋዜጣ አስተሳሰባቸውን አንፀባርቀዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ ከሀገሪቱ ፖለቲካዊ ተፈጥሮ ተቃራኒ የሆነን የማርክሳዊ-ሌኒናዊ ርዕዮትን በማሰራጨት ረገድ ቀዳሚዎችም ነበሩ። የአውሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማህበር ልሳን የሆነውም “ታጠቅ” እጅግ የሚዋጉ ቃላትን በመጠቀም የሀገር ውስጡን የተማሪ እንቅስቃሴ ማጋጋሉ ይታወቃል። ለምሳሌ በሃምሌ 1961 ዓ.ም የወጣው ታጠቅ “በፊውዳሊዝም እና በኢምፔሪያሊዝም መቃብር ላይ የሁላችን የሆነች ህዝባዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት ኢትዮጵያውያን የሆንን ሁሉ እፍኝ ከማይሞሉት ጨቋኞችና ደጋፊዎቻቸው በቀር በአንድ የትግል ግምባር ውስጥ ተሰብስበንና ተደራጅተን በአንድነት መራመድ አለብን” ሲል ጥሪ አስተላልፏል። ከዚህ በኋላ የነበረው ቋንቋ፡-

“መሬት፣ መሬት፣ መሬት ላራሹ፣ ተዋጉለት አትሽሹ።” ሆነ።

የተማሪዎች ማህበር በታገል መፅሔቱ የሚያወጣቸው አብዮታዊና ተዋጊ ፅሑፎቹ እየበረከቱ ሄዱ። ዋለልኝ መኮንን ማኒፌስቶ በሚባለው ዶክመንቱ የጆሴፍ ስታሊንን “የብሔሮች ጥያቄ” በማንሳት የብሔር እንቅስቃሴዎች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን እስከመገንጠል ድረስ ያላቸውን መብት ማወቅ ያስፈልጋል ሲል ሶሻሊስታዊውን የህብረተ-ሰብ መብቶች የመፍቻ መንገድ አስነበበ። ይህም ጽሑፍ የትግራይን፣ የኦሮሞንና የኤርትራን ወጣቶች ቀልብ በእጅጉ መሳቡ አልቀረም። አልፎ ተርፎም በየፊናቸው የፖለቲካ ማህበር እንዲያቋቁሙ ገፋፋቸው።

ከዚህ ጊዜ በኋላ የኢትዮጵያ ተማሪዎች እየተቧደኑ የግል ጎጇቸውን ለመቀለስ ተፍ፣ ተፍ አሉ። በጋራ ጉዳዮች ከመነጋገር ይልቅ ፖለቲካዊ ቡድንተኝነትን ተከተሉ፤ ጽንፈኝነት ይበልጥ ሥር ሰደደ። በዚህም የተነሳ አንዳንድ ጥናቶች (ለምሳሌ የሹመት ሲሻኝ) እንደሚጠቁሙት ዋለልኝ የጀብሃ የፖለቲካ ፍላጎት አስፈፃሚና ልሳን ነበር እስከማለት የደረሱ ወገኖች አሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት የነበረው ጥላሁን ግዛው በክብር ዘበኛ ጦር አንጋች ኃይል ተገደለ። ሌ/ ኰሎኔል ፍስሐ ደስታ ስለዚሁ ጉዳይ ሲነግረን “ስለ ጥላሁን ግድያ የተለያዩ ነገሮች ቢወሩም … ሐቁ ግን ግድያው የተፈፀመው በንጉሠ-ነገሥቱ የክብር ዘበኛ፣ የንጉሱ የቅርብ አጃቢ ወይም አንጋች ክፍል ምክትል አዛዥ በነበሩት በኰሎኔል ጣሰው ሞጃ ትዕዛዝና ከብሔራዊ ጦር ተዛውረው እኔው ራሴ ደብረ-ብርሃን ካሰለጠንኳቸው በኋላ የአንጋች ክፍል ባልደረባ በሆኑት ሁለት ወታደሮች ነበር። ለዚሁ ድርጊታቸውም ሁለቱም የምክትል መቶ እልቅና ማዕረግ የተሰጣቸው መሆኑን የድርጊቱ ፈፃሚዎች ነግረውኛል” ብሏል።

ይህ የሚያመለክተው የአጼው መንግሥት ከፖለቲካዊ መቻቻል ይልቅ እመቃ የማያዳግም ፖለቲካዊ መፍትሔ ይሰጣል ብሎ ማመኑንና ከስህተቱ አለመማሩን ነው። እውነታው ግን የተገላቢጦሽ ሆነ። ትግሉ በተማሪዎች ዘንድ ብቻ ሳይሆን ገዢዎች ወደ ሚተማመኑበት ወታደርም ክፍል ተዛመተ። አመፃው የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን እንደ ሰደድ እሳት እያዳረሰ ተጓዘ።

“ጥላሁን፣ ለምን ለምን ሞተ?

ማርታ፣ ለምን ለምን ሞተች?

ገርማሜ፣ ለምን ለምን ሞተ?

ታከለ፣ ለምን ለምን ሞተ?

በኃይል በትግል ነው፣

ነፃነት የሚገኘው”

የሚሉ መዝሙሮች ሀገሪቱን አናወጧት። ኃይል፣ ትግል፣ ደም ማፍሰስ የሚሉ ቃላት በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር ተንሰራፉ። በእያንዳንዱ ለውጥ ፈላጊ ጆሮ ላይ አንሾካሾኩ። ሆኖም መሠረታዊ ችግሮቹ ተባባሱ እንጂ እልባት አላገኙም። የፖለቲካ ምህዳሩ አሣታፊ ባለመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሊፈጠሩ አልቻሉም። ሥራ አጥነት፣ ረሃብ፣ በንጉሡ አገዛዝ እርካታ ማጣት ተንሰራፋ። በዚያው ልክ መኳንንትና መሳፍንቱ ሀገሪቱን በቀድሞው መልክ ለመግዛት ሙጭጭ በማለታቸው በፖለቲካው ምህዳሩ ውስጥ አፍራሽ ሚና ተጫወቱ።

በየካቲት 66 የግፍ ፅዋው ሲሞላ የፖለቲካ ውጥረቱን ለማስታገስ ሲባል የፀሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ካቢኔ ከፖለቲካ መድረኩ ተሰናበተ። የልጅ እንዳልካቸው በምትካቸው ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የመሳፍንቱን ወገን ያስደሰተ ቢሆንም፣ በግራ ዘመም ተማሪዎችና ምሁራን ዘንድ ግን ተቀባይነት አልነበረውም። የመንግሥት ለውጥ የተደረገ ቢመስልም፣ የፖለቲካ ሥፍራውን ለክርክር፣ ለአዲስ ሃሳብ ሥፍራ ከመስጠት ይልቅ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማህበር በሕገ ወጥ ድርጅትነት ተፈርጆ ማህበሩ እንዲሰረዝ ተደረገ። የተለያዩ ሰላማዊ ሰልፎች፣ የሥራ ማቆም አድማዎች እየተጠናከሩ የመንግሥቱን መዋቅር አንገጫገጩት። ካህናትና ዲያቆናት ሳይቀሩ የጡረታ መብታቸው እንዲጠበቅላቸው በመጠየቅ ሰልፍ ወጡ ይለናል ኰሎኔል ፍስሐ ደስታ። እኔ እንኳ በተማሪነቴ ዘመን እንደማስታውሰው በጂማው ሁሴን እስማዔል አመራር የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ የአካባቢ ሥልጣንን ወደ መቀማት ሄዶ የጅማ ከተማን እስከ ማስተዳደር ደርሶ ነበር።

የፖለቲካውን መንተክተክ ተከትሎ በተማሪዎችና በምሁራን ዘንድ በርካታ ኅቡዕ የጥናት ህዋሶች ተደራጁ። ወደ ፓርቲነት ለመሸጋገርም መድረክ መፍጠራቸውን ቀጠሉ። ሆኖም የወቅቱ የፖለቲካ ባሕል በፈጠረው መሰናክል የተነሳ የታሰበው ሊሆን አልቻለም። በእንቅስቃሴው ውስጥ ተሳታፊ የነበረው ገብሩ አሥራት “ድብቅነት፣ ተንኮለኝነት፣ ምቀኝነትና ማንአኽሎኝነትን የሚቃወምን በጠላትነት መፈረጅ፣ የተለየ ሃሳብን ያለመቀበል፣ ተቻችሎ አለመኖር ወዘተ. የፖለቲካ ቡድኖቹና የጥናት ህዋሶቹ ወደ ፖለቲካ ድርጅት ሲሸጋገሩም አልተለዩአቸውም ነበር” ሲል የዚያን ዘመን ፖለቲካዊ ተቃርኖ በቁጭት ያስታውሳል።

የሞልዬርን አባባል እዚሁ ላይ ልጠቀምና ጽሑፌን ልቋጭ። ሞልዬር እንዲህ ይላል፡- “በእርግጠኝነት ልንገራችሁ፣ ካልተማረ ሞኝ ይልቅ የተማረው ሞኝ ይበልጥ ሞኝ ነው።”

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top