ጥበብ በታሪክ ገፅ

የሥነ-ጽሑፍ አሐዛቢው

ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ተርጓሚ፣ ሐያሲ እና ትጉህ የሥነ-ጽሑፍ ተመራማሪ ናቸው- አስፋው ዳምጤ። በዚህ የተነሳም የሒስ ተግባራቸው በአንባቢያንና በኪነጥበብ ባለሟሎች ዘንድ ጎልቶ ይታያል። ዘመነኛቸው ደራሲ ስብሐት ለአብ ገብረ እግዚሓብኤር በአንድ ወቅት ‹‹አስፋው! እርግጥ አጭር ልቦለድ፣ ግጥም፣ መጻፍ ያምርሃል፤ ትፈልጋለህ። ጻፍክ። ጥሩ ነው። ግን በዚህ በኩል አስር ሰው አለ- ጥሩ የሆነ ነገር ሊጽፍ የሚችል። የአንተ ቢጎድል እነርሱ ያሟሉታል። ስለዚህ፣ እዚህ ላይ ብዙ ጊዜ ከምታጠፋ ዋናውን ጉልበትህን ሥነ-ጽሑፍን ማሳወቁና ሒስ ላይ ብትሰራ በዚህ ዘርፍ ከአንተ እኩል ሊሰራ የሚችል ያለ አይመስለኝም፤ ይሄን የሚተካው የለም። እንግዲህ መስዋዕትነት ትከፍል!? እነዚህን ተወት አድርጎ ሒስ ላይ የማተኮርና መጻሕፍትንና ደራሲዎቹን ማስተዋወቅ ላይ መትጋት። አየህ፣ በደራሲነትህ አንድ ሰው ነህ- አንድ ደራሲ ወይም አንድ ገጣሚ። በሐያሲነትህ ግን፣ በሥነ-ጽሑፍ አስተዋዋቂነትህ ግን ብዙ- ብዙ ሰው ነህ። በርከት ያሉትን የነገ ደራሲያንና ገጣሚያንን ታፈራለህና፤ እባክህ እየፃፍክም ቢሆን በሐያሲነት በርትተህ ትጋ።›› ሲል የመከራቸው ዘወትር በአዕምሯቸው እንደሚያቃጭል ይገልፃሉ። እናም ስብሐት እንዳለው በሐያሲነቱና በ‹‹ጥበበ-ቃላት›› አስተዋዋቂነቱ በረቱ። ይሄን ብርታት ተከትሎ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-ጽሑፍ መምህር የሆኑት ገጣሚ ፈቃደ አዘዘ (ዶ/ር) አስፋው ዳምጤን ‹‹የሥነ-ጽሑፍ አሐዛቢ›› በሚል ይጠሯቸዋል። እኚህ ጎምቱ የሥነ-ጽሑፍ (እርሳቸው የሚሉት ‹‹ጥበበ ቃላት›› ነው) ሰው፤ በአሁኑ ወቅት ሰማኒያ ሁለት ዓመት ተኩል እንደሆናቸው ለዚህ ቃለ-መጠይቅ ባለሟል ጌታቸው ወርቁ ሹክ ብለውታል። እነሆ የሥነ-ጽሑፍ አሐዛቢው ‹‹መልካም ንባብ›› ይሉዎታል!

ታዛ፡- ጋሽ አስፋው፣ በአሁኑ ጊዜ ምን እየሰሩ ነው?

አስፋው ዳምጤ፡- አነባለሁ፣ እጽፋለሁ፣ እተረጉማለሁ፣ በዋናነት እሔሳለሁ። እርግጥ እኔ በብዛት የምፈልጋቸው ሥራዎች እንደ ‹‹ጥበበ ቃላት›› (ሥነ-ጽሑፍ) ዓይነት የምናብ ውጤት የሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን ነው። ነገር ግን በርከት ያሉ በሙያና በእውቀት ዘርፎች በኢ-ልቦለድ መልክ ብዙ- ብዙ መጻሕፍት እየወጡ ነው። እነዚህም መነበብ አለባቸው ባይ ነኝ።

ታዛ፡- ዶ/ር ፈቃደ አዘዘ፣ አስፋው ዳምጤ ‹‹የሥነ-ጽሑፍ አሐዛቢ›› ይሉዎታል፤ ምን ማለታቸው ይሆን? በመሠረቱ ሒስ ማለትስ ምንድን ነው?

አስፋው ዳምጤ፡- ይሄን ጥያቄ መቼም በትክክል የሚመልሰው ራሱ ዶ/ር ፈቃደ ነው። እኔ የምረዳው ግን፣ የምሰራቸውን ሥራዎች በማየት ማለትም ስለአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ ዋና-ዋና የፈጠራ ሥራዎች እና ስለ ይዘታቸውም፣ ስለ ቅርፃቸውም ለአንባቢያን በማስተዋወቅ፣ እግረ መንገዱን ደራሲዎቻቸውንም ከነሥራዎቻቸው አብረው እንዲታወቁ የመሞከርና የአማርኛ የፈጠራ ድርሰቶችን በአጠቃላይም በተለያዩ የእውቀት ዘርፍ የተጻፉትንም ፊደል የቆጠረው፣ ተማረ የሚባለው ወደ ንባብ እንዲሳብ፣ የንባብ ባህልን ለማዳበር እንዲያግዝ የማደርገውን ሙከራ በማየት ‹‹አሐዛቢ›› ሲል፣ የግዕዙን ቃል ወስዶ የአማርኛ ቅጽል እንዳረገው በመቁጠር አስተዋዋቂ፣ ሥነ-ጽሑፍን ከህዝብ ጋር አገናኚ፣ ህዝብ እነዚህን ነገሮች እያነበበ ገንዘቡ እንዲያደርግ በሒስ መንገድ የሚጣጣር ለማለት ነው።

በመሠረቱ ሒስ ማለትስ ምንድን ነው ላልከው፣ በሒስ ሥራ አጽንዖት የሚደረግበት ሥራዎቹን ብጥስጥሳቸውን እያወጡ ይሄ አይመጥንም፣ እዚህ አይደርስም የሚል ፍርድ የመስጠት አካሄድ አይመስለኝም። አሁን አንዳንድ ሰዎች ‹‹አንተ ደራሲዎቹንና ሥራዎቻቸውን አዎንታዊ ጎኑን ብቻ እየገለጽክ፣ ደካማ ጎናቸው ላይ ብዙ አትልም የሚል ነው። ይሄ አስተሳሰብ ሒስን አቃቂር ማውጣት ነው ብሎ የሚያምን መንፈስ ዝንባሌ ነው ባይ ነኝ። የኔ ዓላማ ግን መጀመሪያ እስቲ ደህና አድርገን አዎንታዊ የሆነ ጎናቸውን እንወቀው። እሱን ካወቅን በኋላ አጠቃላይ ዕትሙን ስናይ፣ አይ እዚህ ጋር እኮ ይቺ ትንሽ እንዲህ ሆናለች ለማለት ያስችለናል የሚል መንፈስ ነው። ምክንያቱም መጀመሪያ አንባቢ ፈልጎ እንዲያነባቸው የሚገፋ ነገር መቼ ተሰራና ነው!? መጀመሪያ ይሄንን እናድርግ፣ ከዚያ በኋላ ብርቱ አንባቢ ሲፈጠር ብርቱ ሐያሲም ከዛ መሐል ነው የሚወጣው፤ የሚወለደው።

እኔ አሁን በትምህርት ተቋማት አንደኛ ነጥብ ይሄ፣ ሁለተኛ ነጥብ ይሄ እያሉ ጥበበ-

“ይሄ አስተሳሰብ ሒስን አቃቂር ማውጣት ነው ብሎ
የሚያምን መንፈስ ዝንባሌ ነው ባይ ነኝ”

ቃላትን በሕግ ዓይነት መሔስ አይሰራም ባይ ነኝ። አሁን በተቋማት ደረጃ ሂስ በሚሰጥበት ጊዜ የዘመናችን ሒስ ትልቁ ችግር ቀጥታ እንደተለመደው የፈረንጆቹን አምጥተን፣ በዛው መልክ የእኛን ማየት ስንጀምር ነው። በመጀመሪያ ደረጃ እያንዳንዱ ሥነ-ጽሑፍ፣ እያንዳንዱ የጥበብ ሥራ በዛ ሥነ-ጽሑፍ ውስጥ ትኩረቱ የራሱ ማኅበረሰብ ነው። በትክክል የተሰሩ የጥበበ-ቃላት ሥራዎች እንደ መስታወት ለማሳየት የሚሞክሩት የራሳቸውን ኅብረተሰብ ጠንካራና ደካማ ጎን፣ አስቀያሚና ውብ የሆነ ገጽታ ነው። እና ይሄንን ከኅብረተሰቡ ጋር (ኅብረተሰቡ ስንል ባህሉን፣ ዕምነቱን፣ ሥነ-ልቦናውን፣ ሀሴቱን ሁሉ ይዞ ነው) እንጂ የሌላውን ኅብረተሰብ በታሪክ አካሄዱና አሁን የደረሰበት ደረጃ የመጣበት መንገድ ከኛ ፍጹም የተለየውን ያንን ወደዚህ ለማምጣት አይቻልም።

ይሄን ስል ግን ከግንዛቤ መክተት ያለብን፣ የሰው ልጅ መሠረታዊ በሆነ የሰብዕና አፈጣጠር አንድ የሚያደርገው የተፈጥሮ ሂደት መኖሩን ነው። በትርጉም የሌላውን ሥራ ስታነብ የሚስብህና የሚኮረኩርህ እነዚያ የጋራ ኹነቶች ስላሉ ነው። እነዚህን የጋራ ኹነቶች እንውሰድ እንጂ፣ ጭራሽ ወካይ ጽንሰ-ሃሳቦችን የማያቅፍ ነገር አንውሰድ። በእውቀት እናድርገው ነው ትልቁ ነጥብ።

ታዛ፡- ‹‹አንዳንድ ነጥቦች ስለ አማርኛ ‹ጥበበ ቃላት››› በሚል በተለያዩ መጽሔቶችና ጋዜጦች ላይ ሒስ ይጽፉ ነበር። እነዚህ በሳል ሥራዎች ተሰባስበው ለምን በመጽሐፍ መልክ ታትመው ለመቅረብ አልቻሉም?

አስፋው ዳምጤ፡- አንድ አሳታሚ ድርጅት ሊያሳትመው ተነጋግረን ነበር። ነገር ግን ባለቤቶቹ በገጠማቸው የግል ጉዳይ እስካሁን አልታተመም። ያም ሆነ ይህ ግን እኔ የማስበው እርሱን ሰብስቤ ማሳተሙ ለምን? እኔ አሁን ብዙዎቹን መጣጥፎች ደግሜ ሳነባቸው አንደኛ ያን ጊዜ በመጽሔት ዓምድ የገጽ ፍጆታ የተፃፉ ናቸው። ሁለተኛ የዛን ጊዜ የነበሩኝ መረጃዎች በአጠቃላይ ስለ አነሳኋቸው ነጥቦችም ጭምር አሁን ካለኝ መረጃ አነስ ያለ ነበርና በሂደት ብዙ መረጃና በአንዳንድ አቅጣጫም የአተያይ ክለሳ የማደርግበት ሁኔታ ስላጋጠመኝ መቆየቱ ካልቀረ ዘንዳ አሁን ባልኩት መሠረት ለዚህ መጽሔት ወይም ለዛኛው መጽሔት እያልኩ በነርሱ ልኬት መሠረት የሰራሁትን ትቼ ከስር ጀምሬ አንድ ወጥ አድርጌ አስተካክዬ ለምን አልጽፈውም በሚል ነው።

ታዛ፡- እርስዎ ‹‹ሥነ-ጽሑፍ›› በሚለው የቃል መግለጫ አይስማሙም። ይልቁኑ ‹‹ጥበበ ቃላት›› ነው የሚሉት። አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ‹‹ሥነ-ጽሑፍ›› የሚለውን ሐረግ በአቻነት ይጠቀማሉ። ለዚህ የሃሳብ ሙግት መነሻው ምንድን ነው?

አስፋው ዳምጤ፡- በአንድ መጣጥፌ ‹‹ጥበበ ቃላት›› ስለሚለው የጻፍኳት ነገር አለች። ጥበበ ቃላትን ደግሞ ምን አመጣው የሚሉ ቢኖሩ አያስገርምም ብዬ ስለዛ ለማስረዳት ሞክሬ ነበር። እኔ እስከማስታውሰው ድረስ ሁለቱም (ሥነ- ጽሑፍ እና ጥበበ-ቃላት) በተተካኪ እንደ እኩል የሚያገለግሉበት ጊዜ ነበር። በኋላ ሥነ-ጽሑፍ የሚለው በአብዛኛው በጋዜጦች ተደጋግሞ ጥቅም ላይ በመዋሉ ነው ጎልቶ የወጣው የሚል ነጥብ አለበት። አሁን በትክክል የማውቀው ጥበበ ቃላት የሚለውን መጀመሪ የሰማሁት ከመንግስቱ ለማ ነው። የካቲት (ቀኑ ተረሳኝ) ወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማኅበር (ወወክማ) በሚባለው እንደ ትልቅ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም፣ ንግግር የሚያደርጉ ሰዎች በየሙያውና በየዘርፉ ይጋበዙ ነበር። መቼም ህዝብ ይጎርፋል፣ ያዳምጣል፣ ይጠይቃል። የሚገርመው እኔ ኮከበ-ጽባህ ት/ቤት ተማሪ ሆኜ አሥራ አንደኛ ክፍል ነበርኩ። ከት/ቤት ከቀበና 11፡00 ሰዓት ላይ ስንለቀቅ፣ እዛ እየገባን የምሁራንን ንግግር እናደምጥ ነበር። በኋላ እንደውም የፕሮግራሙ ደንበኛ ሆንኩ።

መንግስቱ ለማ ንግግር ያደረገ ዓመት እኔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የአንደኛ ዓመት (‹‹ፍሬሽ››) ተማሪ ነበርኩ። ያን ጊዜ መንግስቱ ለማ እንግሊዝ አገር ሰባት ዓመት ቆይቶ የመጣ ‹‹ሌጀንድ›› ነበር። በዚያ ጊዜ በህዝባዊ ንግግር ላይ ‹‹ጥበበ- ቃላት› ልንለው እንችላለን›› ብሎ ሲያብራራ አድምጬዋለሁ። አስታውሳለሁ ‹‹እንግሊዞች- ‹ሊትሬቸር›፣ ፈረንሳዮች- ‹ሊተራቲዩ› የሚሉትን እኛም ግጥምን፣ አጭር ልቦለድን፣ ረጅም ልቦለድና የመሳሰሉትን በመደበኛነት ‹‹ጥበበ-ቃላት›› ልንለው እንችላለን ብሎ ሲናገር ያኔ ያቺን ቀለብ አደረግኩ። ሲያስረዳ ደግሞ እጅግ ይችልበታል፤ ፈታ አድርጎ መግለጽ ይችልበታል። ያኔ ምናልባት ሲቪል አቪዬሽን ሠራተኛ ሆኖ በወወክማ ተጋባዥ ንግግር አድራጊ ሆኖ ቀርቦ ነው። ያኔ ሰዉ ዘመናዊ እውቀት ለመገብየት እጅግ ይሻ ነበርና አዳራሹ ሙሉ ነበር።

በለጠቀው ዓመት ደግሞ ‹‹መስከረም›› የሚባል የአጫጭር ልቦለዶች ታሪክ ታደሰ ሊበን ያሳትማል። መግቢያው ውስጥ ‹‹በዓለም ጥበበ-ቃላት አጫጭር ልቦለድ ታሪኮች ሁነኛ የሆነ ቦታ ያላቸው ናቸው እንጂ የአንድ ትልቅ ረጅም ልቦለድ ምናምን ብጣቂ ወይም ኩርማን አይደሉም። ረጅም ልቦለድ እና አጭር ልቦለድን በእንጀራ እና በእንጎቻ ልንመስላቸው እንችላለን። እንጎቻ ወግን እና እንጀራን ስናስተያይ እንጎቻ የትልቅ እንጀራ ኩርማን ወይም ብጣቂ አይደለችም፤ እራሷን የቻለች ትንሽ እንጀራ ነች›› ብሎ ምሳሌ ሁሉ የሰጠበትን አየሁ። እርሱም ጥበበ-ቃላት ነው የሚለው፤ ይህን ከተቀበሉት አንዱ ነበራ። ‹‹ሌላው መንገድ›› የሚለውን ሁለተኛ ሥራውን በ1952 ዓ.ም. ሲያሳትምም እንደዛው ነው ያደረገው። መቅድሙ ላይ አለ። እና እኔ ይሄንን ጭንቅላቴ ውስጥ ይዤ ብዙ አሰላስዬዋለሁ።

አሁንም የማምነው ማንኛውንም ዓይነት ጽሑፍ (የፈጠራ፣ የምናብ ሥራ ያልሆኑትን) የ‹‹ሥነ-ጽሑፍ›› አካል ልንል እንችላለን፤  ሥነ-ጽሑፍ የኢ-ልቦለድና የልቦለድ ሥራዎችንም ያካትታል። ነገር ግን፣ የምናብና የፈጠራ ሥራዎችን ነጥለን ደግሞ ‹‹ጥበበ-ቃላት›› ብለን ብንጠቀም የተሻለ ገላጭ ይመስለኛል። (በሁለቱ ቃላት መካከል በማትማቲክስ እንደሚባለው የ‹‹ሴት›› እና የ‹‹ሰብ-ሴት›› ትውር /ቲዎሪ/ ዓይነት ልዩነት አለ)። ለምንድን ነው ትክክል (ኤግዛክት) ለመሆን የማንወደው!?

ታዛ፡- በአሁኑ ጊዜ ልበ ሙሉ ሆኖ በሒስ ተግባር ላይ በቋሚነት ሲሰራ የተመለከቱትና ተስፋ የሚያደርጉበት ጎልማሳ ወይም ወጣት ባለሟል አለ? ካለስ ማን ነው!?

አስፋው ዳምጤ፡- እኔ አሉ ባይ ነኝ። ምርጫቸውና አካሄዳቸው ወደፊት እየጎለበተ ሲሄድ እናያለን። ለምሳሌ ዓለማየሁ ገላጋይ፣ ደረጀ በላይነህ እና ሌሎችም ጎበዝ የሆኑ ልጆች አሉ። አብደላ ዕዝራ ለአማርኛ ጥበበ-ቃላት በተከታታይ እና በብስለት ብዙ አስተዋጽኦ አድርጎ አልፏል። እንደ እርሱ በጣም ከልቡ የሥነ-ጽሑፍ ሂስ የጣረና የሞከረ ሰው የነበረ አይመስለኝም። ትልቅ ‹‹ክሬዲት›› ሊሰጠው ይገባል። ነገሮችን በብስለትና በጥልቀት ይመለከታልና አስተዋጽኦው የጎላ ነው።

ታዛ፡- ቀደም ሲል የእንግሊዛዊቷን ስመ-ጥር ደራሲ የጆን ኦስቴንን ‹‹ፕራይድ ኤንድ ፕሪጁዲስ›› መጽሐፍ እየተረጎሙ ነበር። ለመሆኑ ከምን ደረሰ? መጽሐፉን ለመተርጎም እንዴት ሊመርጡት ቻሉ?

አስፋው ዳምጤ፡- ደራሲዋ ወንዶች ደፍረው በማያሳትሙበት ጊዜ ደፍራ ያሳተመች፣ ገና ሃያ ዓመት ሳይሞላት ጀምራ የምትጽፍ ነበረች። በዚያን ጊዜዋ እንግሊዝ አንዲት ልጅ እድሜዋ ለአቅመ ሄዋን ሲደርስ አደባባይ ወጣ የማለት ሁኔታ አለ። ለምሳሌ ሁለተኛ ልጅ ከሆነችና ታላቋ ካገባች ቀጣይዋ እርሷ ናት የምትጠበቀው። የቤቱ ወይዘሪት ናት ማለት ነው። እንግዲህ ባል ሳታገባ ከቀረች በእኛ ሀገር የልጆች አስጠኚ እንደሚባለው፣ በእንግሊዝ ውስጥ ግን መልክ በያዘ መንገድ (ገቨርነንስ) ወይም የትምህርትና የእውቀት ሞግዚት ነው የምትሆነው። እንደ ምሳሌ ፈረንሳይኛ የምታውቅ ከሆነ ፈረንሳይኛ፣ ወይ ጀርመንኛ ወይ ጣሊያንኛ ልጆቻቸውን ታስጠናለች። እናም ጆን ኦስቴን ይሄን በዘመኗ የተመለከተችውን የመሳፍንት የጋብቻ መንገድ ነው በመጽሐፏ የዳሰሰችው።

እኔ መጽሐፉን ለመተርጎም ስነሳ መጀመሪያ የመጽሐፉን ባህሪ አየሁ። እርሷ የቪክቶሪያን እንግልጣን (እንግሊዝ) ገጠር ቀመስ ደህና ኑሮ የሚኖሩ ቤተሰቦችን ህይወት ነው በድርሰቷ የዳሰሰችው። የእርሷ ወላጆች እኩዮች የሆኑትንና በዚያ ዙሪያ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ህይወት ማለት ነው። ጆን ኦስቴን ካሏት ስድስት መጻሕፍት ውስጥ ሁሉም ዞሮ-ዞሮ በተለያየ አተያይ የፍቅርና የጋብቻ ነገር ነው የሚያነሱት። እዚህ ላይ የመደብ ጥያቄ የመሳሰሉት ሁሉ የሚንጸባረቁበት ነው። በዛ ገጠር ቀመስ ኅብረተሰብ ውስጥ ያሉትን ልማዶች፣ የባህል መገለጫዎች ጭምር ለማንጸባረቅ ነው የምትሞክረው።

ስለዚህ፣ የመጀመሪያው ሃሳቤ ደራሲዋ በመጽሐፏ ለማመላከት የሞከረችውን ሃሳብ ወደ አማርኛ ቋንቋ ለማምጣት ልሞክር በሚል ነው። ለምሳሌ ራሴላስ መስፍን የኢትዮጵያ ታሪክ የሚል በዶ/ር ሳሙኤል ጆንሰን በእንግሊዝኛ በ1730 ውስጥ የታተመ ነበር። እርሱ በእውነቱ በሚያስደንቅ አኳኋን በቋንቋ ደረጃ እንኳ ከእንግሊዝኛው አቻ በሆነ አማርኛ ጥሩ ተደርጎ የተተረጎመና በአማርኛ ትርጉም ሥራ በከፍተኛ እርከን ላይ የተቀመጠ ነው። የብላቴን ጌታ ኅሩይ ሁለተኛ ልጅ ሲራክ ኅሩይ ናቸው የተረጎሙት። እሳቸው ከዚያ በኋላ ምንም አልተረጎሙም። የወቅቱን አንባቢ አይተው ተስፋ ሳይቆርጡ አልቀሩም።

ደራሲዋ በገጸባህሪዎቿ ያስተላለፈችውን መልዕክት የሀገራችን አንባቢ ቢረዳ በሚል መተርጎሙን ተያያዝኩት። ነገር ግን ወቅቱ የኮምፒውተር የጽሕፈት አገልግሎት ገና እየተስፋፋ የመጣበት ወቅት ስለነበር፣ በነገራችን ላይ፣ ያኔ የተለያዩ ሶፍትዌሮች ነበሩ። አንዱ ብቻ ገበያ ላይ ገኖ ህዝባዊ አልሆነም ነበር። ፓወር ግዕዝ ዩኒ ኮድ ሶፍትዌር ከዛ በኋላ ነው ገበያው ላይ ገኖ የወጣው። እኔ ያኔ ‹‹ዋሸራ›› የሚል ሶፍት ዌር ነበር የምጠቀመው። ነፍሱን ይማረውና ዶ/ር ዮናስ አድማሱ ከአሜሪካን አገር አንድ ወዳጁ ሶፍት ዌሩን ሲልክለት ለኔም ጫነልኝ። የሆሄያቶቹ ቅርጽ ዋሸራ ፕራይመሪ፣ ዋሸራ ሰከንደሪ፣ ኢትዮጵያ ፕራይመሪ፣ ኢትዮጵያ ሰከንደሪ፣ ውቅያኖስ፣ እንደዚህ- እንደዚህ የሚል ‹‹ኮርስቮይ›› የሚሉት አይነትና መደበኛውን ፊደል ሳየው በጣም ድንቅ ስለነበር፣ በዚሁ ሶፍት ዌር መጻፍ ጀመርኩ። እናም የመጽሐፉን ሦስት አራተኛ ክፍል ተርጉሜና በኮምፒውተር ተይቤ አጠናቀቅኩ።

ሆኖም በኋላ ላይ ፓወር ግዕዝ ዩኒኮድ ገበያውን አሸነፈና በከተማው ውስጥ በየትኛውም መሥሪያ ቤት ተቀባይነት ያገኘው እርሱ ብቻ ሲሆን ጊዜ፣ ያ የጻፍኩት ሁሉ ወደ ፓወር ግዕዝ ‹‹ኮንቨርት›› የማይደረግ ሆነ። እናም እንደገና በፓወር ግዕዝ ሀ ብዬ መፃፍ ጀምሬ፣ ነሐሴ 2006 ዓ.ም አጠናቅቄ በትንንሽ ፈደሎች የጻፍኩበት ኮምፒውተሬ ላይ አለ። ነገር ግን፣ የትርጉሙን ጉድለት ለማስተዋል የጻፍኩትን ልርሳውና እንደገና ላንብበው ብዬ ዘንድሮ ማንበብ ጀምሬያለሁ። ጎን ለጎንም የደራሲዋን “ብርቱ አንባቢ ሲፈጠር ብርቱ ሐያሲም ከዛ መሐል ነው የሚወጣው፤ የሚወለደው” ኦርጅናል ሥራ እያነበብኩ ‹‹እዚህ ላይ ለማለት የፈለገችው እንዲህ ነው እንዴ?›› እያልኩ አስተውላለሁ። በዚህ መንገድ አሁን ከመቶ ገጽ በላይ ደርሻለሁ። ይህ ሲያልቅ ወደ ህትመት ሂደት ይገባል። 

ታዛ፡- የካርል ማርክስ አድናቂ ነዎት? ብዙ ሰዎች የፂምዎ አስተዳደግ፣ ቀደም ሲልም በ ጎፈሬዎት ወደ እርሱ መማለልዎትን ያሳያል የሚሉ አንባቢያን አሉ። እውነት ነው የማርክስ ተጽዕኖ አለብዎት?

አስፋው ዳምጤ፡- (ሳቅ) እኔ የካርል ማርክስ አድናቂ ከመሆኔ በፊት ነው ፂም ማሳደግ የጀመርኩት። እንደውም እንግሊዝ አገር በ1952/53 ዓ.ም የሁለተኛ ዓመት የኢኮኖሚክስ ተማሪ ሳለሁ ነው ፂሜን መላጨት ያቆምኩት። ምክንያቱም ምላጭ ስጠቀም በአግባቡ መጠቀም አልቻልኩም መሰል ቆዳዬ መቆጣት ጀመረ። በዚህ ምክንያት ነው ፂም ማሳደግ የጀመርኩት። ሆኖም፣ ‹‹ዳስ ካፒታል››ን ሳነብ በማርክስ ሃሳብ የበለጠ ማለልኩ። አድናቂው ሆንኩ። በዩኒቨርስቲው ውስጥ ግን እኔ የሌበር ፓርቲ ክበብ እንጂ የማርክሲስት ፓርቲ ክበብ አባል አልነበርኩም። ነገር ግን፣ ካርል ማርክስ ወደ ግል ሰብዕናው ስንመጣ በዘመኑ የታተሙ መጻሕፍትን ሁሉ ማትማቲክስ ይሁን ፊዚክስ፣ ኬምስትሪ ይሁን ፍልስፍና ፣ ቋንቋ ይሁን ምን ጥርግ አድርጎ ያነባል። ይሄ ሰብዕናው ይደንቃል። ደግሞም ያማልላል።

ታዛ፡- የካርል ማርክስን የህይወት ታሪክ በመጽሐፍ መልክ አዘጋጅተው ለአንባቢያን ለማቅረብ ቃል ገብተው ነበር፤ ከምን ደረሰ!?

አስፋው ዳምጤ፡- ስለማርክስ ሳስብ በምሥራቅም (በሶቭዬት ሕብረት አጋፋሪነት) የታተሙትን፣ በምዕራብ አውሮፓም የሚያጣጥሉትን ደራሲያን፣ ‹‹ባዮግራፈርስ››፣ ምሁራን መጻሕፍትን፣ መረጃዎችን (ወደ ሃያ ይጠጋሉ) አሰባስቤ፣ ልጽፍ በምነሳበት ጊዜ፣ በወቅቱ መጻሕፍቱን ያዋስኳቸው ሰዎች ሳይመልሱልኝ ቀሩ። ያኔ በደርግ ጊዜ እንዲህ ዓይነት መጻሕፍት ወረት ነበሩ። ያዋስኳቸው ሰዎች አንዱ ሲያልፍ፣ ሌላው ሲሰደድ በቃ ተበታትነው ቀሩ። ብቻ በደርግ ጊዜ የካቲት መጽሔት ላይ ማርክስን ‹‹በዓለም የኖረ ታላቅ ነብስ›› በሚል ለመጽሐፍ ዝግጅቱ እንደ መነሻ የሚሆን ጽፌያለሁ። በነገራችን ላይ ያኔ አንዳንድ ሰዎች ማርክስን ማምለክ ጀምረው ነበር። ይሄ ለኔ ጸረ ማርክስ ነው። እኔ ለማመላከት የፈለግኩትም ያ ምሁር ማን ነው? የሚለውን ከልቀቱ፣ ከጥንካሬውም፣ ከብርታቱም እንደ ሰው ደግሞ ከድክመቱም፣ ከጥፋቱም፣ ከተንኮሉም- ከጭቦውም ጭምር ማሳየትና መጻፍ ነው። ወቅቱ ይሄን ለማድረግ ባለመፍቀዱ ማሳተም አልቻልኩም። ግን ‹‹ማርክስ ሰውዬው›› በሚል ርዕስ አውት ላይኑ እና ማስታወሻዎቹ አሉ።

ታዛ፡- ቀደም ሲል ‹‹የካቲት›› መጽሔት ላይ የርስዎ የአጻጻፍ ለዛ ያላቸው ሥራዎች ‹‹አዳም ናደው›› በሚል የብዕር ስም ይወጡ ነበር። ካልተሳሳትኩ አዳም ናደው- አስፋው ዳምጤ ነው!?

አስፋው ዳምጤ፡- (ሳቅ) ምን እንደው ገሃድ የወጣ የብዕር ሥም ነው። እኔን በቅርበት የሚያውቁኝ ሥሜ አስፋው ነው- አ፣ የአባቴ ስም ዳምጤ ነው- ዳም፣ ናደው ደግሞ የአያቴ ሥም ነው። ስለዚህ ለመታወቅ የተጋለጠ ነው ማለት ነው፤ እንግዲህ ይፋ ይውጣ።

ታዛ፡- ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት በአርታዒነት ሰርተዋል፤ ያን ጊዜ አንድ መጽሐፍ ለህትመት ለመብቃት ምን ዓይነት የህትመት ሂደት ማለፍ ነበረበት? ዛሬስ መጽሐፍ ማሳተም የፈለገ በግሉ የፈለገውን ማሳተም ይችላል? እስቲ ሁለቱን ኹነቶች በማወዳደር ለአንባቢው የትኛው የህትመት ሂደት ለበሳል መጻሕፍት መበርከት አስተዋጽኦ ያደርጋል ብለው ያስባሉ?

አስፋው ዳምጤ፡- ይሄ ጥያቄ አሳታሚው ራሱ ደራሲው /ጸሐፊው የመሆንን ሁኔታ እንድናገናዝብ ነው የሚያደርገን። በመጀመሪያ ደረጃ ኩራዝ የሚያሳትመው መጽሐፉን የጻፈው ሰውዬ ለኩራዝ አሳታሚ ድርጅት የሚከፍለው ቤሳ-ቤስቲን የለም። ደራሲው ጽሑፉን ያቀርባል፣ ኩራዝ የአርታዒያን ክፍል አለው፣ ሥራው ወደ እነርሱ ይመራል። እነርሱ በብስለት ይገመግማሉ። አስተያየታቸውን ለደራሲው-፣ ይሄ እንዲህ ቢሆን ይሄ እንዲህ ቢሆን የሚል ሙያዊ አስተያየት ሰጥተውና ተከራክረው ደራሲውን ያሳምኑታል። በዛ መሠረት በተስማማበት ላይ አብዛኛውን ጊዜ በአርታዒው የሚሰጠው ገንቢ የሆነ ሃሳብ ወይም አስተያየት ስለሆነ አብዛኛው ደራሲ ይቀበላል።

ሁለተኛ እንዲህ ዓይነት ጣጣ መኖሩን የማያውቁ ደራሲያን ደግሞ ብዙ ናቸው። ለምሳሌ ደራሲ ብርሃኑ ዘሪሁን ‹‹ማዕበል፣ የአብዮት ዋዜማ››ን አሳትሞ በዛን ጊዜ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ባህል ማዕከል ሲያነጋግረው፣ ‹‹ይሄ ስለ ቴክኒክ ምን የሚባል ነገር እኔ የማውቀው የለም። እኔ አንድ ማለት የምፈልገው ነገር አለ። በዚያ መሠረት ነው የምጽፈው እንጂ፣ የአጻጻፍ ቴክኒክ ምንትሴ የሚባለውን ነገር አላውቅም ነበረ፤ ይህ አያስጨንቀኝም›› ብሎ ተናግሯል። ስለዚህ የአርታዒውን ሃሳብ የማይቀበሉ ደራሲያንም አሉ። ያን ጊዜ ይነጋገራሉ። ለምሳሌ አዳም ረታ ‹‹ማኅሌት›› የተባለ ድርሰቱን ሊያሳትም ሲል አርታዒዎቹ የሆኑ ነገሮች ውስጥ ይሄ እንዲህ እንዲህ ጉድለት አለበት ብለው፣ እኔ የአሳታሚው ክፍል የበላይ ተቆጣጣሪ ተብዬ እንደ ምክትል ተመድቤ ስለነበረ፣ ታዲያ ምንድን ነው ‹‹ኮምፕሌን›› የምታደርገው? ይሄ ያሉት ሁሉ አለ፤ ይሄ አለ- የለም! ድክመቱ እዛ ውስጥ ይታያል- አይታይም! እዚህ የተባለው ዝም ብሎ የፈጠራ ነው- አይደለም፤ ያሉት ሁሉ ልክ ነው። በሚል በመነጋገር ታተመ። ሰው ሁሉ ጉድ አለ፤ ወደዱት። እና ምን ማለቴ ነው አርታዒው በተለመደው መንገድ እንዲህ እንዲህ የሚለውን ምክር ይሰጣል።

አሁን ያለውን የህትመት ሁኔታስ እንዴት ነው የሚያዩት ላልከኝ፣ አሁንማ ዝም ብሎ ነው የሚታተመው። የህትመት አማራጩ መብዛቱ ጥሩ ነው ግን ደግሞ፣ አሁን አንተ ለማሳተም የሚያስፈልግህ ገንዘብ ነው። በድሮ ጊዜ አሳታሚ ድርጅቱ ሁሉን ጣጣ ይችልልህ ነበር። ጎበዝ ደራሲ ገንዘብ ባይኖረው አሳታሚው ገንዘቡን ከፍሎ አሳትሞ ስርጭቱና ሽያጩ የአሳታሚው ጣጣ ነው የሚሆነው። አሁን ግን ማ ከማን ያንሳል ነው ነገሩ። ብዙዎች የሚታተሙት በእውቀትና ክህሎት ሳይሆን፣ በድፍረት ሆኗል። የቀድሞው የተሻለ ብዙ በሳል ስራዎችን ሰጥቶናል ብዬ አስባለሁ። መጽሐፉ የብዙ በሳል አርታዒዎች ውጤት ነውና። ደራሲው ሊያስተላልፈው የፈለገውን ነገር በክህሎት እንዲዳብር ያደርጉ ነበር። በአግባቡ የአዋላጅነት ተግባር ነበር የሚሰሩት።

አሁን አሁን በግል አቅም ያለው እንደልቡ የማሳተም ዕድል ቢኖረውም አዲስ የታተሙ መጻሕፍትን ለመግዛት ስወጣ አልቋል እባላለሁ። ምክንያቱም የሚታተሙ መጻሕፍት በህትመት ቁጥር (ኮፒ) በጣም ጥቂት ናቸው። አንዳንድ የማውቃቸውን ደራሲያን አንድ መጽሐፍ ደጋግመው ሲያሳትሙ ተመልክቼ ‹‹የህትመቱን ሁኔታ እንዴት ትችሉታላችሁ?›› ብዬ ስጠይቃቸው ‹‹እከሌ የተባለውን መጽሐፌን እኮ አምስት መቶ ኮፒ ነበር ያሳተምኩት›› ሲሉኝ በጣም እደነግጣለሁ። በአሁኑ ጊዜ የማሳተሚያ ዋጋ እጅግ ውድ ነውና።

እንደ ዛሬው ሁሉ፣ በአሥራ ዘጠኝ አርባዎቹ እና ሃምሳዎቹ ወቅት አሳታሚ አልነበረም። ግለሰቡ- ደራሲው ራሱ ነበር የሚያሳትመው። ያኔ እንኳን እንደዚህ አምስት መቶ ኮፒ አይታተምም ነበር። በትንሹ አንድ ሺህ አምስት መቶ፣ ሁለት ሺህ እና ሦስት ሺህ እያሉ ነበር የሚያሳትሙት። በኋላ ሁኔታዎች እጅግ እየተሻሻሉ ሄደው የአንድ መጽሐፍ የህትመት ኮፒ የትና- የት እጥፍ አድጎ ነበር። ዛሬ አምስት መቶ ኮፒ ህትመት አስደንጋጭ ቁጥር ነው። ያሳዝናል።

ታዛ፡- አመሰግናለሁ

 

Click to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

To Top